-
ልማዶችህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?ንቁ!—2016 | ቁጥር 4
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
ልማዶችህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
ኦስቲን ማለዳ ላይ ከእንቅልፉ እንዲቀሰቅሰው የሞላው ሰዓት ሲጮኽ በደንብ ባይነቃም ከአልጋው ዘሎ በመውረድ ማታ ያዘጋጀውን የስፖርት ልብስ ከለባበሰ በኋላ ደጅ ወጥቶ ይሮጣል፤ በሳምንት ሦስት ጊዜ የሚሮጥ ሲሆን ይህን ማድረግ ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል።
ሎሪ ከባለቤቷ ጋር ተጣልታለች። በሁኔታው በጣም ስለተበሳጨች ወደ ኩሽናዋ ሄዳ የታሸገ ቸኮሌት በማውጣት ሙሉውን በላችው፤ በተበሳጨች ቁጥር እንዲህ የማድረግ ልማድ አላት።
ኦስቲን እና ሎሪ የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው? አወቁትም አላወቁት፣ ልማድ በሁለቱም ሕይወት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።
አንተስ? በሕይወትህ ውስጥ ልታዳብራቸው የምትፈልጋቸው ጥሩ ልማዶች አሉ? ምናልባትም አዘውትረህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ፣ በቂ እንቅልፍ የማግኘት ወይም ቤተሰብህን አዘውትረህ የመጠየቅ ግብ ይኖርህ ይሆናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሲጋራ ማጨስን፣ ለጤና ጠቃሚ ያልሆኑ ምግቦች በብዛት መብላትን ወይም ኢንተርኔት በመቃኘት ብዙ ጊዜ ማሳለፍን የመሳሰሉ መጥፎ ልማዶችን ማስወገድ ትፈልግ ይሆናል።
መጥፎ ልማድን ማሸነፍ ከባድ ሊሆን እንደሚችል አይካድም። እንዲያውም መጥፎ ልማድ፣ በብርድ ቀን የሞቀ አልጋ ውስጥ የመግባትን ያህል ቀላል እንደሆነ ይነገራል፤ ከሞቀ አልጋ መውጣት ከባድ እንደሆነ ሁሉ ከመጥፎ ልማድ መላቀቅም አስቸጋሪ ነው!
ልማዶችህን መቆጣጠር ብሎም ጠቃሚ እንጂ ጎጂ እንዳይሆኑብህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የቀረቡትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ መመሪያዎች ላይ የተመሠረቱ ሦስት ነጥቦች እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
-
-
1 ምክንያታዊ ሁንንቁ!—2016 | ቁጥር 4
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ልማዶችህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
1 ምክንያታዊ ሁን
በሕይወትህ ውስጥ ማድረግ የምትፈልጋቸውን ለውጦች በሙሉ ወዲያውኑ ለማድረግ ትጓጓ ይሆናል። “በዚህ ሳምንት ማጨስ አቆማለሁ፣ መሳደብ እተዋለሁ፣ በጊዜ መተኛት እጀምራለሁ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እጀምራለሁ፣ አመጋገቤን አስተካክላለሁ እንዲሁም ለአያቶቼ ስልክ እደውላለሁ” ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ግቦችህን ሁሉ በአንድ ጊዜ ለማሳካት የምትሞክር ከሆነ አንዱም ላይ ሳትደርስ ትቀራለህ!
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።”—ምሳሌ 11:2
ልኩን የሚያውቅ ሰው ምክንያታዊ ነው። ጊዜውም ሆነ ጉልበቱ እንዲሁም ያሉት ቁሳዊ ነገሮች ውስን እንደሆኑ ይገነዘባል። በመሆኑም ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለመቀየር ከመሞከር ይልቅ ቀስ በቀስ ማሻሻያ ለማድረግ ይጥራል።
ግቦችህን ሁሉ በአንድ ጊዜ ለማሳካት የምትሞክር ከሆነ አንዱም ላይ ሳትደርስ ትቀራለህ!
ምን ማድረግ ትችላለህ?
