የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ተስማሚ የድምፅ መጠን
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • ጥናት 8

      ተስማሚ የድምፅ መጠን

      ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

      ንግግር ስትሰጥ የድምፅህ መጠን ወይም ኃይል በቂ ሊሆን ይገባል። የድምፅህ መጠን ተስማሚ መሆንና አለመሆኑን ለመወሰን (1) የአድማጮችህን ብዛትና እነማን መሆናቸውን፣ (2) የሚረብሹ ድምፆች መኖር አለመኖራቸውን፣ (3) የሚቀርበውን ትምህርት እንዲሁም (4) ዓላማህን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል።

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      አድማጮችህ በቀላሉ ሊሰሙህ ካልቻሉ አእምሮአቸው ሽርሽር ሊሄድ እንዲሁም የምታቀርበው ትምህርት ግልጽ ላይሆንላቸው ይችላል። በጣም ከጮህክ ደግሞ ሊረበሹ አልፎ ተርፎም ለእነርሱ አክብሮት እንደሌለህ ሊሰማቸው ይችላል።

      አንድ የሕዝብ ተናጋሪ የሚፈለገውን ያህል የድምፅ መጠን ከሌለው አንዳንዶቹ አድማጮች ማንቀላፋት ሊጀምሩ ይችላሉ። አንድ አስፋፊ በአገልግሎት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ቅስስ የሚል ከሆነ ከልብ ላያዳምጡት ይችላሉ። በስብሰባዎች ላይም ቢሆን አድማጮች መልስ ሲሰጡ ድምፃቸው በደንብ የማይሰማ ከሆነ መልሳቸው ሌሎችን የሚያበረታታ ሊሆን አይችልም። (ዕብ. 10:​24, 25) በሌላ በኩል ደግሞ ተናጋሪው የማያስፈልግ ቦታ ላይ ድምፁን ከፍ የሚያደርግ ከሆነ አድማጮቹ ሊሳቀቁ አልፎ ተርፎም ሊረበሹ ይችላሉ።​—⁠ምሳሌ 27:​14

      አድማጮችህን ግምት ውስጥ አስገባ። እየተናገርህ ያለኸው ለማን ነው? ለአንድ ግለሰብ? ለቤተሰብ? በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ ለተገኙ ጥቂት ወንድሞች? ለመላው ጉባኤ? ወይስ በትልቅ ስብሰባ ላይ ለተገኙ ብዙ ሰዎች? ለእያንዳንዱ ሁኔታ ተስማሚ የሚሆነው የድምፅ መጠን የተለያየ ነው።

      የአምላክ አገልጋዮች ብዙ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ንግግር ያደረጉባቸው ጊዜያት ነበሩ። በሰሎሞን ዘመን በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ ሲመረቅ የድምፅ ማጉያ መሣሪያ አልነበረም። ከዚህም የተነሣ ሰሎሞን ሕዝቡን በመረቀበት ወቅት ከፍ ብሎ በተሠራ መድረክ ላይ ቆሞ “በታላቅ ድምፅ” መናገር አስፈልጎታል። (1 ነገ. 8:​55፤ 2 ዜና 6:​12, 13) ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በፈሰሰበት ወቅት በኢየሩሳሌም የነበሩት ጥቂት ክርስቲያኖች የሚናገሩትን ለመስማት ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ነበር። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በመካከላቸው ‘በመቆም ድምፁንም ከፍ አድርጎ’ ተናገረ። (ሥራ 2:​14) በዚህ መንገድ የአድማጮቹን ልብ የሚነካ ምሥክርነት ሰጥቷል።

      የድምፅህ መጠን ለሁኔታው የሚስማማ መሆን አለመሆኑን እንዴት ማወቅ ትችላለህ? ይህንን ማወቅ የምትችልበት አንዱ ጥሩ ዘዴ የአድማጮችን ሁኔታ መመልከት ነው። ከአድማጮች መካከል አንዳንዶቹ ለመስማት እንደተቸገሩ ካስተዋልክ የድምፅህን መጠን ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል።

      እየተናገርህ ያለኸው ለአንድ ግለሰብም ይሁን በርከት ላሉ ሰዎች አድማጭህን ግምት ውስጥ ማስገባትህ ብልህነት ነው። የመስማት ችግር ያለበት ሰው ከሆነ ድምፅህን ከፍ ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። ይሁን እንጂ በዕድሜ ስለገፉ ብቻ ከእነርሱ ጋር ስትነጋገር ጮክ ብለህ የምታወራ ከሆነ ደስ አይላቸውም። እንዲያውም ለእነርሱ አክብሮት የጎደለህ ሊያስመስልብህ ይችላል። በአንዳንድ ባሕሎች ጮክ ብሎ መናገር መቆጣትን ወይም ትዕግሥት ማጣትን የሚያመለክት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።

