የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ የሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ
በዛሬው ጊዜ ሰዎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች የተነሳ በእጅጉ ተከፋፍለዋል። የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን በሚነኩ ሕጎች ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው። ደግሞም ለዚህ ፖለቲካዊ አቋማቸው ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሕግ አውጪዎችና ሌሎች ባለሥልጣናት በአብዛኛው እርስ በርሱ የሚቃረን አቋም ያላቸው ሲሆን ማንኛቸውም ለመስማማት ፈቃደኛ አይደሉም። እንዲህ ያሉት ልዩነቶች መንግሥት ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን የሚያሽመደምድ ፖለቲካዊ ቀውስ ይፈጥራሉ።
በተለይ በዩናይትድ ስቴትስና ዩናይትድ ኪንግደም ተብሎ በሚጠራው በብሪታንያ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ ትኩረታችንን የሚስብ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ አገራት ውስጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። ደግሞም አምላክ በሰማይ ያቋቋመው መንግሥት በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የሚገባው በዚህ ወቅት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
“በመጨረሻዎቹ ቀናት” የሚፈጠር ፖለቲካዊ ቀውስ
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዳንኤል መጽሐፍ አስደናቂ ትንቢት ይዟል። በዚህ ትንቢት ላይ አምላክ ወደፊት በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ስለሚፈጸም ወሳኝ ክስተት ለዳንኤል አሳውቆታል። “በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚሆነውን ነገር” ገልጦለታል።—ዳንኤል 2:28
አምላክ ይህን ትንቢት የገለጠው ለባቢሎን ንጉሥ ባሳየው ሕልም አማካኝነት ነው። ንጉሡ ከተለያዩ ማዕድናት የተሠራ ግዙፍ ምስል በሕልሙ አየ። በኋላ ላይ ነቢዩ ዳንኤል ከራስ እስከ እግር ያሉት የምስሉ ክፍሎች በታሪክ ዘመናት የሚነሱና የሚወድቁ የዓለም ኃያላን መንግሥታትን እንደሚወክሉ አብራራ።a በመጨረሻም ምስሉ በአምላክ የተቋቋመን መንግሥት ወይም መስተዳድር በሚወክል ድንጋይ ተመቶ ሙሉ በሙሉ ይወድማል።—ዳንኤል 2:36-45
ትንቢቱ ላይ እንደተገለጸው ሁሉም ሰብዓዊ መንግሥታት በአምላክ መንግሥት ይተካሉ። ኢየሱስ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ሲያስተምራቸው እየተናገረ የነበረው ስለዚህ መንግሥት ነው።—ማቴዎስ 6:10
ይሁንና ፖለቲካዊ ቀውስ እንደሚኖር የሚናገረው የትኛው የትንቢቱ ክፍል ነው? የምስሉ እግሮች “ከፊሉ ብረት፣ ከፊሉ ደግሞ ሸክላ” እንደሆኑ ልብ በል። (ዳንኤል 2:33) ወጥ ከሆኑ ማዕድናት ከተሠሩት ከሌሎቹ የምስሉ ክፍሎች በተለየ እግሮቹ ከሁለት ዓይነት ነገር የተሠሩ ናቸው። ይህም አንዱ የዓለም ኃያል መንግሥት ከሌሎቹ የተለየ እንደሚሆን የሚጠቁም ነው። እንዴት? የዳንኤል ትንቢት እንዲህ ሲል መልሱን ይሰጠናል፦
በትንቢቱ መሠረት በምስሉ እግሮች የተወከለው የዓለም ኃያል መንግሥት ፖለቲካዊ ቀውስ ያጋጥመዋል። የገዛ ሕዝቦቹ ጥንካሬውን ያዳክሙታል።
የዳንኤል ትንቢት በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ ነው
የምስሉ እግር በአሁኑ ጊዜ ያለውን ግዙፉን የዓለም ኃይል ማለትም የዩናይትድ ስቴትስንና የብሪታንያን ጥምረት ያመለክታል። በዘመናችን ያሉ ክስተቶች ወደዚህ መደምደሚያ እንድንደርስ የሚያደርጉን እንዴት ነው?
