በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት እና የኋላ ታሪካቸው ጥናት
ጥናት ቁጥር 6—የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት
የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት እንዴት እንደተገለበጡ፤ በግሪክኛና በሌሎች ቋንቋዎች እንዴት ለዘመናችን እንደደረሱ፤ የዘመናችን ቅጂዎች አስተማማኝ ስለመሆናቸው።
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በጽሑፍ የሰፈረውን ‘የይሖዋን ቃል’ በዓለም ዙሪያ የሚያስተምሩና የሚያዘጋጁ ሰዎች ነበሩ። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ሲል የተናገረውን ቃል ለመፈጸም ተጣጥረዋል። (ኢሳ. 40:8፤ ሥራ 1:8) ኢየሱስ በተነበየው መሠረት የመጀመሪያዎቹ 120 ደቀ መዛሙርት ታላቅ ኃይል እንዲያገኙ ያስቻላቸውን መንፈስ ቅዱስ ተቀብለዋል። ይህ የሆነው በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነበር። ጴጥሮስ በዚያው ቀን የተሟላ ምሥክርነት በመስጠት አዲሱን የትምህርት ዘመቻ ከፍቷል። በውጤቱም ብዙዎች መልእክቱን ከልባቸው ከመቀበላቸውም በላይ 3,000 የሚያክሉ ሰዎች አዲስ ወደተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ ተጨምረዋል።—ሥራ 2:14-42
2 እነዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በታሪክ ዘመናት በሙሉ ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ ለስብከቱ ሥራ በመነሳሳታቸው ይህ የትምህርት ፕሮግራም በዘመኑ ይታወቁ በነበሩት የዓለም ማዕዘናት በሙሉ ተዳርሶ ነበር። (ቆላ. 1:23) አዎ፣ እነዚህ ለይሖዋ ያደሩ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት፣ ከከተማ ወደ ከተማና ከአገር ወደ አገር በእግራቸው እየተዘዋወሩ ‘የተሻለ ነገር እንደሚመጣ የሚገልጸውን ምሥራች’ በታላቅ ጉጉት አውጀዋል። (ሮም 10:15) ይህ ምሥራች ስለ ክርስቶስ የቤዛ ዝግጅት፣ ስለ ትንሣኤ ተስፋና ስለ መጪው የአምላክ መንግሥት የሚገልጽ ነበር። (1 ቆሮ. 15:1-3, 20-22, 50፤ ያዕ. 2:5) ገና ስላልታዩ ነገሮች እንዲህ በስፋት ለሰው ልጆች ምሥክርነት ተሰጥቶ አያውቅም። በዚህ ጊዜ በኢየሱስ ቤዛ አማካኝነት ይሖዋን ሉዓላዊ ጌታቸው አድርገው ለተቀበሉ በርካታ ሰዎች ‘እውነተኛዎቹ ነገሮች ባይታዩም እንኳ መኖራቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ’ የሆነው እምነት እንዳላቸው ማሳያ ሆኖላቸዋል።—ዕብ. 11:1፤ ሥራ 4:24፤ 1 ጢሞ. 1:14-17
3 እነዚህ ወንዶችና ሴቶች ክርስቲያን አገልጋዮች የተማሩ የአምላክ አገልጋዮች ነበሩ። ማንበብና መጻፍ ይችሉ ነበር። ቅዱሳን መጻሕፍትን የተማሩ ነበሩ። የዓለምን ሁኔታዎች የሚያውቁ ሰዎች ነበሩ። ወደተለያዩ ቦታዎች የመጓዝ ልማድ ነበራቸው። ምሥራቹን ለማሠራጨት የሚያደርጉትን ግስጋሴ ምንም ዓይነት ነገር እንዲያደናቅፍባቸው የማይፈቅዱ በመሆናቸው እንደ አንበጣ ያሉ ሰዎች ነበሩ። (ሥራ 2:7-11, 41፤ ኢዩ. 2:7-11, 25) በዚያ የመጀመሪያ መቶ ዘመን ዓ.ም. የነበሩ ክርስቲያኖች በዘመናችን ከሚኖሩ ሰዎች ጋር በበርካታ መንገዶች ተመሳሳይነት ላላቸው ሰዎች ምሥራቹን አድርሰዋል።
4 የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እድገት የሚያደርጉ ‘የሕይወት ቃል’ ሰባኪዎች እንደመሆናቸው መጠን ያገኟቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅልሎች በሙሉ በጥሩ ሁኔታ ተጠቅመዋል። (ፊልጵ. 2:15, 16፤ 2 ጢሞ. 4:13) ከእነሱም መካከል አራቱ ማለትም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ‘ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች’ በጽሑፍ አስፍረዋል። (ማር. 1:1፤ ማቴ. 1:1) እንደ ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ይሁዳ ያሉት አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ደግሞ በመንፈስ እየተመሩ መልእክቶችን ጽፈዋል። (2 ጴጥ. 3:15, 16) ሌሎች ደግሞ እነዚህን በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መልእክቶች ገልብጠው በቁጥር እየጨመሩ የመጡት ጉባኤዎች እየተለዋወጡ እንዲያነቧቸው ያደርጉ ነበር። (ቆላ. 4:16) ከዚህም ሌላ ‘በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች’ በአምላክ መንፈስ እየተመሩ መሠረተ ትምህርትን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን ያደርጉ ነበር። እነዚህ ውሳኔዎች ወደፊት ተግባራዊ እንዲሆኑ በጽሑፍ እንዲሰፍሩ ተደርጓል። ይህ ማዕከላዊ የበላይ አካል ተበታትነውና ተራርቀው ለሚገኙ ጉባኤዎች መመሪያ የያዙ ደብዳቤዎች ይልክ ነበር። (ሥራ 5:29-32፤ 15:2, 6, 22-29፤ 16:4) ለዚህም የራሱን የመላኪያ ዘዴ ማደራጀት ነበረበት።
