የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
    • ምዕራፍ 4

      ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?

      እውነት ወይስ ሐሰት?

      መጠናናት የጀመሩ ሁለት ሰዎች በምንም ተአምር መነካካት የለባቸውም።

      □ እውነት

      □ ሐሰት

      አንድ ወንድና አንዲት ሴት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ባይፈጽሙም ዝሙት እንደፈጸሙ የሚያስቆጥር ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ።

      □ እውነት

      □ ሐሰት

      መጠናናት የጀመሩ ወንድና ሴት በመተቃቀፍ፣ በመደባበስ እና በመሳሳም ፍቅራቸውን ካልገለጹ ይዋደዳሉ ማለት አይቻልም።

      □ እውነት

      □ ሐሰት

      ይህን ጉዳይ ብዙ ጊዜ አስበህበት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ከአንዲት ወጣት ጋር እየተጠናናህ ከሆነ ፍቅራችሁን የምትገልጹበት መንገድ ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ እንደሆነ ማወቅ አስቸጋሪ ሊሆንባችሁ ይችላል። እስቲ እውነት ወይም ሐሰት ብለህ እንድትመልስ ከላይ የቀረቡትን ሦስት ጥያቄዎች እንመርምር፤ ከዚያም “ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት የአምላክ ቃል እንዴት እንደሚረዳን እንመለከታለን።

      ● መጠናናት የጀመሩ ሁለት ሰዎች በምንም ተአምር መነካካት የለባቸውም።

      ሐሰት። መጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት ባለውና ተገቢ በሆነ መልኩ ፍቅርን መግለጽን አይከለክልም። ለምሳሌ ያህል፣ በጣም ስለሚዋደዱ አንዲት ሱላማጢስ ወጣትና አንድ እረኛ የሚናገር ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። እነዚህ ወጣቶች የሚጠናኑት ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ነበር። ያም ሆኖ ከመጋባታቸው በፊትም ቢሆን በአንዳንድ መንገዶች አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን ይገልጹ እንደነበር ከታሪኩ በግልጽ መመልከት ይቻላል። (ማሕልየ መሓልይ 1:2፤ 2:6፤ 8:5) በዛሬው ጊዜም ለመጋባት የወሰኑ አንድ ወንድና ሴት ንጹሕ በሆነ መንገድ ፍቅራቸውን መግለጻቸው ተገቢ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል።a

      ይሁንና የሚጠናኑ ሰዎች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። መሳሳም፣ መተቃቀፍ ወይም የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ማንኛውንም ነገር ማድረግ የፆታ ብልግና ወደ መፈጸም ሊያመራ ይችላል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንዲህ ያሉትን የፍቅር መግለጫዎች የሚያሳዩት በንጹሕ ልቦና ተነሳስተው ቢሆንም እንኳ ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው በቀላሉ የፆታ ብልግና ሊፈጽሙ ይችላሉ።​—ቆላስይስ 3:5

      ● አንድ ወንድና አንዲት ሴት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ባይፈጽሙም ዝሙት እንደፈጸሙ የሚያስቆጥር ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ።

      እውነት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዝሙት” ተብሎ የተተረጎመው ፖርኒያ የተባለው የግሪክኛ ቃል ሰፊ ትርጉም አለው። ይህ ቃል ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን ማንኛውንም ዓይነት የፆታ ግንኙነትና የፆታ ብልቶችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀምን ያመለክታል። በመሆኑም ዝሙት የሚለው ቃል የሚያመለክተው የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸምን ብቻ ሳይሆን በአፍና በፊንጢጣ የፆታ ግንኙነት እንደ መፈጸምና የሌላውን የፆታ ብልት እንደ ማሻሸት የመሳሰሉትን ድርጊቶች ጭምር ነው።

      መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘው ዝሙት መፈጸምን ብቻ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ናቸው፤ እነሱም፦ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ብልግና [ናቸው።] . . . እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።”​—ገላትያ 5:19-21

      “ርኩሰት” ምንድን ነው? “ርኩሰት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በንግግርም ሆነ በድርጊት የጎደፉ መሆንን ያመለክታል። እጅን የሌላው ሰውነት ውስጥ ማስገባት፣ የሌላውን ልብስ ለማወላለቅ መሞከር ወይም ሊነኩ የማይገባቸውን የሰውነት ክፍሎች ለምሳሌ ጡትን መደባበስ ርኩስ ድርጊት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጡትን መደባበስን የሚገልጸው በተጋቡ ሰዎች መካከል ብቻ ከሚፈጸሙ ድርጊቶች እንደ አንዱ አድርጎ ነው።​—ምሳሌ 5:18, 19

      አንዳንድ ወጣቶች ያለምንም እፍረት የአምላክን መሥፈርቶች ይጥሳሉ። ሆን ብለው ገደቡን ያልፋሉ፤ አሊያም ስግብግብ በመሆን ካገኙት ሰው ሁሉ ጋር የፆታ ርኩሰት ለመፈጸም ይፈልጋሉ። እንደዚህ የሚያደርጉ ወጣቶች ሐዋርያው ጳውሎስ “ብልግና” ብሎ የጠራውን ድርጊት ፈጽመዋል ሊባል ይችላል። “ብልግና” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ‘ጋጠወጥነት፣ ልቅነት፣ ስድነት፣ ገደብ የለሽ የፆታ ፍላጎት’ የሚል ፍቺ አለው። “የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለደነዘዘ በስግብግብነት ማንኛውንም ዓይነት ርኩሰት ለመፈጸም ራሳቸውን ለብልግና አሳልፈው ሰጥተዋል” እንደተባሉት ሰዎች መሆን እንደማትፈልግ ግልጽ ነው።​—ኤፌሶን 4:17-19

      ● መጠናናት የጀመሩ ወንድና ሴት በመተቃቀፍ፣ በመደባበስ እና በመሳሳም ፍቅራቸውን ካልገለጹ ይዋደዳሉ ማለት አይቻልም።

      ሐሰት። አንዳንዶች ከሚያስቡት በተቃራኒ ተገቢ ያልሆኑ የፍቅር መግለጫዎች በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር አያደርጉም። ከዚህ ይልቅ በመካከላቸው መከባበርና መተማመን እንዳይኖር ያደርጋሉ። ሎራ የገጠማትን ሁኔታ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን እናቴ ባልነበረችበት ሰዓት የወንድ ጓደኛዬ ቴሌቪዥን ለማየት በሚል ሰበብ ቤታችን መጣ። መጀመሪያ ላይ እጄን ብቻ ነበር የያዘኝ። ይሁንና ሳላስበው ሰውነቴን ይደባብሰኝ ጀመር። እጁን እንዲሰበስብ ብነግረው ተበሳጭቶ ሊሄድ ይችላል ብዬ ስላሰብኩ ‘ተው’ እንዳልለው ፈራሁ።”

      የሎራ የወንድ ጓደኛ ከልቡ የሚወዳት ይመስልሻል? ወይስ የሚፈልገው የራሱን ስሜት ለማርካት ብቻ ነበር? አንድ ሰው ርኩሰት እንድትፈጽሙ ሊያነሳሳሽ የሚሞክር ከሆነ ከልቡ ይወድሻል ማለት ይቻላል?

