የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በትምህርት ቤቱ የሚሰጡህን የተማሪ ክፍሎች መዘጋጀት
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • በትምህርት ቤቱ የሚሰጡህን የተማሪ ክፍሎች መዘጋጀት

      በትምህርት ቤቱ የምታቀርበው እያንዳንዱ ክፍል እድገት ማድረግ የምትችልበትን አጋጣሚ ለማግኘት ይረዳሃል። ከልብ ጥረት የምታደርግ ከሆነ አንተም እድገት እያደረግህ እንዳለ ይታወቅሃል፤ ሌሎችም ይህንን ማስተዋላቸው አይቀርም። (1 ጢሞ. 4:​15) ትምህርት ቤቱ ችሎታዎችህን ይበልጥ እያሻሻልህ እንድትሄድ ያግዝሃል።

      በጉባኤ ክፍል ስለማቅረብ ስታስብ ፍርሃት ፍርሃት ይልሃል? በትምህርት ቤቱ ክፍል ስታቀርብ የመጀመሪያህ ባይሆንም እንኳ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊሰማህ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን ፍርሃትህን ሊያቃልሉልህ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ይኖራሉ። እቤትህ ስትሆን ድምፅህን ከፍ አድርገህ የማንበብ ልማድ ይኑርህ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ መልስ ለመስጠት ሞክር። አስፋፊ ከሆንህ ደግሞ ዘወትር በአገልግሎት ተካፈል። ይህም በሰዎች ፊት የመናገር ልምድ እንድታዳብር ይረዳሃል። ከዚህም በተጨማሪ ክፍልህን ቀደም ብለህ ተዘጋጅና እንደምታቀርበው ሆነህ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ተለማመደው። ክፍልህን የምታቀርበው ቀና አመለካከት ላላቸው አድማጮች መሆኑን አስታውስ። ማንኛውንም ክፍል ከማቅረብህ በፊት ወደ ይሖዋ ጸልይ። ይሖዋ ወደ እርሱ ለሚጸልዩ አገልጋዮቹ መንፈስ ቅዱሱን በልግስና ይሰጣቸዋል።​—⁠ሉቃስ 11:​13፤ ፊልጵ. 4:​6, 7

      በአንድ ጊዜ ተሞክሮ ያለው ተናጋሪ መሆን ወይም በማስተማር ረገድ ውጤታማ ሆኖ መገኘት ስለማይቻል ተዓምራዊ ለውጥ አደርጋለሁ ብለህ አትጠብቅ። (ሚክ. 6:​8) ለትምህርት ቤቱ አዲስ ተማሪ ከሆንክ ገና በመጀመሪያው በሁሉም ረገድ የተዋጣለት ክፍል አቀርባለሁ ብለህ አታስብ። ከዚህ ይልቅ አንድ ክፍል ስታቀርብ በአንድ ምክር መስጫ ነጥብ ላይ ብቻ አተኩር። የምክር መስጫ ነጥቡ የተብራራበትን የዚህን መጽሐፍ ክፍል አጥና። የተሰጠውንም መልመጃ ለመለማመድ ሞክር። ይህም ክፍልህን ከማቅረብህ በፊት ከምክር መስጫ ነጥቡ ጋር በደንብ እንድትተዋወቅ የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ እንድትሻሻል ያግዝሃል።

      በንባብ የሚቀርብ ክፍል መዘጋጀት

      ለሌሎች ለማንበብ ስትዘጋጅ በጽሑፉ ላይ ያሉትን ቃላት ማንበብ መቻልህ ብቻውን በቂ አይደለም። የትምህርቱ መልእክት ምን እንደሆነ ለመረዳት ጥረት አድርግ። ይህን ግብ በመያዝ ክፍሉ እንደተሰጠህ ወዲያው አንብበው። ንባብህ ሐሳቡን በትክክል የሚያስተላልፍና ተገቢውን ስሜት የሚያንጸባርቅ እንዲሆን እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር የሚያስተላልፈውን መልእክት ለመረዳትና የእያንዳንዱን አንቀጽ ዋና ነጥብ ለማግኘት ሞክር። የሚቻል ከሆነ እንግዳ የሆኑትን ቃላት ትክክለኛ አነባበብ ለማወቅ ሌላ ሰው ጠይቅ። ትምህርቱ በደንብ ይግባህ። በዚህ ረገድ ወላጆች ትናንሽ ልጆቻቸውን መርዳት ያስፈልጋቸው ይሆናል።

