ምዕራፍ 13
“ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ”
ራሳችንን የወሰንን የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በምንናገረውም ሆነ በምናደርገው ነገር የይሖዋን ክብር የማንጸባረቅ ግዴታ አለብን። ሐዋርያው ጳውሎስ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ” በማለት ልንመራበት የሚገባ መሠረታዊ ሥርዓት አስፍሯል። (1 ቆሮ. 10:31) ይህም ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖርን ይጠይቃል፤ እነዚህ መሥፈርቶች ፍጹም የሆነው አምላክ ባሕርይ ነጸብራቅ ናቸው። (ቆላ. 3:10) እኛም የአምላክ ቅዱስ ሕዝብ ስለሆንን እሱን መምሰል ይኖርብናል።—ኤፌ. 5:1, 2
2 ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ለዚህ ጉዳይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ሲጠቁም እንዲህ ብሏል፦ “ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን አቁሙ፤ ከዚህ ይልቅ የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ‘እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ’ ተብሎ ተጽፏልና።” (1 ጴጥ. 1:14-16) እንደ ጥንቱ የእስራኤል ብሔር ሁሉ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉትም ቅዱስ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይህም ሲባል ከኃጢአትና ከዓለም እድፍ በመራቅ ከብክለት ነፃ ሆነው መኖር አለባቸው ማለት ነው። በዚህ መንገድ ለቅዱስ አገልግሎት የተለዩ ሕዝቦች ይሆናሉ።—ዘፀ. 20:5
3 በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በግልጽ የተቀመጡትን የይሖዋን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ የምንከተል ከሆነ ምንጊዜም ቅድስናችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን። (2 ጢሞ. 3:16) መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስለ ይሖዋና ስለ መንገዶቹ ተምረናል፤ እንዲሁም ወደ እሱ መቅረብ ችለናል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን መንግሥት መፈለግ እንዳለብን እንዲሁም የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያውን ሊይዝ እንደሚገባ አምነን እንድንቀበል አድርጎናል። (ማቴ. 6:33፤ ሮም 12:2) ይህ ደግሞ አዲሱን ስብዕና መልበስን ጠይቆብናል።—ኤፌ. 4:22-24
መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና
4 የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ጠብቆ መኖር ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ባላጋራችን ሰይጣን ዲያብሎስ ከእውነት መንገድ ሊያስወጣን ይፈልጋል። በተጨማሪም ይህ ዓለም የሚያሳድርብን መጥፎ ተጽዕኖ እንዲሁም የራሳችን የኃጢአት ዝንባሌ የይሖዋን መሥፈርቶች መጠበቅ ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርጉበት ጊዜ አለ። ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር መንፈሳዊ ውጊያ ማድረግ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ ተቃውሞ ወይም ፈተና ሲደርስብን መደነቅ እንደሌለብን ይገልጻል። ለጽድቅ ስንል መከራ መቀበል ይኖርብናል። (2 ጢሞ. 3:12) እንዲያውም ፈተናዎች ሲደርሱብን ልንደሰት እንችላለን፤ ምክንያቱም ይህ በራሱ የአምላክን ፈቃድ እያደረግን እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—1 ጴጥ. 3:14-16፤ 4:12, 14-16
