-
የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ ነው!ንቁ!—2017 | ቁጥር 2
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ምትሃታዊ ድርጊቶች ምን ጉዳት አላቸው?
የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ ነው!
“ቫምፓየሮች፣ ጭራቆችና ዞምቢዎች ጊዜ አልፎባቸዋል፤ አጋንንት ስላደሩባቸው ሰዎች የሚያሳዩና አጋንንትን ስለማስወጣት የሚናገሩ መዝናኛዎች ተወዳጅ እየሆኑ መጥተዋል።” —ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል
አስማተኞች፣ ጠንቋዮችና ቫምፓየሮች የመጻሕፍት፣ የፊልምና የቪዲዮ ጨዋታ ኢንዱስትሪዎችን ካጥለቀለቁ ምትሃታዊ ኃይል ያላቸው ገጸ ባሕርያት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ለመሆኑ እነዚህ መዝናኛዎች ይህን ያህል ተወዳጅ የሆኑት ለምንድን ነው?a
የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ክሎድ ፊሸር እንዲህ ብለዋል፦ “ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በሙታን መናፍስት የሚያምኑ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት፣ በሙታን መናፍስት የሚያምነው ከአሥር አሜሪካውያን አንዱ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን ከሦስት አሜሪካውያን አንዱ በሙታን መናፍስት ያምናል። ከሰው በላይ የሆነ የማወቅ ችሎታ አላቸው የሚባሉ ሰዎችን እንዳማከሩ የሚናገሩ እንዲሁም የሙታን መናፍስት እንዳሉና እነዚህ መናፍስት በአንዳንድ ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ የሚያምኑ ወጣት አሜሪካውያን ቁጥር እንዲህ ያለ አመለካከት ካላቸው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ይበልጣል።”
አጋንንት ስላደሩባቸው ሰዎች የሚናገሩ ታሪኮች በአስደንጋጭ ሁኔታ ዳግም ተወዳጅነት እያገኙ መጥተዋል፤ ይህም የሚያስገርም አይደለም። ማይክል ካሊያ የተባለው ጸሐፊ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል በተባለው መጽሔት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ባለፉት አሥር ዓመታት ዞምቢዎች፣ ጭራቆችና ቫምፓየሮች ሰፊ ተቀባይነት የነበራቸው መሆኑ በአሁኑ ጊዜ በአጋንንት በተያዙ ሰዎች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ታሪኮች ተወዳጅነት እንዲያገኙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።”
አንድ ሪፖርት እንደዘገበው “በዓለም ዙሪያ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል ከ25 እስከ 50 በመቶ የሚሆኑት በሙታን መናፍስት ያምናሉ፤ እንዲሁም በብዙ ባሕሎች ውስጥ ስለ ሙታን መናፍስት የሚናገሩ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች አሉ።” በተጨማሪም የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ክሪስቶፈር ቤደር እና ካርሰን ሜንከን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያካሄዱት ጥናት እንደሚያሳየው “ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን በምትሃታዊ ኃይል ከሚፈጸሙ ድርጊቶች መካከል ቢያንስ በአንዱ ላይ ጠንካራ እምነት አላቸው።”
በእርግጥ ከምትሃታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ባላቸው ነገሮች መካፈል ምንም ጉዳት የለውም?
a በዚህ ርዕስ ውስጥ “ምትሃታዊ ድርጊቶች” የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው በሳይንስ ወይም በተፈጥሮ ሕጎች ሊብራሩ የማይችሉ ክንውኖችን ነው።
-
-
መጽሐፍ ቅዱስ መናፍስታዊ ድርጊቶችን በተመለከተ ምን ያስተምራል?ንቁ!—2017 | ቁጥር 2
-
-
የመዝናኛው ኢንዱስትሪ መናፍስታዊ ድርጊቶችንና እነዚህን ድርጊቶች የሚፈጽሙ ገጸ ባሕርያትን ማራኪ አድርጎ ቢያቀርብም እንዲህ ባሉት ነገሮች መዝናናት አደገኛ እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ምትሃታዊ ድርጊቶች ምን ጉዳት አላቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች ምን ያስተምራል?
