-
ልጆችን መቅጣት ቀረ እንዴ?ንቁ!—2015 | ሚያዝያ
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
ልጆችን መቅጣት ቀረ እንዴ?
ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በምዕራባውያን አገሮች የቤተሰብ ሕይወት በአስገራሚ ሁኔታ ተለውጧል። ቀደም ባሉት ጊዜያት በቤት ውስጥ አመራር የሚሰጡት ወላጆች ሲሆኑ ልጆች ደግሞ ወላጆቻቸው የሚሏቸውን ይሰሙ ነበር። አሁን ግን በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ሁኔታው የተገላቢጦሽ የሆነ ይመስላል። እስቲ ከዚህ በታች የቀረቡትን ምሳሌዎች ተመልከት፤ እነዚህ ምሳሌዎች ብዙ ጊዜ በሚያጋጥሙ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው።
አንድ የአራት ዓመት ልጅ ከእናቱ ጋር ሱቅ ሄዶ አንድ መጫወቻ አነሳ። እናቱ፣ መጫወቻውን የማትገዛበትን ምክንያት ልታስረዳው ሞከረች። “አንተ እኮ በቂ መጫወቻዎች አሉህ፤ አይደል?” አለችው። ይህን ጥያቄ ማንሳት እንዳልነበረባት የተገነዘበችው ግን ከተናገረች በኋላ ነው። “ይሄንንም እፈልገዋለኋ!” በማለት ልጁ ተነጫነጨ። በዚህ ጊዜ እናቲቱ፣ ልጁ እንደለመደው እንዳይጮኽ በመፍራት መጫወቻውን እንዲወስድ ፈቀደችለት።
አንዲት የአምስት ዓመት ልጅ፣ አባቷ ከአንድ ትልቅ ሰው ጋር እያወራ ሳለ አቋርጣው “እዚህ መሆን ሰልችቶኛል። ቤት መሄድ እፈልጋለሁ!” አለችው። አባቷም የጀመረውን ዓረፍተ ነገር እንኳ ሳይጨርስ ወደ ልጅቱ ጎንበስ ብሎ “ትንሽ ብቻ ታገሺኝ፤ እሺ የኔ ቆንጆ” በማለት አባበላት።
የ12 ዓመቱ ጄምስ አሁንም መምህሩ ላይ በመጮኹ ተከስሷል። የጄምስ አባት በልጁ ሳይሆን በመምህሯ ተናደደ። ጄምስን እንዲህ አለው፦ “እሷ ደግሞ አንተ ብቻ ነህ እንዴ የምትታያት? ቆይ፣ ለትምህርት ቤቱ ኃላፊ እከስሳታለሁ!”
ከላይ የቀረቡት ምሳሌዎች እውነተኛ ታሪክ ባይሆኑም እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን ማየት በጣም የተለመደ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው ሥርዓት የጎደለው ነገር ሲያደርጉ በቸልታ የሚመለከቱ፣ ልጆቻቸው የሚጠይቋቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያደርጉላቸው እንዲሁም ጥፋታቸው የሚያስከትልባቸውን መዘዝ እንዳይቀምሱ የሚከላከሉላቸው ከሆነ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ዘ ናርሲሲዝም ኤፒደሚክ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆች ሥልጣናቸውን ለትናንሽ ልጆቻቸው ሲለቁላቸው ማየት እየተለመደ መጥቷል። . . . ከጥቂት ዓመታት በፊት ልጆች የቤቱ ኃላፊ ማን እንደሆነ ይኸውም እነሱ እንዳልሆኑ ያውቁ ነበር።”
እርግጥ ነው፣ አሁንም ቢሆን ብዙ ወላጆች ጥሩ ምሳሌ በመሆን እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጥብቅ የሆነ ሆኖም ፍቅር የሚንጸባረቅበት እርማት በመስጠት ለልጆቻቸው ተገቢ የሥነ ምግባር እሴቶችን ለማስተማር ይጥራሉ። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የተጠቀሰው መጽሐፍ እንደገለጸው እንዲህ ማድረግ ያለውን ጥቅም የሚገነዘቡ ወላጆች በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ካገኘው አካሄድ ተቃራኒ የሆነ ነገር ማድረግ ጠይቆባቸዋል።
ይሁንና ሁኔታው እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው እንዴት ነው? ለልጆች ተግሣጽ መስጠት የቀረው ለምንድን ነው?
