ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ቡልጋሪያ
በቡልጋሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸውን እውነት ለሰዎች በማስተማሩ ሥራ ተጠምደዋል። በሌሎች አገሮች የሚኖሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ወንድሞችና እህቶች ለመርዳት ከ2000 ዓ.ም. አንስቶ ወደ ቡልጋሪያ ተዛውረዋል። ለመሆኑ ወደ ሌላ አገር ተዛውሮ መስበክ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት? የሚከፈልለት መሥዋዕትነት አያስቆጭም የምንለውስ ለምንድን ነው? ወደ ቡልጋሪያ ተዛውረው የሚያገለግሉ ሰዎች የሰጡትን አስተያየት እንመልከት።
ግብ ማውጣት
“ከድሮ ጀምሮ፣ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር ተዛውሮ የማገልገል ግብ ነበረን” በማለት በእንግሊዝ ይኖር የነበረው ዳረን ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ከዶን ጋር ከተጋባን በኋላ በሩሲያኛ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ሥራ ለመርዳት ወደ ለንደን ተዛወርን። ወደ ሌላ አገር ሄደን ለማገልገል በተደጋጋሚ ዕቅድ አውጥተን የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች አልተሳካልንም። ተስፋ ልንቆርጥ ተቃርበን ነበር፤ ከዚያ ግን አንድ ወዳጃችን ሁኔታችን እንደተቀየረና አሁን ግባችን ላይ መድረስ እንደምንችል እንድናስተውል ረዳን።” ዳረን እና ዶን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ይበልጥ የሚያስፈልጉበትና እነሱ ተዛውረው ሊኖሩ የሚችሉበት አገር መፈለግ ጀመሩ። በ2011 ወደ ቡልጋሪያ ተዛወሩ።
ዳረን እና ዶን
አንዳንዶች ቀደም ሲል ወደ ሌላ አገር ተዛውሮ የማገልገል ግብ ባይኖራቸውም ይህን እርምጃ የወሰዱ ወንድሞችና እህቶች ያገኙትን ደስታ ማየታቸው ምሳሌያቸውን እንዲከተሉ አነሳስቷቸዋል። ከባለቤቷ ከሉካ ጋር በጣሊያን ትኖር የነበረችው ጃዳ “ደቡብ አሜሪካና አፍሪካ ውስጥ በአስደሳች አገልግሎት እየተካፈሉ ካሉ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝቼ ነበር” ብላለች። አክላም እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ተሞክሯቸውን መስማቴና ደስታቸውን ማየቴ ልቤን በጥልቅ ነካው። ይህም መንፈሳዊ ግቦቼ ላይ ማስተካከያ እንዳደርግ ረድቶኛል።”
ሉካ እና ጃዳ
በቼክ ሪፑብሊክ ይኖሩ የነበሩት ቶማሽ እና ቬሮኒካ፣ ክላራ እና ማትያስ ከተባሉ ሁለት ልጆቻቸው ጋር በ2015 ወደ ቡልጋሪያ ተዛወሩ። ይህን እርምጃ እንዲወስዱ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ቶማሽ እንዲህ ብሏል፦ “ዘመዶቻችንን ጨምሮ ወደ ውጭ አገር የተዛወሩ ወንድሞችንና እህቶችን ሁኔታ በቁም ነገር መረመርን። ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ ስናይ ተገረምን፤ ከዚያም አንድ ላይ በቤተሰብ ተወያየንበት።” በአሁኑ ጊዜ ይህ ቤተሰብ ሞንታና በተባለች የቡልጋሪያ ከተማ ውስጥ በተቋቋመ አዲስ ክልል በደስታ እያገለገለ ነው።
ክላራ፣ ቶማሽ፣ ቬሮኒካ እና ማትያስ
ሊንዳ የተባለች እህትም ወደ ቡልጋሪያ ተዛውራ እያገለገለች ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ከብዙ ዓመታት በፊት ኢኳዶርን በጎበኘሁበት ወቅት ወደዚያ ተዛውረው የሚሰብኩ ወንድሞችንና እህቶችን አግኝቼ ነበር። እኔም አንድ ቀን ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር ተዛውሬ ማገልገል እችል እንደሆነ አሰብኩ።” ፔቴሪ እና ናድያ የተባሉ በፊንላንድ ይኖሩ የነበሩ ባልና ሚስትም ሌሎች ሰዎች በተዉት ምሳሌ ላይ አሰላስለዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ጉባኤያችን ውስጥ ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ሲሉ ወደ ሌላ አካባቢ የተዛወሩ ተሞክሮ ያካበቱ አስፋፊዎች ነበሩ። በዚህ አገልግሎት ስላሳለፉት ጊዜ ሲናገሩ ሁሌም ደስታ ይነበብባቸዋል። በሕይወታቸው ውስጥ ከሁሉ የተሻለውን ጊዜ ያሳለፉት በእነዚያ ዓመታት እንደሆነ ይናገራሉ።”