      አንድ ወጣት፣ የሴት ጓደኛው ካገኘችው ክርስቲያናዊ ሥልጠና ጋር የሚጋጭና ሕሊናዋን የሚያቆሽሽ ድርጊት እንድትፈጽም የሚገፋፋት ከሆነ የአምላክን ሕግ የሚጥስ ከመሆኑም በላይ ለእሷ ያለው ፍቅር እውነተኛ መሆኑ አጠያያቂ እንዲሆን ያደርጋል። እንዲህ ያለው ድርጊት እንዲፈጸምባት የምትፈቅድ ወጣትም ብትሆን መጠቀሚያ እየሆነች ነው። ከዚህ የከፋው ደግሞ ርኩሰት መፈጸሟ ነው፤ አልፎ ተርፎም ዝሙት ልትፈጽም ትችላለች።b​—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

      ግልጽ የሆኑ ገደቦችን አብጁ

      እየተጠናናችሁ ከሆነ ተገቢ ያልሆኑ የፍቅር መግለጫዎችን ከማሳየት መቆጠብ የምትችሉት እንዴት ነው? ግልጽ የሆኑ ገደቦችን አስቀድሞ ማበጀት የጥበብ እርምጃ ነው። ምሳሌ 13:10 (NW) “እርስ በርስ በሚመካከሩ ሰዎች ዘንድ . . . ጥበብ አለ” ይላል። ተገቢ የሚባለው የፍቅር መግለጫ ምን ዓይነት እንደሆነ አስቀድማችሁ ተነጋገሩ። ስሜታችሁ ከተነሳሳ በኋላ ገደብ ለማበጀት መሞከር ቤታችሁ በእሳት ቢያያዝ እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ እስኪሆን ድረስ እርምጃ ሳትወስዱ እንደመቆየት ይሆናል።

      እርግጥ ነው፣ በተለይ መጠናናት እንደጀመራችሁ አካባቢ እንዲህ ያለውን ውይይት ማድረግ ከባድ እንዲያውም የሚያሳፍር ሊሆንባችሁ ይችላል። ሆኖም አስቀድማችሁ ገደብ ማበጀታችሁ በኋላ ላይ ከባድ ችግር ውስጥ እንዳትገቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ገደቦች ማበጀታችሁ እሳት ሊያስነሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ከማስወገድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ስለ እነዚህ ጉዳዮች መወያየት መቻላችሁ ግንኙነታችሁ የሚያዛልቅ መሆኑን ይጠቁማል። ደግሞም በጋብቻ ውስጥ በፆታ ግንኙነት ለመደሰት ራስን መግዛትንና ትዕግሥትን ማዳበር እንዲሁም ራስ ወዳድነትን ማስወገድ እጅግ አስፈላጊ ነው።​—1 ቆሮንቶስ 7:3, 4

      ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ቀላል እንዳልሆነ አይካድም። ያም ቢሆን ይሖዋ በሚሰጥህ ምክር መተማመን ትችላለህ። በኢሳይያስ 48:17 ላይ ይሖዋ “የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። ይሖዋ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንድታገኝ ይመኝልሃል!

      ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 24 ተመልከት

      በሚቀጥለው ምዕራፍ

      አንዲት ወጣት ድንግልናዋን ጠብቃ ስለቆየች ችግር አለባት ማለት አይደለም። እንዲያውም እንዲህ ማድረጓ የጥበብ አካሄድ ነው። እንዲህ የምንልበትን ምክንያት እስቲ እንመልከት።

      [የግርጌ ማስታወሻዎች]

      a በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ያልተጋቡ ወንድና ሴት በሰዎች ፊት ፍቅራቸውን መግለጻቸው ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ከመሆኑም ሌላ እንደ ነውር ይቆጠራል። ክርስቲያኖች ሌሎችን የሚያሰናክል ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ አለባቸው።​—2 ቆሮንቶስ 6:3

      b በዚህ አንቀጽ ላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች እንደሚሠሩ ግልጽ ነው።

      ቁልፍ ጥቅስ

      “ፍቅር . . . ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም።”​—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

      ጠቃሚ ምክር

      ከፍቅር ጓደኛችሁ ጋር ለመጠናናት ስትገናኙ ሌሎችም እንዲኖሩ አድርጉ፤ አሊያም ቢያንስ አንድ ሰው አብሯችሁ መሆን ይኖርበታል። ችግር ውስጥ እንድትገቡ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን አስወግዱ፤ ለምሳሌ የቆመ መኪና ወይም ቤት ውስጥ ብቻችሁን አትሁኑ።

      ይህን ታውቅ ነበር?

      ተጫጭታችሁ ከሆነ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋችኋል። ይሁን እንጂ በስልክ ስታወሩም ሆነ የጽሑፍ መልእክት ስትላላኩ የፆታ ስሜትን ለመቀስቀስ የታሰቡ ቃላትን መጠቀም ርኩሰት ነው።

      ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

      የሥነ ምግባር ብልግና ወደ መፈጸም ሊመሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማስወገድ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

      የፍቅር ጓደኛዬ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንድንፈጽም ሊገፋፋኝ ቢሞክር እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

      ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

      ምን ይመስልሃል?

      ● ከፍቅር ጓደኛችሁ ጋር አብራችሁ ስትሆኑ በመካከላችሁ በሚኖረው አካላዊ ቅርበት ረገድ ምን ዓይነት ገደብ ታበጃላችሁ?

      ● በዝሙት፣ በርኩሰትና፣ በብልግና መካከል ያለውን ልዩነት አብራራ።

      [በገጽ 46 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      “እኔና እጮኛዬ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ስለመቆየት የሚገልጹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አብረን አንብበናል። እነዚህ ጽሑፎች ንጹሕ ሕሊና እንድንይዝ እንደረዱን ይሰማናል።”​—ለቲሺያ

      [በገጽ 44 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ገደቡን አልፋችሁ ብትሄዱስ?