5 ኢየሱስ ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተምሯል። ለሰይጣን ፈተናዎች እጅ ሰጥቶ ወይም በዓለም ላሉ ነገሮች ጉጉት አድሮበት አያውቅም። (ማቴ. 4:1-11፤ ዮሐ. 6:15) በተጨማሪም አቋሙን ለማላላት ለአፍታም እንኳ ያሰበበት ጊዜ የለም። የታማኝነት ጎዳና መከተሉ በዓለም እንዲጠላ ቢያደርገውም የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች በጥብቅ ይከተል ነበር። ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት፣ ለደቀ መዛሙርቱ ዓለም እነሱንም እንደሚጠላቸው አስጠንቅቋቸዋል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የኢየሱስ ተከታዮች መከራ ሲደርስባቸው ቆይቷል፤ ይሁን እንጂ የአምላክ ልጅ ዓለምን እንዳሸነፈ ማወቃቸው ብርታት ሰጥቷቸዋል።—ዮሐ. 15:19፤ 16:33፤ 17:16
6 የዓለም ክፍል ላለመሆን ጌታችን እንዳደረገው ሁሉ እኛም የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች መጠበቅ ይኖርብናል። በዓለም ፖለቲካዊም ሆነ ማኅበራዊ ጉዳዮች ከመሳተፍ መራቅ ያለብን ከመሆኑም ሌላ በዓለም ላይ የሚታየው ወራዳ ሥነ ምግባር ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። በያዕቆብ 1:21 ላይ የሚገኘውን “ጸያፍ የሆነውን ነገር ሁሉና ክፋትን ሁሉ አስወግዳችሁ እናንተን ሊያድን የሚችለውን በውስጣችሁ የሚተከለውን ቃል በገርነት ተቀበሉ” የሚለውን ምክር በቁም ነገር እንመለከተዋለን። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችንና በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን የእውነት ቃል በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ ‘እንዲተከል’ ያስችላል፤ ይህም ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች ፈጽሞ እንዳንመኝ ይረዳናል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከዓለም ጋር መወዳጀት ከአምላክ ጋር ጠላትነት መፍጠር እንደሆነ አታውቁም? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ራሱን የአምላክ ጠላት ያደርጋል።” (ያዕ. 4:4) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች እንድንጠብቅና ከዓለም የተለየን እንድንሆን አጥብቆ የሚመክረን በዚህ ምክንያት ነው።
7 የአምላክ ቃል አሳፋሪና ወራዳ የሆነ ምግባር ከመፈጸም እንድንቆጠብ ያስጠነቅቀናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለቅዱሳን የማይገባ ስለሆነ የፆታ ብልግናና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ” በማለት ይናገራል። (ኤፌ. 5:3) ስለዚህ አእምሯችን ነውረኛ፣ አሳፋሪ ወይም ወራዳ የሆኑ ነገሮችን እንዲያውጠነጥን መፍቀድ የለብንም፤ በተጨማሪም እንዲህ ስላሉ ነገሮች ፈጽሞ አናወራም። በዚህ መንገድ፣ ይሖዋ ያወጣቸውን ንጹሕ የሆኑና በጽድቅ ላይ የተመሠረቱ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መጠበቅ እንደምንፈልግ እናሳያለን።
አካላዊ ንጽሕና
8 ክርስቲያኖች መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ከመጠበቅ በተጨማሪ አካላዊ ንጽሕናቸውን የመጠበቅን አስፈላጊነት ይገነዘባሉ። ቅዱስ አምላክ የሆነው ይሖዋ እስራኤላውያን ሰፈራቸውን በንጽሕና እንዲይዙ ይጠብቅባቸው ነበር። እኛም ይሖዋ “ነውር የሆነ ምንም ነገር [እንዳያይብን]” ንጹሕ መሆን ይኖርብናል።—ዘዳ. 23:14
9 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅድስናና አካላዊ ንጽሕና የማይነጣጠሉ ነገሮች እንደሆኑ ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ . . . ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እንዲሁም አምላክን በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ።” (2 ቆሮ. 7:1) ስለዚህ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች አዘውትረው ገላቸውን በመታጠብና ልብሳቸውን በማጠብ ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። የኑሮ ሁኔታ ከአገር አገር የተለያየ ቢሆንም በጥቅሉ ሲታይ ራሳችንንም ሆነ ልጆቻችንን በንጽሕና ለመያዝ የሚያስችል በቂ ውኃና ሳሙና ማግኘት እንችላለን።
