-
ተስፋችን መቅረቡን የሚያመለክቱ ችግሮችመጠበቂያ ግንብ—2011 | ግንቦት 1
-
-
ተስፋችን መቅረቡን የሚያመለክቱ ችግሮች
“በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን [ይመጣል]።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1
ከሚከተሉት አሳዛኝ ክስተቶች ውስጥ ቢያንስ ስለ አንዱ ሰምተህ አሊያም በገዛ ዓይንህ ተመልክተህ ታውቃለህ?
● አንድ ቀሳፊ በሽታ የብዙዎችን ሕይወት ቀጠፈ።
● በአንድ ቦታ የተከሰተ ረሃብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ዳረገ።
● በአንድ አገር የደረሰ የመሬት ነውጥ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲገድል ብዙዎችን ቤት አልባ አደረገ።
ስለ ዓለም ሁኔታ ቆም ብለህ እንድታስብ የሚያደርጉህ እነዚህን ስለመሰሉ ክስተቶች የሚናገሩ አንዳንድ እውነታዎች በቀጣዮቹ ገጾች ላይ ቀርበውልሃል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ እነዚህ ነገሮች እንደሚከሰቱ አስቀድሞ ትንቢት እንደተናገረ ትመለከታለህ።a
የእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ዓላማ በችግር በተሞላ ዓለም ውስጥ እንደምንኖር አንተን ማሳመን አይደለም። ችግሮቹን በገዛ ዓይንህ አይተህ ሊሆን ስለሚችል ይህን ለአንተ መንገር ለቀባሪው አረዱት ማለት ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ርዕሶቹ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩሕ ተስፋ እንዲኖርህ ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ከመሆኑም ሌላ ስድስቱ ትንቢቶች ፍጻሜ ማግኘታቸው “መጨረሻዎቹ ቀኖች” የሚደመደሙበት ጊዜ መቅረቡን የሚያመለክት እንደሆነ ያሳያሉ። በተጨማሪም በቀረቡት ማስረጃዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚሰነዘሩ አንዳንድ የተቃውሞ ሐሳቦችን የሚያቀርቡ ሲሆን በቅርቡ የተሻለ ነገር የሚመጣ መሆኑን እንድናምን የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያትም ይሰጡናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አምላክ እነዚህ መጥፎ ሁኔታዎች እንዲከሰቱ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ለማወቅ በዚህ እትም ከገጽ 16-17 ላይ የሚገኘውን “አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
-
-
ትንቢት 1. የምድር ነውጦችመጠበቂያ ግንብ—2011 | ግንቦት 1
-
-
ትንቢት 1. የምድር ነውጦች
“ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ።”—ሉቃስ 21:11
● ሄይቲ ውስጥ ዊኒ የተባለች የዓመት ከአራት ወር ሕፃን ከተቀበረችበት ፍርስራሽ ወጣች። ስለ አደጋው ሲዘግብ የነበረ አንድ የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ቡድን ዊኒ ስታቃስት ሰማ። በመሆኑም ሕፃኗ በሕይወት ስትተርፍ ወላጆቿ ግን በደረሰው የምድር ነውጥ ሳቢያ ሞቱ።
እውነታው ምን ያሳያል? ጥር 2010 ላይ ሄይቲ በሬክተር መለኪያ 7.0 በደረሰ ርዕደ መሬት ስትመታ ከ300,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በተጨማሪም 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቅጽበት ቤት አልባ ሆነዋል። በሄይቲ የደረሰው ነውጥ ከፍተኛ ቢሆንም እንዲህ ያለ ከባድ ነውጥ በምድራችን ላይ ሲከሰት ይህ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው አይደለም። ከሚያዝያ 2009 እስከ ሚያዝያ 2010 ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 18 ከባባድ የምድር ነውጦች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተከስተዋል።
በተደጋጋሚ የሚሰነዘረው የተቃውሞ ሐሳብ ምንድን ነው? ድሮ ከኖሩት ሰዎች በበለጠ ዘመናዊው ቴክኖሎጂ የተከሰቱትን ነውጦች ብዛት እንድናውቅ ስላደረገን ነው እንጂ የሚከሰቱት የመሬት ነውጦች ቁጥር ጨምሮ አይደለም።
ይህ የተቃውሞ ሐሳብ ትክክል ነው? የሚከተለውን እውነታ ልብ በል፦ መጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት ያደረገው በመጨረሻዎቹ ቀናት በሚከሰቱት የምድር ነውጦች ብዛት ላይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው “ታላላቅ የምድር ነውጦች” “በተለያየ ስፍራ” እንደሚከሰቱ ነው፤ ይህ ደግሞ የምንኖረው ወሳኝ በሆነ የታሪክ ወቅት ላይ መሆኑን ለይተው ከሚያሳውቁን ነገሮች አንዱ ነው።—ማርቆስ 13:8፤ ሉቃስ 21:11
ምን ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ታላላቅ የምድር ነውጦች እየተከሰቱ እንደሆነ ይሰማሃል?
የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የመሬት ነውጦች ብቻቸውን በቂ ማስረጃ ሆነው ላይታዩህ ይችላሉ። የመሬት ነውጥ በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ ካሉት ትንቢቶች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው። እስቲ ሁለተኛውን ትንቢት እንመልከት።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“እኛ የሥነ ምድር ፊዚክስ ባለሙያዎች [ርዕደ መሬቶቹን] ታላላቅ የምድር ነውጦች እንላቸዋለን። ሌሎች ሰዎች ደግሞ አሰቃቂ ክስተቶች ይሏቸዋል።”—ኬን ሃድነት፣ የዩ ኤስ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© William Daniels/Panos Pictures
-
-
ትንቢት 2. ረሃብመጠበቂያ ግንብ—2011 | ግንቦት 1
-
-
ትንቢት 2. ረሃብ
“የምግብ እጥረት ይከሰታል።”—ማርቆስ 13:8
● አንድ ሰው ሕይወቱን ለማቆየት ሲል በኒጀር ወደምትገኘው ወደ ኩዋራተጂ መንደር ተሰደደ። የቅርብ ዘመዶቹን ጨምሮ ወንድሞቹና እህቶቹ ከረሃብ ለመሸሽ ሲሉ ርቆ ከሚገኝ የአገሪቱ ክፍል ወደዚህ መንደር መጥተዋል። ሆኖም ይህ ሰው መሬት ላይ አንጥፎ ብቻውን ተኝቷል። ለመሆኑ ከዘመዶቹ ተነጥሎ ብቻውን የሆነው ለምንድን ነው? “[ቤተሰቡን] መመገብ ስላልቻለ ዓይናቸውን ማየት ከብዶት ነው” በማለት ሲዲ የተባሉት የመንደሩ አለቃ ገልጸዋል።
እውነታው ምን ያሳያል? በመላው ዓለም ከ7 ሰዎች መካከል 1ዱ ለማለት ይቻላል በየቀኑ የሚበላው በቂ ምግብ አያገኝም። ከሰሃራ በታች ባለው የአፍሪካ ክፍል ደግሞ ሁኔታው የከፋ ነው፤ በእነዚህ አገራት ከ3 ሰዎች መካከል 1ዱ ለረዥም ጊዜ በረሃብ እየተሠቃየ እንደሚኖር ይታሰባል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት አባት፣ እናትና አንድ ልጅ ያሉበትን ቤተሰብ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ያላቸው ምግብ ለሁለት ሰው ብቻ የሚበቃ ከሆነ ወላጆቹ በቅድሚያ ልጃቸው በልቶ እንዲያድር ያደርጉ ይሆናል፤ ጥያቄው ግን ከሁለቱ ጦሙን የሚያድረው ማን ነው የሚለው ነው። አባትየው ወይስ እናትየው? እንዲህ ያሉ ቤተሰቦች በየዕለቱ ይህን የመሰለ ምርጫ ለማድረግ ይገደዳሉ።
በተደጋጋሚ የሚሰነዘረው የተቃውሞ ሐሳብ ምንድን ነው? ምድር ለሁሉም ሰው የሚሆን ከበቂ በላይ የሆነ ምግብ ታመርታለች። የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር የምድርን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ብቻ ነው።
ይህ የተቃውሞ ሐሳብ ትክክል ነው? በእርግጥ ገበሬዎች በታሪክ ውስጥ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብዙ ምግብ ማምረትና ምርታቸውን ወደ ተለያዩ ቦታዎች ማጓጓዝ ችለዋል። በመሠረቱ ሰብዓዊ መንግሥታት ረሃብን ለማስቀረት የምድርን የምግብ አቅርቦት በተሳካ መንገድ ማስተዳደር መቻል ነበረባቸው። ሆኖም ለብዙ አሥርተ ዓመታት ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ምን ይመስልሃል? ማርቆስ 13:8 በመፈጸም ላይ እንደሆነ ይሰማሃል? ቴክኖሎጂ ከፍተኛ እመርታ ቢያሳይም የምግብ እጥረት አሁንም የሰው ልጆችን እያሠቃየ ያለ ዓለም አቀፋዊ ችግር እንደሆነ ይሰማሃል?
