የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ijwyp ርዕስ 81
  • ሲደብረኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሲደብረኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?
  • የወጣቶች ጥያቄ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ማወቅ የሚኖርብህ ነገር
  • ምን ማድረግ ትችላለህ?
  • ልጄ ቤት ውስጥ ቁጭ ማለት ቢሰለቸውስ?
    ለቤተሰብ
  • እቤት መሆን ይሰለችሃልን?
    ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
  • በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር አሰልቺ አይሆንም?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት መደሰት የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2012
ለተጨማሪ መረጃ
የወጣቶች ጥያቄ
ijwyp ርዕስ 81
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ልጅ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ቢኖሩትም አልጋው ላይ ተጋድሞ የቤቱ ኮርኒስ ላይ ሲያፈጥ

የወጣቶች ጥያቄ

ሲደብረኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?

አንዳንዶች፣ የሚሄዱበት ቦታ ወይም የሚያደርጉት ነገር ሳይኖራቸው ዝናባማ በሆነ ቀን ቤታቸው ዝም ብለው እንደ መቀመጥ የሚደብራቸው ነገር የለም። ሮበርት የተባለ አንድ ወጣት “እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲገጥመኝ ምን ማድረግ እንደምችል ስለማላውቅ ዝም ብዬ ቁጭ እላለሁ” በማለት ተናግሯል።

አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ሊረዳህ ይችላል!

  • ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

  • ምን ማድረግ ትችላለህ?

  • እኩዮችህ ምን ይላሉ?

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

  • ቴክኖሎጂ መጠቀም መፍትሔ ላይሆን ይችላል።

    የኢንተርኔት ገጾችን ማሰስ ጊዜን ለማሳለፍ ቢረዳም አዳዲስ ነገሮችን ከመሞከር ሊያግድህ ይችላል፤ ይህም ይበልጥ እንዲደብርህ ሊያደርግ ይችላል። የ21 ዓመቱ ጄረሚ “ስለ ምንም ነገር ሳላስብ ስክሪኑ ላይ ብቻ አፍጥጬ ቁጭ እላለሁ” ብሏል።

    ኤለና የተባለች ወጣት በዚህ ሐሳብ ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “ቴክኖሎጂ ተጠቅመህ ማከናወን የምትችለው ነገር ገደብ አለው። ከእውነታው ዓለም ተገልለህ እንድትቆይ ስለሚያደርግህ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያህን መጠቀምህን ስታቆም የበለጠ ይደብርሃል።”

  • አመለካከት ለውጥ ያመጣል

    ልታከናውነው የምትችለው ብዙ ነገር ያለህ መሆኑ ብቻ እንዳይደብርህ ያደርጋል? ይህ ለምታከናውነው ነገር ባለህ ፍቅር ላይ የተመካ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ካረን የተባለች ወጣት እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ትምህርት ቤት ስውል ቀኑን ሙሉ ላከናውነው የምችለው ብዙ ነገር ቢኖረኝም በጣም ይሰለቸኝ ነበር። የምትሠራው ነገር እንዳይደብርህ ሥራውን ልትወደው ይገባል።”

ይህን ታውቅ ነበር? “ምንም የምትሠራው ነገር የሌለህ” መሆኑ እንቅፋት ሳይሆን ጥሩ አጋጣሚ ነው፤ ይህን አጋጣሚ የፈጠራ ችሎታህን ለማሳደግ እንደሚረዳ ለም አፈር ልትቆጥረው ትችላለህ።

ከአንድ ተክል ውስጥ ጊታር፣ እስክሪብቶና እርሳስ እንዲሁም ሥዕል መሳያ ሲወጡ

ትርፍ ጊዜ የፈጠራ ችሎታህን ለማሳደግ እንደሚረዳ ለም አፈር ነው

ምን ማድረግ ትችላለህ?

የተለያዩ ነገሮችን ለማከናወን ሞክር። አዳዲስ ጓደኞች ለማፍራት ጣር። አዲስ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ለማግኘት ሞክር። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምርምር አድርግ። የተለያየ ነገር የሚሞክሩ ሰዎች ብቻቸውን ሲሆኑ ቶሎ አይደብራቸውም፤ ሌሎች ሰዎችም ከእነሱ ጋር ሲሆኑ አይደብራቸውም!

