የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • yp2 ምዕ. 24 ገጽ 199-207
  • ወላጆቼ የሚጨቃጨቁ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወላጆቼ የሚጨቃጨቁ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?
  • ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ወላጆች መግባባት የሚያቅታቸው ለምንድን ነው?
  • ማድረግ ያለብህ ነገር
  • ማድረግ የሌለብህ ነገር
  • ወላጆቼ ሲጨቃጨቁ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?
    ንቁ!—2007
  • ወላጆቼን ይበልጥ ላውቃቸው የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2009
  • ይህን ያህል መመሪያ የሚበዛብኝ ለምንድን ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • ወላጆችህን የምትመለከታቸው እንዴት ነው?
    ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
ለተጨማሪ መረጃ
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
yp2 ምዕ. 24 ገጽ 199-207

ምዕራፍ 24

ወላጆቼ የሚጨቃጨቁ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

ወላጆችህ በአንተ ፊት ተጨቃጭቀው ያውቃሉ? ከሆነ በስተ ቀኝ ከተዘረዘሩት መካከል ብዙ ጊዜ የሚያጨቃጭቃቸው ጉዳይ የትኛው ነው?

□ ገንዘብ

□ የቤት ውስጥ ሥራዎች

□ ዘመዶች

□ አንተ

የወላጆችህ መጨቃጨቅ የሚፈጥርብህን ስሜት በተመለከተ ልትነግራቸው የምትፈልገው ነገር አለ? ሐሳብህን ከታች ጻፍ።

․․․․․

በወላጆችህ መካከል የሚፈጠረው ጭቅጭቅ በአንተ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ደግሞም ወላጆችህን ስለምትወዳቸውና የሚያስፈልጉህን ነገሮች የሚያሟሉልህ እነሱ ስለሆኑ እርስ በርስ ሲጨቃጨቁ ማየትህ ሊያስጨንቅህ ይችላል። ማሪ የተባለች ወጣት በተናገረችው ሐሳብ ትስማማ ይሆናል፤ “ወላጆቼ እርስ በርስ እንደማይከባበሩ እየተሰማኝ እነሱን ማክበር ይከብደኛል” ብላለች።

ወላጆችህ ሲነታረኩ መመልከትህ አንድ አሳዛኝ እውነታ እንድትገነዘብ ያደርግሃል፦ ወላጆችህ የምታስበውን ያህል ፍጹማን አይደሉም። ይህ ሐቅ ዱብ ዕዳ ሊሆንብህና ስጋት እንዲያድርብህ ሊያደርግህ ይችላል። የወላጆችህ ጭቅጭቅ የማያባራ ወይም የከረረ ከሆነ ትዳራቸው በቋፍ ላይ እንዳለ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ማሪ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ሲጨቃጨቁ ስሰማ መፋታታቸው እንደማይቀርና እኔም ከማንኛቸው ጋር እንደምኖር መምረጥ እንደሚኖርብኝ አስባለሁ። ከዚህም ሌላ ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር እንዳልለያይ እፈራለሁ።”

ወላጆች መግባባት የሚያቅታቸው ለምንድን ነው? መነታረክ በሚጀምሩበት ጊዜስ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ወላጆች መግባባት የሚያቅታቸው ለምንድን ነው?

በጥቅሉ ሲታይ ወላጆችህ ‘እርስ በርስ በፍቅር ተቻችለው እየኖሩ’ ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 4:2) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” ይላል። (ሮም 3:23) ወላጆችህ ፍጹማን አይደሉም። በመሆኑም አንዳቸው በሌላው ሲበሳጩና ሁኔታው እየተባባሰ ሄዶ አንዳንድ ጊዜ ሲጨቃጨቁ ብትመለከት ሊያስገርምህ አይገባም።

በተጨማሪም የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ ውስጥ እንደሆነ አስታውስ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) የቤተሰቡን ጉሮሮ ለመድፈንና የቤት ወጪዎችን ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት እንዲሁም በሥራ ቦታ የሚያጋጥመው ውጥረት አንድ ላይ ተዳምረው በትዳር ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራሉ። ከዚህም በላይ ሁለቱም ወላጆችህ ሰብዓዊ ሥራ ካላቸው አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማን ያከናውን የሚለው ጉዳይ አለመግባባት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።

ወላጆችህ በአንዳንድ ጉዳዮች አልተስማሙም ማለት ትዳራቸው አበቃለት ማለት አይደለም። ምንም እንኳ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም አሁንም መዋደዳቸው አይቀርም።

ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ከቅርብ ጓደኞችህ ጋር አንድ ፊልም ከተመለከታችሁ በኋላ ስለ ፊልሙ የሰጣችሁት አስተያየት የተለያየበት ጊዜ የለም? ይህ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው። በጣም የሚቀራረቡ ሰዎችም እንኳ ስለ አንዳንድ ነገሮች ያላቸው አመለካከት ይለያያል። በወላጆችህ መካከል የሚፈጠረው ሁኔታም ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ሁለቱም የቤተሰቡ የገንዘብ አቅም ያሳስባቸው ይሆናል፤ በጀት ማውጣት ላይ ግን ሊለያዩ ይችላሉ። ሁለቱም በቤተሰብ ለመዝናናት ይፈልጉ ይሆናል፤ ይሁንና የሁለቱ የመዝናኛ ምርጫ የተለያየ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ሁለቱም በትምህርትህ ጥሩ ውጤት ስታመጣ ለማየት ይጓጓሉ፤ ሆኖም ይህን ለማሳካት የሚጠቀሙበት ዘዴ የተለያየ ሊሆን ይችላል።

ሊተላለፍ የተፈለገው ነጥብ ይህ ነው፦ ሁለት ሰዎች አንድነት አላቸው ሲባል በሁሉም ነገር አንድ ናቸው ማለት አይደለም። እርስ በርስ የሚዋደዱ ሁለት ሰዎችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን የሚመለከቱበት አቅጣጫ ሊለያይ ይችላል። ያም ሆኖ ወላጆችህ ሲጨቃጨቁ መስማት ሊከብድህ ይችላል። እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም ምን ልታደርግ ትችላለህ? አሊያም ምን ልትል ትችላለህ?

ማድረግ ያለብህ ነገር

አክብራቸው። ወላጆችህ ነጋ ጠባ የሚጨቃጨቁ ከሆነ ብትበሳጭባቸው የሚያስገርም ላይሆን ይችላል። ደግሞም ለአንተ ጥሩ አርዓያ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው እነሱ ናቸው እንጂ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሊሆን አይገባውም። ይሁንና ወላጆችን አለማክበር በቤተሰብ ውስጥ ያለውን ውጥረት ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። ከሁሉ በላይ ልብ ልትለው የሚገባው ነገር ደግሞ፣ ወላጆችህን ማክበርና ለእነሱ መታዘዝ ቀላል በማይሆንበት ጊዜም እንኳ እንዲህ እንድታደርግ ይሖዋ አምላክ የሚጠብቅብህ መሆኑን ነው።​—ዘፀአት 20:12፤ ምሳሌ 30:17

ይሁን እንጂ ወላጆችህ ያልተግባቡበት ነገር አንተን በቀጥታ የሚመለከት ቢሆንስ? ለምሳሌ ያህል፣ አንደኛው ወላጅህ ክርስቲያን ሲሆን ሌላኛው ግን የማያምን ነው እንበል። ክርስቲያን ከሆነው ወላጅህ ጋር በአምልኮ ለመተባበር በምትመርጥበት ጊዜ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። (ማቴዎስ 10:34-37) ምንጊዜም አቋምህን “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” ግለጽ። በዚህ ረገድ ምሳሌ መሆንህ የማያምነው ወላጅህ አንድ ቀን በምግባርህ ተማርኮ ወደ ይሖዋ እንዲሳብ ሊያደርገው ይችላል።​—1 ጴጥሮስ 3:1, 15

ገለልተኛ ሁን። ወላጆችህ አንተን በቀጥታ በማይመለከቱ ጉዳዮች ረገድ ከአንዳቸው ጋር እንድትወግን ጫና ቢያደርጉብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ገለልተኛ አቋም ለመያዝ ጥረት አድርግ። ምናልባትም እናትህንና አባትህን አክብሮት በተሞላበት መንገድ እንዲህ ልትላቸው ትችላለህ፦ “እኔ ሁለታችሁንም እወዳችኋለሁ። እባካችሁ ከአንዳችሁ ጋር እንድወግን አትጠይቁኝ። ይህ እኔን የሚመለከት ሳይሆን ሁለታችሁ ልትፈቱት የሚገባ ጉዳይ ነው።”

ወላጆችህን አነጋግራቸው። የወላጆችህ መነታረክ በአንተ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረብህ እንደሆነ ግለጽላቸው። ሊያዳምጡኝ ይችላሉ የምትልበትን አመቺ ጊዜ ምረጥ፤ ከዚያም የሁለቱ ጭቅጭቅ ምን ያህል እንደሚያበሳጭህና እንደሚያናድድህ አልፎ ተርፎም ስጋት እንደሚፈጥርብህ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ንገራቸው።​—ምሳሌ 15:23፤ ቆላስይስ 4:6

