የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ሙሴ ይሖዋን ለማምለክ መረጠ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • የፈርዖን ልጅ ሕፃኑን ሙሴን ስታገኘው ሚርያም በአካባቢው ሆና እየተመለከተች ነው

      ትምህርት 17

      ሙሴ ይሖዋን ለማምለክ መረጠ

      የያዕቆብ ቤተሰቦች ወደ ግብፅ ከሄዱ በኋላ እስራኤላውያን ተብለው መጠራት ጀመሩ። ያዕቆብና ዮሴፍ ከሞቱ በኋላ አዲስ ፈርዖን በግብፅ ላይ መግዛት ጀመረ። ይህ ንጉሥ እስራኤላውያን ከግብፃውያን የበለጠ ኃያል እንዳይሆኑ ፈርቶ ነበር። ስለሆነም ፈርዖን እስራኤላውያንን ባሪያዎች አደረጋቸው። ጡብ እንዲሠሩ እንዲሁም በእርሻ ቦታ ላይ እንደ ባሪያ እንዲያገለግሉ አደረገ። ግብፃውያን እንደ ባሪያ ቢያሠሯቸውም የእስራኤላውያን ቁጥር እየጨመረ ሄደ። ፈርዖን ይህ ሁኔታ ስላሳሰበው እስራኤላውያን የሚወልዷቸው ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ። እስራኤላውያን ምን ያህል ፈርተው ሊሆን እንደሚችል ልትገምት ትችላለህ?

      በዚህ ጊዜ ዮካቤድ የተባለች አንዲት እስራኤላዊት የሚያምር ወንድ ልጅ ወለደች። ልጁ እንዳይገደል ስትል ቅርጫት ውስጥ አድርጋ በአባይ ወንዝ ዳር በሚገኝ ቄጠማ መሃል ደበቀችው። የልጁ እህት የሆነችው ሚርያም በአካባቢው ሆና የሚሆነውን ነገር ትከታተል ነበር።

      የፈርዖን ሴት ልጅ ወንዙ ውስጥ ገላዋን ልትታጠብ ስትመጣ ቅርጫቱን አየችው። ቅርጫቱ ውስጥ ያለው ሕፃን እያለቀሰ መሆኑን ስታይ አዘነችለት። ሚርያምም ‘ልጁን እያጠባች የምታሳድግልሽ ሞግዚት ልፈልግልሽ?’ ብላ ጠየቀቻት። የፈርዖን ልጅ በሐሳቡ ስትስማማ ሚርያም እናቷን ዮካቤድን ይዛ መጣች። የፈርዖን ልጅ ዮካቤድን ‘ልጁን ተንከባክበሽ አሳድጊልኝ፤ እኔ ገንዘብ እከፍልሻለሁ’ አለቻት።

      ሙሴ ሲሸሽ

      ልጁ ሲያድግ ዮካቤድ ወደ ፈርዖን ልጅ አመጣችው፤ የፈርዖን ልጅም ሙሴ ብላ ስም ያወጣችለት ሲሆን እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ አሳደገችው። ሙሴ የንጉሥ ልጅ ሆኖ አደገ፤ በመሆኑም የፈለገውን ነገር ሁሉ ማግኘት ይችል ነበር። ሆኖም ሙሴ ይሖዋን አልረሳም። በፈርዖን ቤት ቢያድግም እስራኤላዊ እንጂ ግብፃዊ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሖዋን ለማገልገል መረጠ።

      ሙሴ 40 ዓመት ሲሞላው እስራኤላውያንን ለመርዳት ወሰነ። አንድ ግብፃዊ አንድን እስራኤላዊ ባሪያ ሲደበድብ አየና ግብፃዊውን መትቶ ገደለው። ከዚያም አሸዋ ውስጥ ደበቀው። ፈርዖን ይህን ሲሰማ ሙሴን ለመግደል ሞከረ። ሆኖም ሙሴ ሸሽቶ ወደ ምድያም ምድር ሄደ። እዚያ ከሄደ በኋላ ይሖዋ ሙሴን ተንከባክቦታል።

      ‘ሙሴ የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ ለመጠራት በእምነት እንቢ አለ፤ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን መረጠ።’—ዕብራውያን 11:24, 25

      ጥያቄ፦ ግብፃውያን በእስራኤላውያን ላይ ምን በደል ይፈጽሙ ነበር? ሙሴ ወደ ምድያም የሸሸው ለምንድን ነው?