ብዙ ጊዜ የምድር ነውጥንና ረሃብን ተከትሎ የሚመጣ አንድ ችግር ያለ ሲሆን ይህም የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክት ሌላ ገጽታ ነው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በሳንባ ምች፣ በተቅማጥና በሌሎች በሽታዎች ከሚሞቱት ሕፃናት መካከል ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት በቂ ምግብ ቢያገኙ ኖሮ ሕይወታቸው ሊተርፍ ይችል ነበር።”—አን ቬነመን፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት የቀድሞ ዳይሬክተር
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Paul Lowe/Panos Pictures
-
-
ትንቢት 3. በሽታመጠበቂያ ግንብ—2011 | ግንቦት 1
-
-
ትንቢት 3. በሽታ
“ሰዎች . . . አስከፊ በሆኑ በሽታዎች ይሠቃያሉ።”—ሉቃስ 21:11 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን
● በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመስ አንዲት የአፍሪካ አገር ውስጥ የጤና መኮንን ሆኖ የሚሠራው ቦንዛሊ፣ ማርበርግ በተባለ ቫይረስ እያለቁ ያሉትንና እሱ ባለበት ከተማ የሚኖሩትን የማዕድን ሠራተኞች ለመታደግ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እያደረገ ነው።a እርዳታ ለማግኘት በአንድ ትልቅ ከተማ ላሉ ባለሥልጣናት አቤት ቢልም መልስ ሳያገኝ ቀረ። በስተመጨረሻ ከአራት ወራት በኋላ ጥያቄው ምላሽ ቢያገኝም ቦንዛሊ ግን ሕይወቱ አልፎ ነበር። ማርበርግ የያዛቸውን የማዕድን ሠራተኞች ለማዳን በሚያደርገው ጥረት በሽታው ተጋብቶበት ነበር።
እውነታው ምን ያሳያል? በሰው ዘር ላይ እልቂት እያስከተሉ ካሉት በሽታዎች መካከል በታችኛው የመተንፈሻ አካላት ላይ የሚያጋጥሙ እንደ ሳንባ ምች ያሉ በሽታዎች፣ የተቅማጥ በሽታ፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ ሳንባ ነቀርሳና ወባ ይገኙባቸዋል። በቅርቡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ እነዚህ አምስት ዓይነት በሽታዎች 10.7 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። ስሌቱን በሌላ መንገድ ስናስቀምጠው እነዚህ በሽታዎች ዓመቱን ሙሉ ያለማቋረጥ በየሦስት ሴኮንዱ የአንድ ሰው ሕይወት ቀጥፈዋል ማለት ይቻላል።
በተደጋጋሚ የሚሰነዘረው የተቃውሞ ሐሳብ ምንድን ነው? የዓለም ሕዝብ ብዛት እየጨመረ በመጣ ቁጥር በበሽታ የሚያዙትም ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። ገና ብዙ ሰዎች ይታመማሉ።
ይህ የተቃውሞ ሐሳብ ትክክል ነው? የዓለም ሕዝብ ብዛት በአስደንጋጭ ፍጥነት ጨምሯል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በሽታን በምርመራ ለይቶ የማወቅ፣ የመቆጣጠርና የማከም ችሎታውም የዚያኑ ያህል አድጓል። ታዲያ እንዲህ ከሆነ በሽታ በሰው ዘር ላይ የሚያደርሰው ችግር እየቀነሰ መምጣት አልነበረበትም? ሁኔታው ግን የተገላቢጦሽ ነው።
ምን ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ሰዎች አስከፊ በሆኑ በሽታዎች እየተሠቃዩ እንዳሉ ይሰማሃል?
በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጥፋት የሚያደርሱት የምድር ነውጦች፣ ረሃብና በሽታ እንደ ሰው ሊወቀሱ አይችሉም። ሌሎች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ግን በመሰሎቻቸው መከራና ሥቃይ ይደርስባቸዋል፤ በአብዛኞቹ ላይ እንዲህ ያለ ጥቃት የሚያደርሱት አለኝታ ሊሆኗቸው የሚገቡ ሰዎች ናቸው። በዚህ ረገድ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የሚናገረውን ሐሳብ ልብ በል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ማርበርግ ሄመሬጂክ ፊቨር፣ ከኤቦላ ጋር በሚዛመድ ቫይረስ የሚመጣ በሽታ ነው።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በአንበሳ ወይም በሌላ አውሬ መበላት በጣም ዘግናኝ ነገር ነው፤ አስከፊ የሆነ በሽታ ውስጣችንን ሲበላውም ሆነ በዙሪያችን ያሉት ሰዎች እንዲህ ያለ ነገር ሲደርስባቸው መመልከቱም የዚያኑ ያህል እጅግ ዘግናኝ ነው።”—ኤፔዲሚዮሎጂስት፣ ሚካኤል ኦስተርሆልም
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© William Daniels/Panos Pictures
-
-
ትንቢት 4. የተፈጥሯዊ ፍቅር መጥፋትመጠበቂያ ግንብ—2011 | ግንቦት 1
-
-
ትንቢት 4. የተፈጥሯዊ ፍቅር መጥፋት
‘ሰዎች ለቤተሰባቸው ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው ይሆናሉ።’—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3 ጎድስ ዎርድ ባይብል
● ክሪስ የሚሠራው በቤት ውስጥ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች በሚረዳ በሰሜናዊ ዌልስ የሚገኝ አንድ ማኅበር ውስጥ ነው። “ከዚህ በፊት የማውቃት አንዲት ሴት ማንነቷን መለየት እስኪያቅተኝ ድረስ ክፉኛ ተደብድባ ስትመጣ ትዝ ይለኛል” በማለት ክሪስ ይናገራል። “ሌሎች ሴቶች ደግሞ ከፍተኛ የስሜት ጉዳት ስለደረሰባቸው ቀና ብለው ማየት እንኳ ይፈራሉ።”
እውነታው ምን ያሳያል? በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ ከ3 ሴቶች መካከል 1ዷ በልጅነቷ የፆታ ጥቃት እንደተፈጸመባት ይገመታል።በዚያች አገር የተካሄደ አንድ ጥናት ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ወንዶች ሚስቶቻቸውን መደብደብ ምንም እንደማይመስላቸው ደርሶበታል። ይሁንና በቤት ውስጥ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሴቶች ብቻ አይደሉም። ለምሳሌ በካናዳ ከ10 ወንዶች መካከል 3ቱ በትዳር ጓደኞቻቸው ተደብድበዋል ወይም ሌላ ዓይነት ጥቃት ደርሶባቸዋል።
በተደጋጋሚ የሚሰነዘረው የተቃውሞ ሐሳብ ምንድን ነው? በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት ምንጊዜም ያለ ነገር ነው። አሁን የበዛ የመሰለው ከቀድሞ የበለጠ ትኩረት ስለተሰጠው ብቻ ነው።
ይህ የተቃውሞ ሐሳብ ትክክል ነው? በቤት ውስጥ ለሚፈጸም ጥቃት የሚሰጠው ትኩረት ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ መጨመሩ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ለችግሩ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው መሆኑ በቤት ውስጥ የሚፈጸመው ጥቃት ቁጥሩ እየቀነሰ እንዲሄድ አድርጎታል? በጭራሽ አላደረገውም። እንዲያውም ከምንጊዜውም የበለጠ ተፈጥሯዊ ፍቅር እየጠፋ መጥቷል።
ምን ይመስልሃል? ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1-3 በመፈጸም ላይ እንደሆነ ይሰማሃል? ብዙ ሰዎች በተፈጥሮ ሊኖራቸው የሚገባውን ቤተሰባዊ ፍቅር እንዳጡ ይሰማሃል?