በአንድ ጊዜ፣ አንድ ወይም ሁለት ልማዶችን ለማዳበር አሊያም ለማስወገድ ጥረት አድርግ። በዚህ ረገድ ቀጥሎ የቀረቡት ነጥቦች ሊረዱህ ይችላሉ፦
ልታዳብራቸው የምትፈልጋቸውን ጥሩ ልማዶችም ሆነ ልታስወግዳቸው የምትፈልጋቸውን መጥፎ ልማዶች በሁለት ረድፍ ዘርዝረህ ጻፋቸው። የተወሰኑ ልማዶችን ብቻ መጻፍ እንዳለብህ አይሰማህ፤ በእያንዳንዱ ዝርዝር ላይ ወደ አእምሮህ የመጣውን ልማድ ሁሉ ጻፍ።
በጻፍከው ዝርዝር ላይ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ለይ፤ ትልቅ ቦታ ከምትሰጣቸው ጀምረህ በቅደም ተከተል አስፍራቸው።
በእያንዳንዱ ረድፍ ላይ ካሰፈርካቸው ልማዶች መካከል አንድ ወይም ሁለቱን ምረጥና በእነዚህ ላይ ለመሥራት ጥረት አድርግ። ከዚያ በኋላ በዝርዝርህ ላይ ባሰፈርካቸው ሌሎች ልማዶች ላይ ትኩረት ማድረግ ትችላለህ።
መጥፎ ልማዶችህን በጥሩ ልማዶች መተካትህ፣ ልማዶችህን ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሳካልህ ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ቴሌቪዥን በመመልከት ብዙ ጊዜ የማጥፋት ልማድህን ማስወገድ እንዲሁም ቤተሰብህን አዘውትረህ የመጠየቅ ልማድ ማዳበር ትፈልግ ይሆናል፤ ‘በየዕለቱ ከሥራ ወደ ቤቴ እንደገባሁ ቴሌቪዥን ከመክፈት ይልቅ አንድ ጓደኛዬ ወይም የቤተሰቤ አባል ጋ ደውዬ አዋራቸዋለሁ’ የሚል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።
-
-
2 አመቺ ሁኔታዎችን ፍጠርንቁ!—2016 | ቁጥር 4
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ልማዶችህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
2 አመቺ ሁኔታዎችን ፍጠር
አመጋገብህን ለማስተካከል ቆርጠሃል፤ ሆኖም አይስክሬሙን ስታይ ትፈተናለህ።
ማጨስ ለማቆም ወስነሃል፤ ይሁንና ጓደኛህ ውሳኔህን እያወቀ ሲጋራ ሰጠህ።
ከዛሬ ጀምረህ ስፖርት ለመሥራት ወስነሃል፤ ይሁን እንጂ ከቁም ሣጥንህ ውስጥ የስፖርት ጫማህን መፈለግ በራሱ ትልቅ ሥራ ሆኖብሃል!
ከላይ የተገለጹትን ሁኔታዎች የሚያመሳስላቸው ምን እንደሆነ ልብ ብለሃል? በተደጋጋሚ እንደታየው፣ ያለንበት ሁኔታና አብረናቸው ጊዜ የምናሳልፋቸው ሰዎች ጥሩ ልማዶችን ማዳበርም ሆነ መጥፎ ልማዶችን ማሸነፍ እንድንችል ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”—ምሳሌ 22:3
መጽሐፍ ቅዱስ አርቀን እንድናስብ ይመክረናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ግባችን ላይ እንዳንደርስ እንቅፋት የሚሆኑ ሁኔታዎችን ማስወገድና ለግባችን መሳካት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንችላለን። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) በአጭር አነጋገር፣ አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር የጥበብ አካሄድ ነው።
መጥፎ የሆነውን ማድረግ ከባድ እንዲሆንብህ፣ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ደግሞ ቀላል እንዲሆንልህ አድርግ
ምን ማድረግ ትችላለህ?
