የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 መስከረም ገጽ 26-30
  • ይሖዋ ‘በተተከልንበት ቦታ እንድናብብ’ ረድቶናል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ‘በተተከልንበት ቦታ እንድናብብ’ ረድቶናል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ ከጠበቅኩት በላይ አትረፍርፎ ባርኮኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • ይሖዋ ‘ጎዳናዬን ቀና አድርጎልኛል’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • ይሖዋ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • አዲስ የአገልግሎት ምድብን መልመድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 መስከረም ገጽ 26-30
ማትስና አን-ካትሪን በገጠራማ ክልል ውስጥ ከመኪናቸው አጠገብ ቆመው።

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ‘በተተከልንበት ቦታ እንድናብብ’ ረድቶናል

ማትስ እና አን-ካትሪን ካስሆልም እንደተናገሩት

“በተተከላችሁበት ቦታ አብቡ” የሚለው ምክር እንግዳ ምክር ሊመስል ይችላል። ሆኖም ማትስ እና አን-ካትሪን የተባሉት ስዊድናዊ ባልና ሚስት ብዙ ጊዜ “ተተክለዋል።” በምን መንገድ? የተሰጣቸው ምክር የረዳቸውስ እንዴት ነው?

ማትስ እና አን-ካትሪን በ1979 በጊልያድ ትምህርት ቤት የተካፈሉ ሲሆን ባለፉት በርካታ ዓመታት በኢራን፣ በሞሪሸስ፣ በምያንማር፣ በታንዛንያ፣ በኡጋንዳና በዛየር እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። በጊልያድ ትምህርት ቤት ሳሉ ጃክ ሬድፎርድ የተባለው አስተማሪ የሰጠው ምክር በተደጋጋሚ “በተተከሉበት፣” “በተነቀሉበት” እና “እንደገና በተተከሉበት” ወቅት በጣም ረድቷቸዋል። እስቲ ታሪካቸውን ይንገሩን።

በመጀመሪያ እውነትን እንዴት እንደሰማችሁ እስቲ ንገሩን።

ማትስ፦ አባቴ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሚኖረው ፖላንድ ውስጥ ነበር። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ግብዝነት ተመልክቷል። ያም ቢሆን “እውነት የሆነ ቦታ መኖር አለበት” ብሎ ብዙ ጊዜ ይናገር ነበር። ውሎ አድሮ፣ አባቴ የተናገረው ነገር ትክክል መሆኑን አረጋገጥኩ። ያገለገሉ መጻሕፍትን ብዙ ጊዜ እገዛ ነበር። ከገዛኋቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለ ሰማያዊ መጽሐፍ ነው። ርዕሱ ትኩረቴን ሳበው። መጽሐፉን በገዛሁበት በዚያው ዕለት ሙሉ በሙሉ አንብቤ ጨረስኩት። መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ እውነትን እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ!

ከሚያዝያ 1972 ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጇቸውን ሌሎች በርካታ ጽሑፎች አንብቤያለሁ፤ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎቼም መልስ አገኘሁ። በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ነጋዴ ዓይነት ስሜት ተሰማኝ፤ ያ ነጋዴ ከፍተኛ ዋጋ ያለው አንድ ዕንቁ ሲያገኝ ዕንቁውን ለመግዛት ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ሸጦ ነበር። እኔም ያገኘሁትን የእውነት “ዕንቁ” ለመግዛት ስል ዩኒቨርሲቲ ተምሬ ሐኪም የመሆን ዕቅዴን “ሸጥኩት።” (ማቴ. 13:45, 46) ታኅሣሥ 10, 1972 ተጠመቅኩ።