በአሁኑ ጊዜ ሲፈጸም እያየህ ያለኸው አምስተኛው ትንቢት መኖሪያችን የሆነችውን ምድርን የሚመለከት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን እንደሚል ልብ በል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት በማኅበረሰቡ ውስጥ በብዛት ይፋ ከማይወጡ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይታመናል። አንዲት ሴት ለፖሊስ ቀርባ ከማመልከቷ በፊት በትዳር ጓደኛዋ በአማካይ 35 ጊዜ ትደበደባለች።”—በዌልስ የሚገኘው የቤት ውስጥ ጥቃት ለደረሰባቸው በስልክ የምክር አገልግሎት የሚሰጠው ተቋም ቃል አቀባይ
-
-
ትንቢት 5. የምድር መበላሸትመጠበቂያ ግንብ—2011 | ግንቦት 1
-
-
ትንቢት 5. የምድር መበላሸት
‘አምላክ ምድርን እያጠፉ ያሉትን ያጠፋል።’—ራእይ 11:18
● በክፖር፣ ናይጄሪያ ውስጥ የሚኖረው ሚስተር ፒሪ ከዘንባባ የሚገኝ ወይን ጠጅ በማምረት ተግባር የተሰማራ ነው። በናይጀር ደለል ውስጥ በፈሰሰው ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ዘይት የተነሳ የሚስተር ፒሪ ሥራ ኪሳራ ደርሶበታል። “ነዳጅ ዘይቱ ዓሦቻችንን ፈጅቶብናል፤ ቆዳችንን አበላሽቶብናል፤ ጅረቶቻችንን በክሎብናል” በማለት ሚስተር ፒሪ ተናግሯል። “ሌላ ምንም መተዳደሪያ የለኝም።”
እውነታው ምን ያሳያል? አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ በየዓመቱ 6.5 ሚሊዮን ቶን ቆሻሻ ወደ ውቅያኖሶች ይገባል። ከዚህ ቆሻሻ ውስጥ 50 በመቶ ገደማ የሚሆነው ፕላስቲክ ሲሆን ፕላስቲክ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከመበስበሱ በፊት ለብዙ መቶ ዓመታት ተንሳፍፎ ሊቆይ ይችላል። ሰዎች ምድርን ከመበከላቸውም በተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብቷን አስደንጋጭ በሆነ ፍጥነት እየጨረሱት ነው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ምድራችን፣ ሰዎች በአንድ ዓመት ውስጥ የሚፈጁትን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ አንድ ዓመት ከአምስት ወር ይፈጅባታል። “የዓለም ሕዝብ ቁጥርና የተፈጥሮ ሀብት ፍጆታ እየጨመረ የመምጣቱ ሂደት በዚሁ ከቀጠለ በ2035 ከምድራችን ጋር የሚመጣጠኑ ሁለት ፕላኔቶች ያስፈልጉናል” በማለት ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ የተሰኘው የአውስትራሊያ ጋዜጣ ዘግቧል።
በተደጋጋሚ የሚሰነዘረው የተቃውሞ ሐሳብ ምንድን ነው? የሰው ልጆች ብልሃተኞች ስለሆኑ መላ አያጡም። አሁን ያሉትን ችግሮች ማስወገድና ምድርን መታደግ እንችላለን።
ይህ የተቃውሞ ሐሳብ ትክክል ነው? በግለሰብም ይሁን በቡድን ደረጃ ብዙዎች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰዎች ስለ አካባቢ መበከል ያላቸው ግንዛቤ ከፍ እንዲል አድርገዋል። ምድር ግን አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እየተበከለች ነው።
ምን ይመስልሃል? በቃሉ ላይ በሠፈረው ተስፋ መሠረት አምላክ ጣልቃ በመግባት ፕላኔታችንን ከጥፋት መታደጉ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል?
