ልጆችን ለወሲብ መጠቀሚያ ማድረግ ዓለም አቀፍ ችግር ሆኗል
በስዊድን የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ሰብዓዊው ኅብረተሰብ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በሰፊው ባልታወቀ ከፍተኛ መጠንና ባሕርይ ባለውና እጅግ አስደንጋጭ በሆነ በልጆች ላይ በሚፈጸም በደል በመናጥ ላይ ይገኛል። የ130 ብሔራት ተወካዮች ይህን ችግር ለመግታት ምን ማድረግ እንደሚቻል ለመመካከር በስቶክሆልም፣ ስዊድን ልጆችን የወሲባዊ ንግድ መጠቀሚያ ማድረግን የሚከላከል የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጉባኤ አድርገዋል። በስዊድን የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢም በሥፍራው ተገኝቶ ነበር።
ማግዳሊን 14 ዓመት እንደሞላት ሰዎች አታልለው ወስደው በፊሊፒንስ አገር በማኒላ ከተማ በሚገኝ አንድ ቡና ቤት “አስተናጋጅ” ሆና እንድትሠራ አደረጓት። ሥራዋ ግን ወንዶች ደንበኞችን ወደ አንድ ትንሽ ክፍል ከወሰደች በኋላ ልብሷን አወላልቃ ገላዋን ለወንዶቹ ወሲባዊ ፈቃድ ማቅረብ ነበር። በአንድ ምሽት በአማካይ 15 ወንዶችን፣ በቅዳሜ ቀናት ደግሞ እስከ 30 የሚደርሱ ወንዶችን ታስተናግዳለች። አንዳንድ ጊዜ ‘ከዚህ በላይ አልችልም’ ብላ እምቢተኛ ስትሆን አሠሪዋ እንድትቀጥል ያስገድዳታል። አብዛኛውን ጊዜ ደክማና ዝላ እንዲሁም መፈጠሯን እየረገመች ከሌሊቱ በአሥር ሰዓት የዕለቱን ሥራዋን ትጨርሳለች።
ሳሬኡን በካምቦድያ፣ ፕኖም ፔን የሚኖር እናትና አባቱ የሞቱበት የጎዳና ተዳዳሪ ልጅ ነው። ቂጥኝ ይዞት እንደነበረና ከውጭ አገር ዜጎች ጋር ‘ወጥቶ’ እንደነበረ ይታወቃል። መነኩሴ ለነበረ አንድ ሰው እንዲያሳድገው ተሰጠና በሰገነት ላይ በሚገኝ አንድ አነስተኛ ቤት ውስጥ መኖር ጀመረ። ይህ ሰው ግን ወሲባዊ ብልግና ከፈጸመበት በኋላ የውጭ አገር ሰዎች ወሲባዊ ግንኙነት እንዲፈጽሙበት ማቅረብ ጀመረ። ሳሬኡን ይኖርባት የነበረችው አነስተኛ ቤት ስትፈርስ ከአክስቱ ጋር መኖር ቢጀምርም አሁንም በዝሙት አዳሪነት እንዲሠማራ መገደዱ አልቀረም።
እነዚህ በነሐሴ 27, 1996 ልጆችን የወሲባዊ ንግድ መጠቀሚያ ማድረግን ለመከላከል ታቅዶ የተደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤ መፍትሔ ሊያገኝላቸው ከሞከራቸው አሳዛኝ ችግሮች መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው። እንዲህ ያለው ድርጊት ምን ያህል የተስፋፋ ነው? በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ፣ እንዲያውም አንዳንዶች እንደሚሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች እንዲህ ባለው ኑሮ ተጠምደዋል። አንድ ተወካይ እንዲህ በማለት ችግሩን አጠቃለው ገልጸውታል:- “ልጆች እንደ ኢኮኖሚያዊና ወሲባዊ ሸቀጦች ተቆጥረው ይሸጣሉ፣ ይገዛሉ። እንደ ኮንትሮባንድ ዕቃ ከድንበር ወደ ድንበር ይጫናሉ። በዝሙት ቤቶች ውስጥ እስረኛ ሆነው በግድ ከበርካታ ሰዎች ጋር ወሲብ እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ።”
የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ዮራን ፔርሶን ለስብሰባው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ይህን ልጆችን ለወሲብ መጠቀሚያ ማድረግን “ከማንኛውም ዓይነት ወንጀል የበለጠ አሰቃቂ፣ አረመኔያዊና በጣም ዘግናኝ ወንጀል ነው” ብለውታል። አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ “በልጆች ላይ ከሁሉም አቅጣጫ የተሰነዘረ ጥቃት ነው። . . . ፍጹም የሚያሳፍር ብልግና ሲሆን ከማንኛውም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ረገጣ የከፋ ነው” ብለዋል። የልጆች ወሲባዊ መጠቀሚያ መሆን ያለው ባሕርይ፣ ስፋት፣ ውጤትና ምክንያት በተመረመረበት በዚህ ጉባኤ ላይ እነዚህን የመሰሉ በርካታ የምሬትና የሐዘኔታ መግለጫዎች ከመድረኩ ተደምጠዋል።
አንድ ምንጭ እንደጠቆመው “የችግሩ ስፋት መላውን ዓለም ያጠቃለለ ሲሆን የሚያስከትለው ጉዳት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ነው።” ሌላ ምንጭ ደግሞ “በየዓመቱ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ልጆች ወደ ባለ ብዙ ቢልዮን ዶላሩ የወሲብ ንግድ ዓለም እንደሚገቡ ይታመናል” ብሏል። ታዲያ ይህ ምን ውጤት ያስከትላል? “ልጆች ለራሳቸው ያላቸው ግምት፣ ማንነታቸውና ጨዋነታቸው ይበላሻል። ሰውን የማመን ችሎታቸው ይሟጠጣል። አካላዊና ስሜታዊ ጤንነታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል፣ መብታቸው ይደፈራል፣ መላው የወደፊት ሕይወታቸው ይበላሻል።”
አንዳንድ ምክንያቶች
ይህ ችግር እንዲህ በእጅጉ እንዲስፋፋ ምክንያት የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው? አንዳንድ ልጆች “በዝሙት አዳሪነት የሚሰማሩት በሁኔታዎች አስገዳጅነት ማለትም የጎዳና ላይ ኑሯቸውን ለማሸነፍ፣ ቤተሰባቸውን በገንዘብ ለመደጎም ወይም ልብስና አንዳንድ ነገሮችን መግዣ ለማግኘት ሲሉ ነው። ሌሎቹ ደግሞ መገናኛ ብዙሐን በሚያቀርቧቸው የማስታወቂያዎች ውርጅብኝ ተታልለው ወደዚህ ኑሮ ይገባሉ።” ተጠልፈው ከተወሰዱ በኋላ በዝሙት አዳሪነት እንዲሰማሩ የሚገደዱም አሉ። በሁሉም አካባቢዎች የጥሩ ሥነ ምግባር እሴቶች በከፍተኛ ፍጥነት እየተሸረሸሩ መሄዳቸውና አጠቃላይ የሆነ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት መስፋፋቱ ከምክንያቶቹ መካከል እንደሆኑ ተጠቅሷል።
የወላጆቻቸውን ዱላ ለመሸሽ ወይም የቅርብ ዘመዳቸው በጾታ ስላስነወራቸው ከቤታቸው ወጥተው የጎዳና ተዳዳሪ መሆናቸው ለዝሙት አዳሪነት ያጋለጣቸው ወንዶችና ሴቶች ልጆች በርካታ ናቸው። የጎዳና ተዳዳሪ ከሆኑ በኋላ በልጆች ላይ ወሲብ መፈጸም በሚያስደስታቸው ሰዎች፣ ሌላው ቀርቶ በአንዳንድ ፖሊሶች የመደፈር አደጋ ይገጥማቸዋል። ይህንኑ ችግር በማስመልከት የቀረበ ኪድስ ፎር ሃየር የተባለ ሪፖርት ካቲያ ስለተባለች የስድስት ዓመት ብራዚላዊት ሕፃን ይገልጻል። አንድ ፖሊስ ይይዛትና አስገድዶ የብልግና ድርጊት ከፈጸመባት በኋላ ለአለቃው ብትናገርበት ቤተሰቦቿን እንደሚገድልባት በመናገር ያስፈራራታል። በማግስቱ ሌሎች አምስት ወንዶችን ይዞ ይመጣና ሁሉም ለፖሊሱ እንዳደረገችው እንድታደርግላቸው ይጠይቋታል።