      ዘፍጥረት 49:33፤ ዘፀአት 1:1-14, 22፤ 2:1-15፤ የሐዋርያት ሥራ 7:17-29፤ ዕብራውያን 11:23-27

  • በእሳት የተያያዘው ቁጥቋጦ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ሙሴ በእሳት በተያያዘው ቁጥቋጦ አጠገብ ሆኖ

      ትምህርት 18

      በእሳት የተያያዘው ቁጥቋጦ

      ሙሴ በምድያም ምድር 40 ዓመት ኖረ። በዚያም ሚስት አግብቶ ልጆች ወለደ። አንድ ቀን በሲና ተራራ አጠገብ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ የሚገርም ነገር አየ። አንድ ቁጥቋጦ በእሳት ተያይዞ የነበረ ቢሆንም ቁጥቋጦው አልተቃጠለም! ሙሴ ቁጥቋጦው ለምን እንዳልተቃጠለ ለማየት ሲጠጋ ከቁጥቋጦው ውስጥ እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማ፦ ‘ሙሴ! ወደዚህ አትጠጋ። የቆምክበት መሬት ቅዱስ ስለሆነ ጫማህን አውልቅ።’ ሙሴን በአንድ መልአክ አማካኝነት ያነጋገረው ይሖዋ ነበር።

      በዚህ ጊዜ ሙሴ ስለፈራ ፊቱን ሸፈነ። ከቁጥቋጦው ውስጥ የተሰማው ድምፅ እንዲህ አለው፦ ‘እስራኤላውያን እየደረሰባቸው ያለውን ሥቃይ አይቻለሁ። ከግብፃውያን ነፃ አውጥቼ ወደ መልካም ምድር አመጣቸዋለሁ። ሕዝቤን እየመራህ ከግብፅ የምታወጣው አንተ ነህ።’ ሙሴ ይህን ሲሰማ በጣም ተገርሞ መሆን አለበት።

      ሙሴ ‘ሰዎቹ ማን ነው የላከህ ብለው ሲጠይቁኝ ምን ልበላቸው?’ አለ። አምላክም ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ የሆነው ይሖዋ ነው በላቸው’ ሲል መለሰለት። ከዚያም ሙሴ ‘ሕዝቡ ባይሰማኝስ?’ ብሎ ጠየቀ። ይሖዋ ሙሴን እንደሚረዳው የሚያሳይ ማረጋገጫ ሰጠው። ሙሴን ዱላውን ወደ መሬት እንዲጥል ነገረው። በዚህ ጊዜ ዱላው እባብ ሆነ! ሙሴ የእባቡን ጅራት ሲይዘው እባቡ ተመልሶ ዱላ ሆነ። ይሖዋም ‘ይህን ተአምር ስታሳይ እኔ እንደላኩህ ያምናሉ’ አለው።

      ሙሴም ‘እኔ በደንብ መናገር አልችልም’ አለ። ይሖዋም ‘ምን ማለት እንዳለብህ እነግርሃለሁ፤ እንዲሁም ወንድምህ አሮን እንዲረዳህ እልከዋለሁ’ በማለት ቃል ገባለት። ሙሴ፣ ይሖዋ ከእሱ ጋር እንደሚሆን በመተማመን ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ወደ ግብፅ ተመለሰ።

      “እንዴት ወይም ምን ብለን እንመልሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋልና።”—ማቴዎስ 10:19

      ጥያቄ፦ ሙሴ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ ምን አየ? ይሖዋ ሙሴን ምን እንዲያደርግ ነገረው?

      ዘፀአት 3:1–4:20፤ የሐዋርያት ሥራ 7:30-36

  • የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቅሰፍቶች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ሙሴና አሮን በፈርዖን ፊት ቆመው

