የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ቤተሰብ እንዲጋጭ የሚያደርገው ነገር
    ንቁ!—2015 | ታኅሣሥ
    • በወላጆቻቸው ጭቅጭቅ የተጨነቁ ልጆች

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ

      ቤተሰብ እንዲጋጭ የሚያደርገው ነገር

      ከያዕቆብa ጋር ለ17 ዓመታት በትዳር ያሳለፈችውና በጋና የምትኖረው ሣራ “ብዙ ጊዜ የሚያጋጨን የገንዘብ ጉዳይ ነው” በማለት ተናግራለች። አክላም “እኔ ቤተሰቡን ለመንከባከብ ብደክምም እሱ ግን ስለ በጀታችን አናግሮኝ አያውቅም። ለሳምንታት የምንኮራረፍበት ጊዜ አለ” ብላለች።

      ባለቤቷ ያዕቆብ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ልክ ነው፤ ኃይለ ቃል የምንነጋገርባቸው ጊዜያት አሉ። ብዙውን ጊዜ ለዚህ ምክንያቱ ተነጋግሮ አለመግባባትና ትርጉም ያለው ውይይት አለማድረግ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የምንጋጨው ቶሎ ቱግ ስለምንል ነው።”

      በቅርቡ ትዳር የመሠረተውና በሕንድ የሚኖረው ናታን አንድ ቀን የሚስቱ አባት በሚስቱ እናት ላይ ሲጮኽባት የተፈጠረውን ነገር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ስለተበሳጨች ቤቱን ጥላ ወጣች። ለምን እንደዛ እንደጮኸባት ስጠይቀው እንደናቅኩት ተሰማው። ከዚያም ሁላችንም ላይ መጮኽ ጀመረ።”

      እናንተም ብትሆኑ በአጉል ሰዓት የተነገሩ ወይም ያልታሰበባቸው ቃላት በቤታችሁ ውስጥ ምን ያህል ግጭት እንደሚፈጥሩ ሳታስተውሉ አትቀሩም። ረጋ ባለ መንፈስ የተጀመረ ውይይት በድንገት ወደ ቃላት ጦርነት ሊቀየር ይችላል። ማናችንም ብንሆን ሁልጊዜ ትክክል የሆነ ነገር ልንናገር አንችልም፤ ስለዚህ ሌሎች የተናገሩትን ነገር ወይም አንድን ነገር ያደረጉበትን ምክንያት በተሳሳተ መንገድ ልንተረጉመው እንችላለን። ያም ቢሆን በቤተሰብ ውስጥ ሰላም ማግኘትና ተስማምቶ መኖር ይቻላል።

      የጦፈ ጭቅጭቅ በሚነሳበት ጊዜ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በቤታችሁ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት መልሶ እንዲሰፍን ለማድረግ ምን እርምጃዎች ልትወስዱ ትችላላችሁ? ቤተሰቦች፣ በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? መልሱ በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ ይገኛል።

      a በእነዚህ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

  • በቤት ውስጥ ግጭት እንዳይፈጠር ምን ማድረግ ይቻላል?
    ንቁ!—2015 | ታኅሣሥ
    • ባልና ሚስት ቁጭ ብለው ሲነጋገሩ፤ ሚስት ስሜቷን ስትገልጽ ባል በጥሞና ያዳምጣል

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ

      በቤት ውስጥ ግጭት እንዳይፈጠር ምን ማድረግ ይቻላል?

      ከቤታችሁ ግጭት የማይጠፋ ከሆነስ? ምናልባትም ግጭቶቹ እየተደጋገሙና እየከረሩ ሄደው ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ አለመግባባቱ እንዴት እንደተፈጠረ እንኳ ላታውቁ ትችላላችሁ። ይሁንና እርስ በርስ እንደምትዋደዱና አንዳችሁ ሌላውን መጉዳት እንደማትፈልጉ የታወቀ ነው።

      የሐሳብ ልዩነት ተፈጠረ ማለት ቤተሰባችሁ አለቀለት ማለት እንዳልሆነ ምንጊዜም አስታውሱ። ቤታችሁ ጠብ የነገሠበት እንዲሆን የሚያደርገው የተፈጠረው አለመግባባት ሳይሆን አለመግባባቱን ለመፍታት የምትሞክሩበት መንገድ ነው። ግጭት እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚረዷችሁን አንዳንድ እርምጃዎች እስቲ እንመልከት።