      የሚረብሹ ድምፆችን ግምት ውስጥ አስገባ። በአገልግሎት ላይ ከሰዎች ጋር ስትነጋገር የምትጠቀምበትን የድምፅ መጠን ለመወሰን የሚረዳህ በወቅቱ የሚኖረው ሁኔታ ነው። በመንገድ ላይ የሚተላለፉ ተሽከርካሪዎች፣ የሚንጫጩ ልጆች፣ የሚጮኹ ውሾች፣ ከፍ ተደርጎ የተከፈተ ሙዚቃ ወይም ቴሌቪዥን ከሚያሰሙት ድምፅ በላይ መናገር ይኖርብህ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ በጣም የተጠጋጉ ቤቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የጎረቤቶችን ትኩረት እስከምትስብ ድረስ ጮክ ብለህ የምትናገር ከሆነ የምታነጋግረው ሰው ሊሸማቀቅ ይችላል።

      በጉባኤ ወይም በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ንግግር የሚያቀርቡ ወንድሞችም የተለያዩ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል። ሜዳ ላይ ለተሰበሰቡ ሰዎችና ድምፅ ጥርት ብሎ እንዲሰማ በሚያስችል አዳራሽ ውስጥ ለተሰበሰቡ አድማጮች ንግግር መስጠት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በላቲን አሜሪካ ሁለት ሚስዮናውያን በአቅራቢያቸው በሚገኝ አደባባይ ርችት እየተተኮሰና ከጎረቤት ያለማቋረጥ የሚጮህ ዶሮ እየረበሻቸው ፍላጎት በነበረው አንድ ሰው መኖሪያ ግቢ ውስጥ የሕዝብ ንግግር ለመስጠት ተገድደዋል!

      ንግግር እየሰጠህ እያለ የሚረብሽ ድምፅ ቢፈጠር ጋብ እስኪል ድረስ ቆም ማለት ወይም ድምፅህን ከፍ አድርገህ መናገር ሊያስፈልግህ ይችላል። ለምሳሌ ስብሰባው የሚካሄደው ጣሪያው ቆርቆሮ በሆነ አዳራሽ ውስጥ ከሆነ ድንገት ኃይለኛ ዝናብ መዝነብ ቢጀምር አድማጮች ተናጋሪውን ማዳመጥ ሊቸገሩ ይችላሉ። የሚያለቅስ ሕፃን ካለ ወይም አርፍደው የመጡ ሰዎች እየገቡ ከሆነ የሚረብሽ ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። አድማጮች ትኩረታቸው ሳይሰረቅ ከምታቀርበው ትምህርት የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ ለማድረግ አንድ እርምጃ መውሰድ ይኖርብሃል።

      የድምፅ ማጉያ መሣሪያ መኖሩ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ይሁንና መሣሪያው ቢኖርም ድምፅህን ከፍ አድርገህ እንድትናገር የሚጠይቅ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በተደጋጋሚ ጊዜ የኤሌክትሪክ መቋረጥ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ተናጋሪዎች ያለ ማይክሮፎን ንግግራቸውን ለመቀጠል ይገደዳሉ።

      ትምህርቱን ግምት ውስጥ አስገባ። የትምህርቱ ይዘት የምትጠቀመውን የድምፅ መጠን በመወሰን ረገድ የራሱ ድርሻ አለው። ርዕሰ ጉዳዩ ጠንከር ባለ መንገድ መቅረብ የሚያስፈልገው ከሆነ ድምፅህን ለስለስ በማድረግ የትምህርቱን ኃይል ማዳከም አይኖርብህም። ለምሳሌ ያህል የውግዘት መልእክት ያዘለ ጥቅስ በምታነብበት ጊዜ የሚኖርህ የድምፅ መጠን ፍቅር ስለማሳየት የሚመክር ጥቅስ ከምታነብበት የድምፅ መጠን ይበልጥ ጠንከር ማለት ይኖርበታል። የድምፅህ መጠን ለትምህርቱ የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። ይህን ስታደርግ ግን የአድማጮችን ትኩረት ወደ ራስህ እንዳትስብ መጠንቀቅ አለብህ።

