-
ትምህርት አዘል ምሳሌዎችበቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
-
-
ነበር። ዳዊት ራሱ እረኛ ስለነበር የዚህች ጠቦት ባለቤት ምን ሊሰማው እንደሚችል አሳምሮ ያውቃል። ይህ ድሃ ሰው የነበረችውን አንዲት ጠቦት ከጉያው ነጥቆ በወሰደው ባለጠጋ ድርጊት ዳዊት እጅግ ተቆጣ። ከዚያም ናታን “ያ ሰው አንተ ነህ” ሲል በቀጥታ ነገረው። ዳዊት ልቡ ስለተነካ እውነተኛ ንስሐ ገብቷል። (2 ሳሙ. 12:1-14) ልምድ እያገኘህ ስትሄድ የሰዎችን ስሜት የሚነኩ ጉዳዮችን በጥበብ መያዝ ትማራለህ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት ታሪኮች መካከል ለማስተማር የሚረዱ ብዙ ግሩም ምሳሌዎችን መጥቀስ ትችላለህ። ኢየሱስ “የሎጥን ሚስት አስቡአት” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ታሪክ ለማስተማር ተጠቅሞበታል። (ሉቃስ 17:32) ሥልጣኑን እንደያዘ የሚጠቁሙትን ምልክቶች ሲዘረዝር ‘የኖኅን ዘመን’ ጠቅሷል። (ማቴ. 24:37-39) ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ውስጥ የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ 16 ወንዶችና ሴቶችን በስም ጠቅሷል። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በደንብ እያወቅህ ስትሄድ በውስጡ የተጠቀሱትን ሰዎችና ክንውኖች እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ጥሩ አድርገህ ማስተማር ትችላለህ።—ሮሜ 15:4፤ 1 ቆሮ. 10:11
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በዚህ ዘመን የተፈጸሙ እውነተኛ ታሪኮችን በመጥቀስ ትምህርቱን ማጠናከሩ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህንን ስታደርግ የምትጠቅሰው ታሪክ እውነተኝነቱ የተረጋገጠና በአድማጮች መካከል ያሉትን አንዳንድ ሰዎች የማያሸማቅቅ መሆን ይኖርበታል። ወይም በአድማጮች አእምሮ ውስጥ ከርዕሱ ጋር የማይገናኝ አወዛጋቢ ጥያቄ እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆን የለበትም። ደግሞም ተሞክሮውን ስትጠቅስ አንድ ዓላማ ይዘህ መሆን እንዳለበት አትዘንጋ። ከንግግርህ ዓላማ የሚያዘናጉ አላስፈላጊ ዝርዝር ጉዳዮችን መተረክ የለብህም።
አድማጮች በቀላሉ ይረዱታል? የምትጠቀምበት ምሳሌ ምንም ዓይነት ይሁን ምን የሚያከናውነው አንድ ዓላማ ሊኖር ይገባል። ምሳሌው እየተወያያችሁበት ካለው ርዕስ ጋር ምን ዝምድና እንዳለው ባታስረዳቸው አድማጮችህ ራሳቸው ሊያዛምዱት ይችላሉ?
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “የዓለም ብርሃን” እንደሆኑ ከተናገረ በኋላ ሰዎች መብራትን እንዴት እንደሚጠቀሙበትና ይህም ለደቀ መዛሙርቱ ምን ትርጉም እንዳለው በአጭሩ ገልጿል። (ማቴ. 5:15, 16) ስለጠፋችው በግ ከተናገረው ምሳሌ በኋላ ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ምን ያህል ደስታ እንደሚሆን ገልጿል። (ሉቃስ 15:7) ስለ ደጉ ሳምራዊ ታሪክ ከተናገረ በኋላም ያዳምጠው ለነበረው ሰው አንድ ግልጽ ጥያቄ በማቅረብ እርሱም እንደዚያው እንዲያደርግ ቀጥተኛ ምክር ሰጥቶታል። (ሉቃስ 10:36, 37) በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ስለተለያዩ የአፈር ዓይነቶችና በማሳው ውስጥ ስለተዘራው እንክርዳድ የሚገልጹትን ምሳሌዎች ትርጉም የማወቅ ጉጉት ለነበራቸው ጥቂት አድማጮቹ አብራርቶላቸዋል። (ማቴ. 13:1-30, 36-43) ኢየሱስ ከመሞቱ ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ ነፍሰ ገዳይ ስለሆኑ የወይን አትክልት ገበሬዎች ምሳሌ ተናግሯል። ምሳሌው ግልጽ ስለነበር ምንም ማብራሪያ መስጠት አላስፈለገውም። ‘የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተውለው ነበር።’ (ማቴ. 21:33-45) ስለዚህ አንድ ምሳሌ ከጠቀስክ በኋላ ከጉዳዩ ጋር ለማዛመድ ተጨማሪ ማብራሪያ የመስጠቱን አስፈላጊነትም ሆነ የማብራሪያውን ርዝማኔ የሚወስነው የምሳሌው ዓይነት፣ የአድማጮች አመለካከትና ምሳሌውን የጠቀስክበት ዓላማ ነው።
