የንግግርና የማስተማር ችሎታን ለማዳበር የሚረዳ ፕሮግራም
ይህ ኮርስ ትንሽ፣ ትልቅ፣ ወንድ፣ ሴት ሳይል ሁላችንም ውጤታማ በሆነ መንገድ ሐሳባችንን የመግለጽ ብቃት እንዲኖረንና የተሻልን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንድንሆን የሚረዳ ነው።
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለተመዘገቡት ተማሪዎች ክፍል የሚደለድለው የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ይሆናል። በሚቀጥሉት ሦስት ገጾች ላይ የምክር መስጫ ነጥቦችን የያዘ ቅጽ ታገኛለህ። ከእያንዳንዱ ምክር መስጫ ነጥብ ፊት የሚገኙት ቁጥሮች የጥናቶቹን ተራ ቁጥር የሚያመለክቱ ናቸው። በእያንዳንዱ ጥናት ውስጥ ደግሞ የንግግርና የማስተማር ችሎታን ለማዳበር የሚረዱ የተለያዩ ምክሮች እንዲሁም እያንዳንዱ የንግግር ባሕርይ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ የሚገልጹ ሐሳቦች ይገኛሉ። በተጨማሪም በዚያ ጥናት ውስጥ ያለውን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ የሚጠቁም መመሪያ ታገኛለህ።
የምክር መስጫ ነጥቦችን በያዘው ቅጽ ላይ ያሉት ቀለማት (1) ለአድማጮች በንባብ ለሚቀርብ ክፍል፣ (2) ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሰዎችን ለሚያሳትፍ ሠርቶ ማሳያ ወይም (3) ለጉባኤው ለሚቀርብ ንግግር የሚሠሩት ነጥቦች የትኞቹ እንደሆኑ የሚጠቁሙ ናቸው። የምትሠራበትን ነጥብ የሚመድብልህ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ነው። በአንድ ጊዜ በአንድ ነጥብ ላይ ብቻ መሥራቱ የተሻለ ነው። በተመደበልህ ጥናት መጨረሻ ላይ የሚገኘውን መልመጃ መሥራቱ ይጠቅምሃል። በዚህ ጥናት ውስጥ ያለውን ምክር በሚገባ እንደሠራህበት የሚታይ ከሆነ ምክር ሰጪህ በሚቀጥለው ጊዜ የምትሠራበትን ሌላ ነጥብ ይመድብልሃል።
ክፍልህ በሠርቶ ማሳያ የሚቀርብ ከሆነ መቼት እንዲኖርህ ያስፈልጋል። በገጽ 82 ላይ የተለያዩ መቼቶች ተዘርዝረዋል። ይሁን እንጂ መቼትህ ከዚህ ዝርዝር ውጭ መሆን አይችልም ማለት አይደለም። ምክር ሰጪህ ልምድ እንድታገኝ በማሰብ በአንድ የተወሰነ መቼት እንድትሠራ ይጠይቅህ ወይም ምርጫውን ለአንተ ይተውልህ ይሆናል።
ክፍል ሲሰጥህ ብቻ ሳይሆን በሌላም ጊዜ ይህን መጽሐፍ ማንበብህና መልመጃዎቹን መሥራትህ እድገትህን ያፋጥንልሃል። ምናልባትም በአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ አንድ ምክር መስጫ ነጥብ መሸፈን ትችል ይሆናል።
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትም ሆነ በመስክ አገልግሎት ለረጅም ጊዜ ስትካፈል የቆየህ ብትሆንም እንኳ ልታሻሽለው የምትችለው ነገር እንደሚኖር የታወቀ ነው። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንድትሆን ምኞታችን ነው።