5 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ቅዱሳን መጻሕፍት ለማመሳከር የሚመቹ እንዲሆኑ እንዲሁም ስርጭታቸውንም ለማቀላጠፍ ሲሉ ይገለገሉባቸው የነበሩትን የመጻሕፍት ጥቅልሎች፣ ኮዴክስ በተባሉት በጥራዝ መልክ በሚዘጋጁ መጻሕፍት ተክተዋል። ኮዴክስ የዘመናችንን መጽሐፍ የሚመስል ቅርጽ ስለነበረው አንድ ጥቅስ ለማመሳከር ሙሉ ጥቅልል ከመተርተር ይልቅ ገጾቹን በቀላሉ ማገላበጥ ያስችላል። ከዚህም በላይ ቅዱሳን መጻሕፍትን በተለያዩ ጥቅልሎች ለየብቻ ከማስቀመጥ ይልቅ በአንድ ጥራዝ ለማሰባሰብ አስችሏል። የጥንት ክርስቲያኖች ኮዴክስ በመጠቀም ረገድ ግንባር ቀደም ነበሩ። ምናልባትም የፈለሰፉት እነሱ ሳይሆኑ አይቀሩም። ክርስቲያን ያልሆኑ ጸሐፊዎች በኮዴክስ መጠቀም የጀመሩት ቆየት ብለው ቢሆንም አብዛኞቹ የሁለተኛውና የሦስተኛው መቶ ዘመን የክርስቲያኖች የፓፒረስ ጽሑፎች የተዘጋጁት በኮዴክስ መልክ ነበር።a
6 የኮይኔ (የጋራ መግባቢያ ቋንቋ የነበረው ግሪክኛ) ሚና። የግሪክኛ ቋንቋ ክላሲካል ዘመን የቆየው ከዘጠነኛው እስከ አራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ድረስ ነበር። ይህ ዘመን የአቲክ እና የአዮኒክ ቀበሌኛዎች በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉበት ዘመን ከመሆኑም ሌላ በርካታ ግሪካውያን ጸሐፌ ተውኔቶች፣ ባለቅኔዎች፣ ዲስኩረኞች፣ ታሪክ ፀሐፊዎች፣ ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች የተነሱበት ነበር። ከእነሱም መካከል እንደ ሆሜር፣ ሄሮዶተስ፣ ሶቅራጠስ፣ ፕላቶና ሌሎች እውቅ ሰዎች ከፍተኛ ዝና ያተረፉት በዚህ ዘመን፣ በተለይም በአምስተኛውና በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነበር። ከአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እስከ ስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ያለው ጊዜ የኮይኔ ወይም የጋራ መግባቢያ ቋንቋ የሆነው ግሪክኛ ዘመን ነበር። ይህ የግሪክኛ ዘይቤ የተፈጠረው በአብዛኛው በታላቁ እስክንድር የጦር እንቅስቃሴ ምክንያት ሲሆን ሠራዊቱ ከመላው የግሪክ ግዛት የተሰባሰቡ ወታደሮችን ያቀፈ ነበር። እነዚህ ወታደሮች የተለያየ የግሪክኛ ቀበሌኛ ይናገሩ ስለነበር አንድ ላይ ሲቀላቀሉ ኮይኔ የተባለው የጋራ ቀበሌኛ የተፈጠረ ከመሆኑም ሌላ በሰፊው ይሠራበትም ጀመር። እስክንድር ግብፅንና እስያን እስከ ሕንድ ድረስ በመውረሩ ምክንያት ኮይኔ ወደ በርካታ ሕዝቦች ስለተሰራጨ ከዚያን ዘመን አንስቶ ለበርካታ መቶ ዓመታት ዓለም አቀፍ ቋንቋ ሆኖ ቆየ። የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም የተጠቀመበት ግሪክኛ በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. በግብፅ፣ እስክንድርያ ይሠራበት የነበረው ኮይኔ ነው።
7 በኢየሱስና በሐዋርያት ዘመን ኮይኔ በመላው የሮም ግዛት የሚሠራበት ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ይህንን ያረጋግጣል። ኢየሱስ በእንጨት ላይ በተቸነከረ ጊዜ በአናቱ ላይ የተለጠፈውን ጽሑፍ የአይሁድ ቋንቋ በነበረው በዕብራይስጥ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ መንግሥታዊ ቋንቋ በነበረው በላቲን እንዲሁም ከሮም፣ ከእስክንድርያና ከአቴና ባልተናነሰ ሁኔታ በኢየሩሳሌም አደባባዮች ይነገር በነበረው በግሪክኛ መጻፍ አስፈላጊ ሆኖ ነበር። (ዮሐ. 19:19, 20፤ ሥራ 6:1) ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ግሪክኛ ለሚናገሩ አይሁድ ምሥራቹን እንደሰበከ የሐዋርያት ሥራ 9:29 ያመለክታል። በዚያ ዘመን ኮይኔ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ፣ ሕያውና በሚገባ የተደራጀ ቋንቋ ስለነበር ክቡር ለሆነው መለኮታዊውን ቃል የማሠራጨት ሥራ ብቁና አመቺ ቋንቋ ለመሆን በቅቷል።
የግሪክኛ ግልባጮችና ጽሑፎቹ ከዘመን ወደ ዘመን የተላለፉባቸው መንገዶች
8 በጥናት 5 ላይ ይሖዋ የሕይወትን ውኃ በጽሑፍ በሰፈሩ ሰነዶች ባሕር ውስጥ ማለትም በመንፈስ መሪነት በተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንዳቆየ ተመልክተናል። ይሁንና ሐዋርያትና ሌሎች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስለጻፏቸው ቅዱሳን መጻሕፍትስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህንም ለእኛ ለማቆየት ተመሳሳይ ጥንቃቄ ተደርጓል? በግሪክኛና በሌሎች ቋንቋዎች ተገልብጠው የቆዩትን በጣም በርካታ ቅጂዎች ብንመረምር በከፍተኛ ጥንቃቄ ተጠብቀው እንደቆዩልን ማረጋገጥ እንችላለን። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል 27 መጻሕፍት የተካተቱበት እንደሆነ ቀደም ሲል ተገልጿል። እነዚህ 27 መጻሕፍት እንዴት እንደተላለፉ በመመልከት የመጀመሪያው ግሪክኛ ጽሑፍ እስከ ዘመናችን ድረስ በትክክል መተላለፉን እናረጋግጥ።
