-
ቁርባንከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
-
-
ቁርባን
ፍቺ:- የተቀደሰው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሥርዓተ አምልኮ ጉባኤ እንደ ገለጸው ሥርዓተ ቁርባን “የመስቀል መሥዋዕት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ መሥዋዕት፣ ‘ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት’ ላለው ጌታ ሞትና ትንሣኤ መታሰቢያ ነው። (ሉቃስ 22:19) የአምላክ ሕዝቦች የጌታን ሥጋና ደም በመቀበል የፋሲካ መሥዋዕት የሚያስገኘውን ጥቅም የሚካፈሉበት፣ አምላክ ለአንዴና ለዘላለም በክርስቶስ ደም አማካይነት ከሰው ልጆች ጋር የገባውን አዲስ ቃል ኪዳን የሚያድሱበት፣ በአብ መንግሥት የሚደረገውን የምጽአት ግብዣ በተስፋና በእምነት በመጠበቅ ‘ጌታ እስኪመጣ’ ድረስ ሞቱን የሚናገሩበት ቅዱስ ግብዣ ነው።” (ዩካሪስቲኩም ሚስቴሪዩም፣ ግንቦት 25, 1967) ይህ ሥርዓት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ራት ላይ አድርጓል ብላ የምታምነውን የሚደግም ሥርዓት ነው።
ቂጣውና ወይኑ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደምነት ይለወጣልን?
ሊቀ ጳጳስ ጳውሎስ 6ኛ ሰኔ 30, 1968 ባወጡት “የእምነት መግለጫ” የሚከተለውን ብለው ነበር። “ጌታ በመጨረሻው ራት ላይ ባርኮ የቀደሰው ቂጣና ወይን ለእኛ ሲል በመስቀል ላይ ወደቀረበው የጌታ ሥጋና ደም እንደተለወጠ ሁሉ ቄሱም ባርኮ የሚቀድሰው ቂጣና ወይን በሰማይ በክብር ዙፋን ላይ ወደተቀመጠው የኢየሱስ ሥጋና ደም እንደሚለወጥ እናምናለን። በተጨማሪም ከቡራኬው በፊትም ሆነ በኋላ ለዓይናችን ያልተለወጠ መስሎ በሚታየው ቂጣና ወይን አማካኝነት የሚገለጠው ምሥጢራዊ የሆነ የጌታ መገኘት እውነተኛ፣ እርግጠኛና ገሃድ የሆነ መገኘት ነው። . . . ይህ ምሥጢራዊ መለወጥ በቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ቁርባን (ትራንሰብስታንሲያሽን ) ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው።” (ኦፊሻል ካቶሊክ ቲቺንግስ—ክራይስት አወር ሎርድ፣ ዊልሚንግተን፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ 1978፣ አማንዳ ጂ ዋትሊንግተን፣ ገጽ 411) ቅዱሳን መጻሕፍት ከዚህ እምነት ጋር ይስማማሉን?
ኢየሱስ “ይህ ሥጋዬ ነው”፣ “ይህ ደሜ ነው” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
ማቴ. 26:26–29:- “ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና:- እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ:- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፣ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም።”
“ይህ ሥጋዬ ነው”፣ “ይህ ደሜ ነው” ስለሚሉት አገላለጾች የሚከተለውን ልብ ማለት ይገባል። ሞፋት እንዲህ ይላል:- “ይህ ሥጋዬ ማለት ነው”፣ “ይህ ደሜ ማለት ነው።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) አዓት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ለፈ “ይህ ሥጋዬን ይወክላል ”፣ “ይህ ደሜን ይወክላል ” ይላል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ይህ አተረጓጎም በተለያዩ የካቶሊክ ትርጉሞች በቁጥር 29 ላይ ከተገለጸው ሐሳብ ጋር ይስማማል። ኖክስ እንዲህ በማለት ተርጉሞታል:- “በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር አዲስ ወይን እስከምጠጣ ድረስ ከዚህ የወይን ፍሬ ዳግመኛ አልጠጣም።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በተጨማሪም ኮክ፣ ኒአባ እና ዱዌይ ኢየሱስ በጽዋው ውስጥ የነበረውን መጠጥ “የወይን ፍሬ” ብሎ እንደጠራ አመልክተዋል። ኢየሱስ ይህን የተናገረው “ይህ ደሜ ነው” ካለ በኋላ ነበር።
“ይህ ሥጋዬ ነው”፣ “ይህ ደሜ ነው” የሚሉትን አገላለጾች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከተሠራባቸው ሌሎች ምሳሌያዊ አነጋገሮች ጋር ማስተያየት ይገባል። ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ”፣ “እኔ የበጐች [ማደሪያ] በር ነኝ”፣ “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ” ብሏል። (ዮሐ. 8:12፤ 10:7፤ 15:1) ከእነዚህ አነጋገሮች አንዳቸውም እንኳን በተአምር መለወጥን አያመለክቱም።
ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 11:25 (ጀባ ) ላይ ስለ መጨረሻው ራት ሲጽፍ ያንኑ ተመሳሳይ ሐሳብ ትንሽ ለየት ባሉ ቃላት ገልጾታል። ኢየሱስ ስለ ጽዋው “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ . . . የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” ያለውን በቀጥታ በመጥቀስ ፈንታ እንደሚከተለው ብሏል:- “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።” ይህ ማለት ጽዋው በተአምር ተለውጦ አዲስ ቃል ኪዳን ሆነ ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በጽዋው ውስጥ የነበረው አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናበትን የኢየሱስ ደም ይወክል ነበር ብሎ መደምደም የበለጠ ምክንያታዊ አይሆንምን?
ኢየሱስ በዮሐንስ 6:53–57 ላይ ያለውን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?
“ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፣ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፣ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።”—ዮሐ. 6:53–57
ይህን አነጋገር ቃል በቃል የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙንም መጠጣት እንደሚገባቸው እንደሚገልጽ አድርገን መረዳት ይገባናልን? እንዲህ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ አምላክ በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ እንዲጣስ ይሰብክ ነበር ማለት ነው። ሕጉ ማናቸውም ደም እንዳይበላ ይከለክል ነበር። (ዘሌ. 17:10–12) ኢየሱስ ግን ማናቸውም የሕጉ ክፍል እንዳይጣስ አጥብቆ ያስተምር ስለነበር ደም እንዲጠጣ አላስተማረም። (ማቴ. 5:17–19) ስለዚህ ኢየሱስ የተናገረው ፍጹም በሆነው ሰብዓዊ መሥዋዕት በማመን በምሳሌያዊ ሁኔታ ደሙን እንዲጠጡ ነበር።—ከዮሐንስ 3:16፤ 4:14ና 6:35, 40 ጋር አወዳድር።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ ሳይሆን መሥዋዕቱን የሚያድስ ሥነ ሥርዓት እንዲያከናውኑ ማዘዙ ነበርን?
ዘ ዶኩሜንትስ ኦቭ ቫቲካን 2 እንደሚለው ከሆነ:- “አዳኛችን አልፎ በተሰጠበት በመጨረሻው ራት ላይ የሥጋወደሙን የቁርባን መሥዋዕት አቋቋመ። ይህን ያደረገው የመስቀሉ መሥዋዕት በተደጋጋሚ እንዲቀርብ ሲል ነው። . . .”—(ኒው ዮርክ፣ 1966)፣ በደብልዩ ኤም አቦት የተዘጋጀ፣ ገጽ 154፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቁርባን ‘እውነተኛና ትክክለኛ መሥዋዕት’ የሚቀርብበት ሥርዓት እንደሆነ አድርጋ ትቆጥራለች። . . . ይሁን እንጂ የእኛ እምነት ዋና መሠረት ከጥንት ዘመናት ጀምሮ በሥርዓተ ቁርባን የሚቀርበው መሥዋዕት ትልቅ ዋጋ እንዳለው የሚያምነው ሃይማኖታዊ ወግ ነው።”—(1913)፣ ጥራዝ 10፣ ገጽ 6, 17
ኢየሱስ ራሱ:- “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏል። (ሉቃስ 22:19፤ 1 ቆሮ. 11:24) ሉቃስ 22:19ን ኖክስ፣ ዱዌይ እና ኒአባ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት ተርጉመውታል። ኢየሱስ በመጨረሻው ራት ላይ ያደረገው የእርሱ መሥዋዕት እንደሆነ ወይም ደቀ መዛሙርቱ መሥዋዕቱን በየጊዜው እንዲያድሱ አልተናገረም።
ዕብ. 9:25–28:- “[እንደ አይሁዶች] ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፣ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን . . . ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፣ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፣ . . . አንድ ጊዜ [ተሠዋ።]” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።)
“ነገሩ ለመረዳት የማይቻል ጥልቅ ምሥጢር” ነውን?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለኮታዊ ምሥጢሮች ወይም ቅዱስ ምሥጢሮች ይናገራል። ነገር ግን ከእነዚህ መካከል አንዱም እንኳ ቢሆን በግልጽ ከቀረቡት ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ጋር የሚጋጭ አይደለም። ከቅዱሳን መጻሕፍት ይልቅ ወጎቻቸውን አስበልጠው ይከተሉ ስለነበሩት ሰዎች ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ ስለ እናንተ:- ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።”—ማቴ. 15:7–9
ኢየሱስ ይህ መታሰቢያ በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ እንዲከበር አስቦ ነበርን?
