የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 መስከረም ገጽ 2-7
  • ‘ሽማግሌዎችን ጥራ’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ሽማግሌዎችን ጥራ’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ሽማግሌዎችን መጥራት’ የሚኖርብን መቼ ነው?
  • ሽማግሌዎችን መጥራት የሚኖርብን ለምንድን ነው?
  • ሽማግሌዎች የሚረዱን እንዴት ነው?
  • የግል ኃላፊነታችን
  • ለኃጢአተኞች ፍቅርና ምሕረት ማሳየት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • የክርስቲያን ጉባኤ አደረጃጀት ምን ይመስላል?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
  • ወንድሞች—የጉባኤ ሽማግሌ ለመሆን እየተጣጣራችሁ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ለይሖዋ ሕዝቦች ጥቅም የቆሙ እረኞች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 መስከረም ገጽ 2-7

የጥናት ርዕስ 36

መዝሙር 103 እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች

‘ሽማግሌዎችን ጥራ’

“የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ።”—ያዕ. 5:14

ዓላማ

መንፈሳዊ እርዳታ በሚያስፈልግህ ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌዎችን ጠይቅ።

1. ይሖዋ በጎቹ ለእሱ በጣም ውድ መሆናቸውን ያሳየው እንዴት ነው?

የይሖዋ በጎች ለእሱ በጣም ውድ ናቸው። በኢየሱስ ደም የዋጃቸው ከመሆኑም ሌላ መንጋውን እንዲንከባከቡ የጉባኤ ሽማግሌዎችን ሾሟል። (ሥራ 20:28) አምላክ በጎቹ በርኅራኄ እንዲያዙ ይፈልጋል። ሽማግሌዎች በክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው ለበጎቹ የእረፍት ምንጭ ይሆናሉ፤ እንዲሁም ከመንፈሳዊ አደጋ ይጠብቋቸዋል።—ኢሳ. 32:1, 2

2. ይሖዋ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ለእነማን ነው? (ሕዝቅኤል 34:15, 16)

2 ይሖዋ ለሁሉም በጎቹ በጥልቅ የሚያስብ ቢሆንም ችግር ላጋጠማቸው አገልጋዮቹ ግን ለየት ያለ እንክብካቤ ያደርግላቸዋል። መንፈሳዊ ችግር ያጋጠማቸውን አገልጋዮቹን በሽማግሌዎች አማካኝነት ይረዳቸዋል። (ሕዝቅኤል 34:15, 16⁠ን አንብብ።) ሆኖም ይሖዋ እርዳታ ሲያስፈልገን እንድንጠይቅ ይጠብቅብናል። እንዲህ ባሉት ጊዜያት፣ ይሖዋ እንዲረዳን ልባዊ ጸሎት ከማቅረብ በተጨማሪ በጉባኤ ውስጥ ያሉ “እረኞችና አስተማሪዎች” እንዲረዱን ልንጠይቅ ይገባል።—ኤፌ. 4:11, 12

3. ሁላችንም የሽማግሌዎችን ሚና መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ አምላክ በሽማግሌዎች አማካኝነት መንፈሳዊ እርዳታ እንድናገኝ ያደረገውን ዝግጅት እንመረምራለን። የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቅ የሚኖርብን መቼ ነው? እንዲህ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? እነሱ የሚረዱንስ እንዴት ነው? በአሁኑ ወቅት ችግር ውስጥ ባንሆንም እንኳ እነዚህን ጥያቄዎች መመለሳችን ለይሖዋ ዝግጅት ያለንን አድናቆት ይጨምርልናል፤ ምናልባት ደግሞ አንድ ቀን ሕይወታችንን ሊያድንልን ይችላል።

‘ሽማግሌዎችን መጥራት’ የሚኖርብን መቼ ነው?

