የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • “ክርስቲያን” የተባለ ሁሉ ክርስቲያን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2012 | መጋቢት 1
    • “ክርስቲያን” የተባለ ሁሉ ክርስቲያን ነው?

      በዛሬው ጊዜ ምን ያህል ክርስቲያኖች አሉ? አትላስ ኦቭ ግሎባል ክርስቲያኒቲ የተባለው መጽሐፍ በገለጸው መሠረት በ2010 በመላው ዓለም ወደ 2.3 ቢሊዮን የሚጠጉ ክርስቲያኖች ነበሩ። ይሁንና ይኸው ጽሑፍ እንደሚያመለክተው እነዚህ ክርስቲያኖች ከ41,000 በሚበልጡ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ውስጥ የታቀፉ ሲሆን እያንዳንዱ ቡድን የየራሱ መሠረተ ትምህርትና የሥነ ምግባር ደንብ አለው። ይህን ያህል ብዛት ያላቸው “የክርስትና” ሃይማኖቶች ከመኖራቸው አንጻር አንዳንዶች በሁኔታው ግራ ቢጋቡ፣ አልፎ ተርፎም ተስፋ ቆርጠው የሃይማኖትን ነገር እርግፍ አድርገው ቢተዉት አያስገርምም። እነዚህ ሰዎች፣ ‘ለመሆኑ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ በእርግጥ ክርስቲያኖች ናቸው?’ የሚለው ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይችላል።

      እስቲ ጉዳዩን ከሌላ አቅጣጫ እንመልከተው። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ተጓዥ ወደ አንድ አገር ሲገባ ዜግነቱን እንዲናገር ይጠበቅበታል። በተጨማሪም ማንነቱን የሚያረጋግጥ መታወቂያ ወረቀት ምናልባትም ፓስፖርት በማሳየት የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን የሚጠቁም መረጃ ማቅረብ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በክርስቶስ እንደሚያምን ከመናገር ባለፈ ተጨማሪ መለያ ሊኖረው ይገባል። ይህ መለያ ምንድን ነው?

      “ክርስቲያን” የሚለው ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በ44 ዓ.ም. ገደማ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ “ደቀ መዛሙርቱም በመለኮታዊ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ክርስቲያኖች’ ተብለው የተጠሩት በአንጾኪያ ነበር” በማለት ዘግቧል። (የሐዋርያት ሥራ 11:26) ክርስቲያኖች ተብለው የተጠሩት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደነበሩ ልብ በል። ይሁን እንጂ አንድን ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሚያስብለው ምንድን ነው? ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲዎሎጂ እንዲህ ይላል፦ “የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ሲባል በሕይወት እስካሉ ድረስ . . . መላ ሕይወትን ያለ ገደብ መሥዋዕት ማድረግ ማለት ነው።” ስለዚህ አንድ ሰው እውነተኛ ክርስቲያን የሚባለው የክርስትና መሥራች የሆነውን የኢየሱስን ትምህርቶችና መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ እና ያለ ምንም ገደብ የሚከተል ከሆነ ነው።

      በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን እንደሆኑ ከሚናገሩት ብዙ ሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል እንዲህ ዓይነት ሰዎች ማግኘት ይቻላል? ኢየሱስ ራሱ፣ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ ተለይተው ከሚታወቁበት ምልክት ጋር በተያያዘ ምን ብሏል? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንድትመረምር እናበረታታሃለን። በቀጣዮቹ ርዕሶች ውስጥ የኢየሱስን እውነተኛ ተከታዮች ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉንን እሱ የተናገራቸውን አምስት ነጥቦች እንመረምራለን። እንዲሁም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እነዚህን ብቃቶች እንዴት እንዳሟሉ እንመለከታለን። ከዚያም በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ከሚናገሩት ብዙ ሃይማኖቶች መካከል እነዚህን ብቃቶች እያሟሉ ያሉት እነማን እንደሆኑ ለማየት እንሞክራለን።

  • ‘በቃሌ ኑሩ’
    መጠበቂያ ግንብ—2012 | መጋቢት 1
    • ‘በቃሌ ኑሩ’