በአንድ ዓመት ውስጥ ወላጆቼና ታናሽ ወንድሜም እውነትን ተቀብለው ተጠመቁ። ሐምሌ 1973 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። በጉባኤያችን ውስጥ ካሉት ቀናተኛ አቅኚዎች መካከል ውብና መንፈሳዊ የሆነች አን-ካትሪን የተባለች እህት ትገኝበታለች። ከእሷ ጋር ስለተዋደድን በ1975 ተጋባን። ቀጣዮቹን አራት ዓመታት የኖርነው ስትረምሱንድ በተባለችው የስዊድን ከተማ ነው። ክልሉ ውብና ፍሬያማ ነበር።

አን-ካትሪን፦ አባቴ እውነትን የሰማው ስቶክሆልም ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ሊያጠናቅቅ በተቃረበበት ወቅት ነው። በወቅቱ ገና የሦስት ወር ሕፃን ብሆንም ስብሰባና አገልግሎት ይዞኝ ይሄድ ነበር። እናቴ በዚህ አልተደሰተችም። የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ስህተት መሆኑን ለማሳየት ቆርጣ ተነሳች። ሆኖም ይህን ማድረግ ስላልቻለች ውሎ አድሮ እሷም ተጠመቀች። እኔ ደግሞ በ13 ዓመቴ ተጠመቅኩ፤ ከዚያም በ16 ዓመቴ አቅኚ ሆንኩ። የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት በኡሜዮ ካገለገልኩ በኋላ ልዩ አቅኚ ሆንኩ።

እኔና ማትስ ከተጋባን በኋላ ብዙ ሰዎች እውነትን እንዲማሩ የመርዳት መብት አግኝተናል። ከእነሱ መካከል አንዷ ማይቨር የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት ነች። ማይቨር ስፖርተኛ የመሆን ግቧን ትታ ከታናሽ እህቴ ጋር በአቅኚነት ማገልገል ጀመረች። በ1984 በጊልያድ ትምህርት ቤት የተካፈሉ ሲሆን ኢኳዶር ውስጥ በሚስዮናዊነት እያገለገሉ ነው።

የተለያዩ የሚስዮናዊ ምድቦችን በተቀበላችሁበት ወቅት ‘በተተከላችሁበት ቦታ እንድታብቡ’ የተሰጣችሁን ምክር በሥራ ላይ ያዋላችሁት እንዴት ነው?

ማትስ፦ በተደጋጋሚ አዳዲስ ቦታዎች ላይ “ተተክለናል።” ሆኖም ኢየሱስን ለመምሰል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ በእሱ ላይ ‘ሥር ሰደን’ ለመኖር ጥረት እናደርጋለን። በተለይ ትሕትናውን ለመኮረጅ እንሞክራለን። (ቆላ. 2:6, 7) ለምሳሌ በተመደብንበት አካባቢ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች እኛን እንዲመስሉ ከመጠበቅ ይልቅ የእነሱን የአኗኗር ዘይቤ ለመረዳት ጥረት እናደርጋለን። አስተሳሰባቸውንና ባሕላቸውን ለመረዳት እንፈልጋለን። ኢየሱስን ይበልጥ በመሰልን መጠን “በጅረቶች ዳር እንደተተከለ” ዛፍ በተመደብንበት ቦታ ሁሉ ማበብ እንደምንችል ተሰማን።—መዝ. 1:2, 3

ማትስና አን-ካትሪን ሻንጣና ምግብ ተሸክመው።

ብዙ ጊዜ ጉባኤዎችን ለመጎብኘት እንጓዝ ነበር

አን-ካትሪን፦ አንድ ዛፍ አዲስ ቦታ ላይ ከተተከለ በኋላ እንዲያድግ የፀሐይ ብርሃንም ያስፈልገዋል። ይሖዋ ምንጊዜም “ፀሐይ” ሆኖልናል። (መዝ. 84:11) ሞቅ ያለና ፍቅር የሰፈነበት የወንድማማች ማኅበር ሰጥቶናል። ለምሳሌ በቴህራን፣ ኢራን በሚገኘው ትንሽ ጉባኤያችን ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ዓይነት የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አጣጥመናል። ኢራን ውስጥ ብንቆይ ደስ ይለን ነበር። ሆኖም ሐምሌ 1980 የይሖዋ ምሥክሮች በመንግሥት እገዳ ተጣለባቸው፤ እኛም በ48 ሰዓት ውስጥ አገሪቱን ለቀን እንድንወጣ ታዘዝን። አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በዛየር (የአሁኗ ኮንጎ) እንድናገለግል ተመደብን።

