የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w21 ጥቅምት ገጽ 29-31
  • 1921—የዛሬ መቶ ዓመት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • 1921—የዛሬ መቶ ዓመት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ደፋር ሰባኪዎች
  • የግልና የቤተሰብ ጥናት
  • አዲስ መጽሐፍ!
  • የሚጠብቃቸው ሥራ
  • ይሖዋ የሚጠይቀንን ማድረግ በረከት ያስገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • 1922—የዛሬ መቶ ዓመት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ደስተኛ ለመሆን የሚረዳ ምርጫ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ለሰባት ትውልዶች ሲተላለፍ የቆየ ውርስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
w21 ጥቅምት ገጽ 29-31

1921—የዛሬ መቶ ዓመት

“ታዲያ በዚህ ዓመት የሚጠብቀን ሥራ ምንድን ነው?” የጥር 1, 1921 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ቀናተኛ ለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህን ጥያቄ አቅርቦ ነበር። መጠበቂያ ግንቡ መልሱን ለመስጠት፣ ስለ ስብከት ተልእኮ የሚገልጸውን ኢሳይያስ 61:1, 2⁠ን ጠቀሰ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ የዋህ ለሆኑ ሰዎች ምሥራች እንድናገር ቀብቶኛል። . . . ይሖዋ በጎ ፈቃድ የሚያሳይበትን ዓመት፣ አምላካችን የሚበቀልበትንም ቀን እንዳውጅ . . . ልኮኛል።”

ደፋር ሰባኪዎች

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ተልእኳቸውን ለመፈጸም ደፋሮች መሆን ያስፈልጋቸው ነበር። የዋህ ለሆኑ ሰዎች “ምሥራች” ለክፉዎች ደግሞ አምላካችን ‘ስለሚበቀልበት ቀን’ ማወጅ ነበረባቸው።

በካናዳ የሚኖረው ወንድም ጆን ሄንሪ ሆስከን ተቃውሞ ቢያጋጥመውም በድፍረት ይሰብክ ነበር። በ1921 መጀመሪያ አካባቢ ከአንድ የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ ጋር ተገናኘ። በውይይቱ መጀመሪያ ላይ ወንድም ሆስከን እንዲህ አለ፦ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስደሳች ውይይት ማድረግ እንችላለን፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ካልተስማማን ደግሞ በሰላም እንለያያለን።” የሆነው ግን ይህ አልነበረም። ወንድም ሆስከን እንዲህ ብሏል፦ “ገና ጥቂት ደቂቃዎች እንደተነጋገርን [ሰባኪው] በሩን በኃይል መታው፤ የበሩ መስታወት የሚረግፍ መስሎኝ ነበር።”

ሰባኪው “ወደ አሕዛብ ሄደህ እነሱን አታናግርም?” ብሎ ጮኸበት። ወንድም ሆስከን ምላሽ አልሰጠውም፤ ሆኖም እየሄደ ሳለ በልቡ “አንተስ ከእነሱ መች ተለየህ?” ብሎ አሰበ።

ሰባኪው በቀጣዩ ቀን በቤተ ክርስቲያን ሲያስተምርም ስለ ወንድም ሆስከን መጥፎ ነገር መናገሩን ቀጠለ። ወንድም ሆስከን እንዲህ ብሏል፦ “በከተማው ውስጥ እንደ እኔ ዓይነት አጭበርባሪ ታይቶ እንደማይታወቅ ምዕመናኑን ያስጠነቀቃቸው ሲሆን ልገደል እንደሚገባ ተናገረ።” ወንድም ሆስከን ግን በዚህ ሳይበገር በስብከቱ ሥራ ቀጠለ፤ ደግሞም ጥሩ ውጤት አገኘ። እንዲህ ብሏል፦ “በስብከቱ ሥራ በጣም አስደሳች ጊዜ አሳልፌያለሁ። አንዳንዶቹ ሰዎች ‘የአምላክ ሰው እንደሆንክ እናውቃለን!’ ይሉኝ ነበር፤ በተጨማሪም የሚያስፈልገኝ ነገር ካለ ሊሰጡኝ እንደሚፈልጉ ይነግሩኝ ነበር።”

