የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w20 የካቲት ገጽ 8-13
  • አባታችንን ይሖዋን በጣም እንወደዋለን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አባታችንን ይሖዋን በጣም እንወደዋለን
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ጠብቃችሁ ኑሩ
  • ታዛዦች በመሆን ፍቅራችሁን አሳዩ
  • ሌሎች አባታችንን እንዲወዱት እርዷቸው
  • አባታችንን በመውደድ ደስተኞች ሁኑ
  • አባታችን ይሖዋ በጣም ይወደናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • ከመንፈሳዊ ቤተሰብህ ጋር ተቀራረብ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት አጠናክር
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • የአምላክ ፍቅር ለዘላለም ይኖራል
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
w20 የካቲት ገጽ 8-13

የጥናት ርዕስ 7

አባታችንን ይሖዋን በጣም እንወደዋለን

“እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን።”—1 ዮሐ. 4:19

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

ማስተዋወቂያa

1-2. ይሖዋ የቤተሰቡ አባል እንድንሆን መንገድ የከፈተልን ለምንድን ነው? ይህን ያደረገውስ እንዴት ነው?

ይሖዋ የእሱን አገልጋዮች ያቀፈው ቤተሰብ አባል እንድንሆን ጋብዞናል። ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ግብዣ ነው! የዚህ ቤተሰብ አባላት፣ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ናቸው። ቤተሰባችን ደስተኛ ነው። በዛሬው ጊዜ ትርጉም ያለው ሕይወት የምንመራ ከመሆኑም ሌላ ወደፊት በሰማይ ወይም ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስላለን ደስተኞች ነን።

2 ይሖዋ ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ቢጠይቅበትም በፍቅር ተነሳስቶ የቤተሰቡ አባል መሆን የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። (ዮሐ. 3:16) በእርግጥም ‘በዋጋ ተገዝተናል።’ (1 ቆሮ. 6:20) ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት የምንችልበት አጋጣሚ ሰጥቶናል። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀውን አካል፣ አባታችን ብለን የመጥራት መብት አግኝተናል። ደግሞም ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው እንደ ይሖዋ ያለ አባት የለም።

3. ምን ዓይነት ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል? (“ይሖዋ እኔን ትኩረት ሰጥቶ ይመለከተኛል?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

3 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዳለው “ላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለይሖዋ ምን እመልስለታለሁ?” ብለን እንጠይቅ ይሆናል። (መዝ. 116:12) እንደ እውነቱ ከሆነ መቼም ቢሆን የሰማያዊ አባታችንን ውለታ መክፈል አንችልም። ያም ቢሆን እሱ ያደረገልን ነገር በምላሹ እንድንወደው ያነሳሳናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐ. 4:19) ታዲያ ሰማያዊ አባታችንን እንደምንወደው ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ይሖዋ እኔን ትኩረት ሰጥቶ ይመለከተኛል?

አንዲት ሴት ብዙ ሰዎች በሚተላለፉበት ጎዳና ላይ ቆማለች። ወደ ላይ ቀና ብላ እያየች ነው፤ ‘አምላክ እኔን ትኩረት ሰጥቶ ይመለከተኛል?’ ብላ የምትጠይቅ ትመስላለች።

‘በምድር ላይ ካሉት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ይሖዋ እኔን ትኩረት ሰጥቶ የሚመለከትበት ምን ምክንያት አለ?’ ብለህ ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህ? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ታስተውለው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ቦታ ትሰጠውስ ዘንድ ሟች የሆነው የሰው ልጅ ምንድን ነው?” (መዝ. 144:3) ዳዊት፣ ይሖዋ በደንብ እንደሚያውቀው እርግጠኛ ነበር። (1 ዜና 17:16-18) ዛሬም ይሖዋ ለእሱ ያለህን ፍቅር እንደሚያስተውል በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ያረጋግጥልሃል። በዚህ እንድትተማመን የሚያደርጉ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሐሳቦችን እስቲ እንመልከት፦