      ትምህርት 19

      የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቅሰፍቶች

      ግብፃውያን እስራኤላውያንን ባሪያ አድርገዋቸው ስለነበር የጉልበት ሥራ ያሠሯቸው ነበር። ይሖዋ ሙሴንና አሮንን ወደ ፈርዖን በመላክ ‘“ወደ ምድረ በዳ ሄደው እንዲያመልኩኝ ሕዝቤን ልቀቅ” ብላችሁ ንገሩት’ አላቸው። ፈርዖን ‘ይሖዋ የፈለገውን ቢል ግድ አይሰጠኝም፤ እስራኤላውያንን አለቅም’ በማለት በትዕቢት መለሰ። ከዚያም ፈርዖን የእስራኤላውያንን ሥራ የባሰ አከበደባቸው። ይሖዋ ግን ፈርዖንን አንድ ትልቅ ትምህርት ሊያስተምረው ነው። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ? በግብፅ ላይ አሥር መቅሰፍቶች በማምጣት ነው። ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ፈርዖን የእኔን ትእዛዝ አልሰማም። ጠዋት ላይ ወደ አባይ ወንዝ ይሄዳል። ስለዚህ ወደ እሱ ሂድና “ሕዝቤን አለቅም ስላልክ አባይ ውስጥ ያለው ውኃ በሙሉ ወደ ደም ይቀየራል” በለው።’ ሙሴ ይሖዋን በመታዘዝ ወደ ፈርዖን ሄደ። ፈርዖን እያየ አሮን የአባይን ወንዝ በዱላው ሲመታው ወንዙ ወደ ደም ተቀየረ። በዚህ ጊዜ ወንዙ መሽተት ጀመረ፤ ዓሦቹም ሞቱ፤ በዚህ የተነሳ ሕዝቡ ከአባይ ወንዝ መጠጣት አልቻለም። ፈርዖን ግን አሁንም እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

      ከሰባት ቀን በኋላ ይሖዋ ሙሴን እንደገና ወደ ፈርዖን በመላክ እንዲህ ብሎ እንዲነግረው አዘዘው፦ ‘ሕዝቤን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ካልሆንክ የግብፅ ምድር በሙሉ በእንቁራሪት ይሞላል።’ አሮንም ዱላውን አነሳ። ከዚያም እንቁራሪቶች ከውኃ እየወጡ ወደ ሰዎች ቤት ገቡ፤ ዕቃቸው ሁሉ በእንቁራሪት ተሞላ፤ አልጋቸውም ላይ ወጡ። ሁሉም ቦታ በእንቁራሪት ተሞልቶ ነበር! በዚህ ጊዜ ፈርዖን ሙሴን ‘ይህን መቅሰፍት እንዲያቆምልን ይሖዋን ለምንልን’ አለው። ፈርዖን እስራኤላውያንን እንደሚለቅ ቃል ገባ። ስለዚህ ይሖዋ መቅሰፍቱን አስቆመ፤ ግብፃውያኑም የሞቱትን እንቁራሪቶች ሰብስበው ከመሯቸው። ምድሪቱም መሽተት ጀመረች። ፈርዖን ግን አሁንም ሕዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

      ከዚያም ይሖዋ ሙሴን ‘አሮን መሬቱን በዱላው ይምታው፤ ከዚያም አቧራው ወደ ትንኝ ይቀየራል’ አለው። ወዲያውኑ ምድሩ በሙሉ በትንኝ ተወረረ። የፈርዖን አገልጋዮች ራሳቸው ፈርዖንን ‘ይህ መቅሰፍት ከአምላክ የመጣ ነው’ አሉት። ፈርዖን ግን እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

      በግብፅ ላይ ከደረሱት አሥር መቅሰፍቶች መካከል ሦስቱ፦ የአባይ ወንዝ ወደ ደም መቀየር፣ እንቁራሪቶች እና ትንኞች

      “ኃይሌንና ብርታቴን እንዲያውቁ አደርጋለሁ፤ እነሱም ስሜ ይሖዋ መሆኑን ያውቃሉ።”—ኤርምያስ 16:21

      ጥያቄ፦ የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቅሰፍቶች የትኞቹ ናቸው? ይሖዋ እነዚህን መቅሰፍቶች ያመጣው ለምንድን ነው?

