ኦሌህ ራድዚሚንስኪ | የሕይወት ታሪክ
የእስር ቤት ግንብ ከይሖዋ አልለየኝም
የተወለድኩት በ1964 በሳይቤሪያ ነው፤ ወላጆቼ ከዩክሬን ከተወሰዱ በኋላ የሚኖሩት እዚያ ነበር። እስከማስታውሰው ድረስ ወላጆቼና አያቶቼ፣ በታሰሩበት ጊዜም ጭምር በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ነበራቸው። አያቴ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ በሚያከናውነው ሥራ ምክንያት ለሰባት ዓመት ታስሮ ነበር። ከጊዜ በኋላ እኔም የታሰርኩ ሲሆን በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት የሚፈትን ሁኔታ አጋጥሞኛል።
በ1966 ወደ ዩክሬን ተመለስን። ስለ ልጅነቴ ካሉኝ ትዝታዎች አንዱ የአራት ዓመት ልጅ ሳለሁ እስር ቤት የነበረውን አያቴን ለመጠየቅ የምናደርገው ጉዞ ነው። እኔና እናቴ በዩክሬን ከምትገኘው ከክሪቪ ሪህ ተነስተን በማዕከላዊ ሩሲያ ወደሚገኘው የሞርዶቪያ የእስረኞች የጉልበት ሥራ ካምፕ ለመድረስ ለረጅም ሰዓት በባቡር እንጓዛለን። ከአያቴ ጋር እንድናሳልፍ የሚፈቀድልን ሁለት ሰዓት ብቻ ነበር፤ ያውም ጠባቂዎች ባሉበት። ሆኖም ጠባቂዎቹ አቅፎኝ እንዲቀመጥ ይፈቅዱለት ነበር።
በትምህርት ቤት በይሖዋ መታመን
ከወንድሜ ከሚክሃይሎ ጋር፤ በስተ ቀኝ ያለው እሱ ነው
ልጅ ሳለሁ ዩክሬን ውስጥ በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት የሚፈትኑ ብዙ ነገሮች አጋጥመውኛል። ለምሳሌ ልጆች ትምህርት ሲጀምሩ ሌኒንን በልጅነቱ የሚያሳይን ባለኮከብ ባጅ ዩኒፎርማቸው ላይ እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸው ነበር።a ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ ልጆች የሌኒንን መርሆች እንደሚደግፉ ለማሳየት አንገታቸው ላይ ቀይ ጨርቅ ማሰር ነበረባቸው። እኔ ግን ሙሉ በሙሉ ታማኝ መሆን ያለብን ለይሖዋ እንደሆነ ስለማውቅ እነዚህን ፖለቲካዊ ምልክቶች ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበርኩም።
ወላጆቼ በፖለቲካ ገለልተኛ እንደመሆን ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በትዕግሥት በማብራራትና በማስረዳት እውነትን የራሴ እንዳደርግ ረድተውኛል። በተጨማሪም በትምህርቴ ጎበዝ መሆኔ ይሖዋን እንደሚያስከብረው ይነግሩኝ ነበር።
አንድ ቀን ናውኡካ ኢ ሪሊጂያ (ሳይንስ እና ሃይማኖት) የተባለው መጽሔት ጋዜጠኛ ወደ ትምህርት ቤታችን መጣ፤ መንግሥት የሚያዘጋጀው ይህ መጽሔት አምላክ የለሽነትን የሚያበረታታ ነበር። ጋዜጠኛው በአምላክ ላይ ያለንን እምነት ውድቅ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀውን ንግግሩን ሲያቀርብ አስተማሪዎቼ ፊተኛው መደዳ ላይ ቁጭ ብዬ እንዳዳምጥ አደረጉኝ።
ጋዜጠኛው ንግግሩን ሲጨርስ ወደ መድረኩ ጀርባ ወሰዱኝና እንዲያነጋግረኝ ጠየቁት። ሃይማኖቴ ምን እንደሆነ ሲጠይቀኝ ያለአንዳች ማመንታት “የይሖዋ ምሥክር ነኝ” አልኩት። በዚህ ጊዜ ንግግሩን በጥሞና ስላዳመጥኩ ከማመስገን በቀር ሌላ ምንም ሊለኝ አልቻለም። ይህም አስተማሪዎቹን በጣም አበሳጫቸው!