አንድ የስዊድን የልጆች እንባ ጠባቂ ተቋም ለጉባኤተኞቹ “ልጆች በዝሙት አዳሪነት እንዲሰማሩ የሚያስገድዱት ምክንያቶች ምን እንደሆኑ ጥናት ሲደረግ [የወሲብ] ቱሪዝም ዋነኛው ምክንያት ሆኖ እንደተገኘ ጥርጥር የለውም” ብሏል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው “የልጆች ዝሙት አዳሪነት ባለፉት አሥር ዓመታት ለማመን በሚያዳግት መጠን እንዲስፋፋ ምክንያት የሆነው የቱሪዝም መስፋፋት ነው። የልጆች ዝሙት አዳሪነት ታዳጊ አገሮች ከሚያቀርቧቸው የቱሪስት መስህቦች አንዱ ሆኗል። ከአውሮፓ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከጃፖንና ከሌሎች አገሮች የሚነሱ “የወሲብ ጉዞዎች” በመላው ዓለም ዝሙት አዳሪ ልጆች በጣም ተፈላጊ እንዲሆኑ አድርጓል። አንድ የአውሮፓ አየር መንገድ የሚያደርገውን የወሲብ ጉዞ ለማስተዋወቅ አንዲት ሕፃን ልጅ የጾታ ስሜት በሚያነሳሳ መንገድ ተስላ በሚያሳይ የካርቱን ሥዕል ተጠቅሟል። የጉዞ ወኪሎች በየዓመቱ በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች የወሲብ ጉዞዎች ያዘጋጃሉ።
የልጆች ወሲብ ኢንዱስትሪ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት በመላው ዓለም እንዲታወቅ መደረጉ ለችግሩ መስፋፋት ከሚጠቀሱት በርካታ ምክንያቶች አንዱ ሆኗል። ኢንተርኔትና ሌሎች ተመሳሳይ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂዎች ዋነኛ የወሲብ ፊልሞችና ሥዕሎች ማስፋፊያ ሆነዋል። በተጨማሪም የቪዲዮ መሣሪያዎች ዋጋ አነስተኛ መሆን ልጆች የተሳተፉባቸው የብልግና ፊልሞችን ማዘጋጀት ቀላል እንዲሆን አድርጓል።
በዚህ ተግባር የሚሰማሩት እነማን ናቸው?
በትናንሽ ልጆች ላይ ወሲብ ከሚፈጽሙ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በልጆች ላይ ወሲብ መፈጸም የሚያስደስታቸው ሰዎች ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በእንግሊዝኛ ፒዶፋይልስ ይባላሉ። የስዊድን የልጆች እምባ ጠባቂ እንዳለው ከሆነ “እነዚህ ሰዎች ሸምገል ያሉ፣ የዝናብ ልብስ የለበሱ ወይም ጉልበተኛ መስለው የሚታዩ ወንዳ ወንድ ሰዎች ላይሆኑ ይችላሉ። ዓይነተኛዎቹ ፒዶፋይል በደንብ የተማሩ፣ በመካከለኛ ዕድሜ የሚገኙና አብዛኛውን ጊዜ አስተማሪ፣ ሐኪም፣ የማኅበራዊ ኑሮ ሠራተኛ ወይም ቄስ በመሆናቸው ምክንያት ከልጆች ጋር ብዙ ጊዜ የሚቀራረቡ ሰዎች ናቸው።”
የስዊድን ልዑካን ቡድን ለወሲብ ቱሪስትነት ከኦስትርያ የሄደ ዶክተር ያስነወራትን የ12 ዓመትዋን ፊሊፒናዊት ልጃገረድ ሮዛርዮን ጠቅሷል። የፈጸመባት ጥቃት ለሞት ዳርጓታል።