      ተገቢ ያልሆነ ነገር ከፈጸማችሁ ምን ማድረግ አለባችሁ? ችግሩን በራሳችሁ እንደምታስተካክሉት በማሰብ ራሳችሁን አታታልሉ። አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “‘ሁለተኛ እንዲህ እንዳናደርግ እርዳን’ ብዬ እጸልይ ነበር። ገደቡን ሳናልፍ በመመላለስ ረገድ አንዳንድ ጊዜ ቢሳካልንም የተሳሳትንባቸው ወቅቶችም ነበሩ።” ስለዚህ ጉዳዩን ለወላጆቻችሁ መንገር ያስፈልጋችኋል። መጽሐፍ ቅዱስም ‘የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንድትጠሩ’ የሚያበረታታ ጠቃሚ ምክር ይሰጣል። (ያዕቆብ 5:14) እነዚህ ክርስቲያን እረኞች ከአምላክ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ለማስተካከል የሚረዳችሁ ምክር፣ ተግሣጽና ወቀሳ ይሰጧችኋል።

      [በገጽ 47 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ቤታችሁ በእሳት ቢያያዝ እርምጃ ለመውሰድ እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ እስኪሆን ትጠብቃላችሁ? በፍቅር መግለጫዎች ረገድ ገደብ ለማበጀትም ስሜታችሁ እስኪነሳሳ መጠበቅ የለባችሁም

  • ድንግልናዬን መጠበቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
    • ምዕራፍ 5

      ድንግልናዬን መጠበቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?

      “ከየአቅጣጫው የሚመጣው ተጽዕኖ ‘የፆታ ግንኙነት ምን እንደሚመስል ሞክሬ ባየው’ ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል።”​—ኬሊ

      “የፆታ ግንኙነት ሳልፈጽም እስካሁን መቆየቴ ያሳፍረኛል።”​—ጆርደን

      “ዘንድሮም ድንግል ነሽ?”a እንዲህ ያለው ጥያቄ ሽምቅቅ እንድትዪ ያደርግሽ ይሆናል። በብዙ ቦታዎች አንዲት ወጣት ድንግል ከሆነች ችግር እንዳለባት ተደርጋ ትታያለች። ከዚህ አንጻር በርካታ ወጣቶች ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ መሆኑ ምንም አያስገርምም!

      ፍላጎታችሁና እኩዮቻችሁ የሚያሳድሩባችሁ ተጽዕኖ

      ክርስቲያን ከሆንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከዝሙት እንድትርቂ’ የሚሰጠውን ማሳሰቢያ ታውቂያለሽ። (1 ተሰሎንቄ 4:3) ያም ሆኖ የፆታ ስሜትሽን መቆጣጠር አስቸጋሪ ሊሆንብሽ ይችላል። ፖል የተባለ ወጣት እንዲህ ሲል በግልጽ ተናግሯል፦ “አንዳንድ ጊዜ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ሐሳቦች ያለ ምንም ምክንያት ወይም ሳልፈልግ ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ።” አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ስሜት በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው።

      ይሁንና ድንግል በመሆንሽ ጓደኞችሽ ነጋ ጠባ የሚያሾፉብሽና የሚነዘንዙሽ ከሆነ ሁኔታው ከባድ ነው። ለምሳሌ፣ አንድን ወጣት እኩዮቹ ‘የፆታ ግንኙነት የማትፈጽም ከሆነማ ወንድ ነኝ አትበል’ የሚሉት ቢሆንስ? አሊያም ደግሞ አንዲትን ወጣት ጓደኞቿ ‘የፆታ ግንኙነት ካልፈጸምሽ ምኑን ሴት ሆንሽው’ ቢሏትስ? ሔለን እንዲህ ብላለች፦ “እኩዮቻችሁ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚያስደስትና ሁሉም ሰው የሚያደርገው ነገር እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህም ከዚያም ጋር ካልተኛችሁ ከሰው የተለያችሁ እንደሆናችሁ አድርገው ይቆጥሯችኋል።”

      ይሁንና ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ጋር በተያያዘ እኩዮችሽ የሚደብቁሽ ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር የፆታ ግንኙነት የፈጸመች ማሪያ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ድርጊቱን ከፈጸምኩ በኋላ በኀፍረትና በጥፋተኝነት ስሜት ተዋጥኩ። ራሴን ጠላሁት፤ የወንድ ጓደኛዬንም ጨርሶ ላየው አልፈለግኩም።” አብዛኞቹ ወጣቶች ባያውቁትም እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ብዙውን ጊዜ የስሜት ሥቃይ የሚያስከትል ከመሆኑም ሌላ አስከፊ መዘዞች አሉት!

      ያም ሆኖ ሻንዳ የተባለች ወጣት “አምላክ በጋብቻ ውስጥ ካልሆነ በቀር የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንደሌለባቸው እያወቀ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት ፍላጎት እንዲኖራቸው ለምን አደረገ?” የሚል ጥያቄ አንስታለች። ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው። እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፦

      ከፆታ ፍላጎት ሌላ ኃይለኛ ስሜት አድሮብሽ አያውቅም? እንደሚያውቅ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ አምላክ የፈጠረሽ የተለያየ ዓይነት ፍላጎትና ስሜት እንዲኖርሽ አድርጎ ነው።

      እንዲህ ያሉ ስሜቶች በውስጥሽ በተቀሰቀሱ ቁጥር ልታስተናግጃቸው ይገባል ማለት ነው? በፍጹም። ምክንያቱም አምላክ ሲፈጥርሽ ስሜትሽን የመቆጣጠር ችሎታም ሰጥቶሻል።

      ታዲያ ነጥቡ ምንድን ነው? አንዳንድ ስሜቶች በውስጥሽ እንዳይቀሰቀሱ ማድረግ አትችዪ ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህን ፍላጎቶችሽን ከመፈጸም ራስሽን መግታት ትችያለሽ። እውነቱን ለመናገር፣ የፆታ ስሜትሽ በተቀሰቀሰ ቁጥር ፍላጎትሽን ለማርካት መነሳት አንድ ሰው ባናደደሽ ቁጥር ከመማታት ባልተናነሰ ስህተትና ቂልነት ነው።

      አምላክ የመራቢያ አካላችንን የሰጠን አላግባብ እንድንጠቀምበት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ዕቃ እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት [ሊያውቅ ይገባል]” ይላል። (1 ተሰሎንቄ 4:4) መጽሐፍ ቅዱስ “ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው” ይላል። በተመሳሳይም የፆታ ፍላጎትን ለማርካትም ሆነ ይህን ከማድረግ ለመቆጠብ ጊዜ አለው። (መክብብ 3:1-8) በዚያም ሆነ በዚህ ስሜትሽን መቆጣጠር የምትችይው አንቺ ነሽ!

