የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ የመንግሥቱ ምሥራች አስፋፊዎች እንዲሆኑ እርዷቸው
1 በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ተልዕኮ በእርግጥም በጣም ሰፊ ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች፣ ደቀ መዛሙርት እንዲያፈሩ ታዘው የነበረ ሲሆን እነዚህም በተራቸው ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንዲካፈሉ ይጠበቅባቸው ነበር። በዚያ ወቅት፣ ከፍ ያለ ግምት በሚሰጠው በዚህ የፍጻሜ ዘመን ውስጥ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጨረሻ ጊዜ ለማወጅ የሚያስችል መሠረት ተጥሏል።—ማቴ. 24:14
2 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምንላቸው ልጆቻችንን አሊያም መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናቸውን ሌሎች ሰዎች ሊሆን ይችላል። እነዚህ ጥናቶቻችን፣ እነሱም በበኩላቸው ሌሎች ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ የመርዳት ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን እንዲገነዘቡና ይህን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከልብ ልንረዳቸው እንፈልጋለን።—ሉቃስ 6:40
3 ምሥክርነት መስጠት እንዲችሉ አዘጋጇቸው:- ጥናቶቻችሁ የሚማሩትን ነገር ለሌሎች እንዲያካፍሉ አበረታቷቸው። የሚያበረታቱ የመስክ አገልግሎት ተሞክሮዎችን ንገሯቸው። ልጆቻችሁን ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምረው እንደ አቅማቸው ትርጉም ባለው መንገድ በአገልግሎት መካፈል እንዲችሉ አሠልጥኗቸው። (መዝ. 148:12, 13) በሕይወታችሁ ውስጥ ለአገልግሎት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጡ በአንደበታችሁም ሆነ በተግባራችሁ አሳዩአቸው።—1 ጢሞ. 1:12
4 ይሖዋ፣ እንዲያገለግሉት የሚፈልገው የጽድቅ መሥፈርቶቹን የሚቀበሉና ከእነዚህም ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሰዎችን ብቻ ነው። አዳዲስ አስፋፊዎች፣ ልምድ ካላቸውና ራሳቸውን ወስነው ከተጠመቁ የመንግሥቱ አገልጋዮች እኩል እውቀት እንደማይኖራቸው የተረጋገጠ ነው። ሆኖም እነዚህ አዲስ አስፋፊዎች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች ማመንና ያመኑበትን ለሌሎች ማስረዳት መቻል ይገባቸዋል። (የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 79-82 ተመልከቱ።) ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ መውጣት ብሎም ከማንኛውም የፖለቲካ ጉዳይ ገለልተኛ መሆን የሚገባቸው ከመሆኑም ባሻገር አዘውትረው በጉባኤ ስብሰባዎች መገኘት ይኖርባቸዋል።—ራእይ 18:2, 4፤ ዮሐ. 17:16፤ ዕብ. 10:24, 25
5 ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችህ መካከል አንዱ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን የሚያስችለውን ብቃት እንዳሟላ ሲሰማህ ሁኔታውን በተቻለ ፍጥነት ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ መንገር ያስፈልግሃል። ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ያልተጠመቀ የመንግሥቱ ምሥራች አስፋፊ ሆኖ ከጉባኤው ጋር ማገልገል ይችል እንደሆነ ለማረጋገጥ ሁለት ሽማግሌዎች አንተ በተገኘህበት እንዲያነጋግሩት አስፈላጊውን ዝግጅት ያደርጋል። ከዚያም በኋላ ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ አብሮህ ወደ መስክ አገልግሎት ሲወጣ ቀጣይነት ያለው ሥልጠና የመስጠት ልዩ ኃላፊነት አለብህ።