ቤዚክ ካቴኪዝም የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ካቶሊክ ክርስቲያኖች በየሳምንቱ እሑድና በበዓል ቀናት በሚፈጸመው ሥርዓተ ቁርባን ላይ የመገኘት ግዳጅ አለባቸው።” (ቦስተን፣ 1980፣ ገጽ 21) “ታማኝ ምዕመናን ሁሉ እንዲያስቆርቡና አዘውትረው እንዲያውም በየቀኑም እንኳ ቢሆን ሥጋወደሙን እንዲቀበሉ እናበረታታለን።”—ዘ ቲቺንግ ኦቭ ክራይስት—ኤ ካቶሊክ ካቴኪዝም ፎር አደልትስ፣ በአጭሩ የተዘጋጀ (ሁንቲንግ፣ ኢንዲያና፣ 1979)፣ ገጽ 281
በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ‘እንጀራ ስለመቁረስ’ የሚናገሩት ጥቅሶች በሙሉ ስለ ክርስቶስ ሞት መከበር የሚገልጹ ናቸውን? (ሥራ 2:42, 46፤ 20:7) ኢየሱስ ከመጨረሻው ራት በፊት እንኳ ምግብ በሚቀርብበት ጊዜ ‘እንጀራን ቆርሶ’ ይሰጥ ነበር። (ማር. 6:41፤ 8:6) አይሁዳውያን በዚያን ጊዜ ይበሉት የነበረው እንጀራ ዛሬ በብዙ ሰዎች ዘንድ የታወቀው ዓይነት አይደለም። ብዙውን ጊዜ ምግብ በሚበሉበት ወቅት እንጀራ ወይም ደረቅ ያለ ስስ ቂጣ እየቆረሱ ይበሉ ነበር።
ኢየሱስ የሞቱ መታሰቢያ ምን ያህል ጊዜ መከበር እንዳለበት ገልጾ አልተናገረም። ይሁን እንጂ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ያቋቋመው የአይሁዳውያን የማለፍ በዓል በሚከበርበት ቀን ላይ ነው። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይህን የአይሁዳውያን የማለፍ በዓል በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ተክተዋል። የማለፍ በዓል የሚከበረው በየዓመቱ ኒሳን 14 ቀን ነበር። በተመሳሳይም የአይሁድ የቂጣ በዓል፣ የሣምንታት (የጰንጠቆስጤ) በዓል፣ የዳስ በዓል እና የሥርየት ቀን ይከበሩ የነበሩት በዓመት አንድ ጊዜ ነበር።
የቁርባን ሥርዓት በሚከናወንበት ጊዜ የሚቀርበው ጸሎት በመንጽሔ ያሉትን ነፍሳት ነፃ ያወጣቸዋልን?