      ዘፀአት 5:1-18፤ 7:8–8:19፤ ነህምያ 9:9, 10

  • ስድስቱ መቅሰፍቶች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • የአንበጣ መንጋ

      ትምህርት 20

      ስድስቱ መቅሰፍቶች

      ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው ‘ሕዝቤን የማትለቅ ከሆነ በግብፅ ላይ ተናካሽ ዝንብ አመጣለሁ’ በማለት አምላክ የተናገረውን መልእክት ነገሩት። ተናካሽ ዝንቦች የግብፃውያንን ቤቶች በሙሉ ወረሩ። አገሪቱ በሙሉ በተናካሽ ዝንቦች ተሞላች። እስራኤላውያን በሚኖሩበት በጎሸን ምድር ግን ምንም ተናካሽ ዝንብ አልነበረም። ከዚህኛው ማለትም ከአራተኛው መቅሰፍት ጀምሮ ያሉት መቅሰፍቶች የጎዱት ግብፃውያንን ብቻ ነው። ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ‘እነዚህን ዝንቦች እንዲያስወግድልኝ ይሖዋን ለምኑልኝ። ሕዝቡን እለቃለሁ’ አላቸው። ሆኖም ይሖዋ ተናካሽ ዝንቦቹን ሲያስወግድላቸው ፈርዖን ሐሳቡን ቀየረ። ፈርዖን ከስህተቱ የሚማረው መቼ ይሆን?

      ይሖዋም ‘ፈርዖን ሕዝቤን የማይለቅ ከሆነ የግብፃውያን እንስሳት ታመው ይሞታሉ’ አለ። በቀጣዩ ቀን እንስሳቱ መሞት ጀመሩ። የእስራኤላውያን እንስሳት ግን አልሞቱም። በዚህ ጊዜም ቢሆን ፈርዖን ሕዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

      ከዚያም ይሖዋ ሙሴን አመድ ይዞ ወደ ፈርዖን በመሄድ አመዱን አየር ላይ እንዲበትነው ነገረው። አመዱ አቧራ ሆኖ አየሩን ሞላውና በግብፃውያኑ ሁሉ ላይ አረፈ። በዚህ የተነሳ በግብፃውያንና በእንስሶቻቸው ሁሉ ላይ የሚያም ቁስል ወጣ። ፈርዖን ግን አሁንም እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

      በግብፅ ላይ የደረሱት አራተኛ፣ አምስተኛና ስድስተኛ መቅሰፍቶች፦ ተናካሽ ዝንቦች፣ የእንስሳት መሞት፣ ቁስል

      ይሖዋ ሙሴን ወደ ፈርዖን መልሶ በመላክ ይህን መልእክት እንዲነግረው አዘዘው፦ ‘አሁንም ሕዝቤን አትለቅም ማለት ነው? ነገ በምድሪቱ ላይ በረዶ ይዘንባል።’ በቀጣዩ ቀን ይሖዋ በረዶ፣ ነጎድጓድና እሳት ላከ። ከዚያ በፊት በግብፅ ላይ እንዲህ ያለ ኃይለኛ ዝናብ ዘንቦ አያውቅም። ዛፎቹና ተክሎቹ በሙሉ ወደሙ፤ በጎሸን ያሉት ተክሎች ግን ምንም አልሆኑም። ፈርዖንም ‘ይሖዋ ይህን እንዲያስቆምልኝ ለምኑልኝ! ከዚያ መሄድ ትችላላችሁ’ አለ። ሆኖም ልክ በረዶውና ዝናቡ እንዳቆመ ፈርዖን ሐሳቡን ቀየረ።

      ከዚያም ሙሴ ‘ከበረዶው የተረፈውን ተክል አንበጦች ይበሉታል’ አለ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንበጦች መጥተው በእርሻውና በዛፎቹ ላይ የቀረውን በሙሉ በሉት። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ‘ይሖዋ እነዚህን አንበጦች እንዲያስወግድልኝ ለምኑልኝ’ አለ። ፈርዖን ግን ይሖዋ አንበጦቹን ካስወገዳቸው በኋላም ሕዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

      ይሖዋ ሙሴን ‘እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ’ አለው። ወዲያውኑም ሰማዩ ሙሉ በሙሉ ጨለመ። ለሦስት ቀን ያህል ግብፃውያን ምንም ነገር ማየት አልቻሉም። እስራኤላውያን በሚኖሩበት አካባቢ ግን ብርሃን ነበር።

      በግብፅ ላይ የደረሱት ሰባተኛ፣ ስምንተኛና ዘጠነኛ መቅሰፍቶች፦ በረዶ፣ አንበጦች፣ ጨለማ

      ፈርዖን ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘አንተና ሕዝብህ መሄድ ትችላላችሁ። እንስሶቻችሁን ግን እዚሁ ትታችሁ ሂዱ።’ ሙሴም ‘ለአምላካችን መሥዋዕት አድርገን ስለምናቀርባቸው እንስሶቻችንን መውሰድ አለብን’ አለው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን በጣም ተናደደ። ‘ከፊቴ ጥፋ! ከዚህ በኋላ አጠገቤ ብትደርስ እገድልሃለሁ’ በማለት ጮኸበት።