ምሳሌዎችን ጥሩ አድርጎ የመጠቀም ችሎታን ማዳበር ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም በውጤቱ ትደሰታለህ። ምሳሌው በደንብ የታሰበበት ከሆነ የአድማጮችን አእምሮና ልብ ይማርካል። እውነታውን እንዲሁ ተናግሮ ከማለፍ ይልቅ በምሳሌ አስደግፎ ማስረዳት መልእክቱ ይበልጥ ኃይል እንዲኖረው ያደርጋል።
-
-
የተለመዱ ነገሮችን ምሳሌ አድርጎ መጠቀምበቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
-
-
ጥናት 46
የተለመዱ ነገሮችን ምሳሌ አድርጎ መጠቀም
የምትጠቀምበት ምሳሌ ምንም ይሁን ምን ከትምህርቱ ጋር የሚስማማ መሆን እንዳለበት አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ ጥሩ ውጤት እንዲኖረው ከተፈለገ ከትምህርቱ ብቻ ሳይሆን ከአድማጮችም ሁኔታ ጋር ሊጣጣም ይገባል።
ንግግር ስትሰጥ የምትጠቀምባቸውን ምሳሌዎች በመምረጥ ረገድ የአድማጮችህ ማንነት ወሳኝ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያደርግ ነበር? እርሱን ለመስማት ለሚሰበሰቡት ሰዎችም ይሁን ለደቀ መዛሙርቱ ንግግር ሲሰጥ የሚጠቀምባቸው ምሳሌዎች በእስራኤል ምድር የሚኖር ማንኛውም ሰው በቀላሉ የሚያውቃቸው ነበሩ። በሌሎች ባሕሎች ብቻ የሚታወቁ ነገሮችን እንደ ምሳሌ ተጠቅሞ ቢሆን ኖሮ ለአድማጮቹ እንግዳ ይሆንባቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ስለ ግብፅ የቤተ መንግሥት ሕይወት ወይም ስለ ሕንድ ሃይማኖታዊ ልማድ ምንም የጠቀሰው ነገር የለም። ያም ሆኖ ምሳሌዎቹ በሁሉም አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ከሚያውቋቸው ነገሮች ጋር የተያያዙ ነበሩ። ልብስ ስለ መጣፍ፣ ስለ መነገድ፣ ውድ ዕቃ ስለጠፋበት ሰው እንዲሁም ለሠርግ ስለ መታደም ጠቅሷል። ሰዎች የተለያየ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ምን እንደሚሰማቸው ያውቅ ስለነበር ምሳሌዎቹም ይህንኑ የሚያንጸባርቁ ነበሩ። (ማር. 2:21፤ ሉቃስ 14:7-11፤ 15:8, 9፤ 19:15-23) ኢየሱስ በዋነኝነት ይሰብክ የነበረው ለእስራኤል ሕዝብ ስለሆነ በምሳሌዎቹ የሚጠቅሰው በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያዩአቸውንና የሚያደርጓቸውን ነገሮች ነበር። ከዚህ የተነሳ ስለ ግብርና፣ በበጎችና በእረኛቸው መካከል ስላለው ግንኙነት እንዲሁም ከእንስሳት ቆዳ የተሠራ አቁማዳ ለወይን ጠጅ ማከማቻነት እንዴት እንደሚያገለግልና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ጠቅሷል። (ማር. 2:22፤ 4:2-9፤ ዮሐ. 10:1-5) በተጨማሪም አድማጮቹ የሚያውቋቸውን ታሪኮች እየጠቀሰ ተናግሯል። የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት መፈጠር፣ የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ፣ የሰዶምና ጎሞራ ጥፋት እንዲሁም የሎጥ ሚስት አሟሟት ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። (ማቴ. 10:15፤ 19:4-6፤ 24:37-39፤ ሉቃስ 17:32) አንተስ የምትጠቀምባቸውን ምሳሌዎች ስትመርጥ በአድማጮችህ ዘንድ የተለመዱ ተግባሮችን እንዲሁም ባሕላቸውን ግምት ውስጥ ታስገባለህ?