4. ያዕቆብ 5:14-16, 19, 20 የሚናገረው ስለ መንፈሳዊ ሕመም ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

4 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ፣ አምላክ መንፈሳዊ እርዳታ እንድናገኝ ስላደረገው ዝግጅት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ።” (ያዕቆብ 5:14-16, 19, 20⁠ን አንብብ።) ያዕቆብ እየተናገረ ያለው ስለ መንፈሳዊ ሕመም እንደሆነ ከአውዱ መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ የታመመው ሰው ይጥራ የተባለው ሐኪም ሳይሆን ሽማግሌዎችን ነው። በተጨማሪም የኃጢአት ይቅርታ ከፈውሱ ጋር ተያይዞ ስለተጠቀሰ ጥቅሱ የሚናገረው ስለ መንፈሳዊ ሕመም ነው ማለት እንችላለን። መንፈሳዊ ሕመምን ለማከም የሚወሰዱት እርምጃዎች አካላዊ ሕመምን ለማከም ከሚወሰዱት እርምጃዎች ጋር በአንዳንድ መንገዶች ይመሳሰላሉ። አካላዊ ሕመም ሲያጋጥመን ሐኪም ጋ እንሄዳለን፤ የሕመሙን ምልክቶች እንነግረዋለን፤ እንዲሁም የሚሰጠንን መመሪያ እንከተላለን። በተመሳሳይም መንፈሳዊ ሕመም ሲያጋጥመን ወደ አንድ ሽማግሌ መቅረብ፣ ያለንበትን ሁኔታ መግለጽ ከዚያም የሚሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።

ሥዕሎች፦ 1. አንድ ሰው የትከሻ ሕመሙን አስመልክቶ ሐኪም ሲያነጋግር። 2. አንድ ወንድም ከአንድ ሽማግሌ ጋር ደጅ ተቀምጦ ያለበትን ሁኔታ ለሽማግሌው ሲገልጽለት።

አካላዊ ሕመም ሲያጋጥመን ሐኪም ጋ እንሄዳለን፤ መንፈሳዊ ሕመም ሲያጋጥመን ደግሞ ወደ ሽማግሌዎች መሄድ ይኖርብናል (አንቀጽ 4ን ተመልከት)


5. በመንፈሳዊ ለመታመም እንደተቃረብን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

5 በያዕቆብ ምዕራፍ 5 ላይ የተጠቀሰው ዝግጅት መንፈሳዊ ጤንነታችን በሆነ መንገድ እንደተቃወሰ ሲሰማን ሽማግሌዎችን እንድናነጋግር ያበረታታናል። ይሁን እንጂ፣ ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና ከመበላሸቱ በፊት እርዳታ መጠየቃችን የጥበብ እርምጃ ነው። ለራሳችን ሐቀኞች መሆን አለብን። ቅዱሳን መጻሕፍት ያለንበትን መንፈሳዊ ሁኔታ በተመለከተ ራሳችንን እንዳናታልል ያስጠነቅቁናል። (ያዕ. 1:22) በጥንቷ ሰርዴስ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ስህተት ሠርተው ነበር፤ ኢየሱስም ስላሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ አስጠንቅቋቸዋል። (ራእይ 3:1, 2) መንፈሳዊ ጤንነታችንን መገምገም የምንችልበት አንዱ መንገድ ለአምልኳችን አሁን ያለንን ቅንዓት ከዚህ ቀደም ከነበረን ጋር በማወዳደር ነው። (ራእይ 2:4, 5) ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፦ ‘መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማሰላሰል የማገኘው ደስታ ቀንሷል? ለስብሰባ ሳልዘጋጅ መሄድ ወይም አልፎ አልፎ ከስብሰባ መቅረት ጀምሬያለሁ? ለአገልግሎት ያለኝ ቅንዓት ቀዝቅዟል? አብዛኛውን ጊዜ የማስበው ስለ ገንዘብ ወይም ስለ መዝናኛ ነው?’ ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዱንም እንኳ ‘አዎ’ ብለህ ከመለስክ መንፈሳዊ ድክመት እንዳለብህ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል፤ መፍትሔ ካላበጀህለት ይህ ድክመት እየተባባሰ መሄዱ አይቀርም። ድክመታችንን በራሳችን ልናስተካክል ካልቻልን ወይም ደግሞ ድክመቱ የይሖዋን መሥፈርቶች እንድንጥስ አድርጎን ከሆነ ሽማግሌዎች እንዲረዱን መጠየቅ ይኖርብናል።

6. ከባድ ኃጢአት የፈጸመ አንድ ክርስቲያን ምን ማድረግ ይኖርበታል?