መጥፎ የሆነውን ማድረግ ከባድ እንዲሆንብህ አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ ለጤና የማይጠቅሙ ምግቦችን ማስወገድ የምትፈልግ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ምግቦች ቤትህ ውስጥ እንዳይኖሩ አድርግ። ይህን ማድረግህ፣ እንዲህ ዓይነቱን ምግብ መብላት ቢያምርህም እንኳ ምግቡን ማግኘት ቀላል ስለማይሆን ጠቃሚ ያልሆነ ምግብ ከመብላት ትቆጠባለህ።
ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ቀላል እንዲሆንልህ አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ ጠዋት ከእንቅልፍህ እንደተነሳህ ስፖርት ለመሥራት ግብ ካወጣህ ማታ ከመተኛትህ በፊት የስፖርት ልብስህን አዘጋጅተህ እደር። ማዳበር የምትፈልገውን ልማድ መጀመሩ ቀላል እንዲሆንልህ ካደረግክ ይህን ልማድ ይዞ መቀጠሉ ብዙም አይከብድህም።
ጓደኞችህን በጥንቃቄ ምረጥ። ብዙውን ጊዜ አብረናቸው የምንሆነውን ሰዎች መምሰል ይቀናናል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ስለዚህ ልታስወግደው የምትፈልገውን ልማድ እንድትቀጥልበት ከሚያበረታቱህ ሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት ላይ ገደብ አብጅ፤ እንዲሁም ጥሩ ልማዶችን እንድታዳብር ከሚረዱህ ሰዎች ጋር ተቀራረብ።
-
-
3 ተስፋ አትቁረጥንቁ!—2016 | ቁጥር 4
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ልማዶችህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
3 ተስፋ አትቁረጥ
‘አዲስ ልማድ ለማዳበር 21 ቀናት ይፈጃል’ የሚል የተለመደ አባባል አለ። እውነታው ሲታይ ግን አንዳንድ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ጉልህ ለውጥ ለማድረግ ከዚህ ያነሰ ጊዜ የሚፈጅባቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ የበለጠ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ይህ ተስፋ ሊያስቆርጥህ ይገባል?
እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ አስብ፦ በሳምንት ሦስት ቀን ስፖርት የመሥራት ልማድ ማዳበር ትፈልጋለህ እንበል።
በመጀመሪያው ሳምንት ግብህን ማሳካት ቻልክ።
በሁለተኛው ሳምንት ስፖርት የሠራኸው ሁለት ቀን ብቻ ነው።
በሦስተኛው ሳምንት እንደገና ግብህ ላይ መድረስ ቻልክ።
በአራተኛው ሳምንት ስፖርት የሠራኸው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
በአምስተኛው ሳምንት ግብህን እንደገና አሳካህ፤ ከዚያ በኋላም በየሳምንቱ ስፖርት መሥራትህን ቀጠልክ።
አዲሱን ልማድህን ለማዳበር አምስት ሳምንት ወሰደብህ። ይህ ረጅም ጊዜ ቢመስልም ግብህ ላይ መድረስ ከቻልክ በኋላ ግን አዲስ ልማድ በማዳበርህ ደስ ይልሃል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ መልሶ ይነሳል።”—ምሳሌ 24:16
መጽሐፍ ቅዱስ ቶሎ ተስፋ እንዳንቆርጥ ያበረታታል። ዋናው ነገር፣ ምን ያህል ጊዜ ወደቅን የሚለው ጉዳይ ሳይሆን ምን ያህል ጊዜ መልሰን ተነሳን የሚለው ነው።
ዋናው ነገር፣ ምን ያህል ጊዜ ወደቅን የሚለው ጉዳይ ሳይሆን ምን ያህል ጊዜ ተነሳን የሚለው ነው
ምን ማድረግ ትችላለህ?
መጥፎ ልማድህ ስላገረሸብህ ይህን ልማድ ጨርሶ ማስወገድ አትችልም ማለት አይደለም። ግብህ ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ አንዳንድ እንቅፋቶች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉ መጠበቅ ይኖርብሃል።
ግብህ ላይ መድረስ የቻልክባቸውን ጊዜያት መለስ ብለህ አስብ። ለምሳሌ ያህል፣ ከልጆችህ ጋር የምትነጋገርበትን መንገድ ለማሻሻል እየጣርክ ከሆነ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በልጆቼ ተናድጄ እነሱ ላይ ለመጮኽ ቢቃጣኝም ይህን ከማድረግ የተቆጠብኩት መቼ ነበር? በእነሱ ላይ ከመጮኽ ይልቅ ምን አድርጌያለሁ? አሁንም እንዲህ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ እንደነዚህ ያሉት ጥያቄዎች፣ ግብህን እንዳታሳካ ያደረጉህን እንቅፋቶች እያሰብክ ከመብሰልሰል ይልቅ ባደረግከው መልካም ነገር ላይ ለማተኮር ይረዱሃል።
በሌሎች የሕይወት ዘርፎች ለምሳሌ ጭንቀትን መቋቋም፣ ደስተኛ ቤተሰብ መገንባትና እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻልባቸውን መንገዶች በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እንዴት ሊረዱህ እንደሚችሉ ማወቅ ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮችን ማናገር ወይም jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን መመልከት ትችላለህ።
-