      “እናንተም በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ዳግመኛ ታያላችሁ።”—ሚልክያስ 3:18

      ጥያቄ፦ ይሖዋ በመቀጠል የትኞቹን መቅሰፍቶች አመጣ? እነዚህ መቅሰፍቶች ከመጀመሪያዎቹ ሦስት መቅሰፍቶች የሚለዩት በምንድን ነው?

      ዘፀአት 8:20–10:29

  • አሥረኛው መቅሰፍት
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • አንድ እስራኤላዊ የቤቱ መግቢያ ላይ ደም እየቀባ

      ትምህርት 21

      አሥረኛው መቅሰፍት

      ሙሴ ወደ ፈርዖን ተመልሶ እንደማይመጣ ተናገረ። ሆኖም ከፈርዖን ፊት ከመውጣቱ በፊት እንዲህ አለው፦ ‘እኩለ ሌሊት ላይ ከፈርዖን ልጅ ጀምሮ እስከ ባሪያው ልጅ ድረስ በግብፅ ያለ የበኩር ልጅ በሙሉ ይሞታል።’

      ይሖዋ ለእስራኤላውያን ልዩ ራት አዘጋጅተው እንዲበሉ ነገራቸው። እንዲህ አላቸው፦ ‘አንድ ዓመት የሆነው በግ ወይም ፍየል አርዳችሁ ደሙን የቤታችሁ መግቢያ ላይ ቀቡት። ሥጋውን ጥበሱና ካልቦካ ቂጣ ጋር ብሉት። ልብሳችሁን ለብሳችሁና ጫማችሁን አድርጋችሁ ለጉዞ ተዘጋጁ። በዚህ ሌሊት ነፃ አወጣችኋለሁ።’ እስራኤላውያን ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው።

      እኩለ ሌሊት ላይ የይሖዋ መልአክ በግብፅ ወዳሉ ቤቶች በሙሉ ሄደ። መግቢያቸው ላይ ደም ባልተቀባባቸው ቤቶች ውስጥ ያሉት የበኩር ልጆች ሞቱ። ሆኖም መልአኩ ደም የተቀባባቸውን ቤቶች አልፎ ሄደ። በእያንዳንዱ የግብፃውያን ቤተሰብ ውስጥ ያለ የበኩር ልጅ ሁሉ ሞተ። ሆኖም ከእስራኤላውያን ልጆች መካከል አንዳቸውም አልሞቱም።

      በዚህ ጊዜ የፈርዖን ልጅም ጭምር ሞተ። ፈርዖን ከዚህ በላይ ሊቋቋም አልቻለም። ወዲያውኑ ሙሴንና አሮንን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ ‘ተነሱ። ከዚህ ውጡ። አምላካችሁን አምልኩ። እንስሶቻችሁንም ይዛችሁ ሂዱ!’

      ጨረቃዋ ሙሉ ሆና ትታይ በነበረበት በዚያ ሌሊት እስራኤላውያን በቤተሰብና በነገድ ተከፋፍለው ከግብፅ ወጡ። በዚያ ጊዜ ከግብፅ የወጡት እስራኤላውያን ወንዶች 600,000 ሲሆኑ በርካታ ሴቶችና ልጆችም ነበሩ። በተጨማሪም ከእስራኤላውያን ጋር ይሖዋን ለማምለክ የመረጡ ሌሎች ብዙ ሰዎች አብረዋቸው ሄዱ። በመጨረሻ እስራኤላውያን ነፃ ወጡ!

      እስራኤላውያን ይሖዋ እንዴት እንዳዳናቸው ማስታወስ እንዲችሉ በየዓመቱ ያንን ልዩ ራት እንዲመገቡ ትእዛዝ ተሰጣቸው። ይህ ልዩ ራት ፋሲካ ይባላል።

      እስራኤላውያን ከግብፅ ሲወጡ

      “በሕይወት ያቆየሁህ ኃይሌን በአንተ ለማሳየትና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ለማድረግ ነው።”—ሮም 9:17

      ጥያቄ፦ አሥረኛው መቅሰፍት ምን ነበር? እስራኤላውያን የበኩር ልጆቻቸው እንዳይገደሉ ከፈለጉ ምን ማድረግ ነበረባቸው?