የወላጆች ሥልጣን እየተዳከመ ነው
የወላጆች ሥልጣን መዳከም የጀመረው ጠበብት የተባሉ ሰዎች ወላጆች በልጆች አያያዛቸው ለቀቅ ያሉ እንዲሆኑ መምከር ከጀመሩበት ጊዜ ማለትም ከ1960ዎቹ ወዲህ እንደሆነ አንዳንዶች ይናገራሉ። እነዚህ ባለሙያዎች ለወላጆች እንደሚከተሉት ያሉ ምክሮችን ይሰጡ ነበር፦ ‘ለልጆቻችሁ ጓደኛ ሁኗቸው እንጂ ባለሥልጣን አትሁኑባቸው።’ ‘ልጆችን ማመስገን ለእነሱ እርማት ከመስጠት የተሻለ ነው።’ ‘ስህተታቸውን ከማረም ይልቅ የሚያደርጉትን መልካም ነገር ፈልጋችሁ አመስግኗቸው።’ እንዲህ ዓይነቱ ምክር፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በማመስገንና ለእነሱ እርማት በመስጠት ረገድ ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ አያበረታታም፤ ከዚህ ይልቅ ልጆችን መገሠጽ ገና በለጋ ዕድሜያቸው ስሜታቸው እንዲጎዳና ካደጉ በኋላ ወላጆቻቸውን እንዲጠሉ ሊያደርግ ይችላል የሚል መልእክት ያስተላልፋል።
ብዙም ሳይቆይ ባለሙያዎቹ፣ ልጆች ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ማድረግ ጥሩ ነገር እንደሆነ መለፈፍ ጀመሩ። ጥሩ የልጅ አስተዳደግ ሚስጥር በድንገት የተገለጠላቸው ይመስል ነበር፤ ይህም በአጭሩ ‘ልጆቻችሁ ስለ ራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው አድርጉ’ የሚል ነበር። እርግጥ ነው፣ ልጆች በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ መርዳት አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ለራስ ጥሩ ግምት ማሳደር የሚለው አመለካከት ወደ ሌላኛው ጽንፍ ሄዶ ነበር። ባለሙያዎቹ ለወላጆች እንደሚከተሉት ያሉ ምክሮችን ይሰጡ ነበር፦ ‘አይሆንም እና መጥፎ ነው እንደሚሉት ያሉ አሉታዊ ቃላትን አትጠቀሙ።’ ‘ልጆቻችሁ፣ ልዩ እንደሆኑና መሆን የሚፈልጉትን ሁሉ መሆን እንደሚችሉ ደጋግማችሁ ንገሯቸው።’ እንደ ባለሙያዎቹ አባባል ከሆነ ጥሩ ከመሆን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ልጆቹ ስለ ራሳቸው ጥሩ የሚሰማቸው መሆኑ ነው።
ለራስ ጥሩ ግምት ማሳደር የሚለው አመለካከት ልጆች የሁሉ ባለሥልጣን እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርጓል
በውጤቱ እንደታየው ከሆነ ለራስ ጥሩ ግምት ማሳደር የሚለው አመለካከት ልጆቹ ዓለም ሁሉ እነሱን የማገልገል ግዴታ ያለበት ይመስል የሁሉ ባለሥልጣን እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርጓል። በተጨማሪም ጀነሬሽን ሚ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ይህ ዓይነቱ አመለካከት ብዙ ትናንሽ ልጆች “በእውኑ ዓለም ትችት ቢደርስባቸው እንዲሁም አልፎ አልፎ ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሳኩላቸው ቢቀሩ ሁኔታውን መያዝ ስለሚችሉበት መንገድ በቂ ሥልጠና እንዳይኖራቸው” አድርጓል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “በሥራው ዓለም ለራስህ ጥሩ ግምት ይኑርህ የሚባል ነገር የለም። . . . በመሥሪያ ቤትህ ጥሩ ዝግጅት ያልተደረገበት ሪፖርት ጽፈህ ብታቀርብ አለቃህ ‘የጻፍክበትን ወረቀት ቀለሙን ወድጄዋለሁ’ አይልህም። በመሆኑም ልጆችን በዚህ መንገድ ማሳደግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል።”
በየጊዜው የሚለዋወጡ አመለካከቶች
ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የነበሩት የልጅ አስተዳደግ ልማዶች በየጊዜው የሚለዋወጠውን የሰዎች አመለካከት የሚያንጸባርቁ ነበሩ። ሮናልድ ሞሪሽ የተባሉ ምሁር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ተግሣጽ አሰጣጥ በየጊዜው ይለዋወጣል። ይህም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ለውጦች የሚያንጸባርቅ ነው።”a ወላጆች መጽሐፍ ቅዱስ ‘በማዕበል የሚነዱ ይመስል በማንኛውም የትምህርት ነፋስ፣ የሚንገዋለሉና ወዲያና ወዲህ የሚሉ’ በማለት እንደሚገልጻቸው ዓይነት ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።—ኤፌሶን 4:14
በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ወላጆች ተግሣጽ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ልል መሆናቸው አሉታዊ ውጤቶች አምጥቷል። ይህ መሆኑ የወላጆች ሥልጣን እንዲዳከም አድርጓል፤ በተጨማሪም ልጆች ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ እንዲሁም በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በራስ በመተማመን ስሜት ለመጋፈጥ የሚያስችላቸውን ሥልጠና እንዳያገኙ አድርጓል።
ታዲያ ከዚህ የተሻለ መንገድ ይኖር ይሆን?
a በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ ሴክሬትስ ኦቭ ዲሲፕሊን፦ 12 ኪስ ፎር ሬይዚንግ ሪስፖንሲብል ችልድረን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።
-
-
ጠቃሚ የሆነ ተግሣጽንቁ!—2015 | ሚያዝያ
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ልጆችን መቅጣት ቀረ እንዴ?
ጠቃሚ የሆነ ተግሣጽ
የወላጅ ኃላፊነት ከባድ እንደሆነ አይካድም። ይሁን እንጂ ወላጆች ተግሣጽ መስጠት ሲኖርባቸው ይህን ሳያደርጉ መቅረታቸው ሁኔታውን ይበልጥ ያከብደዋል። ለምን? ምክንያቱም ልጆች ተግሣጽ ካልተሰጣቸው (1) ከስህተታቸው አይታረሙም፤ ይህ ደግሞ ወላጆች እንዲሰለቻቸው ያደርጋል፤ እንዲሁም (2) ወላጆች ወጥ የሆነ መመሪያ ስለማይሰጡ ልጆቹ ግራ ይጋባሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በፍቅር የተሰጠ ሚዛናዊ ተግሣጽ የአንድን ልጅ አስተሳሰብ እንዲሁም ሥነ ምግባር ለመቅረጽ ያስችላል። በተጨማሪም ልጆቹ አድገው ትልቅ ሰው ሲሆኑ በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ይሁን እንጂ ለልጆችህ ተግሣጽ በመስጠት ረገድ የሚጠቅምህ አስተማማኝ የሆነ መመሪያ ከየት ማግኘት ትችላለህ?
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ያላቸው ጥቅም
የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ራሱ እንደሚናገረው “ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ለማረምና በጽድቅ ለመገሠጽ” የሚጠቅም መጽሐፍ እንደሆነ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 የግርጌ ማስታወሻ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ልጅ አስተዳደግ ብቻ ሳይሆን ለመላው ቤተሰብ የሚጠቅሙ መመሪያዎችን ይዟል። እስቲ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሞኝነት በልጅ ልብ ውስጥ ታስሯል።”—ምሳሌ 22:15
ልጆች አሳቢና ደግ ቢሆኑም በአብዛኛው የሞኝነት ድርጊት ይፈጽማሉ። በመሆኑም ልጆች ተግሣጽ ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 13:24) ይህን ሐቅ አምነህ መቀበልህ የወላጅነት ኃላፊነትህን እንድትወጣ ይረዳሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ልጅን ከመገሠጽ ወደኋላ አትበል።”—ምሳሌ 23:13
ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተግሣጽ መስጠትህ የልጆችህን ስሜት እንደሚጎዳው ወይም ካደጉ በኋላ እንዲጠሉህ እንደሚያደርግ በማሰብ መፍራት የለብህም። ተግሣጽ የምትሰጠው በፍቅር ከሆነ ልጆችህ የሚሰጣቸውን እርማት በትሕትና መቀበልን ይማራሉ፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ሰው ሲሆኑ የሚጠቅማቸው ችሎታ ነው።—ዕብራውያን 12:11
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።”—ገላትያ 6:7
