-
አካላዊ መግለጫዎችበቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
-
-
ጥናት 12
አካላዊ መግለጫዎች
በአንዳንድ ባሕሎች ሰዎች ሲያወሩ አካላዊ መግለጫዎችን እንደ ልብ ይጠቀማሉ። በሌሎች ባሕሎች ደግሞ ሁኔታው እንደዚያ ላይሆን ይችላል። ይሁንና ሁሉም ሰው ለማለት ይቻላል ከአንድ ግለሰብ ጋር ሲወያይም ይሁን ንግግር ሲሰጥ ፊቱ ላይ ከሚነበበው ስሜት በተጨማሪ አንዳንድ አካላዊ መግለጫዎችን መጠቀሙ አይቀርም።
ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ አካላዊ መግለጫዎችን ይጠቀሙ ነበር። በአንድ ወቅት አንድ ሰው እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ይፈልጋሉ የሚል መልእክት ይዞ ወደ ኢየሱስ መጣ። ኢየሱስም “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል ከጠየቀ በኋላ ‘እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ:- እነሆ እናቴና ወንድሞቼ’ በማለት እንደተናገረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ማቴ. 12:48, 49) ከሌሎች ቦታዎች በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ በሥራ 12:17 እና 13:16 ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስም ሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ አካላዊ መግለጫ እንደተጠቀሙ ይጠቁማል።
ሐሳብንና ስሜትን መግለጽ የሚቻለው በድምፅ ብቻ ሳይሆን አካላዊ መግለጫዎችን በመጠቀም ጭምር ነው። አንድ ተናጋሪ አካላዊ መግለጫዎችን በሚገባ ሳይጠቀም ከቀረ ለንግግሩ ብዙም ትኩረት እንዳልሰጠ ሊያስመስልበት ይችላል። ይሁን እንጂ አካላዊ መግለጫዎችን ጥሩ አድርጎ መጠቀም ንግግሩ የተዋጣለት እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ሌላው ቀርቶ በስልክ እንኳ ስትነጋገር እንደ አስፈላጊነቱ አካላዊ መግለጫዎችን የምትጠቀም ከሆነ መልእክትህ ምን ያህል ክብደት እንዳለውና አንተ ራስህ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚሰማህ ከድምፅህ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። እንግዲያው በቃልህ ስትናገርም ይሁን ከጽሑፍ ስታነብብ ወይም አድማጮች ቀና ብለው እያዩህም ይሁን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እያነበቡ በማንኛውም ጊዜ አካላዊ መግለጫዎችን መጠቀምህ በጣም አስፈላጊ ነው።
የምትጠቀምባቸው አካላዊ መግለጫዎች ከመጽሐፍ የተጠኑ መሆን የለባቸውም። ሳቅን ወይም ቁጣን ከሌላ ሰው አልተማርክም። አካላዊ መግለጫዎች በውስጥህ ያለውን ስሜት የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው። እነዚህ መግለጫዎች ብዙ ሳትጨነቅ በራሳቸው የሚመጡ ከሆነ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል።