በቤተሰብ ደረጃ በይሖዋ መታመን
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ቤታችን ውስጥ ለማተምና ለማሰራጨት መላው ቤተሰባችን በይሖዋ መታመን አስፈልጎታል። በተጨማሪም አባቴ የወረዳ የበላይ ተመልካች ስለነበር በማዕከላዊ ዩክሬን የሚገኙ ጉባኤዎችንና ቡድኖችን ይጎበኝ ነበር።
የካቲት 1978 ታናሽ ወንድማችን ፓቭሊክ ከመወለዱ ልክ ከሁለት ቀን በፊት የሆነውን ነገር አልረሳውም፤ አንድ ቀን ከሰዓት ከትምህርት ቤት ስመለስ ቤታችንን ተተረማምሶ አገኘሁት። ፖሊሶች ቤታችንን በርብረው ጽሑፎቻችንን ሁሉ ይዘው ሄደው ነበር።
ቤታችን በተበረበረ ማግስት ትምህርት ቤት ስንሄድ አስተማሪዎቹ እኔንና ታናሽ ወንድሜን ሚክሃይሎን ያዩበት መንገድ የሚያስቅ ነበር፤ የአሜሪካ ሰላዮች ልጆች እንደሆንን በማሰብ ፍጥጥ ብለው ነበር ያዩን። በጊዜ ሂደት ግን ብዙዎቹ አስተማሪዎች እንደተሳሳቱ ተገነዘቡ። እንዲያውም አብረውኝ ከተማሩ ልጆች መካከል አንዳንዶቹ በኋላ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል!
በ1981 ቤታችን በድጋሚ ተበረበረ። በወቅቱ ገና 18 ዓመት ባይሆነኝም ከአባቴና ከአያቴ ጋር ወደ አቃቤ ሕጉ ቢሮ ተጠራሁ። ዋናው መርማሪ እስር ቤት እንደሚያስገባኝ በመዛት ሊያስፈራራኝ ሞከረ። መደበኛ ልብስ የለበሰ ሌላ ሰውዬ ደግሞ ከተባበርኩ የወደፊት ሕይወቴ ጥሩ እንደሚሆን ቃል ገባልኝ። አንዱ እያስፈራራኝ ሌላው ደግሞ እያግባባኝ ነበር ማለት ይቻላል። ሰዎቹ ሐሳቤን ለማስቀየር በሚያደርጉት ጥረት አባቴ፣ አያቴና አጎቶቼም ታስረው እንደነበር ነገሩኝ። ፖሊሶቹ ያልተገነዘቡት ነገር ግን እንዲህ ሲሉኝ እኔም ብታሰር እንኳ በይሖዋ እርዳታ ልጸና እንደምችል እያረጋገጡልኝ ነበር።—ፊልጵስዩስ 4:13
ከመታሰሬ ከጥቂት ጊዜ በፊት የተነሳነው ፎቶ። ከግራ ወደ ቀኝ፦ አባቴ፣ እኔ፣ ፓቭሊክ፣ እናቴ እና ሚክሃይሎ
እስር ቤት ውስጥ በይሖዋ መታመን
አሥራ ስምንት ዓመት በሞላኝ ቀን ማግስት ለውትድርና አገልግሎት እንድመዘገብ ጥሪ ደረሰኝ። የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኔ ወደ ማረፊያ ቤት ተወሰድኩ። ሰማንያ አምስት ሰዎች አብረው የታሰሩበት ሰፊ ክፍል ውስጥ አስገቡኝ፤ በክፍሉ ውስጥ ያሉት አልጋዎች 34 ብቻ ስለሆኑ የምንተኛው በየተራ ነበር። ገላችንን እንድንታጠብ የሚፈቀድልን ደግሞ በሳምንት አንዴ ብቻ ነው።
ወደ ክፍሉ ገብቼ በሩ ጓ ብሎ ሲዘጋ የሁሉም እስረኞች ዓይን እኔ ላይ አረፈ። አንዱ ጥግ ላይ የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ ምን ወንጀል ፈጽሜ እንደታሰርኩ ጠየቁኝ። ፍርሃት ቢሰማኝም የአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎም ምንም ጉዳት ያልደረሰበትን የዳንኤልን ታሪክ አስታወስኩ። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንድታመንና እንድረጋጋ ረድቶኛል።—ኢሳይያስ 30:15፤ ዳንኤል 6:21, 22
ራት ከበላን በኋላ ከእስረኞቹ አንዱ ስለ እምነቴ ብዙ ጥያቄዎችን ይጠይቀኝ ጀመር። ቀስ በቀስ ሌሎች እስረኞችም ውይይታችንን ማዳመጥ ስለጀመሩ በመላው ክፍል ውስጥ ጸጥታ ሰፈነ። ለአራት ወይም ለአምስት ሰዓት ገደማ፣ ስለማምንባቸው ነገሮች ሳብራራላቸው ቆየሁ። ይሖዋ በዚህ መንገድ ስለረዳኝ ልቤ በአመስጋኝነት ተሞላ!
