ራሳችንን ለይሖዋ አገልግሎት በማቅረባችን ደስተኞች ነን!
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያናዊ አገልግሎቱን ለመፈጸም ሲል ‘ራሱን በመስጠቱ’ ደስተኛ ነበር። (2 ቆሮ. 12:15) ዛሬም በተመሳሳይ በርካታ ክርስቲያኖች አቅኚዎች ሆነው በትጋት እየሠሩ ነው። ከባድ የቤተሰብ ኃላፊነቶች ያሉባቸው ሌሎች ክርስቲያኖች ፕሮግራማቸው የተጣበበ ቢሆንም በየሳምንቱ በአገልግሎት ለመካፈል የሚያስችል ጊዜ መድበዋል። አንዳንዶች ደግሞ ከባድ የጤና ችግሮች ቢኖሩባቸውም ባላቸው ውስን አቅም መንግሥቱን ለማስቀደም ይጣጣራሉ። የይሖዋ ሕዝቦች ዕድሜም ሆነ ሌሎች ችግሮች ሳይገድቧቸው ራሳቸውን ለይሖዋ አገልግሎት ሲያቀርቡ መመልከት እንዴት የሚያበረታታ ነው!
2 ለሰዎች ያለን ፍቅር:- ይሖዋን ለማገልገል የአቅማችንን ሁሉ በማድረግ ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር እንዳለን እናሳያለን፤ ይህ ደግሞ ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረን ያስችለናል። ጳውሎስ ምሥራቹን ለማካፈል ሲል ሕይወቱን ጭምር አሳልፎ ሰጥቶ ስለነበር “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ መሆኔን በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ” ብሎ በደስታ ለመናገር ችሏል። (ሥራ 20:24, 26፤ 1 ተሰ. 2:8) ሁኔታችን የሚፈቅድልንን ያህል በአገልግሎት መካፈላችን በደም ዕዳ ተጠያቂ ከመሆን ይጠብቀናል።—ሕዝ. 3:18-21
3 ሌሎችን ለመርዳት ተግተን መሥራታችን ደስታ ያስገኝልናል። (ሥራ 20:35) አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “አገልግሎት ውዬ ምሽት ላይ ወደ ቤት ስመለስ ድካም እንደሚሰማኝ ግልጽ ነው፤ ይሁንና ደስተኛ ነኝ። ማንም ሰው ሊወስድብኝ የማይችለውን ደስታ ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።”
4 ለአምላክ ያለን ፍቅር:- ራሳችንን ለይሖዋ አገልግሎት የምናቀርብበት ዋነኛው ምክንያት በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን የሚያስደስተው መሆኑ ነው። ለአምላክ ያለን ፍቅር ትእዛዛቱን እንድንጠብቅ የሚገፋፋን ሲሆን ይህ ደግሞ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ይጨምራል። (1 ዮሐ. 5:3) ሰዎች ግድ የለሽ አሊያም ተቃዋሚ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ ለይሖዋ ተግተን መሥራታችንን በደስታ እንቀጥላለን።
5 ያለንበት ጊዜ ከአገልግሎታችን ወደኋላ የምንልበት አይደለም። የምንኖረው በመከር ወቅት ነው። (ማቴ. 9:37) አንድ ገበሬ ምርቱ መበላሸት ከመጀመሩ በፊት እህሉን ለመሰብሰብ ያለው ጊዜ ውስን ስለሆነ በመከር ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ረዘም ላለ ሰዓት ይሠራል። ለመንፈሳዊው የመከር ሥራ የተሰጠው ጊዜም ውስን ነው። ያለንበትን ጊዜ በአእምሯችን በመያዝ ሁላችንም አገልግሎታችንን በትጋት ማከናወናችንን እንቀጥል።—ሉቃስ 13:24፤ 1 ቆሮ. 7:29-31