የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ
‘መንፈሳዊ ስጦታችንን’ መጠቀም
ሁላችንም ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ጊዜ ስናሳልፍ እንበረታታለን። ሆኖም የሚያበረታታን አብረን ጊዜ ማሳለፋችን ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳችን የሌላውን እምነት ለማጠናከር የምንሰጠውን ማበረታቻ “መንፈሳዊ ስጦታ” ብሎ ይጠራዋል። (ሮም 1:11, 12) ይህን ስጦታ በተሟላ ሁኔታ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
በንግግራችን ሌሎችን ማበረታታት። ለምሳሌ በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ በራሳችን ላይ ሳይሆን በይሖዋ፣ በቃሉና በሕዝቡ ላይ ያተኮረ ሐሳብ መስጠት እንችላለን። ከእምነት አጋሮቻችን ጋር በምንጨዋወትበት ጊዜም ስለሚያንጹ ርዕሰ ጉዳዮች ለማውራት መምረጥ እንችላለን።
በውሳኔዎቻችንና በምግባራችን ሌሎችን ማበረታታት። ለምሳሌ አንዳንዶች ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል መርጠዋል። ሌሎች ደግሞ ሥራ የሚበዛባቸው ወይም ከባድ የጤና ችግር ያለባቸው ቢሆንም በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ አዘውትረው ይገኛሉ።
አንተስ በንግግርህና በድርጊትህ ወንድሞችህንና እህቶችህን ታበረታታለህ? እነዚህን መንፈሳዊ ስጦታዎች ለመቀበልስ ንቁ ነህ?