አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም
የ2008 የአገልግሎት ዓመት የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም “እኛ ሸክላዎች፣ ይሖዋ ደግሞ ሠሪያችን ነው” የሚል ጭብጥ ያለው ሲሆን በኢሳይያስ 64:8 (NW) ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ የምናገኛቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ ላለው ጥበብ፣ ፍትሕ፣ ኃይልና ፍቅር ያለንን አድናቆት ይጨምሩልናል።
የወረዳ የበላይ ተመልካቹ “በስብከቱ ሥራ የክብር ዕቃ ሆኖ ማገልገል” በሚል ርዕስ የሚያቀርበው ንግግር ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሰዎች እውነትን በማወቃቸውና ይህንንም ለሌሎች በማካፈላቸው ምን ያህል እንደተባረኩ የሚገልጽ ነው። “ማሰላሰል ከችግር ይጠብቃችኋል” የሚለው ንግግር በይሖዋ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በቁም ነገር ማሰላሰላችን ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት እንደሆነ ያብራራል። ጎብኚ ተናጋሪው “ይህን ዓለም አትምሰሉ” እና “በታላቁ ሸክላ ሠሪ ለመቀረጽ ፈቃደኞች ሁኑ” የሚሉ ንግግሮችን ያቀርባል። “ለይሖዋ ጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች” እና “ወላጆች ልጆችን በመቅረጹ ሂደት ያላቸው ወሳኝ ሚና” በሚል ጭብጥ ከሚቀርቡት ንግግሮች ወላጆችም ሆኑ ወጣቶች ማበረታቻ ያገኛሉ። በስብሰባው ላይ በሚቀርቡልን ሠርቶ ማሳያዎችና ቃለ ምልልሶች አማካኝነት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአገልግሎታቸው ምን ውጤት እያገኙ እንዳሉ መስማት መንፈስን የሚያነቃቃ ይሆናል። ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት ለማሳየት የሚፈልጉ ሁሉ በተቻለ ፍጥነት ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ሊያሳውቁት ይገባል። በልዩ ስብሰባው ሳምንት የሚጠናውን መጠበቂያ ግንብ ይዛችሁ መምጣታችሁን አትርሱ።
ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ ዓላማዎቹ ምንም ይሁኑ ምን ከግብ ያደርሳቸዋል። ነገር ግን እሱ እኛን የሚቀርጽበትን መንገድ መቀበልም ሆነ አለመቀበል የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። በቅርጽ ማውጫ መሣሪያ ላይ እንደተቀመጠ ጭቃ ይሖዋ እነሱን ለመቅረጽና ለማሳመር ያደረገውን ዝግጅት ሁሉ በፈቃደኝነት የሚቀበሉትን ሰዎች ቀርጾና አስተካክሎ ጠቃሚ ዕቃ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። በዚህ ረገድ ከይሖዋ ጋር መተባበራችን ሉዓላዊነቱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ለእኛም ብዙ በረከት ያስገኝልናል።