      ክፍልህ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ ወይም የተወሰኑ የመጠበቂያ ግንብ አንቀጾች በማንበብ የሚቀርብ ነውን? የምታነብበው ጽሑፍ በቋንቋህ በካሴት የተዘጋጀ ከሆነ ይህንን ካሴት በማዳመጥ የቃላቱን አነባበብ፣ አሰባበሩን፣ ግነቱን እንዲሁም የድምፅ ቃናና ፍጥነት አለዋወጡን ልብ ብሎ ማዳመጡ ሊጠቅምህ ይችላል። ከዚያም የሰማሃቸውን ነገሮች በንባብህ ለማንጸባረቅ ሞክር።

      ክፍልህን መዘጋጀት ከመጀምረህ በፊት፣ የተሰጠህን የምክር መስጫ ነጥብ የሚያብራራውን ትምህርት በጥንቃቄ ማጥናት ይኖርብሃል። የተሰጠህን ክፍል ደጋግመህ ከተለማመድህ በኋላ ከቻልህ ይህንኑ ትምህርት እንደገና ከልሰው። በተቻለ መጠን ይህን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ጣር።

      በዚህ መንገድ የምታገኘው ሥልጠና ለአገልግሎት ይጠቅምሃል። በመስክ አገልግሎት ስትካፈል ለሌሎች የምታነብባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ይኖሩሃል። የአምላክ ቃል የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል ስላለው ስታነብብ ጥሩ አድርገህ ማንበብህ በጣም አስፈላጊ ነው። (ዕብ. 4:​12) አንድ ወይም ሁለት ክፍል ስላቀረብህ ብቻ ንባብን ውጤታማ በሚያሰኙት ዘርፎች ሁሉ ይዋጣልኛል ብለህ አታስብ። ሐዋርያው ጳውሎስ የብዙ ዓመታት ተሞክሮ ለነበረው ክርስቲያን ሽማግሌ ሲጽፍ “እኔ እስክመጣ ድረስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለሕዝብ በማንበብ . . . ትጋ” ብሎታል።​—⁠1 ጢሞ. 4:​13 የ1980 ትርጉም 

      ከጭብጡና ከመቼቱ ጋር የሚስማማ ዝግጅት

      በትምህርት ቤቱ እንድታቀርበው የተሰጠህ ክፍል መቼት ያለው ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

      ትኩረት የሚያሻቸው ሦስት ዋና ዋና ነገሮች አሉ። እነዚህም:- (1) የተመደበልህ ጭብጥ (2) መቼትህና የምታነጋግረው ሰው እንዲሁም (3) እንድትሠራበት የተሰጠህ ምክር መስጫ ነጥብ ናቸው።

      ለተሰጠህ ጭብጥ የሚስማሙ ነጥቦችን ማሰባሰብ ያስፈልግሃል። ይሁን እንጂ ብዙ ከመግፋትህ በፊት ስለ መቼትህና ስለምታነጋግረው ሰው በጥሞና አስብ። ምክንያቱም መቼትህና የምታነጋግረው ሰው ማንነት የምታቀርባቸውን ነጥቦችና የትምህርቱን አቀራረብ ይወስናሉ። የምትጠቀመው መቼት ምን ዓይነት ነው? ለምታውቀው ሰው ምሥራቹን እንዴት እንደምታቀርብ የሚያሳይ ነው? ወይስ አንድን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነጋግር የሚያሳይ? ግለሰቡ በዕድሜ ከአንተ ይበልጣል ወይስ ያንሳል? ልታወያየው ስላሰብከው ርዕሰ ጉዳይ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይችላል? ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይስ ከአሁን ቀደም ምን የሚያውቀው ነገር ይኖራል? ውይይቱን ስታደርግ ይዘኸው የተነሣኸው ዓላማ ምንድን ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ምን ማድረግ እንዳለብህ ይጠቁምሃል።