10 በስብከቱ ሥራችን የተነሳ፣ በምንኖርበት አካባቢ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች በደንብ ያውቁናል። ቤታችንንም ሆነ ግቢያችንን በንጽሕናና በሥርዓት መያዛችን በራሱ ለጎረቤቶቻችን ምሥክርነት ይሰጣል። ይህ የመላውን ቤተሰብ ትብብር የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ወንድሞች፣ ቤታቸውም ሆነ ግቢያቸው በንጽሕና መያዙ በሰዎች አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በመገንዘብ ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። የቤተሰብ ራሶች ይህን ማድረጋቸውና በመንፈሳዊ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ሆነው አመራር መስጠታቸው ቤተሰባቸውን በተገቢው ሁኔታ እንደሚያስተዳድሩ ያሳያል። (1 ጢሞ. 3:4, 12) እህቶችም በተለይ ከቤት አያያዝ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጉዳዮች የመከታተል ኃላፊነት አለባቸው። (ቲቶ 2:4, 5) ጥሩ ሥልጠና ያገኙ ልጆች የራሳቸውን ንጽሕና በመጠበቅ እንዲሁም ክፍላቸውን በሥርዓትና በንጽሕና በመያዝ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ። በዚህ መንገድ ቤተሰቡ የአምላክ መንግሥት ለሚያስተዳድረው አዲስ ዓለም የሚስማማ ጥሩ የንጽሕና ልማድ ያዳብራል።
11 በዛሬው ጊዜ ብዙዎቹ የይሖዋ ሕዝቦች ወደ ስብሰባ የሚሄዱት በመኪና ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ለአገልግሎት መኪና መጠቀም የግድ አስፈላጊ ሆኗል። መኪናችን ንጹሕና በጥሩ ሁኔታ የተያዘ መሆን ይኖርበታል። ቤታችንም ሆነ መኪናችን ንጹሕና ቅዱስ የሆነው የይሖዋ ሕዝብ ክፍል መሆናችንን ሊመሠክሩ ይገባል። የአገልግሎት ቦርሳችንና መጽሐፍ ቅዱሳችንም ንጹሕና በሥርዓት የተያዙ መሆን አለባቸው።
12 አለባበሳችንና አጋጌጣችን አምላክ ካወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። የተዝረከረከ ወይም ቤት ውስጥ የምንለብሰውን ልብስ ለብሰን አንድ ባለሥልጣን ፊት እንደማንቀርብ የታወቀ ነው። ታዲያ ይሖዋን ወክለን መስክ አገልግሎት ስንወጣ ወይም መድረክ ላይ ቆመን ስናስተምር ይበልጥ ጠንቃቃ ልንሆን አይገባም? አለባበሳችንና አጋጌጣችን ሰዎች ለይሖዋ አምልኮ በሚኖራቸው አመለካከት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። በዚህ ረገድ ልካችንን የማናውቅ ወይም ለሌሎች ስሜት ግድ የሌለን መሆን አይገባንም። (ሚክ. 6:8፤ 1 ቆሮ. 10:31-33፤ 1 ጢሞ. 2:9, 10) በመሆኑም አገልግሎት ለመውጣት አሊያም ወደ ጉባኤ፣ ወደ ወረዳ ስብሰባ ወይም ወደ ክልል ስብሰባ ለመሄድ ስንዘጋጅ ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ አካላዊ ንጽሕናም ሆነ ስለ ልከኝነት የሚናገሩትን ሐሳብ ማስታወስ ይኖርብናል። ምንጊዜም ይሖዋን ማስከበርና ከፍ ከፍ ማድረግ እንፈልጋለን።
ራሳችንን የወሰንን የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በምንናገረውም ሆነ በምናደርገው ነገር የይሖዋን ክብር የማንጸባረቅ ግዴታ አለብን
13 የይሖዋ ምሥክሮችን ዋና መሥሪያ ቤት ወይም ቅርንጫፍ ቢሮ በምንጎበኝበት ጊዜም ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት እንከተላለን። ቤቴል የሚለው ቃል “የአምላክ ቤት” የሚል ትርጉም እንዳለው አስታውስ። ስለዚህ ወደ ቤቴል ስንሄድ የሚኖረን አለባበስና የምናሳየው ምግባር በስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ ከሚኖረን አለባበስና ከምናሳየው ምግባር ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይገባል።
14 በምንዝናናበት ጊዜም ቢሆን ለአለባበሳችንና ለአጋጌጣችን ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር የምችልበት አጋጣሚ ባገኝ በአለባበሴ የተነሳ መስበክ ያሳፍረኛል?’