      ዓላማህን ግምት ውስጥ አስገባ። አድማጮችህን በቅንዓት ለማነሳሳት ድምፅህን ጠንከር ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። ሆኖም የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያደርጉ የምትፈልግ ከሆነ ከሚገባ በላይ ጮክ ብለህ በመናገር ትኩረታቸውን እንዲነፍጉህ ልታደርግ አይገባም። ለማጽናናት የምትፈልግ ከሆነ ብዙውን ጊዜ ለስለስ ያለ ድምፅ መጠቀሙ የተሻለ ይሆናል።

      ከፍ ባለ የድምፅ መጠን በአግባቡ መጠቀም። በሥራ የተጠመደ አንድ ሰው ትኩረቱን እንዲሰጥህ ከፈለግህ አብዛኛውን ጊዜ ድምፅህን ከፍ አድርገህ መናገርህ የተሻለ ይሆናል። ወላጆች ይህን ስለሚያውቁ ልጆቻቸው ጨዋታቸውን አቁመው ወደቤት እንዲገቡ በሚጣሩበት ጊዜ ጮክ ብለው ይናገራሉ። በተጨማሪም በጉባኤ ወይም በትልቅ ስብሰባ ላይ የመድረክ ሊቀ መንበር ሆኖ የሚያገለግል ወንድም አድማጮች ቦታቸውን እንዲይዙ ድምፁን ከፍ አድርጎ መናገር ሊያስፈልገው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ አስፋፊዎች አገልግሎት ላይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሰላምታ መስጠት ያስፈልጋቸው ይሆናል።

      ሰውዬው አንተን ማዳመጥ ከጀመረም በኋላ ቢሆን በቂ የድምፅ መጠን ሊኖርህ ይገባል። በጣም ዝቅ ያለ ድምፅ ተናጋሪው በቂ ዝግጅት ያላደረገ ወይም በሚናገረው ነገር በደንብ የማያምንበት ሊያስመስል ይችላል።

      ድምፅህን ከፍ አድርገህ የምትናገረው መልእክት ትእዛዝ አዘል ከሆነ ሰዎችን ለተግባር ሊያነሳሳ ይችላል። (ሥራ 14:​9, 10) በተመሳሳይም ጮክ ባለ ድምፅ የሚሰጥ ትእዛዝ ሰዎች ላይ አደጋ እንዳይደርስ ለማስጠንቀቅ ሊረዳ ይችላል። በፊልጵስዩስ አንድ የእስር ቤት ጠባቂ እስረኞቹ ያመለጡ ስለመሰለው ራሱን ሊገድል አስቦ ነበር። “ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ:- ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ።” በዚህ ምክንያት ሰውዬው ሕይወቱን ከማጥፋት ድኗል። ከዚያ በኋላ ጳውሎስና ሲላስ ለእስር ቤቱ ጠባቂና ለቤተሰቡ መስክረውላቸው ሁሉም እውነትን ለመቀበል በቅተዋል።​—⁠ሥራ 16:​27-33

      የድምፅህን መጠን ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች ሲናገሩ ተስማሚ የድምፅ መጠን ለመጠቀም ለየት ያለ ጥረት በማድረግ መለማመድ ያስፈልጋቸዋል። አንድ ሰው ድምፁ ሰላላ ይሆንና በሚናገርበት ጊዜ በደንብ አይሰማ ይሆናል። ድምፁ ወፍራም ይሆንለታል ማለት ባይሆንም ጥረት ካደረገ ማሻሻል ይችላል። አተነፋፈስህንና አቋቋምህን ተከታተል። ቀጥ ብለህ መቀመጥና መቆምን ተለማመድ። ትከሻህን ወደኋላ ለጠጥ አድርገህ አየር በደንብ ወደ ውስጥ አስገባ። የሳንባዎችህ የታችኛው ክፍሎች በአየር ሊሞሉ ይገባል። በምትናገርበት ጊዜ የድምፅህን መጠን መቆጣጠር የምትችለው ይህን በሳንባህ የታችኛው ክፍሎች የተጠራቀመውን አየር በተገቢ ሁኔታ እየተቆጣጠርህ ስታወጣ ነው።

      የአንዳንዶች ችግር ደግሞ በሚናገሩበት ጊዜ ከልክ በላይ መጮህ ነው። ይህን ልማድ ያዳበሩት ከቤት ውጭ ወይም ጫጫታ በሚበዛበት አካባቢ ስለሚሠሩ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ በባሕላቸው ሰዎች እየተጯጯሁ ማውራታቸውና አንዱ በሌላው ንግግር መሐል ጣልቃ መግባቱ የተለመደ ሊሆን ይችላል። ከዚህ የተነሣ ሌሎች እንዲያዳምጧቸው ሲሉ ይበልጥ ጮክ ማለት እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይችላል። “ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሥራ ላይ እያዋሉ ሲሄዱ በተገቢው የድምፅ መጠን መነጋገርን ይለምዳሉ።​—⁠ቆላ. 3:​12