      የተሰጠህን ጭብጥ ለማዳበር የሚረዳ ሐሳብ ከየት ማግኘት ትችላለህ? በዚሁ መጽሐፍ ከገጽ 33 እስከ 38 ላይ “ምርምር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?” በሚል ርዕስ የቀረበ ትምህርት አለ። ይህንን ምዕራፍ አንብብና ልታገኛቸው የምትችላቸውን ለምርምር የሚረዱ ጽሑፎች ተጠቀም። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምትፈልገው በላይ ብዙ ሐሳቦችን እንደምታገኝ እሙን ነው። ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ምን ያህል መረጃ ማግኘት እንደምትችል ለማወቅ አቅምህ የፈቀደውን ያህል አንብብ። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ለክፍልህ ልትጠቀምበት ያሰብከውን መቼትም ሆነ የምታነጋግረውን ግለሰብ ማንነት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። ተስማሚ ሆነው ያገኘሃቸው ነጥቦች ላይ ምልክት አድርግ።

      ለክፍልህ የሚሆኑትን ነጥቦች መርጠህ ከማጠናቀቅህ በፊት የተሰጠህን የምክር መስጫ ነጥብ አንብብ። ክፍል የምታቀርብበት ዋናው ምክንያት የምክር መስጫ ነጥቡን እንድትሠራበት ነው።

      የተመደበልህ ጊዜ ካለቀ ማቆም ስላለብህ ነጥቦችህን በተሰጠህ ጊዜ ውስጥ መጨረስህ ንግግርህን ባሰብከው መንገድ በመደምደም እርካታ እንድታገኝ ያስችልሃል። በመስክ አገልግሎት ግን የሰዓት ጉዳይ ሁልጊዜ አሳሳቢ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ ስትዘጋጅ ምን ያህል ጊዜ እንደ ተሰጠህ ግምት ውስጥ አስገባ። ሆኖም ትልቁ ነገር ትምህርቱን በጥሩ ሁኔታ ማቅረብህ ነው።

      ስለ መቼቱ ጥቂት እንበል:- በገጽ 82 ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች በመመርመር በአገልግሎትህ የሚጠቅምህንና ትምህርቱን ተግባራዊ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የሚረዳህን አንድ መቼት ምረጥ። በትምህርት ቤቱ ክፍል ስታቀርብ ቆይተህ ከሆነ ይህንን አጋጣሚ ለተጨማሪ ኃላፊነት ብቁ ሆኖ ለመገኘትና ለአገልግሎት የሚረዳህን ችሎታ ለማዳበር ተጠቀምበት።

      መቼቱን የሰጠህ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካቹ ከሆነ በዚህ በተሰጠህ መቼት ለመሥራት ሞክር። ብዙዎቹ መቼቶች ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱን መቼት በአገልግሎት ተጠቅመህበት የማታውቅ ከሆነ በዚህ ረገድ ተሞክሮ ያላቸውን አስፋፊዎች ምክር ጠይቅ። ከቻልክ በትምህርት ቤቱ ልትጠቀምበት ያሰብከውን መቼት ተጠቅመህ የክፍልህን ነጥቦች በአገልግሎት ከምታገኘው ሰው ጋር ተወያይባቸው። ይህን ማድረግህ የሥልጠናውን ዋና ዓላማ ዳር ለማድረስ ይረዳሃል።

