-
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያለብኝ ለምንድን ነው?መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017 | ቁጥር 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስደሳች ማድረግ
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያለብኝ ለምንድን ነው?
“መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለመረዳት ከባድ የሆነ መጽሐፍ ይመስለኝ ነበር።”—ጁቪ
“በጣም አሰልቺ እንደሚሆን ተሰምቶኝ ነበር።”—ክዊኒ
“መጽሐፍ ቅዱስን ሳየው፣ መቼም ቢሆን አንብቤ ልጨርሰው እንደማልችል ስለተሰማኝ ተስፋ ቆረጥኩ።”—ኢዚክኤል
አንተስ ከላይ እንደተጠቀሱት ሰዎች ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? በዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ወደ ኋላ ብለህ ይሆን? ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጣም ከባድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆንና አርኪ ሕይወት እንድትመራ እንደሚረዳህ ብታውቅስ? እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስደሳች እንዲሆንልህ የሚረዱ አንዳንድ ዘዴዎች እንዳሉ ብትረዳስ? መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ አትነሳሳም?
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በመጀመራቸው ጥቅም ያገኙ አንዳንድ ሰዎች የተናገሩትን ሐሳብ እስቲ ተመልከት።
በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ኢዚክኤል እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል፣ የት እንደሚሄድ ሳያውቅ ዝም ብሎ መኪና እንደሚነዳ ሰው ነበርኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ ግን ሕይወቴ ዓላማ ያለው እንዲሆን ረድቶኛል። በዕለት ተዕለት ሕይወቴ ልሠራበት የምችል ጠቃሚ ምክር ይዟል።”
በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ፍሪዳ የተባለች ወጣትም እንዲህ ብላለች፦ “ቀደም ሲል ቶሎ እበሳጭ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ ግን ራሴን መቆጣጠር እንድችል ረድቶኛል። ይህም በቀላሉ የምቀረብ እንድሆን ስለረዳኝ አሁን ብዙ ጓደኞች ማፍራት ችያለሁ።”
በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ዩኒስ የተባለች ሴት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስትናገር “የተሻልኩ ሰው እንድሆንና መጥፎ ልማዶቼን እንድተው እየረዳኝ ነው” ብላለች።
ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን እንደሚረዳ ተመልክተዋል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ፣ እውነተኛ ጓደኞችን ለማፍራት፣ ውጥረትን ለመቋቋም፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ስለ አምላክ እውነቱን ለማወቅ ይረዳል፤ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምክር ምንጭ አምላክ ነው፤ በመሆኑም ምክሩ መቼም ቢሆን የተሳሳተ ሊሆን አይችልም። አምላክ መጥፎ ምክር እንደማይሰጠን የታወቀ ነው።
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ወደ ኋላ አትበል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንድትጀምርና ንባብህን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ የሚረዱ ምን ዘዴዎች አሉ?