9 የግሪክኛ ግልባጮች። ሃያ ሰባቱ የክርስቲያን ቅዱሳን መጻሕፍት ቀኖናዊ መጻሕፍት የተጻፉት የዘመኑ መግባቢያ ቋንቋ በነበረው ግሪክኛ ነበር። የማቴዎስ መጽሐፍ ግን የአይሁድን ሕዝብ ለመጥቀም ሲባል በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥ ነበር። ጀሮም የተባለው የአራተኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ከጊዜ በኋላ በግሪክኛ እንደተተረጎመ መግለጹ ይህን ያረጋግጣል።b ማቴዎስ የሮም መንግሥት ሠራተኛ፣ ማለትም ቀረጥ ሰብሳቢ ስለነበር ዕብራይስጥ፣ ላቲንና ግሪክኛ እንደሚችል የታወቀ ነው። ስለሆነም መጽሐፉን የተረጎመው እሱ ራሱ መሆን አለበት።—ማር. 2:14-17
10 ሌሎቹ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የነበሩት ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ፣ ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ይሁዳ መልእክታቸውን የጻፉት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችና የአብዛኞቹ ሌሎች ሕዝቦች የዕለት ተዕለት መግባቢያ በነበረው በኮይኔ ነበር። የመጨረሻው መጽሐፍ የተጻፈው በ98 ዓ.ም. በዮሐንስ ነበር። እስካሁን እንደሚታወቀው ከእነዚህ 27 በኩረ ጽሑፎች መካከል አንዳቸውም ለዘመናችን አልደረሱም። ይሁን እንጂ የእነዚህ የዋናዎቹ ጽሑፎች ቅጂዎች፣ የቅጂ ቅጂዎችና በአንድ ቡድን የሚፈረጁ ቅጂዎች በብዛት ስላሉ በርካታ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ስብስብ ይገኛል።
11 ከአሥራ ሦስት ሺህ የሚበልጡ ግልባጮችን የያዘ ስብስብ። በዘመናችን የ27ቱ ቀኖናዊ መጻሕፍት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ግልባጮች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ሰፋ ያሉ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎችን የያዙ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ትናንሽ ቁርጥራጮች ናቸው። በአንድ ስሌት መሠረት በጥንቱ ግሪክኛ የተጻፉ ከ5,000 በላይ ግልባጮች ይገኛሉ። በተጨማሪም በሌሎች የተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ ከ8,000 በላይ ግልባጮች ስለሚገኙ በጠቅላላው ከ13,000 የሚበልጡ ግልባጮች አሉ። ከሁለተኛው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ 16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ የተዘጋጁት እነዚህ ግልባጮች የመጀመሪያውን ጽሑፍ ይዘት በትክክል እንድናውቅ ይረዱናል። ከእነዚህ በርካታ ግልባጮች መካከል በዕድሜ አንጋፋ የሆነው በማንቸስተር፣ እንግሊዝ ባለው የጆን ራይላንድስ ቤተ መጻሕፍት የሚገኘውና P52 በሚል ቁጥር የሚታወቀው የዮሐንስ ወንጌል የፓፒረስ ቁራጭ ሲሆን በሁለተኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ፣ ምናልባትም በ125 ዓ.ም. እንደተጻፈ ይታመናል።c ስለዚህ ይህ ቅጂ የተገለበጠው የመጀመሪያው ጽሑፍ ከተጻፈ ከ25 ዓመት ገደማ በኋላ ነበር ማለት ነው። የአብዛኞቹን የክላሲካል ዘመን ጸሐፊዎች መጻሕፍት ትክክለኛነት ለማረጋገጥ በጣት ከሚቆጠሩ ግልባጮች በላይ ልናገኝ እንደማንችልና እነዚህም ቢሆኑ ከመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት በጥቂት መቶ ዓመታት ልዩነት የተጻፉ መሆናቸውን ስንመለከት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ትክክለኛ ይዘት ለማወቅ የሚያስችሉን ማስረጃዎች ምን ያህል በርካታ እንደሆኑ መገንዘብ እንችላለን።
12 የፓፒረስ ግልባጮች። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የመጀመሪያ ግልባጮች፣ እንደ ቀደምቶቹ የሰብዓ ሊቃናት ግልባጮች ሁሉ የተጻፉት በፓፒረስ ላይ ሲሆን እስከ አራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ለመገልበጥ ያገለገለው ይኸው ፓፒረስ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ለክርስቲያን ጉባኤዎች ደብዳቤ በሚጽፉበት ጊዜም በፓፒረስ ይጠቀሙ እንደነበረ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል።