      1. አጸፋ አትመልሱ።

      ጭቅጭቅ የሚፈጠረው ቢያንስ በሁለት ሰዎች መካከል ነው፤ አንዱ ሲናገር ሌላው ጸጥ ብሎ ካዳመጠ ግን ጠቡ እየረገበ ይሄዳል። በመሆኑም የሚያስቆጣ ነገር ሲያጋጥማችሁ አጸፋ ከመመለስ ተቆጠቡ። ራሳችሁን በመቆጣጠር ክብራችሁን ለመጠበቅ ጥረት አድርጉ። በቤታችሁ ውስጥ ሰላም መስፈኑ ተከራክሮ ከመርታት የበለጠ ዋጋ እንዳለው አስታውሱ።

      “እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ ስም አጥፊ ከሌለ ደግሞ ጭቅጭቅ ይበርዳል።”—ምሳሌ 26:20

      2. የቤተሰባችሁን አባላት ስሜት ተረዱ።

      አንድ ሰው ጣልቃ ሳይገባ ወይም ለመፍረድ ሳይቸኩል በትኩረትና በርኅራኄ ማዳመጡ ቁጣን ለማብረድና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ያስችላል። በሌላው ሰው ላይ ለመፍረድ ከመቸኮል ይልቅ ስሜቱን ለመረዳት ጥረት አድርጉ። በአለፍጽምና ምክንያት ያደረገውን ነገር በክፋት ተነሳስቶ እንደፈጸመው አድርጋችሁ አትደምድሙ። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው ጎጂ ንግግር የሚናገረው በክፋት ተነሳስቶ ሳይሆን በግድየለሽነት ወይም ስሜቱ በመጎዳቱ ሊሆን ይችላል።

      “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ።”—ቆላስይስ 3:12

      3. ጊዜ ወስዳችሁ ተረጋጉ።

      በቀላሉ የምትቆጡ ከሆነ እስክትረጋጉ ድረስ በዘዴ ከአካባቢው ዞር ማለታችሁ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ስሜታችሁ እስኪረጋጋ ድረስ ወደ ሌላ ክፍል ልትገቡ ወይም ወጣ ብላችሁ በእግር ልትንሸራሸሩ ትችላላችሁ። አንድ ሰው እንዲህ ማድረጉ ከችግሩ ለመሸሽ እንደሞከረ ወይም በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ፍላጎት እንደሌለው አሊያም እንዳኮረፈ የሚያሳይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህን አጋጣሚ ይሖዋ ትዕግሥትና ማስተዋል እንዲሰጠው ለመጠየቅ ሊጠቀምበት ይችላል።

      “ጥል ከመነሳቱ በፊት ከአካባቢው ራቅ።”—ምሳሌ 17:14

      4. ምን እና እንዴት መናገር እንዳለባችሁ ቆም ብላችሁ አስቡ።

      የቤተሰባችሁን አባል ስሜት ሊጎዳ የሚችል መልስ መስጠታችሁ ምንም ፋይዳ የለውም። ከዚህ ይልቅ የተጎዳውን ሰው ስሜት ሊፈውስ የሚችል ነገር ለመናገር ሞክሩ። በተጨማሪም ምን ዓይነት ስሜት ሊያድርበት እንደሚገባ ከምትነግሩት ይልቅ የተሰማውን ስሜት በግልጽ እንዲነግራችሁ ለስለስ ባለ መንገድ ጠይቁት፤ ከዚያም የልቡን አውጥቶ ሲናገር አመስግኑት።