-
-
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ መጀመር የምችለው እንዴት ነውመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017 | ቁጥር 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስደሳች ማድረግ
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ መጀመር የምችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስደሳች እንዲሆንልህና ከንባብህ ይበልጥ ጥቅም ማግኘት እንድትችል ምን ሊረዳህ ይችላል? ብዙ ሰዎች ውጤታማ ሆነው ያገኟቸውን አምስት ነጥቦች ተመልከት።
ለማንበብ አመቺ የሆነ ቦታ ምረጥ። ጸጥ ያለ ቦታና ጊዜ ለማግኘት ሞክር። በምታነበው ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ እንድትችል ሐሳብ የሚከፋፍሉ ነገሮችን አስወግድ። በቂ ብርሃንና ንጹሕ አየር ያለበት ቦታ ሆነህ ማንበብህ ከንባብህ የተሻለ ጥቅም እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።
አእምሮህን ክፍት አድርገህ አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ካለው አባታችን ያገኘነው ስጦታ ነው፤ አንድ ልጅ አፍቃሪ ከሆነ ወላጁ ለመማር እንደሚጓጓ ሁሉ አንተም እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ይዘህ ማንበብህ ከንባብህ የተሻለ ጥቅም እንድታገኝ ይረዳሃል። አምላክ እንዲያስተምርህ ከፈለግክ በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ያሉህን አሉታዊ አመለካከቶች ከአእምሮህ ማውጣት አለብህ።—መዝሙር 25:4
ማንበብ ከመጀመርህ በፊት ጸልይ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ ሐሳብ ነው፤ በመሆኑም ሐሳቡን መረዳት እንድንችል የአምላክ እርዳታ የሚያስፈልገን መሆኑ አያስገርምም። አምላክ ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጣቸው’ ቃል ገብቷል። (ሉቃስ 11:13) መንፈስ ቅዱስ የአምላክን አስተሳሰብ እንድትረዳ ያግዝሃል። በጊዜ ሂደት፣ ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮችም’ ሳይቀር መረዳት እንድትችል አእምሮህን ይከፍትልሃል።—1 ቆሮንቶስ 2:10
የምታነበውን ነገር ለመረዳት ሞክር። የተወሰኑ ገጾችን ለመሸፈን ብቻ ብለህ አታንብብ። የምታነበውን ነገር ለማስተዋል ጥረት አድርግ። ራስህን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቅ፦ ‘በዘገባው ላይ የተጠቀሰው ግለሰብ ምን ጥሩ ባሕርያት አሉት? እነዚህን ባሕርያት በሕይወቴ ውስጥ ማንጸባረቅ የምችለው እንዴት ነው?’
ግብ አውጣ። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ለራስህ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ለማግኘት ግብ አድርግ። ለምሳሌ ስለ አምላክ ይበልጥ ለማወቅ ግብ አድርገህ ልታነብ ትችላለህ። አሊያም ደግሞ የተሻለ ሰው ወይም ባል መሆን የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለመማር ግብ ማውጣት ትችላለህ። ከዚያም ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ የሚረዱህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምረጥ።a
እነዚህ አምስት ነጥቦች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንድትጀምር ይረዱሃል። ሆኖም ንባብህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ረገድ የሚረዱህን አንዳንድ ሐሳቦች ይዟል።
a ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ የሚረዳህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የቱ እንደሆነ ካላወቅክ የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።
-
-
የመጽሐፍ ቅዱስን ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017 | ቁጥር 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስደሳች ማድረግ
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን ስለ ማንበብ ስታስብ ምን ይሰማሃል? አሰልቺ እንደሆነ ይሰማሃል? ወይስ አስደሳች? በአብዛኛው ይህን የሚወስነው የምታነብበት መንገድ ነው። የማንበብ ጉጉት እንዲያድርብህና ንባብህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆንልህ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
እምነት የሚጣልበትና ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ምረጥ። የምታነበው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከባድ ወይም በአሁኑ ጊዜ የማይሠራባቸው ቃላት የበዙበት ከሆነ ንባብህ አስደሳች እንደማይሆንልህ የታወቀ ነው። ስለዚህ ልብህን የሚነካና ለመረዳት ቀላል የሆነ ቋንቋ የሚጠቀም ትርጉም ፈልግ። ሆኖም ትርጉሙ በጥንቃቄና በትክክለኛው መንገድ የተተረጎመ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብሃል።a
የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቀም። በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ብቻ ሳይሆን በኤሌክትሮኒክ ቅጂም ማግኘት ይቻላል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ኢንተርኔት ላይ እንዳለህ አሊያም በኮምፒውተር፣ በታብሌት ወይም በሞባይል ስልክ ላይ አውርደህ ማንበብ ትችላለህ። አንዳንድ አፕሊኬሽኖች፣ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስታነብ ከጥቅሱ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ሌሎች ጥቅሶችን በቀላሉ ለማውጣት ወይም ከተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጋር ለማመሳከር የሚያስችል ገጽታ አላቸው። ከማንበብ ይልቅ መስማት የምትመርጥ ከሆነ ደግሞ በድምፅ የተቀዳ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገኝባቸው ቋንቋዎችም አሉ። ብዙ ሰዎች በትራንስፖርት ሲጓዙ፣ ልብስ ሲያጥቡ ወይም አመቺ በሆኑ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሲካፈሉ የተቀዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ማዳመጥ ያስደስታቸዋል። ታዲያ አንተስ የሚቀልህን ዘዴ መርጠህ ለምን አትሞክረውም?
መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተዘጋጁ መሣሪያዎችን ተጠቀም። እነዚህ መሣሪያዎች ከንባብህ ይበልጥ ጥቅም እንድታገኝ ይረዱሃል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ቦታዎችን የሚያሳዩ ካርታዎች አሉ፤ እነዚህ ካርታዎች በምታነበው ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት ቦታዎች የት እንደሚገኙ ለማወቅና ዘገባውን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያግዙሃል። በዚህ መጽሔት ላይ እንዲሁም በjw.org/am ላይ “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች” በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡት ርዕሶች የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምን መልእክት እንደሚያስተላልፉ እንድትገነዘብ ይረዱሃል።
የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቀም። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ማንበብ ከባድ እንደሆነ ከተሰማህ ይበልጥ ትኩረትህን ከሚስበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለምን አትጀምርም? እንዲህ ማድረግህ የማንበብ ጉጉትህ እንዲቀሰቀስ ይረዳሃል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተደጋጋሚ ስለሚጠቀሱ ሰዎች ማወቅ ከፈለግክ ስለ እነዚህ ሰዎች የሚገልጸው ዘገባ የሚገኝበትን ክፍል መርጠህ ማንበብ ትችላለህ። “በውስጡ ስለተጠቀሱት ሰዎች በማንበብ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር” በሚለው ሣጥን ውስጥ የተጠቀሰውን ሐሳብ እንደ ናሙና መጠቀም ትችላለህ። አሊያም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በርዕሰ ጉዳይ ወይም ነገሮች በተከናወኑበት ቅደም ተከተል መሠረት ማንበብ ትፈልግ ይሆናል። ከእነዚህ ዘዴዎች መካከል አንዱን ለምን አትሞክርም?
a ብዙዎች አዲስ ዓለም ትርጉምን ትክክለኛ፣ እምነት የሚጣልበትና ለማንበብ ቀላል ሆኖ አግኝተውታል። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከ130 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ይገኛል። ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማግኘት ከፈለግክ ከjw.org/am ላይ ማውረድ ወይም JW Library የተባለውን አፕሊኬሽን መጫን ትችላለህ። አሊያም ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ቤትህ ድረስ እንዲያመጡልህ መጠየቅ ትችላለህ።
-
-
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴ እንዲሻሻል የሚረዳኝ እንዴት ነው?መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017 | ቁጥር 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስደሳች ማድረግ
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴ እንዲሻሻል የሚረዳኝ እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ የተለየ ነው። የፈጣሪያችንን ምክር የያዘ መጽሐፍ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መልእክቱ በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው” ይላል። (ዕብራውያን 4:12) መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሕይወታችን እንዲሻሻል ያደርጋል፤ አንደኛ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምንመራበት ምክር ይሰጠናል፤ ሁለተኛ ደግሞ አምላክንና ተስፋዎቹን እንድናውቅ ይረዳናል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8፤ ያዕቆብ 4:8
ሕይወታችንን የምንመራበት ምክር ይሰጠናል። መጽሐፍ ቅዱስ በግል ሕይወትህ ውስጥ በሚያጋጥሙህ ጉዳዮችም ረገድ ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ስለሚከተሉት ጉዳዮች ጠቃሚ ምክር ይሰጣል፦
ከሌሎች ጋር ስላለን ግንኙነት። —ኤፌሶን 4:31, 32፤ 5:22, 25, 28, 33
ስለ ስሜታዊና አካላዊ ጤንነት። —መዝሙር 37:8፤ ምሳሌ 17:22
ስለ ሥነ ምግባር እሴቶች።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
