የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ከጥንት ጀምሮ የነበረውን መሰናክል ማለፍ
    ንቁ!—2016 | ቁጥር 3
    • የተለያየ ዘርና ብሔር ያላቸው ሰዎች

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የቋንቋ ልዩነት—መሰናክሎቹና መፍትሔው

      ከጥንት ጀምሮ የነበረውን መሰናክል ማለፍ

      በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ 7,000 ያህል ቋንቋዎች አሉ፤ የእነዚህ ቋንቋዎች ብዛትና የቋንቋዎቹ ባሕርይ መለያየት ጉዞ፣ ንግድ፣ ትምህርትና አስተዳደር አስቸጋሪ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። ይህ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ችግር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በ475 ዓ.ዓ. ገደማ ፋርሳውያን በንጉሥ አሐሽዌሮስ (ቀዳማዊ ጠረክሲስ ሳይሆን አይቀርም) አገዛዝ ሥር ንጉሣዊ አዋጆችን በፋርስ ግዛት ለነበሩት ሕዝቦች አስተላልፈዋል፤ “ከሕንድ አንስቶ እስከ ኢትዮጵያ ላሉት 127 አውራጃዎች . . . ጻፉ፤ ለእያንዳንዱ አውራጃ በራሱ ጽሑፍ፣ ለእያንዳንዱም ሕዝብ በራሱ ቋንቋ ተጻፈለት።”a

      በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ድርጅቶች አልፎ ተርፎም መንግሥታት እንዲህ ዓይነቱን ከባድ ሥራ ሊሠሩት ቀርቶ ሊሞክሩት እንኳ አልቻሉም። ሆኖም ይህን ሥራ በተሳካ ሁኔታ ማከናወን የቻለ አንድ ድርጅት አለ። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሔቶችን፣ የኦዲዮ ቪዲዮ ፕሮግራሞችን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ በርካታ መጻሕፍትን በድምሩ ከ750 በሚበልጡ ቋንቋዎች ያዘጋጃሉ። ይህም 80 የሚያህሉ የምልክት ቋንቋዎችን ይጨምራል። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ለዓይነ ስውራን የተለያዩ ጽሑፎችን በብሬይል ያዘጋጃሉ።

      የሚያስገርመው ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ሥራ የሚያከናውኑት የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት ብለው አለመሆኑ ነው። እንዲያውም ተርጓሚዎቹም ሆኑ ሌሎች ሥራዎችን የሚያከናውኑት ሰዎች በሙሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎችን በበርካታ ቋንቋዎች ለመተርጎም ይህን ያህል ጥረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው? የትርጉም ሥራቸውን የሚያከናውኑትስ እንዴት ነው?

      a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቴር 8:9⁠ን ተመልከት።

  • የቋንቋ ልዩነት—መሰናክሎቹና መፍትሔው—የትርጉም ሥራው ምን ይመስላል?
    ንቁ!—2016 | ቁጥር 3
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

      የቋንቋ ልዩነት—መሰናክሎቹና መፍትሔው—የትርጉም ሥራው ምን ይመስላል?

      “አንዳንድ ሰዎች ከትርጉም ሥራ ይበልጥ የተወሳሰበ ሥራ እንደሌለ ይናገራሉ።”—“ዘ ካምብሪጅ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ላንግዌጅ”

      የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸው ጽሑፎች የሚጻፉት በጥንቃቄ ታስቦባቸውና ምርምር ተደርጎባቸው ነው፤ ከዚያም ለትርጉም ይላካሉ። ጽሑፎቹ በሚዘጋጁበት ወቅት ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ያለው የጽሑፍ ዝግጅት ክፍል፣ የተጻፈው መረጃ ትክክል፣ በቀላሉ የሚገባና የቋንቋውን የሰዋስው ሕግ የጠበቀ መሆኑን በጥንቃቄ ይመረምራል።a

      ከዚያም የጽሑፍ ዝግጅት ክፍሉ በመላው ዓለም ለሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትርጉም ቡድኖች ጽሑፉን ይልከዋል፤ አብዛኞቹ ተርጓሚዎች የሚኖሩትና የሚሠሩት ጽሑፉን የሚተረጉሙበት ቋንቋ በሚነገርበት አካባቢ ነው። ብዙዎቹ የሚተረጉሙት ወደ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ነው። ተርጓሚዎቹ የመጀመሪያውን ጽሑፍ ሐሳብም ሆነ የሚተረጉሙበትን ቋንቋ በደንብ ማወቅ አለባቸው።

