የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
ወንድሞቻችንንም ሆነ ፕላኔታችንን የሚጠቅሙ አረንጓዴ ፕሮጀክቶች
ሚያዝያ 1, 2025
እኛ የይሖዋ ምሥክሮች በቅርቡ ይሖዋ አምላክ ጣልቃ ገብቶ ፕላኔታችንን ሰዎች እያስከተሉባት ካለው ጥፋት እንደሚታደጋት በሚገባ እናውቃለን። (ራእይ 11:18) እስከዚያው ድረስ ግን ምድራችንን ለመንከባከብ የቻልነውን ጥረት እናደርጋለን። ለምሳሌ፣ ለይሖዋ አምልኮ የሚያገለግሉ ሕንፃዎችን ስንገነባ በአካባቢው ተፈጥሮ ላይ ጉዳት የማያስከትሉ የግንባታ ንድፎችን እንጠቀማለን።
አረንጓዴ ፕሮጀክት የሚባለው ሕንፃዎቻችን በአካባቢው ተፈጥሮ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት በተቻለ መጠን ለመቀነስ የሚደረግ ጥረት ነው። ታዲያ ምን ዓይነት አረንጓዴ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረግን ነው? እነዚህ ፕሮጀክቶች በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ በጥበብ ለመጠቀም ያስቻሉንስ እንዴት ነው?
የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሾችን ለማቀዝቀዝ የሚረዳ መፍትሔ
ሞዛምቢክ ውስጥ በማቶላ የሚገኘው የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ መጀመሪያ ሲገነባ ከጎንና ከጎን ክፍት ሆኖ ጣሪያው ቆርቆሮ የለበሰ ነው። ጣሪያው የፀሐይ ሙቀት ስለሚሰበስብ አዳራሹ በጣም ይሞቃል። በዚያ አካባቢ የሚገኝ አንድ ወንድም እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል፦ “ከሙቀቱ የተነሳ ላብ በላብ እንሆናለን! ወንድሞች ፕሮግራሙ እንዳበቃ ነፋስ ለማግኘት ቶሎ ብለው ወደ ውጭ ይወጣሉ።” ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሙቀት ሳያስቸግራቸው ስብሰባውን መካፈል እንዲችሉ ምን ማሻሻያ ተደረገ?
ለዚህ ችግር፣ አካባቢውን የማይጎዳ ጥሩ መፍትሔ ተገኘለት፦ በነፋስ የሚሠሩ ማራገቢያዎችን መግጠምና ኮርኒስ መሥራት። ኮርኒሱ ቆርቆሮውን አልፎ የሚመጣው የፀሐይ ሙቀት እንዲቀንስ ያደርጋል፤ ማራገቢያዎቹ ደግሞ አየሩ እንዲዘዋወር ያደርጋሉ። ማራገቢያዎቹ በነፋስ ስለሚሠሩ ሌላ የኃይል ምንጭ አያስፈልጋቸውም፤ ነፋስንና ተፈጥሯዊ የሆነውን የአየር እንቅስቃሴ በመጠቀም አዳራሹ ውስጥ ሙቅ አየር እንዳይታመቅ ያደርጋሉ። እነዚህ የነፋስ ማራገቢያዎች እያንዳንዳቸው 50 ዶላር ያወጣሉ።a
በማቶላ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ የሚገኝ በነፋስ የሚሠራ ማራገቢያ
ይህ መፍትሔ በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ያለው አየር ለጤና ተስማሚ እንዲሆን አድርጓል። አየሩ ስለሚንቀሳቀስ በሕንፃው ውስጥ እርጥበትና ሻጋታ አይከማችም። በተጨማሪም ይህ ለውጥ በአዳራሹ ውስጥ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን እንዲቀንስና ኦክስጅን በደንብ እንዲዘዋወር አስችሏል። በውጤቱም ተሰብሳቢዎች በንቃትና በተመቻቸ ሁኔታ ስብሰባውን መከታተል ችለዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አሁን፣ ስብሰባው እንዳለቀ ሮጠን ወደ ውጭ አንወጣም። ከዚህ ይልቅ በምሳ እረፍት ላይ እዚያው አዳራሹ ውስጥ ሆነን ከጓደኞቻችን ጋር እንጨዋወታለን። አዳራሽ ውስጥ ስንቀመጥ ደስ የሚል ትልቅ ዛፍ ሥር እንደተቀመጥን ይሰማናል!”
