-
እውነተኛ ስኬት ምንድን ነው?ንቁ!—2014 | ጥቅምት
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
እውነተኛ ስኬት ምንድን ነው?
እውነተኛ ያልሆነ ስኬት ካገኘ ሰው ጨርሶ ያልተሳካለት ሰው ይሻላል። ምክንያቱም አንድ ነገር ሞክሮ ያልተሳካለት ሰው ሁኔታውን ለማስተካከል አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል። ሌላው ቢቀር ከውድቀቱ ትምህርት የሚያገኝ ከመሆኑም ሌላ በሚቀጥለው ጊዜ ስህተቱን ላለመድገም ያለው ቁርጠኝነት ይጠናከራል።
እውነተኛ ያልሆነ ስኬት ግን ከዚህ ይለያል። አንተ ተሳክቶልኛል ብለህ ታስብ ይሆናል፤ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርብህ የምትገነዘበው ደግሞ ጊዜው ካለፈ በኋላ ሊሆን ይችላል።
አንድ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት “አንድ ሰው ዓለሙን ሁሉ የራሱ ቢያደርግ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?” ሲል ጠይቆ ነበር። (ማቴዎስ 16:26) ይህ ሐሳብ መላ ሕይወታቸውን ገንዘብንና ገንዘብ ሊገዛ የሚችላቸውን ነገሮች ለማሳደድ ባዋሉ ሰዎች ላይ ይሠራል፤ እነዚህ ሰዎች የሚያገኙት ስኬት፣ እውነተኛ ላልሆነ ስኬት እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። የሥራ መስክ ምርጫ አማካሪ የሆኑት ቶም ዴናም እንዲህ ብለዋል፦ “ነጋ ጠባ ስለ ሥራ እድገት፣ ተጨማሪ ገንዘብ ስለ ማግኘት ወይም ብዙ ንብረት ስለ ማካበት ብቻ ማሰብ ለነፍስ እርካታን አያስገኝም። ስኬትን ከገንዘብ አንጻር ብቻ መለካት ብስለት እንደሌለን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የኋላ ኋላ የባዶነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል።”
በአሁኑ ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች በዚህ እንደሚስማሙ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ለተሳካ ሕይወት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ” ተብለው ከተዘረዘሩ 22 ነገሮች መካከል “ብዙ ገንዘብ ማግኘት” 20ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ጤንነት፣ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት እና በሚወዱት የሥራ መስክ ላይ መሰማራት ግን መጀመሪያ አካባቢ ከተቀመጡት ነገሮች መካከል ይገኙበታል።
ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው፣ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ተግባራዊ ባያደርጉትም እንኳ እውነተኛ የሆነን ስኬት እውነተኛ ካልሆነው መለየት አይከብዳቸውም። ይበልጥ ከባድ የሚሆነው ግን ስለ ስኬት ትክክለኛ አመለካከት እንዳለን የሚያሳይ ውሳኔ ማድረግ ነው።
-
-
አንተ ስኬትን የምትለካው እንዴት ነው?ንቁ!—2014 | ጥቅምት
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | እውነተኛ ስኬት ምንድን ነው?
አንተ ስኬትን የምትለካው እንዴት ነው?
ራስህን ለመፈተሽ የሚከተሉትን ሁኔታዎች አስብ።
እውነተኛ ስኬት እንዳገኘ የሚሰማህ ማን ነው?