ዛየር ውስጥ በገጠራማ መንደር የሚገኝ ትንሽ ቤት።

በዛየር ያሳለፍነው አስደሳች ጊዜ፣ 1982

አፍሪካ ውስጥ እንደተመደብን ስሰማ አለቀስኩ። እዚያ ስላሉ እባቦችና በሽታዎች የሰማሁት ነገር አስፈርቶኝ ነበር። ሆኖም አፍሪካ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ ሁለት የቅርብ ጓደኞቻችን እንዲህ አሉን፦ “ገና ስላልሄዳችሁ ነው። ሞክሩት። አፍሪካን እንደምትወዱት ምንም ጥያቄ የለውም።” ደግሞም ወደድነው! ወንድሞችና እህቶች አፍቃሪና ሞቅ ያሉ ናቸው። እንዲያውም በሥራችን ላይ በተጣለው እገዳ የተነሳ ከስድስት ዓመት በኋላ ዛየርን ለቀን ለመውጣት ስንገደድ በአግራሞት ፈገግ አልኩ። ምክንያቱም ወደ ይሖዋ “እባክህ አፍሪካ ውስጥ እንድንቆይ እርዳን” ብዬ መጸለይ ጀምሬ ነበር።

ባለፉት ዓመታት የትኞቹን በረከቶች አግኝታችኋል?

አን-ካትሪን ከኩምቢ ቮልሳቸው አጠገብ ታጣፊ ወንበር ላይ ተቀምጣ።

በታንዛንያ የነበረው “መኝታ ክፍላችን፣” 1988

ማትስ፦ የተለያየ ዜግነትና ባሕል ካላቸው ሚስዮናውያን ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት ትልቅ በረከት ነው። በአንዳንዶቹ ምድቦቻችን ደግሞ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት የሚያስገኘውን ልዩ ደስታ አጣጥመናል፤ ሁለታችንም ሃያ ሃያ ገደማ ጥናቶችን የምንመራበት ጊዜ ነበር። በአፍሪካ የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያሳዩን ፍቅርና እንግዳ ተቀባይነትም ሳልጠቅሰው የማላልፈው ነገር ነው። ታንዛንያ ውስጥ ያሉ ጉባኤዎችን በምንጎበኝበት ወቅት እንደ መኝታ ክፍላችን የምንጠቀምባትን ኩምቢ ቮልሳችንን የወንድሞች ቤት አጠገብ እናቆም ነበር። በዚህ ጊዜ “ከአቅማቸው በላይ” እንግዳ ተቀባይነት አሳይተውናል። (2 ቆሮ. 8:3) በጣም የምንወደው ሌላው ነገር ደግሞ “የተሞክሮ ሰዓት” ብለን የምንጠራውን ጊዜ ነው። እኔና አን-ካትሪን በእያንዳንዱ ምሽት ቁጭ ብለን በዕለቱ ውስጥ ስላጋጠሙን ነገሮች እናወራና ይሖዋን ስለ እርዳታው እናመሰግነዋለን።

አን-ካትሪን፦ ለእኔ ትልቅ ደስታ ያስገኘልኝ ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር ማጣጣሜ ነው። ፋርስኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ሉጋንዳ እና ስዋሂሊን ጨምሮ አዳዲስ ቋንቋዎችን ተምረናል፤ እንዲሁም ደስ የሚሉ የተለያዩ ባሕሎችን አይተናል። አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን አስተምረናል፤ እውነተኛ ወዳጆች አፍርተናል፤ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ከእነሱ ጋር ‘እጅ ለእጅ ተያይዘን’ ሠርተናል።—ሶፎ. 3:9