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኃይልህ አከናውን።”—መክብብ 9:10

“በቅርቡ ማንዳሪን ቻይንኛ መማር ጀምሬያለሁ፤ በየቀኑ ቋንቋውን መለማመዴ አዲስ ነገር መማር በጣም አስደሳች ነገር እንደሆነ እንዳስታውስ አድርጎኛል። አዲስ ፕሮጀክት ያለኝ መሆኑን በጣም ወድጄዋለሁ። በተጨማሪም አእምሮዬ እንዳይባዝንና ጊዜዬን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድጠቀምበት ረድቶኛል።”—ሜሊንዳ

ዓላማህ ላይ ትኩረት አድርግ። አንድ ነገር የምታከናውንበትን ዓላማ ከተገነዘብክ ሥራውን ለማከናወን የበለጠ መጓጓትህ አይቀርም። ዓላማህን በአእምሮህ መያዝህ ትምህርት ቤት የተሰጠህን የቤት ሥራ መሥራት እንኳ ቶሎ እንዳይሰለችህ ያደርጋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰው . . . ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት የሚሻለው ነገር የለም።”—መክብብ 2:24

“ትምህርት ልጨርስ አካባቢ ወደ ኋላ የቀረሁበትን ጥናት ለማካካስ በየቀኑ ለስምንት ሰዓታት ማጥናት አስፈልጎኝ ነበር። ዓላማዬን ለማሳካት ቆርጬ ስለነበር ይህ አሰልቺ አልሆነብኝም። ፈተናውን አልፌ ለመመረቅ የነበረኝን ዓላማ በአእምሮዬ መያዜ በትጋት ለማጥናት አነሳስቶኛል።”—ሐና

መለወጥ የማትችለውን ነገር አምነህ ተቀበል። በጣም የሚያስደስትህ ነገር እንኳ አንዳንድ አሰልቺ ነገሮች እንደሚኖሩት የታወቀ ነው። በጣም የምትወዳቸው ጓደኞችህም ቀጠሯችሁን በመሰረዛቸው የተነሳ ጊዜህን የምታሳልፍበት ነገር ልታጣ ትችላለህ። እንዲህ ያለው ሁኔታ ደስታህን እንዲያሳጣህ ከመፍቀድ ይልቅ ነገሩን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለመመልከት ጣር።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ደስተኛ ልብ ያለው ሰው . . . ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ያለ ያህል ነው።”—ምሳሌ 15:15

“አንዲት ጓደኛዬ ለብቻዬ ሆኜም አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ እንድለምድ መከረችኝ። በተጨማሪም ከሌሎችም ጋርም ሆነ ለብቻችን የምናሳልፈውን ጊዜ ማመጣጠን፣ ሁላችንም ሊኖረን የሚገባ በጣም አስፈላጊ ችሎታ እንደሆነ ነግራኛለች።”—አይቪ

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

ሐና

“አስደሳች ሕይወት እየመሩ በሚመስሉ ሰዎች በጣም እቀና ነበር። ሆኖም እንደዚያ የሆኑት የተለያዩ ነገሮችን ስለሚያደርጉ እንጂ የተለዩ ሰዎች ስለሆኑ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ስለዚህ እኔም የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ ጀመርኩ። በትርፍ ጊዜ ላደርገው የምችለው ነገር መረጥኩ እንዲሁም ትኩረቴን በሚስቡ ርዕሶች ላይ ምርምር አደረግኩ። ስለምንኖርበት ዓለም ያለንን ግንዛቤ ስናሰፋ ይበልጥ ለመማር እንነሳሳለን፤ ይህም ጊዜያችንን የምናሳልፍበት ነገር ለማግኘት ያስችለናል።”—ሐና

ካሌብ

“በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳለሁ እንዳይደብረኝ ስል የቪዲዮ ጨዋታዎች በመጫወት ጊዜ አሳልፍ ነበር። ዕድሜዬ ከፍ እያለ ሲሄድ ግን የቪዲዮ ጨዋታዎች መጫወት ብዙ ነገሮች እያሳጣኝ እንዳለ አስተዋልኩ። ብዙ ጊዜህን የቪዲዮ ጨዋታዎች እየተጫወትክ ማሳለፍ ትችላለህ፤ ተጫውተህ ስትጨርስ ግን ምንም ጠቃሚ ነገር እንዳላከናወንክ ትረዳለህ። አሁን ጊዜዬን ላሳልፍ የምችልባቸው የተሻሉ ነገሮች አግኝቻለሁ።”—ካሌብ

ሚካኤላ

“ሰፊ ጊዜ ቢኖረኝም ምንም ልሠራው የምችል ነገር እንደሌለኝ ይሰማኝ ነበር፤ ይሁንና ሰዎች ጓደኛ እንዲያደርጉኝ ከፈለግኩ ቅድሚያውን ወስጄ ልቀርባቸው እንደሚገባ ውሎ አድሮ ተገነዘብኩ። እንደዚያ በማድረጌም በእጅጉ ተጠቅሜያለሁ። አሁን አሁን፣ ለብቻዬ የማሳልፋቸውን ‘አሰልቺ’ ጊዜያት ማድነቅ ጀምሬያለሁ፤ ምክንያቱም አሁን ለብቻዬ የምሆንባቸው አጋጣሚዎች በጣም ጥቂት ናቸው።”—ሚካኤላ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