13 በግብጽ አገር ፋዩም በሚባል ክልል እጅግ በርካታ የሆኑ የፓፒረስ ጽሑፎች ተገኝተዋል። በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የፓፒረስ ጽሑፎች ተገኝተዋል። በዘመናችን ከሚገኙት ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው የጥንት ጽሑፎች ግኝቶች መካከል አንዱ በ1931 ለሕዝብ ይፋ የሆነው ግልባጭ ነው። ይህ ግኝት 11 ኮዴክሶች በከፊል የሚገኙበት ሲሆን 8 የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትና 15 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ተካትተውበታል። ሁሉም በግሪክኛ የተጻፉ ናቸው። እነዚህ የፓፒረስ መጻሕፍት የተጻፉት ከሁለተኛው መቶ ዘመን እስከ አራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። የዚህ ግኝት አብዛኞቹ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች በቼስተር ቢቲ ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን P45፣ P46 እና P47 የሚል ቁጥር ተሰጥቷቸዋል። “P” የሚያመለክተው “ፓፒረስ”ን ነው።
14 ሌላ በጣም አስደናቂ የሆነ የፓፒረስ ስብስብ ደግሞ ከ1956 እስከ 1961 በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ ለሕዝብ ይፋ ሆኗል። ቦድመር ፓፒራይ በመባል የሚታወቀው ይህ ስብስብ ከሦስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ የተዘጋጁ የሁለት ወንጌሎችን (P66 እና P75) ግልባጭ ይዟል። በጥናት 5 ሥር በሚገኘው ሠንጠረዥ ላይ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው አንዳንድ የዕብራይስጥና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የፓፒረስ ቅጂዎች ተዘርዝረዋል። በመጨረሻው አምድ ውስጥ አዲስ ዓለም ትርጉም ከሌሎች ትርጉሞች በተለየ ሁኔታ የተረጎማቸው ጥቅሶችና ለዚህም ማስረጃ የሚሆኑ የፓፒረስ ግልባጮች ሰፍረዋል። ይህም በጥቅሶቹ የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ ተመልክቷል።
15 የእነዚህ የፓፒረስ መጻሕፍት መገኘት 66ቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ቀደም ባሉ ዓመታት ተሟልተው የተጠናቀቁ መሆኑን ያመለክታል። ከቼስተር ቢቲ ፓፒራይ መካከል አንዱ የኮዴክስ ጥራዝ አራቱ ወንጌሎችና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በከፊል የሚገኙበት (P45) ሲሆን ሌላኛው ጥራዝ ደግሞ ከጳውሎስ 14 መልእክቶች ዘጠኙን ያካተተ (P46) ነው። እነዚህ ሁለት ጥራዞች በመንፈስ የተጻፉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ሐዋርያት በሙሉ ከሞቱ ብዙም ሳይቆይ ተሰባስበው መጠናቀቃቸውን ያመለክታሉ። እነዚህ የኮዴክስ ጥራዞች በዚያ አካባቢ በስፋት ተሰራጭተው ከዚያም ግብፅ እስኪደርሱ ድረስ ረዘም ያለ ጊዜ መፍጀቱ ስለማይቀር እነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት ተሰባስበው ቋሚ መልካቸውን የያዙት እጅግ ቢዘገይ በሁለተኛው መቶ ዘመን መሆን ይገባዋል። ስለዚህ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ብሎም የመላው መጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና የተጠናቀቀው በሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ እንደሆነ አያጠያይቅም።
16 የብራና ግልባጮች። ጥናት 5 ላይ እንደተመለከትነው ከአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ በፓፒረስ ምትክ ከጥጃ፣ ከበግ ወይም ከፍየል ቆዳ በሚሠራ ለረጅም ዘመን በሚቆይና ጥራት ባለው ብራና ላይ መጻፍ ተጀመረ። በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት በጣም ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ግልባጮች መካከል አንዳንዶቹ የተጻፉት በብራና ላይ ነው። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን የብራና ቅጂዎች ቀደም ስንል ተመልክተናል። በጥናት 5 ሥር በሚገኘው ሠንጠረዥ ላይ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው አንዳንድ የክርስቲያን ግሪክኛና የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የብራና ግልባጮች ተዘርዝረዋል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ሥር የተዘረዘሩት ሙሉ በሙሉ በትላልቅ ፊደላት የተጻፉ ሲሆን ኡንስያል ተብለው ይጠራሉ። ኒው ባይብል ዲክሽነሪ፣ 274 የሚያክሉ ኡንስያል የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች እንዳሉ ሲዘግብ እነዚህ በሙሉ ከአራተኛው መቶ ዘመን እስከ አሥረኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተጻፉ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ከ5,000 የሚበልጡ በትናንሽ (ሚኒስኪዩል) እና ቅጥልጥል ሆሄያት የተጻፉ ግልባጮች አሉ።