የምስሉ እግሮች የብረትና የሸክላ ውህድ መሆናቸው እምብዛም ጥንካሬ እንዳይኖራቸው ያደርጋል። (ዳንኤል 2:42) በዛሬው ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ በገዛ ሕዝቦቻቸው የተነሳ ጥንካሬያቸው ተዳክሟል። ለምሳሌ በሁለቱም አገራት ውስጥ ዜጎች እርስ በርሳቸው ተከፋፍለዋል። ሰዎች ዓምፀው በመነሳት መብታቸውን ለማስከበር ጥረት ያደርጋሉ። የመረጧቸው ተወካዮቻቸው በአብላጫ ድምፅ የሚስማሙባቸው ጉዳዮች በጣም ጥቂት ናቸው። እነዚህ መንግሥታት ዜጎቻቸው በእጅጉ የተከፋፈሉ ከመሆናቸው የተነሳ አንዳንዴ ፖሊሲያቸውን ማስፈጸም ሳይችሉ ይቀራሉ።
ዳንኤል ምዕራፍ 2 መንግሥታት ስላሉበት ሁኔታ የሚገልጽ ትንቢት ይዟል
በዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተገለጹ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች ምን ትርጉም እንዳላቸውና በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት፦
ትንቢት፦ “መንግሥቱም የተከፋፈለ ይሆናል፤ ሆኖም . . . በተወሰነ መጠን የብረት ጥንካሬ ይኖረዋል።”—ዳንኤል 2:41
ትርጉሙ፦ ሕዝቦቻቸው በፖለቲካዊ ጉዳዮች የተከፋፈሉ ቢሆኑም ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል አላቸው። በዚህም የተነሳ እንደ ብረት ባለ ጥንካሬ እርምጃ መውሰድ ይችላሉ።
ፍጻሜው
በ2023 ዩናይትድ ስቴትስና ዩናይትድ ኪንግደም ለወታደራዊ ዓላማ በጋራ ያወጡት ወጪ ከእነሱ ቀጥሎ ብዙ ወጪ ያወጡት 12 አገራት በድምሩ ካወጡት ወጪ የበለጠ ነው።—ስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም
“በዩናይትድ ኪንግደምና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለው ወታደራዊ ጥምረት . . . በየትኞቹም አገራት መካከል ካለው ጥምረት የበለጠ ጠንካራ፣ የጠበቀና ተራማጅ ነው። . . . አብረን እንሠራለን፤ አብረን እንቆማለን፤ አብረን እንዋጋለን።”—ስትራቴጂያዊ አመራር፣ የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር፣ ሚያዝያ 2024
ትንቢት፦ “የእግሮቹ ጣቶች ከፊሉ ብረት፣ ከፊሉ ሸክላ እንደሆኑ ሁሉ ይህም መንግሥት በከፊል ብርቱ፣ በከፊል ደግሞ ደካማ ይሆናል።”—ዳንኤል 2:42
ትርጉሙ፦ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ቢኖራቸውም ዲሞክራሲያዊ በሆነው የፖለቲካ መዋቅራቸው የተነሳ፣ ማድረግ የሚፈልጉትን ሁሉ ማድረግ አይችሉም። አንዳንዴ የአብላጫውን ድምፅ ድጋፍ ስለማያገኙ ያቀዱትን ነገር ለማስፈጸም ይቸገራሉ።
ፍጻሜው
“አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደገለጹት አሜሪካ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ክፍፍል ዩናይትድ ስቴትስ ከደህንነት አንስቶ እስከ ንግድ ጉዳዮች ድረስ በዓለም አቀፉ መድረክ ያሰበችውን እንዳታደርግ እንቅፋት ሆኖባታል።”—“ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል”
“ፖለቲከኞች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፖለቲካዊ ቀውስ የተነሳ ትኩረታቸው ተከፋፍሏል፤ በመሆኑም የብሪታንያ ሲቪል ሰርቪስb የመንግሥትን የለውጥ አጀንዳ ማራመድ አልቻለም።”—ኢንስቲትዩት ፎር ጋቨርመንት
ትንቢት፦ “እነሱም [ይህ መንግሥት ማለት ነው] ከተራው ሕዝብ ጋር ይደባለቃሉ፤ ሆኖም . . . አንዱ ከሌላው ጋር አይጣበቁም።”—ዳንኤል 2:43 የግርጌ ማስታወሻ
ትርጉሙ፦ ተራው ሕዝብ፣ መንግሥት በሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ለውጥ ማምጣት ቢችልም ባለሥልጣናቱም ሆኑ ድምፃቸውን የሚሰጡት ሰዎች ሙሉ በሙሉ የሚያረካ ውጤት አላገኙም።
ፍጻሜው
“በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ አሜሪካውያን ስለ ፖለቲካም ሆነ ስለ ፖለቲከኞች ያላቸው አመለካከት በጣም አሉታዊ ነው።”—ፒው የምርምር ማዕከል
