-
መከራ ሲደርስንቁ!—2014 | ሐምሌ
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መከራ ሲደርስብህ—መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
መከራ ሲደርስ
ይዋል ይደር እንጂ ሁሉም ሰው መከራ ይደርስበታል። ሁሉ ነገር የተሟላላቸው የሚመስሉ ሰዎችም እንኳ ከመከራ አያመልጡም።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦
“ሩጫ ለፈጣኖች፣ ውጊያም ለኀያላን አይደለም፤ እንጀራ ለጥበበኞች፣ ወይም ባለጠግነት ለብልኆች፣ ወይም ሞገስ ለዐዋቂዎች አይሆንም፤ ጊዜና ዕድል [“ያልተጠበቁ ክስተቶች፣” NW] ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።”—መክብብ 9:11
እንግዲያው ጥያቄው ‘መከራ ያጋጥምህ ይሆን?’ የሚል ሳይሆን ‘መከራ ሲያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ?’ የሚለው ነው። ለምሳሌ፦
በተፈጥሮ አደጋ ንብረትህ በሙሉ ቢወድምብህስ?
ለሕይወት የሚያሰጋ በሽታ እንዳለብህ ቢነገርህስ?
የምትወደውን ሰው በሞት ብታጣስ?
የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች፣ መከራ ቢደርስብህ ሁኔታውን እንድትቋቋመው አልፎ ተርፎም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ጠንካራ ተስፋ እንዲኖርህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚረዳህ ያምናሉ። (ሮም 15:4) ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ ሦስት ተሞክሮዎችን እስቲ እንመልከት።
-
-
ንብረትን ማጣትንቁ!—2014 | ሐምሌ
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መከራ ሲደርስብህ—መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
ንብረትን ማጣት
መጋቢት 11, 2011 ዓርብ ዕለት፣ ጃፓን በሬክተር መለኪያ 9.0 በደረሰ የምድር መናወጥ ተመታች፤ በዚህ አደጋ ከ15,000 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ200 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚበልጥ ዋጋ ያለው ንብረት ወድሟል። የ32 ዓመቱ ኬይ፣ ሱናሚ እየመጣ እንዳለ ማስጠንቀቂያ ሲሰማ ሕይወቱን ለማትረፍ ከፍ ወዳለ ቦታ ሄደ። ኬይ እንዲህ ብሏል፦ “በማግስቱ የተረፈ ነገር ካለ ለመውሰድ ብዬ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ይሁን እንጂ እኖርበት የነበረውን አፓርተማ ጨምሮ ሁሉ ነገር ተጠራርጎ ባሕር ገብቶ ነበር። ከሕንፃው መሠረት ሌላ ምንም የቀረ ነገር አልነበረም።
“አንዳንድ ዕቃዎችን ብቻ ሳይሆን ያሉኝን ነገሮች በሙሉ እንዳጣሁ አምኜ ለመቀበል ጊዜ ወስዶብኛል። መኪናዬ፣ ለሥራ የምጠቀምባቸው ኮምፒውተሮች፣ እንግዶቼን የማስተናግድባቸው ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮችና ሶፋ፣ ኪቦርዴ፣ ጊታሬ፣ ዩከሌሌ የሚባለው የሙዚቃ መሣሪያዬና ዋሽንቴ እንዲሁም በውኃና በዘይት ቀለም ለመሳል የምጠቀምባቸው የሥዕል መሣሪያዎቼ ብሎም የሥዕል ሥራዎቼ በሙሉ በጎርፍ ተወስደዋል።”
መከራውን መቋቋም
ያጣኸውን ነገር ሳይሆን አሁን ያለህን ነገር ለማሰብ ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ [አይደለም]” ብሏል። (ሉቃስ 12:15) ኬይ ያሳለፈውን ሁኔታ ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦ “መጀመሪያ ላይ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች በዝርዝር ጻፍኩ፤ ይህ ግን የጠፉብኝን ነገሮች እንዳስታውስ ከማድረግ በቀር የፈየደልኝ ነገር አልነበረም። በመሆኑም በጣም የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ብቻ ለመጻፍ ወሰንኩ፤ እንዲሁም አንድ የሚያስፈልገኝ ነገር በተሟላልኝ ቁጥር የጻፍኩት ዝርዝር ላይ ማስተካከያ አደርጋለሁ። ይህም ሕይወቴን እንደ አዲስ ለመጀመር ረድቶኛል።”
ስለ ራስህ ችግር እያሰብክ ከመቆዘም ይልቅ ባገኘኸው ተሞክሮ በመጠቀም ሌሎችን ለማጽናናት ሞክር። ኬይ እንዲህ ብሏል፦ “የእርዳታ ድርጅቶችና ጓደኞቼ ብዙ ድጋፍ አድርገውልኛል፤ ይሁን እንጂ የሌሎችን እጅ ማየት ልማድ ስለሆነብኝ ለራሴ ያለኝ ግምት እየቀነሰ መጣ። በሐዋርያት ሥራ 20:35 ላይ የሚገኘውን ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አስታወስኩ። በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ልሰጥ የምችለው ብዙም ነገር ስላልነበረኝ አደጋ የደረሰባቸውን ሌሎች ሰዎች ለማበረታታት አሰብኩ። በዚህ መንገድ ልግስና ማሳየቴ በጣም ረድቶኛል።”