አለማየሁ
አለማየሁ የራሱ ንግድ አለው። ሐቀኛ፣ ታታሪና ትሑት ሰው ነው። ንግዱ ትርፋማ ስለሆነለት እሱና ቤተሰቡ የተመቻቸ ሕይወት ይመራሉ።
ካሳሁን
ካሳሁንም በተመሳሳይ ንግድ ላይ የተሰማራ ሲሆን ከአለማየሁ የሚበልጥ ገቢ አለው። ይሁንና ከተፎካካሪዎቹ በልጦ ለመገኘት ሲል ከልክ በላይ ይሠራል፤ በዚህም ምክንያት ብዙ በሽታ ይዞታል።
ያኔት
ያኔት ትምህርት የምትወድና በትጋት የምታጠና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነች። በመሆኑም በትምህርቷ ጥሩ ውጤት ታመጣለች።
ሔለን
ሔለን ከያኔት የተሻለ ውጤት ያላት ሲሆን የደረጃ ተማሪ ነች፤ ነገር ግን ፈተና ላይ ትኮርጃለች፤ የመማር ፍላጎቷም አነስተኛ ነው።
ካሳሁን እና ሔለን ወይም አራቱም ግለሰቦች ስኬታማ እንደሆኑ ከተሰማህ ስኬትን የምትለካው ሰዎች ባገኙት ውጤት ብቻ ነው ማለት ነው፤ ውጤቱን ያገኙት በምን መንገድ ነው የሚለውን ግምት ውስጥ አላስገባህም።
ስኬታማ እንደሆኑ የሚሰማህ አለማየሁ እና ያኔት ብቻ ከሆኑ ግን ስኬትን የምትለካው በግለሰቡ ባሕርይ ወይም በሥራ ባሕሉ ነው ማለት ነው። ይህ ተገቢ የሆነ መሥፈርት ነው። እስቲ የሚከተሉትን ሁኔታዎች አስብ፦
ያኔት ለወደፊት ሕይወቷ የሚጠቅማት ከፍተኛ ውጤት ማግኘቷ ነው ወይስ ለትምህርት ፍቅር ያላት መሆኑ?
ለአለማየሁ ልጆች የሚሻለው የቱ ነው? ገንዘብ ሊገዛ የሚችለውን ነገር ሁሉ ማግኘታቸው ነው ወይስ አባታቸው ከነሱ ጋር ጊዜ የሚያሳልፍ መሆኑ?
ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ እውነተኛ ያልሆነ ስኬት የሚለካው ከውጭ በሚታዩ ነገሮች ነው፤ እውነተኛ ስኬት የሚለካው ግን ከትክክለኛ መሥፈርቶች አንጻር ነው።
-
-
እውነተኛ ስኬት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?ንቁ!—2014 | ጥቅምት
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | እውነተኛ ስኬት ምንድን ነው?
እውነተኛ ስኬት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ስኬት ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታናል። ስኬት ጥቂት ዕድለኛ ሰዎች ብቻ የሚያገኙት ነገር እንደሆነ አያስተምርም። በሌላ በኩል ደግሞ በተረት መጻሕፍት ላይ የሚንጸባረቀውን ‘ልብህ የሚልህን ከተከተልክ የምትፈልገውን ሁሉ ታገኛለህ’ የሚለውን ሐሳብ አይደግፍም። ልጆች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የሚነገራቸው ይህ ሐሳብ ብዙ ጊዜ እውን ስለማይሆን ውሎ አድሮ ለብስጭት ሊዳረጉ ይችላሉ።
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ማንኛውም ሰው እውነተኛ ስኬት ሊያገኝ ይችላል፤ ይሁንና ጥረት ማድረግ አለበት። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እንመልከት፦
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም።”—መክብብ 5:10
ይህ ምን ማለት ነው? ሀብትና ንብረትን በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት እርካታ ለማግኘት ዋስትና አይሆንም። እንዲያውም ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሊሆን ይችላል። ዶክተር ጂን ትዌንጂ የተባለች አንዲት ጸሐፊ ጀነሬሽን ሚ በተባለ መጽሐፏ ላይ እንዲህ ብላለች፦ “በሕይወታቸው ውስጥ ለገንዘብ ዋነኛ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረትን ከፍ አድርገው ከሚመለከቱ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ የበለጠ ጭንቀትና ውጥረት ይሰማቸዋል። . . . በርካታ ጥናቶች ገንዘብ ደስታ ሊያስገኝ እንደማይችል አረጋግጠዋል፤ መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚበቃ ገቢ እስካላችሁ ድረስ የገቢያችሁ መጠን በሚኖራችሁ እርካታ ላይ ያን ያህል ለውጥ አይኖረውም።”
ምን ማድረግ ትችላለህ? ሀብትና ንብረት ከማካበት የተሻለ እርካታ የሚያስገኝ ግብ አውጣ። ኢየሱስ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ ስላልሆነ ተጠንቀቁ፤ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” ብሏል።—ሉቃስ 12:15
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ትዕቢት ጥፋትን፣ የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች።”—ምሳሌ 16:18