      በንግግር የሚቀርብ ክፍል

      ወንዶች አጭር ንግግር ለጉባኤው እንዲያቀርቡ ይመደባሉ። እነዚህን ክፍሎች ስትዘጋጅ ልታስብባቸው የሚገቡት መሠረታዊ ነጥቦች በሠርቶ ማሳያ የሚቀርቡትን የተማሪ ክፍሎች በተመለከተ ከተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ጉልህ ልዩነት የሚኖረው በአድማጮችና በአቀራረብ ረገድ ነው።

      አብዛኛውን ጊዜ ሁሉም አድማጮች ከትምህርቱ ሊጠቀሙ በሚችሉበት መንገድ መዘጋጀቱ የተሻለ ይሆናል። በስብሰባው ላይ ከተገኙት መካከል አብዛኞቹ መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያውቃሉ። የምታቀርበውንም ርዕሰ ጉዳይ በደንብ ያውቁት ይሆናል። ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ የሚያውቁት ምን ያህል ነው የሚለውን ግምት ውስጥ አስገባ። አድማጮችህ ከምታቀርበው ክፍል በሆነ መልኩ ጥቅም እንዲያገኙ ለመርዳት ጥረት አድርግ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ይህ ርዕሰ ጉዳይ እኔም ሆንኩ አድማጮቼ ለይሖዋ ያለንን አድናቆት እንድናሳድግ የሚረዳን እንዴት ነው? ትምህርቱ የአምላክን ፈቃድ እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው? የሥጋ ምኞት ገንኖ በሚታይበት ዓለም ውስጥ ጤናማ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው?’ (ኤፌ. 2:​3) ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስትጠቅስ ጥቅሶቹን አንብበህ ብቻ ከማለፍ ይልቅ ልታብራራቸው እንዲሁም እነዚህ ጥቅሶች ወደ አንድ መደምደሚያ ለመድረስ የሚረዱት እንዴት እንደሆነ ግልጽ ልታደርግ ይገባል። (ሥራ 17:​2, 3) ብዙ ነጥብ ለማካተት አትሞክር። ትምህርቱን በቀላሉ ማስታወስ በሚያስችል መንገድ አቅርበው።

      በዝግጅትህ ወቅት ስለ አቀራረብህም ልታስብ ይገባል። ይህ ትኩረት ልትሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ክፍልህን ለሌሎች እንደምታቀርብ ሆነህ ተለማመድ። የተለያዩ የንግግር ባሕርያትን ለማጥናትና ምክሩን ሥራ ላይ ለማዋል የምታደርገው ጥረት ለእድገትህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። አዲስም ሆንክ ልምድ ያለህ ተናጋሪ በጉዳዩ እንደምታምንበት በሚያሳይ መንገድና ለትምህርቱ በሚስማማ ስሜት ለመናገር እንድትችል ጥሩ ዝግጅት አድርግ። በትምህርት ቤቱ የሚሰጥህን እያንዳንዱን ክፍል ተዘጋጅተህ ስታቀርብ ዓላማህ ይሖዋ የሰጠህን የንግግር ችሎታ ለእርሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ መጠቀም እንደሆነ አትዘንጋ።​—⁠መዝ. 150:​6

  • ለጉባኤ የሚቀርቡ ንግግሮችን መዘጋጀት
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • ለጉባኤ የሚቀርቡ ንግግሮችን መዘጋጀት

      በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚካተቱት ክፍሎች ለሁሉም የጉባኤ አባላት ጥቅም ታስበው የሚዘጋጁ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በሌሎቹ የጉባኤ ስብሰባዎች፣ በወረዳና በልዩ እንዲሁም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ጠቃሚ ትምህርቶች ይቀርባሉ። ከእነዚህ ስብሰባዎች በአንዱ ላይ ክፍል እንድታቀርብ ከተመደብህ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎብሃል ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች የነበረው ጢሞቴዎስ ለማስተማር ሥራው እንዲጠነቀቅ አሳስቦታል። (1 ጢሞ. 4:​16) ከአምላክ ጋር ስላላቸው ዝምድና ለመማር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሁሉ ወደ እነዚህ ስብሰባዎች የሚመጡት ውድ ጊዜያቸውን ሠውተው ነው። አንዳንዶቹም ተጨማሪ መሥዋዕትነት ይጠይቅባቸዋል። በእርግጥም ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና በተመለከተ ሰዎችን ማስተማር ትልቅ መብት ነው! ታዲያ ይህንን መብት በአግባቡ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው?

      የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች

      በትምህርት ቤቱ የሚቀርበው ይህ ክፍል ለሳምንቱ በሚመደበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ላይ የተመሠረተ ነው። ትምህርቱ እኛን እንዴት ይነካናል የሚለው ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በ⁠ነህምያ 8:​8 ላይ እንደተገለጸው ዕዝራና አብረውት የነበሩት ሰዎች የአምላክን ቃል ለሕዝቡ እያነበቡ በማብራራትና ‘ትርጉሙን በማስረዳት’ ሕዝቡ ማስተዋል እንዲያገኝ አድርገዋል። አንተም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦችን በምታቀርብበት ጊዜ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ።

      ይህን ክፍል ለማቅረብ መዘጋጀት የሚኖርብህ እንዴት ነው? ከቻልክ ክፍሉ የሚቀርብባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ከአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ ከሚበልጥ ጊዜ በፊት አስቀድመህ አንብብ። ከዚያም ስለ ጉባኤህና ጉባኤው ስለሚያስፈልገው ነገር አስብ። ክፍሉን ለጉባኤው በሚጠቅም መንገድ ማቅረብ እንድትችል ጸልይ። በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ውስጥ ጉባኤው የሚያስፈልገውን ነገር በተመለከተ ምን ምክር፣ ምሳሌ እና መሠረታዊ ሥርዓት ይገኛሉ?

      ምርምር ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫን ምርምር ለማድረግ ልትጠቀምበት ትችላለህ። በማውጫው ላይ ያሉትን ጽሑፎች ተመርኩዘህ በመረጥካቸው ጥቅሶች ላይ ምርምር ስታደርግ እውቀት ሰጪ የሆኑ ተጨማሪ ነጥቦች፣ ፍጻሜያቸውን ስላገኙ ትንቢቶች የተሰጠ ማብራሪያ፣ ጥቅሶቹ ስለ ይሖዋ ባሕርይ የሚገልጹትን እውነት በተመለከተ ወይም ስለ መሠረታዊ ሥርዓቶች የቀረበ ትምህርት ታገኝ ይሆናል። በጣም ብዙ ነጥቦች ለማብራራት አትሞክር። ከዚህ ይልቅ በተመረጡ ጥቂት ጥቅሶች ላይ ብቻ አተኩር። ጥቂት ቁጥሮች ላይ ብቻ አተኩሮ እነርሱን በሚገባ ማብራራቱ የተሻለ ይሆናል።

      ክፍልህ አድማጮች ከሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ያገኙትን ጥቅም እንዲናገሩ መጋበዝን የሚያካትት ሊሆን ይችላል። ለግልም ሆነ ለቤተሰብ ጥናት ወይም ለአገልግሎት የሚጠቅም ወይም በሕይወታቸው የሚሠሩበት ምን ትምህርት አግኝተዋል? ይሖዋ ከሰዎችና ከብሔራት ጋር ባደረገው ግንኙነት ስላሳያቸው ባሕርያት ምን ይነግረናል? የአድማጮች እምነት እንዲጠነክርና ለይሖዋ ያላቸው አድናቆት እንዲጨምር የሚያደርግ ምን ትምህርት ይዟል? ዝርዝርና ውስብስብ ማብራሪያ ለመስጠት ከመሞከር ይልቅ የመረጥካቸውን ነጥቦች ትርጉምና ተግባራዊ ጠቀሜታ ጎላ አድርገህ ግለጽ።