      “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው።”—ምሳሌ 12:18

      5. አትጩኹ፤ እርቅ ለማውረድ እንደምትፈልጉ የሚያሳይ የድምፅ ቃና ይኑራችሁ።

      አንደኛው የቤተሰብ አባል ትዕግሥት ማጣቱ ሌላኛውም በቀላሉ እንዲቆጣ ሊያደርገው ይችላል። በጣም ቅር ብትሰኙም እንኳ በአሽሙር ወይም በንቀት ላለመናገር አሊያም ላለመጮኽ ጥረት አድርጉ። “ለእኔ ግድ የለህም” ወይም “አንድ ቀን እንኳ በሥርዓት አዳምጠሽኝ አታውቂም” እንደሚሉት ያሉ ጎጂ ንግግሮችን አስወግዱ። ከዚህ ይልቅ የትዳር ጓደኛችሁ ባደረገው ነገር የተነሳ ምን እንደተሰማችሁ ረጋ ባለ መንፈስ ተናገሩ (“. . . ስታደርግ ይከፋኛል”)። መገፍተርንና በጥፊ ወይም በእርግጫ መምታትን ጨምሮ በትዳር ጓደኛችሁ ላይ ማንኛውንም ዓይነት አካላዊ ጥቃት መሰንዘር ፈጽሞ ተገቢ አይደለም። መሳደብ፣ መዝለፍና መዛትም ቢሆን ተቀባይነት የለውም።

      “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ እንዲሁም ክፋት ሁሉ ከእናንተ መካከል ይወገድ።”—ኤፌሶን 4:31

      6. ይቅርታ ለመጠየቅ ፈጣን ሁኑ፤ ችግሩን ለመፍታት ምን ለማድረግ እንደወሰናችሁ ተናገሩ።

      አሉታዊ ስሜቶች ግባችሁን እንድትዘነጉ ሊያደርጓችሁ አይገባም፤ ግባችሁ ሰላም መፍጠር ነው። ከአንድ ሰው ጋር ከተጣላችሁ ሁለታችሁም ተሸናፊ ናችሁ። ሰላም ከፈጠራችሁ ግን ሁለታችሁም ታሸንፋላችሁ። በመሆኑም ለተፈጠረው ግጭት የእናንተም ጥፋት እንዳለበት አምናችሁ ተቀበሉ። ምንም ጥፋት እንደሌለባችሁ ቢሰማችሁም እንኳ ስለተቆጣችሁ፣ ጥሩ ያልሆነ ምላሽ ስለሰጣችሁ ወይም ሆን ብላችሁ ባይሆንም ሌላኛውን ግለሰብ ስላበሳጫችሁት ይቅርታ ልትጠይቁ ትችላላችሁ። በኩራት የተነሳ ከማኩረፍ ወይም ተከራክሮ ከማሸነፍ ይልቅ አስፈላጊ የሆነው ሰላም መፍጠር እንደሆነ አትዘንጉ። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ይቅርታ ከጠየቃችሁ ይቅር ለማለት ፈጣን ሁኑ።

      “ሂድና ባልንጀራህን በትሕትና አጥብቀህ ለምነው።”—ምሳሌ 6:3

      ክርክሩ ካበቃ በኋላ በቤታችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ምን ማድረግ ትችላላችሁ? የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።

  • በቤተሰብ መካከል ሰላም ማስፈን የሚቻልበት መንገድ
    ንቁ!—2015 | ታኅሣሥ
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ

      በቤተሰብ መካከል ሰላም ማስፈን የሚቻልበት መንገድ

      መጽሐፍ ቅዱስ በቤት ውስጥ ሰላም ለማስፈን ሊረዳ ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር ቀጥሎ የተጠቀሱት ሰዎች ከተናገሩት ጠቃሚ ሐሳብ ጋር እንድታወዳድሩ እንጋብዛችኋለን። ግጭትን ለማስወገድ፣ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ እንዲሁም ዘላቂ ትስስር ለመፍጠር የሚረዷችሁን ነጥቦች ለማግኘት ሞክሩ።

      ሰላም ለማስፈን የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች

      አንዳችሁ ለሌላው ጥሩ አመለካከት አዳብሩ።

      በባሕር ዳርቻ እየተዝናና ያለ ቤተሰብ

      “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ፤ ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:3, 4

      “የትዳር ጓደኛችንን ከራሳችንም ሆነ ከሌሎች አስበልጠን መመልከት ጥሩ እንደሆነ ተገንዝበናል።”—ሲ. ፒ. ለ19 ዓመታት በትዳር የኖረች

      አፍራሽ አስተሳሰብ ሳትይዙ በጥሞና አዳምጡ።

      “ጠበኞች እንዳይሆኑ ከዚህ ይልቅ ምክንያታዊ እንዲሆኑና ለሰው ሁሉ ገርነትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያንጸባርቁ አሳስባቸው።”—ቲቶ 3:2