ዕፁብ ድንቅ የሆኑትን የይሖዋ የተለያዩ ፍጥረታት የማድነቅ አጋጣሚም አግኝተናል። በይሖዋ አገልግሎት አዲስ ምድብ በተቀበልን ቁጥር ይሖዋን አስጎብኚያችን አድርገን ከእሱ ጋር እየተጓዝን እንዳለን ይሰማናል። ይሖዋ በራሳችን ቢሆን ኖሮ ፈጽሞ ልናገኝ የማንችላቸውን ተሞክሮዎች እንድናገኝ ረድቶናል።

ፎቶግራፎች፦ 1. ማትስና አን-ካትሪን ለአንዲት እናትና ለልጆቿ ሲሰብኩ። 2. አን-ካትሪን የማሳይ ጎሳ አባል ለሆነ አንድ ሰው ስትመሠክር።

ታንዛንያ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች ስናገለግል

የትኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋችኋል? የተቋቋማችኋቸውስ እንዴት ነው?

ማትስ፦ ባለፉት ዓመታት ወባን ጨምሮ በተለያዩ በሽታዎች ተይዘናል። አን-ካትሪንም በተደጋጋሚ ድንገተኛ ቀዶ ሕክምና አስፈልጓታል። በተጨማሪም በዕድሜ የገፉት ወላጆቻችን ጉዳይ ያሳስበን ነበር። በመሆኑም ታናናሽ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ኃላፊነቱን ወስደው ወላጆቻችንን በመንከባከባቸው በጣም አመስጋኞች ነን። በትዕግሥት፣ በደስታና በፍቅር ይህን ሥራ አከናውነዋል። (1 ጢሞ. 5:4) ያም ቢሆን፣ ወላጆቻችንን በቅርበት መርዳት ባለመቻላችን አንዳንድ ጊዜ ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር እንታገል ነበር።

አን-ካትሪን፦ በ1983 በዛየር እያገለገልን ሳለን ኮሌራ ይዞኝ በጠና ታመምኩ። ሐኪሙ ማትስን “ዛሬውኑ ከዚህ አገር ይዘሃት ውጣ!” አለው። ልናገኝ የቻልነው ወደ ስዊድን የሚሄድ አውሮፕላን የጭነት አውሮፕላን ብቻ ስለነበር በማግስቱ ያንን አውሮፕላን ተሳፍረን ሄድን።

ማትስ፦ የሚስዮናዊነት አገልግሎታችንን ለማቆም እንደተገደድን ስለተሰማን አምርረን አለቀስን። ሆኖም ሐኪሙ ካሰበው በተለየ መልኩ አን-ካትሪን አገገመች። ከዚያም ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ዛየር መመለስ ቻልን። አሁን ደግሞ የተመደብነው በሉቡምባሺ በሚገኝ አነስተኛ የስዋሂሊ ጉባኤ ውስጥ እንድናገለግል ነው።

አን ካትሪን፦ በሉቡምባሺ ሳለን ጽንስ ጨነገፈብኝ። ቀድሞውንም ቢሆን ልጆች የመውለድ ዕቅድ አልነበረንም፤ ሆኖም ልጃችንን ማጣታችን ለመቋቋም የሚያዳግት መሪር ሐዘን አስከትሎብኛል። ነገር ግን በዚያ የሐዘን ወቅት ከይሖዋ ያልተጠበቀ ስጦታ አገኘን። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስጀመርን። አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የጉባኤያችን አስፋፊዎች ቁጥር ከ35 ወደ 70 ደረሰ፤ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ደግሞ ከ40 ወደ 220 አደገ። በአገልግሎት በጣም ተጠመድን። የይሖዋ በረከት ይህ ነው የማይባል መጽናኛ አስገኝቶልኛል። ያም ቢሆን ስለ ውድ ልጃችን ብዙ ጊዜ እናስባለን እንዲሁም እናወራለን። ይሖዋ ልባችንን ሙሉ በሙሉ የሚጠግንልን እንዴት እንደሆነ ለማየት እንጓጓለን።