በእስያ የሚኖሩ ቪሰንትና አነሉ የተባሉ አንድ ወጣት ባልና ሚስት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። እንደ ሌሎቹ አዲስ ተጋቢዎች ሁሉ እነሱም በባሕርይ እርስ በርስ መጣጣም እንዲሁም በግልጽ መነጋገር ከባድ ሆኖባቸው ነበር። በኋላ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበቡትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ቪሰንት እንዲህ ብሏል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበብኩት ነገር በትዳራችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመፍታት ረድቶኛል። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋላችን ደስተኛ እንድንሆን ረድቶናል።” ባለቤቱ አነሉ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች ማንበባችን ረድቶናል። አሁን በትዳራችንም ሆነ በሕይወታችን ውስጥ ባሉን ግቦች ደስተኛ ነኝ።”
አምላክን እንድታውቅ ይረዳሃል። ቪሰንት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከትዳር ሕይወቱ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በሌላ አቅጣጫም እንደረዳው ሲናገር “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋb እንድቀርብ ረድቶኛል” ብሏል። ቪሰንት የተናገረው ሐሳብ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ ይኸውም ስለ አምላክ እንድታውቅ እንደሚረዳህ ይጠቁማል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብህ አምላክ ከሚሰጠው ምክር ተጠቃሚ እንድትሆን ብቻ ሳይሆን ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድትመሠርትም ይረዳሃል። በተጨማሪም አምላክ ለሰው ልጆች አስደሳች ተስፋ እንዳዘጋጀ እንድትገነዘብ ያስችልሃል፤ ወደፊት ሁላችንም “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” እያጣጣምን ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) እንዲህ ስላለው ተስፋ ልታውቅ የምትችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከጀመርክና በዚያው ከገፋህበት፣ ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሞች ልታገኝ ይኸውም ሕይወትህ ሊሻሻልና አምላክን ልታውቅ ትችላለህ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ብዙ ጥያቄዎች ሊፈጠሩብህ ይችላሉ። ጥያቄዎች ሲፈጠሩብህ፣ ከ2,000 ዓመታት በፊት የኖረ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን የተወውን ጥሩ ምሳሌ ለመከተል ጥረት አድርግ። ይህ ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩት። የሚያነበውን ነገር ይረዳው እንደሆነ ሲጠየቅ “የሚመራኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” በማለት መልሷል።c ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ብቃት ያለው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው ፊልጶስ የሰጠውን እርዳታ በደስታ ተቀብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 8:30, 31, 34) አንተም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ከፈለግክ www.pr2711.com/am በተባለው ድረ ገጽ ላይ የሚገኘውን ቅጽ መሙላት ወይም በዚህ መጽሔት ላይ ካሉት አድራሻዎች ወደ አንዱ መጻፍ ትችላለህ። አሊያም ደግሞ በአቅራቢያህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር ወይም በአካባቢህ ወደሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ አዳራሽ መሄድ ትችላለህ። ታዲያ ዛሬውኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ለምን አትጀምርም? እንዲህ ማድረግህ ወደተሻለ ሕይወት ይመራሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት ስለመሆኑ ጥያቄ ካለህ መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጣ መሆኑን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? የሚለውን አጭር ቪዲዮ እንድትመለከት እንጋብዝሃለን። ቪዲዮውን jw.org/am ላይ የሕትመት ውጤቶች > ቪዲዮዎች > መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው ሥር ማግኘት ትችላለህ።
a መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጣቸው ሌሎች ጠቃሚ ምክሮች ለማወቅ jw.org/am የተባለውን ድረ ገጻችንን መጎብኘት ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው በሚለው ሥር ተመልከት።
b መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።
c በተጨማሪም በዚህ መጽሔት ውስጥ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ መረዳት ያለው አደጋ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
-