የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?
    ንቁ!—2015 | የካቲት
    • የተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

      መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?

      “በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ደስታ አገኘሁ።”

      ሂልተን የቦክስ ስፖርት ይወድ ነበር። ገና በሰባት ዓመቱ በቦክስ ውድድር ላይም ሆነ በሌሎች ጊዜያት ከሰዎች ጋር መደባደብ ጀመረ! ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ የሚደበድበው ሰው ለመፈለግ ከጓደኞቹ ጋር ይዞር ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እሰርቅ፣ ቁማር እጫወት፣ ፖርኖግራፊ እመለከት፣ ሴቶችን አስቸግር እንዲሁም ወላጆቼን እሳደብ ነበር። በጣም መጥፎ ጠባይ ስለነበረኝ ወላጆቼ ፈጽሞ ልሻሻል እንደማልችል ያስቡ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንደጨረስኩ ከቤት ወጣሁ።”

      ሂልተን ከ12 ዓመት በኋላ ወደ ቤቱ ሲመለስ ወላጆቹ ልጃቸው መሆኑን ማመን አቃታቸው። ሂልተን ረጋ ያለ፣ ራሱን የሚገዛና ሰው አክባሪ ሆኖ ነበር። እንዲህ ያለ አስደናቂ ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? ከቤት ወጥቶ በነበረበት ጊዜ ሕይወቱ ወዴት እያመራ እንዳለ በጥሞና ማሰብ ጀመረ። ሕይወቱን ለማሻሻል እንደሚረዳው በማሰብም መጽሐፍ ቅዱስን መረመረ። ሂልተን እንዲህ ብሏል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማነብበውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ፤ ይህ ደግሞ የቀድሞ ጠባዬን ማስወገድንና በኤፌሶን 6:2, 3 ላይ የሚገኘውን ወላጆቼን ማክበር እንዳለብኝ የሚገልጸውን መመሪያ መታዘዝን ይጠይቅብኝ ነበር። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ደስታ አገኘሁ፤ ለአባቴና ለእናቴም ምሬትና ሐዘን ሳይሆን ደስታ የማመጣ ልጅ ሆንኩ።”

      የሂልተን ታሪክ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የሥነ ምግባር እሴቶች በዛሬው ጊዜም ጠቃሚ እንደሆኑ እንዲሁም የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳላቸው ያሳያል። (ዕብራውያን 4:12) እንደ ሐቀኝነት፣ ራስን መግዛት፣ ታማኝነትና ፍቅር ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ እሴቶች የሰዎች ሕይወት እንዲሻሻል ያደረጉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

      ጊዜ ያለፈበት መጽሐፍ ነው?

      አሮጌ የኮምፒውተር ዕቃዎች የተጣሉበት ቆሻሻ መጣያ

      አንዳንድ ሰዎች እንደ አሮጌ ኮምፒውተር የአጠቃቀም መመሪያ ጽሑፍ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ንጽጽር በደንብ ያልታሰበበት ከመሆኑም ሌላ አሳሳች ነው። ኮምፒውተር በየጊዜው ይሻሻላል፤ በመሆኑም ለኮምፒውተሩ የተዘጋጀው የአጠቃቀም መመሪያ ጊዜ ያልፍበታል። የሰው ልጆች መሠረታዊ ባሕርያት ግን አይለወጡም። ለምሳሌ ያህል፣ ጥንትም ሆነ ዛሬ ሰዎች ለፍቅርና ለጥላቻ፣ ለታማኝነትና ለክህደት እንዲሁም ለደግነትና ለጭካኔ ያላቸው አመለካከት ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር በተያያዘ “ከፀሐይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም” ሊባል ይችላል።—መክብብ 1:9

  • ለሁሉም ሰው የሚጠቅሙ ጊዜ የማይሽራቸው እሴቶች​—ሐቀኝነት
    ንቁ!—2015 | የካቲት
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?