ዘ ቲቺንግ ኦቭ ክራይስት—ኤ ካቶሊክ ካቴኪዝም ፎር አደልትስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “‘መንጽሔ’ የሚለው ቃልም ሆነ ትምህርቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። . . . የአበው መጻሕፍት ግን መንጽሔ መኖሩን ብቻ ሳይሆን በመንጽሔ ውስጥ ያሉ ምዕመናን ሕያዋን በሚያቀርቡት ጸሎትና በተለይም በቁርባን መሥዋዕት ሊረዱ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።”—ገጽ 347, 348
ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ ይላሉ:- “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉ፣ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም።” (መክ. 9:5) “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ [“ነፍስ” ኖክስ፤ “ሰው” ጀባ ] እርስዋ ትሞታለች።” (ሕዝ. 18:4) (በተጨማሪ በገጽ 99–101 ላይ “ሞት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)
-
-
የመታሰቢያ በዓል (የጌታ ራት)ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
-
-
የመታሰቢያ በዓል (የጌታ ራት)
ፍቺ:- የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሚታሰብበት ራት ነው። በዚህ ራት ከማንኛውም ሰው ሞት የበለጠ ውጤት ያስገኘው የክርስቶስ ሞት ይታሰባል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ መታሰቢያ በዓል እንዲያከብሩለት ያዘዘው ለሞቱ ብቻ ነው። በተጨማሪም ይህ መታሰቢያው የጌታ ራት ተብሎ ይጠራል።—1 ቆሮ. 11:20
የመታሰቢያው በዓል ትርጉም ምንድን ነው?
ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። (ሉቃስ 22:19) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ለተወለዱት የክርስቲያን ጉባኤ አባሎች ሲጽፍ:- “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።” (1 ቆሮ. 11:26) ስለዚህ መታሰቢያው የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የይሖዋን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ ያለውን ትልቅ ቦታ ያሳስባል። በተጨማሪም የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት በተለይ ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ያለውን ትርጉምና ሞቱ አብረውት መንግሥተ ሰማያትን በሚወርሱ ሰዎች ላይ የሚኖረውን ውጤት አጉልቶ ያሳያል።—ዮሐ. 14:2, 3፤ ዕብ. 9:15
በተጨማሪም መታሰቢያው በዓል በዘፍጥረት 3:15 እና ከዚያ በኋላ በተገለጸው የአምላክ ዓላማ መሠረት የተፈጸመው የኢየሱስ ሞትና አሟሟት በይሖዋ ስም ላይ የደረሰውን ነቀፋ ያስወገደ መሆኑን ያስታውሰናል። ኢየሱስ ለይሖዋ ያለውን ፍጹም አቋም እስከሞት ድረስ ሳያጐድፍ በመገኘቱ አዳም ኃጢአት የሠራው በሰው ልጅ ላይ የአፈጣጠር ጉድለት ስለኖረ እንዳልሆነና የሰው ልጅ ከባድ ተጽእኖ ቢደርስበት እንኳን ፍጹም አቋሙን ሊጠብቅ ይችል እንደነበረ አረጋግጧል። በዚህም ኢየሱስ የይሖዋን ፈጣሪነትና ጽንፈ ዓለማዊ የበላይ ገዥነት አረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ የኢየሱስ ሞት የአዳም ዘሮችን ለመቤዠት የሚያስችል ፍጹም ሰብዓዊ መሥዋዕት እንዲሆን የይሖዋ ዓላማ ነበር። ይህም በመጀመሪያው የይሖዋ ዓላማና ለሰው ልጆች ባለው ታላቅ ፍቅር መሠረት በኢየሱስ የሚያምኑ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል።—ዮሐ. 3:16፤ ዘፍ. 1:28
ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ባሳለፋት የመጨረሻ ምሽት ላይ በጣም ከባድ ሸክም ወድቆበት ነበር። ሰማያዊ አባቱ ምን ዓላማ እንዳዘጋጀለት ጠንቅቆ የሚያውቅ ቢሆንም በሚደርስበት ፈተና ሁሉ ታማኝነቱን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት ያውቅ ነበር። በፈተናው ተሸንፎ ቢሆን በአባቱ ላይ ከፍተኛ ነቀፋ ይመጣ ነበር። በሰው ልጆችም ላይ ከፍተኛ የሆነ ኪሣራ በደረሰ ነበር። ሞቱ በሚያስገኛቸው ከፍተኛ ውጤቶች ምክንያት ሞቱ እንዲታሰብ መመሪያ መስጠቱ ተገቢ ነበር።
በመታሰቢያው ላይ የሚቀርበው ቂጣና ወይን ትርጉሙ ምንድን ነው?