እስካሁን ከተመለከትናቸው አምስት ትንቢቶች በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ደስ የሚያሰኙ ክንውኖችም እንደሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮአል። በስድስተኛ ደረጃ የተገለጸውን ትንቢት እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ትንሿን ገነቴን ተቀምቼ መርዛማ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ እንደተረከብኩ ሆኖ ይሰማኛል።”—በዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ጠረፍ አካባቢ የሚኖሩት ኤሪን ታምበር የተባሉ ሴት በ2010 በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ላይ ነዳጅ ዘይት መፍሰሱ የፈጠረባቸውን ስጋት አስመልክተው የሰጡት አስተያየት
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተጠያቂው አምላክ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ የምናያቸውን መጥፎ ሁኔታዎች አስቀድሞ መተንበዩ አምላክን ተጠያቂ ያደርገዋል? መከራና ሥቃይ እንዲደርስብን የሚያደርገው እሱ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 11ን ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
U.S. Coast Guard photo
-
-
ትንቢት 6. ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራመጠበቂያ ግንብ—2011 | ግንቦት 1
-
-
ትንቢት 6. ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ
“ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር ይሰበካል።”—ማቴዎስ 24:14
● ቫየቲያ የምትኖረው ቱአሞቱ ተብለው ከሚጠሩት እጅብ ብለው የሚገኙ የፓስፊክ ደሴቶች መካከል በአንዷ ውስጥ ነው። ቱአሞቱ 802,900 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የተቀመጡ መሃላቸው ላይ ሐይቅ የሚገኝባቸው 80 ባለ ቀለበት ቅርጽ ደሴቶችን ያቀፈ ቢሆንም የሕዝቡ ብዛት 16,000 ብቻ ነው። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ቫየቲያ ወዳለችበት ደሴት በመሄድ እሷን እና የአካባቢዋን ሰዎች አነጋግረዋቸዋል። ለምን? ምክንያቱም የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች የሚኖሩት የትም ይሁን የት ያሉበት ቦታ ድረስ ሄደው ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች ሊያካፍሏቸው ስለሚፈልጉ ነው።
እውነታው ምን ያሳያል? የአምላክ መንግሥት መልእክት ወደ ሁሉም የምድር ማዕዘኖች እየደረሰ ነው። በ2010 ብቻ የይሖዋ ምሥክሮች በ236 አገሮች ምሥራቹን በማወጅ ከ1.6 ቢሊዮን በላይ ሰዓት አሳልፈዋል። ይህም ማለት እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር በየቀኑ በአማካይ 30 ደቂቃ በስብከቱ ሥራ ላይ አሳልፏል ማለት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር የሚረዱ ከ20 ቢሊዮን የሚበልጡ ጽሑፎችን በማተም አሰራጭተዋል።
በተደጋጋሚ የሚሰነዘረው የተቃውሞ ሐሳብ ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲሰበክ ኖሯል።