ማድረግ የሌለብህ ነገር

የጋብቻ አማካሪ ለመሆን አትሞክር። አንተ ገና ወጣት በመሆንህ በወላጆችህ መካከል የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስችል ብቃት የለህም። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በአንድ አነስተኛ አውሮፕላን ላይ ተሳፍረሃል እንበል፤ በጉዞ ላይ እያላችሁ የአውሮፕላኑ አብራሪና ረዳቱ ሲጨቃጨቁ ሰማህ። ሁኔታው እንደሚያበሳጭህ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ያለቦታህ በመግባት አብራሪዎቹ አውሮፕላኑን እንዴት ሊያበሩት እንደሚገባ ለመናገር ይባስ ብሎም አውሮፕላኑን ራስህ ለማብረር ብትሞክር ምን ይፈጠራል?

በተመሳሳይም በወላጆችህ ትዳር ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ጣልቃ ገብተህ ለመፍታት መሞከር ትርፉ ነገር ማባባስ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ያለቦታው የሚገባ ወይም “እብሪተኛ ሰው ጠብ ከመፍጠር ውጪ የሚያመጣው ነገር የለም፤ እርስ በርስ በሚመካከሩ ሰዎች ዘንድ ግን ጥበብ አለ።” (ምሳሌ 13:10 NW) ወላጆችህ በመካከላቸው ያለውን ችግር ሊፈቱ የሚችሉበት የተሻለው መንገድ ሁለቱ ለብቻቸው ሆነው መመካከራቸው ነው።​—ምሳሌ 25:9

ንትርኩ ውስጥ አትግባ። የእነሱ መጯጯኽ ሳያንስ ያንተ መደረብ ምን ይሉታል? እርግጥ ነው፣ ወላጆችህ ሲነታረኩ ዝም ብሎ ማየት አላስችል ይልህ ይሆናል፤ ሆኖም በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት የእነሱ እንጂ የአንተ ኃላፊነት አይደለም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመክረው “በሌሎች ሰዎች [የግል] ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት” ጥረት አድርግ። (1 ተሰሎንቄ 4:11) በወላጆችህ መካከል በሚፈጠረው ንትርክ ውስጥ አትግባ።

በወላጆችህ መካከል ክፍፍል አትፍጠር። አንዳንድ ወጣቶች በወላጆቻቸው መካከል ግጭት እንዲፈጠር ያደርጋሉ። እናታቸው አንድ ነገር ስትከለክላቸው አባታቸውን በማባበል ያንን ነገር እንዲፈቅድላቸው ለማድረግ ይሞክራሉ። እንዲህ ያለው ማምታታት የፈለግከውን ለማድረግ በመጠኑም ቢሆን ነፃነት ያስገኝልህ ይሆናል፤ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን በቤተሰባችሁ ውስጥ የተፈጠረው ግጭት ቶሎ መፍትሔ እንዳያገኝ እንቅፋት ይሆናል።

የወላጆችህ ባሕርይ ወደ አንተ እንዲጋባ አትፍቀድ። ፒተር የተባለ አንድ ወጣት፣ ክርስቲያናዊ ባልሆኑ ድርጊቶች መካፈል የጀመረው አስቸጋሪ ባሕርይ የነበረውን አባቱን ለመበቀል ሲል እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ተገነዘበ። ፒተር “እሱን ማበሳጨት ፈልጌ ነበር” ብሏል። “እናቴን ጨምሮ በእኔና በእህቴ ላይ በሚፈጽመው በደል የተነሳ በጣም እጠላው ነበር።” ብዙም ሳይቆይ ግን ፒተር ድርጊቱ ያስከተለውን መዘዝ ለማጨድ ተገደደ። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? መጥፎ ምግባር በቤተሰብህ ውስጥ ያለብህን ችግር ከማባባስ ውጪ የሚያመጣው ጥቅም የለም።​—ገላትያ 6:7

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከተዘረዘሩት ነጥቦች መካከል ይበልጥ ልትሠራበት እንደሚገባ የሚሰማህን በክፍት ቦታው ላይ ጻፍ። ․․․․․

ወላጆችህ እንዳይጨቃጨቁ ማድረግ እንደማትችል ግልጽ ነው። ሆኖም የእነሱ ንትርክ የሚፈጥርብህን ጭንቀት መቋቋም እንድትችል ይሖዋ እንደሚረዳህ እርግጠኛ ሁን።​—ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ 1 ጴጥሮስ 5:7

ከላይ የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ የተቻለህን ያህል ጥረት አድርግ። ውሎ አድሮ ወላጆችህ በጉዳዩ ላይ በቁም ነገር አስበውበት ችግራቸውን ለመፍታት ይነሳሱ ይሆናል። ማን ያውቃል፣ ንትርካቸውን ያቆሙም ይሆናል።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

በነጠላ ወላጅ ማደግ የሚያስከትላቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዴት መቋቋም ትችላለህ?