  • ይሖዋ ከመወለድህ በፊት እንኳ አውቆሃል።​—መዝ. 139:16

  • ይሖዋ ስሜትህንና ሐሳብህን ያውቃል።​—1 ዜና 28:9

  • ይሖዋ የምታቀርበውን ጸሎት በሙሉ እሱ ራሱ ያዳምጣል።​—መዝ. 65:2

  • የምታደርገው ነገር ይሖዋን ሊያስደስተው ወይም ሊያሳዝነው ይችላል።​—ምሳሌ 27:11

  • ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ወደ ራሱ ስቦሃል።​—ዮሐ. 6:44

  • ይሖዋ በደንብ ስለሚያውቅህ ከሞት ሊያስነሳህ ይችላል። የቀድሞህን የሚመስል አካል ይሰጥሃል፤ እንዲሁም ከሞት የምትነሳው ትዝታዎችህንና የማንነትህ መለያ የሆኑ ባሕርያትህን ጨምሮ በአእምሮህ ያከማቸኸውን መረጃ በሙሉ ይዘህ ነው።​—ዮሐ. 11:21-26, 39-44፤ ሥራ 24:15

ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ጠብቃችሁ ኑሩ

ምስሎች፦ 1. አንዲት እህት እየጸለየች፤ የተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ ከአጠገቧ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጧል። 2. አንድ ወጣት ወንድም አብሮት የሚማር ልጅ ሲጋራ እንዲያጨስ ያቀረበለትን ግብዣ ውድቅ ሲያደርግ። 3. አንድ ወንድም መኪና ውስጥ ምግብ ለሚያበስል ሰው ትራክት ሲያሳይ።

የሰማዩን አባታችንን ይሖዋን አዘውትረን በጸሎት በማነጋገር፣ እሱን በመታዘዝ እንዲሁም ሌሎች እንዲወዱት በመርዳት እሱን በጣም እንደምንወደው እናሳያለን (ከአንቀጽ 4-14⁠ን ተመልከት)

4. ያዕቆብ 4:8 እንደሚያሳየው ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ ወደ እሱ እንድንቀርብና እንድናነጋግረው ይፈልጋል። (ያዕቆብ 4:8⁠ን አንብብ።) “ሳትታክቱ ጸልዩ” በማለት ያበረታታን ከመሆኑም ሌላ በማንኛውም ጊዜ እኛን ለመስማት ፈቃደኛ ነው። (ሮም 12:12) እኛን ለመስማት የሚሆን ጊዜ አያጣም፤ እንዲሁም ጸሎታችንን ለመስማት አይታክትም። እኛ ደግሞ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም ቃሉን ለመረዳት የሚያስችሉንን ጽሑፎች በማንበብ ይሖዋን ማዳመጥ እንችላለን። በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ በትኩረት በመከታተል እሱን ማዳመጥ እንችላለን። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር አዘውትረው የሚነጋገሩ ከሆነ በመካከላቸው ያለው ዝምድና እንደሚጠናከር ሁሉ እኛም ከይሖዋ ጋር አዘውትረን መነጋገራችን ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት ጠብቀን ለመኖር ይረዳናል።

አንዲት እህት እየጸለየች፤ ጠረጴዛ ላይ የተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ አለ።

አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት

5. የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?

5 እስቲ ለአምላክ የምታቀርበውን ጸሎት ይዘት ለመገምገም ሞክር። ይሖዋ ወደ እሱ ስንጸልይ ልባችንን እንድናፈስስ ይፈልጋል። (መዝ. 62:8) እንግዲያው ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ጸሎት ሳቀርብ የሌላ ሰውን ሐሳብ የምደግም እመስላለሁ? ወይስ ጸሎቴ በእጄ እንደጻፍኩት ደብዳቤ ከልብ የመነጨ ነው?’ ይሖዋን በጣም እንደምትወደውና ከእሱ ጋር ያለህ ወዳጅነት ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። ይህ እንዲሆን ግን አዘውትረህ ልታነጋግረው ይገባል። ይሖዋን ሚስጥረኛህ አድርገው። የሚያስደስትህንና የሚያሳዝንህን ነገር ንገረው። እርዳታ በሚያስፈልግህ ጊዜ ምንም ሳትሳቀቅ ለምነው።