      ለሁሉም ሰው የሚጠቅሙ ጊዜ የማይሽራቸው እሴቶች​—ሐቀኝነት

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? . . . አካሄዱ ንጹሕ የሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር።”—መዝሙር 15:1, 2

      የሚያስገኘው ጥቅም፦ አብዛኞቹ ሰዎች ለሐቀኝነት ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸሙ ጥቅም የሚያስገኝለት ቢሆንና ሐቀኝነት ማጉደሉን ማንም ሰው እንደማያውቅበት ቢሰማው ምን ያደርጋል? በዚህ ጊዜ የሚወስደው እርምጃ ውስጣዊ ማንነቱን ማለትም በልቡ ውስጥ ያለውን ነገር በግልጽ ያሳያል።

      ራኬል ሥራዋ ከዕቃ ግዢ ጋር የተያያዘ ሲሆን እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ የሽያጭ ወኪሎች ጉቦ እንስጥሽ ይሉኝ ነበር። ከእነሱ ዕቃ ከገዛሁ የተወሰነ ገንዘብ በድብቅ እንደሚሰጡኝ ቃል ይገቡ ነበር። እኔ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐቀኝነት የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ስለፈለግኩ እምቢ አልኳቸው። አለቃዬ ይህን ስትሰማ በእኔ ላይ ያላት እምነት ጨመረ።”

      ራኬል በቀረበላት ጥያቄ ተታልላ ቢሆን ኖሮ ለጊዜውም ቢሆን የገንዘብ ጥቅም ታገኝ ነበር። ይሁን እንጂ አሠሪዋ ሁኔታውን ብታውቅስ? ራኬል ከሥራዋ ልትባረር ትችል ነበር። ወደፊት ሥራ የማግኘት አጋጣሚዋ ደግሞ ሊቀንስ ይችላል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ራኬል ሕሊናዋን ማቆሸሽ እንዲሁም ለራስዋ ያላትን አክብሮት ማጣት አልፈለገችም። ምሳሌ 22:1 “መልካም ስም ከብዙ ብልጽግና ይመረጣል፤ መከበርም ከብርና ከወርቅ ይበልጣል” ይላል።

      ጄሲ በሥራ ቦታው

      ጄሲ ሐቀኛ ሠራተኛ በመሆኑ ጥሩ ስም አትርፏል

      ጄሲ ሐቀኛና እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆኑ በአሠሪው ዘንድ ጥሩ ስም አትርፏል። ይህስ ምን ጥቅም አስገኘለት? የኃላፊነት ቦታ የተሰጠው ከመሆኑም በላይ ከሥራ ሰዓቱ ጋር በተያያዘ የበለጠ ነፃነት አለው። በመሆኑም ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ እንዲሁም መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ሰፋ ያለ ጊዜ ማግኘት ችሏል።

      አንዳንድ አሠሪዎች ሠራተኛ በሚቀጥሩበት ጊዜ በሐቀኝነታቸው የሚታወቁ አባሎች ያሏቸውን ድርጅቶች የጠየቁበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ በፊሊፒንስ የሚገኝ የአንድ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ በአገሩ ላለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ደብዳቤ በመጻፍ የይሖዋ ምሥክሮች ወደዚህ ኩባንያ የሥራ ማመልከቻ እንዲያስገቡ ግብዣ አቅርቦ ነበር። ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክሮች “ጠንካራ ሠራተኞች፣ ሐቀኞችና ታታሪዎች” እንደሆኑ ገልጿል። እርግጥ ነው፣ ለዚህ ሁሉ ሊመሰገን የሚገባው ‘ክፉውን እንድንጠላና መልካሙን እንድንወድ’ የሚያስተምረን ይሖዋ አምላክ ነው።—አሞጽ 5:15

  • ለሁሉም ሰው የሚጠቅሙ ጊዜ የማይሽራቸው እሴቶች​—ራስን መግዛት
    ንቁ!—2015 | የካቲት
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?

      ለሁሉም ሰው የሚጠቅሙ ጊዜ የማይሽራቸው እሴቶች​—ራስን መግዛት

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ተላላ ሰው ቍጣውን ያለ ገደብ ይለቀዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ራሱን ይቈጣጠራል።”—ምሳሌ 29:11

      “ከሞት የተነሳሁ ያህል ሆኖ ይሰማኛል!”

