ሁለት አዳዲስ የበላይ አካል አባላት
ጥቅምት 5, 2024 በተካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እንዲህ የሚል ልዩ ማስታወቂያ ተነግሮ ነበር፦ ወንድም ጆዲ ጄድሊ እና ወንድም ጄከብ ረምፍ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባላት ሆነው እንዲያገለግሉ ተሹመዋል። ሁለቱም ወንድሞች ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል።
ጆዲ ጄድሊ እና ባለቤቱ ደማሪስ
ወንድም ጄድሊ የተወለደው በሚዙሪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን ያደገው እውነት ውስጥ ነው። ቤተሰቦቹ የሚኖሩት እምብዛም ባልተሰበከበት ክልል አቅራቢያ ነበር። በመሆኑም በዚያ አካባቢ ለመስበክ ከተለያየ ቦታ ከሚመጡ በርካታ ወንድሞች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ አግኝቷል። እነዚህ ወንድሞች ያላቸው ፍቅርና አንድነት ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። ጥቅምት 15, 1983 በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ሳለ ተጠመቀ። አገልግሎት ይወድ ስለነበር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ መስከረም 1989 በዘወትር አቅኚነት ማገልገል ጀመረ።
ወንድም ጄድሊ ወጣት ሳለ ወላጆቹ እሱንና እህቱን ቤቴልን እንዲጎበኙ ይወስዷቸው ነበር። ይህም ወንድም ጄድሊና እህቱ በቤቴል የማገልገል ግብ እንዲያወጡ ረድቷቸዋል፤ ሁለቱም እዚህ ግብ ላይ መድረስ ችለዋል። ወንድም ጄድሊ መስከረም 1990 በዎልኪል ቤቴል ማገልገል ጀመረ። በመጀመሪያ በጽዳት ክፍል፣ በኋላም በሕክምና አገልግሎት ክፍል ሠርቷል።
በወቅቱ በአቅራቢያው ባሉ የስፓንኛ ጉባኤዎች ውስጥ እድገት ስለነበር በዚያ የሚያገለግሉ ወንድሞች ያስፈልጉ ነበር። በመሆኑም ወንድም ጄድሊ በአንዱ የስፓንኛ ጉባኤ ውስጥ ማገልገልና ቋንቋውን መማር ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ በዚያው ወረዳ ውስጥ በአቅኚነት ከምታገለግል ደማሪስ ከተባለች እህት ጋር ተዋወቀ። ውሎ አድሮ ተጋቡ፤ እሷም አብራው በቤቴል ማገልገል ጀመረች።
በ2005 ታማኝ ወላጆቻቸውን ለመንከባከብ ሲሉ ከቤቴል ወጡ። በዚያ ወቅት በዘወትር አቅኚነት አገልግለዋል። ወንድም ጄድሊ በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ያስተምር ነበር፤ እንዲሁም በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴና በአካባቢ የግንባታ ኮሚቴ ውስጥ አገልግሏል።
በ2013 ወንድም ጄድሊና ባለቤቱ ለዎርዊክ የግንባታ ፕሮጀክት በድጋሚ ወደ ቤቴል ተጠሩ። ከዚያ ወዲህ በፓተርሰንና በዎልኪልም አገልግለዋል። ወንድም ጄድሊ በአካባቢ ንድፍና ግንባታ ክፍል እንዲሁም በሆስፒታል መረጃ አገልግሎት ውስጥ ሠርቷል። መጋቢት 2023 የበላይ አካሉ የአገልግሎት ኮሚቴ ረዳት ሆኖ ተሾመ። እስካሁን ስላገለገለባቸው የአገልግሎት ምድቦች መለስ ብሎ ሲያስብ እንዲህ ብሏል፦ “አዲስ ምድብ ሲሰጠን አንዳንድ ጊዜ በጣም ልንፈራ እንችላለን። ሆኖም በይሖዋ መታመን እንዳለብን ልናስታውስ የሚገባን ያኔ ነው፤ ምክንያቱም እንድንሆን የሚያደርገን እሱ ነው።”
ጄከብ ረምፍ እና ባለቤቱ ኢንጋ
ወንድም ረምፍ የተወለደው በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነው። ልጅ ሳለ እናቱ የቀዘቀዘች ክርስቲያን ብትሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለእሱ ለማስተማር ጥረት ታደርግ ነበር። በተጨማሪም ታማኝ የይሖዋ ምሥክር የሆነችውን አያቱን በየዓመቱ ይጠይቅ ነበር። እሷም እውነትን የመማር ጉጉት እንዲያድርበት ረዳችው፤ በ13 ዓመቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራለት ጠየቀ። መስከረም 27, 1992 በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለ ተጠመቀ። ደስ የሚለው እናቱ ተነቃቃች፤ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላትም እድገት አድርገው ተጠመቁ።
ወንድም ረምፍ ወጣት ሳለ አቅኚዎች ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ተመልክቶ ነበር። በመሆኑም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ መስከረም 1995 በአቅኚነት ማገልገል ጀመረ። በ2000 ወደ ኢኳዶር ተዛውሮ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል ጀመረ። እዚያ ሳለ ከካናዳ ከመጣች ኢንጋ የተባለች አቅኚ ጋር ተዋወቀ። ከተጋቡ በኋላ ጥቂት አስፋፊዎች ባሉበት አንድ የኢኳዶር መንደር ውስጥ ማገልገል ጀመሩ። በአሁኑ ወቅት በዚያ መንደር ውስጥ ጠንካራ ጉባኤ አለ።
ውሎ አድሮ ወንድም ረምፍና ባለቤቱ ልዩ አቅኚዎች ሆነው ተሾሙ፤ በኋላም በወረዳ ሥራ ማገልገል ጀመሩ። በ2011 በጊልያድ ትምህርት ቤት 132ኛ ክፍል እንዲማሩ ተጋበዙ። ከተመረቁ በኋላ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አገልግለዋል፤ እንዲሁም ቤቴልን፣ ሚስዮናዊነትንና የወረዳ ሥራን ጨምሮ በተለያዩ የአገልግሎት ምድቦች ተካፍለዋል። በተጨማሪም ወንድም ረምፍ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት የማስተማር መብት አግኝቷል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወንድም ረምፍና ባለቤቱ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለሱ። በዎልኪል ቤቴል እንዲያገለግሉ የተጋበዙ ሲሆን ወንድም ረምፍ በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ሥልጠና ወሰደ። ከጊዜ በኋላ ወደ ኢኳዶር ቅርንጫፍ ቢሮ ተመልሰው ወንድም ረምፍ በቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ ማገልገል ጀመረ። በ2023 ወደ ዎርዊክ ተዛወሩ። ጥር 2024 ወንድም ረምፍ የበላይ አካሉ የአገልግሎት ኮሚቴ ረዳት ሆኖ ተሾመ። ወንድም ረምፍ እስካሁን ስላገለገለባቸው ቦታዎች መለስ ብሎ ሲያስብ እንዲህ ብሏል፦ “አንድን የአገልግሎት ምድብ ልዩ የሚያደርገው ቦታው አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አብረውን የሚያገለግሉት ሰዎች ናቸው።”
እነዚህ ወንድሞች በትጋት የሚያከናውኑትን ሥራ እናደንቃለን፤ እንዲሁም ‘እንዲህ ያሉትን ሰዎች በአክብሮት እንይዛቸዋለን።’—ፊልጵ. 2:29