በትምህርት ቤቱ የሚሰጡህን የተማሪ ክፍሎች መዘጋጀት
በትምህርት ቤቱ የምታቀርበው እያንዳንዱ ክፍል እድገት ማድረግ የምትችልበትን አጋጣሚ ለማግኘት ይረዳሃል። ከልብ ጥረት የምታደርግ ከሆነ አንተም እድገት እያደረግህ እንዳለ ይታወቅሃል፤ ሌሎችም ይህንን ማስተዋላቸው አይቀርም። (1 ጢሞ. 4:15) ትምህርት ቤቱ ችሎታዎችህን ይበልጥ እያሻሻልህ እንድትሄድ ያግዝሃል።
በጉባኤ ክፍል ስለማቅረብ ስታስብ ፍርሃት ፍርሃት ይልሃል? በትምህርት ቤቱ ክፍል ስታቀርብ የመጀመሪያህ ባይሆንም እንኳ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊሰማህ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን ፍርሃትህን ሊያቃልሉልህ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ይኖራሉ። እቤትህ ስትሆን ድምፅህን ከፍ አድርገህ የማንበብ ልማድ ይኑርህ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ መልስ ለመስጠት ሞክር። አስፋፊ ከሆንህ ደግሞ ዘወትር በአገልግሎት ተካፈል። ይህም በሰዎች ፊት የመናገር ልምድ እንድታዳብር ይረዳሃል። ከዚህም በተጨማሪ ክፍልህን ቀደም ብለህ ተዘጋጅና እንደምታቀርበው ሆነህ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ተለማመደው። ክፍልህን የምታቀርበው ቀና አመለካከት ላላቸው አድማጮች መሆኑን አስታውስ። ማንኛውንም ክፍል ከማቅረብህ በፊት ወደ ይሖዋ ጸልይ። ይሖዋ ወደ እርሱ ለሚጸልዩ አገልጋዮቹ መንፈስ ቅዱሱን በልግስና ይሰጣቸዋል።—ሉቃስ 11:13፤ ፊልጵ. 4:6, 7
በአንድ ጊዜ ተሞክሮ ያለው ተናጋሪ መሆን ወይም በማስተማር ረገድ ውጤታማ ሆኖ መገኘት ስለማይቻል ተዓምራዊ ለውጥ አደርጋለሁ ብለህ አትጠብቅ። (ሚክ. 6:8) ለትምህርት ቤቱ አዲስ ተማሪ ከሆንክ ገና በመጀመሪያው በሁሉም ረገድ የተዋጣለት ክፍል አቀርባለሁ ብለህ አታስብ። ከዚህ ይልቅ አንድ ክፍል ስታቀርብ በአንድ ምክር መስጫ ነጥብ ላይ ብቻ አተኩር። የምክር መስጫ ነጥቡ የተብራራበትን የዚህን መጽሐፍ ክፍል አጥና። የተሰጠውንም መልመጃ ለመለማመድ ሞክር። ይህም ክፍልህን ከማቅረብህ በፊት ከምክር መስጫ ነጥቡ ጋር በደንብ እንድትተዋወቅ የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ እንድትሻሻል ያግዝሃል።
በንባብ የሚቀርብ ክፍል መዘጋጀት
ለሌሎች ለማንበብ ስትዘጋጅ በጽሑፉ ላይ ያሉትን ቃላት ማንበብ መቻልህ ብቻውን በቂ አይደለም። የትምህርቱ መልእክት ምን እንደሆነ ለመረዳት ጥረት አድርግ። ይህን ግብ በመያዝ ክፍሉ እንደተሰጠህ ወዲያው አንብበው። ንባብህ ሐሳቡን በትክክል የሚያስተላልፍና ተገቢውን ስሜት የሚያንጸባርቅ እንዲሆን እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር የሚያስተላልፈውን መልእክት ለመረዳትና የእያንዳንዱን አንቀጽ ዋና ነጥብ ለማግኘት ሞክር። የሚቻል ከሆነ እንግዳ የሆኑትን ቃላት ትክክለኛ አነባበብ ለማወቅ ሌላ ሰው ጠይቅ። ትምህርቱ በደንብ ይግባህ። በዚህ ረገድ ወላጆች ትናንሽ ልጆቻቸውን መርዳት ያስፈልጋቸው ይሆናል።
ክፍልህ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ ወይም የተወሰኑ የመጠበቂያ ግንብ አንቀጾች በማንበብ የሚቀርብ ነውን? የምታነብበው ጽሑፍ በቋንቋህ በካሴት የተዘጋጀ ከሆነ ይህንን ካሴት በማዳመጥ የቃላቱን አነባበብ፣ አሰባበሩን፣ ግነቱን እንዲሁም የድምፅ ቃናና ፍጥነት አለዋወጡን ልብ ብሎ ማዳመጡ ሊጠቅምህ ይችላል። ከዚያም የሰማሃቸውን ነገሮች በንባብህ ለማንጸባረቅ ሞክር።
ክፍልህን መዘጋጀት ከመጀምረህ በፊት፣ የተሰጠህን የምክር መስጫ ነጥብ የሚያብራራውን ትምህርት በጥንቃቄ ማጥናት ይኖርብሃል። የተሰጠህን ክፍል ደጋግመህ ከተለማመድህ በኋላ ከቻልህ ይህንኑ ትምህርት እንደገና ከልሰው። በተቻለ መጠን ይህን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ጣር።