አካላዊ መግለጫዎች በጥቅሉ በሁለት ይከፈላሉ። እነርሱም ገላጭና ማጠናከሪያ ይባላሉ። ገላጭ የሚባሉት አንድን ድርጊት የሚገልጹ ወይም መጠንና አቅጣጫን የሚጠቁሙ ናቸው። በትምህርት ቤቱ ውስጥ አካላዊ መግለጫዎች በሚለው ነጥብ በምትሠራበት ጊዜ አንድ ወይም ሁለት አካላዊ መግለጫ በማሳየትህ ብቻ መርካት የለብህም። ንግግርህ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ብዙም ሳትጨነቅ አካላዊ መግለጫዎችን ለማሳየት ሞክር። ይህንን ማድረግ የሚያስቸግርህ ከሆነ አቅጣጫን፣ ርቀትን፣ መጠንን፣ ቦታን ወይም አቀማመጥን ለሚያመለክቱ ቃላት ትኩረት መስጠቱን ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ሌሎች ስለ አንተ የሚኖራቸውን ግምት እያሰብህ ከመጨነቅ ይልቅ በትምህርቱ መመሰጥና ንግግርህም ሆነ እንቅስቃሴህ እንደወትሮህ እንዲሆን ማድረግህ አስፈላጊ ነው። አንድ ሰው ዘና ብሎ የሚናገር ከሆነ አካላዊ መግለጫዎችን ለማሳየት አይቸገርም።
ማጠናከሪያ የሚባሉት አካላዊ መግለጫዎች የተናጋሪውን ስሜትና ጽኑ እምነት የሚያንጸባርቁ ናቸው። መልእክቱን ለማጉላት፣ ሕያው ለማድረግና ይበልጥ ለማጠናከር ያገለግላሉ። ማጠናከሪያ አካላዊ መግለጫዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው። ይሁን እንጂ ካልተጠነቀቅህ አጉል ልማድ ሊሆኑብህም ይችላሉ። አንድ ዓይነት አካላዊ መግለጫ ደግመህ ደጋግመህ የምትጠቀም ከሆነ ንግግርህን የሚያጠናክር መሆኑ ይቀርና የአድማጮችን ትኩረት ወደ አንተ የሚስብ ይሆናል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በዚህ ረገድ ችግር እንዳለብህ ከጠቆመህ ለተወሰነ ጊዜ ገላጭ የሆኑትን አካላዊ መግለጫዎች ብቻ ለመጠቀም ሞክር። ከጊዜ በኋላ ማጠናከሪያ አካላዊ መግለጫዎችን እንደገና መጠቀም ልትጀምር ትችላለህ።
ማጠናከሪያ አካላዊ መግለጫዎችን ምን ያህል መጠቀም እንዳለብህና የትኞቹን ብትጠቀም የተሻለ እንደሚሆን ለመወሰን የሚያዳምጡህን ሰዎች ስሜት ከግምት ውስጥ አስገባ። ጣትህን ብትቀስርባቸው ልታሸማቅቃቸው ትችላለህ። በአንዳንድ ባሕሎች አንድ ወንድ መገረሙን ለማሳየት አፉን በእጁ እንደ መያዝ የመሳሰሉ አካላዊ መግለጫዎችን ቢጠቀም እንደ ሴት እንደተቅለሰለሰ ሊቆጠርበት ይችላል። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ አንዲት ሴት እጆቿን እያወራጨች የምትናገር ከሆነ ሥርዓታማ እንዳልሆነች ተደርጎ ይታያል። እንግዲያው እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ባለባቸው አካባቢዎች እህቶች ከእጆቻቸው ይልቅ ፊት ላይ በሚነበቡ መግለጫዎች ይበልጥ መጠቀም ያስፈልጋቸው ይሆናል። በየትኛውም የዓለም ክፍል ለማለት ይቻላል አንድ ሰው በጥቂት ሰዎች ፊት የተጋነነ አካላዊ መግለጫ የሚጠቀም ከሆነ ሆነ ብሎ ሰዎችን ለማሳቅ እንዳደረገው ሊቆጠር ይችላል።
ተሞክሮ እያዳበርክ ስትሄድና ይበልጥ በነፃነት መናገር ስትጀምር የምትጠቀምባቸው ማጠናከሪያ አካላዊ መግለጫዎች በሙሉ ውስጣዊ ስሜትህን የሚገልጹና በጉዳዩ ከልብ እንደምታምንበት የሚያሳዩ ይሆናሉ። ንግግርህንም ይበልጥ ሕያው ያደርጉልሃል።
ፊትህ ላይ የሚነበበው ስሜት። ከየትኛውም የሰውነት ክፍል ይልቅ ብዙውን ጊዜ ስሜትህ የሚነበበው ፊትህ ላይ ነው። ዓይኖችህ እንዲሁም የአፍህና የጭንቅላትህ እንቅስቃሴ ሁሉ የየራሳቸው መልእክት አላቸው። አንድም ቃል ሳትተነፍስ ፊትህ ላይ ግዴለሽነት፣ መጸየፍ፣ ግራ መጋባት፣ መገረም ወይም ደስታ ሊነበብ ይችላል። ፊት ላይ የሚነበቡት እንዲህ ያሉት ስሜቶች የሚነገረውን ቃል ይበልጥ ሕያው ያደርጉታል። አምላክ በፊታችን አካባቢ በአጠቃላይ ከ30 የሚበልጡ ጡንቻዎችን ፈጥሮልናል። ፈገግ ስትል ከእነዚህ መካከል ግማሽ የሚያህሉትን ጡንቻዎች ትጠቀማለህ።