በጄኔቫ የሚገኘው የዩኒሴፍ (የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት) ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካሮል ቤላሚ ስለዚህች የ12 ዓመት ፊሊፒናዊት የሚከተለውን ብለዋል:- “ይህን የሚዘገንን ድርጊት የሚፈቅዱትና የሚያስፋፉት አብዛኛውን ጊዜ ልጆችን የመጠበቅና የመንከባከብ ግዴታ የተጣለባቸው ሰዎች ናቸው። በሚሰጣቸው ከበሬታና ሥልጣን ተጠቅመው ልጆችን በጾታ የሚያስነውሩ መምህራን፣ የጤና ባለሞያዎች፣ ፖሊሶች፣ የፖለቲካ ሰዎችና ቀሳውስት ናቸው።”
የሃይማኖትም እጅ አለበት
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ በስቶክሆልሙ ጉባኤ ላይ ልጆችን የወሲብ መጠቀሚያ ማድረግ “በጣም አስነዋሪ ወንጀል ከመሆኑም በላይ የሥነ ምግባር እሴቶች እየፈራረሱ በመምጣታቸው የተስፋፋ ችግር ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትዋ በሚፈጽሙት ይህን መሰል ድርጊት ምክንያት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ትገኛለች።
ኒውስዊክ መጽሔት በነሐሴ 16, 1993 እትሙ ላይ “ቀሳውስትና የፆታ ብልግና” በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት እንዲህ ብሏል:- “በዩናይትድ ስቴትስ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ የቀሳውስት ቅሌት አጋጥሟታል። ከ1982 ወዲህ 400 በሚያክሉ ቀሳውስት ላይ ክስ የተመሠረተ ቢሆንም አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች እንደሚሉት 2,500 የሚደርሱ ቀሳውስት ልጆችን ወይም ወጣቶችን አስነውረዋል። . . . ይህን የመሰለው ቅሌት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ካደረሰው የገንዘብ ኪሣራ የሚከፋው በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሐፍረትና ውርደት ማስከተሉ ብቻ ሳይሆን የሥነ ምግባር አቋሟን አጠያያቂ ማድረጉም ነው።” በመላው ዓለም ያሉ ሌሎች ሃይማኖቶችም የሚገኙበት ሁኔታ ከዚህ እምብዛም የማይሻል ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም የወሲባዊ ወንጀሎች አማካሪ የሆኑት ሬይ ዋይር ለስቶክሆልሙ ጉባኤ አንድ ቄስ አስገድዶ ስላስነወራቸው ሁለት ወንድ ልጆች ተናግረዋል። አንደኛው ልጅ በአሁኑ ጊዜ በቀሳውስት የተደፈሩ ልጆችን የሚረዳ ድርጅት በማስተዳደር ላይ ሲሆን ሌላው ልጅ ግን ልጆችን አስገድዶ የሚደፍር ሆኗል።
የቡድሂስት ሃይማኖት ምሁር የሆኑት ታይላንዳዊው ሜታናንዶ ቢኩ የሚከተለውን ሪፖርት አቅርበዋል:- “አንዳንድ የቡድሂስት ሃይማኖት ልማዶች በታይላንድ በተለያየ ደረጃ ለሚፈጸመው የልጆች ወሲባዊ ንግድ ምክንያት ሆነዋል። በታይላንድ በገጠር መንደሮች የሚኖሩ መነኮሳት ለዝሙት አዳሪነት የተሸጡት ልጆች ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ከሚያመጡት ገንዘብ ተጠቃሚ ሆነዋል።”
ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል?