d እነዚህም በብራና ላይ የተጻፉ ሲሆኑ ከዘጠነኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ የኅትመት ሥራ እስከተጀመረበት ጊዜ ድረስ የዘለቀ ዕድሜ ነበራቸው። የኡንስያል ግልባጮች በዕድሜያቸው ቀዳሚነት ያላቸውና በትክክለኛነታቸውም ይበልጥ አስተማማኝ በመሆናቸው ምክንያት የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ ከግሪክኛው ቅጂ ሲተረጉም በአብዛኛው የተጠቀመው በእነዚህ ግልባጮች ነው። ይህም “ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው አንዳንድ የብራና ጽሑፎች” በሚለው ሠንጠረዥ ውስጥ ተመልክቷል።
የጽሑፎች ትንታኔና የማጥራት ዘመን
17 የኢራስመስ ቅጂ። የላቲን ቋንቋ የበላይነቱን በያዘበትና ምዕራብ አውሮፓ በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የብረት መዳፍ ሥር በነበረበት ረጅም የጨለማ ዘመን ትምህርትና ምሁራዊ ሥራዎች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኙ ነበር። ይሁን እንጂ በ15ኛው መቶ ዘመን ተንቀሳቃሽ የማተሚያ መሣሪያ ከተፈለሰፈና በ16ኛው መቶ ዘመን የተሐድሶ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ወዲህ ከበፊቱ የበለጠ ነፃነት የተገኘ ከመሆኑም ሌላ ግሪክኛን የማወቅ ፍላጎት ተቀሰቀሰ። ዲሲድየስ ኢራስመስ የተባለው ዝነኛ የሆላንድ ምሁር “የአዲስ ኪዳን” እናት ቅጂ የመጀመሪያ እትሙን ያዘጋጀው በዚህ የተሐድሶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነበር። (እንዲህ ያለው እናት ቅጂ የሚዘጋጀው የተለያዩ ቅጂዎችን በጥንቃቄ ካነጻጸሩ በኋላ በአብዛኞቹ ቅጂዎች ተቀባይነት ያገኙትን የመጀመሪያዎቹን ቃላት ብቻ በመጠቀምና አብዛኛውን ጊዜም በአንዳንድ ቅጂዎች የሚገኙትን ለየት ያሉ አተረጓጎሞች ለብቻቸው በማሳየት ነው።) ይህ የመጀመሪያ እትም በ1516 በባዝል፣ ስዊዘርላንድ የታተመው በጀርመን አገር የተሐድሶ እንቅስቃሴ ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር። ይህ እትም በርካታ ግድፈቶች የተገኙበት ቢሆንም በ1519, በ1522, በ1527 እና በ1535 በተዘጋጁ ተከታታይ እትሞች የተስተካከሉ ቅጂዎች ወጥተዋል። ኢራስመስ እናት ቅጂውን ሲያዘጋጅ ለማመሳከሪያነት ያገኘው በቅጥልጥል ሆሄያት የተጻፉ ጥቂት ቅጂዎችን ብቻ ነበር።
18 የተጣራው የኢራስመስ የግሪክኛ ቅጂ በበርካታ የምዕራብ አውሮፓ ቋንቋዎች የተሻሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንዲዘጋጁ መሠረት ሆኖ አገልግሏል። ቀደም ሲል ከላቲን ቩልጌት ከተተረጎሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የበለጠ ጥራት ያላቸው ትርጉሞች እንዲገኙ አስችሏል። የኢራስመስን ቅጂ ለመጠቀም የመጀመሪያ ሰው የሆነው በ1522 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደ ጀርመንኛ ተርጉሞ የጨረሰው የጀርመኑ ማርቲን ሉተር ነው። እንግሊዛዊው ዊልያም ቲንደል ይወርድበት የነበረውን ከባድ ስደት ተቋቁሞ የኢራስመስን ቅጂ መሠረት በማድረግ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሞ የጨረሰው በ1525 በአውሮፓ አህጉር በስደት ሳለ ነበር። በ1530 ጣሊያናዊው አንቶኒዮ ብሩቾሊ የኢራስመስን ቅጂ ወደ ጣሊያንኛ ተርጉሟል። ከኢራስመስ የግሪክኛ ቅጂ ወዲህ የጽሑፎች ትንታኔ ዘመን ተጀመረ። የጽሑፎች ትንታኔ የሚባለው ምሁራን የበኩረ ጽሑፉን ቃል ለመመለስ የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው።
19 በምዕራፎችና በቁጥሮች መከፋፈል። ሮበርት ኤትየን ወይም ስቴፋነስ በ16ኛው መቶ ዘመን በፓሪስ እውቅ የሆነ አታሚና አርታኢ (ኤዲተር) ነበር። አርታኢ በመሆኑም በምዕራፎችና በቁጥሮች መከፋፈል ለማመሳከር የሚኖረውን አመቺነትና ተግባራዊ ጠቀሜታ ስለተገነዘበ በ1551 ራሱ ያዘጋጀውን የግሪክኛ-ላቲን አዲስ ኪዳን በምዕራፍና በቁጥር ከፋፈለ። ቀደም ብሎም ማሶሪታውያን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በቁጥር የከፋፈሏቸው ቢሆንም መላው መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ባለው መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፋፈለው በ1553ቱ የስቴፋነስ የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ከዚያ በመቀጠል የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ይህንኑ ሥርዓት መከተል የጀመሩ ከመሆኑም ሌላ ይህ አሠራር የመጽሐፍ ቅዱስ የጥቅስ ማውጫ ለማዘጋጀት አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል። በዚህ ረገድ በ1737 በአሌክሳንደር ክሩደን የተዘጋጀው የጥቅስ ማውጫም ሆነ በ1873 በሮበርት ያንግ ተዘጋጅቶ በመጀመሪያ በኤድንበርግ የታተመው በኋላ ደግሞ በ1894 በጀምስ ስትሮንግ ተዘጋጅቶ በኒው ዮርክ የታተመው የኦቶራይዝድ ቨርሽን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት የተሟሉ የጥቅስ ማውጫዎች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።
