የተፈጥሮ አደጋ ቢደርስ ዝግጁ ናችሁ?
1. የተፈጥሮ አደጋ ከመድረሱ በፊት ቅድመ ዝግጅት ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ የሆነው ለምንድን ነው?
1 በየዓመቱ፣ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድርቅ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በሱናሚ፣ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣ በኃይለኛ ዓውሎ ነፋስና በውኃ መጥለቅለቅ ጉዳት ይደርስባቸዋል። የተፈጥሮ አደጋዎች ሳይታሰብ ሊከሰቱና የሁላችንንም ሕይወት ሊነኩ ስለሚችሉ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 21:5
2. ወቅታዊ አድራሻችንንና የስልክ ቁጥራችንን በየጊዜው ለጉባኤ ሽማግሌዎች ማሳወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ቅድመ ዝግጅት፦ አንዳንድ ጊዜ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሊከሰቱ ስለሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ማስጠንቀቂያ ይሰጡ ይሆናል። ለእነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 22:3) እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ፣ ሽማግሌዎች አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ለመርዳት ሲሉ በጉባኤያቸው ውስጥ የሚሰበሰቡትን ሁሉ ለማግኘት ይጥራሉ። የተፈጥሮ አደጋ ከደረሰም በኋላ ቢሆን ሽማግሌዎች በጉባኤያቸው ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ደህንነት ለማረጋገጥና ምን እርዳታ እንደሚያስፈልግ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች የወንድሞችና የእህቶች ወቅታዊ አድራሻ ከሌላቸው ውድ የሆነ ጊዜ ሊባክን ይችላል። ስለሆነም አስፋፊዎች ወቅታዊ አድራሻቸውንና የስልክ ቁጥራቸውን ለጉባኤው ጸሐፊ እንዲሁም ለመጽሐፍ ጥናታቸው የበላይ ተመልካች መስጠታቸው አስፈላጊ ነው።
3. ለአደጋ በተጋለጠ አካባቢ ውስጥ የምንኖር ከሆነ ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር መተባበር የምንችለው እንዴት ነው?
3 ጉባኤው የሚገኘው ለአደጋ በተጋለጠ አካባቢ ውስጥ ከሆነ አስፋፊዎች ከክልሉ ውጪ የሚኖር የአደጋ ጊዜ ተጠሪ የሚሆን ዘመዳቸውን ወይም ጓደኛቸውን ስምና ስልክ ቁጥር ለሽማግሌዎች እንዲሰጡ ይጠየቁ ይሆናል። ይህ ደግሞ ሽማግሌዎቹ ከአካባቢው ለቅቀው የወጡ አስፋፊዎች የት እንዳሉ ለማወቅ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም ሽማግሌዎቹ በድንገተኛ አደጋ ጊዜ የሚያገለግል ንድፍ ሊያወጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይህ ንድፍ ድንገተኛ አደጋ ሲከሰት ለእያንዳንዱ ግለሰብ ወዲያውኑ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች ዝርዝር፣ አካባቢውን ለቅቆ ለመውጣት መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች እንዲሁም ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸውን መርዳት የሚቻልበትን መንገድ የሚገልጽ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ካሉት ፍቅራዊ ዝግጅቶች ጋር መተባበር አስፈላጊ ነው።—ዕብ. 13:17
4. በአካባቢያችን የተፈጥሮ አደጋ ቢከሰት ምን ማድረግ ይገባናል?
4 አደጋው ከተከሰተ በኋላ፦ በአካባቢህ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ቤተሰብህ በአፋጣኝ የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ማግኘቱን ማረጋገጥ ይኖርብሃል። ከቻልክ ደግሞ በአደጋው ለተጎዱ ሌሎች ሰዎች አስፈላጊውን እርዳታ አድርግ። በተቻለህ ፍጥነት ከመጽሐፍ ጥናታችሁ የበላይ ተመልካች አሊያም ከሌላ ሽማግሌ ጋር ለመገናኘት ጥረት አድርግ። ምንም ጉዳት ባይደርስብህና እርዳታ የማያስፈልግህ ብትሆን እንኳ እንዲህ ማድረግ ይገባሃል። እርዳታ ካስፈለገህ ወንድሞች አንተን ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ እርግጠኛ ሁን። (1 ቆሮ. 13:4, 7) ይሖዋ ያለህበትን ሁኔታ እንደሚያውቅ አስታውስ፤ እንደሚደግፍህም ተማመን። (መዝ. 37:39፤ 62:8) ለሌሎች መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችልህን አጋጣሚ በንቃት ተከታተል። (2 ቆሮ. 1:3, 4) በተቻለህ ፍጥነት ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችህን ማካሄድ ጀምር።—ማቴ. 6:33
5. ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን የተፈጥሮ አደጋዎች ለሚፈጥሩት ስጋት ምን አመለካከት አለን?
5 የተፈጥሮ አደጋዎች ስጋት ዓለምን እያስጨነቀ ቢሆንም እኛ ግን የወደፊቱን ጊዜ በመተማመን መጠባበቅ እንችላለን። በቅርቡ ሁሉም አደጋዎች የሚያከትሙበት ጊዜ ይመጣል። (ራእይ 21:4) እስከዚያው ድረስ ግን የምሥራቹን በቅንዓት እየሰበክን ለመከራም ሆነ ለችግር ጊዜ ለመዘጋጀት የሚያስችሉንን ተገቢ እርምጃዎች እንወስዳለን።