ማትስ፦ በአንድ ወቅት አን-ካትሪን ኃይሏ ተሟጠጠ። እኔ ደግሞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የአንጀት ካንሰር እንዳለብኝ ታወቀ፤ በዚህም ምክንያት ከባድ ቀዶ ሕክምና አስፈለገኝ። አሁን ግን ጤንነቴ ተሻሽሏል፤ አን-ካትሪንም አቅሟ የፈቀደውን እያደረገች ነው።

ፈተና እያጋጠመን ያለነው እኛ ብቻ እንዳልሆንን ተገንዝበናል። በ1994 በሩዋንዳ ከተካሄደው የዘር ጭፍጨፋ በኋላ በስደተኛ ካምፖች ውስጥ ያሉ በርካታ ወንድሞችንና እህቶችን ጎብኝተን ነበር። እምነታቸውን፣ ጽናታቸውንና በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ውስጥ የሚያሳዩትን እንግዳ ተቀባይነት ማየታችን ይሖዋ ሕዝቦቹን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የመደገፍ ኃይል እንዳለው አስገንዝቦናል።—መዝ. 55:22

አን-ካትሪን፦ ሌላ ፈተና ያጋጠመን ደግሞ በ2007 በኡጋንዳ በተካሄደው የቅርንጫፍ ቢሮ ውሰና ላይ በተገኘንበት ወቅት ነው። ከፕሮግራሙ በኋላ 25 ገደማ ከሚሆኑ ሚስዮናውያንና ቤቴላውያን ጋር ወደ ናይሮቢ፣ ኬንያ መጓዝ ጀመርን። የኬንያ ድንበር ከመድረሳችን በፊት በተቃራኒ አቅጣጫ ይመጣ የነበረ ጭነት መኪና ድንገት መንገድ ስቶ ወደ እኛ መስመር መጣ፤ ከዚያም ፊት ለፊት ተጋጨን። ሹፌሩና ከወንድሞቻችን መካከል አምስቱ ወዲያውኑ ሞቱ፤ አንዲት እህት ደግሞ ሆስፒታል ከገባች በኋላ ሞተች። ጓደኞቻችንን ዳግመኛ ለማግኘት በጣም እንናፍቃለን።—ኢዮብ 14:13-15

ውሎ አድሮ ከደረሱብኝ አካላዊ ጉዳቶች አገገምኩ። ሆኖም እኔና ማትስ እንዲሁም ከተሳፋሪዎቹ መካከል አንዳንዶቹ በአደጋው የተነሳ በከባድ ጭንቀት መሠቃየት ጀመርን። በዚህም የተነሳ ሌሊት ላይ ልብ ድካም የሚመስል ሕመም ተሰምቶኝ በድንገት እባንን ነበር። በጣም ያስፈራ ነበር። ሆኖም ወደ ይሖዋ አጥብቀን መጸለያችን እንዲሁም ከምንወዳቸው ጥቅሶች ያገኘነው መጽናኛ ሁኔታውን ለመቋቋም ረድቶናል። የሕክምና እርዳታም አግኝተናል፤ ይህም በጣም ጠቅሞናል። አሁን ጭንቀቱ እየቀለለልን መጥቷል። ይሖዋ እንዲህ ያለ ችግር ያጋጠማቸውን ሌሎች ሰዎች ለማጽናናት እንዲረዳን እንጸልያለን።

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ስለቻላችሁበት መንገድ ስትናገሩ ይሖዋ “እንደ እንቁላል” እንደያዛችሁ ገልጻችኋል። እንዲህ ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው?