      ዘፀአት 11:1–12:42፤ 13:3-10

  • በቀይ ባሕር የተፈጸመው ተአምር
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ፈርዖንና ሠራዊቱ

      ትምህርት 22

      በቀይ ባሕር የተፈጸመው ተአምር

      ፈርዖን፣ እስራኤላውያን ግብፅን ለቀው መውጣታቸውን ሲሰማ እነሱን መልቀቁ ቆጨው። ወታደሮቹን እንዲህ በማለት አዘዛቸው፦ ‘የጦር ሠረገሎቼን በሙሉ አዘጋጁና እስራኤላውያንን እናሳዳቸው! እነሱን መልቀቅ አልነበረብንም።’ ፈርዖንና አብረውት ያሉት ሰዎች እስራኤላውያንን ማሳደድ ጀመሩ።

      ይሖዋ ሕዝቡን ቀን ቀን በደመና፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በእሳት ይመራቸው ነበር። ወደ ቀይ ባሕር እየመራ ወሰዳቸው፤ ከዚያም በባሕሩ አጠገብ ድንኳናቸውን እንዲተክሉ ነገራቸው።

      እስራኤላውያን ዞር ብለው ሲመለከቱ ፈርዖንና ሠራዊቱ እያሳደዷቸው እንደሆነ አዩ። ከፊታቸው ባሕር፣ ከኋላቸው ደግሞ የግብፅ ሠራዊት ስላለ ማምለጫ አልነበራቸውም። ስለዚህ እንዲህ በማለት ወደ ሙሴ ጮኹ፦ ‘በቃ መሞታችን ነው! እዚያው ግብፅ ብትተወን ይሻለን ነበር።’ ሙሴ ግን ‘አትፍሩ። ይሖዋ እንዴት እንደሚያድነን ታያላችሁ’ አላቸው። በእርግጥም ሙሴ በይሖዋ ላይ ትልቅ እምነት ነበረው።

      ይሖዋ እስራኤላውያንን ድንኳናቸውን ነቅለው እንዲጓዙ ነገራቸው። በዚያ ምሽት ይሖዋ ደመናው በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል እንዲሆን አደረገ። ግብፃውያን ባሉበት አካባቢ ጨለማ ነበር። እስራኤላውያን ባሉበት አካባቢ ግን ብርሃን ነበር።

      ይሖዋ ሙሴን እጁን በባሕሩ ላይ እንዲዘረጋ ነገረው። ከዚያም ይሖዋ ሌሊቱን ሙሉ ኃይለኛ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ። ባሕሩ ለሁለት ተከፈለና መሃል ላይ ማለፊያ መንገድ ተከፈተ። በሚሊዮን የሚቆጠሩት እስራኤላውያን እንደ ግድግዳ በቆመው ውኃ መካከል በደረቅ መሬት ላይ ተሻገሩ።

      እስራኤላውያን እንደ ግድግዳ በቆመው ውኃ መሃል በደረቅ መሬት ላይ ሲሻገሩ

      የፈርዖን ወታደሮች እስራኤላውያንን ተከትለው ወደተከፈለው ባሕር ገቡ። ከዚያም ይሖዋ የግብፅ ወታደሮች ግራ እንዲጋቡ አደረገ። የሠረገሎቻቸው እግሮችም ወላለቁ። በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ ‘ከዚህ እንውጣ! ይሖዋ እየተዋጋላቸው ነው’ በማለት ጮኹ።

      ይሖዋ ሙሴን ‘እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ’ አለው። ወዲያውኑም እንደ ግድግዳ የቆመው ውኃ ተመልሶ የግብፅን ወታደሮች በሙሉ አለበሳቸው። ፈርዖንና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ሞቱ። አንዳቸውም አልተረፉም።

      ባሕሩን ተሻግረው ያለፉት እስራኤላውያን ይሖዋን እንዲህ በማለት በመዝሙር አወደሱት፦ “በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ እዘምራለሁ። ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው።” ሕዝቡ ሲዘምር ሴቶቹ ይጨፍሩና ከበሮ ይመቱ ነበር። እስራኤላውያን ከግብፃውያን ባርነት ነፃ በመውጣታቸው በጣም ተደሰቱ።

      “ስለዚህ በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን።”—ዕብራውያን 13:6

      ጥያቄ፦ እስራኤላውያን ቀይ ባሕር ጋ ሲደርሱ ምን የሚያስፈራ ሁኔታ አጋጠማቸው? ይሖዋ እስራኤላውያንን ያዳናቸው እንዴት ነው?