ብዙ ሰዎች ምትሃታዊ ወይም መናፍስታዊ ድርጊት የሚባል ነገር እንደሌለ አሊያም የፊልም ደራሲዎች ፈጠራ እንደሆነ ያስባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ የተለየ ሐሳብ ይዟል። የአምላክ ቃል መናፍስታዊ ድርጊቶችን በተመለከተ ግልጽ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘዳግም 18:10-13 እንዲህ ይላል፦ “ሟርተኛ፣ አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ።” መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው ለምንድን ነው? የጥቅሱ ቀጣይ ሐሳብ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ሁሉ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው። . . . በአምላክህ በይሖዋ ፊት እንከን የለሽ ሆነህ መገኘት አለብህ።”
መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት አጥብቆ የሚያወግዘው ለምንድን ነው?
ከበስተጀርባው ያሉት አጋንንት ናቸው
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ምድርን ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ወይም መላእክትን እንደፈጠረ ይናገራል። (ኢዮብ 38:4, 7፤ ራእይ 5:11) አምላክ ለሁሉም መላእክት ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። ሆኖም አንዳንዶቹ መላእክት የመምረጥ ነፃነታቸውን ተጠቅመው በአምላክ ላይ ዓመፁ፤ ከዚያም በሰማይ ላይ የነበራቸውን ቦታ ትተው ወደ ምድር በመምጣት በምድር ላይ ችግር መፍጠር ጀመሩ። በዚህም ምክንያት ምድር ‘በዓመፅ ተሞላች።’—ዘፍጥረት 6:2-5, 11፤ ይሁዳ 6
መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ክፉ መላእክት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደሚያሳስቱ ይናገራል። (ራእይ 12:9) ሌላው ቀርቶ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ያላቸውን ተፈጥሯዊ ጉጉት በመጠቀም ተጽዕኖ ለማሳደር ይሞክራሉ።—1 ሳሙኤል 28:5, 7፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ መናፍስታዊ ድርጊቶች ሰዎችን የሚረዱ ሊመስሉ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 11:14) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የክፉ መላእክት ዓላማ ሰዎችን መርዳት ሳይሆን የሰዎችን አእምሮ በማሳወር ስለ አምላክ እውነቱን እንዳያውቁ ማድረግ ነው።—2 ቆሮንቶስ 4:4
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ከክፉ መናፍስት ጋር ንክኪ ባላቸው ድርጊቶች መካፈል ምንም ጉዳት የሌለው መዝናኛ አይደለም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የመሆን ፍላጎት የነበራቸው በጥንት ዘመን የኖሩ ሰዎችም ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች እውነቱን ሲማሩ ቆራጥ እርምጃ የወሰዱት ለዚህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎች ስለወሰዱት እርምጃ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት . . . አቃጠሉ።” እነዚህ ሰዎች ይህን እርምጃ መውሰዳቸው ትልቅ የገንዘብ ኪሳራ ቢያስከትልባቸውም እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አላሉም።—የሐዋርያት ሥራ 19:19
“በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ በጥንቆላ የሚያምኑ ሴት ልጆች ቁጥር እንዲያድግ ምክንያት የሆነው ጠንቋዮች በቴሌቪዥን፣ በፊልሞችና በመጻሕፍት ላይ ውብና ማራኪ ተደርገው መቅረባቸው ሊሆን ይችላል።” —ጋለፕ ዩዝ ሰርቬይ፣ 2014
በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ካለው ማንኛውም ድርጊት ወይም መዝናኛ ለመራቅ ወስነዋል። ለምሳሌ ማሪያa የ12 ዓመት ልጅ በነበረችበት ወቅት፣ ወደፊት ስለሚፈጸሙ አንዳንድ ክስተቶች ወይም አደጋዎች የማወቅ ችሎታ እንዳላት ይሰማት ነበር። አብረዋት ለሚማሩ ልጆች የጥንቆላ ካርዶችን (ታሮት ካርድ) ታነብላቸው የነበረ ሲሆን የምትተነብየው ነገር እንደሚፈጸም ስታይ ደግሞ በዚህ ድርጊት መካፈሉን ይበልጥ እየወደደችው መጣች።