አሁን ትላልቅ ስብሰባዎች ለወንድሞቻችን ይበልጥ አስደሳች ሆነውላቸዋል
ታዳሽ የኃይል ምንጮችን መጠቀም
በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ሕንፃዎቻችን ላይ የፀሐይ ብርሃንን ተጠቅመው ኃይል የሚያመነጩ መሣሪያዎችን ገጥመናል። እነዚህ መሣሪያዎች በሶላር ፓነሎች አማካኝነት ታዳሽ የኃይል ምንጭ ከሆነው ከፀሐይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫሉ። በመሆኑም ከከሰል ወይም ከነዳጅ የሚመነጭን የኤሌክትሪክ ኃይል የድሮውን ያህል አንጠቀምም። የፀሐይ ብርሃንን ተጠቅሞ ኃይል ማመንጨት፣ ብክለትን የሚቀንስ ከመሆኑም ሌላ በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ ለመቆጠብ ያስችላል።
በ2023 ይህ የኃይል ማመንጫ ዘዴ በስሎቬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ጥቅም ላይ ዋለ። ለሕንፃው ከሚያስፈልገው የኃይል አቅርቦት ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነው የሚሸፈነው በዚህ መንገድ ነው። ይህ የኃይል ማመንጫ ከሚፈለገው በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ካመነጨ የተረፈው ኃይል ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚሰጥበት ዝግጅት ተደርጓል። የኃይል ማመንጫው 360,000 ዶላር ወጥቶበታል። ሆኖም ቅርንጫፍ ቢሮው ለኤሌክትሪክ የሚያወጣው ወጪ ስለቀነሰ በአራት ዓመት ውስጥ ለኃይል ማመንጫው የወጣውን ወጪ መሸፈን ይቻላል።
የስሎቬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ
በ2024 በስሪ ላንካ ቅርንጫፍ ቢሮ ሶላር ፓነሎችንና ትልቅ ባትሪ ገጠምን። ይህ ፕሮጀክት 3 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የፈጀ ሲሆን ይህ የኃይል ማመንጫ ዘዴ 70 በመቶ የሚሆነውን የቅርንጫፍ ቢሮውን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ይሸፍናል። በዚህ መልኩ የተቆጠበው ገንዘብ ለሶላር ፓነሎቹ የወጣውን ወጪ በሦስት ዓመት ውስጥ ለመሸፈን ያስችላል። በዚያው ዓመት በኔዘርላንድስ ቅርንጫፍ ቢሮም ይህን የኃይል ማመንጫ ገጥመን ነበር። ይህ ሥራ 1.1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን 35 በመቶ የሚሆነውን የቅርንጫፍ ቢሮውን የኃይል ፍጆታ ይሸፍናል። ይህን የኃይል ማመንጫ ለመግጠም የወጣውን ወጪ በዘጠኝ ዓመት ውስጥ መሸፈን ይቻላል።
የኔዘርላንድስ ቅርንጫፍ ቢሮ
በሜክሲኮ በሚገኙ አንዳንድ የርቀት የትርጉም ቢሮዎችም ሶላር ፓነሎች ተገጥመዋል። እስቲ አንዱን እንደ ምሳሌ እንጥቀስ፦ በቺዋዋ ግዛት የሚገኘው የታራሁማራ (ማዕከላዊ) የርቀት የትርጉም ቢሮ። በክረምት ወራት ቅዝቃዜው ከዜሮ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች ሊወርድ ይችላል፤ በበጋ ደግሞ ሙቀቱ ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚበልጥበት ጊዜ አለ! ያም ሆኖ በአገሪቱ ኤሌክትሪክ ውድ ስለሆነ ወንድሞች ማሞቂያና ማቀዝቀዣ አይጠቀሙም። በርቀት የትርጉም ቢሮው የሚያገለግል ጆናታን የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ክረምት ላይ ብርድ ልብስና ወፋፍራም ልብሶችን እንለብሳለን፤ በጋ ላይ ደግሞ መስኮት እንከፍታለን።”