በዚህ መንገድ የምታገኘው ሥልጠና ለአገልግሎት ይጠቅምሃል። በመስክ አገልግሎት ስትካፈል ለሌሎች የምታነብባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ይኖሩሃል። የአምላክ ቃል የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል ስላለው ስታነብብ ጥሩ አድርገህ ማንበብህ በጣም አስፈላጊ ነው። (ዕብ. 4:12) አንድ ወይም ሁለት ክፍል ስላቀረብህ ብቻ ንባብን ውጤታማ በሚያሰኙት ዘርፎች ሁሉ ይዋጣልኛል ብለህ አታስብ። ሐዋርያው ጳውሎስ የብዙ ዓመታት ተሞክሮ ለነበረው ክርስቲያን ሽማግሌ ሲጽፍ “እኔ እስክመጣ ድረስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለሕዝብ በማንበብ . . . ትጋ” ብሎታል።—1 ጢሞ. 4:13 የ1980 ትርጉም
ከጭብጡና ከመቼቱ ጋር የሚስማማ ዝግጅት
በትምህርት ቤቱ እንድታቀርበው የተሰጠህ ክፍል መቼት ያለው ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
ትኩረት የሚያሻቸው ሦስት ዋና ዋና ነገሮች አሉ። እነዚህም:- (1) የተመደበልህ ጭብጥ (2) መቼትህና የምታነጋግረው ሰው እንዲሁም (3) እንድትሠራበት የተሰጠህ ምክር መስጫ ነጥብ ናቸው።
ለተሰጠህ ጭብጥ የሚስማሙ ነጥቦችን ማሰባሰብ ያስፈልግሃል። ይሁን እንጂ ብዙ ከመግፋትህ በፊት ስለ መቼትህና ስለምታነጋግረው ሰው በጥሞና አስብ። ምክንያቱም መቼትህና የምታነጋግረው ሰው ማንነት የምታቀርባቸውን ነጥቦችና የትምህርቱን አቀራረብ ይወስናሉ። የምትጠቀመው መቼት ምን ዓይነት ነው? ለምታውቀው ሰው ምሥራቹን እንዴት እንደምታቀርብ የሚያሳይ ነው? ወይስ አንድን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነጋግር የሚያሳይ? ግለሰቡ በዕድሜ ከአንተ ይበልጣል ወይስ ያንሳል? ልታወያየው ስላሰብከው ርዕሰ ጉዳይ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይችላል? ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይስ ከአሁን ቀደም ምን የሚያውቀው ነገር ይኖራል? ውይይቱን ስታደርግ ይዘኸው የተነሣኸው ዓላማ ምንድን ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ምን ማድረግ እንዳለብህ ይጠቁምሃል።
የተሰጠህን ጭብጥ ለማዳበር የሚረዳ ሐሳብ ከየት ማግኘት ትችላለህ? በዚሁ መጽሐፍ ከገጽ 33 እስከ 38 ላይ “ምርምር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?” በሚል ርዕስ የቀረበ ትምህርት አለ። ይህንን ምዕራፍ አንብብና ልታገኛቸው የምትችላቸውን ለምርምር የሚረዱ ጽሑፎች ተጠቀም። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምትፈልገው በላይ ብዙ ሐሳቦችን እንደምታገኝ እሙን ነው። ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ምን ያህል መረጃ ማግኘት እንደምትችል ለማወቅ አቅምህ የፈቀደውን ያህል አንብብ። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ለክፍልህ ልትጠቀምበት ያሰብከውን መቼትም ሆነ የምታነጋግረውን ግለሰብ ማንነት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። ተስማሚ ሆነው ያገኘሃቸው ነጥቦች ላይ ምልክት አድርግ።
ለክፍልህ የሚሆኑትን ነጥቦች መርጠህ ከማጠናቀቅህ በፊት የተሰጠህን የምክር መስጫ ነጥብ አንብብ። ክፍል የምታቀርብበት ዋናው ምክንያት የምክር መስጫ ነጥቡን እንድትሠራበት ነው።
የተመደበልህ ጊዜ ካለቀ ማቆም ስላለብህ ነጥቦችህን በተሰጠህ ጊዜ ውስጥ መጨረስህ ንግግርህን ባሰብከው መንገድ በመደምደም እርካታ እንድታገኝ ያስችልሃል። በመስክ አገልግሎት ግን የሰዓት ጉዳይ ሁልጊዜ አሳሳቢ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ ስትዘጋጅ ምን ያህል ጊዜ እንደ ተሰጠህ ግምት ውስጥ አስገባ። ሆኖም ትልቁ ነገር ትምህርቱን በጥሩ ሁኔታ ማቅረብህ ነው።