      ማስተማሪያ ንግግር

      ይህ ንግግር በመጠበቂያ ግንብ ወይም በንቁ! መጽሔት ርዕስ ወይም ከአንድ መጽሐፍ በተወሰደ ክፍል ላይ ተመሥርቶ የሚቀርብ ነው። በአብዛኛው በተመደበልህ ጊዜ ውስጥ ልታቀርበው ከምትችለው በላይ ብዙ ነጥቦች ይኖራሉ። ታዲያ ይህን ክፍል ማቅረብ የሚኖርብህ እንዴት ነው? አድማጮችህን ማስተማር አለብህ እንጂ እንዲሁ ትምህርቱን መሸፈንህ ብቻ በቂ አይሆንም። አንድ የበላይ ተመልካች “ለማስተማር የሚበቃ” ሊሆን ይገባል።​—⁠1 ጢሞ. 3:​2

      ለመዘጋጀት ስትነሣ በመጀመሪያ እንድታቀርበው የተመደበውን ጽሑፍ አጥና። ጥቅሶቹን አውጥተህ አንብብ። አሰላስል። ይህንን ማድረግ ያለብህ ክፍልህን የምታቀርብበት ቀን ከመድረሱ በፊት ነው። ንግግሩ የተመሠረተበትን ጽሑፍ ወንድሞችም አንብበውት እንደሚመጡ አትዘንጋ። የአንተ ኃላፊነት ነጥቦቹን መከለስ ወይም ጨምቆ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ማስረዳት ነው። ተስማሚ ሆነው ያገኘሃቸውን ነጥቦች ጉባኤውን ሊጠቅም በሚችል መንገድ አቅርባቸው።

      እያንዳንዱ ልጅ የየራሱ ባሕርይ እንዳለው ሁሉ እያንዳንዱ ጉባኤም ልዩ የሚያደርገው የራሱ ባሕርይ ይኖረዋል። አንድ ወላጅ የሚያስተምረው ነገር ውጤት እንዲኖረው ከፈለገ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን በመዘርዘር ብቻ አይወሰንም። አሳማኝ በሆነ መንገድ ያስረዳል። የልጁን ባሕርይና የሚያጋጥሙትን ችግሮች ግምት ውስጥ ያስገባል። በተመሳሳይም በጉባኤ ውስጥ ያሉ አስተማሪዎች አድማጮቻቸው ምን እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ ተስማሚ የሆነ ትምህርት ለማቅረብ ይጥራሉ። ይሁን እንጂ አስተዋይ የሆነ አስተማሪ በአድማጮቹ መካከል ያሉ ግለሰቦችን የሚያሸማቅቅ ምሳሌ አይጠቀምም። በይሖዋ መንገድ መመላለስ ያስገኘላቸውን ጥቅም ይጠቅሳል። እንዲሁም የጉባኤው አባላት የሚገጥማቸውን ችግር በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚረዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ጎላ አድርጎ ይገልጻል።

      ጥሩ የማስተማር ችሎታ የአድማጮችን ልብ ለመንካት ያስችላል። ይህ ደግሞ እውነታውን ከማስቀመጥ አልፎ የነጥቦቹን ትርጉም እንዲያስተውሉ መርዳትን ይጠይቃል። እንዲሁም ለአድማጮች ከልብ አሳቢነት ማሳየትን ይጨምራል። መንፈሳዊ እረኞች በጉባኤያቸው ያሉትን ወንድሞችና እህቶች በደንብ ሊያውቋቸው ይገባል። የጉባኤው አባላት ስለሚገጥሟቸው የተለያዩ ችግሮች ከልብ የሚያስቡ ከሆነ ችግራቸውን በመረዳት፣ በርኅራኄና በአዘኔታ ስሜት የሚያበረታታ ንግግር ያቀርባሉ።