በዩናይትድ ኪንግደም የላይሰስተር ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ጁልያ ኦኮነል ዴቪድሰን ጉባኤው አስነዋሪዎቹ ድርጊታቸውን ትክክል ለማስመሰል የሚያቀርቡትን ምክንያት እንዲዋጋ ጥሪ አቅርበዋል። አስነዋሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ልጆቹ ቀድሞም ቢሆን የተበላሹና የባለጉ ናቸው በማለት በልጆች ምግባረ ብልሹነት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያደርጋሉ። ሌሎቹ ደግሞ ድርጊታቸው በልጁ ላይ ምንም ጉዳት የማያስከትል ከመሆኑም በላይ ጥቅም ያገኝበታል በማለት የተጣመመና ፈጽሞ ውሸት የሆነ ሐሳብ ያቀርባሉ።
ስለ ወሲባዊ ቱሪዝም ሲነጋገር የቆየ አንድ ቡድን በትምህርት ቤቶች በሚሰጥ የትምህርት መርሃ ግብር አማካኝነት መዋጋት እንደሚገባ ሐሳብ አቅርቧል። በተጨማሪም ልጆችን የወሲብ መጠቀሚያ ማድረግን የሚያወግዙ መረጃዎች ለመንገደኞች በሙሉ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት፣ በጉዞ ላይ እንዳሉና መውረጃቸው ላይ ሊሰጥ ይገባል።
አዳዲሶቹን የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች በተመለከተም አንድ የጥናት ቡድን ልጆችን የወሲብ መጠቀሚያ የሚያደርጉ ነገሮችን ለማስወገድ የሚያስችሉ መመሪያዎች ለመንግሥታት መቅረብ እንደሚኖርበት ሐሳብ ሰጥቷል። በዚህ መስክ የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያስተባብር አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት የሚቋቋምበት ሁኔታም ተመክሯል። ሌላ የጥናት ቡድን ደግሞ ከኮምፒዩተር የሚመነጩ የልጆች ወሲባዊ ፊልሞችና ሥዕሎችን መመልከት እንዲሁም ማንኛውንም የልጆች ወሲባዊ ፊልምና ሥዕል ይዞ መገኘት በሁሉም አገሮች በሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል መሆን እንደሚገባው ሐሳብ አቅርቧል።
ወላጆችስ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? መገናኛ ብዙሐን ስላላቸው ሚና ሲመክር የቆየ አንድ የጥናት ቡድን ወላጆች ልጆቻቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስቧል። “ወላጆች ልጆቻቸው ሚዛናቸውን የጠበቁ የመገናኛ ብዙሐን ተከታታዮች እንዲሆኑ መምራት ብቻ ሳይሆን የሚያስከትሉባቸውን ተጽእኖዎች ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ማብራሪያና የመረጃ ምንጭ ማቅረብ፣ እንዲሁም የልጁ የማስተዋል ችሎታ እንዲያድግ ማድረግ አለባቸው” ብሏል።
አንድ የስዊድን ቴሌቪዥን ፕሮግራም ስለጉባኤው ባቀረበው ሪፖርት ወላጆች ልጆቻቸውን በቅርብ የመከታተልና የመጠበቅ እንዲሁም ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ አደጋዎች የማስጠንቀቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስቧል። ይሁን እንጂ የሚከተለውን ምክር አክሎ ሰጥቷል:- “ልጆቻችሁን ‘ሸምገልና ቆሸሽ ካሉ ሰዎች’ ተጠንቀቁ ብቻ ብትሏቸው . . . ጥቃት የሚያደርሱባቸው ቆሸሽ ያለ ልብስ የለበሱና ዝርክርክ የሆኑ ሰዎች ብቻ ይመስሏቸዋል። ይሁን እንጂ ጥሩ ልብስ የለበሱና ጥሩ ቁመና ያላቸው ሰዎችም እንደነዚህ ያሉትን ወንጀሎች ይፈጽማሉ። ስለዚህ ከተለመደው ጨዋነት ውጭ የሆነ ፍላጎት ከሚያሳዩአቸው እንግዳ ሰዎች ሁሉ እንዲጠበቁ አስጠንቅቋቸው።” ከዚህም በላይ ልጆቹ የሚያውቋቸውም ቢሆን እንኳ ተገቢ ያልሆነ የብልግና ባሕርይ የሚያሳዩአቸው ከሆነ ለባለ ሥልጣኖች እንዲናገሩ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው ይገባል።
ብቸኛው መፍትሔ