6. ምንጊዜም ከሰማዩ አባታችን ጋር ተቀራርበን ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

6 ከሰማዩ አባታችን ጋር ምንጊዜም ተቀራርበን ለመኖር የአመስጋኝነት መንፈስ ማዳበር ያስፈልገናል። እኛም እንደሚከተለው ብሎ እንደጻፈው መዝሙራዊ ይሰማናል፦ “ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ ያደረግካቸው ድንቅ ሥራዎች፣ ለእኛ ያሰብካቸው ነገሮችም ብዙ ናቸው። ከአንተ ጋር ሊወዳደር የሚችል ማንም የለም፤ ስለ እነዚህ ነገሮች ላውራ፣ ልናገር ብል፣ ዘርዝሬ ልጨርሳቸው አልችልም!” (መዝ. 40:5) ለይሖዋ ያለን አመስጋኝነት ከስሜት ባለፈ በንግግራችንና በተግባራችን ሊገለጽ ይገባል። ይህን ማድረጋችን በዛሬው ጊዜ ካሉ ብዙ ሰዎች የተለየን እንድንሆን ያደርገናል። በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች አምላክ ላደረገላቸው በርካታ ነገሮች ምንም አድናቆት የላቸውም። እንዲያውም “በመጨረሻዎቹ ቀናት” እንደምንኖር ከሚጠቁሙት ነገሮች አንዱ ሰዎች የማያመሰግኑ መሆናቸው ነው። (2 ጢሞ. 3:1, 2) እንዲህ ያለ ዝንባሌ ፈጽሞ እንዳይጋባብን እንጠንቀቅ!

7. ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል? ለምንስ?

7 ወላጆች ልጆቻቸው እርስ በርስ ተስማምተው እንዲኖሩ እንጂ እንዲጣሉ አይፈልጉም። በተመሳሳይም ይሖዋ ሁሉም ልጆቹ ተስማምተው እንዲኖሩ ይፈልጋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን ለይቶ የሚያሳውቀውም አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅር ነው። (ዮሐ. 13:35) “እነሆ፣ ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” ብሎ እንደጻፈው መዝሙራዊ ይሰማናል። (መዝ. 133:1) ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የምንወድ ከሆነ ይሖዋን እንደምንወድ እናሳያለን። (1 ዮሐ. 4:20) ‘አንዳቸው ለሌላው ደግ የሆኑና ከአንጀት የሚራሩ’ ወንድማማቾችና እህትማማቾች ያሉበት ቤተሰብ አባል መሆን ምንኛ አስደሳች ነው!—ኤፌ. 4:32

ታዛዦች በመሆን ፍቅራችሁን አሳዩ

አንድ ወጣት ወንድም አብሮት የሚማር ልጅ ሲጋራ እንዲያጨስ ያቀረበለትን ግብዣ ውድቅ ሲያደርግ።

አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት

8. በ1 ዮሐንስ 5:3 መሠረት ይሖዋን የምንታዘዝበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

8 ይሖዋ፣ ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ እንደሚጠብቅባቸው ሁሉ እኛም እሱን እንድንታዘዘው ይጠብቅብናል። (ኤፌ. 6:1) ይሖዋ ስለፈጠረን፣ ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ስለሚያሟላልን እንዲሁም ከየትኛውም ወላጅ የበለጠ ጥበበኛ ስለሆነ ልንታዘዘው ይገባል። ይሁን እንጂ ይሖዋን እንድንታዘዝ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ለእሱ ያለን ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 5:3⁠ን አንብብ።) ይሖዋን እንድንታዘዝ የሚያነሳሱ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም እሱ ይህን እንድናደርግ አያስገድደንም። ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ በመሆኑም ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን ስንታዘዘው ይደሰታል።