ማሪያ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችላትን ይህን ስጦታ ያገኘችው ከአምላክ እንደሆነ ተሰምቷት ነበር። ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ የሚረብሸኝ ነገር ግን ነበር። ካርዶቹን ለሌሎች ሰዎች ብቻ እንጂ ለራሴ ማንበብ አልችልም ነበር። ስለ ራሴ የወደፊት ሕይወት ማወቅ እፈልግ የነበረ ቢሆንም ይህን ማድረግ አልቻልኩም።”
ማሪያ ለነበሯት በርካታ ጥያቄዎች መልስ ባለማግኘቷ ግራ ስለተጋባች ወደ አምላክ ጸለየች፤ በኋላም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘች ሲሆን እነሱም መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምሯት ጀመር። ማሪያ መጽሐፍ ቅዱስን ስትማር፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታዋን ያገኘችው ከአምላክ እንዳልሆነ ተረዳች። እንዲሁም የአምላክ ወዳጅ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያላቸውን ዕቃዎች በሙሉ ማስወገድ እንዳለባቸው ተገነዘበች። (የሐዋርያት ሥራ 19:19) ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ማሪያ የአስማት ዕቃዎቿንና መጻሕፍቷን በሙሉ አስወገደች። በአሁኑ ጊዜ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማረችውን እውነት ለሌሎች በመናገሩ ሥራ ትካፈላለች።
ማይክል በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለ፣ ምትሃታዊ ኃይል ስላላቸው ገጸ ባሕርያት የሚናገሩ ልብ ወለዶችን ማንበብ በጣም ያስደስተው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በገሃዱ ዓለም በማይገኙ ቦታዎች ስለሚኖሩ በእኔ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ጀብደኛ ሰዎች ማንበብ ያስደስተኝ ነበር።” ቀስ በቀስ ማይክል ስለ አስማትና ከሰይጣን ጋር ተያያዥነት ስላላቸው የአምልኮ ሥርዓቶች የማንበብ ልማድ ተጠናወተው። እንዲህ በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “የነበረኝ የማወቅ ጉጉት እንዲህ ስላሉ ነገሮች የሚያወሱ መጽሐፎችን ለማንበብና ፊልሞችን ለማየት አነሳሳኝ።”
ሆኖም ማይክል መጽሐፍ ቅዱስን መማሩ የሚያነበውን ነገር በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለበት አስገነዘበው። እንዲህ ብሏል፦ “ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ በዝርዝር ጻፍኩ፤ ከዚያም ሁሉንም አስወገድኳቸው። አንድ ጠቃሚ ትምህርት አግኝቻለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 10:31 ላይ ‘ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ’ በማለት ይናገራል። በመሆኑም ራሴን እንዲህ ብዬ እጠይቃለሁ፦ ‘ይህ መጽሐፍ አምላክን የማያስደስት ነገር ይዟል?’ ከሆነ ለአምላክ ክብር ስለማያመጣ መጽሐፉን አላነበውም።”
በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መብራት ተደርጎ መገለጹ ተገቢ ነው። የመናፍስታዊ ድርጊትን ትክክለኛ ምንነት የሚያጋልጠው ብቸኛው የብርሃን ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (መዝሙር 119:105) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በማድረግ ብቻ አይወሰንም። ከክፉ መናፍስት ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ዓለም እንደሚመጣ የሚናገር ግሩም ተስፋም ይሰጣል። ይህም ለሰው ልጆች ትልቅ እፎይታ ያስገኛል። መዝሙር 37:10, 11 እንዲህ ይላል፦ “ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ በቀድሞ ቦታቸው ትፈልጋቸዋለህ፤ እነሱ ግን በዚያ አይገኙም። የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።”
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።
-