ውጤታማ የሆነ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ቁልፉ ዝግጅት ነው
1. በአንደኛው መቶ ዘመን የተጀመረው የስብከት ሥራ የተስፋፋው እንዴት ነው?
1 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ውጤታማ በሆነ መንገድ መስበክ እንዲችሉ በሚገባ አሰልጥኗቸዋል። (ማቴ. 4:23፤ 9:35) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስልጠናውን በሰጠበት ወቅት ስብከታቸው ያተኮረው በፓለስቲና ምድር ላይ ብቻ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት፣ ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ ብሎ ሲናገር የስብከቱ ሥራ እንደሚስፋፋ ማመልከቱ ነበር።—ማቴ. 28:19, 20
2. ኢየሱስ ‘ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ማክበር ምን ነገሮችን ይጨምራል?
2 ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ፣ ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ፍላጎት ያሳዩ ግለሰቦችን ተመልሶ መጠየቅን እንዲሁም ክርስቶስ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቁ ማስተማርን የሚያካትት ነው። ውጤታማ የሆነ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ በደንብ መዘጋጀት ይኖርብናል።
3. በመጀመሪያ ቀን ላይ እንኳ ለተመላልሶ መጠየቅ መሠረት መጣል የምትችለው እንዴት ነው?
3 አስቀድመህ እቅድ አውጣ:- አንዳንድ አስፋፊዎች የመጀመሪያ ቀን ውይይታቸውን ከመደምደማቸው በፊት የቤቱን ባለቤት ጥያቄ ከጠየቁ በኋላ በሌላ ጊዜ መጥተው መልስ እንደሚሰጡት ቃል ይገባሉ። አስፋፊዎቹ በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ሐሳቦች ጠቅሰው መናገራቸው ወዲያው ጥናት ለማስጀመር ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።
4. ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ አዳዲስ መጽሔቶች እስኪደርሱን ድረስ መጠበቅ የማይገባን ለምንድን ነው?
4 የሚበረከቱት የንቁ እና የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት እትሞች የሚወጡት በወር አንዴ ብቻ መሆኑ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ቀጣዮቹን እትሞች የምናበረክትበት ወር እስኪደርስ ድረስ እንጠ ብቃለን ማለት አይደለም። ቀደም ሲል ባበረከትንለት መጽሔት ውስጥ ያሉትን ሐሳቦች በማወያየት የግለሰቡን ፍላጎት ማሳደግ ይቻል ይሆናል።
5. ተመላልሶ መጠየቅ ከማድረግህ በፊት ግብ ማውጣትህ ምን ጥቅም አለው?
5 ግብ ይኑርህ:- ተመላልሶ መጠየቅ ከማድረግህ በፊት ጥቂት ጊዜ ወስደህ የያዝከውን ማስታወሻ ከልስ እንዲሁም በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ማከናወን የምትፈልገውን ነገር አስቀድመህ ወስን። ለምሳሌ ያህል፣ ካበረከትክለት ጽሑፍ ውስጥ አንድ ነጥብ አንስተህ ለማወያየት አሊያም ከዚህ በፊት ያደረግከውን ውይይት የሚያብራራ ሌላ ጽሑፍ ለመስጠት ትወስን ይሆናል። ቀደም ሲል አንድ ጥያቄ አንስተህ ከነበረ በቀጣዩ ውይይት ላይ ለጥያቄው መልስ መስጠት ከግቦችህ አንዱ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። እየተወያያችሁት ያለውን ነጥብ የሚደግፍ ጥቅስ መጠቀም በምትፈልግበት ወቅት በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ጥረት አድርግ።
6. ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግበት ዓላማ ምንድን ነው?
6 ዓላማችን:- እርግጥ ነው፣ ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግበት ዓላማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ነው። አንድ ወንድም ተመላልሶ መጠየቅ ለሚያደርግለት ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ግብዣ አቀረበለት፤ ሆኖም ግለሰቡ ለማጥናት ፈቃደኛ አልነበረም። ወንድም በሌላ ጊዜ አዲስ የወጡ መጽሔቶችን ከሰጠው በኋላ “ሰዎች ለሚያነሱት አንድ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ ባሳይህ ደስ ይለኛል” አለው። ወንድም፣ ሌሎች የሚያነሱትን ጥያቄ ግለሰቡን ከጠየቀው በኋላ የሰጠውን ምላሽ አዳመጠ። ከዚያም ለተነሳው ጥያቄ ድጋፍ የሚሆን ጥቅስ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ከምንጠቀምበት ጽሑፍ ላይ ተስማሚ የሆነ አንድ አንቀጽ አነበበለት። በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ።
7. ጥሩ ዝግጅት ማድረግህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የረዳህ እንዴት ነው?
7 ተመላልሶ መጠየቅ ከማድረጋችን በፊት ጊዜ መድበን ለመዘጋጀት ጥረት ማድረጋችን የሚያስቆጭ አይሆንም። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ደስታችን ይጨምራል እንዲሁም “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ” ሰዎች ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዙ የመርዳት መብት እናገኛለን።—ሥራ 13:48