“ሰዎች በመንግሥት፣ በፖለቲከኞች እና በመንግሥት ሥርዓታቸው ላይ ያላቸው እምነት ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ የአሁኑን ያህል ዝቅ ብሎ አያውቅም።”—“ብሔራዊ የማኅበራዊ ምርምር ማዕከል”
የዳንኤል ትንቢት ወደፊት የሚያገኘው ፍጻሜ
በዳንኤል ትንቢት መሠረት የአምላክ መንግሥት ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት በሚተካበት ጊዜ የሚኖረው ትልቁ የዓለም ኃይል የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ጥምር ኃይል ነው።—ዳንኤል 2:44
በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኝ ስለዚሁ ጊዜ የሚናገር ሌላ ትንቢት በአርማጌዶን ጦርነት ላይ ማለትም ‘ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን በሚካሄደው ጦርነት’ ላይ ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ’ ከይሖዋc አምላክ ጋር ለመዋጋት እንደሚሰበሰቡ ይናገራል። (ራእይ 16:14, 16፤ 19:19-21) በዚህ ጦርነት ላይ ይሖዋ ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት ይደመስሳል። በመሆኑም በዳንኤል ትንቢት ላይ የተገለጸው ምስል የሚወክላቸው የዓለም ኃያላን መንግሥታት ሁሉ ድምጥማጣቸው ይጠፋል።
ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “የአርማጌዶን ጦርነት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ስለ ፖለቲካዊ ቀውስ የሚናገረውን የዳንኤልን ትንቢት ማወቅህ የሚያስገኝልህ ጥቅም
መጽሐፍ ቅዱስ በዩናይትድ ስቴትስና በብሪታንያ ውስጥ ስለሚኖረው ፖለቲካዊ ቀውስ የተናገረው ትንቢት በዛሬው ጊዜ በትክክል እየተፈጸመ ነው። ስለዚህ ትንቢት ማወቅህ አሁን እየተከሰቱ ስላሉት ክንውኖች ያለህን እይታ ይቀይረዋል።
ኢየሱስ ተከታዮቹን ከዚህ ዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ገለልተኛ እንዲሆኑ ያዘዛቸው ለምን እንደሆነ ትረዳለህ። (ዮሐንስ 17:16) በተጨማሪም አምላክ በሰማይ ያቋቋመው መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው ኢየሱስ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” ብሎ የተናገረው ለምን እንደሆነ ትገነዘባለህ።—ዮሐንስ 18:36
የአምላክ መንግሥት እርምጃ የሚወስድበት እንዲሁም አምላክ ለሰው ልጆች ቃል የገባቸውን በረከቶች በመንግሥቱ አማካኝነት የሚያመጣበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን ስትገነዘብ ትጽናናለህ።—ራእይ 21:3, 4
በመንግሥታት መካከል ያሉ ሽኩቻዎች ዓለማችንን ያጠፏታል የሚል ስጋት ስለማያድርብህ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት ትጠባበቃለህ።—መዝሙር 37:11, 29
የዳንኤል ትንቢት፣ የሰው ልጆችን የሚገዛው የመጨረሻው የዓለም ኃያል መንግሥት በምስሉ እግሮች የተወከለው የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ጥምር ኃይል እንደሆነ ይጠቁማል። ቀጥሎ የሚመጣው ከሰማይ ሆኖ የሚገዛው ፍጹም መስተዳድር ማለትም የአምላክ መንግሥት ነው!
የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች ምን እንደሚያደርግ ለማወቅ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የተባለውን ቪዲዮ ተመልከት።
a “በዳንኤል ትንቢት ላይ የተገለጹት የዓለም ኃያላን መንግሥታት የትኞቹ ናቸው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b ሲቪል ሰርቪስ የሚለው አገላለጽ “ለዜጎች አገልግሎት እንዲሰጡ መንግሥት የቀጠራቸውን ሰዎች በሙሉ” ያመለክታል።—ሜሪያም ዌብስተርስ አንአብሪጅድ ዲክሽነሪ
c ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።