ፍርድ ቤት ከመቅረቤ በፊት፣ ለማምንባቸው ነገሮች ጥብቅና ለመቆም የሚያስችል ጥበብና ድፍረት እንዲሰጠኝ ይሖዋን ለመንኩት። አቃቤ ሕጉ ‘በአምላክ አምናለሁ’ የምለው የውትድርና አገልግሎት ላለመስጠት እንደሆነ ፍርድ ቤቱን ለማሳመን ሞከረ። እኔም ወታደር መሆኔ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀውን አካል እንደሚያሳዝን ለማስረዳት ጥረት አደረግኩ። ያም ሆኖ በ1982 በጉልበት ሥራ ካምፕ ውስጥ ለሁለት ዓመት እንድታሰር ተፈረደብኝ።
በጉልበት ሥራ ካምፑ ውስጥ ሌሎች አምስት የይሖዋ ምሥክሮችን በማግኘቴ ተደሰትኩ። ማውራት የምንችለው ለአጭር ጊዜ፣ ምናልባትም ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ቢሆንም በዚያች ጊዜ ውስጥ ሁሌም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ እንወያያለን። ማናችንም መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖረንም ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን ሲጽፉልን በደብዳቤያቸው ላይ በአብዛኛው ጥቅሶችን ያካትቱ ነበር። አንዳንዴ በዓለማዊ ጽሑፎች ላይ ጭምር ጥቅሶችን እናገኛለን!
ድንገተኛ አደጋ ባጋጠመኝ ወቅት በይሖዋ መታመን
በ1983 እስር ቤት ውስጥ እየሠራሁ ሳለ ክሬን ላይ የተንጠለጠለ ሁለት ቶን (2,000 ኪ.ግ.) ገደማ የሚመዝን ቆርቆሮ ድንገት ወደቀ። ቆርቆሮው ከኋላዬ ሲመታኝ መሬት ላይ ተዘረርኩ፤ ከዚያም ክብደቱ ግራ እግሬን ጨፈለቀው።
የሚሰማኝን ከባድ ሥቃይ ለመቋቋም ብርታት እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። የእስር ቤቱ ነርስ ጮክ ብዬ ብሳደብ ሕመሙ ቀለል እንደሚልልኝ ነገረችኝ፤ እኔ ግን መዝሙር መዘመር ጀመርኩ።
ሆስፒታል ለመድረስ በጭነት መኪና፣ በሞተር ጀልባና በአምቡላንስ መጓዝ ነበረብኝ። ስድስት ሰዓት በፈጀው ጉዞ ላይ ብዙ ደም ፈሰሰኝ። ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልገኝ እርግጠኛ ነበርኩ። ስለዚህ ይሖዋ ለሐኪሞቹ ጥበብ እንዲሰጣቸውና ከደም ጋር በተያያዘ ያለኝን ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም እንዲያከብሩልኝ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። የማምንበትን ነገር ለሐኪሙ ስነግረው ሊሰማኝ ፈቃደኛ አልሆነም። ግን ውሳኔዬን እንዲያከብርልኝ ለመንኩት። ያለደም የሚሰጠኝ ሕክምና የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን ኃላፊነቱን እኔ እንደምወስድ ነገርኩት። በመጨረሻም ያለደም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ሲስማማ ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ። ያም ሆኖ የግራ እግሬ የተወሰነው ክፍል መቆረጡ ግድ ሆነ።