ለአንድ ሰው ወይም ለጥቂት ሰዎች ብቻ እየተናገርህ ቢሆንስ? ለእነዚህ ሰዎች የሚስማማ ምሳሌ ለመምረጥ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። ኢየሱስ በሲካር የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት ሴት ሲመሠክር ‘የሕይወት ውኃ፣’ “ለዘላለም አይጠማም” እንዲሁም “ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ” የሚሉትን አነጋገሮች ተጠቅሟል። እነዚህ ሁሉ ከሴትዮዋ ሥራ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ናቸው። (ዮሐ. 4:7-15) መረባቸውን ሲያጥቡ ካገኛቸው ሰዎች ጋር ሲነጋገር የተጠቀመባቸው ምሳሌያዊ አነጋገሮች ከዓሣ ማጥመድ ሥራ ጋር የተያያዙ ነበሩ። (ሉቃስ 5:2-11) ሳምራዊቷ ሴትም ሆነች ዓሣ አጥማጆቹ የሚኖሩበት ኅብረተሰብ በግብርና የሚተዳደር ስለነበር ስለ ግብርና የሚጠቅሱ ምሳሌዎችን ሊጠቀም ይችል ነበር። ሆኖም በቀጥታ ከሰዎቹ ሥራ ጋር የተያያዘ ምሳሌ መጥቀሱ ነጥቡ ቁልጭ ብሎ እንዲታያቸው አድርጓል። አንተስ እንዲህ ለማድረግ ትጥራለህ?
ኢየሱስ የሰበከው “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች” ሲሆን ጳውሎስ ደግሞ የተላከው ለእስራኤላውያን ብቻ ሳይሆን ለአሕዛብም ጭምር ነበር። (ማቴ. 15:24፤ ሥራ 9:15) ታዲያ ይህ ጳውሎስ በሚጠቀምባቸው ምሳሌዎች ላይ ያመጣው ለውጥ ነበር? አዎን። በቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ሲጽፍ ስለ ሩጫ ውድድር፣ በጣዖት ቤት ተገኝቶ ስለመመገብ እንዲሁም ስለ ድል ሰልፍ ጠቅሷል። እነዚህ ምሳሌዎች ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች በደንብ የሚያውቋቸው ነገሮች ነበሩ።—1 ቆሮ. 8:1-10፤ 9:24, 25፤ 2 ቆሮ. 2:14-16
እንደ ኢየሱስና እንደ ጳውሎስ የምታስተምርባቸውን ምሳሌዎች በጥንቃቄ ትመርጣለህ? የአድማጮችህን ሕይወትና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ ታስገባለህ? እርግጥ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ወዲህ በዓለም ላይ ብዙ ለውጦች ተካሂደዋል። ብዙ ሰዎች በቴሌቪዥን አማካኝነት የዓለምን ዜና ስለሚከታተሉ በተለያዩ አገሮች ስላሉት ሁኔታዎች ያውቃሉ። አድማጮችህ ይህ አጋጣሚ ካላቸው በዜና የሰማሃቸውንና ያየሃቸውን ነገሮች እንደ ምሳሌ ብትጠቅስ ምንም አይደለም። ያም ሆኖ ሰዎች ልባቸው ይበልጥ የሚነካው ከግል ሕይወታቸው ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ማለትም ስለ ቤታቸው፣ ስለ ቤተሰባቸው፣ ስለ ሥራቸው፣ ስለሚመገቡት ምግብና ስለ አካባቢያቸው የአየር ጠባይ ቢጠቀስ ነው።
አድማጮች የተጠቀምህበትን ምሳሌ እንዲረዱት ብዙ ማብራራት የሚያስፈልግህ ከሆነ የጠቀስከው ነገር በእነርሱ ዘንድ የተለመደ አይደለም ማለት ነው። እንዲህ ያለው ምሳሌ የትምህርቱን ቁም ነገር ያድበሰብስብሃል። ከዚህ የተነሣ አድማጮችህ ልታስተምር የፈለግኸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ረስተው ምሳሌውን ብቻ ሊያስታውሱ ይችላሉ።
ኢየሱስ እንደ ምሳሌ የተጠቀመው ቀላልና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ጉዳዮችን እንጂ የተወሳሰቡ ነገሮችን አልነበረም። ከባድ ወይም ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮችን ለማስረዳት ቀላል ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። ኢየሱስ ቅዱስ ጽሑፋዊውን እውነት ከዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ጋር በማዛመድ ትምህርቱን እንዲረዱትና እንዲያስታውሱት አድርጓል። ይህ የማስተማር ዘዴ ልንኮርጀው የሚገባ እንዴት ግሩም ምሳሌ ነው!
-