ሊንዳ
ናድያ እና ፔቴሪ
አስቀድሞ ዕቅድ ማውጣት
ወደ ውጭ አገር ተዛውረው ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ ጥሩ ዕቅድ ማውጣታቸው አስፈላጊ ነው። (ሉቃስ 14:28-30) ከቤልጅየም የመጣች ኔለ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በሌላ አገር ስለማገልገል በቁም ነገር ማሰብ ስጀምር ስለ ጉዳዩ ጸለይኩ፤ እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጽሑፎች ለማግኘት ጥረት አደረግኩ። ጽሑፎቹን በማጥናት ልሠራባቸው የምችላቸውን ነጥቦች ለማስተዋል ሞከርኩ።”
ኔለ (በስተቀኝ)
ከፖላንድ የመጡት ክሪስቲያን እና ኢርሚና፣ ቡልጋሪያ መኖር ከጀመሩ ዘጠኝ ዓመት አልፏቸዋል። ከመዛወራቸው በፊት በፖላንድ ባለ የቡልጋሪያ ቋንቋ ቡድን ውስጥ መሰብሰባቸው በጣም እንደጠቀማቸው ይሰማቸዋል። ቡድኑ ያበረታታቸው ከመሆኑም ሌላ ቋንቋውን እንዲማሩ ረድቷቸዋል። ክሪስቲያን እና ኢርሚና እንዲህ ብለዋል፦ “ራሳችሁን በፈቃደኝነት ስታቀርቡ ይሖዋ አምላክ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ እንዴት እንደሚያሟላላችሁ ማየት ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ ተገንዝበናል። ይሖዋን በፈቃደኝነት ‘እነሆኝ! እኔን ላከኝ!’ ስትሉት ፈጽሞ ልታደርጉት እንደማትችሉ የሚሰማችሁን ነገር ማድረግ ትችላላችሁ።”—ኢሳይያስ 6:8
ክሪስቲያን እና ኢርሚና
ሬቶ እና ኮርኔሊያ የተባሉ ከስዊዘርላንድ የመጡ ባልና ሚስት ወደ ሌላ አገር ለመዛወር የሚያስችላቸውን ዝግጅት ለማድረግና ገንዘብ ለማጠራቀም ሲሉ ኑሯቸውን ቀላል ለማድረግ ወሰኑ። እንዲህ ብለዋል፦ “ከመዛወራችን ከአንድ ዓመት በፊት ስለ ቡልጋሪያ በደንብ ማወቅ ስለፈለግን ለአንድ ሳምንት ያህል ወደዚያ ሄደን ነበር። እዚያ ሳለን፣ ተሞክሮ ያላቸውን ሚስዮናውያን ያነጋገርን ሲሆን እነሱም ጠቃሚ ምክር ሰጥተውናል።” ሬቶ እና ኮርኔሊያ የተሰጣቸውን ምክር ሥራ ላይ በማዋል ወደ ቡልጋሪያ ተዛወሩ፤ አሁን በዚያ ማገልገል ከጀመሩ 20 ዓመት አልፏቸዋል።
ኮርኔሊያ እና ሬቶ፣ ከልጆቻቸው ከሉካስ እና ከያኒክ ጋር
ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣት
ወደ ውጭ አገር የሚዛወሩ ሰዎች አዳዲስ ብሎም ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ይኖርባቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 16:9, 10፤ 1 ቆሮንቶስ 9:19-23) ብዙዎች የሚያጋጥማቸው ትልቁ ፈተና አዲስ ቋንቋ መማር ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሉካ “በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የልባችንን አውጥተን ሐሳብ መስጠት ያስደስተን ነበር” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ቡልጋሪያኛ መማር ከጀመርን በኋላ ግን ለተወሰነ ጊዜ ያህል እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ቀላል ሐሳብ እንኳ ለመስጠት ተቸግረን ነበር! መልሰን ሕፃናት እንደሆንን ተሰማን። እንዲያውም የአገሪቱ ተወላጅ የሆኑት ልጆች ከእኛ በጣም የተሻለ ሐሳብ ይሰጡ ነበር።”