      ዘፀአት 13:21–15:21፤ ነህምያ 9:9-11፤ መዝሙር 106:9-12፤ 136:11-15፤ ዕብራውያን 11:29

  • እስራኤላውያን ለይሖዋ ቃል ገቡ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • እስራኤላውያን በሲና ተራራ ሥር ቆመው

      ትምህርት 23

      እስራኤላውያን ለይሖዋ ቃል ገቡ

      እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ ወደ ሲና ተራራ ደረሱ፤ በዚያም ድንኳናቸውን ተከሉ። ሙሴ ወደ ተራራው ከወጣ በኋላ ይሖዋ ጠራውና እንዲህ አለው፦ ‘እስራኤላውያንን ያዳንኳቸው እኔ ነኝ። ከታዘዙኝና ሕጎቼን ከጠበቁ ለእኔ ልዩ ሕዝብ ይሆናሉ።’ ከዚያም ሙሴ ተመልሶ ወረደና ይሖዋ ያለውን ነገር ለእስራኤላውያን ነገራቸው። እነሱም ‘ይሖዋ አድርጉ ያለንን ነገር በሙሉ እናደርጋለን’ ሲሉ መለሱ።

      ሙሴ ተመልሶ ወደ ተራራው ወጣ። ይሖዋም እንዲህ አለው፦ ‘በሦስት ቀን ውስጥ አነጋግርሃለሁ። ሕዝቡ ወደ ሲና ተራራ ለመውጣት እንዳይሞክሩ አስጠንቅቃቸው።’ ሙሴ ከተራራው ወረደና እስራኤላውያንን ‘የይሖዋን ቃል ለመስማት ተዘጋጁ’ አላቸው።

      እስራኤላውያን በሲና ተራራ ላይ የወረደውን መብረቅና ጥቁር ደመና ሲያዩ

      በሦስተኛው ቀን፣ እስራኤላውያን ተራራው ላይ መብረቅና ጥቁር ደመና አዩ። የነጎድጓድና የቀንደ መለከት ድምፅም ሰሙ። ከዚያም ይሖዋ ወደ ተራራው በእሳት ወረደ። እስራኤላውያን በጣም ከመፍራታቸው የተነሳ ተንቀጠቀጡ። መላው ተራራ በኃይል ተናወጠ፤ እንዲሁም በጭስ ተሞላ። የቀንደ መለከቱ ድምፅም ይበልጥ እየጨመረ መጣ። ከዚያም አምላክ እንዲህ አለ፦ ‘እኔ ይሖዋ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክትን ማምለክ የለባችሁም።’

      ሙሴ ተመልሶ ወደ ተራራው ወጣ፤ ይሖዋም ሕዝቡ እንዴት ሊያመልኩት እንደሚገባ እንዲሁም ማድረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ነገሮች የሚገልጽ ሕግ ሰጠው። ሙሴ ሕጉን ጻፈና ለእስራኤላውያን አነበበላቸው። እነሱም ‘ይሖዋ እንድናደርግ ያዘዘንን ነገር በሙሉ እናደርጋለን’ በማለት ለአምላክ ቃል ገቡ። ታዲያ ቃላቸውን ይጠብቁ ይሆን?

      “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።”—ማቴዎስ 22:37

      ጥያቄ፦ በሲና ተራራ ላይ ምን ተከናወነ? እስራኤላውያን ምን ለማድረግ ቃል ገቡ?