ጤናማ መዝናኛዎችና ጊዜ ማሳለፊያዎች
15 እረፍትም ሆነ መዝናኛ ሚዛናዊና ጤናማ ሕይወት ለመምራት አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ገለል ወዳለ ስፍራ አብረውት እንዲሄዱና ‘ትንሽ አረፍ እንዲሉ’ ሐሳብ አቅርቦላቸው ነበር። (ማር. 6:31) እረፍት እንዲሁም ጤናማ መዝናኛ ወይም የጊዜ ማሳለፊያ ዘና እንድንል ሊያደርገን ይችላል። ኃይላችን እንዲታደስና ዕለታዊ እንቅስቃሴያችንን በጥሩ ሁኔታ እንድናከናውን ይረዳናል።
16 በዛሬው ጊዜ ብዙ ዓይነት መዝናኛዎች ስላሉ ክርስቲያኖች በአምላካዊ ጥበብ በመመራት ጥሩ ምርጫ ማድረግ ይኖርባቸዋል። መዝናኛ ጠቃሚ ቢሆንም በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ አይገባም። “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ሰዎች “ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል። (2 ጢሞ. 3:1, 4) መዝናኛ ወይም ጊዜ ማሳለፊያ ተብለው የሚቀርቡት አብዛኞቹ ነገሮች የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች መጠበቅ በሚፈልጉ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም።
17 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በዙሪያቸው ያለው ተድላ ወዳድ ዓለም የሚያሳድርባቸውን መጥፎ ተጽዕኖ መቋቋም ነበረባቸው። በሮማውያን የሰርከስ ትርዒቶች ላይ፣ ተመልካቾች የሌሎችን ሥቃይ በማየት ይዝናኑ ነበር። ተመልካቹን ለማዝናናት ሲባል ጭካኔ፣ ደም መፋሰስና የፆታ ብልግና የሞሉባቸው ትርዒቶች ይቀርቡ ነበር፤ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ግን እንዲህ ባሉት ነገሮች ከመዝናናት ይርቁ ነበር። በዛሬው ጊዜ ዓለም የሚያቀርበው አብዛኛው መዝናኛ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ከመሆኑም ሌላ የሰዎችን ወራዳ ፍላጎት ለማርካት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በመሆኑም የሥነ ምግባር አቋማችንን ከሚያበላሹ መዝናኛዎች ልንርቅና እንዴት እንደምንመላለስ ‘ምንጊዜም በጥንቃቄ ልናስተውል’ ይገባል። (ኤፌ. 5:15, 16፤ መዝ. 11:5) ከዚህም ሌላ መዝናኛው በራሱ አጠያያቂ ባይሆንም በዚያ መዝናኛ መካፈላችን ለመጥፎ ተጽዕኖ ሊያጋልጠን ይችላል።—1 ጴጥ. 4:1-4
18 ለክርስቲያኖች የሚሆኑ ጥሩ ዓይነት መዝናኛዎችና ጊዜ ማሳለፊያዎች አሉ። ብዙዎች በጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችና ሚዛናዊ ሐሳቦች በመከተላቸው ተጠቅመዋል።
19 የተወሰኑ ቤተሰቦች ሰብሰብ ብለው እንዲጫወቱ ወደ አንድ ቤት ይጋበዙ ይሆናል። በተጨማሪም ወንድሞችና እህቶች በሠርግ ወይም በሌላ ግብዣ ላይ እንዲገኙ ሊጠሩ ይችላሉ። (ዮሐ. 2:2) ጋባዦቹ በግብዣው ላይ ለሚከናወነው ነገር ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይገባል። በርከት ያሉ ሰዎች የሚገኙበት ግብዣ ስናዘጋጅ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው። በእነዚህ ግብዣዎች ላይ ያለው ዘና ያለ ሁኔታ አንዳንዶች ከልክ በላይ እንደ መብላት ወይም መጠጣት ያሉ ድርጊቶችን በመፈጸም ተገቢ ከሆነ ክርስቲያናዊ ምግባር አልፈው እንዲሄዱ አልፎ ተርፎም ከዚህ የከፋ ኃጢአት እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል። ይህን አደጋ የተገነዘቡ አስተዋይ ክርስቲያኖች፣ የተጋባዦቹን ቁጥርም ሆነ ግብዣው የሚቆይበትን ሰዓት መገደቡን ጥበብ ሆኖ አግኝተውታል። የአልኮል መጠጥ የሚቀርብ ከሆነ ልከኛ መሆን ያስፈልጋል። (ፊልጵ. 4:5) ከወንድሞቻችን ጋር ሰብሰብ ብለን የምንጫወትባቸውን ዝግጅቶች ስናደርግ ትኩረት ልንሰጥ የሚገባው ዝግጅቱን ጤናማና በመንፈሳዊ የሚያንጽ እንዲሆን ለማድረግ እንጂ ለምግብና ለመጠጥ መሆን የለበትም።
20 እንግዳ ተቀባይ መሆን የሚያስመሰግን ባሕርይ ነው። (1 ጴጥ. 4:9) ለምግብ፣ ሻይ ቡና ለማለት አሊያም አብረን ለመጨዋወት ወንድሞችን ቤታችን በምንጋብዝበት ወቅት እምብዛም ትኩረት የማይሰጣቸውን ሰዎች መዘንጋት አይኖርብንም። (ሉቃስ 14:12-14) እንዲህ ባለው ዝግጅት ላይ ተጋብዘን ስንገኝ ምግባራችን በማርቆስ 12:31 ላይ ካለው ምክር ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። ሌሎች ላሳዩን ደግነት ምንጊዜም አመስጋኝ መሆናችን ተገቢ ነው።