በ2024 በዚህ የርቀት የትርጉም ቢሮ የፀሐይ ብርሃንን የሚጠቀም የኃይል ማመንጫ ተገጠመ። ይህን የኃይል ማመንጫ ለመግጠም 21,480 ዶላር ወጥቷል፤ ሆኖም የሚቆጠበው ገንዘብ ይህን ወጪ በአምስት ዓመት ውስጥ ለመሸፈን ያስችላል። አሁን ወንድሞቻችን ማሞቂያውንና ማቀዝቀዣውን ከበፊቱ ይበልጥ በነፃነት መጠቀም ይችላሉ። ጆናታን እንዲህ ብሏል፦ “በሥራችን ይበልጥ ደስተኛና ውጤታማ ሆነናል። የድርጅቱ ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነና ይህ ዘዴ አካባቢውን እንደማይበክል ማወቃችንም ያስደስተናል።”
የታራሁማራ (ማዕከላዊ) የትርጉም ቡድን አሁን ይበልጥ አመቺ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየሠራ ነው
የዝናብ ውኃን ማጠራቀም
በአፍሪካ አንዳንድ የስብሰባ አዳራሾች አስተማማኝ የውኃ አቅርቦት የላቸውም። በመሆኑም ወንድሞች በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ ወደ ስብሰባ አዳራሻቸው ውኃ ተሸክመው ማምጣት ያስፈልጋቸዋል። በሌሎች የስብሰባ አዳራሾች ደግሞ ወንድሞች ውኃ በመኪና አስጭነው ያመጣሉ፤ ሆኖም ይህ አማራጭ ውድ ከመሆኑም ሌላ አካባቢን ይበክላል።
ወንድሞቻችን ውኃ በቀላሉ እንዲያገኙ ሲባል በአፍሪካ ባሉ በርካታ የስብሰባ አዳራሾች አሸንዳዎችንና ትላልቅ የውኃ ማጠራቀሚያዎችን አስገብተናል። ሆኖም እነዚህ ነገሮች ከመገጠማቸው በፊት ወንድሞች የስብሰባ አዳራሹ ባለበት አካባቢ ያለውን የአየር ጠባይ እንዲያጠኑ ተደረገ፤ ይህም ለእያንዳንዱ አዳራሽ ውጤታማ የሆነ ንድፍ ለማውጣት አስችሏል። አሸንዳዎቹንና የውኃ ማጠራቀሚያዎቹን ለመግጠም ከ600 እስከ 3,000 ዶላር ድረስ ያስፈልጋል። ሆኖም እንዲህ ከተደረገ በኋላ ወንድሞች ለውኃ መክፈል ስለማያስፈልጋቸው የስብሰባ አዳራሹ ወጪ በአብዛኛው ይቀንሳል።
በፑትሃዲትጃባ፣ ደቡብ አፍሪካ ባለ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የተገጠመ የውኃ ማጠራቀሚያ
የዝናብ ውኃን ለማጠራቀም የተደረገው ጥረት ወንድሞቻችንን ጠቅሟል። በሞዛምቢክ የምትኖር ኖኤምያ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ቀደም ሲል ለስብሰባ አዳራሹ ውኃ ለመቅዳት በጣም ረጅም ርቀት እንጓዝ ነበር። አዳራሽ የምንደርሰው በጣም ደክሞንና ዝለን ነው። በዚያ ላይ የውኃ እጥረት ስላለ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ እንቸገር ነበር። አሁን ግን ሁሉም ሰው እጁን መታጠብ ይችላል። አዳራሽ የምንደርሰው ደክሞን ስላልሆነ ስብሰባውን በንቃት መከታተል እንችላለን። ከልብ እናመሰግናለን!”
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ አንዲት እህትና ልጇ የተጠራቀመ የዝናብ ውኃ ሲጠቀሙ
ለእነዚህ አረንጓዴ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነው እንዴት ነው? ለዓለም አቀፉ ሥራ በሚደረገው መዋጮ ነው፤ እንዲህ ካሉት መዋጮዎች አብዛኞቹ የሚደረጉት donate.jw.org ላይ በተጠቀሱት የተለያዩ አማራጮች አማካኝነት ነው። በልግስና ለምታደርጉት መዋጮ ከልብ እናመሰግናለን!
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሰው ዶላር የሚያመለክተው የአሜሪካን ዶላር ነው።