የግልና የቤተሰብ ጥናት

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ፣ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ሲሉ ወርቃማው ዘመንa በተባለው መጽሔት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ዓምዶችን ያወጡ ነበር። “የልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ” የተባለው ዓምድ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሊወያዩባቸው የሚችሉ አንዳንድ ጥያቄዎችን ይዞ ይወጣ ነበር። ወላጆች “ለልጆቻቸው እነዚህን ጥያቄዎች ካቀረቡላቸው በኋላ መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያገኙ ይረዷቸዋል።” “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስንት መጻሕፍት አሉ?” እንደሚሉት ያሉ አንዳንድ ጥያቄዎች መሠረታዊ እውቀት የሚያስጨብጡ ነበሩ። “ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ስደት እንደሚደርስባቸው መጠበቅ ይኖርባቸዋል?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ደግሞ ልጆች ደፋር ሰባኪዎች እንዲሆኑ ያዘጋጇቸው ነበር።

ለጎለመሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ደግሞ “የመለኮታዊው የዘመናት ዕቅድ ጥልቅ ጥናት” የተባለ ዓምድ ይዘጋጅ ነበር፤ ይህ ዓምድ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ የመጀመሪያ ጥራዝ ላይ የተመሠረቱ የሚያመራምሩ ጥያቄዎችን የያዘ ነበር። እነዚህ ዓምዶች በሺዎች የሚቆጠሩ አንባቢዎችን ጠቅመዋል፤ ሆኖም የታኅሣሥ 21, 1921 ወርቃማው ዘመን መጽሔት ሁለቱም ዓምዶች መውጣት እንደሚያቆሙ አስታወቀ። እንዲህ ያለ ድንገተኛ ለውጥ የተደረገው ለምንድን ነው?

አዲስ መጽሐፍ!

የአምላክ በገና የተባለው መጽሐፍ

የሚነበበውን ክፍል የሚጠቁም ካርድ

ጥያቄዎችን የያዘ ካርድ

አመራር የሚሰጡት ወንድሞች፣ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መሠረታዊ እውነቶችን በተደራጀ መንገድ መማር እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘቡ። ለዚህም ሲባል ኅዳር 1921 የአምላክ በገና (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ወጣ። መጽሐፉን የወሰዱ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች “የአምላክ በገና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም” የተባለውን ኮርስም ይወስዱ ነበር። በዚህ ኮርስ ላይ ተማሪዎቹ ራሳቸውን የሚያስተምሩ ሲሆን “አምላክ ለሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ስላለው ዓላማ” ይማሩ ነበር። ትምህርቱ የሚካሄደው እንዴት ነበር?

አንድ ሰው መጽሐፉን ሲወስድ፣ ከመጽሐፉ ላይ የሚያነብባቸውን ገጾች የሚገልጽ ትንሽ ካርድ ይሰጠዋል። በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ ባነበባቸው ገጾች ላይ የተመሠረቱ ጥያቄዎችን የያዘ ሌላ ካርድ ይላክለታል። በዚህኛው ካርድ መጨረሻ ላይ፣ ለቀጣዩ ሳምንት እንዲያነብ የሚጠበቅበት ገጽ ይነገረዋል።

ለ12 ሳምንታት ያህል ተማሪው በአቅራቢያው ካለ ጉባኤ አዲስ ካርድ ይላክለታል። አብዛኛውን ጊዜ ካርዶቹን የሚልኩት በዕድሜ የገፉ ወይም የአቅም ገደብ ያለባቸው ወንድሞችና እህቶች ናቸው። ለምሳሌ በሚልቬል፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው አና ካትሪን ጋርድነር እንዲህ ብላ ነበር፦ “ታማሚ የነበረችው እህቴ ቴል የአምላክ በገና የተባለው መጽሐፍ ሲወጣ በአገልግሎቷ ተጨማሪ ተሳትፎ ማድረግ ቻለች፤ ጥያቄዎች የያዙ ካርዶችን በየሳምንቱ ለሰዎች ትልክ ነበር።” ተማሪው ኮርሱን ሲያጠናቅቅ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማግኘት እንዲችል አንድ ክርስቲያን በአካል ሄዶ ያነጋግረዋል።

