የግርጌ ማስታወሻ
b በሙት ባሕር የተገኙ ጥንታዊ ቅጂዎች በሙሉ አሁን ካሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ ማለት አይደለም። አንዳንዶቹ ብዙ የይዘት ለውጥ ይታይባቸዋል። ይሁን እንጂ የጥቅሱ መሠረታዊ ትርጉም ተዛብቷል ማለት አይደለም። በአሜሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ፓትሪክ ደብልዩ ሰኬሃን እንደገለጹት አብዛኛዎቹ ለውጦች “[የመጽሐፍ ቅዱሱ ጥቅስ] መሠረተ ሐሳቡን ሳይለቅ ያንኑ መልእክት ሰፋ አድርጎ ለመግለጽ የተደረጉ ለውጦች ናቸው። . . . ከዚህ ሥራ በስተጀርባ የተንጸባረቀው እንደ ቅዱስ ተደርጎ ለሚታየው ጽሑፍ ከፍተኛ አክብሮታዊ ፍርሃት የማሳየትና (እንደ እኛ አገላለጽ) መጽሐፍ ቅዱስን በመጽሐፍ ቅዱስ የማብራራት ዝንባሌ ነው።”8
ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “እርግጠኛ መሆን የማይቻልባቸው ነገሮች መኖራቸው ባይካድም ዛሬ በእጃችን ላይ ያለው ጽሑፍ በጥቅሉ ወደ ሦስት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት የኖሩትን (አንዳንዶቹ) ጸሐፊዎች ትክክለኛ ቃላት በበቂ ሁኔታ የሚያንጸባርቁ መሆናቸው የማይታበል ሐቅ ነው። በይዘቱ ላይ የተደረጉት በርከት ያሉ ለውጦች ብሉይ ኪዳን የያዘውን መልእክት ጠቃሚነት ይቀንሱብናል የሚል ስጋት ሊያድርብን አይገባም።”9