ኢየሱስ መታሰቢያውን ባቋቋመበት ጊዜ ለሐዋርያቱ ስለሰጣቸው ያልቦካ ቂጣ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ይህ ሥጋዬ ማለት ነው።” (ማር. 14:22 አዓት ) ይህ ቂጣ ኃጢአት የሌለበትን ሥጋውን ይወክላል። ይህን ሥጋውን የሰው ልጆች የሕይወት ተስፋ እንዲያገኙ ሲል ሰጥቷል። በዚህ ዕለት ይህ መሥዋዕት ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት ተካፋዮች እንዲሆኑ ለሚመረጡት ሰዎች ለሚያስገኘው የሕይወት ተስፋ ልዩ ትኩረት ይደረጋል።
ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ ወይኑን በሰጣቸው ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈሰው ‘የቃል ኪዳን ደሜ’ ማለት ነው።” (ማር. 14:24 አዓት ) ይህ ወይን የኢየሱስን ደመ ሕይወት ይወክላል። በፈሰሰው ደሙ የሚያምኑ ሁሉ በዚህ ደም አማካኝነት የኃጢአት ሥርየት ያገኛሉ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አጉልቶ የገለጸው ወደ ፊት ከእርሱ ጋር ተባባሪ ወራሾች የሚሆኑት ስለሚያገኙት የኃጢአት ሥርየት ነበር። በተጨማሪም የተናገረው ቃል በይሖዋ አምላክና በመንፈስ በተቀባው የክርስቲያን ጉባኤ መካከል የተደረገው አዲስ ቃል ኪዳን በዚህ ደም አማካኝነት ሥራውን እንደሚጀምር ያመለክታል።
በተጨማሪ በገጽ 261–263 ላይ “ቁርባን” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።
ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት እነማን ናቸው?
ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ የጌታን ራት ባቋቋመበት ጊዜ ከቂጣውና ከወይኑ የተካፈሉት እነማን ነበሩ? ኢየሱስ “አባቴ ከእኔ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን እንዳደረገ እኔ ደግሞ ከእናንተ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ” ያላቸው አሥራ አንድ ታማኝ ተከታዮች ነበሩ። (ሉቃስ 22:29 አዓት ) ሁሉም ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት እንዲካፈሉ የተጋበዙ ሰዎች ነበሩ። (ዮሐ. 14:2, 3) ዛሬም ቢሆን ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉ ሁሉ ክርስቶስ ወደዚህ ‘የመንግሥት ቃል ኪዳን’ ያስገባቸው ሰዎች መሆን ይኖርባቸዋል።
ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል ነው? የሰማያዊ መንግሥት ሽልማት የሚያገኙት “ታናሽ መንጋ” ብቻ እንደሚሆኑ ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:32) ሙሉ ቁጥራቸው 144,000 ነው። (ራእይ 14:1–3) የዚህ ቡድን አባሎች መመረጥ የጀመሩት በ33 እዘአ ነበር። ስለዚህ ዛሬ ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት ሰዎች ቁጥር በጣም ትንሽ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።
ዮሐንስ 6:53, 54 ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት ብቻ ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚያገኙ ያመለክታልን?
ዮሐ. 6:53, 54:- “ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፣ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።”
እዚህ ላይ የተናገረለት መብላትና መጠጣት በምሳሌያዊ ሁኔታ የሚፈጸም መሆን እንደሚገባው ግልጽ ነው። አለዚያ ሥጋና ደም የሚበላውና የሚጠጣው ሰው የአምላክን ሕግ ይጥሳል። (ዘፍ. 9:4፤ ሥራ 15:28, 29) ኢየሱስ በዮሐንስ 6:53, 54 ላይ የሚገኘውን ቃል የተናገረው ከጌታ ራት መቋቋም ጋር አዛምዶ እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል። ኢየሱስ ሲናገር ከሰሙት መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ የክርስቶስን ሥጋና ደም በሚወክል ቂጣና ወይን አማካኝነት ስለሚከበር በዓል የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ይህ ዝግጅት የተጀመረው ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ በስሙ በሚጠራው ወንጌል ውስጥ ስለ ጌታ ራት የገለጸው (በዮሐንስ 14 ላይ) ከሰባት ምዕራፎች በኋላ ነው።
ታዲያ አንድ ሰው ‘የሰውን ልጅ ሥጋ የሚበላውና ደሙን የሚጠጣው’ በመታሰቢያው ዕለት ከቂጣውና ከወይኑ በመካፈል ካልሆነ በምሳሌያዊ መንገድ ሥጋውን ሊበላና ደሙን ሊጠጣ የሚችለው እንዴት ነው? ቂጣውን የሚበሉና ደሙን የሚጠጡ “የዘላለም ሕይወት” እንደሚኖራቸው ኢየሱስ ተናግሯል። ከዚህ ቀደም ብሎ በቁጥር 40 ላይ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከፈለጉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲገልጽ የአባቱ ፈቃድ ምን እንደሆነ ተናገረ? “ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት” ይኖረዋል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) እንግዲያውስ በምሳሌያዊ አነጋገር ሥጋውን መብላትና ደሙን መጠጣት የሚቻለው የመዋጀት ኃይል ባለው በኢየሱስ ሥጋና መሥዋዕት ሆኖ በፈሰሰው ደሙ በማመን ነው። ይህ እምነት በሰማያት ከክርስቶስ ጋር ከሚሆኑትም ይሁን ገነት በምትሆነው በምድር ላይ ከሚኖሩት ይፈለግባቸዋል።
የመታሰቢያው በዓል መከበር የሚኖርበት በየስንት ጊዜው ነው? የሚከበረውስ መቼ ነው?