      የሚያስገኘው ጥቅም፦ ራስን መግዛት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ዘርዝረን መጨረስ አንችልም! ለአብነት ያህል፣ ለጤንነታችን የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማንሳት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰከነ ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” በማለት ይናገራል። በተጨማሪም “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኅኒት ነው” ይላል። (ምሳሌ 14:30 NW፤ 17:22) በአንጻሩ ደግሞ ጠበኛና ግልፍተኛ የሆኑ ሰዎች በተለያዩ በሽታዎች በተለይ ከልብ ጋር በተያያዙ ሕመሞች የመጠቃት አጋጣሚያቸው ከፍተኛ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። እርግጥ ነው፣ ራስን መግዛት የሚጠቅመው ለጤንነታችን ብቻ አይደለም።

      ካስያስ በአሁኑ ጊዜ በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን እንዲህ ብሏል፦ “ጠበኛና ግልፍተኛ የነበርኩ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ጊዜ ከሰዎች ጋር ለመጣላት ነገር እፈላልግ ነበር። ለራሴ አክብሮት አልነበረኝም። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ሥራ ላይ ማዋል ስጀምር ግን ይህ ሁሉ ተለወጠ። ቁጣዬን መቆጣጠር እንዲሁም ትሑትና ይቅር ባይ መሆን ቻልኩ። እንዲህ ባላደርግ ኖሮ ዛሬ የምገኘው እስር ቤት ነበር። በእርግጥም ከሞት የተነሳሁ ያህል ሆኖ ይሰማኛል!”

      አንድ የተናደደ ሹፌር ካስያስ ላይ ቢጮኽበትም ካስያስ ሳይበሳጭ ሞተር ሳይክሉን እየነዳ ነው

      ካስያስ ቁጣውን መቆጣጠርና ይቅር ባይ መሆን ችሏል

  • ለሁሉም ሰው የሚጠቅሙ ጊዜ የማይሽራቸው እሴቶች​—ታማኝነት
    ንቁ!—2015 | የካቲት
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?

      ለሁሉም ሰው የሚጠቅሙ ጊዜ የማይሽራቸው እሴቶች​—ታማኝነት

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን።”—ዕብራውያን 13:4

      የሚያስገኘው ጥቅም፦ አንዳንድ ሰዎች ይህ ሐሳብ ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በጣም ተሳስተዋል! ለትዳር ጓደኛ ታማኝ አለመሆን መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜም ከባድ ጉዳት ያስከትላል።—ምሳሌ 6:34, 35

      ጄሲ ባለትዳርና የልጆች አባት ሲሆን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በትዳራችን ውስጥ አንዳችን ለሌላው ታማኝ መሆናችን ከባለቤቴ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖረንና ቤተሰባችን ደስተኛ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። በእርግጥም መተማመን በትዳር ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነው። ለትዳር ጓደኛ ታማኝ አለመሆን ግን ይህ የመተማመን ስሜት እንዲጠፋ ያደርጋል።” ከዚህም በተጨማሪ በልጆች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራል።

      ሊጋያa ትዳሯን አደጋ ላይ ጥላ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “መጥፎ ምግባር ካላቸው ሰዎች ጋር ጓደኝነት መሠረትኩ። በዚህም የተነሳ ወደ ምሽት ክበቦች መሄድ ጀመርኩ፤ እንዲሁም ምንዝር በመፈጸም ታማኝነቴን አጎደልኩ።” ታዲያ ይህ አኗኗሯ ደስታ አስገኝቶላታል? ከባለቤቷ ጋር ሁልጊዜ ይጨቃጨቁ የነበረ ሲሆን ደስታ አጣች። ሊጋያ እንዲህ ብላለች፦ “ምን ያህል አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ እንደተዘፈቅኩ ሳስብ ወላጆቼ ‘መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል’ ይሉኝ የነበረው ትዝ አለኝ።”—1 ቆሮንቶስ 15:33