      ይሁን እንጂ አንዲት ወጣት በፌዝ መልክ “አሁንም ድንግል ነኝ እንዳትይኝ ብቻ” ብትልሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ? በዚህ ጊዜ መደናገጥ የለብሽም። ዓላማዋ በአንቺ ላይ ማሾፍ ከሆነ “አዎ፣ አሁንም ድንግል ነኝ። ደግሞም ድንግል በመሆኔ ቅንጣት ታክል አላፍርም!” ብለሽ ልትመልሺላት ትችያለሽ። አሊያም “ይህ የግል ጉዳዬ ስለሆነ አንቺን አይመለከትሽም” ማለት ትችያለሽ።b (ምሳሌ 26:4፤ ቆላስይስ 4:6) በሌላ በኩል ግን እንዲህ ላለችሽ ወጣት ስለ አቋምሽ የበለጠ ልታስረጃት እንደሚገባ ይሰማሽ ይሆናል። ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አቋምሽን በተመለከተ አንዳንድ ነገሮች ልትነግሪያት ትችያለሽ።

      አንዲት ወጣት በፌዝ መልክ “አሁንም ድንግል ነኝ እንዳትይኝ ብቻ” ብትልሽ ሌላስ ምን ልትያት ትችያለሽ? መልስሽን ከታች አስፍሪው።

      ․․․․․

      ውድ ስጦታ

      ሰዎች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ቢፈጽሙ አምላክ ምን ይሰማዋል? ለአንድ ጓደኛሽ ስጦታ ገዝተሻል እንበል። ይሁንና ጓደኛሽ ስጦታውን ገና ሳትሰጫት ለማየት ጓጉታ ብትከፍተው ምን ይሰማሻል? በሁኔታው አትበሳጪም? አንቺም ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ብትፈጽሚ አምላክ ምን እንደሚሰማው ልትገምቺ ትችያለሽ። አምላክ ከሰጠሽ ስጦታ ማለትም ከፆታ ግንኙነት ደስታ ለማግኘት እስክታገቢ ድረስ እንድትቆዪ ይፈልጋል።​—ዘፍጥረት 1:28

      ‘ታዲያ የፆታ ስሜቴ እንዳያስቸግረኝ ምን ባደርግ ይሻለኛል?’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል። በአጭር አነጋገር፣ ስሜትሽን መቆጣጠር መማር ይኖርብሻል። ደግሞም እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል ብቃት አለሽ! ይሖዋ እንዲረዳሽ ጸልዪ። የአምላክ መንፈስ ራስን የመግዛት ባሕርይ ይበልጥ እንድታዳብሪ ሊረዳሽ ይችላል። (ገላትያ 5:22, 23) ይሖዋ “በቅንነት የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም” የሚለውን ጥቅስ አስታውሺ። (መዝሙር 84:11) ጎርደን የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆነ ማሰብ ከጀመርኩ እንዲህ ያለው ድርጊት በመንፈሳዊነቴ ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት አሰላስላለሁ፤ ይህም ኃጢአት በመፈጸም የማገኘው ደስታ የፈለገ ቢሆን ከይሖዋ ጋር ካለኝ ዝምድና ሊበልጥብኝ እንደማይችል እንድገነዘብ ያደርገኛል።”

      ድንግል መሆንሽ ችግር እንዳለብሽ የሚያሳይ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ክብርን ዝቅ የሚያደርገውና የሚያሳፍረው ብሎም ጎጂ የሚሆነው የፆታ ብልግና መፈጸም ነው። በመሆኑም ዓለም የሚያናፍሰው ፕሮፓጋንዳ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መኖርሽ ስህተት እንደሆነ እንዲሰማሽ አያድርግሽ። ድንግልናሽን ጠብቀሽ መቆየትሽ ስሜታዊ ጉዳት እንዳይደርስብሽ የሚረዳሽ ከመሆኑም ሌላ ጤንነትሽን ለመጠበቅ ያስችልሻል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአምላክ ጋር ያለሽ ዝምድና እንዳይበላሽ ይረዳሻል።

      ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 24 ተመልከት

      [የግርጌ ማስታወሻዎች]

      a በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

      b ኢየሱስ በአንድ ወቅት ሄሮድስ ጥያቄ ሲያቀርብለት ዝምታን እንደመረጠ መገለጹ ትኩረት የሚስብ ነው። (ሉቃስ 23:8, 9) ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች ሲቀርቡልን ብዙውን ጊዜ የተሻለው ነገር መልስ አለመስጠት ነው።

      ቁልፍ ጥቅስ

      “[አንድ ሰው] ድንግልናውን ጠብቆ ለመኖር በልቡ ከወሰነ . . . መልካም ያደርጋል።”​—1 ቆሮንቶስ 7:37

      ጠቃሚ ምክር

      አንዳንድ ወጣቶች እንደ አንቺ ዓይነት እምነት እንዳላቸው ቢናገሩም እንኳ ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም ከሌላቸው ከእነሱ ጋር ጓደኝነት ላለመመሥረት ተጠንቀቂ።

      ይህን ታውቅ ነበር?

      ልቅ የሆነ የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ልማድ ያላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ካገቡም በኋላ ይህ አመላቸው አይለቃቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ ከማግባታቸው በፊት ለአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ታማኝ የነበሩ ሰዎች ካገቡም በኋላ ለትዳር ጓደኛቸው ታማኝ የመሆናቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው።

      ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

      እስከማገባ ድረስ ድንግልናዬን ጠብቄ ለመቆየት እንድችል እንዲህ ማድረግ ያስፈልገኛል፦ ․․․․․

      ጓደኞቼ በአቋሜ እንዳልጸና የሚያስቸግሩኝ ከሆነ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

      ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

      ምን ይመስልሃል?

      ● አንዳንዶች፣ ድንግል የሆኑ ወጣቶች ላይ የሚያሾፉባቸው ለምንድን ነው?

      ● ድንግልናን ጠብቆ መቆየት አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

      ● እስኪያገቡ ድረስ ድንግል ሆኖ መቆየት ምን ጥቅሞች አሉት?

      ● ድንግልናን ጠብቆ መቆየት ያለውን ጥቅም ለታናናሾቻችሁ ማስረዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

      [በገጽ 51 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      ‘ሴሰኛ ወይም ርኩስ የሆነ ማንኛውም ሰው በአምላክ መንግሥት ምንም ውርሻ እንደሌለው’ ሁልጊዜ ማስታወሴ የፆታ ብልግና እንድፈጽም የሚያጋጥመኝን ፈተና ለመቋቋም አስችሎኛል።” (ኤፌሶን 5:5)​—ሊዲያ

      [በገጽ 49 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      የመልመጃ ሣጥን

      በእርግጥ ከዚያ በኋላ ምን ይሆናል?

      አብዛኛውን ጊዜ እኩዮችሽም ሆኑ በብዙኃኑ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚያስከትለውን መዘዝ አድበስብሰው ያልፉታል። እስቲ የሚከተሉትን ሦስት ሁኔታዎች እንመልከት። እነዚህ ወጣቶች በእርግጥ ምን ያጋጠማቸው ይመስልሻል?