ከጀርመን የመጣው ራቪል እንዲህ ብሏል፦ “ቋንቋውን መማር አድካሚ ነበር። ሆኖም ‘ስህተት ስትሠራ አትደናገጥ፤ ቀልደህ ለማለፍ ሞክር’ እያልኩ በተደጋጋሚ ለራሴ እነግረው ነበር። የሚያጋጥሙኝን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደ ችግር ሳይሆን ለይሖዋ የማቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ክፍል እንደሆኑ አድርጌ እመለከታቸዋለሁ።”
ራቪል እና ሊሊ
ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሊንዳ እንዲህ ብላለች፦ “ቋንቋ መማር ላይ ጎበዝ አይደለሁም። ቡልጋሪያኛ ደግሞ ከባድ ቋንቋ ነው፤ ስለዚህ ብዙ ጊዜ ለማቆም አስቤ ነበር። ከሰዎች ጋር መነጋገርና እነሱ የሚሉትን መረዳት ሳትችሉ ስትቀሩ የብቸኝነት ስሜት ይሰማችኋል። በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኜ ለመቀጠል ስል ሁሉንም ነገር የማጠናው በስዊድንኛ ነበር። በጊዜ ሂደት፣ ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ ባደረጉልኝ እርዳታ ቋንቋውን መማር ችያለሁ።”
ሌላው ተፈታታኝ ነገር ደግሞ ናፍቆት ነው። ወደ ሌላ አካባቢ የሚዛወሩ ሰዎች ከሚወዷቸው ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ይለያያሉ። ከባለቤቷ ከያኒስ ጋር ወደ ቡልጋሪያ የተዛወረችው ኤቫ “መጀመሪያ ላይ ብቸኝነት ተሰምቶኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። አክላም “ይህን ስሜት ለማሸነፍ በትውልድ አገራችን ካሉ ወዳጆቻችን እና ቤተሰቦቻችን ጋር በተደጋጋሚ እናወራለን፤ እዚህም አዳዲስ ወዳጆች አፍርተናል” ብላለች።
ያኒስ እና ኤቫ
ሌሎች ተፈታታኝ ነገሮችም አሉ። ከስዊዘርላንድ የመጡት ሮበርት እና ሊያና እንዲህ ብለዋል፦ “ቋንቋውንና ባሕሉን ለመልመድ ተቸግረን ነበር። በዚያ ላይ በቡልጋሪያ ክረምቱ በጣም ቀዝቃዛ ነው፤ እኛም ለዚህ ሁኔታ አልተዘጋጀንም ነበር።” ሆኖም እነዚህ ባልና ሚስት አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝና ሁኔታውን ቀለል አድርገው ለማየት ጥረት በማድረጋቸው ላለፉት 14 ዓመታት ቡልጋሪያ ውስጥ በታማኝነት ማገልገል ችለዋል።
ሮበርት እና ሊያና
ያገኟቸው በረከቶች
ሊሊ ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ሁሉ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደው እንዲያገለግሉ ታበረታታለች። እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋን እርዳታ ለየት ባሉ መንገዶች ማየት ችያለሁ፤ ምናልባት በትውልድ አገሬ ብሆን ኖሮ እንዲህ ያለ አጋጣሚ ላላገኝ እችል ነበር። አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው ሌሎችን በመርዳት ነው፤ ይህም መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ እንዲሁም ደስታና እርካታ እንዳገኝ ረድቶኛል።” ባለቤቷ ራቪልም በዚህ ሐሳብ ይስማማል። እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ከሁሉ የተሻለ የሕይወት ጎዳና ነው፤ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ረገድ ብዙ ተሞክሮ ካላቸው በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ቀናተኛ ክርስቲያኖች ጋር የምትተዋወቁበት ልዩ አጋጣሚ ይሰጣችኋል። ከእነሱ ብዙ ተምሬያለሁ።”
ብዙዎች ራሳቸውን በፈቃደኝነት በማቅረባቸው “የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር” በተሳካ ሁኔታ ሊሰበክ ችሏል። (ማቴዎስ 24:14) የፈቃደኝነት መንፈስ በማሳየት ወደ ቡልጋሪያ የተዛወሩ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋ የልባቸውን ፍላጎት ሲያሟላላቸውና ዕቅዳቸውን ሁሉ ሲያሳካላቸው የማየት አጋጣሚ አግኝተዋል።—መዝሙር 20:1-4