21 ክርስቲያኖች ከአምላክ ባገኟቸው የተትረፈረፉ ስጦታዎች የሚደሰቱ ከመሆኑም ሌላ ‘በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም ተግተው በሚሠሩት ሥራ ሁሉ ደስታ ማግኘት’ በመቻላቸው እርካታ ይሰማቸዋል። (መክ. 3:12, 13) ጋባዦችም ሆን ተጋባዦች “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር” የምናደርግ ከሆነ አብረን በመጫወት ያሳለፍነውን በመንፈሳዊ የሚያድስ ጊዜ መለስ ብለን ስናስብ ደስታ ይሰማናል።
የትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎች
22 የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች መሠረታዊ የሆነ የቀለም ትምህርት መቅሰማቸው ጠቃሚ ነው። ትምህርት ቤት ገብተው መማራቸው ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በትምህርት ቤት የሚሰጡ ሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ወጣቶች መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት ሊጠቅሟቸው ይችላሉ። በትምህርት ቤት በሚያሳልፏቸው ዓመታት ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት ‘ታላቁን ፈጣሪያቸውን ለማሰብ’ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።—መክ. 12:1
23 ትምህርትህን እየተከታተልክ ያለህ ወጣት ክርስቲያን ከሆንክ ከዓለማዊ ወጣቶች ጋር አላስፈላጊ ቅርርብ ላለመፍጠር መጠንቀቅ ይኖርብሃል። (2 ጢሞ. 3:1, 2) ይሖዋ ጥበቃ እንድናገኝ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎልናል፤ በመሆኑም ራስህን ከዓለማዊ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ ማድረግ የምትችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። (መዝ. 23:4፤ 91:1, 2) ስለዚህ ራስህን ከአደጋ ለመጠበቅ ይሖዋ ባዘጋጃቸው ዝግጅቶች ተጠቀም።—መዝ. 23:5
24 አብዛኞቹ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ከዓለም የተለዩ ለመሆን ሲሉ በትምህርት ቤት ቆይታቸው ከትምህርት ሰዓት ውጭ በሚደረጉ እንደ ስፖርትና ክበቦች ባሉ እንቅስቃሴዎች ላለመካፈል ወስነዋል። አብረውህ የሚማሩ ልጆችና አስተማሪዎችህ እንዲህ የምታደርግበት ምክንያት አይገባቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ዋናው ነገር አምላክን ማስደሰትህ ነው። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናህ በመመራት፣ የፉክክር መንፈስ አሊያም ብሔራዊ ስሜት ከሚንጸባረቅባቸው እንቅስቃሴዎች ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ ታደርጋለህ ማለት ነው። (ገላ. 5:19, 26) እናንት ወጣቶች፣ ክርስቲያን ወላጆቻችሁ የሚሰጧችሁን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመስማትና በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ወዳጆችን በማፍራት የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች መጠበቅ ትችላላችሁ።
ሰብዓዊ ሥራና ጓደኞቻችን
25 የቤተሰብ ራሶች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር የማሟላት ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ አለባቸው። (1 ጢሞ. 5:8) ያም ሆኖ የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናቸው መጠን ሰብዓዊ ሥራቸው፣ ከመንግሥቱ ጉዳዮች ጋር ሲወዳደር ሁለተኛ ደረጃ እንደሚይዝ ያውቃሉ። (ማቴ. 6:33፤ ሮም 11:13) ለአምላክ ያደሩ በመሆን እንዲሁም ምግብና ልብስ በማግኘታቸው ረክተው በመኖር ቁሳዊ ነገሮችን ማሳደድ ከሚያስከትለው ጭንቀትና ወጥመድ ይድናሉ።—1 ጢሞ. 6:6-10