      “በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።”​—ዮሐንስ 8:31, 32

      ይህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ “ቃሌ” ያለው እሱ ያስተማረውን ትምህርት ሲሆን ይህ ትምህርት የመነጨውም ከእሱ በላይ ሥልጣን ካለው አካል ነው። ኢየሱስ “ምን እንደምልና ምን እንደምናገር ያዘዘኝ የላከኝ አብ ራሱ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 12:49) ኢየሱስ በሰማይ ወዳለው አባቱ ይኸውም ወደ ይሖዋ አምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። ላስተማረው ትምህርት ድጋፍ እንዲሆነውም የአምላክን ቃል በተደጋጋሚ ይጠቅስ ነበር። (ዮሐንስ 17:17፤ ማቴዎስ 4:4, 7, 10) በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚባሉት፣ ‘በቃሉ የሚኖሩ’ ይኸውም የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን “እውነት” እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱ እንዲሁም ከሚያምኑባቸው ነገሮችና ከተግባራቸው ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መጨረሻው ባለሥልጣን አድርገው የሚቀበሉ ሰዎች ናቸው።

      የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ብቃት አሟልተዋል? በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የጻፈው ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ልክ እንደ ኢየሱስ ለአምላክ ቃል አክብሮት ነበረው። ጳውሎስ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም . . . ይጠቅማል” ብሏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸውን እንዲያስተምሩ የተሾሙ ወንዶችም ‘የታመነውን ቃል አጥብቀው መያዝ’ ነበረባቸው። (ቲቶ 1:7, 9) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ” የሚል ምክር ተሰጥቷቸው ነበር።​—ቆላስይስ 2:8

      በዛሬው ጊዜ ብቃቱን የሚያሟሉት እነማን ናቸው? ቫቲካን በ1965 በተቀበለችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማስተማሪያ ጽሑፍ (እንግሊዝኛ) ላይ የተጠቀሰው መለኮታዊ ራእይን የሚመለከት የቫቲካን ድንጋጌ (እንግሊዝኛ) እንደሚለው የቤተ ክርስቲያኗ አቋም የሚከተለው ነው፦ “[የካቶሊክ] ቤተ ክርስቲያን ስለተገለጠላት ስለ እያንዳንዱ ነገር ማስረጃ አድርጋ የምታቀርበው ቅዱስ ጽሑፉን ብቻ አይደለም። በመሆኑም ቅዱሳን ወጎችንም ሆነ ቅዱሳን መጻሕፍትን እኩል በሆነ መልኩ እምነት ልንጥልባቸውና ልዩ አክብሮት ልንሰጣቸው ይገባል።” ማክሊንስ በተሰኘ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ መጣጥፍ በቶሮንቶ፣ ካናዳ የምትገኝ አንዲት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሚከተለውን ጥያቄ እንዳቀረበች ጠቅሶ ነበር፦ “ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በተጻፈ ‘የለውጥ’ ድምፅ መመራት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? የራሳችን የሆኑ ድንቅ ሐሳቦች አሉን፤ ይሁንና ለእነዚህ ሐሳቦች ከኢየሱስና ከቅዱስ ጽሑፉ ድጋፍ ማግኘት ስለሚጠበቅብን ሁልጊዜ ኃይላቸው ይዳከምብናል።”

      ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ስለ የይሖዋ ምሥክሮች ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ብቸኛው የእምነታቸው መሠረትና የሥነ ምግባር መመሪያቸው አድርገው ይመለከቱታል።” በቅርቡ በካናዳ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለአንድ ሰው ራሷን ስታስተዋውቅ ግለሰቡ አቋረጣትና ወደ መጽሐፍ ቅዱሷ እያመለከተ “ማንነትሽን በምልክትሽ አውቄያለሁ” አላት።

  • ‘የዓለም ክፍል አይደሉም’
    መጠበቂያ ግንብ—2012 | መጋቢት 1
    • ‘የዓለም ክፍል አይደሉም’

      “የዓለም ክፍል ስላልሆኑ ዓለም ጠላቸው።”​—ዮሐንስ 17:14

      ይህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ የዓለም ክፍል ስላልነበር በዘመኑ በነበሩት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ረገድ ገለልተኛ ነበር። “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:36) ተከታዮቹንም የአምላክ ቃል ከሚያወግዘው ዝንባሌ፣ ንግግርና ምግባር እንዲርቁ አሳስቧቸዋል።​—ማቴዎስ 20:25-27

      የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ብቃት አሟልተዋል? ስለ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የሚጽፉት ጆናታን ዳይመንድ እንደተናገሩት የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “መዘዙ ምንም ይሁን ምን፣ ውርደትና እስራት ወይም ሞት ቢያስከትልባቸው እንኳ [በጦርነት] አይካፈሉም ነበር።” እነዚያ ክርስቲያኖች የገለልተኝነት አቋማቸውን ከማላላት ይልቅ መሠቃየትን ይመርጡ ነበር። የሚከተሉት የሥነ ምግባር ደንብም ቢሆን ከሌሎች የተለዩ ያደርጋቸው ነበር። ክርስቲያኖች “ይህን በመሰለው ያዘቀጠ ወራዳ ሕይወት ከእነሱ ጋር መሮጣችሁን ስለማትቀጥሉ ይደነቃሉ እንዲሁም ይሰድቧችኋል” ተብለዋል። (1 ጴጥሮስ 4:4) የታሪክ ምሁር የሆኑት ዊል ዱራንት፣ የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ “ተድላ ያሳበደውን አረማዊ ዓለም በመንፈሳዊ አቋሙና በመልካም ምግባሩ ይኮንነው ነበር” በማለት ጽፈዋል።

      በዛሬው ጊዜ ብቃቱን የሚያሟሉት እነማን ናቸው? ክርስቲያናዊ ገለልተኝነትን በተመለከተ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል፦ “በሕሊና ምክንያት በጦርነት አለመካፈል ከሥነ ምግባር አንጻር ተቀባይነት የለውም።” የ1994ቱን የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አስመልክቶ አንድ የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ያወጣው ዘገባ “ከይሖዋ ምሥክሮች በስተቀር” ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ጭፍጨፋ መካፈላቸውን እንዳረጋገጠ ሬፎርሚርቴ ፕሬሴ ላይ የወጣ ርዕስ ይገልጻል።

      አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ናዚዎች ያደረሱትን እልቂት አስመልክቶ እንዲህ በማለት በምሬት ተናግሯል፦ “ያን ሁሉ ውሸትና ጭካኔ እንዲሁም ውሎ አድሮ የተከተለውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በድፍረት የተቃወመ . . . አንድም ቡድን ወይም ድርጅት አልነበረም።” ይህ አስተማሪ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን የናዚ እልቂት ሰለባዎች ቤተ መዘክር ከጎበኘ በኋላ ግን “አሁን መልሱን አግኝቻለሁ” በማለት ጽፏል። መምህሩ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ ሥቃይ ቢደርስባቸውም በእምነታቸው ጸንተው እንደቆሙ ማወቅ ችሏል።

      የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚከተሉት የሥነ ምግባር ደንብስ ምን ማለት ይቻላል? “በዛሬው ጊዜ ካሉት ወጣት ካቶሊኮች መካከል አብዛኞቹ፣ ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖርን [እና] ሳይጋቡ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸምን በመሳሰሉት ጉዳዮች ረገድ ቤተ ክርስቲያኗ የምታስተምረውን ትምህርት አይቀበሉም” በማለት ዩ ኤስ ካቶሊክ የተሰኘው መጽሔት ይናገራል። አንድ የቤተ ክርስቲያን ዲያቆን “አብዛኞቹ ተጋቢዎች፣ ምናልባትም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት አብረው ሲኖሩ የቆዩ ናቸው” በማለት እንደተናገረ መጽሔቱ ይጠቅሳል። በሌላ በኩል ግን ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ እንደገለጸው የይሖዋ ምሥክሮች “በአኗኗራቸው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደንቦችን መከተል እንዳለባቸው ያምናሉ።”

  • ‘በመካከላችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’
    መጠበቂያ ግንብ—2012 | መጋቢት 1
    • ‘በመካከላችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’

      “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እየሰጠኋችሁ ነው፤ ልክ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”​—ዮሐንስ 13:34, 35

      ይህ ምን ማለት ነው? ክርስቶስ ልክ እሱ እንደወደዳቸው እነሱም እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። ኢየሱስ እነሱን የወደዳቸው እንዴት ነበር? ኢየሱስ በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ በተለየ መልኩ ሰዎችን በብሔር እና በፆታ ሳይለይ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ፍቅር አሳይቷል። (ዮሐንስ 4:7-10) ኢየሱስ ሌሎችን ለመርዳት ሲል ጊዜውን፣ ጉልበቱንና የግል ምቾቱን መሥዋዕት እንዲያደርግ የገፋፋው ፍቅር ነበር። (ማርቆስ 6:30-34) በመጨረሻም ክርስቶስ ከሁሉ በሚበልጠው መንገድ ፍቅሩን አሳይቷል። “እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ፤ ጥሩ እረኛ ነፍሱን ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ይሰጣል” በማለት ተናግሯል።​—ዮሐንስ 10:11

      የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ብቃት አሟልተዋል? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ‘ወንድም’ ወይም ‘እህት’ እየተባባሉ ይጠራሩ ነበር። (ፊልሞና 1, 2) ክርስቲያኖች “የሁሉም ጌታ አንድ ስለሆነ በአይሁዳዊና በግሪካዊ መካከል ምንም ልዩነት [እንደሌለ]” ያምኑ ነበር፤ በመሆኑም ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ተቀብለዋቸዋል። (ሮም 10:11, 12) በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ በኢየሩሳሌም የነበሩት ደቀ መዛሙርት “ያላቸውን ሀብትና ንብረት በመሸጥ ገንዘቡን ለእያንዳንዱ ሰው እንደሚያስፈልገው ያከፋፍሉ ነበር።” ይህን ያደረጉት ለምንድን ነው? በቅርብ የተጠመቁት ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ቆይተው “የሐዋርያትን ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን” መቀጠል እንዲችሉ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:41-45) ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ሐዋርያት ከሞቱ ወደ 200 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ተርቱሊያን ሌሎች ሰዎች ስለ ክርስቲያኖች የተናገሩትን ጠቅሶ ሲጽፍ “እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚዋደዱ፣ . . . አልፎ ተርፎም አንዳቸው ለሌላው ለመሞት ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑ ተመልከቱ” ብሎ ነበር።

      በዛሬው ጊዜ ብቃቱን የሚያሟሉት እነማን ናቸው? ዘ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዲክላይን ኤንድ ፎል ኦቭ ዘ ሮማን ኢምፓየር (1837) የተሰኘው መጽሐፍ እንደገለጸው ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚናገሩ ግለሰቦች “አንዳቸው በሌላው ላይ የፈጸሙት የጭካኔ ድርጊት የማያምኑ ሰዎች ካደረሱባቸው የከፋ ነው።” በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳሳየው ሃይማኖተኛ ሰዎች (አብዛኞቹ ክርስቲያን ነን ባዮች ናቸው) ብዙውን ጊዜ የዘር መድሎ ይፈጽማሉ። በአንድ አገር ያሉ ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ብዙውን ጊዜ በሌላ አገር ካሉ የራሳቸው ሃይማኖት አባላት ጋር ኅብረት ስለሌላቸው የእምነት አጋሮቻቸውን በችግራቸው ወቅት ለመርዳት አይችሉም ወይም ይህን ለማድረግ አይፈልጉም።

      በ2004 ፍሎሪዳ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በተከታታይ በአራት ኃይለኛ አውሎ ነፋሶች በተመታች ወቅት፣ የፍሎሪዳ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የእርዳታ አቅርቦታቸው በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ለማረጋገጥ ምርመራ አድርገው ነበር። እኚህ ሰው፣ የይሖዋ ምሥክሮችን ያህል በደንብ የተደራጀ ሌላ ቡድን እንዳላዩ የተናገሩ ሲሆን የሚያስፈልጋቸውን የእርዳታ አቅርቦት ለይሖዋ ምሥክሮች ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ከዚያ ቀደም ብሎ ይኸውም በ1997 በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች የእርዳታ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውንና ሌሎችንም የተቸገሩ ሰዎች ለመርዳት መድኃኒት፣ ምግብና ልብስ ይዘው ወደዚያ ተጉዘው ነበር። እርዳታው የተገኘው በአውሮፓ ያሉ የእምነት አጋሮቻቸው በድምሩ አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የእርዳታ አቅርቦት በኮንጎ ላሉት ወንድሞቻቸው በመለገሳቸው ነው።

  • ‘ስምህን አሳውቄአለሁ’
    መጠበቂያ ግንብ—2012 | መጋቢት 1
    • ‘ስምህን አሳውቄአለሁ’

      “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። . . . ስምህን ለእነሱ አሳውቄአለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።”​—ዮሐንስ 17:6, 26

      ይህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ በአገልግሎቱ ላይ የአምላክን ስም በመጠቀም ይህ ስም እንዲታወቅ አድርጓል። ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ያደርገው እንደነበረው ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በሚያነብበት ጊዜ የአምላክን የግል ስም ይጠራ ነበር። (ሉቃስ 4:16-21) ተከታዮቹም “አባት ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯል።​—ሉቃስ 11:2

      የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ብቃት አሟልተዋል? ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ አምላክ ከብሔራት መካከል “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን” እንደወሰደ በኢየሩሳሌም ለነበሩት ሽማግሌዎች ነግሯቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 15:14) ሐዋርያትም ሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖች “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” እያሉ ሰብከዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:21፤ ሮም 10:13) በተጨማሪም እነሱ በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ መለኮታዊውን ስም ተጠቅመዋል። የአይሁዳውያንን ሕጎች አሰባስቦ የያዘውና በ300 ዓ.ም. ገደማ የተጠናቀቀው ዘ ቶሴፍታ የተባለው መጽሐፍ፣ ተቃዋሚዎች ስላቃጠሏቸው የክርስቲያን ጽሑፎች እንደሚከተለው ብሏል፦ “የወንጌላውያንንና የሚኒምን [አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እንደሆኑ ይታመናል] መጻሕፍት ከእሳት መታደግ አልተቻለም። መጻሕፍቱን በተገኙበት ቦታ ሁሉ . . . በውስጣቸው ከሰፈረው መለኮታዊ ስም ጋር አቃጥለዋቸው ነበር።”

      በዛሬው ጊዜ ብቃቱን የሚያሟሉት እነማን ናቸው? በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ብሔራዊ ምክር ቤት ፈቃድ የተዘጋጀው ዘ ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ባይብል የተሰኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በመቅድሙ ላይ እንዲህ ይላል፦ “ከአንዱና ብቸኛ ከሆነው አምላክ መለየት የሚኖርባቸው ሌሎች አማልክት ያሉ ይመስል እርሱን በተጸውኦ ስም መጥራት ከክርስትና ዘመን በፊት በአይሁዳውያን ሃይማኖት ውስጥ የቀረ ነገር ነው፤ ለዓለም አቀፉ የክርስትና እምነትም አምላክን በተጸውኦ ስም መጥራት ተገቢ አይደለም።” በመሆኑም ይህ ትርጉም መለኮታዊውን ስም “ጌታ” በሚለው የማዕረግ ስም ተክቶታል። በቅርቡ ደግሞ ቫቲካን “በመዝሙሮችም ሆነ በጸሎቶች ላይ፣ በአራት የዕብራይስጥ ፊደላት የሚወከለውን የሐወሐa የሚለውን የአምላክን ስም መጠቀምም ሆነ መጥራት አይገባም” የሚል መመሪያ ለጳጳሶቿ አስተላልፋለች።

      በዛሬው ጊዜ የአምላክን የግል ስም የሚጠቀሙትና የሚያሳውቁት እነማን ናቸው? ሰርጌይ በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን የሚገልጽ ፊልም ኪርጊስታን ውስጥ ተመልክቶ ነበር። ከዚያ በኋላ አሥር ለሚያህሉ ዓመታት መለኮታዊውን ስም ማንም ሲጠራው አልሰማም። ከጊዜ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ መኖር የጀመረ ሲሆን በአንድ ወቅት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤቱ መጥተው የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩት። ሰርጌይ ይሖዋ በሚለው የአምላክ ስም የሚጠቀም ሃይማኖታዊ ቡድን በማግኘቱ በደስታ ፈነደቀ። የሚገርመው ዌብስተርስ ሰርድ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ “ጀሆቫ ጎድ” (ይሖዋ አምላክ) የሚለውን ሐረግ “ከሁሉ በላይ የሆነና የይሖዋ ምሥክሮች የሚያመልኩት ብቸኛ አምላክ” ብሎ ፈትቶታል።

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a በአማርኛ መለኮታዊው ስም አብዛኛውን ጊዜ የሚጻፈው “ይሖዋ” ተብሎ ነው።

  • ‘ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ይሰበካል’
    መጠበቂያ ግንብ—2012 | መጋቢት 1
    • ‘ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ይሰበካል’

      “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”​—ማቴዎስ 24:14

      ይህ ምን ማለት ነው? የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ይጓዝ ነበር” ብሏል። (ሉቃስ 8:1) ኢየሱስ ራሱም “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 4:43) ምሥራቹን በከተሞችና በመንደሮች እንዲሰብኩ ደቀ መዛሙርቱን የላካቸው ሲሆን ቆየት ብሎም “እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል።​—የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ ሉቃስ 10:1

      የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ብቃት አሟልተዋል? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እሱ የነገራቸውን ለመፈጸም ጊዜ አልወሰደባቸውም። “በየቀኑ በቤተ መቅደስም ሆነ ከቤት ወደ ቤት ስለ ክርስቶስ . . . የሚናገረውን ምሥራች ያለማሰለስ ማስተማራቸውንና ማወጃቸውን ቀጠሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 5:42) መስበክ ልዩ ቦታ ላላቸው የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተሰጠ ሥራ አልነበረም። የታሪክ ምሁር የሆነው ኒያንደር እንደሚከተለው ብሏል፦ “ክርስትናን በመቃወም የጻፈው የመጀመሪያ ሰው ይኸውም ሴልሰስ ሸማኔዎች፣ ጫማ ሠሪዎች፣ ቆዳ ፋቂዎች፣ ያልተማሩና ተራ የሆኑ ሰዎች ቀናተኛ የወንጌሉ ሰባኪዎች በመሆናቸው አፊዟል።” ዣን በርናርዲ የቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ታሪክ (እንግሊዝኛ) በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “[ክርስቲያኖች] በየቦታው እየሄዱ ላገኙት ሰው ሁሉ መናገር ነበረባቸው። በአውራ ጎዳናዎችና በከተሞች፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው አደባባዮችና በየቤቱ እየሄዱ ለሚያገኟቸው ሰዎች ሁሉ መናገር ነበረባቸው። ተቀባይነት ቢያገኙም ባያገኙም . . . እስከ ምድር ጫፍ ድረስ መስበክ ነበረባቸው።”

      በዛሬው ጊዜ ብቃቱን የሚያሟሉት እነማን ናቸው? የአንግሊካን ቄስ የሆኑት ዴቪድ ዋትሰን “በዛሬው ጊዜ በሰፊው ለሚታየው የመንፈሳዊ ፍላጎት መጥፋት አንዱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን መስበክና ማስተማርን በቁም ነገር አለመፈጸሟ ነው” በማለት ጽፈዋል። ሆሴ ሉዊስ ፔሬስ ጉዋዳሉፔ ካቶሊኮች ቤተ ክርስቲያኗን እየተዉ ያሉት ለምንድን ነው? (እንግሊዝኛ) በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ኢቫንጀሊካሎች፣ አድቬንቲስቶችና ሌሎች ሃይማኖቶችም ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሲጽፉ “ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ አይሰብኩም” ብለዋል። የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ግን “ሥርዓት ባለው መንገድ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ይሰብካሉ” በማለት ጽፈዋል።

      ካቶ ሱፕሪም ኮርት ሪቪው 2001-2002 በሚለው ጽሑፍ ላይ ጆናታን ተርሌ የሰጡት በእውነታ ላይ የተመሠረተ አስተያየት ትኩረት የሚስብ ነው፤ እንዲህ ብለዋል፦ “ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብታነሱ አብዛኞቹ ሰዎች ወዲያውኑ ወደ አእምሯቸው የሚመጡት በአጉል ሰዓት ቤታችንን የሚያንኳኩት ሰባኪዎች ናቸው። ለይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ፣ እምነታቸውን ለማራመድ ሲሉ ብቻ የሚያደርጉት ሳይሆን ለእምነታቸው አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው።”

      [በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ምልክቶቹን አስተዋልካቸው?

      እስከ አሁን ባየናቸው ተከታታይ ርዕሶች ላይ ከተወያየንባቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች አንጻር በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች እነማን ይመስሉሃል? ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ቢኖሩም ኢየሱስ ለተከታዮቹ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል፦ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ነው።” (ማቴዎስ 7:21) የአብን ፈቃድ እያደረጉ ያሉትን ይኸውም የእውነተኛውን ክርስትና ምልክቶች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያሳዩትን ክርስቲያኖች ለይቶ ማወቅና ከእነሱ ጋር መተባበር በአምላክ መንግሥት ሥር ዘላለማዊ በረከቶችን ለማግኘት ያበቃል። ይህን መጽሔት ያመጡልህን የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡህ እንድትጠይቃቸው እናበረታታሃለን።​—ሉቃስ 4:43

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