6 አንድ ክርስቲያን ከጉባኤ እንዲወገድ ሊያደርገው የሚችል ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ አንድ ሽማግሌ ማነጋገር ይኖርበታል። (1 ቆሮ. 5:11-13) በከባድ ኃጢአት የተሸነፈ ማንኛውም ክርስቲያን ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለማደስ እርዳታ ያስፈልገዋል። በቤዛው አማካኝነት የይሖዋን ይቅርታ ለማግኘት “ለንስሐ የሚገባ ሥራ” መሥራት ይኖርብናል። (ሥራ 26:20) ይህ ሥራ፣ ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን ሽማግሌዎችን ማነጋገርን ይጨምራል።

7. ከባድ ኃጢአት ከፈጸሙ ክርስቲያኖች በተጨማሪ እነማን የሽማግሌዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል?

7 ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ክርስቲያኖችን ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ የደከሙትንም ይረዳሉ። (ሥራ 20:35) ለምሳሌ ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምታደርገው ትግል እየተሸነፍክ እንዳለ ሊሰማህ ይችላል። በተለይ እውነትን ከመስማትህ በፊት ዕፅ የመውሰድ ወይም ፖርኖግራፊ የመመልከት ልማድ ከነበረህ አሊያም ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ትመራ ከነበረ ትግሉ ይበልጥ ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። እነዚህን ፈተናዎች ብቻህን መጋፈጥ አያስፈልግህም። አንድ ሽማግሌ ልታነጋግር ትችላለህ። እሱም የሚያሳስብህን ነገር ስትነግረው ያዳምጥሃል፤ ጠቃሚ ምክር ይሰጥሃል፤ እንዲሁም መጥፎ ምኞትህን ከመፈጸም ተቆጥበህ ይሖዋን ማስደሰት እንደምትችል ያረጋግጥልሃል። (መክ. 4:12) ያነጋገርካቸው ሽማግሌዎች፣ ‘በትግሉ እየተሸነፍኩ ነው’ ብለህ መጨነቅህ በራሱ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ከፍ አድርገህ እንደምትመለከተውና ከልክ በላይ በራስህ እንደማትተማመን የሚያሳይ እንደሆነ ያስታውሱሃል።—1 ቆሮ. 10:12

8. ወደ ሽማግሌዎች መሄድ የማያስፈልገን እንዴት ላሉ ችግሮች ነው?

8 ከመንፈሳዊ ጤንነታችን ጋር ለተያያዘ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ወደ ሽማግሌዎች መሄድ አያስፈልገንም። ለምሳሌ አንድን ወንድም ወይም አንዲትን እህት የሚጎዳ ነገር ተናገርክ እንበል፤ ምናልባትም በቁጣ ገንፍለህ ተናግረሃቸው ይሆናል። ጉዳዩን ወደ አንድ ሽማግሌ ከመውሰድ ይልቅ ኢየሱስ ከወንድምህ ወይም ከእህትህ ጋር ሰላም ስለመፍጠር የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ። (ማቴ. 5:23, 24) እንደ ገርነት፣ ትዕግሥትና ራስን መግዛት ባሉት ባሕርያት ላይ ምርምር ማድረግ ትችላለህ፤ ይህም እነዚህን ግሩም ባሕርያት ወደፊት በተሻለ ሁኔታ ለማንጸባረቅ ይረዳሃል። እንዲህ አድርገህም ለችግሩ እልባት ማግኘት ካልቻልክ ግን አንድ ሽማግሌ እንዲረዳህ መጠየቅ ትችላለህ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኤዎድያንንና ሲንጤኪን እንዲያስታርቅ በስም ያልተጠቀሰን አንድ ወንድም ጠይቆ ነበር። በጉባኤህ ያለ አንድ ሽማግሌ ለአንተም እንዲህ ያለ እርዳታ ሊያደርግልህ ይችላል።—ፊልጵ. 4:2, 3

ሽማግሌዎችን መጥራት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

9. የኀፍረት ስሜት ሽማግሌዎችን ከመጥራት ወደኋላ እንድንል እንዲያደርገን ልንፈቅድ የማይገባው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 28:13)