26 ሰብዓዊ ሥራ የሚሠሩ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መዘንጋት አይኖርባቸውም። ከምንሠራው ሥራ ጋር በተያያዘ ሐቀኛ መሆን ሲባል የአምላክን ወይም የአገሪቱን ሕግ በሚያስጥሱ ሥራዎች ከመካፈል መቆጠብ ማለት ነው። (ሮም 13:1, 2፤ 1 ቆሮ. 6:9, 10) መጥፎ ጓደኝነት የሚያስከትለውን አደጋ መቼም ቢሆን አንዘነጋም። የክርስቶስ ወታደሮች እንደመሆናችን መጠን አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች እንድንጥስ፣ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችንን እንድናላላ ወይም መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ እንድንጥል በሚያደርጉ የንግድ ሥራዎች ከመሳተፍ እንቆጠባለን። (ኢሳ. 2:4፤ 2 ጢሞ. 2:4) በተጨማሪም የአምላክ ጠላት ከሆነችው “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ ከምትጠራው የሐሰት ሃይማኖት ድርጅት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖረን አንፈልግም።—ራእይ 18:2, 4፤ 2 ቆሮ. 6:14-17
27 የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች በጥብቅ መከተላችን ክርስቲያናዊ ግንኙነታችንን፣ የንግድ ጉዳዮችን ወይም ሌሎች የግል ጥቅሞችን ለማራመድ ከመጠቀም እንድንቆጠብ ያደርገናል። በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ከሌሎች ጋር የምንገናኝበት ብቸኛው ዓላማ ይሖዋን ለማምለክ ነው። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ይሖዋ ካዘጋጀው መንፈሳዊ ማዕድ የምንመገብ ከመሆኑም ሌላ ‘እርስ በርሳችን የምንበረታታበት’ አጋጣሚ እናገኛለን። (ሮም 1:11, 12፤ ዕብ. 10:24, 25) እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ምንጊዜም በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆን ይገባዋል።
ክርስቲያናዊ አንድነትን ጠብቆ መኖር
28 የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች መጠበቅ “[በሰላም] ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት” ማድረግን ይጨምራል። (ኤፌ. 4:1-3) እያንዳንዳችን ራሳችንን ለማስደሰት ከመጣር ይልቅ ለሌሎች መልካም የሆነውን እናደርጋለን። (1 ተሰ. 5:15) በጉባኤህ ውስጥ እንዲህ ያለ መንፈስ እንደተመለከትክ ምንም ጥርጥር የለውም። ዘራችን፣ ብሔራችን፣ ማኅበራዊ ሁኔታችን፣ የኑሮ ወይም የትምህርት ደረጃችን ምንም ይሁን ምን ሁላችንም የምንመራበት የጽድቅ መሥፈርት አንድ ዓይነት ነው። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ የይሖዋ ሕዝቦች በዚህ ረገድ የተለዩ መሆናቸውን ማስተዋል ችለዋል።—1 ጴጥ. 2:12
29 መጽሐፍ ቅዱስ ለአንድነታችን መሠረት የሆነውን ነገር ይበልጥ ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የተጠራችሁበት አንድ ተስፋ እንዳለ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት አለ፤ ደግሞም ከሁሉ በላይ የሆነ፣ በሁሉም አማካኝነት የሚሠራና በሁሉም ላይ የሚሠራ የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።” (ኤፌ. 4:4-6) እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ሐሳብ መሠረታዊም ሆነ ጥልቅ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በመረዳት ረገድ አንድነት ሊኖረን እንደሚገባ ይጠቁማል፤ በዚህ መንገድ ለይሖዋ ሉዓላዊነት ዕውቅና እንደምንሰጥ እናሳያለን። በእርግጥም፣ ይሖዋ የእውነትን ንጹሕ ቋንቋ ለሕዝቡ በመስጠት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያገለግሉት አስችሏቸዋል።—ሶፎ. 3:9
30 የክርስቲያን ጉባኤ አንድነትና ሰላም ይሖዋን ለሚያመልኩ ሁሉ የብርታት ምንጭ ነው። ይሖዋ “በጉረኖ ውስጥ እንዳለ በግ . . . በአንድነት አኖራቸዋለሁ” ሲል የገባውን ቃል ፍጻሜ ማየት ችለናል። (ሚክ. 2:12) ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን በመኖር ሰላማዊ አንድነታችን እንዳይጠፋ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንፈልጋለን።
31 ንጹሕ በሆነው የይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ተቀባይነት ያገኙ ሁሉ ምንኛ ደስተኞች ናቸው! የይሖዋን ስም የመሸከም መብታችንን ላለማጣት ስንል ማንኛውንም ዓይነት መሥዋዕት መክፈላችን ፈጽሞ አያስቆጨንም። ከይሖዋ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና ጠብቀን ስንኖር የጽድቅ መሥፈርቶቹን ለማሟላት ትጋት የተሞላበት ጥረት የምናደርግ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም ይህንኑ እንዲያደርጉ እናበረታታለን።—2 ቆሮ. 3:18