ከመድረክ ስትናገርም ይሁን በመስክ አገልግሎት ስትሳተፍ ለአድማጮችህ አንድ አስደሳች መልእክት ልታካፍላቸው እየሞከርህ ነው። ሞቅ ያለ ፈገግታ ማሳየትህ ደግሞ ይህንኑ እንዲገነዘቡ የሚረዳቸው ይሆናል። በሌላ በኩል ፊትህ ላይ ምንም ዓይነት ስሜት የማይነበብ ከሆነ አድማጮች ከልብ እየተናገርህ መሆንህን ሊጠራጠሩ ይችላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ፈገግታ ማሳየትህ በደግነት እያነጋገርካቸው እንዳለ እንዲሰማቸው ያደርጋል። በተለይ ዛሬ ብዙ ሰዎች የማያውቁት ሰው ሲያነጋግራቸው ስጋት ስለሚያድርባቸው ፈገግ ማለትህ በጣም አስፈላጊ ነው። ፈገግታህ ሰዎች ዘና እንዲሉና በቀላሉ መልእክትህን እንዲቀበሉ ሊያደርግ ይችላል።
-
-
አድማጮችን ማየትበቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
-
-
ጥናት 13
አድማጮችን ማየት
ዓይናችን በውስጣችን የሚሰማንን ስሜትና አመለካከታችንን ያንጸባርቃል። መገረም፣ ፍርሃት፣ ርኅራኄ፣ ፍቅር፣ ጥርጣሬ ወይም ሐዘን ሊነበብበት ይችላል። አንድ አረጋዊ ሰው አብረዋቸው ብዙ መከራ ስላሳለፉ የአገራቸው ልጆች ሲናገሩ “በዓይናችን እንግባባ ነበር” ብለዋል።
ሌሎች ደግሞ ዓይናችን የሚያርፍበትን በማየት ስለ እኛም ሆነ ስለምንናገረው ነገር አንድ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። በብዙ ባሕሎች ሰዎች በወዳጃዊ ስሜት እያየ የሚያነጋግራቸውን ግለሰብ ማመን አይከብዳቸውም። በአንጻሩ ደግሞ መሬት መሬት የሚያይ ወይም ዓይኑ ሌላ ቦታ የሚያማትር ሰው ከገጠማቸው ሰውዬው ከልቡ እየተናገረ መሆኑን ወይም ችሎታውንና ብቃቱን ሊጠራጠሩ ይችላሉ። በሌሎች ባሕሎች ደግሞ አንድ ሰው ሲያወራ ትክ ብሎ ዓይን ዓይን የሚያይ ከሆነ እንደ ዓይን አውጣነት ወይም እንደ ድፍረት ይቆጠርበታል። ከተቃራኒ ፆታ ወይም ከአለቃው ወይም ከሌላ ባለ ሥልጣን ጋር ሲነጋገርም ቢሆን ትክ ብሎ የሚያይ ከሆነ ተመሳሳይ ስሜት ሊያሳድር ይችላል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ አንድ ልጅ ከአረጋዊ ሰው ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ ዓይኑን የማይሰብር ከሆነ እንደናቃቸው ይቆጠራል።
ይሁን እንጂ እንደ ነውር የማይቆጠር ከሆነ አንድ በጣም አስፈላጊ ነጥብ ስንናገር የሰውዬውን ዓይን ትኩር ብለን ማየታችን ለመልእክቱ ክብደት ይሰጠዋል። ተናጋሪው ጉዳዩን ከልብ እንደሚያምንበትም ሊያሳይ ይችላል። ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ተገርመው “እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል?” ብለው በጠየቁ ጊዜ ኢየሱስ እንዴት እንደመለሰላቸው ልብ በል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- ‘ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ:- ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው።’ (ማቴ. 19:25, 26) ሐዋርያው ጳውሎስም በአድማጮቹ ፊት ላይ የሚነበበውን ስሜት በአንክሮ ይከታተል እንደነበር ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳያሉ። በአንድ ወቅት ጳውሎስ ንግግር ሲሰጥ ከልጅነቱ ጀምሮ ሽባ የነበረ አንድ ሰው በቦታው ተገኝቶ ነበር። ሥራ 14:9, 10 እንዲህ ይላል:- ‘ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ይሰማ ነበር፤ እርሱም ትኵር ብሎ ተመለከተውና ይድን ዘንድ እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፣ በታላቅ ድምፅ:- ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም አለው። ብድግ ብሎም ተነሥቶ ይመላለስ ነበር።’