      አክላም ሊጋያ እንዲህ ብላለች፦ “ነገሮች ከመባባሳቸው በፊት መጥፎ አካሄዴን አቁሜ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና የተማርኩትን በሚገባ ሥራ ላይ ለማዋል ወሰንኩ።” ውጤቱስ? ትዳሯ ከመፍረስ ዳነ፤ ባለቤቷም ከበፊቱ ይበልጥ በደግነትና በአክብሮት ይይዛት ጀመር። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን ለውጦታል፤ የቀድሞ አኗኗሬንና ጓደኛ ብዬ የያዝኳቸውን ሰዎች እርግፍ አድርጌ በመተዌ ፈጽሞ አልቆጭም።”

      a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

  • ለሁሉም ሰው የሚጠቅሙ ጊዜ የማይሽራቸው እሴቶች​—ፍቅር
    ንቁ!—2015 | የካቲት
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?

      ለሁሉም ሰው የሚጠቅሙ ጊዜ የማይሽራቸው እሴቶች​-ፍቅር

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ፍቅርን ልበሱ፤ ምክንያቱም ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።”—ቆላስይስ 3:14

      የሚያስገኘው ጥቅም፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት የተጠቀሰው የፍቅር ዓይነት በወንድና በሴት መካከል የሚፈጠረው ፆታዊ ፍቅር አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንደ ርኅራኄ፣ ይቅር ባይነት፣ ትሕትና፣ ታማኝነት፣ ደግነት፣ ገርነትና ትዕግሥት ያሉትን ባሕርያት ያካተተ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን መሠረት ያደረገ የፍቅር ዓይነት ነው። (ሚክያስ 6:8፤ ቆላስይስ 3:12, 13) ይህ ዓይነቱ ፍቅር፣ በጊዜ ብዛት እየከሰመ ከሚሄደው የወረት ፍቅር በተለየ መልኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይሄዳል።

      ብሬንዳ በትዳር ሕይወት 30 ዓመታት ገደማ አሳልፋለች፤ እንዲህ ብላለች፦ “በአዲስ ተጋቢዎች መካከል የሚኖረው ፍቅር ለረጅም ጊዜ በትዳር ዓለም በቆዩ ሰዎች መካከል ካለው ፍቅር ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም።”

      ሳም ትዳር ከመሠረተ ከ12 ዓመት በላይ ሆኖታል፤ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “እኔና ባለቤቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ምን ያህል ውጤታማና ቀላል እንደሆኑ ስንመለከት ከመደሰት አልፈን በጣም የተደነቅንባቸው ጊዜያት አሉ። ምክሮቹን ተግባራዊ ካደረግህ ሁሉ ነገር ይሳካልሃል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ብፈልግም እንዲህ ሳላደርግ የምቀርባቸው ጊዜያት አሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥመኝ ከመጠን በላይ ስሜታዊ ስሆን፣ የራስ ወዳድነት ስሜት ሲያድርብኝ ወይም ስደክም ነው። እንደነዚህ ባሉት ጊዜያት መጥፎ ስሜቶችን እንዳስወግድ እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። በኋላም ባለቤቴን ሄጄ እቅፍ አደርጋታለሁ፤ ከዚያም የተፈጠረውን ነገር ሙሉ በሙሉ እንረሳዋለን!”

      “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል”

      ኢየሱስ ክርስቶስ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” ብሏል። (ማቴዎስ 11:19) መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ሲመዘን የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። የያዛቸው ትምህርቶችና እሴቶች ጠቃሚ ናቸው። ጊዜ አይሽራቸውም። ባሕል ወይም ብሔር የሚገድባቸው አይደሉም። የሰው ልጆችን ተፈጥሮ ግምት ውስጥ ያስገቡ በመሆናቸው የመጽሐፉ ምንጭ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በእርግጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ጠቀሜታ ማየት የሚቻልበት ዋነኛው መንገድ ምክሮቹን ተግባራዊ በማድረግ ውጤቱን መመልከት ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ” በማለት ይጋብዘናል። (መዝሙር 34:8) ይህን ግብዣ ትቀበላለህ?

      መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴ እንዲሻሻል ረድቶኛል

      ሊን የምትኖረው በደቡብ ምሥራቅ እስያ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቷ እንዲሻሻል የረዳት እንዴት እንደሆነ ለንቁ! መጽሔት ተናግራለች።

      የቀድሞ ሃይማኖትሽ ምን ነበር?

      ቤተሰቦቼ የአባቶቻቸውን ወግ በጥብቅ የሚከተሉ የቡድሂስት እምነት ተከታዮች ናቸው። ስለ እውነተኛው አምላክ የማውቀው ነገር አልነበረም።

      በሕይወትሽ ደስተኛ ነበርሽ?

      በፍጹም! ብዙ ችግሮች ነበሩብኝ። ገንዘቤን አብቃቅቼ መጠቀም አልችልም ነበር፤ ጥሩ ጓደኞችን መምረጥ የምችለው እንዴት እንደሆነ አላውቅም ነበር፤ ወላጆቼንም በችግራቸው መርዳት አልቻልኩም።

      ከዚያ በኋላ ሕይወትሽ መሻሻል ጀመረ። ይህ የሆነው እንዴት እንደሆነ እስቲ ንገሪን።

      የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ወጣት ሴቶች መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምሩኝ ጀመር። ችግር ሲያጋጥመኝ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አማክራቸዋለሁ። በዕድሜ ከእኔ ቢያንሱም በጣም ጥሩ ምክር ይሰጡኝ ነበር፤ የሚሰጡኝ ምክር ግን በራሳቸው አመለካከት ላይ የተመሠረተ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ያሳዩኝ ነበር።

      የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ሥራ ላይ ማዋል ያለውን ጠቀሜታ በራሴ ሕይወት ስላየሁ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው አምላክ እንደሆነና ምክሮቹን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጣጣር ማንኛውም ሰው እንደሚጠቀም እርግጠኛ ነኝ። ሰብዓዊ ትምህርት የተወሰነ ጥቅም ቢኖረውም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሊሆን አይችልም።

      ምን ማለትሽ እንደሆነ ይበልጥ ልታብራሪልን ትችያለሽ?

      ወላጆቼ ኮሌጅ ገብተው የተማሩ ሲሆን በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት አላቸው። ያም ሆኖ ችግሮቻቸውን መፍታት አልቻሉም። እንዲያውም ፍቺ ከመፈጸማቸውም በላይ በሕይወታቸው ደስተኛ አይደሉም። እንዲሁም የማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ አንዳንድ ጊዜ ዓመፅ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ኮሌጅ በነበርኩበት ወቅት ተምሬ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ግን አምላክ ራሳችንን በራሳችን እንድናስተዳድር ችሎታም ሆነ ሥልጣን ስላልሰጠን የሰው ልጆች በዚህ ረገድ የሚያደርጓቸው ጥረቶች ዘላቂ ስኬት ሊያስገኙ እንደማይችሉ ይናገራል። የትኛውም ዓይነት ሰብዓዊ አገዛዝ ጉድለት የማያጣውa እንዲሁም ከሙስና የጸዳ ሊሆን ያልቻለው በዚህ ምክንያት ነው። ራሳችንን ለአምላክ ስናስገዛ ግን ሕይወታችን የሚሻሻል ከመሆኑም ሌላ በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር እንችላለን።

      መጽሐፍ ቅዱስ የረዳሽ እንዴት ነው?

      መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ መንገድ ረድቶኛል። አሁን ብዙ የሚያስጨንቁኝ ነገሮች የሉም፤ ጥሩ ጓደኞች አሉኝ። ገንዘቤን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንዳለብኝ ስለተማርኩ ሌላው ቀርቶ ወጣ ብዬ ሌሎች አካባቢዎችን ለማየት የሚበቃ ገንዘብ አለኝ። ከሁሉ በላይ ደግሞ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት ችያለሁ።

      a መክብብ 8:9⁠ን እና ኤርምያስ 10:23⁠ን ተመልከት።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