ወላጆች ልጆቻቸውን ከችግር ለመጠበቅ መፈለጋቸው ተፈጥሯዊ እንዲሁም ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድም ቢሆን ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል። ልጆችህ፣ የፈጸሙት ስህተት የሚያስከትለው መዘዝ እንዳይነካቸው ለማድረግ ብትሞክር ወይም መምህራቸው አሊያም ሌላ ትልቅ ሰው፣ የፈጸሙትን ጥፋት ሲነግርህ ጥብቅና ብትቆምላቸው አትጠቅማቸውም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን ሰው እንደ አጋርህ አድርገህ ተመልከተው። እንዲህ ስታደርግ ልጅህ የአንተንም ሆነ የሌሎችን ሥልጣን ማክበርን ይማራል።—ቆላስይስ 3:20
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “መረን የተለቀቀ ልጅ . . . እናቱን ያሳፍራል።”—ምሳሌ 29:15
አፍቃሪ እና ምክንያታዊ ሁን፤ እንዲሁም ተግሣጽ አሰጣጥህ ወጥ ይሁን
ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በተያያዘ በጣም ጥብቅ መሆን የሌለባቸው ቢሆንም ወደ ተቃራኒው ጽንፍ በማድላት መረን የሚለቁ መሆንም የለባቸውም። “ወላጆች ልጆቻቸውን መረን የሚለቅቋቸው ከሆነ ልጆቹ በቤቱ ውስጥ ሥልጣን ያላቸው አዋቂዎቹ እንደሆኑ አይገነዘቡም” በማለት ዘ ፕራይስ ኦቭ ፕሪቭሌጅ የተሰኘው መጽሐፍ ተናግሯል። ሥልጣኑ የእናንተ መሆኑን ካላሳያችሁ ልጃችሁ በቤቱ ውስጥ ሥልጣን ያለው እሱ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። በዚህም የተነሳ በራሱም ሆነ በእናንተ ላይ ሐዘን የሚያስከትል ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ማድረጉ አይቀርም።—ምሳሌ 17:25፤ 29:21
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘ሰው ከሚስቱ ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’—ማቴዎስ 19:5
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ልጆች የሚወለዱት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ከተጋቡ በኋላ ሲሆን ልጆቹ አድገው ራሳቸውን ከቻሉ በኋላም ባልና ሚስቱ አብረው መኖራቸውን ይቀጥላሉ። (ማቴዎስ 19:5 6) በዚህ ምክንያት ወላጆች፣ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለትዳር ጓደኛቸው እንጂ ለልጆቻቸው አይደለም። ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር የተገላቢጦሽ ከሆነ ግን ልጅህ ‘ስለ ራሱ ከሚገባው በላይ ማሰብ’ ሊጀምር ይችላል። (ሮም 12:3) ከትዳር ጓደኛቸው የበለጠ ለልጃቸው ቅድሚያ የሚሰጡ ወላጆች ትዳራቸው ጠንካራ አይሆንም።
ለወላጆች የሚጠቅም ምክር
የወላጅነት ኃላፊነትህን ስትወጣ እንዲሳካልህ ከፈለግክ ለልጆችህ የምትሰጠው ተግሣጽ ቀጥሎ ከተጠቀሱት መመሪያዎች ጋር የሚስማማ መሆን አለበት።
እርማቱን በፍቅር ስጥ። “አባቶች ሆይ፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።”—ቆላስይስ 3:21
ተግሣጽ አሰጣጥህ ወጥ ይሁን። “ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን።”—ማቴዎስ 5:37
ምክንያታዊ ሁን። “በተገቢው መጠን እገሥጽሃለሁ።”—ኤርምያስ 30:11a
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት jw.orgን ተመልከት። በድረ ገጹ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ባለትዳሮች እና ወላጆች በሚለው ሥር የሚከተሉትን ርዕሶች ማግኘት ይቻላል፦ “ለልጆች ተግሣጽ መስጠት” “ልጆች እልኸኛ ሲሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል?” “በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ የሥነ ምግባር እሴቶችን ትከሉ” እና “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ልጆቻችሁ ተግሣጽ መስጠት የምትችሉት እንዴት ነው?”
-