20 ቴክስቱስ ሪሰፕቱስ። በተጨማሪም ስቴፋነስ የተለያዩ የግሪክኛ “አዲስ ኪዳን” እትሞችን አውጥቷል። እነዚህ እትሞች በዋነኝነት መሠረት ያደረጉት የኢራስመስን ቅጂ ሲሆን በ1522ቱ የኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎትና 15 በሚያክሉ ቀደም ያሉት መቶ ዘመናት የቅጥልጥል ጽሑፍ ቅጂዎች ላይ የተመሠረቱ እርማቶችን አካትተዋል። የ1550ው የስቴፋነስ የግሪክኛ ሦስተኛ እትም ቴክስቱስ ሪሰፕቱስ (በላቲን “ተቀባይነት ያገኘ ጽሑፍ”) ለመሆን የበቃ ሲሆን ሌሎች የ16ኛው መቶ ዘመን እንግሊዝኛ ትርጉሞችና የ1611ዱ የኪንግ ጀምስ ትርጉም በዚያ ላይ ተመሥርተው የተሠሩ ናቸው።
21 የተጣሩ የግሪክኛ ግልባጮች። ቆየት ብሎም የግሪክኛ ቋንቋ ምሁራን ይበልጥ የተጣሩ ግልባጮችን አዘጋጅተዋል። ከእነዚህ መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው በ18ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የሚገኙትን በመቶ የሚቆጠሩ የግሪክኛ ግልባጮች የማመሳከር አጋጣሚ ያገኘው ጄ ጄ ግሪስባኽ ያዘጋጀው ነው። ከሁሉም የተሻለው የግሪስባኽ ሙሉው የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም ከ1796-1806 ባለው ጊዜ ታትሞ ወጣ። የ1840ው የሻርፕ እንግሊዝኛ ትርጉም መሠረት ያደረገው የእሱን እናት ጽሑፍ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በ1864 በታተመው ዚ ኢምፋቲክ ዲያግሎት ላይ የወጣው የግሪክኛ ጽሑፍም የእሱ ነው። ኮንስታንቲን ፎን ቲሸንዶርፍ (1872) እና ኸርማን ፎን ዞደን (1910) በጣም ግሩም የሆኑ ቅጂዎችን ያዘጋጁ ሲሆን የኋለኛው ቅጂ ለ1913ቱ የሞፋት የእንግሊዝኛ ትርጉም መሠረት ሆኗል።
22 የዌስትኮትና የሆርት ቅጂ። የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በነበሩት በቢ ኤፍ ዌስትኮትና በኤፍ ጄ ኤ ሆርት በ1881 የተዘጋጀው የግሪክኛ እናት ቅጂ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። ዌስትኮትና ሆርት በአባልነት የሚገኙበት የብሪታንያ አጣሪ ኮሚቴ የ1881ዱን “አዲስ ኪዳን” ትክክለኛነት በሚያጣራበት ጊዜ የዌስትኮትንና የሆርትን ቅጂ ትክክለኛነት መርምሯል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በእንግሊዝኛ በሚዘጋጅበት ጊዜ በዋነኝነት ያገለገለው ይህ እናት ቅጂ ነው። በተጨማሪም ይህ ቅጂ ለሚከተሉት የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መሠረት ሆኗል:- ዚ ኢምፋሳይዝድ ባይብል፣ አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን፣ አን አሜሪካን ትራንስሌሽን (ስሚዝ-ጉድስፒድ) እና ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርዥን።e መጨረሻ ላይ የተጠቀሰው ትርጉም የኔስልን ቅጂ በተጨማሪነት ተጠቅሟል።
23 የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴም የኔስልን የግሪክኛ ቅጂ (18ኛውን እትም፣ 1948) በማነጻጸሪያነት ተጠቅሟል። በተጨማሪም ኮሚቴው፣ ሆሴ ኤም ቦቨር (1943) እና አውገስቲነስ መርክ (1948) የተባሉት የካቶሊክ ጀስዊት ምሁራን ያዘጋጇቸውን ቅጂዎች አመሳክሯል። የ1984ቱን ባለማጣቀሻ እትም የግርጌ ማስታወሻዎች ወቅታዊ ለማድረግ የ1975ቱ የተባበሩት መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ቅጂና የኔስል-አላንድ የ1979 ቅጂ ለማነጻጸሪያነት አገልግለዋል።f
24 ከግሪክኛው የተወሰዱ የጥንት ትርጉሞች። በዛሬው ጊዜ ከግሪክኛ ግልባጮች በተጨማሪ ለጥናትና ለማመሳከሪያነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የተተረጎሙ በርካታ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉሞች አሉ። ከዚህም ሌላ ከ50 የሚበልጡ የጥንቱ የላቲን ትርጉም ግልባጮች (ወይም ቁርጥራጮች) እና በሺህ የሚቆጠሩ የጀሮም ላቲን ቩልጌት ግልባጮች ይገኛሉ። የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ እነዚህን ግልባጮችም ሆነ የኮፕት፣ የአርመንና የሲርያክ ትርጉሞችን አመሳክሯል።g