ያጋጠመህን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህ ወደ አምላክ ጸልይ። ኬይ፣ አምላክ “ወደ ችግረኞች ጸሎት ይመለከታል” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ላይ ጠንካራ እምነት አለው። (መዝሙር 102:17) አንተም እንዲህ ያለ እምነት ማዳበር ትችላለህ።
ይህን ታውቅ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ማንም ሰው በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ንብረቴ አጣለሁ ብሎ የማይሰጋበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጽ ትንቢት ይዟል።a—ኢሳይያስ 65:21-23
a አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።
-
-
ጤና ማጣትንቁ!—2014 | ሐምሌ
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መከራ ሲደርስብህ—መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
ጤና ማጣት
በአርጀንቲና የምትኖረው ማቤል የፊዚዮቴራፒ ባለሙያ ሆና ትሠራ የነበረ ሲሆን እንቅስቃሴ የበዛበት ሕይወት ትመራ ነበር። ሆኖም በ2007 በጣም ይደክማትና በየቀኑ ከባድ ራስ ምታት ያስቸግራት ጀመር። እንዲህ ብላለች፦ “ወደ ተለያዩ ሐኪሞች የሄድኩ ሲሆን ብዙ ዓይነት መድኃኒቶችንም ሞከርኩ፤ ግን አንዱም አልረዳኝም።” በመጨረሻ ኤም አር አይ በተባለ መሣሪያ አማካኝነት ምርመራ ተደረገላት፤ ምርመራውም የአንጎል ዕጢ እንዳለባት አሳየ። ማቤል እንዲህ ብላለች፦ “በድንጋጤ ክው ብዬ ቀረሁ! እንዲህ ያለውን ጠላት ተሸክሜ እኖር እንደነበር ማመን አልቻልኩም።”
“በሽታው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በደንብ የገባኝ ግን ቀዶ ጥገና ካደረግሁ በኋላ ነው። ከቀዶ ጥገናው ስነቃ ልዩ ክትትል የሚደረግበት ክፍል ውስጥ ነበርኩ፤ አልጋዬ ላይ ተንጋልዬ ጣሪያ ጣሪያውን ከማየት ሌላ ሰውነቴን ጨርሶ ማንቀሳቀስ እንደማልችል ተገነዘብኩ። ቀዶ ጥገና ከማድረጌ በፊት እንደ ልቤ መንቀሳቀስና የፈለግሁትን ማድረግ የምችል ሰው ነበርኩ። ከሕክምናው በኋላ ግን ምንም ነገር ማድረግ የማልችል ሰው ሆንኩ። ልዩ ክትትል በሚደረግበት ክፍል ውስጥ የሕክምና መሣሪያዎችና የድንገተኛ ጥሪዎች ድምፅ እንዲሁም ሌሎች ሕመምተኞች ሲያቃስቱ ይሰማ ነበር። በግራ መጋባት የተዋጥኩ ሲሆን በሥቃይና በመከራ እንደተከበብኩ ሆኖ ይሰማኝ ነበር።
“አሁን በመጠኑም ቢሆን አገግሜያለሁ። ማንም ሳይደግፈኝ መራመድና አልፎ አልፎም ራሴን ችዬ ወደ ውጭ መውጣት ችያለሁ። ይሁን እንጂ ነገሮች ሁለት ሆነው ይታዩኛል፤ እንዲሁም አሁንም ሰውነቴን ማቀናጀት ያቅተኛል።”
መከራውን መቋቋም
አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 17:22 ላይ “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው፤ የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል” ይላል። ማቤል እንዲህ ብላለች፦ “እኔ ጋ የሚታከሙ ሰዎች ፈታኝ ይሆንባቸው የነበረው ነገር እኔም እያገገምኩ በነበረበት ወቅት አጋጥሞኛል። የሰውነት እንቅስቃሴዎቹ በጣም ያሳምሙኝ ስለነበረ ተስፋ ቆርጬ ለማቋረጥ ያሰብኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም የማደርገው ጥረት ውሎ አድሮ ጥሩ ውጤት እንደሚኖረው ስለማውቅ እንደነዚህ ያሉትን አሉታዊ አስተሳሰቦች ለማስወገድ እታገል ነበር።”
መጽናት እንድትችል ተስፋ በሚሰጥህ ነገር ላይ አተኩር። ማቤል እንዲህ ብላለች፦ “በሰዎች ላይ መከራ የሚደርስበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሬያለሁ። እያንዳንዷ ቀን ባለፈች ቁጥር ደግሞ ሥቃይ ጨርሶ ወደሚወገድበት ጊዜ ይበልጥ እየተቃረብን እንደሆነ አውቃለሁ።”a
አምላክ በግለሰብ ደረጃ ለአንተ እንደሚያስብልህ አስታውስ። (1 ጴጥሮስ 5:7) ማቤል ይህን ማሰቧ እንዴት እንደረዳት ታስታውሳለች፦ “ለቀዶ ጥገና በሚወስዱኝ ጊዜ አምላክ ‘እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ’ በማለት በኢሳይያስ 41:10 ላይ የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን ማየት ችያለሁ። እኔ ስለሚያጋጥመኝ ነገር ይሖዋ አምላክ እንደሚያስብ ማወቄ ይህ ነው የማይባል ሰላም እንዳገኝ ረድቶኝ ነበር።”