ከቀዶ ሕክምናው በኋላ በጣም ተዳክሜ ነበር። ለተወሰኑ ሳምንታት በሕይወትና በሞት መካከል ነበርኩ። አንድ ቀን ከሰዓት አንዲት ነርስ ቶሎ ማገገም እንድችል ልዩ ምግብ እንደሚሰጠኝና አቅራቢያዬ ባለ ማቀዝቀዣ ውስጥ እንደሚቀመጥልኝ ነገረችኝ። ይህ ምግብ እስር ቤት ብሆን ከሚሰጠኝ ምግብ የበለጠ ገንቢ ነው። በየዕለቱ አንድ ማንኪያ ማር፣ ትኩስ እንቁላልና ቁራጭ የገበታ ቅቤ እንደሚሰጠኝ ተነገረኝ። ወላጆቼ አደጋ እንደደረሰብኝ ከሰሙ በኋላ እነዚህን የምግብ ዓይነቶች እንዳገኝ ዝግጅት አድርገውልኝ ነበር። ሆኖም ዕቃ እንድትቀበል የተመደበችው ወታደር ምግቦቹን የተቀበለችው አንዴ ብቻ ነው።
ግን የይሖዋ እጅ አጭር አይደለም። (ኢሳይያስ 59:1) ነርሶቹ ቁስሌን ካጸዱልኝ በኋላ ለራሳቸው ያመጡትን ምግብ ያካፍሉኝ ነበር። በተጨማሪም ማቀዝቀዣ ውስጥ የሚቀመጥልኝ ምግብ ሲያልቅ ይተኩልኛል። ይህ አጋጣሚ ከማሰሮዋ ዘይት ስላላለቀባት መበለት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ያስታውሰኛል።—1 ነገሥት 17:14-16
ቀስ በቀስ ማገገም ጀመርኩ። ቤተሰቦቼና ወዳጆቼ የላኩልኝ 107 ደብዳቤዎች ትልቅ የመጽናናትና የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል፤ ደግሞም ለሁሉም ደብዳቤዎች ምላሽ ሰጥቻለሁ። በሌላ እስር ቤት ከታሰሩ ወንድሞች ጭምር መልእክት ይደርሰኝ ነበር!
ሁለት ወር ሙሉ ሳልታጠብ ከቆየሁ በኋላ በመጨረሻ ገላዬን መታጠብ ቻልኩ! ወደ እስር ቤቱ የጉልበት ሥራ ካምፕ ተመልሼ እዚያ ያሉትን ወንድሞቼን ድጋሚ የማገኝበትን ጊዜ መናፈቅም ጀመርኩ።
የሆስፒታል መውጫ ሰነዶቼን እያዘጋጀ የነበረው ሐኪም ወደ ቢሮው ጠራኝና ስለ እምነቴ ብዙ ጥያቄዎችን ጠየቀኝ። በመጨረሻም ጠንካራ ሆኜ በእምነቴ እንድጸና ተመኘልኝ። እነዚህን ቃላት የወታደር ዩኒፎርም ከለበሰ ሰው መስማቴ አስገረመኝ!
ሚያዝያ 1984 ፍርድ ቤቱ የአመክሮ ጥያቄዬን በሰማበት ወቅት “የጦር ሠራዊቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ነህ?” የሚል ጥያቄ ቀረበልኝ። አንድ እግሬን በማጣቴ ያለክራንች መንቀሳቀስ ስለማልችል ይህን ጥያቄ ማንሳት ትርጉም እንደሌለው ገለጽኩ። በኋላ ላይ “ሁለት እግር ቢኖርህስ ኖሮ?” ብለው ሌላ ጥያቄ ጠየቁኝ። እኔም ሁለት እግር ቢኖረኝም እንኳ ፈቃደኛ እንደማልሆንና ምንጊዜም ለአምላኬ ታማኝ መሆን እንደምፈልግ ነገርኳቸው። በዚህ ጊዜ የተፈረደብኝን ሙሉ የእስራት ጊዜ እስክጨርስ ድረስ ከእስር ቤት እንድወጣ እንደማይፈቅዱልኝ ገለጹልኝ። ያም ሆኖ የእስር ጊዜዬ ከማብቃቱ ከሁለት ወር ከ12 ቀን በፊት ነፃ ተለቀቅኩ።
ከጉልበት ሥራ ካምፕ ከተለቀቅኩ በኋላ ከሚክሃይሎ ጋር የተነሳነው ፎቶ፤ በስተ ቀኝ ያለው እሱ ነው
ከእስር ከተፈታሁ በኋላ በይሖዋ መታመን