25 እጅግ ቢዘገይ ከ14ኛው መቶ ዘመን ወዲህ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በዕብራይስጥ ተተርጉመዋል። ከእነዚህ ትርጉሞች መካከል በርካታዎቹ መለኮታዊውን ስም በክርስቲያን ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በማስገባታቸው ትልቅ ግምት ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው። የአዲስ ዓለም ትርጉም “J” እና አናቱ ላይ በደቃቁ የተጻፈ ቁጥር በማሳየት በብዙ ቦታዎች ላይ እነዚህን የዕብራይስጥ ትርጉሞች ይጠቅሳል። ዝርዝሩን ለመረዳት በባለማጣቀሻው የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ገጽ 9-10 ላይ ያለውን መቅድምና በተጨማሪው ክፍል 1D ላይ የሚገኘውን “መለኮታዊው ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ” በሚለው ርዕስ ሥር የሰፈረውን ተመልከት።
የአጻጻፍ ልዩነቶችና ትርጉማቸው
26 ከአሥራ ሦስት ሺህ በሚበልጡት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ግልባጮች ውስጥ በርካታ የአጻጻፍ ልዩነቶች ይገኛሉ። አምስት ሺህ በሚያክሉት የግሪክኛ ግልባጮች ውስጥ እንኳ በርካታ ልዩነቶች አሉ። ከጥንቶቹ ግልባጮች የተቀዱት የጥንት ቅጂዎች የራሳቸው የሆነ የአጻጻፍ ስህተት ሊኖራቸው እንደሚችል መረዳት ከባድ አይሆንም። ከእነኚህ ጥንታዊ ግልባጮች መካከል አንዱ ወደ አንድ አካባቢ ሲላክ ስህተቶቹ በዚያ አካባቢ በሚገለበጡት ጽሑፎች ሁሉ ላይ ስለሚኖሩ በዚያ አካባቢ የሚገለበጡትን ግልባጮች በሙሉ ለይተው የሚያሳውቁ ስህተቶች ይኖራሉ። ተመሳሳይ የሆኑ ግልባጮች ቤተሰብ እየተፈጠረ የመጣው በዚህ መንገድ ነው። ታዲያ በሺህ የሚቆጠሩ ስህተቶች መኖራቸው የሚያስደነግጥ አይደለም? ጽሑፎቹ በትክክል እንዳልተላለፉ የሚያመለክት ማስረጃ አይሆንም? በፍጹም!
27 የዌስትኮትና ሆርት ጽሑፍ ተባባሪ አዘጋጅ የሆኑት ኤፍ ጄ ኤ ሆርት እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “እዚህ ግቡ የማይባሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን . . . ወደ ጎን ብንተው አጠራጣሪ ናቸው የሚባሉት ቃላት ከመላው አዲስ ኪዳን ከአንድ ሺህኛ አይበልጡም። . . . አብዛኞቹ የአዲስ ኪዳን ቃላት ብዙም ለውጥ ስለማይታይባቸውና እንዲሁ መገልበጥ ብቻ የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው ማንኛውንም ትችትና ስህተት ፍለጋ ሊቋቋሙ የሚችሉ ናቸው።”h
28 ግልባጮቹ በትክክል መተላለፋቸውን ማመዛዘን። ይህን ለሚያክሉ በርካታ መቶ ዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩት ቅዱሳን መጻሕፍት አስተማማኝና ትክክለኛ ስለመሆናቸው ምን ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል? እርስ በርሳቸው ሊነጻጸሩ የሚችሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ግልባጮች ከመኖራቸው በተጨማሪ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በ125 ዓ.ም. ገደማ፣ ማለትም ሐዋርያው ዮሐንስ ከሞተበት ከ100 ዓ.ም. ጥቂት ዓመታት ብቻ ቆይተው በግሪክኛ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ግልባጮች ተገኝተዋል። እነዚህ ቅጂዎች በአሁኑ ጊዜ ያለን የግሪክኛ ጽሑፍ የተጣራ ለመሆኑ አስተማማኝ የሆነ ጠንካራ ማስረጃ ይሰጡናል። የብሪትሽ ሙዚየም ዳይሬክተርና የቤተ መጻሕፍት ኃላፊ የነበሩት ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጡትን ሐሳብ እንመልከት:-
29 “በመጀመሪያዎቹ በኩረ ጽሑፎችና በተገኙት እጅግ ጥንታዊ ግልባጮች መካከል ያለው የዕድሜ ልዩነት በጣም ትንሽ በመሆኑ ከቁም ነገር የሚቆጠር አይደለም። በመሆኑም አሁን በእጃችን የሚገኙት ቅዱሳን መጻሕፍት ተለውጠው ይሆናል የሚለው ጥርጣሬ ሙሉ በሙሉ ተወግዷል። የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አስተማማኝነት እና አጠቃላይ ትክክለኛነት ሙሉ በሙሉ ተረጋግጧል ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ አጠቃላይ ትክክለኛነት አንድ ነገር ሲሆን ዝርዝር ትክክለኛነት ግን ሌላ ነገር ነው።”i
30 “ዝርዝር ትክክለኛነትን” በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ በአንቀጽ 27 ላይ የተጠቀሰው ዶክተር ሆርት የጻፉት ሐሳብ መልስ ይሰጣል። ዝርዝር ግድፈቶችን አበጥሮ ማውጣት የግልባጭ አጣሪዎች ሥራ ሲሆን ይህንን ሥራቸውንም በአብዛኛው አከናውነዋል። በዚህም ምክንያት የተጣራው የዌስትኮትና ሆርት የግሪክኛ ጽሑፍ በአብዛኛው ከፍተኛ ጥራት አለው የሚል ተቀባይነት አግኝቷል። የአዲስ ዓለም ትርጉም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል በዚህ ግሩም የሆነ የግሪክኛ ጽሑፍ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በግሪክኛው የእጅ ግልባጮች ባሕር ውስጥ በአስደናቂ መንገድ ተጠብቆ የቆየውን ‘የይሖዋ ቃል’ ለአንባቢዎቹ በታማኝነት ማስተላለፍ ችሏል።—1 ጴጥ. 1:24, 25