9 ከባድ ኃጢአት ስንፈጽም ወይም ከግል ድክመታችን ጋር በምናደርገው ትግል እየተሸነፍን እንደሆነ ሲሰማን የሽማግሌዎችን እርዳታ ለመጠየቅ እምነትና ድፍረት ያስፈልገናል። የሚሰማን የኀፍረት ስሜት ሽማግሌዎችን ከመጥራት ወደኋላ እንድንል እንዲያደርገን መፍቀድ የለብንም። ለምን? የይሖዋን ዝግጅት ስንከተል በእሱ እንዲሁም እኛን በመንፈሳዊ ጤናማና ጠንካራ ለማድረግ በሰጠን መመሪያ እንደምንተማመን እናሳያለን። ልንወድቅ ስንቃረብ ሊረዳን የሚችለው እሱ ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን። (መዝ. 94:18) ኃጢአት ከፈጸምን ደግሞ ከተናዘዝንና ኃጢአት መሥራታችንን ካቆምን የአምላክን ምሕረት እናገኛለን።—ምሳሌ 28:13⁠ን አንብብ።

10. ኃጢአታችንን ለመደበቅ ከሞከርን ምን ሊያጋጥመን ይችላል?

10 እርዳታ ሲያስፈልገን ሽማግሌዎችን ካነጋገርን በረከት እናገኛለን። በአንጻሩ ግን፣ ኃጢአታችንን ለመደበቅ ከሞከርን ሁኔታውን እናባብሰዋለን። ንጉሥ ዳዊት ኃጢአቱን ለመደበቅ በሞከረ ጊዜ ለመንፈሳዊ፣ ለስሜታዊ አልፎ ተርፎም ለአካላዊ ሥቃይ ተዳርጓል። (መዝ. 32:3-5) ልክ እንደ አካላዊ ሕመም ሁሉ መንፈሳዊ ሕመምም በተገቢው መንገድ ካልታከመ እየተባባሰ መሄዱ አይቀርም። ይሖዋ ይህን ይረዳል፤ በመሆኑም በመንፈሳዊ እንድናገግም ባደረገልን ዝግጅት አማካኝነት ከእሱ ጋር ያለንን ‘ችግር ተወያይተን እንድንፈታ’ ጋብዞናል።—ኢሳ. 1:5, 6, 18

11. ከባድ ኃጢአትን መደበቃችን በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል?

11 የፈጸምነውን ከባድ ኃጢአት ከደበቅን ሌሎችን ልንጎዳ እንችላለን። የአምላክ መንፈስ በጉባኤው ውስጥ በነፃነት እንዳይሠራ ልናግድ እንዲሁም በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን መካከል ያለውን ሰላም ልናደፈርስ እንችላለን። (ኤፌ. 4:30) በተመሳሳይም በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ካወቅን ይህ ሰው ሽማግሌዎችን እንዲያነጋግር ልናሳስበው ይገባል።a የሌላን ሰው ከባድ ኃጢአት መደበቅ እኛንም ተጠያቂ ያደርገናል። (ዘሌ. 5:1) ለይሖዋ ያለን ፍቅር እውነቱን እንድንናገር ሊያነሳሳን ይገባል። እንዲህ በማድረግ ለጉባኤው ንጽሕና አስተዋጽኦ እናበረክታለን፤ እንዲሁም ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና እንዲያድሱ እንረዳቸዋለን።

ሽማግሌዎች የሚረዱን እንዴት ነው?

12. ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የደከሙትን የሚረዱት እንዴት ነው?

12 ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የደከሙ ክርስቲያኖችን እንዲደግፉ ታዘዋል። (1 ተሰ. 5:14) ኃጢአት ፈጽመህ ከሆነ ውስጣዊ ስሜትህንና ሐሳብህን ‘ቀድተው ለማውጣት’ አንዳንድ ጥያቄዎችን ሊጠይቁህ ይችላሉ። (ምሳሌ 20:5) ሁኔታውን በግልጽ መናገርህ ለእነሱ ይጠቅማቸዋል። በባሕልህ፣ በባሕሪህ ወይም በተሰማህ ኀፍረት የተነሳ እንዲህ ማድረግ ቀላል ባይሆንልህም እንኳ በግልጽ መናገርህ ጠቃሚ ነው። የማይሆን ነገር እናገራለሁ ብለህ አትፍራ። (ኢዮብ 6:3) ሽማግሌዎች በችኮላ መደምደሚያ ላይ ከመድረስ ይልቅ ምክር ከመስጠታቸው በፊት አንተን በጥሞና በማዳመጥ ስለ ሁኔታው የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። (ምሳሌ 18:13) ለመንጋው እረኝነት ማድረግ ጊዜ እንደሚወስድ ስለሚረዱ ውስብስብ ችግሮችን በአንድ ጊዜ ውይይት ለመፍታት አይሞክሩም።