      ጥሩ አስተማሪ አንድ ንግግር ግልጽ የሆነ ዓላማ ሊኖረው እንደሚገባ ያውቃል። የትምህርቱ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ በሚያስችል መንገድ መቅረብ ይኖርበታል። ይህም እነዚህን ነጥቦች በቀላሉ ለማስታወስ ያስችላል። አድማጮች ሊሠሩባቸው የሚችሏቸውን ነጥቦች መጨበጥ መቻል አለባቸው።

      የአገልግሎት ስብሰባ

      በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡትን ክፍሎች የምታቀርብበት መንገድ ትንሽ ለየት ያለ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ክፍል ብዙውን ጊዜ ጽሑፉ ላይ ያለውን ሐሳብ በሙሉ ማቅረብን እንጂ ይበልጥ ተስማሚ የሆነው ነጥብ የትኛው ነው ብሎ መምረጥን አይጠይቅም። አድማጮች በክፍሉ ውስጥ ለቀረበው ምክር ሁሉ መሠረት የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በደንብ እንዲገባቸው አድርግ። (ቲቶ 1:​9) በአብዛኛው የሚመደበው ጊዜ ውስን ስለሆነ ተጨማሪ ነጥቦች ማካተት አይቻልም።

      በሌላ በኩል ደግሞ ክፍሉ እዚያ የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ላይኖር ይችላል። ምናልባት በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣ ርዕስ ተጠቅሶ ሊሆን ይችላል። አለዚያም በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የተሰጠህ ስለ ክፍሉ የሚገልጽ ጥቂት ሐሳብ ብቻ ይሆናል። ከቀረበው ትምህርት ጋር በተያያዘ ጉባኤው የሚያስፈልገውን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት የአንተ ኃላፊነት ነው። የተፈለገውን ነጥብ የሚያስጨብጥ አጠር ያለ ምሳሌ ወይም ለትምህርቱ የሚስማማ ተሞክሮ መናገር ያስፈልግህ ይሆናል። የተጣለብህ ኃላፊነት ክፍሉን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የጉባኤው አባላት የአምላክ ቃል የሚያዝዘውን ሥራ እንዲሠሩና ይህንንም በደስታ እንዲያደርጉት በሚያበረታታ መንገድ ማስተማር እንደሆነ መዘንጋት የለብህም።​—⁠ሥራ 20:​20, 21

      ክፍልህን ስትዘጋጅ ስለ እያንዳንዱ የጉባኤው አባል አስብ። ስለሚያደርጉት ነገር አመስግናቸው። ክፍሉን በምታቀርብበት ጽሑፍ ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማና ደስተኛ እንዲሆኑ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

      ክፍልህ ሠርቶ ማሳያ ወይም ቃለ ምልልስ አለው? ከሆነ አስቀድመህ ጥሩ ዝግጅት ልታደርግበት ይገባል። ሠርቶ ማሳያ የሚያቀርቡትንም ሆነ ቃለ ምልልስ የምታደርግላቸውን ሰዎች ሌላ ሰው እንዲያዘጋጅልህ ትነግር ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ሁልጊዜ ጥሩ ውጤት አይኖረውም። ሠርቶ ማሳያውንም ሆነ ቃለ ምልልሱን በተቻለ መጠን የስብሰባው ቀን ከመድረሱ በፊት ተለማመዱት። ይህ የንግግርህ ክፍል ስለሆነ ዋናውን ትምህርት በሚያጎለብት መንገድ እንዲቀርብ ማድረግ ይኖርብሃል።

      ትላልቅ ስብሰባዎች

      ግሩም መንፈሳዊ አቋም ያላቸው እንዲሁም ጥሩ የሕዝብ ተናጋሪና አስተማሪ የሆኑ ወንድሞች በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ክፍል እንዲያቀርቡ ይመደባሉ። እነዚህ ስብሰባዎች መንፈሳዊ ትምህርት የሚቀርብባቸው ለየት ያሉ አጋጣሚዎች ናቸው። ክፍሉን

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