      አንድ የትርጉም ቡድን ሥራውን ሲያከናውን

      የትርጉም ሥራ የሚከናወንበት ሂደት

      ይህ ሥዕላዊ መግለጫ ንቁ! መጽሔት ወደ ስፓንኛ ሲተረጎም ያለውን ሂደት የሚያሳይ ነው

      • በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው የመጀመሪያው ጽሑፍ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ስፔን ውስጥ ላለ አንድ የትርጉም ቡድን ይላካል

      • እያንዳንዱ የቡድኑ አባል ጽሑፉን በጥንቃቄ ይመረምራል

      • ቡድኑ መተርጎም ከመጀመሩ በፊት በጽሑፉ ላይ ለመወያየት ይገናኛል

      • ተርጓሚዎቹ የተረጎሙት ጽሑፍ የቋንቋውን ለዛ የጠበቀ፣ ግልጽ፣ ዋናው ጽሑፍ የያዘውን መልእክት የሚያስተላልፍና ከሰዋስው አንጻር ትክክል መሆኑን ያረጋግጣሉ

      • የትርጉም ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የተተረጎመው ጽሑፍ የሕትመትና የስርጭት ሥራ ወደሚሠራባቸው የተለያዩ ቦታዎች ይላካል

      • በመላው ዓለም የሚገኙ አንባቢያን በቋንቋቸው ተዘጋጅቶ ከሚቀርበው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጠቃሚና ጥበብ ያዘለ ምክር ጥቅም ማግኘት ችለዋል

      ተርጓሚዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት እንዴት ነው?

      በብሪታንያ ሆኖ የትርጉም ሥራ የሚሠራው ጌሬንት እንዲህ ይላል፦ “የትርጉም ሥራውን የምናከናውነው በቡድን ነው። ስለዚህ የትብብር መንፈስ ሊኖረን ይገባል። በትርጉም ሥራው ላይ ችግር ሲያጋጥመን በኅብረት መፍትሔ እንፈልጋለን። እንዲህ በምናደርግበት ጊዜ ትኩረት የምናደርገው ቃላት ላይ ሳይሆን ሐረጎች ላይ ነው። የሐረጎቹን ትክክለኛ ትርጉምና ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት በጥንቃቄ እናስባለን፤ ጽሑፉ የተዘጋጀው እነማንን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነም አንዘነጋም።”

      የተርጓሚዎች ግብ ምንድን ነው?

      “ግባችን አንባቢው ጽሑፉ የተዘጋጀው በአፍ መፍቻ ቋንቋው እንደሆነ እንዲሰማው ማድረግ ነው። ሲያነበው የተተረጎመ እንደሆነ ሊሰማው አይገባም። ለዚህም ሲባል የቋንቋውን ለዛ የጠበቁ አገላለጾችን ለመጠቀም እንሞክራለን። አንድ ሰው ጣፋጭ ምግብ ሲበላ ደስ ብሎት እንደሚያጣጥም ሁሉ እኛም ጽሑፉን በዚህ መንገድ ማዘጋጀታችን የአንባቢውን ትኩረት ለመያዝ ያስችለናል።”

      ቋንቋው በሚነገርበት አካባቢ መኖር ምን ጥቅሞች አሉት?

      “ቋንቋው በሚነገርበት አካባቢ መኖር ለሰዎቹ ግልጽ በሆነ መንገድ ለመተርጎም ይረዳል። በዚህ አካባቢ በየቀኑ ቋንቋው ሲነገር የምንሰማበት አጋጣሚ አለን። በተጨማሪም አንዳንድ ቃላት ወይም አገላለጾች የቋንቋውን ለዛ የጠበቁ፣ ለመረዳት የማይከብዱና ማራኪ መሆናቸውን ለማወቅ ሰዎቹ ላይ መሞከር እንችላለን። ይህም የመጀመሪያውን ጽሑፍ ትክክለኛ መልእክት ለማስተላለፍ ይረዳናል።”

      ሥራችሁን የምታደራጁት እንዴት ነው?

      “ለእያንዳንዱ የትርጉም ፕሮጀክት አንድ ቡድን ይመደባል። በመጀመሪያ ሁሉም የቡድኑ አባላት ጽሑፉን በሚገባ ያነብቡታል፤ ይህን የሚያደርጉት የጽሑፉን መልእክትና መሠረታዊ አወቃቀር ለመረዳት እንዲሁም ጽሑፉ የተዘጋጀው እነማንን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ለማወቅ ነው። ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን እንጠይቃለን፦ ‘ይህ ርዕስ የተዘጋጀው ለምንድን ነው? ጭብጡና ዓላማው ምንድን ነው? ከዚህ ርዕስ ምን ትምህርት አገኛለሁ?’ እንዲህ ማድረጋችን አእምሯችንን ለሥራው ያዘጋጀዋል።

      “ቀጥሎ፣ የቡድኑ አባላት ሐሳባቸውን ይለዋወጣሉ፤ ይህ ደግሞ አንዳቸው ከሌላው እንዲማሩ ያስችላቸዋል። ‘የጽሑፉን ሐሳብና መልእክት ተረድተነዋል? በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ ያለውን የአጻጻፍ ስልት መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?’ ዓላማችን ጽሑፉ በተዘጋጀበት ቋንቋ እንዲተላለፍ የተፈለገው ስሜት በሌሎች ቋንቋዎችም እንዲተላለፍ ማድረግ ነው።”

      የቡድኑ አባላት አብረው የሚሠሩት እንዴት ነው?