13. ሽማግሌዎች በጸሎታቸውና በሚሰጡን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ አማካኝነት የሚረዱን እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

13 ሽማግሌዎች የሚሰማህን የጥፋተኝነት ስሜት ላለማባባስ ጥረት ያደርጋሉ። ከዚህ ይልቅ ይጸልዩልሃል። ጸሎታቸው ያለው “ታላቅ ኃይል” ከጠበቅከው በላይ ሊያበረታታህ ይችላል። የሚያደርጉልህ ድጋፍ ‘በይሖዋ ስም ዘይት መቀባትንም’ ይጨምራል። (ያዕ. 5:14-16) ይህ “ዘይት” በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት ያመለክታል። ሽማግሌዎች መጽሐፍ ቅዱስን ጥሩ አድርገው በመጠቀም ሊያረጋጉህና ሊያጽናኑህ ይችላሉ፤ እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ለማደስ ይረዱሃል። (ኢሳ. 57:18) የሚያካፍሉህ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ትክክለኛውን ነገር ማድረግህን ለመቀጠል ያለህን ቁርጠኝነት ሊያጠናክርልህ ይችላል። በእነሱ አማካኝነት የይሖዋ ድምፅ “መንገዱ ይህ ነው። በእሱ ሂድ” ሲልህ መስማት ትችላለህ።—ኢሳ. 30:21

ሥዕሎች፦ 1. ባለፈው ሥዕል ላይ ያለው ሐኪም የሰውየውን ትከሻ ሲመረምር። ትከሻውን የሚያሳይ ራጅ ግድግዳ ላይ ተሰቅሏል። 2. ባለፈው ሥዕል ላይ ያለው ሽማግሌና ሌላ ሽማግሌ ወንድም ቤት ሄደው መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው ሲያበረታቱት። ወንድም ሽማግሌዎቹን በደስታ እያዳመጣቸው ነው።

ሽማግሌዎች የታመሙትን ለማረጋጋትና ለማጽናናት መጽሐፍ ቅዱስን ይጠቀማሉ (አንቀጽ 13-14ን ተመልከት)


14. በገላትያ 6:1 መሠረት ሽማግሌዎች “የተሳሳተ ጎዳና” የተከተሉ ክርስቲያኖችን የሚረዱት እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

14 ገላትያ 6:1⁠ን አንብብ። አንድ ክርስቲያን “የተሳሳተ ጎዳና” ተከተለ የሚባለው ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጭ ነገር ሲያደርግ ነው። ምናልባትም ግለሰቡ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ አድርጎ ወይም ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ ሊሆን ይችላል። ክርስቲያን ሽማግሌዎች በፍቅር ተነሳስተው “እንዲህ ዓይነቱን ሰው በገርነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት” ያደርጋሉ። “ማስተካከል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል፣ ቦታውን የለቀቀን አጥንት ዘላቂ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ወደ ቦታው መመለስን ሊያመለክት ይችላል። ጥሩ ችሎታ ያለው አንድ ሐኪም አንድን የተሰበረ አጥንት ወደ ቦታው በሚመልስበት ጊዜ ሰውየውን ላለማሳመም ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ ሽማግሌዎችም መንፈሳዊ ሕመማችንን በሚያክሙበት ጊዜ በእኛ ላይ ሥቃይ ላለመጨመር ጥረት ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች ‘ለራሳቸው እንዲጠነቀቁም’ ምክር ተሰጥቷቸዋል። ሽማግሌዎች መንገዳችንን እንድናስተካክል ሲረዱን፣ እነሱም ቢሆኑ ፍጽምና እንደሚጎድላቸውና የተሳሳተ ጎዳና ሊከተሉ እንደሚችሉ ይገነዘባሉ። ራሳቸውን ከፍ ከፍ ከማድረግ፣ ተመጻዳቂ ከመሆን ወይም በእኛ ላይ ከመፍረድ ይቆጠባሉ፤ ከዚህ ይልቅ ስሜታችንን ለመረዳት ጥረት ያደርጋሉ።—1 ጴጥ. 3:8

15. ችግር ሲያጋጥመን ምን ልናደርግ እንችላለን?