በየስንት ጊዜው መከበር እንደሚኖርበት ኢየሱስ በግልጽ አልተናገረም። ባጭሩ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏል። (ሉቃስ 22:19) ጳውሎስ እንዲህ አለ:- “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።” (1 ቆሮ. 11:26) “ጊዜ ሁሉ” የሚለው አነጋገር በዓመት ውስጥ ብዙ ጊዜ እንዲህ ታደርጋላችሁ ማለት ላይሆን ይችላል። በየዓመቱ ለብዙ ዘመናት አድርጉት ማለት ሊሆን ይችላል። አንድ ትልቅ በዓል ለምሳሌ የጋብቻህን ቀን የምታከብር ብትሆን ወይም አንድ አገር በታሪኳ ውስጥ የተፈጸመን አንድ ትልቅ ድርጊት የምታከብር ቢሆን ይህ ቀን የሚከበረው ምን ያህል ጊዜ ነው? በዓሉ የሚከበረው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ይህም የጌታ ራት የተቋቋመው አይሁዶች በየዓመቱ ያከብሩ በነበረውና ክርስቲያን በሆኑት አይሁዶች መከበሩ በቀረው የማለፍ በዓል ዕለት ከመሆኑ ጋር ይስማማል።
የይሖዋ ምሥክሮች የመታሰቢያውን በዓል የሚያከብሩት በአንደኛው መቶ ዘመን ይሠራበት በነበረው የአይሁዳውያን የዘመን አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው። የአይሁዳውያን ቀን የሚጀምረው ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ሲሆን በማግሥቱ ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ይቆያል። ስለዚህ ኢየሱስ የሞተው በአይሁዳውያን አቆጣጠር መሠረት የመታሰቢያውን በዓል ባቋቋመበት ዕለት ነበር። የኒሣን ወር የሚጀምረው በፀደይ ወራት የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ እኩል በሚሆንበት ጊዜ ቅርብ የሆነችው አዲስ ጨረቃ በኢየሩሳሌም ከታየች በኋላ ፀሐይ ስትጠልቅ ነው። የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው ይህ ከሆነ ከ14 ቀን በኋላ ነው። (የመታሰቢያው በዓል የዛሬዎቹ አይሁዳውያን ከሚያከብሩት የማለፍ በዓል ጋር አይገጥምም። ለምን? ምክንያቱም የወሮቻቸው መባቻ አዲስ ጨረቃ በኢየሩሳሌም ከሚታይበት ጊዜ ጋር ሳይሆን በከዋክብት ጥናት መሠረት አዲስ ጨረቃ ከምትታይበት ጊዜ ጋር እንዲጋጠም ስላደረጉ ነው። በዚህም ምክንያት ከ18 እስከ 30 ሰዓት ልዩነት ሊኖር ይችላል። በተጨማሪም ዛሬ አብዛኞቹ አይሁዳውያን የማለፍን በዓል የሚያከብሩት ኒሳን 15 ላይ ነው። ይህም የሙሴ ሕግ በሚያዘው መሠረት ኢየሱስ በዓሉን ካከበረበት ከኒሣን 14 የሚለይ ነው።)
-