      ጥሩ ዝግጅት ማድረግ፣ በመስክ አገልግሎት አዘውትረህ በመካፈል ተሞክሮህን ማዳበር እንዲሁም ወደ ይሖዋ መጸለይ ተስማሚ የድምፅ መጠን እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል። ንግግር ስታቀርብም ይሁን በአገልግሎት ካገኘኸው ሰው ጋር ስትነጋገር አድማጭህ እየተናገርኸው ካለው ነገር እንዲጠቀም ልትረዳው የምትችለው እንዴት እንደሆነ አጥብቀህ ልታስብ ይገባል።​—⁠ምሳሌ 18:​21

  • ድምፅን መለዋወጥ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • ጥናት 9

      ድምፅን መለዋወጥ

      ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

      የድምፅህን አወጣጥ መለዋወጥ። በዚህ ጥናት ውስጥ የድምፅን መጠን፣ ፍጥነትና ቃና ስለ መለዋወጥ እንመለከታለን።

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      እንደ አስፈላጊነቱ ድምፅን እየለዋወጡ መናገር ንግግሩ ሕያው እንዲሆን ያደርጋል፣ የአድማጮችን ስሜት ይቀሰቅሳል እንዲሁም ለተግባር ያነሳሳል።

      ይህ ባሕርይ በንግግርህ የማይንጸባረቅ ከሆነ አድማጮች ርዕሰ ጉዳዩ ብዙም እንዳልማረከህ ሊሰማቸው ይችላል።

      በአስፈላጊው ቦታ እያጠበቅህ መናገርህ አድማጮች የምትናገረውን ነገር በቀላሉ እንዲረዱ ያስችላቸዋል። የድምፅህን መጠን፣ ፍጥነትና ቃና በሚገባ እየለዋወጥህ መናገርህ ደግሞ ንግግሩ የበለጠ ጣዕምና ለዛ ያለው እንዲሆን ይረዳል። ከዚህም በላይ አድማጮች ስለ ትምህርቱ ያለህን ስሜት እንዲረዱ ያስችላል። ከመድረክ ስትናገርም ይሁን በመስክ አገልግሎት ካገኘኸው ሰው ጋር ስትወያይ አንተ ለትምህርቱ ያለህ ዝንባሌ በአድማጭህም ላይ ይንጸባረቃል።

      የሰው ድምፅ በብዙ መንገድ ሊለዋወጥ የሚችል ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ነው። በሚገባ ከተጠቀምንበት አንድን ንግግር ሕያው ሊያደርግ፣ የአድማጮችን ልብ ሊነካና ስሜታቸውን ሊቀሰቅስ እንዲሁም ለተግባር ሊያነሳሳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ የት ቦታ ላይ ስትደርስ የድምፅህን መጠን እንደምትጨምር ወይም እንደምትቀንስ፣ ፍጥነትህን እንደምትለውጥ ወይም ቃናህን እንደምትቀይር ማስታወሻህ ላይ ምልክት ስላደረግህ ብቻ ይህን ግብ ማሳካት አትችልም። እንዲህ ባሉት ምልክቶች እየተመሩ ድምፅን ለመለዋወጥ መሞከር ውበት አይኖረውም። ንግግርህ ለዛ ያለውና ሕያው እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ አድማጮችህ ዘና ብለው እንዳይከታተሉህ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ድምፅን እየለዋወጡ መናገር በግድ የሚመጣ የንግግር ባሕርይ አይደለም።

      አንድ ተናጋሪ በጥሩ ሁኔታ ድምፁን እየለዋወጠ የሚናገር ከሆነ አድማጮቹ ትምህርቱን ተመስጠው ይከታተላሉ እንጂ ትኩረታቸው በእርሱ ላይ አይሆንም።

      የድምፅህን መጠን እንደ ሁኔታው አስተካክል። የድምፅህን አወጣጥ ከምትለዋውጥባቸው መንገዶች አንዱ የድምፅህን መጠን እንደ ሁኔታው ማስተካከል ነው። ይህ ሲባል ግን አለፍ አለፍ እያሉ ድምፅን አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ ማድረግ ማለት አይደለም። እንደዚያ ማድረግህ የትምህርቱን መልእክት ያዛባል። አሁንም አሁንም ጮክ እያልክ የምትናገር ከሆነ በአድማጮችህ ላይ የሚያሳድረው ስሜት ጥሩ አይሆንም።