ይህ ምን ማለት ነው? ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት መቋመጥ እውነተኛ ስኬት ለማግኘት አይረዳህም። እንዲያውም ጉድ ቱ ግሬት የተባለው መጽሐፍ ለረጅም ጊዜ ስኬታማ ስለሆኑ የድርጅት ኃላፊዎች ሲናገር “ትሑት፣ ልታይ ልታይ የማይሉ እንዲሁም የተለየ ትኩረት እንዲሰጣቸው የማይፈልጉ ናቸው” ብሏል። አክሎም “በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ የድርጅት ኃላፊ ሆነው ካልተገኙት ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ራሳቸውን ከልክ በላይ ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱ ለድርጅታቸው ውድቀት ወይም እድገት አለማግኘት ምክንያት ሆነዋል” ብሏል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ራስን ከፍ አድርጎ መመልከት ከስኬት ይልቅ ውድቀት ያስከትላል።
ምን ማድረግ ትችላለህ? ለራስህ ክብርና ማዕረግ ከመፈለግ ይልቅ ትሕትናን አዳብር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “አንድ ሰው ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከትበት ምንም ነገር ሳይኖረው ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ ራሱን እያታለለ ነው።” ይህ ደግሞ ስኬት ሊባል አይችልም።—ገላትያ 6:3
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ሰው . . . ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት የሚሻለው ነገር የለም።”—መክብብ 2:24 NW
ይህ ምን ማለት ነው? ጥሩ የሥራ ባሕል ካዳበርክ ሥራህን ይበልጥ ትወደዋለህ። ዶክተር ማደሊን ለቫይን ቲች ዩር ችልድረን ዌል በተባለ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በአንድ ነገር ስኬት እንዳገኘን የሚሰማን ያንን ነገር ጥሩ አድርገን ማከናወን ስንችል ነው፤ አንድን ነገር ጥሩ አድርጎ የመሥራት ችሎታ የሚገኘው ደግሞ በጥረትና ተስፋ ባለመቁረጥ ነው።” ይህ ደግሞ አልፎ አልፎ ባይሳካልህም እንኳ ሁኔታውን ተቋቁመህ ማለፍን ይጠይቃል።
ምን ማድረግ ትችላለህ? በሥራህ የተዋጣልህ እንድትሆን በርትተህ ሥራ፤ እንዲሁም እንቅፋት ሲያጋጥምህ ተስፋ አትቁረጥ። ልጆች ካሉህ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በራሳቸው እንዲወጡ (ዕድሜያቸውንና አቅማቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት) አጋጣሚ ስጣቸው። የሚያጋጥማቸውን ችግር በሙሉ ጣልቃ ገብተህ ለመፍታት አትቸኩል። ልጆች በሕይወታቸው እውነተኛ እርካታ የሚኖራቸው እንዲሁም አዋቂ ሲሆኑ የሚጠቅማቸውን ሥልጠና የሚያገኙት ችግሮችን ተቋቁሞ የማለፍ ችሎታ ካዳበሩ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል።”—መክብብ 9:4
ይህ ምን ማለት ነው? ራስህን ለማስተዳደር የምትሠራው ሥራ የሕይወትህ አንድ ክፍል እንጂ መላው ሕይወትህ መሆን የለበትም። እውነቱን ለመናገር፣ ጤንነትህን ወይም የቤተሰብህን አክብሮት አጥተህ በሥራህ ትልቅ ደረጃ ላይ ብትደርስ ስኬታማ እንደሆንክ ሊሰማህ ይችላል? ለሥራቸው፣ ለጤንነታቸውና ለቤተሰብ ሕይወታቸው ተገቢውን ቦታ የሚሰጡ ሰዎች እውነተኛ ስኬት ያገኛሉ።
ምን ማድረግ ትችላለህ? ራስህን ተንከባከብ። በቂ እረፍት አድርግ። ጤንነትን፣ ቤተሰብንና ወዳጆችን ሠውቶ ሙሉ በሙሉ በሥራ በመጠመድ የሚገኘው ጥቅም ከንቱ ነው፤ ምክንያቱም ይህ እውነተኛ ያልሆነ ስኬት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴዎስ 5:3
ይህ ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በውስጡ የሚገኙትን መመሪያዎች ሥራ ላይ ማዋል ለእውነተኛ ስኬት አስፈላጊ ነው። እንዲያውም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠታቸው ስለ ቁሳዊ ነገሮች ብዙ እንዳይጨነቁ እንደረዳቸው ተገንዝበዋል።—ማቴዎስ 6:31-33
ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ስኬት ለማግኘት ሊረዳህ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ተማር። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከፈለግህ በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ማናገር ወይም www.pr2711.com የተባለውን ድረ ገጽ መመልከት ትችላለህ።
-