ይህን ታውቅ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ በጤና ችግሮች የማይሠቃይበት ጊዜ እንደሚመጣ ያስተምራል።—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።
-
-
የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣትንቁ!—2014 | ሐምሌ
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መከራ ሲደርስብህ—መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት
በብራዚል የሚኖረው ሮናልዱ፣ እናቱንና አባቱን ጨምሮ ለአምስት የቤተሰቡ አባላት ሞት ምክንያት የሆነ የመኪና አደጋ አጋጥሞት ነበር። “ቤተሰቦቼ በአደጋው እንደሞቱ የተነገረኝ ሁለት ወር ያህል ሆስፒታል ከቆየሁ በኋላ ነው” ይላል።
“መጀመሪያ ላይ ሁሉንም እንዳጣሁ ማመን አቅቶኝ ነበር። እንዴት ሁሉም ሊሞቱ ይችላሉ? ነገሩ እውነት መሆኑን ስገነዘብ በከፍተኛ ድንጋጤ ተዋጥኩ። እንደዚያ ያለ ሥቃይ ተሰምቶኝ አያውቅም። ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት፣ እነሱ ከሌሉ ሕይወት ምንም ትርጉም እንደሌለው ተሰማኝ። ለበርካታ ወራት በየቀኑ አለቅስ ነበር! መኪናዋን ሌላ ሰው እንዲነዳ በመፍቀዴ ራሴን ወቀስኩ። እኔ ብነዳ ኖሮ ቤተሰቦቼ አሁን በሕይወት ይኖሩ ነበር ብዬ አሰብኩ።
“ይህ ከሆነ አሥራ ስድስት ዓመታት አልፈዋል፤ እኔም ወደተለመደው ሕይወቴ መመለስ ችያለሁ። ይሁን እንጂ የቤተሰቦቼ አሳዛኝ ሞት ዛሬም ድረስ ሊሽር ያልቻለ ትልቅ ጠባሳ በሕይወቴ ውስጥ ጥሎ አልፏል።”
መከራውን መቋቋም
ሐዘንህ አምቀህ አትያዝ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለማልቀስ ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1, 4) ሮናልዱ እንዲህ ብሏል፦ “ማልቀስ ባሰኘኝ ቁጥር አለቅሳለሁ። እንባዬን ለመቆጣጠር መታገል ምንም ጥቅም አልነበረውም፤ ደግሞም ካለቀስኩ በኋላ ቀለል ይለኛል።” እርግጥ ነው፣ ሰዎች ሐዘናቸውን የሚገልጹበት መንገድ ይለያያል። ስለዚህ ሐዘንህን የምትገልጸው ሌሎች በሚያዩት መንገድ ስላልሆነ ብቻ ስሜትህን አምቀህ ይዘኸዋል ወይም ደግሞ ራስህን አስገድደህ ማልቀስ አለብህ ማለት አይደለም።
ራስህን አታግልል። (ምሳሌ 18:1) ሮናልዱ እንዲህ ብሏል፦ “ከሌሎች እንድርቅ የሚታገለኝን ስሜት ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ ነበረብኝ። ሰዎች ሊጠይቁኝ ሲመጡ በደስታ እቀበላቸዋለሁ። በተጨማሪም ለባለቤቴና ለቅርብ ወዳጆቼ የውስጥ ስሜቴን አውጥቼ እናገራለሁ።”
ሰዎች የሚጎዳ ነገር ቢናገሩህ አትረበሽ። “ሁሉ ለበጎ ነው” እንደሚሉ ያሉ አነጋገሮችን ትሰማ ይሆናል። ሮናልዱ “እኔን ለማጽናናት ተብለው የሚሰነዘሩ አንዳንድ ሐሳቦች ይጎዱኝ ነበር” ብሏል። ጎጂ በሆኑ ቃላት ላይ ከማብሰልሰል ይልቅ “የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማዳመጥ አትሞክር” የሚለውን ጥበብ ያዘለ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተል።—መክብብ 7:21
ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እውነቱን ተማር። ሮናልዱ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ መክብብ 9:5 ላይ የሞቱ ሰዎች እየተሠቃዩ እንዳልሆኑ ይናገራል፤ ይህን ማወቄ ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረኝ ረድቶኛል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የሙታን ትንሣኤ እንደሚኖርና የሞቱ ሁሉ እንደገና በሕይወት እንደሚኖሩ ይገልጻል። ስለሆነም በሞት ያጣኋቸውን ቤተሰቦቼን ሩቅ አገር እንደሄዱ አድርጌ አስባለሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 24:15
ይህን ታውቅ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ሞትን ለዘላለም የሚውጥበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል።a—ኢሳይያስ 25:8
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት።
-