ጦርነት እና ግጭት ሁላችንንም የሚነካን እንዴት ነው?
“ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በዓለም ላይ የአሁኑን ያህል ግጭት በዝቶ አያውቅም። ሁለት ቢሊዮን ሰዎች ማለትም ከዓለም ሕዝብ መካከል ሩብ ያህሉ የሚኖሩት እንዲህ ያለ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ነው።”
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ ጥር 26, 2023
በአሁኑ ወቅት ሰላም ባለባቸው አካባቢዎችም ጦርነትና ግጭት በድንገት ሊከሰት ይችላል። ዓለማችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንደ አንድ መንደር ስለሆነች ጦርነት ካለበት አካባቢ ርቀው የሚኖሩ ሰዎችም እንኳ መዘዙ ሊነካቸው ይችላል። ደግሞም ጦርነት የሚያስከትለው ጉዳት ውጊያው ካበቃ በኋላም ለረጅም ጊዜ ይቀጥላል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት፦
የምግብ እጥረት። የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደገለጸው “አሁንም የረሃብ ትልቁ መንስኤ ጦርነት ነው። በዓለም ላይ ካሉት በረሃብ የተጠቁ ሰዎች መካከል 70 በመቶዎቹ የሚኖሩት በጦርነትና በዓመፅ በሚታመሱ አካባቢዎች ነው።”
አካላዊና አእምሯዊ ሕመም። ሰዎች ጦርነት በማንዣበቡ የተነሳ የሚሰማቸው ስጋት ለጭንቀትና ለውጥረት ሊዳርጋቸው ይችላል። በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ለአካላዊ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ለአእምሯዊ ሕመም የመጋለጣቸው አጋጣሚም ሰፊ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አስቸጋሪ ነው።
ስደት። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር እንደገለጸው እስከ መስከረም 2023 ድረስ በዓለም ዙሪያ ከ114 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ለዚህ ችግር ዋነኛው መንስኤ ጦርነትና ግጭት ነው።
የኢኮኖሚ ችግር። ጦርነት ብዙውን ጊዜ እንደ ዋጋ ግሽበት ያሉ የኢኮኖሚ ችግሮችን ያስከትላል። እንደ ሕክምናና ትምህርት ያሉ አገልግሎቶችን ለማሟላት ይውል የነበረው የመንግሥት ገንዘብ ጦርነትን ለመደገፍ መዋሉ ሰዎችን ለችግር ሊዳርግ ይችላል። ከዚህም ሌላ፣ በጦርነት የወደመውን ንብረት መልሶ ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብ በጣም ብዙ ነው።
ሥነ ምህዳራዊ ችግሮች። ሰዎች፣ የሚገለገሉበት የተፈጥሮ ሀብት ሆን ተብሎ ሲወድም ለመከራ ይዳረጋሉ። የውኃ፣ የአየርና የአፈር ብክለት ዘላቂ የጤና እክሎችን ሊያስከትል ይችላል። የተቀበሩ ፈንጂዎች የሚያስከትሉት አደጋም ውጊያው ካበቃ ከረጅም ጊዜ በኋላም ይቀጥላል።
በእርግጥም ጦርነት አውዳሚና አክሳሪ ነው።