ለመስክ አገልግሎት የሚረዱ ሐሳቦች። በመስክ አገልግሎት ስትካፈል ሰዎችን በወዳጅነትና በፍቅር አነጋግራቸው። ውይይቱን ለመጀመር እንደ ሁኔታው በጋራ የሚያሳስባችሁን ጉዳይ በተመለከተ አንድ ጥያቄ ልታነሳ ትችላለህ። በዚህ ጊዜ የአድማጭህን ዓይን ለማየት ወይም ቢያንስ ገጽታውን በአክብሮትና በደግነት ለመመልከት ጥረት አድርግ። ውስጣዊ ደስታው ዓይኑ ላይ የሚነበብ ሰው የሚያሳየው ሞቅ ያለ ፈገግታ በጣም ይማርካል። ይህም ምን ዓይነት ሰው እንደሆንህ እንዲገነዘብ የሚያስችለው ከመሆኑም ሌላ ዘና ብሎ እንዲያዳምጥህ ሊያደርገው ይችላል።
በሰውዬው ዓይን ላይ የሚነበበውን ስሜት ማስተዋልህ ምን ማድረግ እንዳለብህ ሊጠቁምህ ይችላል። ሰውዬው ከተቆጣ ወይም ደግሞ ምንም ፍላጎት ከሌለው ይህንን ስሜቱን መረዳት ትችል ይሆናል። የምትነግረው ነገር ግራ አጋብቶት ከሆነም ይህንን ልታስተውል ትችላለህ። ቶሎ ከአንተ መገላገል ከፈለገ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ይህንን መረዳት አይቸግርህም። በጉጉት እያዳመጠ ከሆነም ይህን ስሜቱን በግልጽ ማንበብ ይቻላል። ዓይኑ ላይ የሚነበበው ስሜት ፍጥነትህን እንደ አስፈላጊነቱ ለማስተካከል፣ እርሱን ይበልጥ በውይይቱ ለማሳተፍ፣ ውይይቱን ለማቆም ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ በአጭሩ ለማሳየት እንድትወስን ሊረዳህ ይችላል።
ስትመሰክርም ይሁን መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና የሰውዬውን ዓይን በአክብሮት እያየህ ለማነጋገር ጥረት አድርግ። ይሁን እንጂ ሊያሳፍረው ስለሚችል አታፍጥጥበት። (2 ነገ. 8:11) ሆኖም አለፍ አለፍ እያልህ ከሌላው ጊዜ ባልተለየ አስተያየት በወዳጅነት መንፈስ ተመልከተው። ይህ በብዙ አገሮች ከልብ የመነጨ አሳቢነትን የሚገልጽ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሌላ ጽሑፍ ስታነብብለት ዓይንህ ጽሑፉ ላይ ማረፉ አይቀርም። ይሁን እንጂ አንድ ነጥብ ለማጥበቅ ስትፈልግ ለአፍታም ቢሆን ሰውዬውን ትክ ብለህ ትመለከተው ይሆናል። አለፍ አለፍ እያልክ ቀና ብለህ ማየትህ እየተነበበ ስላለው ነገር ምን እንደተሰማው ለማስተዋል ይረዳሃል።
ዓይን አፋር ከሆንክና መጀመሪያ አካባቢ አድማጭህን እያየህ መናገር ከተቸገርህ ተስፋ አትቁረጥ። ልምድ እያገኘህ ስትሄድ እንደ አስፈላጊነቱ አድማጭህን ማየት ቀላል ይሆንልህና ከሌሎች ጋር በምታደርገው ውይይት ይበልጥ ውጤታማ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል።
ንግግር ስታቀርብ። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተራራ ስብከቱን ከመጀመሩ በፊት “ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ” በማለት ይነግረናል። (ሉቃስ 6:20) ከእርሱ ምሳሌ ተማር። ለተሰበሰቡ ሰዎች የምትናገር ከሆነ ንግግርህን ከመጀመርህ በፊት ለጥቂት ሰኮንዶች ቆም በልና በሙሉ ዓይንህ ተመልከታቸው። ይህ በብዙ ቦታዎች በአድማጮች መካከል ያሉ አንዳንድ ሰዎችን ነጥሎ መመልከትን ይጨምራል። ወደ ንግግርህ
-