31 ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን አወር ባይብል ኤንድ ዚ ኤንሸንት ማኑስክሪፕትስ፣ በተባለው መጽሐፋቸው (1962) ገጽ 249 ላይ የጻፉት አስተያየት ልብ ሊባል የሚገባው ነው፦ “የአዲስ ኪዳን ጽሑፍ አጠቃላይ ትክክለኛነት፣ በመጀመሪያዎቹ የእጅ ጽሑፎችና በቅርብ ዓመታት በተገኙት ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል ያለውን የዕድሜ ልዩነት በእጅጉ በቀነሱት የጥንት ግልባጮች በሚገባ የተረጋገጠ በመሆኑ፣ የንባብ ልዩነት ቢኖርም እንኳ በክርስትና እምነት መሠረታዊ ትምህርቶች ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለመኖሩን ማወቃችን ሊያስደስተን ይገባል።” በጥናት 5 ሥር በሚገኘው በመጀመሪያው ሠንጠረዥ ውስጥ የተዘረዘሩት “ለአዲስ ዓለም ትርጉም በምንጭነት ያገለገሉ ጽሑፎች—የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት” እና ሌሎች ተዛማጅ ሰነዶች ትክክለኛ የሆነ የእንግሊዝኛ ትርጉም ለማዘጋጀት አገልግለዋል። እነዚህ አስተማማኝ ትርጉሞች በጣም ጠቃሚ በሆኑ የግርጌ ማስታወሻዎች የተደገፉ ናቸው። የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ ጥራት ያለው ትርጉሙን በሚያዘጋጅበት ጊዜ ባለፉት መቶ ዘመናት በተሰባሰቡት ምርጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራዊ ሥራዎች ተጠቅሟል። ዛሬ የምናገኛቸው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በመንፈስ የተመሩት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የጻፉትን ‘የጤናማ ቃላት ንድፍ’ የያዙ እንደሆኑ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ሁላችንም ይህን ውድ ቃል በእምነትና በፍቅር የሙጥኝ ብለን እንያዝ!—2 ጢሞ. 1:13
32 ይህ የአሁኑም ሆነ ከዚህ በፊት ያለው ጥናት የቅዱሳን መጻሕፍትን የእጅ ግልባጮችና የተጣሩ ቅጂዎችን አብራርቷል። ይህ ጉዳይ እንዲህ በሰፊው የተብራራው ለምንድን ነው? ዓላማው የዕብራይስጥም ሆነ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የጥንት ታማኝ አገልጋዮች በይሖዋ መንፈስ እየተመሩ ከጻፉት በኩረ ጽሑፍ የተለዩ እንዳልሆኑ አሳማኝ በሆነ መንገድ ለማሳየት ነው። በኩረ ጽሑፎቹ በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው። ገልባጮቹ ግን ከፍተኛ ብቃት የነበራቸው ቢሆኑም በመንፈስ የተመሩ አይደሉም። (መዝ. 45:1፤ 2 ጴጥ. 1:20, 21፤ 3:16) ስለሆነም ከታላቁ የሕይወት ውኃ ምንጭ ከይሖዋ የፈለቀው የጠራ የእውነት ውኃ የትኛው እንደሆነ አንጥሮ ለማውጣት በጣም በርካታ የሆኑትን ግልባጮች ማበጠር አስፈላጊ ሆኗል። በጣም አስደናቂ የሆነውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን በመንፈስ መሪነት አነሳሽነት የተጻፈ ቃሉንና ከዚህም ቃሉ የሚወርደውን የመንግሥቱን መልእክት ለሰጠን ለይሖዋ አምላክ ታላቅ ምሥጋና ይድረስ!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 354-355
b በእነዚህ ተከታታይ ቡሮሹሮች ላይ ስለ ማቴዎስ በሚናገረው ርዕስ ሥር አንቀጽ 6ን ተመልከት።
c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 323፤ ኒው ባይብል ዲክሽነሪ፣ ሁለተኛ እትም፣ 1986፣ ጄ ዲ ዳግላስ፣ ገጽ 1187
d ኒው ባይብል ዲክሽነሪ፣ ሁለተኛ እትም፣ ገጽ 1187
e በጥናት 7 ሥር የሚገኘውን “በሰባት ዋና ዋና ቋንቋዎች የተዘጋጁ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች” የሚለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።
f ዘ ኪንግደም ኢንተርሊንየር ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ግሪክ ስክሪፕቸርስ፣ 1985፣ ገጽ 8-9
g በሉቃስ 24:40፤ ዮሐንስ 5:4፤ የሐዋርያት ሥራ 19:23፤ 27:37 እና ራእይ 3:16 ሥር የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
h ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ዚ ኦሪጅናል ግሪክ፣ 1974፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 561
i ዘ ባይብል ኤንድ አርኪኦሎጂ፣ 1940፣ ገጽ 288-289