ቴል ጋርድነር በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆና

የሚጠብቃቸው ሥራ

በዓመቱ መጨረሻ ላይ ወንድም ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ለሁሉም ጉባኤዎች ደብዳቤ ላከ። በደብዳቤው ላይ እንዲህ ብሏል፦ “የመከሩ ወቅት ከጀመረ ወዲህ፣ የዚህን ዓመት ያህል የመንግሥቱ ምሥራች ስብከት ሥራ በስፋትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ተከናውኖ አያውቅም።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ገና የሚቀረን ብዙ ሥራ አለ። ሌሎችም በዚህ የተባረከ ሥራ እንዲካፈሉ አበረታቷቸው።” የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ይህን ምክር በተግባር እንዳዋሉት በግልጽ ማየት ይቻላል። በ1922 ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ስለ መንግሥቱ በድፍረት አውጀዋል።

ደፋር ወዳጆች

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ እርስ በርስ በመረዳዳት የወንድማማች ፍቅር አሳይተዋል። ቀጥሎ የቀረበው ታሪክ እንደሚያሳየው ‘ለመከራ ቀን የተወለዱ’ ደፋር ወዳጆች ነበሩ።—ምሳሌ 17:17

ማክሰኞ፣ ግንቦት 31, 1921 በተልሳ፣ ኦክላሆማ፣ ዩናይትድ ስቴትስ “የተልሳ የዘር ማጥፋት ዘመቻ” ተካሄደ፤ ለዚህም ምክንያት የሆነው አንድ ጥቁር ሰው በአንዲት ነጭ ሴት ላይ ጥቃት ሰንዝሯል በሚል ተከስሶ መታሰሩ ነው። ከ1,000 የሚበልጡ ነጮች ከእነሱ በቁጥር ከሚያንሱ ጥቁሮች ጋር ተጋጩ፤ ጠቡ በፍጥነት እየተባባሰ ሄዶ ግሪንውድ ወደተባለው የጥቁሮች መንደር ደረሰ፤ በዚያ የሚገኙ ከ1,400 የሚበልጡ ቤቶችና ሱቆች ተዘረፉ እንዲሁም ተቃጠሉ። በዚህ ግጭት 36 ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ የተገለጸ ቢሆንም ትክክለኛው ቁጥር ግን በመቶዎች የሚቆጠር ሳይሆን አይቀርም።

በግሪንውድ የሚኖር ሪቻርድ ጆሴፍ ሂል የተባለ ጥቁር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በወቅቱ የተፈጠረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ረብሻው በተነሳበት ምሽት እንደ ወትሮው የጉባኤ ስብሰባ አድርገን ነበር። ስብሰባውን ከጨረስን በኋላ ከተማው ውስጥ ተኩስ ሰማን። ማታ ስንተኛም ተኩስ ይሰማ ነበር።” ረቡዕ ጠዋት ሰኔ 1 ሁኔታው ተባብሶ ነበር። ወንድም ሂል “አንዳንድ ሰዎች መጡና ጥበቃ ማግኘት ከፈለግን ቶሎ ብለን ወደ ማዘጋጃ ቤቱ አዳራሽ መሄድ እንዳለብን ነገሩን” ብሏል። ስለዚህ ወንድም ሂል፣ ባለቤቱና አምስት ልጆቻቸው ወደ ተልሳ ማዘጋጃ ቤት ሸሹ። በማዘጋጃ ቤቱ ውስጥ 3,000 የሚያህሉ ጥቁር ወንዶችና ሴቶች ተሰብስበው፣ ረብሻውን ለማረጋጋት ተብለው በተላኩ ወታደሮች ጥበቃ እየተደረገላቸው ነበር።