      በንግግር ወቅት የምትጠቀምበት የድምፅ መጠን ለትምህርቱ የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። በ⁠ራእይ 14:​6, 7 ወይም በ⁠ራእይ 18:​4 ላይ እንደሚገኘው ያለ አጣዳፊ ትእዛዝ ወይም በ⁠ዘጸአት 14:​13, 14 ላይ እንደሰፈረው ያለ ጠንካራ እምነት የተንጸባረቀበት ንግግር እያነበብህ ነው እንበል። እንደነዚህ ባሉት አጋጣሚዎች ድምፅህን በመጠኑ ከፍ አድርገህ መናገርህ ተገቢ ይሆናል። በተመሳሳይም በ⁠ኤርምያስ 25:​27-38 ላይ የሚገኘውን የመሰለ የውግዘት መልእክት በምታነብበት ጊዜ የድምፅህን መጠን መለዋወጥህ በጥቅሱ ውስጥ ያሉት አንዳንድ አገላለጾች ከሌሎቹ ይልቅ ጎልተው እንዲታዩ ያደርጋል።

      በተጨማሪም የንግግርህን ዓላማ ግምት ውስጥ አስገባ። ዓላማህ አድማጮችህን ለተግባር ማነሳሳት ነው? ወይስ የትምህርቱ ዋና ነጥብ ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ? በጥበብ ከተጠቀምህበት የድምፅህን መጠን ከፍ ማድረግህ ይህን ዓላማህን ለማሳካት ይረዳሃል። ሆኖም እንዲሁ መጮህ ዓላማህን ሊያከሽፍብህ ይችላል። ለምን? የምትናገረው ነገር ወዳጃዊ ስሜት ማንጸባረቅን እንጂ የድምፅ መጠን መጨመርን የሚጠይቅ ላይሆን ይችላል። ይህን በጥናት 11 ላይ እንመለከተዋለን።

      በደንብ በታሰበበት መንገድ ድምፅን ዝቅ ማድረግ አድማጮች ቀጥሎ የምትናገረውን ነገር በጉጉት እንዲጠባበቁ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ወዲያው ድምፅህን ጋል ማድረግ ይኖርብሃል። ዝቅ ባለ ድምፅ ረገጥ አድርጎ መናገር ስጋትን ወይም ፍርሃትን ለመግለጽ ሊያገለግል ይችላል። በተጨማሪም በዙሪያው ካለው ሐሳብ አንጻር ሲታይ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጠውን ነጥብ ለመግለጽ ድምፅን ዝቅ አድርጎ መናገር ይቻላል። ንግግሩ ተጀምሮ እስኪያልቅ ዝቅ ባለ ድምፅ የምትናገር ከሆነ ግን በምትናገረው ነገር እርግጠኛ እንዳልሆንክ ወይም ርዕሰ ጉዳዩ ብዙም ያልማረከህ ሊያስመስል ይችላል። ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ለስለስ ያለ የድምፅ ቃና ስትጠቀም ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ሊኖርህ ይገባል።

      ፍጥነትህን መለዋወጥ። በዕለት ተዕለት ንግግራችን ብዙም ሳንጨነቅ የምንፈልገውን መልእክት ማስተላለፍ እንችላለን። ልዩ ስሜት ስላሳደረብን ነገር ስንናገር ፍጥነት ይኖረናል። የምንናገረውን ነገር ሰዎች በትክክል እንዲያስታውሱ በምንፈልግበት ጊዜ ግን የንግግራችን ፍጥነት ይቀንሳል።

      ይሁን እንጂ ለመድረክ አዲስ የሆኑ ብዙ ተናጋሪዎች ፍጥነታቸውን አይለዋውጡም። ለምን? የሚናገሯቸው ቃላት በጥንቃቄ የተጠኑ ስለሆኑ ነው። ምናልባትም አንድ በአንድ ጽፈውት ይመጡ ይሆናል። ምንም እንኳ ንግግራቸውን ቀጥታ በንባብ መልክ ባያቀርቡትም በቃላቸው ሸምድደውት ሊሆን ይችላል። ከዚህ የተነሣ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የንግግር ፍጥነታቸው አንድ ዓይነት ይሆናል። በአስተዋጽኦ የመጠቀም ልማድ ማዳበር ይህን ችግር ለማረም ይረዳል።

      እያዘገመች ትሄድ የነበረች ድመት፣ ውሻ ስታይ ድንገት ተስፈንጥራ እንደምትሮጥ ሁሉ በድንገት የድምፅህን ፍጥነት አትጨምር። በተጨማሪም የምትናገራቸውን ቃላት አጥርቶ ለመስማት እስኪያስቸግር ድረስ መፍጠን አይኖርብህም።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