ስለ መቼቱ ጥቂት እንበል:- በገጽ 82 ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች በመመርመር በአገልግሎትህ የሚጠቅምህንና ትምህርቱን ተግባራዊ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የሚረዳህን አንድ መቼት ምረጥ። በትምህርት ቤቱ ክፍል ስታቀርብ ቆይተህ ከሆነ ይህንን አጋጣሚ ለተጨማሪ ኃላፊነት ብቁ ሆኖ ለመገኘትና ለአገልግሎት የሚረዳህን ችሎታ ለማዳበር ተጠቀምበት።
መቼቱን የሰጠህ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካቹ ከሆነ በዚህ በተሰጠህ መቼት ለመሥራት ሞክር። ብዙዎቹ መቼቶች ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱን መቼት በአገልግሎት ተጠቅመህበት የማታውቅ ከሆነ በዚህ ረገድ ተሞክሮ ያላቸውን አስፋፊዎች ምክር ጠይቅ። ከቻልክ በትምህርት ቤቱ ልትጠቀምበት ያሰብከውን መቼት ተጠቅመህ የክፍልህን ነጥቦች በአገልግሎት ከምታገኘው ሰው ጋር ተወያይባቸው። ይህን ማድረግህ የሥልጠናውን ዋና ዓላማ ዳር ለማድረስ ይረዳሃል።
በንግግር የሚቀርብ ክፍል
ወንዶች አጭር ንግግር ለጉባኤው እንዲያቀርቡ ይመደባሉ። እነዚህን ክፍሎች ስትዘጋጅ ልታስብባቸው የሚገቡት መሠረታዊ ነጥቦች በሠርቶ ማሳያ የሚቀርቡትን የተማሪ ክፍሎች በተመለከተ ከተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ጉልህ ልዩነት የሚኖረው በአድማጮችና በአቀራረብ ረገድ ነው።
አብዛኛውን ጊዜ ሁሉም አድማጮች ከትምህርቱ ሊጠቀሙ በሚችሉበት መንገድ መዘጋጀቱ የተሻለ ይሆናል። በስብሰባው ላይ ከተገኙት መካከል አብዛኞቹ መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያውቃሉ። የምታቀርበውንም ርዕሰ ጉዳይ በደንብ ያውቁት ይሆናል። ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ የሚያውቁት ምን ያህል ነው የሚለውን ግምት ውስጥ አስገባ። አድማጮችህ ከምታቀርበው ክፍል በሆነ መልኩ ጥቅም እንዲያገኙ ለመርዳት ጥረት አድርግ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ይህ ርዕሰ ጉዳይ እኔም ሆንኩ አድማጮቼ ለይሖዋ ያለንን አድናቆት እንድናሳድግ የሚረዳን እንዴት ነው? ትምህርቱ የአምላክን ፈቃድ እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው? የሥጋ ምኞት ገንኖ በሚታይበት ዓለም ውስጥ ጤናማ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው?’ (ኤፌ. 2:3) ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስትጠቅስ ጥቅሶቹን አንብበህ ብቻ ከማለፍ ይልቅ ልታብራራቸው እንዲሁም እነዚህ ጥቅሶች ወደ አንድ መደምደሚያ ለመድረስ የሚረዱት እንዴት እንደሆነ ግልጽ ልታደርግ ይገባል። (ሥራ 17:2, 3) ብዙ ነጥብ ለማካተት አትሞክር። ትምህርቱን በቀላሉ ማስታወስ በሚያስችል መንገድ አቅርበው።
በዝግጅትህ ወቅት ስለ አቀራረብህም ልታስብ ይገባል። ይህ ትኩረት ልትሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ክፍልህን ለሌሎች እንደምታቀርብ ሆነህ ተለማመድ። የተለያዩ የንግግር ባሕርያትን ለማጥናትና ምክሩን ሥራ ላይ ለማዋል የምታደርገው ጥረት ለእድገትህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። አዲስም ሆንክ ልምድ ያለህ ተናጋሪ በጉዳዩ እንደምታምንበት በሚያሳይ መንገድና ለትምህርቱ በሚስማማ ስሜት ለመናገር እንድትችል ጥሩ ዝግጅት አድርግ። በትምህርት ቤቱ የሚሰጥህን እያንዳንዱን ክፍል ተዘጋጅተህ ስታቀርብ ዓላማህ ይሖዋ የሰጠህን የንግግር ችሎታ ለእርሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ መጠቀም እንደሆነ አትዘንጋ።—መዝ. 150:6