የስቶክሆልሙ ጉባኤ ልጆች ወሲባዊ መጠቀሚያ እንዲሆኑ የሚያደርጉትን ምክንያቶች እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል መጠቆም አልቻለም። ከምክንያቶቹ መካከል አንዳንዶች በሁሉም አካባቢዎች የጥሩ ሥነ ምግባር እሴቶች መፈራረስ፤ ራስ ወዳድነትና የቁሳዊ ንብረቶች ፍቅር እየጨመረ መሄድ፤ ሰዎችን ከጥቃትና ከበደል ለመጠበቅ ታስበው የወጡ ሕጎች አክባሪ ማጣታቸው፤ ለሌሎች ደህንነት፣ ክብርና ሕይወት ደንታ ቢስ መሆን እየጨመረ መሄዱ፤ የሚፈራርሱ ቤተሰቦች ቁጥር መብዛት፤ በሕዝብ ቁጥር መብዛት፣ በሥራ ማጣት፣ በከተሞች መስፋፋትና ከአገር ወደ አገር በመሰደድ ምክንያት ድህነት እየጨመረ መሄዱ፤ እየተስፋፋ የሚሄደው በውጭ አገር ሰዎችና በስደተኞች ላይ የሚሰነዘር የዘር ጥላቻ፤ እያደር እያደገ የመጣው የጎጂ ዕፆች ምርትና ስርጭት እንዲሁም ሃይማኖታዊ አመለካከቶች፣ ልማዶችና ወጎች እየተበላሹ መሄዳቸው ናቸው።
ልጆች ወሲባዊ መጠቀሚያ መሆናቸውን መስማት በራሱ የሚዘገንን ቢሆንም እንዲህ ዓይነቱ ብልግና መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ለሚያጠኑ ሰዎች በጣም የሚያስደንቅ አይሆንም። ለምን? ምክንያቱም ይህ የምንኖርበት ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ “አስጨናቂ” የሚለው “የመጨረሻ ቀን” ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13) ታዲያ ሥነ ምግባር እያዘቀጠ መሄዱ ያስገርማል?
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ለዓለም ታላላቅ ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ ምን እንደሆነ ይጠቁመናል። ሁሉን የሚችለው አምላክ ከሚያከናውነው የማጽዳት እርምጃ ሌላ መፍትሔ ሊኖር አይችልም። በቅርቡ ጻድቅ ለሆኑት ሥርዓቶቹና ሕጎቹ የማይገዙ ሰዎችን ከምድር ገጽ ላይ በማጥፋት ኃይሉን ይገልጣል። “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና። ኃጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”—ምሳሌ 2:21, 22፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-9
ልጆችን ዝሙት አዳሪ የሚያደርጉና በልጆች ላይ ነውር የሚፈጽሙ ብልሹ ሰዎች ‘ከሚነጠቁት’ መካከል ይሆናሉ። የአምላክ ቃል “ሴሰኞች ቢሆኑ . . . ወይም አመንዝሮች ወይም . . . ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) በተጨማሪም “የርኵሳንም . . . የሴሰኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር” ወይም የዘላለም ጥፋት ነው ይላል።—ራእይ 21:8
አምላክ ምድርን አጽድቶ ፍጹም አዲስ የሆነና ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት ማለትም “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” ያመጣል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ከዚያ በኋላ አምላክ በሚያዘጋጀው በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ በንጹሐን ሰዎች ላይ ነውር የሚፈጽሙ ምግባረ ብልሹና ባለጌ ሰዎች አይኖሩም። ንጹሐን ሰዎችን ‘የሚያስፈራቸው ስለማይኖር’ ጉዳት ይደርስብኛል ብለው ስጋት አያድርባቸውም።—ሚክያስ 4:4
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ከማንኛውም ዓይነት ወንጀል የበለጠ አረመኔያዊና በጣም ዘግናኝ ወንጀል”
—የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በየሳምንቱ ከ10 እስከ 12 ሚልዮን የሚደርሱ ወንዶች ወጣት ዝሙት አዳሪዎችን ይጎበኛሉ።”
—ዚ ኢኮኖሚስት፣ ለንደን
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በታዳጊ አገሮች ለልጆች የወሲብ መጠቀሚያ መሆን ዋነኛ ምክንያት የወሲብ ቱሪዝም ነው
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የወሲብ ቱሪዝም—ለምን?