ቁልፍ ጥቅስ

“ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለው . . . ይሁን።”​—ቆላስይስ 4:6

ጠቃሚ ምክር

የወላጆችህ ጭቅጭቅ የማያባራ ወይም የከረረ ከሆነ እርዳታ እንዲሹ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ሐሳብ አቅርብላቸው።

ይህን ታውቅ ነበር?

በጣም በሚዋደዱ ሰዎች መካከልም እንኳ አለመግባባት የሚፈጠርበት ጊዜ ሊኖር ይችላል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ወላጆቼ መጨቃጨቅ ሲጀምሩ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ወላጆቼ ከአንዳቸው ጋር እንድወግን የሚጫኑኝ ከሆነ እንዲህ እላቸዋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● አንዳንድ ወላጆች የሚጋጩት ለምንድን ነው?

● በወላጆችህ መካከል ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂ እንደሆንክ ሊሰማህ የማይገባው ለምንድን ነው?

● የወላጆችህን ምግባር በመመልከት ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

[በገጽ 201 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወላጆቼ ፍጹማን እንዳልሆኑና እነሱም እንደ እኔ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው መገንዘቤ የእነሱ መጨቃጨቅ የሚፈጥርብኝን ስሜት ለመቋቋም ረድቶኛል።”​—ካቲ

[በገጽ 206 እና 207 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ወላጆቼ ቢለያዩስ?

የወላጆችህ መለያየት ጥልቅ ሐዘን ቢያስከትልብህም ሁኔታውን ተቋቁመህ የጥበብ እርምጃ መውሰድ የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ሐሳቦች ልብ በል፦

● የማይሆን ነገር ተስፋ አታድርግ። ወላጆችህ ሲለያዩ መጀመሪያ የሚመጣልህ ሐሳብ እነሱን ማስታረቅ ሊሆን ይችላል። አን እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፦ “ወላጆቼ ከተለያዩም በኋላ አንዳንድ ጊዜ እኔንና እህቴን ለማዝናናት ይዘውን ይወጡ ነበር። በዚህ ጊዜ እኔና እህቴ ‘ሁለቱ ብቻቸውን እንዲሆኑ ትተናቸው እንሂድ’ እንባባል ነበር። ሆኖም ጥረታችን አልተሳካም። ወላጆቼ እንደገና አብረው የመኖራቸው ጉዳይ አክትሞለት ነበር።”

ምሳሌ 13:12 (የ1954 ትርጉም) “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” ይላል። በተፈጠረው ሁኔታ ከሚገባው በላይ በጭንቀት እንዳትዋጥ የወላጆችህን ድርጊት መቆጣጠር እንደማትችል ማስታወስህ ጠቃሚ ነው። የወላጆችህ ትዳር እንዲፈርስ ያደረግኸው አንተ እንዳልሆንክ ሁሉ በእነሱ መሃል ጣልቃ ገብተህ ችግሩን በማስተካከል ትዳራቸውን መጠገን የመቻልህ አጋጣሚም በጣም ጠባብ ነው።​—ምሳሌ 26:17

● ጥላቻ እንዳያድርብህ ተጠንቀቅ። በአባትህ ወይም በእናትህ አሊያም በሁለቱም ላይ መበሳጨትህና የጥላቻ ስሜት ማሳደርህ በአንተ ላይ ዘላቂ ጉዳት ያስከትላል። ቶም የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ወቅት የተሰማውን ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦ “የአባቴ ሁኔታ በንዴት ቅጥል አድርጎኝ ነበር። ‘ጠላሁት’ ለማለት ቢከብደኝም በጣም ተማርሬበት ነበር። ትቶን ሄዶ ሲያበቃ ለእኛ ያስባል የሚለው ነገር ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም።”

