የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • mrt ርዕስ 63
  • መቻቻል—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መቻቻል—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
  • ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው መቻቻል መሠረቱ ምንድን ነው?
  • መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች አክብሮት ስለማሳየት ምን ይላል?
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥላቻ ምን ይላል?
  • ስለ መቻቻል እና መከባበር የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
  • መቻቻል
    ንቁ!—2015
  • መቻቻል ከአንዱ ጽንፍ ወደ ሌላው
    ንቁ!—1998
  • ለሌሎች አክብሮት ማሳየት ቀረ እንዴ?
    ንቁ!—2024
  • በእርግጥ ታጋሽ ነህን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
ለተጨማሪ መረጃ
ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
mrt ርዕስ 63
የተለያየ ዕድሜ፣ ዘር፣ ሥራ እና ባሕል ያላቸው ደስተኛ ሰዎች።

መቻቻል—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ሰላም ሊሰፍን የሚችለው መቻቻል ካለ ብቻ ነው።”—የዩኔስኮ የመቻቻል መርሆች መግለጫ፣ 1995

በተቃራኒው ግን አለመቻቻል በሰዎች ልብ ውስጥ ንቀት ከዚያም አልፎ ጥላቻ እንዲዘራ ያደርጋል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉት ስሜቶች ወደ ጥላቻ ንግግር፣ አድልዎና የኃይል ድርጊት ያመራሉ።

ይሁን እንጂ ሰዎች መቻቻልን የሚረዱበት መንገድ የተለያየ ነው። አንዳንዶች መቻቻል ሲባል ‘ማንኛውም ዓይነት ድርጊትና ባሕርይ ትክክል ነው’ ብሎ መቀበል ማለት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሌሎች ግን በዚህ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዓይነት አመለካከት አላቸው፤ መቻቻል ማለት፣ እነሱ ራሳቸው አንዳንድ እሴቶችና እምነቶች ትክክል እንዳልሆኑ ቢያምኑም እንኳ ሌሎች በዚህ ረገድ የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ መብት እንዳላቸው ማክበር እንደሆነ ይረዳሉ።

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናዊው ዓለም በሚኖሩ ሰዎች መካከል መቻቻል እንዲሰፍን ሊረዳ ይችላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው መቻቻል መሠረቱ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ መቻቻልን ያበረታታል። “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ይላል። (ፊልጵስዩስ 4:5) መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች አሳቢነትና አክብሮት እንድናሳይ እንዲሁም በተገቢው መንገድ እንድንይዛቸው ያበረታታናል። ይህን ምክር ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች የሌላውን ሰው እሴት አይቀበሉት ወይም አይመሩበት ይሆናል፤ ሆኖም ግለሰቡ በመረጠው መንገድ ቢመላለስ አይቃወሙትም።

መጽሐፍ ቅዱስ መቻቻልን ቢያበረታታም አምላክ ለሰዎች ያስቀመጠው መሥፈርት እንዳለ ይገልጻል። “ሰው ሆይ፣ [አምላክ] መልካም የሆነውን ነግሮሃል” ይላል። (ሚክያስ 6:8) ሰዎች የተሻለ ሕይወት መምራት እንዲችሉ አምላክ የሰጣቸው መመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሯል።—ኢሳይያስ 48:17, 18

አምላክ በሌሎች ላይ የመፍረድ ሥልጣን አልሰጠንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሕግ የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ . . . በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?” (ያዕቆብ 4:12) አምላክ ለእያንዳንዳችን የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ነፃነት ሰጥቶናል፤ ለምናደርገው ምርጫ ኃላፊነቱን የምንወስደውም ራሳችን ነን።—ዘዳግም 30:19

መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች አክብሮት ስለማሳየት ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ “ሰውን ሁሉ አክብሩ” ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:17 የ1980 ትርጉም) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች የሚመሩ ሰዎች ሁሉንም ሰው ያከብራሉ፤ ሰዎቹ የሚያምኑበት ነገር ወይም የሚከተሉት አኗኗር ምንም ይሁን ምን አክብሮት ከማሳየት ወደኋላ አይሉም። (ሉቃስ 6:31) ይህ ማለት ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የሚመሩ ሰዎች ማንኛውንም ዓይነት እምነት ወይም አመለካከት ይቀበላሉ አሊያም ሌሎች የሚያደርጉትን ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ይደግፋሉ ማለት አይደለም። ያም ቢሆን ሌሎችን አክብሮት በሌለው ወይም ጨዋነት በጎደለው መንገድ አይዙም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ሌሎችን የያዘበትን መንገድ ለመኮረጅ ጥረት ያደርጋሉ።

አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በአንድ ወቅት ኢየሱስ እሱ የማይደግፈውን ሃይማኖት የምትከተልን አንዲት ሴት አነጋግሮ ነበር። ሴትየዋ ባሏ ካልሆነ ሰው ጋር ትኖር ነበር፤ ይህም ቢሆን ኢየሱስ የማይደግፈው ዓይነት አኗኗር ነው። እንደዚያም ሆኖ ግን ሴትየዋን ያነጋገራት በአክብሮት ነበር።—ዮሐንስ 4:9, 17-24

ኢየሱስ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ አንዲትን ሴት በአክብሮት ሲያነጋግራት።

እንደ ኢየሱስ ሁሉ ክርስቲያኖችም ሊያዳምጧቸው ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ እምነታቸውን ለማስረዳት ዝግጁ ናቸው፤ ይህን የሚያደርጉት ግን “ጥልቅ አክብሮት” በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። (1 ጴጥሮስ 3:15) መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች አመለካከታቸውን በሌሎች ላይ መጫን እንደሌለባቸው ያሳስባል። የክርስቶስ ተከታይ ‘ሊጣላ እንደማይገባው ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር መሆን’ እንዳለበት ይናገራል፤ ይህ ከእሱ የተለየ እምነት ያላቸውን ሰዎችም ይጨምራል።—2 ጢሞቴዎስ 2:24

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥላቻ ምን ይላል?