9-10. አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ማወቃችንና በእነሱ መሠረት ሕይወታችንን መምራታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 ወላጆች ልጆቻቸውን ከአደጋ መጠበቅ ይፈልጋሉ። ልጆቻቸውን የሚጠቅሙ ደንቦች የሚያወጡት ለዚህ ነው። ልጆች እነዚህን ደንቦች ሲታዘዙ፣ በወላጆቻቸው እንደሚተማመኑና ለእነሱ አክብሮት እንዳላቸው ያሳያሉ። ከዚህ አንጻር፣ እኛም የሰማዩ አባታችን ያወጣቸውን መሥፈርቶች ማወቃችንና በእነሱ መሠረት ሕይወታችንን መምራታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ይህን ስናደርግ ይሖዋን እንደምንወደውና እንደምናከብረው የምናሳይ ከመሆኑም ሌላ ራሳችንንም እንጠቅማለን። (ኢሳ. 48:17, 18) ከዚህ በተቃራኒ ግን ይሖዋንና መሥፈርቶቹን የማይቀበሉ ሰዎች ጉዳት ላይ ይወድቃሉ።—ገላ. 6:7, 8

10 ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ ስንኖር ከአካላዊ፣ ከስሜታዊና ከመንፈሳዊ ጉዳት እንጠበቃለን። ይሖዋ ለእኛ የሚበጀውን ያውቃል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ኦውሮራ “ይሖዋን መታዘዝ ምንጊዜም የተሻለ ሕይወት ለመምራት እንደሚረዳ ተገንዝቤያለሁ” ብላለች። ሁላችንም እንዲህ ይሰማናል። አንተስ ፍቅር የተንጸባረቀባቸውን የይሖዋን መመሪያዎች በመታዘዝህ የተጠቀምከው እንዴት ነው?

11. ጸሎት ምን ለማድረግ ይረዳናል?

11 ጸሎት አምላክን መታዘዝ አስቸጋሪ በሚሆንብን ጊዜም እንኳ ይህን ለማድረግ ይረዳናል። ይሖዋን መታዘዝ የሚያታግለን ጊዜ እንደሚኖር የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን ኃጢአት እንድንሠራ የሚገፋፋንን ዝንባሌ መዋጋታችንን ማቆም የለብንም። መዝሙራዊው “አንተን የመታዘዝ ፍላጎት በውስጤ እንዲቀሰቀስ አድርግ” ሲል አምላክን ለምኗል። (መዝ. 51:12) የዘወትር አቅኚ የሆነችው ዴኒስ “ከይሖዋ ትእዛዞች አንዱን ማክበር ሲከብደኝ፣ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ” ብላለች። ይሖዋ እንዲህ ላሉ ልመናዎች ምንጊዜም መልስ እንደሚሰጥ እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—ሉቃስ 11:9-13

ሌሎች አባታችንን እንዲወዱት እርዷቸው

12. በኤፌሶን 5:1 መሠረት ምን ልናደርግ ይገባል?

12 ኤፌሶን 5:1⁠ን አንብብ። የይሖዋ ‘የተወደዱ ልጆች’ እንደመሆናችን መጠን እሱን ለመምሰል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት አፍቃሪ፣ ደግ እና ይቅር ባይ በመሆን የእሱን ባሕርያት ለማንጸባረቅ እንሞክራለን። አምላክን የማያውቁ አንዳንድ ሰዎች መልካም ምግባራችንን ሲመለከቱ ስለ እሱ ለመማር ሊነሳሱ ይችላሉ። (1 ጴጥ. 2:12) ክርስቲያን ወላጆችም ልጆቻቸውን ከሚይዙበት መንገድ ጋር በተያያዘ ይሖዋን መምሰላቸው ተገቢ ነው። ይህን ማድረጋቸው ልጆቻቸውም ከአፍቃሪው አባታችን ጋር የራሳቸውን ወዳጅነት ለመመሥረት እንዲነሳሱ ሊያደርጋቸው ይችላል።

አንድ ወንድም መኪና ውስጥ ምግብ ለሚያበስል ሰው ትራክት ሲያሳይ።

አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት

13. ድፍረት ለማዳበር ምን ሊረዳን ይችላል?