ከእስር ቤት ከወጣሁ ከአንድ ዓመት በኋላ አርቴፊሻል እግር ተሠራልኝ። ሁሌ ጠዋት ጠዋት ይህን እግር ለማድረግ አንድ ሰዓት ይፈጅብኛል። በአርቴፊሻል እግር መንቀሳቀስ በተለይ ክረምት ላይ በጣም ከባድ ነው፤ ምክንያቱም ባልተቆረጠው የእግሬ ክፍል ውስጥ ደም በአግባቡ ስለማይዘዋወር እግሬ በቀላሉ አይሞቅም። ከ19 ዓመቴ ጀምሮ ሮጬ አላውቅም፤ በአዲሱ ዓለም ግን እንደ ልቤ ለመሮጥ እናፍቃለሁ።—ኢሳይያስ 35:6
የሠርጋችን ቀን
ብዙ አሠሪዎች የአካል ጉዳተኛ የሆነ ሰው መቅጠር ስለማይፈልጉ ሥራ ለማግኘት ብዙ ተቸግሬአለሁ። ሆኖም የምንቀሳቀሰው በአርቴፊሻል እግር ቢሆንም ቁጭ ተብሎ የሚሠራ ሥራ ኖሮኝ አያውቅም። ለተወሰነ ጊዜ ያህል መካኒክ ነበርኩ። በኋላም የግንባታ ሥራ ሠርቻለሁ።
በ1986 ስቪትላና የተባለች ደስ የምትል እህት አገባሁ። የስቪትላና ቤተሰቦችም ልክ እንደ እኔ ቤተሰቦች እስከ ሦስተኛ ትውልድ ድረስ የይሖዋ ምሥክር ናቸው። ስቪትላና መጠናናት በጀመርንበት ወቅት በትዳራችን ውስጥ ሁሌም ይሖዋን ለማስቀደም በመስማማታችን ምን ያህል ደስተኛ እንደሆነች በተደጋጋሚ ትናገራለች።
ልጆቻችን ኦሊያ እና ቮሎዲያ የምንኖርበትን አሮጌ ቤት ሳድስ ያግዙኝ ስለነበር የግንባታ ሙያ ተምረዋል። በዚህም የተነሳ ዕድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ በስብሰባ አዳራሽ የግንባታ ፕሮጀክቶች በደስታ መካፈል ጀመሩ። በተጨማሪም የዘወትር አቅኚ ሆኑ። በአሁኑ ጊዜ ኦሊያ የግንባታ አገልጋይ፣ ቮሎዲያ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌ ሆነው እያገለገሉ ነው።
የልጃችን ባል ኦሌግ፤ ልጃችን ኦሊያ፤ ስቪትላና፤ እኔ፤ የልጃችን ሚስት አና እንዲሁም ልጃችን ቮሎዲያ
ስቪትላና ሁሌም ከጎኔ ሆና ስለምትደግፈኝ የጉባኤ ኃላፊነቶቼን መወጣት ችያለሁ። በ1990ዎቹ በዩክሬን የነበሩት አብዛኞቹ ጉባኤዎች ከ200 በላይ አስፋፊዎች ቢኖሯቸውም ያሏቸው ሽማግሌዎች አንድ ወይም ሁለት ብቻ ነበሩ። በወር አንዴ ደግሞ ቅዳሜ እና እሁድን የማሳልፈው በማዕከላዊ ዩክሬን ላሉ ጉባኤዎች ጽሑፎችን በማድረስ ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በይሖዋ መታመን
በ2022 እኔና ስቪትላና፣ ክሪቪ ሪህን ለቀን ለመሄድ ወሰንን። አሁን በኦስትሪያ ባለ ጉባኤ ውስጥ እያገለገልን ነው።
ከባድ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ደስታቸውን ጠብቀው መቀጠል ከቻሉ የይሖዋ ምሥክር ዘመዶቼ ምሳሌ ገና ከልጅነቴ ብዙ ተምሬአለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችንን በደንብ እንድናውቅና ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት ይረዳናል። (ያዕቆብ 4:8) ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው ይህ ወዳጅነት ነው። ባለፍኩባቸው ከባድ ሁኔታዎች ውስጥ ለይሖዋ የሚገባውን ክብር መስጠት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ከስቪትላና ጋር በኦስትሪያ
a ቭላዲሚር ሌኒን የሩሲያ ኮሚኒስት ፓርቲ መሥራችና የሶቪየት ኅብረት የመጀመሪያ መሪ ነበር።