      ● አብሮሽ የሚማር አንድ ወጣት ከበርካታ ሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት እንደፈጸመ በጉራ ይናገራል። ሁኔታው በጣም አስደሳች እንደሆነና ማናቸውም ምንም ችግር እንዳላጋጠማቸው ይገልጻል። ይሁንና እሱም ሆነ ሴቶቹ ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ ያጋጠማቸው ነገር በእርግጥ እንደጠበቁት የሚሆን ይመስልሻል? ․․․․․

      ● አንድ ፊልም እየተመለከትሽ ነው እንበል፤ ፊልሙ የሚደመደመው ሁለት የሚዋደዱ ወጣቶች ገና ሳይጋቡ የፆታ ግንኙነት ሲፈጽሙ በማሳየት ነው። በገሃዱ ዓለም ቢሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ ምን የሚያጋጥማቸው ይመስልሻል? ․․․․․

      ● አንድ ቆንጆ ወጣት የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ ጠየቀሽ። ድርጊቱን ብትፈጽሙ ማንም እንደማያውቅባችሁ ነግሮሻል። ከልጁ ጋር የፆታ ግንኙነት ብትፈጽሚና ሁኔታውን ለመደበቅ ብትሞክሪ ከዚያ በኋላ የሚያጋጥምሽ ነገር በእርግጥ እንደጠበቅሽው የሚሆን ይመስልሻል? ․․․․․

      [በገጽ 54 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም አንድ ስጦታ ሳይሰጥህ አስቀድመህ እንደመክፈት ነው

  • በሰውነቴ ላይ የማየው ለውጥ ምንድን ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
    • ምዕራፍ 6

      በሰውነቴ ላይ የማየው ለውጥ ምንድን ነው?

      “ቁመቴ በአንድ ጊዜ ተመዘዘ። ሁኔታው ሕመም አስከትሎብኝ ነበር። ማደግ ደስ የሚል ነገር ቢሆንም እግሬ ላይ ሕመም ይሰማኝ ነበር። ይህም ያናድደኝ ነበር!”​—ጳውሎስ

      “ሰውነትሽ እየተለወጠ መሆኑ ታውቆሻል፤ እናም ‘ምነው ሌሎች ባላወቁብኝ’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል። ይሁንና ሰዎች አንቺን ለማሸማቀቅ አስበው ባይሆንም ‘ዳሌ አወጣሽ እኮ’ ይሉሻል፤ በዚህ ጊዜ መሬት ተከፍታ ብትውጥሽ ደስ ይልሻል!”​—ሸነል

      ያደግክበትን ሰፈር ለቀህ በሌላ አካባቢ ኖረህ ታውቃለህ? መቼም አዲሱን አካባቢ መልመድ አስቸጋሪ ሳይሆንብህ አልቀረም። ቤትህን፣ ትምህርት ቤትህን እንዲሁም ጓደኞችህን ጨምሮ የለመድካቸውን ነገሮች ሁሉ ትተህ መሄድ ከባድ እንደሆነብህ ግልጽ ነው። ከአዲሱ ሁኔታ ጋር ራስህን ለማስማማት ጊዜ ወስዶብህ ይሆናል።

      የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትደርስ ማለትም በአካላዊ ሁኔታ መጎልመስ ስትጀምር በሕይወትህ ውስጥ ከሚከናወኑት ጉልህ ለውጦች አንዱን ማየት ትጀምራለህ። ሁኔታው የኖርክበትን ሰፈር ለቀህ ወደ አዲስ “አካባቢ” ከመሄድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አዲሱን መኖሪያህን ለማየት እንደምትጓጓ ጥርጥር የለውም! ይሁንና ወደ ጉልምስና የምታደርገው ጉዞ የተደበላለቀ ስሜት ይፈጥርብህ ይሆናል፤ አዲሱን ሁኔታ መልመድም ቀላል ላይሆንልህ ይችላል። በአንድ በኩል የሚያስደስት በሌላ በኩል ደግሞ ግራ የሚያጋባ በሆነው በዚህ ወቅት በሕይወትህ ውስጥ የሚከናወኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?

      ሴቶች ልጆች የሚያጋጥሟቸው ለውጦች

      የጉርምስና ዕድሜ ከፍተኛ ለውጥ የሚከናወንበት ወቅት ነው። ከሚያጋጥሙሽ ለውጦች አንዳንዶቹ በግልጽ የሚታዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ሰውነትሽ የሚያመነጫቸው ሆርሞኖች በፆታ ብልትሽ አካባቢ ፀጉር እንዲያድግ ያደርጋሉ። በተጨማሪም ጡት ማውጣት ትጀምሪያለሽ፣ ዳሌሽ ይሰፋል፤ እንዲሁም ጭንሽና መቀመጫሽ እየተለቀ ይሄዳል። ቀስ በቀስ ልጅነትሽን እየተሰናበትሽ የሴት ቅርጽ እየያዝሽ ትመጫለሽ። ይህ ጤናማ የእድገት ምልክት ስለሆነ ልትጨነቂ አይገባም። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ለውጦች ሰውነትሽ ልጅ ለምትወልጂበት ጊዜ እየተዘጋጀ መሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው።

      በጉርምስና ወቅት የሚያጋጥምሽ ሌላው ለውጥ ደግሞ የወር አበባ ማየት መጀመርሽ ነው። አስቀድመሽ አስፈላጊውን ዝግጅት ካላደረግሽ በሕይወትሽ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የምትጀምሪበት ይህ ወቅት የሚያስፈራ ሊሆንብሽ ይችላል። ሰማንታ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ፔሬዴ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ ምንም አልተዘጋጀሁበትም ነበር። ቁሽሽ እንዳልኩ ሆኖ ተሰማኝ። ሰውነቴ በጣም ስላስጠላኝ ፍትግ አድርጌ እታጠብ ነበር። ከዚህ በኋላ ለዓመታት በየወሩ ፔሬድ ማየት የሚለውን ነገር ሳስበው በጣም አስፈራኝ!”