ማትስ፦ “ቱሜቤብዋ ካማ ማያይ ማቢቺ” የሚል የስዋሂሊ አባባል አለ፤ ትርጉሙ “እንደ እንቁላል ያዘን” ማለት ነው። አንድ ሰው እንቁላል እንዳይሰበርበት ተጠንቅቆ እንደሚይዝ ሁሉ ይሖዋም በእያንዳንዱ ምድባችን ላይ በርኅራኄ ተንከባክቦናል። የሚያስፈልገንን ነገር መቼም አጥተን አናውቅም፤ እንዲያውም ከሚያስፈልገንም በላይ አግኝተናል። የይሖዋን ፍቅርና ድጋፍ ያየንበት አንዱ መንገድ የበላይ አካሉ ባሳየን ርኅራኄ አማካኝነት ነው።

አን-ካትሪን፦ የይሖዋን ርኅራኄ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ብጠቅስ ደስ ይለኛል። አንድ ቀን ስልክ ተደወለልኝና በስዊድን ያለው አባቴ በጠና ታሞ ሆስፒታል እንደገባ ተነገረኝ። ማትስ ወባ ይዞት ገና ማገገሙ ነበር። በወቅቱ ወደ አገራችን መመለሻ የአውሮፕላን ቲኬት ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ አልነበረንም። ስለዚህ መኪናችንን ለመሸጥ ወሰንን። ከዚያ በኋላ ሁለት ስልክ ተደወለልን። በመጀመሪያ የደወሉልን ሁኔታችንን የሰሙ አንድ ባልና ሚስት ነበሩ፤ እነሱም አንድ ቲኬት ሊገዙልን እንደሚችሉ ነገሩን። ቀጥሎ የደወለችልን ደግሞ አንዲት አረጋዊት እህት ነበረች። አንድ ሣጥን ላይ “ለተቸገረ ሰው” የሚል ጽሑፍ ለጥፋ ገንዘብ ስታጠራቅም እንደቆየች ነገረችን። ይሖዋ በደቂቃዎች ውስጥ ታድጎናል።—ዕብ. 13:6

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፋችኋቸው ከ50 የሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ምን ትምህርት አግኝታችኋል?

ማትስና አን-ካትሪን በደስታ ጎን ለጎን ቆመው።

በምያንማር ባለው አዲስ ምድባችን ውስጥ

አን-ካትሪን፦ ‘ሳንረበሽ ተማምነን በመኖር’ ብርታት ማግኘት እንደምንችል ተገንዝቤያለሁ። በይሖዋ ስንታመን እሱ ውጊያችንን ይዋጋልናል። (ኢሳ. 30:15፤ 2 ዜና 20:15, 17) በተሰጠን በእያንዳንዱ ምድብ ይሖዋን አቅማችን በፈቀደ መጠን በማገልገላችን በሌላ በማንኛውም መንገድ ልናገኝ ከምንችለው በላይ ብዙ በረከቶችን አግኝተናል።

ማትስ፦ ያገኘሁት ትልቁ ትምህርት በእያንዳንዱ ሁኔታ ውስጥ በይሖዋ በመታመን እሱ ለእኔ ሲል የሚወስደውን እርምጃ ማየት እንዳለብኝ ነው። (መዝ. 37:5) ይሖዋ እንዲህ ለማድረግ የገባውን ቃል አጥፎ አያውቅም። አሁን በምያንማር ቤቴል በምናገለግልበት ወቅትም የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት እያየን ነው።

አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚፈልጉ በርካታ ወጣት ክርስቲያኖችም ይሖዋ ለእኛ ያሳየንን ታማኝ ፍቅር በሕይወታቸው እንዲያጣጥሙ እንመኛለን። ይሖዋ በተተከሉበት ቦታ ሁሉ ለማበብ እንዲረዳቸው ከፈቀዱ ታማኝ ፍቅሩን ማጣጣም እንደሚችሉ እርግጠኞች ነን።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