13 ብዙውን ጊዜ ትናንሽ ልጆች በአባታቸው ስለሚኮሩ ስለ እሱ ማውራት ያስደስታቸዋል። እኛም በተመሳሳይ በሰማዩ አባታችን በይሖዋ ስለምንኮራ ስለ እሱ ለሌሎች መናገር እንፈልጋለን። ሁላችንም “በይሖዋ እኩራራለሁ” ብሎ እንደጻፈው እንደ ንጉሥ ዳዊት ይሰማናል። (መዝ. 34:2) ይሁንና ስለ ይሖዋ መናገር ቢያስፈራንስ? ድፍረት እንድናገኝ ምን ሊረዳን ይችላል? ስለ ይሖዋ መናገራችን እሱን ምን ያህል እንደሚያስደስተው እንዲሁም ሌሎች ስለ እሱ መማራቸው ምን ያህል እንደሚጠቅማቸው ማሰባችን ድፍረት ለማዳበር ይረዳናል። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ድፍረት ይሰጠናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ወንድሞቻችንን ደፋር እንዲሆኑ እንደረዳቸው ሁሉ እኛንም ይረዳናል።—1 ተሰ. 2:2

14. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ አያዳላም፤ በመሆኑም ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ፍቅር ስናሳይ ይደሰታል። (ሥራ 10:34, 35) ለሰዎች ፍቅር ማሳየት ከምንችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ምሥራቹን መናገር ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ታዲያ የስብከቱ ሥራ ምን ውጤት ያስገኛል? መልእክታችንን የሚሰሙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት የሚመሩ ከመሆኑም ሌላ ወደፊት የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል።—1 ጢሞ. 4:16

አባታችንን በመውደድ ደስተኞች ሁኑ

15-16. ደስተኛ እንድንሆን የሚያስችሉን ምን ምክንያቶች አሉ?

15 ይሖዋ አፍቃሪ አባት ስለሆነ ቤተሰቡ ደስተኛ እንዲሆን ይፈልጋል። (ኢሳ. 65:14) በዛሬው ጊዜ ችግሮች እያጋጠሙንም እንኳ ደስተኛ ለመሆን የሚያስችሉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ፣ የሰማዩ አባታችን በጣም እንደሚወደን እርግጠኞች በመሆናችን ደስተኞች ነን። የአምላክ ቃል ስለሆነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት አለን። (ኤር. 15:16) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋንና ላቅ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን የሚወዱ እንዲሁም እርስ በርስ የሚዋደዱ ሰዎችን ያቀፈ ልዩ ቤተሰብ አባል ነን።—መዝ. 106:4, 5

16 ወደፊት ደግሞ ሕይወት ከዚህ በጣም የተሻለ እንደሚሆን የተረጋገጠ ተስፋ ስላለን ደስተኞች መሆን እንችላለን። በቅርቡ ይሖዋ ክፉዎችን በሙሉ እንደሚያጠፋ እንዲሁም በመንግሥቱ አመራር ሥር ምድር እንደገና ገነት እንደምትሆን እናውቃለን። በተጨማሪም የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር እንደሚገናኙ የሚያረጋግጥ አስደናቂ ተስፋ አለን። (ዮሐ. 5:28, 29) ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል! ከሁሉ በላይ ደስ የሚለው ነገር ደግሞ በቅርቡ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ያለ ፍጥረት በሙሉ ለአፍቃሪው አባታችን የሚገባውን ክብር፣ ውዳሴና አምልኮ እንደሚያቀርብ እርግጠኞች ነን።

የሚከተሉትን ነገሮች ማድረጋችን አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማህ ለምንድን ነው?

  • አዘውትረን መጸለይ

  • ይሖዋን መታዘዝ

  • ስለ ሰማዩ አባታችን ለሌሎች መናገር

መዝሙር 12 ታላቁ አምላክ ይሖዋ

a አባታችን ይሖዋ በጣም እንደሚወደንና የእሱን አገልጋዮች ያቀፈው ቤተሰብ አባል እንድንሆን እንዳደረገ እናውቃለን። ይህም በምላሹ እሱን እንድንወደው ያነሳሳናል። ታዲያ አፍቃሪ ለሆነው አባታችን ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