      የወር አበባ ማየትሽ የመራቢያ አካላትሽ እየዳበሩ መሆናቸውን የሚጠቁም መሆኑን አትዘንጊ። እናት ለመሆን ዝግጁ የምትሆኚው ከዓመታት በኋላ ቢሆንም ወደ ሴትነት የምትሸጋገሪበትን ጉዞ የምትጀምሪው በዚህ ወቅት ነው። ያም ሆኖ የወር አበባሽ መጀመሩ እንድትረበሺ ሊያደርግሽ ይችላል። ኬሊ “ከሁሉ የከፋው ነገር በዚያ ወቅት የሚያጋጥመኝ የስሜት መለዋወጥ ነበር” ብላለች። “ቀኑን ሙሉ ደስ ብሎኝ ውዬ ማታ ላይ ዓይኔ እስኪያብጥ ድረስ አለቅሳለሁ፤ እንዲህ የምሆነው ለምን እንደሆነ አለማወቄ ያበሳጨኝ ነበር።”

      አንቺስ በአሁኑ ወቅት እንደዚህ ይሰማሻል? ከሆነ ተስፋ አትቁረጪ። ውሎ አድሮ ለውጡን እየለመድሽው ትመጫለሽ። የ20 ዓመቷ አኔት እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፦ “ሴትን ሴት የሚያስብላት የወር አበባ ማየቷ እንደሆነና ይህ ደግሞ ይሖዋ ልጅ የመውለድ ችሎታ እንደሰጠኝ የሚያሳይ ምልክት መሆኑን ከጊዜ በኋላ ተገነዘብኩ። ይህን ለመቀበል ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑም በላይ ለአንዳንድ ወጣቶች በጣም ሊከብዳቸው ይችላል። ይሁንና በጊዜ ሂደት ለውጡን መቀበል ትጀምራላችሁ።”

      ከላይ ከተጠቀሱት ለውጦች አንዳንዶቹን በሰውነትሽ ላይ መመልከት ጀምረሻል? ካጋጠሙሽ ለውጦች ጋር በተያያዘ የሚፈጠርብሽን ማንኛውንም ጥያቄ በክፍት ቦታው ላይ አስፍሪ።

      ․․․․․

      ወንዶች ልጆች የሚያጋጥሟቸው ለውጦች

      ወንድ ልጅ ከሆንክ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትደርስ በመልክህና በቁመናህ ላይ ጉልህ ለውጥ መመልከት ትጀምራለህ። ለምሳሌ፣ ቆዳህ አሁንም አሁንም ወዝ ስለሚያወጣ ሰውነትህ ላይ ብጉር ይወጣብህ እንዲሁም ጥቁር ነጠብጣቦች ይታዩብህ ይሆናል።a የ18 ዓመቱ ማት እንዲህ ብሏል፦ “ቆዳህ ብጉር በብጉር ሲሆን በጣም ያበሳጫል። ሁኔታው ጦርነት የተያያዝክ ያህል ነው፤ ብጉሩን ለማጥፋት መታገል ይኖርብሃል። ብጉሩ ከቆዳህ ላይ ጨርሶ ይጥፋ አይጥፋ ወይም ምልክት ይተው አይተው ምንም የምታውቀው ነገር የለም፤ ‘ብጉር ስለወጣብኝ ሰዎች ለእኔ ያላቸው ግምት ይቀንስ ይሆን?’ ብለህም ታስባለህ።”

      ይሁን እንጂ በሰውነትህ ላይ የሚታየው ለውጥ መልካም ጎንም አለው፤ ሰውነትህ እያደገና እየጠነከረ መምጣቱን እንዲሁም ትከሻህ እየሰፋ መሆኑን ታስተውል ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ እግርህና ፊትህ ላይ እንዲሁም ደረትህ አካባቢና ብብትህ ሥር ፀጉር መታየት ይጀምር ይሆናል። በነገራችን ላይ በሰውነትህ ላይ ብዙ ፀጉር መኖሩ የወንድነት መለኪያ አይደለም፤ ይህ በዘር የሚወረስ ነገር ነው።

      ሁሉም የሰውነትህ ክፍሎች በተመጣጠነ መንገድ ስለማያድጉ በዚህ ወቅት ቅልጥፍ ማለት ያስቸግርህ ይሆናል። ድዌን የተባለ አንድ ወጣት ‘እጆቼና እግሮቼ አእምሮዬ የሚያስተላልፈው መልእክት የሚደርሳቸው አይመስልም ነበር’ ብሏል።

      በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ስትሆን ድምፅህ ይጎረንናል፤ ሆኖም ድምፅህ የሚቀየረው ቀስ በቀስ ነው። ጎርነን ባለ ድምፅ እያወራህ ሳለ ሳታስበው ድምፅህ ቀጭንና ስልል ያለ ሊሆንብህና ሽምቅቅ ልትል ትችላለህ። ይሁን እንጂ ይህ መሆኑ ሊያስጨንቅህ አይገባም። ውሎ አድሮ ድምፅህ እየተስተካከለ ይሄዳል። እስከዚያው ድረስ ግን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ በራስህ መቀለድህ የሚሰማህን የኀፍረት ስሜት በመጠኑም ቢሆን ይቀንስልሃል።

      የመራቢያ አካላትህ እየዳበሩ ሲሄዱ የፆታ ብልትህ የሚያድግ ከመሆኑም ሌላ በዙሪያው ፀጉር ይበቅላል። እንዲሁም የመራቢያ አካላትህ የወንድ ዘር ተሸካሚ ፈሳሽ ማምረት ይጀምራሉ። ይህ ፈሳሽ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በዓይን የማይታዩ የወንድ ዘሮችን (ስፐርም) የያዘ ሲሆን የፆታ ግንኙነት በሚደረግበት ወቅት እነዚህ ዘሮች ከሰውነትህ ይወጣሉ። አንድ የወንድ ዘር ከሴቷ እንቁላል ጋር በመዋሃድ ፅንስ እንዲፈጠር ማድረግ ይችላል።

      በሰውነትህ ውስጥ ያለው የወንድ ዘር ተሸካሚ ፈሳሽ መጠን እየጨመረ ሲሄድ ሰውነትህ የተወሰነውን ይጠቀምበታል፤ ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ሌሊት ተኝተህ እያለ ሊፈስ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሁሉም ወንዶች ሊያጋጥማቸው የሚችል ነገር ነው። የዘር መፍሰስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ተጠቅሷል። (ዘሌዋውያን 15:16, 17) ይህ ሁኔታ የመራቢያ አካላትህ በሚገባ እየሠሩ እንደሆነና ወደ ወንድነት የምትሸጋገርበትን ጉዞ እንደጀመርክ የሚጠቁም ነው።

      ከላይ ከተጠቀሱት ለውጦች አንዳንዶቹን በሰውነትህ ላይ መመልከት ጀምረሃል? ካጋጠሙህ ለውጦች ጋር በተያያዘ የሚፈጠርብህን ማንኛውንም ጥያቄ በክፍት ቦታው ላይ አስፍር።

      ․․․․․

      አዳዲስ ስሜቶችን መቋቋም

      ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች የመራቢያ አካላታቸው እየዳበሩ ሲመጡ ስለ ተቃራኒ ፆታ ከዚህ በፊት ተሰምቷቸው የማያውቅ ስሜት ይፈጠርባቸዋል። ማት እንዲህ ብሏል፦ “የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስደርስ ቆንጆ ቆንጆ የሆኑ ብዙ ሴቶች ልጆች እንዳሉ አስተዋልኩ። በሌላ በኩል ደግሞ እስካድግ ድረስ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት እንደማልችል አውቅ ነበር፤ ይህም በጣም የሚያበሳጭ ነበር።” እያደግህ ስትሄድ የሚፈጠርብህን እንዲህ ያለውን ስሜት በተመለከተ ምዕራፍ 29 ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይዟል። እስከዛው ልታውቀው የሚገባው ነገር የፆታ ስሜትህን መቆጣጠርን መልመድህ አስፈላጊ መሆኑን ነው። (ቆላስይስ 3:5) ስሜትህን መቆጣጠር ከባድ ሊመስል ቢችልም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ!