15 በጉባኤያችን ሽማግሌዎች ላይ እምነት መጣል እንችላለን። ሚስጥራችንን መጠበቅ፣ በራሳቸው አመለካከት ላይ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው ምክር መስጠት እንዲሁም ከባድ ሸክማችንን እንድንሸከም በቀጣይነት መርዳት እንዳለባቸው ሥልጠና አግኝተዋል። (ምሳሌ 11:13፤ ገላ. 6:2) ባሕርያቸውና ያላቸው ልምድ የተለያየ ቢሆንም ወደ የትኛውም ሽማግሌ ቀርበን ችግራችንን ለማወያየት ነፃነት ሊሰማን ይገባል። እርግጥ ነው፣ የምንፈልገውን ዓይነት ምክር የሚሰጠን ሽማግሌ እስክናገኝ ድረስ ከአንዱ ወደ ሌላው አንሄድም። እንዲህ ካደረግን፣ በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን “ትክክለኛውን ትምህርት” ከመማር ይልቅ ‘ጆሯቸውን የሚኮረኩርላቸው’ እንደሚፈልጉት ዓይነት ሰዎች ሆንን ማለት ነው። (2 ጢሞ. 4:3) ወደ አንድ ሽማግሌ ቀርበን ችግራችንን ስንነግረው፣ ሌላ ሽማግሌ ጠይቀን እንደሆነና ምን ምክር እንዳገኘን ሊጠይቀን ይችላል። በተጨማሪም ልኩን የሚያውቅ ሽማግሌ በመጀመሪያ ሌላ ሽማግሌ ለማማከር ሊመርጥ ይችላል።—ምሳሌ 13:10

የግል ኃላፊነታችን

16. እያንዳንዳችን ምን ኃላፊነት አለብን?

16 ሽማግሌዎች ምክርና እርዳታ ቢሰጡንም ምን ውሳኔ ማድረግ እንዳለብን አይነግሩንም። ለአምላክ ያደርን ሆነን መኖር የግል ኃላፊነታችን ነው። ስለ ንግግራችንና ስለ ድርጊታችን ለአምላክ መልስ መስጠት ይጠበቅብናል። ተፈታታኝ ቢሆንም፣ በእሱ እርዳታ ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ እንችላለን። (ሮም 14:12) በመሆኑም ሽማግሌዎች አንድ ነገር እንድናደርግ ከማዘዝ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የአምላክን አስተሳሰብ እንድናስተውል ይረዱናል። የሚሰጡንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ‘የማስተዋል ችሎታችንን’ ማሠልጠንና ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ማድረግ እንችላለን።—ዕብ. 5:14

17. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

17 የይሖዋ በጎች መሆን እንዴት ያለ ውድ መብት ነው! ይሖዋ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንድናገኝ ሲል ቤዛውን እንዲከፍልልን “ጥሩ እረኛ” የሆነውን ኢየሱስን ልኮልናል። (ዮሐ. 10:11) እንዲሁም ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ባሉ ሽማግሌዎች አማካኝነት፣ እንዲህ ሲል የገባውን ቃል ፈጽሞልናል፦ “እንደ ልቤ የሆኑ [እረኞች] እሰጣችኋለሁ፤ እነሱም በእውቀትና በጥልቅ ማስተዋል ይመግቧችኋል።” (ኤር. 3:15) በመንፈሳዊ ስንታመም ወይም ስንደክም ሽማግሌዎችን ጠርተን እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ ልንል አይገባም። እንግዲያው፣ ይሖዋ ካደረገልን የጉባኤ ሽማግሌዎች ዝግጅት የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ‘ሽማግሌዎችን መጥራት’ የሚኖርብን መቼ ነው?

  • ሽማግሌዎችን መጥራት ያለብን ለምንድን ነው?

  • ሽማግሌዎች የሚረዱን እንዴት ነው?

መዝሙር 31 ከአምላክ ጋር ሂድ!

a ኃጢአት የፈጸመው ሰው በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ኃጢአቱን ካልተናገረ ለይሖዋ ያለህ ታማኝነት ጉዳዩን ለሽማግሌዎች እንድታሳውቅ ሊያነሳሳህ ይገባል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