Photo by Stringer/Getty Images
ነቅታችሁ ጠብቁ!
የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ዩናይትድ ስቴትስ፣ እስራኤል እና ኢራን እየተሳተፉ ያሉበትን ጦርነት መላው ዓለም በስጋት እየተከታተለ ነው። ጦርነቱ ተባብሶ ሌሎች አገሮችን ያካትት ይሆን? መንግሥታት ይህን አስከፊ ሁኔታ ቀልብሰው ዘላቂ ሰላም ማምጣት ይችሉ ይሆን?
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን የሚያውቁ ሰዎች ‘በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ይህ ጦርነት በራእይ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው የአርማጌዶን ጦርነት መነሻ ይሆን?’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መንግሥታት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ጦርነት ማስቆም ይችሉ ይሆን?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በመኳንንትም ሆነ ማዳን በማይችሉ ሰዎች አትታመኑ።”—መዝሙር 146:3
መንግሥታት በመካከለኛው ምሥራቅ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ሰላም ማስፈን ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚለውን ጊዜ ያሳየናል። ሆኖም የትኛውም የፖለቲካ መሪ፣ ሰብዓዊ መንግሥት ወይም ቡድን ጦርነትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንደማይችል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። ‘ከመላው ምድር ላይ ጦርነትን ማስወገድ’ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።—መዝሙር 46:9
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ጦርነት ይቀራል—እንዴት?” የሚል ርዕስ ያለውን መጠበቂያ ግንብ መጽሔት አንብብ
የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የትንቢት ፍጻሜ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ጦርነትና የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ። . . . ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል።”—ማቴዎስ 24:6, 7
በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ግጭት ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ላይ እንዳለንና “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ እንደምንኖር የሚጠቁም ተጨማሪ ማስረጃ ነው። (ማቴዎስ 24:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) ዛሬ የምናያቸው ጦርነቶች አምላክ በቅርቡ ጦርነትን ለማስወገድ እርምጃ እንደሚወስድ እንዲሁም የሰው ልጆችን እያሠቃዩ ያሉትን ሌሎች ችግሮች የሚደመስስበት ጊዜ እንደደረሰ ይጠቁማሉ።
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ወይም ‘የመጨረሻው ዘመን’ ምልክት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ
አርማጌዶን የሚጀምረው በመካከለኛው ምሥራቅ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እነሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።”—ራእይ 16:16
አርማጌዶን በሰብዓዊ መንግሥታት መካከል የሚደረግ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚጀምር ጦርነት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሁሉም ሰብዓዊ መንግሥታትና በአምላክ መካከል የሚደረግ ዓለም አቀፋዊ ጦርነት ነው።
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የአርማጌዶን ጦርነት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ
የሚያስጨንቁ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ምን ይረዳናል?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።”—ፊልጵስዩስ 4:6
ይሖዋa አምላክ ወደ እሱ እንድንጸልይ ጋብዞናል። አምላክ ስለሚያስብልን ጸሎታችንን ይሰማል እንዲሁም የሚያስጨንቀንን ነገር ለመቋቋም ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 5:7) እንዲህ የሚያደርግበት አንዱ መንገድ ጦርነት የበዛው ለምን እንደሆነ ማሳወቅ ነው። ሆኖም ይህ ብቻ አይደለም፤ አምላክ ጦርነት እንደሚወገድ እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ የደረሰውን ሥቃይና መከራ ለመቀልበስ ምን እርምጃ እንደሚወስድም አሳውቆናል።—ራእይ 21:3, 4
አምላክ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ለማወቅ “መጽሐፍ ቅዱስ ብታነብ የሚያጽናናህ ሐሳብ ታገኝበታለህ” የሚለውን ርዕስ አንብብ
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18