ይህ የተቃውሞ ሐሳብ ትክክል ነው? እውነት ነው፣ ብዙ ሰዎች መልእክቱ ምንም ይሁን ምን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሰብከዋል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ይህን ያደረጉት አጭር ለሆነ ጊዜና ውስን በሆኑ አካባቢዎች ነው። በአንጻሩ ግን የይሖዋ ምሥክሮች በተደራጀ መልክ ዓለም አቀፍ የስብከት ዘመቻ እያካሄዱ ሲሆን መልእክቱንም በብዙ መቶ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ማዳረስ ችለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ ኃያልና ጨካኝ ከሆኑት ድርጅቶች ከባድ ተቃውሞ እየደረሰባቸውም እንኳ በስብከቱ ሥራ በጽናት ቀጥለዋል።a (ማርቆስ 13:13) ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት ተከፍሏቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጊዜያቸውን በፈቃደኝነት ይሰጣሉ እንዲሁም ሰዎች ጽሑፎቻቸውን እንዲወስዱ የሚጋብዙት በነፃ ነው። ሥራቸው ሙሉ በሙሉ የሚካሄደው በፈቃደኝነት በሚደረጉ ወዋጮዎች ነው።
ምን ይመስልሃል? “የመንግሥቱ ምሥራች” በመላው ዓለም እየተሰበከ እንደሆነ ይሰማሃል? የዚህ ትንቢት መፈጸም በቅርቡ አንድ የተሻለ ነገር እንደሚመጣ የሚጠቁም ይሆን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሰራጯቸውን “ፌይዝፉል አንደር ትራያልስ፣” “ፐርፕል ትራያንግልስ” እና “ጀሆቫስ ዊትነስስ ስታንድ ፈርም ኧጌንስት ናዚ ኧሶልት” የተባሉትን ሦስት የቪዲዮ ፊልሞች ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ይሖዋ እስከፈቀደው ጊዜ ድረስ . . . ሰዎችን አግኝተን ለማነጋገር የሚያስችሉንን ዘዴዎች ሁሉ በመጠቀም የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት መስበካችንን እንቀጥላለን።”—የ2010 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ)
-
-
በቅርቡ የተሻለ ጊዜ ይመጣል!መጠበቂያ ግንብ—2011 | ግንቦት 1
-
-
በቅርቡ የተሻለ ጊዜ ይመጣል!
“ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:10, 11
ከላይ የተጠቀሰው ትንቢት ቢፈጸም ደስ ይልሃል? ደስ እንደሚልህ ጥርጥር የለውም። ይህ ተስፋ በቅርቡ እንደሚፈጸም ለማመን የሚያስችሉ ጠንካራ ምክንያቶች አሉ።
የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ መሆኑን በግልጽ የሚጠቁሙ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ከዚህ በፊት ባሉት ርዕሶች ላይ ተመልክተናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አምላክ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በመንፈሱ በመምራት እነዚህን ትንቢቶች እንዲናገሩ ያደረገው ተስፋ እንዲኖረን ብሎ ነው። (ሮም 15:4) ትንቢቶቹ ተፈጸሙ ማለት ዛሬ እየደረሰብን ያለው መከራ የሚያከትምበት ጊዜ ቀርቧል ማለት ነው።
የመጨረሻዎቹ ቀኖች ካበቁ በኋላ ምን ይከሰታል? የአምላክ መንግሥት ሁሉንም የሰው ዘር ይገዛል። (ማቴዎስ 6:9, 10) በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የሚኖረውን ሁኔታ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተመልከት፦
● ረሃብ ጨርሶ አይኖርም። “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ።”—መዝሙር 72:16
● በሽታ ይወገዳል። “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24
● ምድር ትታደሳለች። “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፤ በረሓው ሐሤት ያደርጋል፤ ይፈካል፤ እንደ አደይም ያብባል።”—ኢሳይያስ 35:1
እነዚህ በቅርቡ ከሚፈጸሙት አጽናኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች በቅርቡ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ያህል እርግጠኞች እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲገልጹልህ ለምን አትጠይቃቸውም?
-