(ቱሪስቶች በልጆች ላይ ወሲብ የሚፈጽሙባቸው አንዳንድ ምክንያቶች)
(1) የቱሪስቱ ማንነት የማይታወቅ መሆኑ በአገሩ ሳለ ከሚኖርበት ማኅበራዊ ገደቦች ነጻ ያደርገዋል
(2) ቱሪስቶች የአገሩን ቋንቋ ፈጽሞ ስለማያውቁ ወይም አጣርተው ስለማይናገሩ ከልጅ ጋር ለሚፈጽሙት ወሲብ ዋጋ መክፈላቸው ተቀባይነት ያለው ነገር እንደሆነ ወይም ልጆቹን ከድህነት የሚያላቅቅ ጥሩ ተግባር እንደሆነ እንዲያስቡ ሊደረጉና በቀላሉ ሊታለሉ ይችላሉ
(3) አገር ጎብኚዎች የሚኖራቸው የዘረኝነት አስተሳሰብ ከእነርሱ ያነሰ እንደሆነ የሚቆጥሩትን ሰው የወሲብ መጠቀሚያ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል
(4) ቱሪስቶች በታዳጊ አገሮች በቀላል ወጪ ወሲባዊ አገልግሎቶችን ሊገዙ እንደሚችሉ ሲመለከቱ ሀብታሞች እንደሆኑ ይሰማቸዋል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የችግሩ ዓለም አቀፋዊነት
(የሚከተለው አኃዝ የተለያዩ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖችና ሌሎች ድርጅቶች የሰጡት ግምት ነው)
ብራዚል:- ቢያንስ 250,000 ዝሙት አዳሪ ልጆች
ካናዳ:- በሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ልጃገረዶች በዝሙት አዳሪነት ሞያ ተሰማርተው ለተደራጁ የወሲብ ንግድ አራማጆች ገቢ በማስገኘት ላይ ናቸው
ቻይና:- ከ200,000 እስከ 500,000 የሚደርሱ ዝሙት አዳሪ ልጆች አሉ። በቅርብ ዓመታት 5,000 የሚያክሉ ልጆች በአታላዮች ተይዘው ከአገር እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በሚያንማር ለዝሙት ሥራ ተሽጠዋል
ኮሎምቢያ:- በቦጎታ ጎዳናዎች የወሲብ መጠቀሚያ የሚሆኑ ልጆች ቁጥር ባለፉት ሰባት ዓመታት አምስት እጥፍ ጨምሯል
ምሥራቅ አውሮፓ:- 100,000 የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ይገኛሉ። ብዙዎቹ በምዕራብ አውሮፓ ወደሚገኙ የዝሙት ቤቶች ይላካሉ
ሕንድ:- 400,000 የሚያክሉ ልጆች በወሲብ ኢንዱስትሪ ተሰማርተዋል
ሞዛምቢክ:- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስጠባቂ ወታደሮች ልጆችን የወሲብ መጠቀሚያ አድርገዋል በማለት የእርዳታ ድርጅቶች ከስሰዋል
ሚያንማር:- በየዓመቱ 10,000 የሚያክሉ ልጃገረዶችና ሴቶች በታይላንድ ወደሚገኙ ዝሙት ቤቶች ይጫናሉ
ፊሊፒንስ:- 40,000 ልጆች በዝሙት አዳሪነት ተሰማርተዋል
ስሪላንካ:- ከ6 እስከ 14 በሚደርስ የዕድሜ ክልል የሚገኙ 10,000 ልጆች በዝሙት ቤቶች ውስጥ በባርነት ታስረው የሚያገለግሉ ሲሆን ከ10 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 5,000 ልጆች ራሳቸውን ችለው በቱሪስት መዝናኛ ቦታዎች ይሠራሉ
ታይዋን:- 30,000 ልጆች በዝሙት ይተዳደራሉ
ታይላንድ:- 300,000 ልጆች በዝሙት ይተዳደራሉ
ዩናይትድ ስቴትስ:- ከ100,000 የሚበልጡ ልጆች ዝሙት አዳሪዎች እንደሆኑ መንግሥታዊ ምንጮች ያመለክታሉ