በምሽት አገልግሎት መካፈል ትችላላችሁ?
1. አንድ ምሁር እንደተናገሩት ሐዋርያው ጳውሎስ ከቤት ወደ ቤት የሚሰብከው መቼ ነበር?
1 ዴይሊ ላይፍ ኢን ባይብል ታይምስ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከ10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ድረስ” ከቤት ወደ ቤት እየሄደ የመስበክ ልማድ ነበረው። ጳውሎስ ይህን ፕሮግራም ይከተል እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም ‘ለምሥራቹ ሲል ሁሉን ነገር ለማድረግ’ ፈቃደኛ እንደነበር እናውቃለን። (1 ቆሮ. 9:19-23) ይህ ደግሞ በጣም ውጤታማ በሆነ ወቅት ከቤት ወደ ቤት ለመሄድ ሁኔታዎቹን ማስተካከል ጠይቆበት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።
2. የምሽቱ ጊዜ ለማገልገል ጥሩ ወቅት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
2 በብዙ ቦታዎች፣ አስፋፊዎች በሳምንቱ ውስጥ ጠዋት ላይ ከቤት ወደ ቤት የመሄድ ልማድ አላቸው። ሆኖም በእናንተ አካባቢ አሁንም ቢሆን ከቤት ወደ ቤት ለመሄድ የተሻለው ወቅት የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ነው? አንድ አቅኚ ስለሚያገለግልበት ክልል ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ቀን ላይ ቤቱ የሚገኝ ሰው የለም ማለት ይቻላል። ሆኖም ብዙ ሰዎች ምሽት ላይ ቤታቸው ይገኛሉ።” የምሽት ምሥክርነት በተለይ ለወንዶች ለመስበክ የተሻለ አጋጣሚ ይፈጥራል። በአብዛኛው የቤቱ ባለቤቶች በዚህ ጊዜ ዘና የሚሉ ከመሆኑም በላይ ለመወያየት ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። አስፈላጊ ከሆነ ሽማግሌዎች ምሽት ላይ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ እንዲኖር ማድረግ ይችላሉ።
3. በምሽት ምሥክርነት ስንካፈል አስተዋዮች መሆናችንን የምናሳየው እንዴት ነው?
3 አስተዋይ ሁኑ፦ በምሽት አገልግሎት ላይ ስትካፈሉ አስተዋይ መሆን ይኖርባችኋል። ለምሳሌ ያህል፣ ወደ አንድ ሰው ቤት ስትሄዱ ሁኔታው የማይመች ከሆነ ሌላ ጊዜ እንደምትመለሱ ተናግራችሁ ብትሄዱ የተሻለ ነው። በሩን ስታንኳኩ የቤቱ ባለቤቱ ሊያያችሁ በሚችል ቦታ መቆም ይኖርባችኋል፤ እንዲሁም ማንነታችሁንና የመጣችሁበትን ምክንያት ወዲያውኑ ተናገሩ። በተጨማሪም በቡድን ሆኖ ማገልገል የጥበብ አካሄድ ነው፤ የምታገለግሉት አላፊ አግዳሚ ያለበት አካባቢ ቢሆን ይመረጣል። (ምሳሌ 22:3) ከጨለመ በኋላ ከቤት ወደ ቤት ከማገልገል ይልቅ የቤቱ ባለቤት በሚገኝበት በሌላ ሰዓት ምናልባትም አመሻሹ ላይ ማገልገል የተሻለ ነው።—2 ቆሮ. 6:3
4. በምሽት አገልግሎት ላይ መካፈል ምን በረከት ያስገኛል?
4 በረከት፦ አገልግሎታችን አስደሳች የሚሆንልን ሰዎችን አግኝተን ስናነጋግር ነው። ብዙ ሰዎችን ለማግኘት ጥረት ባደረግን መጠን “ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” የመርዳት ሰፊ አጋጣሚ እናገኛለን። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ታዲያ በምሽት አገልግሎት ላይ ለመካፈል ፕሮግራማችሁን ማስተካከል ትችሉ ይሆን?