      “ዓላማችን አንባቢያን ጽሑፉን ሲያነብቡት ወዲያውኑ እንዲገባቸው ማድረግ ነው። ለዚህም ሲባል የተተረጎመውን እያንዳንዱን አንቀጽ ጮክ ብለን በተደጋጋሚ እናነበዋለን።

      “ተርጓሚው በምንተረጉምበት ቋንቋ አንቀጹን በኮምፒውተር ላይ ሲጽፍ ሌሎቻችን በየራሳችን ኮምፒውተር ላይ እንከታተላለን። እንዲሁም ሳይተረጎም የቀረ ወይም የተጨመረ ሐሳብ ካለ እናጣራለን። በተጨማሪም በሐሳቡ ፍሰት፣ በፊደል ግድፈትና በሰዋስው ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ከዚያም አንዳችን አንቀጹን ጮክ ብለን እናነበዋለን። የሚያነበው ሰው ከተደነቃቀፈ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ እንሞክራለን። ሙሉው ርዕስ ተተርጉሞ ካለቀ በኋላ ደግሞ አንድ የቡድኑ አባል ጮክ ብሎ ሲያነብ ሌሎቹ ማስታወሻ ይዘው መስተካከል ያለበት ነገር ላይ ምልክት ያደርጋሉ።”

      ከባድ ሥራ ይመስላል!

      “አዎ፣ ከባድ ነው! ሙሉ ቀን ስንሠራ ስለምንውል ይደክመናል። ስለዚህ እረፍት ካደረግን በኋላ በማግስቱ የተረጎምነውን ጽሑፍ በድጋሚ እንመለከተዋለን። ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ደግሞ የጽሑፍ ዝግጅት ክፍሉ በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ ያደረገውን የመጨረሻ ማስተካከያ ይልክልናል። ከዚያም የተረጎምነውን ጽሑፍ እንደገና በአዲስ አእምሮ በማንበብ የትርጉሙን ጥራት እናሻሽለዋለን።”

      ምን ዓይነት የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ትጠቀማላችሁ?

      “እርግጥ ኮምፒውተሮች አሁንም ቢሆን በመተርጎም ረገድ ሰዎችን መተካት አልቻሉም። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች የትርጉም ሥራውን የሚያቀላጥፉ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን አዘጋጅተዋል። አንዱ ፕሮግራም በተደጋጋሚ የምንጠቀምባቸውን ቃላትና ሐረጎች የምናሰባስብበት መዝገበ ቃላት ነው። ሌላው ደግሞ እስከ አሁን ድረስ በትርጉም ቡድናችን የተዘጋጁ ጽሑፎችን እንድናገኝ የሚረዳ ፕሮግራም ነው፤ ይህም ለመተርጎም ከባድ የሆኑ አገላለጾች ከዚህ በፊት እንዴት እንደተተረጎሙ ለማየት ያስችለናል።”

      ስለ ሥራችሁ ምን ይሰማችኋል?

      “ሥራችንን የምንመለከተው ለሕዝቡ እንደምንሰጠው ስጦታ አድርገን ነው። ይህን ስጦታ ባማረ ሁኔታ ጠቅልለን መስጠት እንፈልጋለን። በመጽሔት ወይም በድረ ገጽ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ የአንባቢውን ልብ ነክቶት ሕይወቱን ሊያሻሽልለት እንደሚችል ማሰቡ በራሱ በጣም ያስደስታል።”

      ዘላቂ ጥቅሞች

      በምድር ዙሪያ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጇቸውን ጽሑፎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በማንበብ ጥቅም ማግኘት ችለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በጽሑፎቻቸውና በቪዲዮዎቻቸው፣ እንዲሁም jw.org በተሰኘው ድረ ገጻቸው ላይ የሚያቀርቡት ጠቃሚና ጥበብ ያዘለ ምክር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው። ደግሞም ስሙ ይሖዋ የሆነው አምላካችን መልእክቱን ለሁሉም “ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ” እንድናውጅ የሚፈልግ መሆኑን በዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ ገልጿል።—ራእይ 14:6b

      a የመጀመሪያው ጽሑፍ የሚዘጋጀው በእንግሊዝኛ ነው።

      b በራስህ ቋንቋና በመቶዎች በሚቆጠሩ ሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችንና የኦዲዮ ቪዲዮ ፕሮግራሞችን ለማግኘት www.pr2711.comን እንድትጎበኝ እንጋብዝሃለን።

      JW.ORG

      የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ድረ ገጽ

      ከ700 በሚበልጡ ቋንቋዎች

      አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ

      የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጁት ብሮሹር

      ከ640 በሚበልጡ ቋንቋዎች

      መጠበቂያ ግንብ

      የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁት መጽሔት

      ከ250 በሚበልጡ ቋንቋዎች

      ንቁ!

      የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁት መጽሔት

      ከ100 በሚበልጡ ቋንቋዎች

      በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ንቁ! መጽሔት

      “የጤና ችግር አለብኝ። ሐኪሜ ከሚያደርግልኝ እንክብካቤ በተጨማሪ ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን ሐሳብ በቋንቋዬ በማላጋሲ ማንበቤ ጠቅሞኛል። ንቁ! ግልፍተኝነቴን መቆጣጠር እንድችል ረድቶኛል። በተጨማሪም መጽሔቱ ጤናማ ስለሆነ አመጋገብና ስለ አካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚናገር ሐሳብ ይዟል።c ያነበብኩትን ምክር በሥራ ላይ በማዋሌ ጤንነቴ እየተሻሻለ ነው።”—ራናይቭዋሪሶ፣ ማዳጋስካር

      “ሐኪሜ ለሌሎች ስለ ጤና ለማስተማር በጉጅራቲ ቋንቋ የተዘጋጁ በንቁ! መጽሔት ላይ የወጡ ርዕሶችን ትጠቀማለች። ዕፆችንና የአልኮል መጠጥን አላግባብ ስለመጠቀም ከንቁ! ያገኘችውን ሐሳብ በትምህርት ቤት ከተናገረች ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፣ ተማሪዎቹ አባቶቻቸው መጽሔቱ ላይ በወጣው ሐሳብ የተነሳ ለአልኮል መጠጥ የሚያወጡትን ገንዘብ ቀንሰው ለእነሱ እንዳዋሉት ተናግረዋል።”—ጃኔት፣ ሕንድ

      c ንቁ! አንድን ዓይነት አመጋገብ ወይም የጤና አጠባበቅ ዘዴ ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም። እያንዳንዱ ግለሰብ ስለ አመጋገብም ሆነ ስለ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት፣ ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ መመዘን ይኖርበታል።

      አንድ ልጅ መስረቅ መጥፎ ነው የተባለውን ቪዲዮ jw.org ላይ እየተመለከተ

      ንቁ! በአንጎላ ከምትኖር እንዲት እናት እንዲህ የሚል ሪፖርት ደርሶታል፦ “የስምንት ዓመት ልጄ እርሳሶቹ ስለጠፉበት ከክፍሉ ልጆች እርሳስ ሰረቀ። መስረቅ መጥፎ ነው የሚለውን በjw.org ላይ የሚገኝ ቪዲዮ በፖርቱጋልኛ ከተመለከተ በኋላ ግን መስረቁን እንደምንም ተደፋፍሮ ነገረኝ። ከዚያም የክፍሉን ልጆች ይቅርታ ለመጠየቅና እርሳሶቻቸውን የሚመልስላቸው ለምን እንደሆነ ለመንገር ወሰነ፤ በዚህ ወቅት አብሬው እንድሄድ ጠየቀኝ። አስተማሪው ቪዲዮውን ለክፍሉ ልጆች በሙሉ እንድናሳይ ፈቀደልን። ቪዲዮውን ካዩ በኋላ ብዙ ተማሪዎች ዳግመኛ እንደማይሰርቁ ተናግረዋል።”

      አንድ ሰው JW Language የተባለውን አፕሊኬሽን ሲጠቀም

      ቋንቋ ለመማር የሚረዳ መሣሪያ!

      የJW Language አርማ

      የይሖዋ ምሥክሮች በ2014 JW Language የሚባል ነፃ የኤሌክትሮኒክ አፕሊኬሽን አውጥተዋል፤ ይህ ፕሮግራም እንደሚከተሉት ባሉ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ይረዳል፦ ሂንዲ፣ ምያንማርኛ፣ ሩሲያኛ፣ ስዋሂሊ፣ ስፓንኛ፣ ቤንጋሊ፣ ቱርክኛ፣ ታይ፣ ታጋሎግ፣ ቻይንኛ፣ ኢንዶኔዥያኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ኮርያኛ፣ ጀርመንኛ፣ ጃፓንኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ፈረንሳይኛና ፖርቱጋልኛ።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