      በጉርምስና ወቅት የሚታገሉህ ሌሎች ስሜቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ለራስህ ጥሩ አመለካከት አይኖርህ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ወጣቶች የብቸኝነት ስሜት የሚያድርባቸው ከመሆኑም ሌላ አልፎ አልፎ በመንፈስ ጭንቀት ይዋጣሉ። በእነዚህ ጊዜያት ወላጆችህን ወይም የምትተማመንበትን አንድ ትልቅ ሰው ማነጋገርህ ጥሩ ነው። በውስጥህ የሚታገሉህን ስሜቶች በተመለከተ ልታወያየው የምትችል ትልቅ ሰው አለ? ስሙን ከታች አስፍር።

      ․․․․․

      ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነው ነገር

      ከማደግ ጋር በተያያዘ ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነው ነገር ቁመትህ፣ ተክለ ሰውነትህ ወይም መልክህ ሳይሆን በማንነትህ ይኸውም በአስተሳሰብህና በስሜትህ ከሁሉ በላይ ደግሞ በመንፈሳዊነትህ ረገድ የምታደርገው እድገት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር፣ እንደ ሕፃን አስብ እንዲሁም እንደ ሕፃን አመዛዝን ነበር፤ አሁን ሙሉ ሰው ከሆንኩ በኋላ ግን የሕፃንነትን ጠባይ ትቻለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 13:11) ሊተላለፍ የተፈለገው ነጥብ ግልጽ ነው፤ ትልቅ ሰው መስሎ መታየት ብቻውን በቂ አይደለም። አነጋገርህና አስተሳሰብህ እንዲሁም ነገሮችን የምታከናውንበት መንገድ እንደ ትልቅ ሰው ሊሆን ይገባል። ለውስጣዊ ሰውነትህ ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት እስክትዘነጋ ድረስ ስለ ውጫዊ ገጽታህ ከሚገባ በላይ መጨነቅህ ተገቢ አይደለም!

      ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ‘ልብን እንደሚያይ’ አትዘንጋ። (1 ሳሙኤል 16:7) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ንጉሥ ሳኦል ቁመቱ ዘለግ ያለ መልከ ቀና ሰው እንደነበር ይናገራል፤ ይሁንና ከአንድ ትልቅ ሰውም ሆነ ከአንድ ንጉሥ የማይጠበቅ ነገር አድርጓል። (1 ሳሙኤል 9:2) ከዚህ በተቃራኒ፣ ዘኬዎስ “ቁመቱ አጭር” ቢሆንም ውስጣዊ ጥንካሬ ስለነበረው ሕይወቱን አስተካክሎ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ችሏል። (ሉቃስ 19:2-10) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውስጣዊ ማንነት ነው።

      ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ ሁን፦ ጤንነትህን ሳትጎዳ አካላዊ እድገትህን ማፋጠን ወይም ማዘግየት የምትችልበት ምንም መንገድ የለም። ስለዚህ በሰውነትህ ላይ ለውጦች በመታየታቸው ልትጨነቅ ወይም እነዚህን ለውጦች ልትጠላቸው አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ በጸጋ ብትቀበላቸውና በራስህ ላይ መሳቅ ብትለምድ የተሻለ ይሆናል። ጉርምስና በሽታ አይደለም፤ በዚህ ሂደት ለማለፍም አንተ የመጀመሪያው አይደለህም። ጉርምስና ማንንም አልገደለም፤ አንተም ይህን ወቅት እንደምታልፈው እርግጠኛ ሁን። እንደ ማዕበል የሚያንገላታህ የጉርምስና ወቅት ሲያልፍ ሙሉ ሰው ወደ መሆን ትሸጋገራለህ!

      በሚቀጥለው ምዕራፍ

      ራስሽን በመስተዋት ስታዪ መልክሽ ቢያስጠላሽስ? ስለ መልክሽ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር የምትችዪው እንዴት ነው?

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a ሴቶች ልጆችም ብጉር ሊወጣባቸው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ለቆዳ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ችግሩ እንዳይባባስ መከላከል ይቻላል።

      ቁልፍ ጥቅስ

      “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ።”​—መዝሙር 139:14

      ጠቃሚ ምክር

      እያደጋችሁ ስትሄዱ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ልብሶችን ላለመልበስ መጠንቀቅ ይኖርባችኋል። ምንጊዜም አለባበሳችሁ ‘ልከኝነትና ማስተዋል’ የሚንጸባረቅበት ሊሆን ይገባል።​—1 ጢሞቴዎስ 2:9

      ይህን ታውቅ ነበር?

      ጉርምስና ገና በስምንት ዓመት ዕድሜ ወይም ከዘገየ ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ሊጀምር ይችላል። በመሆኑም ጉርምስና የሚጀምርበት ዕድሜ ከሰው ሰው ይለያያል።

      ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

      ወደ ሙሉ ሰውነት በማደርገው ጉዞ በተለይ ላዳብረው የሚገባው ባሕርይ ․․․․․

      በመንፈሳዊ ለማደግ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

      ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

      ምን ይመስልሃል?

      ● በጉርምስና ወቅት የሚያጋጥሙትን አካላዊና ስሜታዊ ለውጦች መቀበል ያን ያህል አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው?

      ● በዚህ የሽግግር ወቅት በጣም አስቸጋሪ የሆነብህ ነገር ምንድን ነው?

      ● በጉርምስና ወቅት ለአምላክ ያለህ ፍቅር ሊቀንስ የሚችለው ለምን ይመስልሃል? ይህ እንዳይሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

      [በገጽ 61 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      “በጉርምስና ወቅት ስጋት እንዲያድርባችሁ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ያጋጥሟችኋል፤ በሰውነታችሁ ላይ ምን ለውጥ እንደሚካሄድ በእርግጠኝነት ማወቅ አትችሉም። ሆኖም እያደጋችሁ ስትሄዱ እነዚህን ለውጦች የምትለምዷቸው ከመሆኑም በላይ ሁኔታውን ተቀብላችሁ መኖር ትጀምራላችሁ።”​—አኔት

      [በገጽ 63 እና 64 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ከአባባ ወይም ከእማማ ጋር ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ማውራት የምችለው እንዴት ነው?