      “የትዳር ጓደኛችንን በሚያበሳጭ መንገድ ከማናገር መቆጠባችን በመካከላችን ውጥረት እንዳይፈጠር ይረዳል። በተናገረው ሐሳብ ባንስማማም እንኳ ጭፍን ሳንሆን ማዳመጣችንና አመለካከቱን ማክበራችን አስፈላጊ ነው።”—ፒ. ፒ. ለ20 ዓመታት በትዳር የኖረች

      ታጋሽና ገር ሁኑ።

      “በትዕግሥት አዛዥን ማሸነፍ ይቻላል፤ ለስላሳም [“የገራም፣” የ1954 ትርጉም] አንደበት አጥንትን ይሰብራል።”—ምሳሌ 25:15

      “ግጭት መፈጠሩ አይቀርም፤ ሆኖም ውጤቱ የተመካው በምናሳየው ባሕርይ ላይ ነው። ምንጊዜም ታጋሾች መሆን አለብን። ምክንያቱም ታጋሽ ከሆንን ችግሮቹን መፍታት እንችላለን።”—ጂ. ኤ. ለ27 ዓመታት በትዳር የኖረች

      ጎጂ ቃላትም ሆነ አካላዊ ጥቃት አትሰንዝሩ።

      “ቁጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትንና ስድብን ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ፤ ጸያፍ ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ።”—ቆላስይስ 3:8

      “ባለቤቴ ራሱን የሚቆጣጠር በመሆኑ አደንቀዋለሁ። ሁልጊዜ የተረጋጋ ሲሆን ጮኾብኝም ሆነ ሰድቦኝ አያውቅም።”—ቢ. ዲ. ለ20 ዓመታት በትዳር የኖረች

      ይቅርታ ለማድረግና አለመግባባቶችን ለመፍታት ፈጣን ሁኑ።

      “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።”—ቆላስይስ 3:13

      “ውጥረት ውስጥ ስትሆኑ መረጋጋት ቀላል አይደለም፤ ሳታስቡት የትዳር ጓደኛችሁን የሚጎዳ ነገር ልትናገሩ ወይም ልታደርጉ ትችላላችሁ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲገጥማችሁ ይቅር መባባል በጣም ጠቃሚ ነው። ይቅር የማትባባሉ ከሆነ ትዳራችሁ ሊሰምር አይችልም።”—ኤ. ቢ. ለ34 ዓመታት በትዳር የኖረች

      በልግስና የመስጠትና ያላችሁን የማካፈል ልማድ ይኑራችሁ።

      “ለሰዎች ስጡ፤ እነሱም ይሰጧችኋል። . . . በምትሰፍሩበት መስፈሪያ መልሰው ይሰፍሩላችኋልና።”—ሉቃስ 6:38

      “ባለቤቴ ምን እንደሚያስደስተኝ ስለሚያውቅ ሁሌ ያልጠበቅኳቸውን ነገሮች ያደርግልኛል። እኔም እንዴት ላስደስተው እንደምችል አስባለሁ። በዚህም የተነሳ አሁንም ድረስ በጣም ደስተኞች ነን።”—ኤች. ኬ. ለ44 ዓመታት በትዳር የኖረች

      ሰላም ለማስፈን የምታደርጉትን ጥረት አታቋርጡ

      ንቁ! ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው ሰዎች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ ተጠቅመው በቤተሰባቸው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የሚረዱ ባሕርያትን ካዳበሩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።a እነዚህ ሰዎች፣ ከቤተሰባቸው አባላት መካከል አንዳንዶቹ ሰላማዊ ለመሆን ጥረት ባያደርጉም እንኳ ሰላም ፈጣሪ መሆን እንደሚክስ ተገንዝበዋል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ሰላምን የሚያራምዱ . . . ደስተኞች ናቸው” ይላል።—ምሳሌ 12:20

      a የቤተሰብን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 14 ተመልከት፤ መጽሐፉ www.pr2711.com/am ላይም ይገኛል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ለቤተሰብ በሚለው ሥር የወጡ ርዕሶችን ተመልከት።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