“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት [እንድናደርግ]” ይመክረናል። (ዕብራውያን 12:14) ከሰዎች ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት የሚያደርግ ሰው ጥላቻን ማስወገድ አለበት። ከሚያምንባቸው ነገሮች ጋር የሚጋጭ ነገር ሳያደርግ፣ ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር አቅሙ የፈቀደውን ያህል ይጥራል። (ማቴዎስ 5:9) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ ማለትም መጥፎ ነገር የሚያደርጉባቸውን ሰዎች በደግነት እንዲይዙ ያበረታታል።—ማቴዎስ 5:44

እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን የሚያዋርዱና በሌሎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ድርጊቶችን አምላክ ‘እንደሚጠላ’ ወይም ‘እንደሚጸየፍ’ ይናገራል። (ምሳሌ 6:16-19) ሆኖም እዚህ ላይ መጥላት የሚለው ቃል የተሠራበት መጥፎ ድርጊቶች በአምላክ ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌላቸው ለማመልከት ነው። አምላክ አኗኗራቸውን ለመቀየርና በእሱ መሥፈርቶች መሠረት ለመኖር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ይቅር እንደሚላቸውና ሊረዳቸው ፈቃደኛ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ኢሳይያስ 55:7

ስለ መቻቻል እና መከባበር የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

ቲቶ 3:2፦ “ምክንያታዊ እንዲሆኑና ለሰው ሁሉ ገርነትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያንጸባርቁ አሳስባቸው።”

ምክንያታዊ የሆነ ሰው የተለያየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በገርነት ይይዛል፤ ይህም በሰዎች መካከል መከባበር እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ማቴዎስ 7:12፦ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።”

ሁላችንም ብንሆን ሌሎች በአክብሮት ሲይዙን እንዲሁም አመለካከታችንንና ስሜታችንን ግምት ውስጥ ሲያስገቡ ደስ ይለናል። ኢየሱስ ያስተማረውን ይህን ታዋቂ የሥነ ምግባር መመሪያ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምትችል ለማወቅ “ወርቃማው ሕግ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

ኢያሱ 24:15፦ “የምታገለግሉትን ዛሬውኑ ምረጡ።”

ሌሎች የራሳቸውን ምርጫ ለማድረግ ያላቸውን መብት ስናከብርላቸው ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናደርጋለን።

የሐዋርያት ሥራ 10:34፦ ‘አምላክ አያዳላም።’

አምላክ የሰዎችን ባሕል፣ ፆታ፣ ዜግነት፣ ዘር ወይም አስተዳደግ ተመልክቶ አድልዎ አያደርግም። አምላክን መምሰል የሚፈልጉ ለሁሉም ሰዎች አክብሮት ያሳያሉ።

ዕንባቆም 1:12, 13፦ ‘አምላክ ክፋትን ዝም ብሎ ማየት አይችልም።’

አምላክ መቻቻልን ቢያበረታታም ትዕግሥቱ ገደብ አለው። ክፋት ለዘላለም እንዲቀጥል አይፈቅድም። ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ለማወቅ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

ሮም 12:19፦ “‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ” ተብሎ ስለተጻፈ [ለአምላክ] ቁጣ ዕድል ስጡ።”a

ይሖዋ ለማንኛውም ሰው፣ የበቀል እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አልሰጠም። እሱ በወሰነው ጊዜ ፍትሐዊ እርምጃ ይወስዳል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ሰዎች ፍትሕ ለማግኘት የሚያሰሙት ጩኸት ተሰሚነት ያገኝ ይሆን?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሰዎችና ሃይማኖቶች ጋር ተቻችሎ በመኖር ያምናሉ?

አንዳንዶች ከሌሎች እምነቶች ጋር ተቻችለን ለመኖር ፈቃደኛ እንዳልሆንን ይሰማቸዋል፤ ለዚህም የስብከቱ ሥራችንን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ። እኛ ግን ሁሉም ሰው የመረጠውን ነገር ለማመን ያለውን መብት እናከብራለን። አመለካከታችንን በሌሎች ሰዎች ላይ ከመጫንም እንቆጠባለን። የራሳቸው ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች የምንሰብከው ለምን እንደሆነ ለማወቅ “የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ያስገድዳሉ?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

ማንኛውም ሰው የይሖዋ ምሥክር እንዲሆን ወይም የይሖዋ ምሥክር ሆኖ እንዲቀጥል አናስገድድም። አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆኑን መተው ከፈለገ ምርጫውን እናከብርለታለን። ይሁንና አንዳንዶች ‘የይሖዋ ምሥክሮች በመቻቻል የሚያምኑ ከሆነ የእነሱ ሃይማኖት ተከታይ የነበሩ ሰዎችን የሚያስወጡት ወይም የሚያገልሉት ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። (1 ቆሮንቶስ 5:11, 13) ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የይሖዋ ምሥክሮች ቀደም ሲል የእነሱ ሃይማኖት አባል የነበረን ሰው ያገላሉ?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