      “ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ጥያቄ ቢኖረኝ በምንም ዓይነት ወላጆቼን አልጠይቃቸውም።”​—ቤዛ

      “እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለማንሳት ድፍረቱ የለኝም።”​—ዳንኤል

      አንተም እንደ ቤዛና እንደ ዳንኤል የሚሰማህ ከሆነ በእርግጥም ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ገጥሞሃል። ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ማወቅ ትፈልጋለህ፤ ወላጆችህ ስለዚህ ጉዳይ ሊነግሩህ ቢችሉም አንተ ግን ወደ እነሱ መሄድ አትፈልግ ይሆናል። የሚከተሉት ጉዳዮች ያሳስቡሃል፦

      ስለ ፆታ ብጠይቃቸው ስለ እኔ ምን ይሰማቸዋል?

      “ብጠይቃቸው በጥርጣሬ ዓይን ያዩኛል ብዬ ስለምፈራ ዝም ማለት እመርጣለሁ።”​—ጄሲካ

      “ወላጆች ምንጊዜም ምንም የማታውቁ ልጆች ሆናችሁ ብትኖሩ ደስ ይላቸዋል፤ ስለ ፆታ ብታዋሯቸው ግን እናንተን እንደ ድሮው ማየት ያቆማሉ።”​—ቤዛ

      ምን ይሉኝ ይሆን?

      “ወላጆቼ፣ ገና ተናግሬ ሳልጨርስ ዘለው አንድ መደምደሚያ ላይ ይደርሱና ማቆሚያ የሌለው ምክር ይሰጡኛል ብዬ እፈራለሁ።”​—ግሎሪያ

      “ወላጆቼ ስሜታቸውን መደበቅ ስለማይችሉ ብጠይቃቸው እንዳዘኑብኝ የሚጠቁም ነገር ፊታቸው ላይ ባይስ ብዬ እፈራለሁ። እንዲያውም አባቴ፣ እኔ እየተናገርኩ እያለ የሚያስበው ምን ብሎ እንደሚመክረኝ ሊሆን ይችላል።”​—ፓም

      በተሳሳተ መንገድ ይረዱኝ ይሆን?

      “ጉዳዩን አክብደው በመመልከት ‘የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም አሰብሽ እንዴ?’ ወይም ‘እኩዮችሽ ግፊት እያሳደሩብሽ ነው?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች መጠየቅ ይጀምሩ ይሆናል። እናንተ ግን ጉዳዩን ያነሳችሁት ለማወቅ ስለፈለጋችሁ ብቻ ሊሆን ይችላል።”​—ሊሳ

      “ስለ ወንድ ባነሳሁ ቁጥር በአባቴ ፊት ላይ የጭንቀት ስሜት አነባለሁ። ከዚያም ወዲያውኑ ስለ ፆታ ጉዳዮች ማውራት ይጀምራል። በዚህ ጊዜ ‘አባባ እኔኮ ልጁ ያምራል ብቻ ነው ያልኩት። ስለ ጋብቻ ወይም ስለ ፆታ ግንኙነት የተናገርኩት ነገር አለ?’ ልለው ይቃጣኛል።”​—ስቴሲ

      ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ከወላጆችህ ጋር ማውራት አንተን እንደሚያሳፍርህ ሁሉ ወላጆችህም ይህን ጉዳይ አንስተው ከአንተ ጋር መወያየት እንደሚያሳፍራቸው ማወቅህ ጭንቀትህን ቀለል ያደርግልህ ይሆናል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ከልጆቻቸው ጋር እንደተነጋገሩ የገለጹት ወላጆች 65 በመቶ ሆነው ሳለ እንዲህ ዓይነት ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት ልጆች ግን 41 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፤ ይህ ልዩነት የተፈጠረው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንዲህ ዓይነት ውይይት ማድረግ ስለሚያሳፍራቸው ሊሆን ይችላል።

      ወላጆችህ ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ማውራት ሊከብዳቸው የሚችል መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። ይህ የሆነው የእነሱም ወላጆች ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ ስላላዋሯቸው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን አትፍረድባቸው፤ ከዚህ ይልቅ ስሜታቸውን ተረዳላቸው። አንተ ራስህ ደፈር ብለህ ጉዳዩን ብታነሳባቸው ሁለታችሁም ትጠቀማላችሁ። እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

      ውይይቱ እንዴት ይጀመር?

      ወላጆችህ ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ሰፊ እውቀት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ካካበቱት ተሞክሮ ብዙ ጠቃሚ ሐሳብ ሊያካፍሉህ ይችላሉ። ከአንተ የሚፈለገው ነገር ለውይይቱ በር መክፈት ብቻ ነው። እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦

      1 ስለ አንድ ጉዳይ ልታነጋግራቸው እንደፈለግክ ሆኖም የሚሰጡህ ምላሽ እንዳስፈራህ በግልጽ ንገራቸው። “ላነጋግራችሁ ያሰብኩት ነገር ነበር፤ ሆኖም . . . ብላችሁ እንዳታስቡ ፈርቻለሁ።”

      2 ከዚያም እነሱን ለማነጋገር የመረጥከው ለምን እንደሆነ ንገራቸው። “አንድ ጥያቄ አለኝ፤ መልሱን ከሌላ ሰው ከምሰማው እናንተ ብትነግሩኝ ይሻላል ብዬ ነው።”

      3 ከዚያም ጥያቄህን በግልጽ አቅርብላቸው። “ልጠይቃችሁ ያሰብኩት . . .”

      4 ውይይታችሁ መደምደሚያ ላይ በሌላም ጊዜ እንደዚሁ ልታነጋግራቸው እንደምትፈልግ ግለጽ። “ሌላ ጥያቄ ከተፈጠረብኝ ስለዚህ ጉዳይ እንደገና ላነጋግራችሁ እችላለሁ?”

      ወላጆችህ የሚሰጡህ መልስ ‘አዎ’ እንደሆነ ብታውቅም ይህን ከእነሱ አንደበት መስማትህ ሌላ ጊዜ ልታነጋግራቸው ብታስብ መንገዱ ክፍት እንዲሆንና የበለጠ ነፃነት እንዲሰማህ ያደርጋል። ታዲያ እነዚህን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ለምን አትሞክርም? አንተም እንደ ትሪና ይሰማህ ይሆናል። አሁን 24 ዓመት የሆናት ይህቺ ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ከእማማ ጋር እያወራን እያለ ‘እንዲህ ያለ ነገር ምነው ባይነሳ’ ብዬ ተመኝቼ ነበር። አሁን ሳስበው ግን እናቴ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ሳትሸፋፍን በግልጽ ስላነጋገረችኝ በጣም ደስተኛ ነኝ። እንዲህ ማድረጓ ትልቅ ጥበቃ ሆኖልኛል!”

      [በገጽ 59 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ልጅነትሽን መሰናበት የኖርሽበትን ሰፈር ለቀሽ የመሄድን ያህል ከባድ ሊሆንብሽ ቢችልም አዲሱን ሁኔታ መልመድ ትችያለሽ

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