በዚህ ወቅት አርተር ክላውስ የተባለ አንድ ነጭ ወንድም ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ አደረገ። እንዲህ ብሏል፦ “ረብሸኞቹ በግሪንውድ እየተዘዋወሩ ቤቶችን እየዘረፉና እያቃጠሉ እንደሆነ ስሰማ ውድ ጓደኛዬ ወንድም ሂል ያለበትን ሁኔታ ለማጣራት ወሰንኩ።”

አርተር ክላውስ የአምላክ በገና በተባለው መጽሐፍ ተጠቅሞ 14 ልጆችን በአንድ ላይ አስጠንቷል

አርተር፣ ወንድም ሂል ቤት ሲደርስ መሣሪያ የያዘ ነጭ ሰው አገኘ። ይህ ሰው የወንድም ሂል ጎረቤትና ወዳጅ ነው፤ ሰውየው አርተርም ከረብሸኞቹ አንዱ መስሎት ነበር። በመሆኑም “እዚህ ምን ትሠራለህ?” ብሎ አርተር ላይ ጮኸበት።

አርተር እንዲህ ብሏል፦ “ሰውየው የሰጠሁት መልስ አጥጋቢ እንደሆነ ባይሰማው ኖሮ ይተኩስብኝ ነበር። እኔም የወንድም ሂል ወዳጅ እንደሆንኩና ቤቱ ብዙ ጊዜ መጥቼ እንደማውቅ ገለጽኩለት።” ወንድም አርተርና ይህ ሰው የወንድም ሂል ንብረት እንዳይዘረፍ ተከላከሉለት።

ብዙም ሳይቆይ አርተር ወንድም ሂልና ቤተሰቡ የማዘጋጃ ቤቱ አዳራሽ ውስጥ እንዳሉ ሰማ። አርተር በዚያ ያሉት ጥቁሮች፣ የወታደሮቹ አዛዥ በሆነው በጄኔራል ባሬት የተፈረመበት ማዘዣ ካልመጣ በስተቀር ከዚያ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተነገረው። አርተር እንዲህ ብሏል፦ “ጄኔራሉን አግኝቶ ማነጋገር በጣም አስቸጋሪ ነበር። ጄኔራሉ ምን እንዳሰብኩ ስነግረው ‘ይሄ ቤተሰብ ጉዳት እንዳይደርስበት ታደርጋለህ? የሚያስፈልጓቸውን ነገሮችስ ታሟላላቸዋለህ?’ ብሎ ጠየቀኝ። እኔም ይህንን በደስታ እንደማደርግ ነገርኩት።”

አርተር ማዘዣውን ካገኘ በኋላ ወደ ማዘጋጃ ቤቱ በፍጥነት ሄደ። ማዘዣውን ለአንድ ወታደር ሲያሳየው ወታደሩ በአግራሞት እንዲህ አለ፦ “እንዴ! ይሄንንማ ጄኔራሉ ራሱ አይደል እንዴ የፈረመበት! በዛሬው ዕለት ማንም ከዚህ ቦታ ሰው ለመውሰድ እንዳልመጣ ታውቃለህ?” ብዙም ሳይቆይ ወታደሩ እና አርተር ወንድም ሂልንና ቤተሰቡን አገኟቸው። ሁሉም በአርተር መኪና ተጭነው ወደ ቤታቸው ሄዱ።

‘ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች በእኩል ዓይን ይተያያሉ’

አርተር ወንድም ሂልና ቤተሰቡ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ አደረገ። አርተር ያሳየው ድፍረትና የወንድማማች ፍቅር ሌሎችን አስደንቋል። አርተር እንዲህ ብሏል፦ “የወንድም ሂልን ንብረት ከዘራፊዎች ያስጣለው ጎረቤቱ፣ ለእውነት ይበልጥ አድናቆት አደረበት። ሌሎች ብዙ ሰዎችም በመካከላችን የዘር መድልዎ እንደሌለና ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች በእኩል ዓይን እንደሚተያዩ ሲመለከቱ ስለ አምላክ መንግሥት የማወቅ ፍላጎት አደረባቸው።”

a ወርቃማው ዘመን (እንግሊዝኛ) በ1937 መጽናኛ (እንግሊዝኛ) የተባለ ሲሆን በ1946 ደግሞ ንቁ! ተብሏል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