ይሁን እንጂ ለወላጆች መለያየት ምክንያቱ አንደኛው ወገን ብቻ እንደሆነና ሌላኛው ምንም ጥፋት እንደሌለበት ማሰብ ትክክል አይደለም። እውነቱን ለመናገር፣ ወላጆችህ ስለ ትዳራቸው ወይም ለመለያየታቸው ምክንያት ስለሆነው ነገር በዝርዝር ሳይነግሩህ ቀርተው ሊሆን ይችላል፤ ሌላው ቀርቶ እነሱ ራሳቸውም እንኳ ምክንያቱን በውል አልተረዱት ይሆናል። ስለ ጉዳዩ ሁሉንም ነገር ስለማታውቅ ከመፍረድ ተቆጠብ። (ምሳሌ 18:13) በእርግጥ ሁኔታው አያበሳጭም ማለት አይቻልም፤ በመሆኑም በወቅቱ በጣም ብትናደድ የሚያስገርም አይሆንም። ይሁንና በነገሩ ተቆጥተህ መቆየትህና ቂም መያዝህ ውሎ አድሮ በማንነትህ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ ያሳድራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከንዴት ተቈጠብ፤ ቍጣንም ተወው” ማለቱ የተገባ ነው።​—መዝሙር 37:8

● ምክንያታዊ ሁን። አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ አብሯቸው የማይኖረውን ወላጅ ከመጥላት ይልቅ ወደ ሌላው ጽንፍ በመሄድ ከማምለክ ባልተናነሰ ይወዱታል። የአልኮል ሱሰኛ የሆነና መጥፎ ሥነ ምግባር ያለው አባት የነበረውን አንድ ወጣት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ የዚህ ወጣት አባት በተደጋጋሚ ጊዜያት ቤተሰቡን ትቶ ይሄድ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም ከሚስቱ ጋር ተፋታ። ያም ሆኖ ይህ ወጣት ምክንያቱ ባይገባውም እንኳ አባቱን ልቡ እስኪጠፋ ይወደው እንደነበር ያስታውሳል!

ይህ ወጣት እንዲህ ያለ ሚዛኑን የሳተ ፍቅር ማሳየቱ ያልተለመደ ነገር አይደለም። በአንድ አገር ውስጥ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ወላጆቻቸው ከተፋቱ ልጆች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ከእናታቸው ጋር የሚኖሩ ሲሆን አባታቸውን የሚያገኙት አልፎ አልፎ ነው። በመሆኑም ተግሣጽ መስጠትን ጨምሮ ልጆቿን በየዕለቱ የመንከባከቡ ኃላፊነት የሚወድቀው በእናትየው ላይ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አባትየው ለልጆቹ ማሳደጊያ የገንዘብ ድጋፍ ቢያደርግም ብዙውን ጊዜ ከፍቺው በኋላ ቤተሰቡን የማስተዳደሩ ኃላፊነት በእናትየው ላይ ብቻ ስለሚወድቅ የኑሮ ደረጃዋ በጣም ይወርዳል። በሌላ በኩል ግን የአባትየው የኑሮ ደረጃ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህ ምን ያስከትላል? ልጆቹ አባታቸው ጋር ስለመሄድ ሲያስቡ ትዝ የሚላቸው ስጦታ ማግኘታቸውና እንደ ልባቸው መሆናቸው ነው! ስለ እናታቸው ሲያስቡ ግን የሚታያቸው በቁጠባ መኖር እንደሚጠበቅባቸውና መመሪያ እንደሚበዛባቸው ነው። የሚያሳዝነው አንዳንድ ወጣቶች፣ ክርስቲያን ከሆነው ወላጃቸው ጋር ከመኖር ይልቅ የበለጠ ሀብት ካለውና እንደፈለጉ እንዲሆኑ ከሚፈቅድላቸው የማያምን ወላጃቸው ጋር ለመኖር መርጠዋል።​—ምሳሌ 19:4

እንዲህ ዓይነት ምርጫ ለማድረግ ከተፈተንክ ቅድሚያ የምትሰጠው ለየትኞቹ ነገሮች እንደሆነ ራስህን መርምር። ሥነ ምግባራዊ መመሪያ፣ ምክርና ተግሣጽ እንደሚያስፈልግህ አስታውስ። አንድ ወላጅ የሚሰጥህ ነገር ምንም ይሁን ምን የእነዚህን ነገሮች ያህል በባሕርይህና በሕይወትህ ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር አይችልም።​—ምሳሌ 4:13

[በገጽ 202 እና 203 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆቹ በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት እንዴት ሊፈቱት እንደሚገባ የሚናገር ወጣት የአውሮፕላን አብራሪዎች እንዴት ማብረር እንደሚገባቸው ለመናገር ከሚሞክር ተሳፋሪ ተለይቶ አይታይም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