      ዘፀአት 19:1–20:21፤ 24:1-8፤ ዘዳግም 7:6-9፤ ነህምያ 9:13, 14

  • ቃላቸውን አልጠበቁም
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • እስራኤላውያን በወርቁ ጥጃ ዙሪያ ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ

      ትምህርት 24

      ቃላቸውን አልጠበቁም

      ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ። ሕጎቼን በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፌ እሰጥሃለሁ።’ ሙሴ ወደ ተራራው ወጣና በዚያ 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆየ። ሙሴ እዚያ በቆየበት ጊዜ ውስጥ ይሖዋ አሥርቱን ትእዛዛት በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ሰጠው።

      ሙሴ የድንጋይ ጽላቶቹን ወደ መሬት ሲወረውር

      ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ሙሴ ትቷቸው የሄደ መሰላቸው። ስለዚህ አሮንን ‘መሪ ያስፈልገናል። አምላክ ሥራልን!’ አሉት። አሮንም ‘ወርቃችሁን ስጡኝ’ አላቸው። ከዚያም ወርቁን አቅልጦ የጥጃ ሐውልት ሠራ። ሰዎቹም ‘ከግብፅ መርቶ ያወጣን አምላካችን ይህ ጥጃ ነው!’ አሉ። በመሆኑም የወርቁን ጥጃ ማምለክ ጀመሩ፤ እንዲሁም ትልቅ ድግስ አዘጋጁ። ይህን ማድረጋቸው ስህተት ነበር? አዎ፣ ምክንያቱም ይሖዋን ብቻ ለማምለክ ቃል ገብተው ነበር። አሁን ግን ይህን ቃላቸውን አልጠበቁም።

      ይሖዋ እስራኤላውያን ያደረጉትን ነገር አየና ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ ሕዝቡ ሂድ። እኔን አልታዘዙም፤ የሐሰት አምላክ እያመለኩ ነው።’ በመሆኑም ሙሴ ሁለቱን ጽላቶች ይዞ ከተራራው ወረደ።

      ሙሴ ወደ ሰፈሩ ሲጠጋ እስራኤላውያን ሲዘምሩ ሰማ። ከዚያም ሲጨፍሩና ለጥጃው ሲሰግዱ ተመለከተ። በዚህ ጊዜ ሙሴ በጣም ተናደደ። ጽላቶቹን ወደ መሬት ሲወረውራቸው ተሰባበሩ። የጥጃውንም ሐውልት ወዲያውኑ ወስዶ አቃጠለው። ከዚያም አሮንን ‘እንዲህ ያለ መጥፎ ነገር ልታደርግ የቻልከው ሕዝቡ ምን ብሎ ቢያሳምንህ ነው?’ ብሎ ጠየቀው። አሮንም እንዲህ አለ፦ ‘እባክህ አትቆጣ። እነሱ እንደሆነ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ ታውቃለህ። አምላክ ሥራልን አሉኝ፤ ስለዚህ ወርቃቸውን እሳቱ ውስጥ ጣልኩት፤ ከዚያ ይህ ጥጃ ወጣ!’ አሮን እንዲህ ማድረግ አልነበረበትም። ሙሴ ተመልሶ ወደ ተራራው በመውጣት ሕዝቡን ይቅር እንዲል ይሖዋን ለመነው።

      ይሖዋ እሱን ለመታዘዝ ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች ይቅር አላቸው። እስራኤላውያን የሙሴን አመራር መከተላቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበር አስተዋልክ?

      “ለአምላክ ስእለት በምትሳልበት ጊዜ ሁሉ ስእለትህን ለመፈጸም አትዘግይ፤ እሱ በሞኞች አይደሰትምና። ስእለትህን ፈጽም።”—መክብብ 5:4

      ጥያቄ፦ ሙሴ ወደ ተራራው ወጥቶ በነበረበት ወቅት እስራኤላውያን ምን አደረጉ? ሙሴ ሲመለስ ምን አደረገ?

      ዘፀአት 24:12-18፤ 32:1-30

  • ለአምልኮ የሚያገለግል የማደሪያ ድንኳን
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • የማደሪያ ድንኳኑና ግቢው

      ትምህርት 25

      ለአምልኮ የሚያገለግል የማደሪያ ድንኳን

      ሙሴ በሲና ተራራ ላይ በነበረበት ወቅት ይሖዋ ለየት ያለ ድንኳን እንዲሠራ አዘዘው፤ ይህ ድንኳን የማደሪያ ድንኳን ተብሎ የተጠራ ሲሆን እስራኤላውያን ይሖዋን ለማምለክ ይጠቀሙበት ነበር። እስራኤላውያን ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የማደሪያውን ድንኳን ይዘው መሄድ ይችሉ ነበር።

      ይሖዋ ሙሴን ‘የማደሪያውን ድንኳን ለመሥራት እስራኤላውያን የቻሉትን ያህል መዋጮ እንዲያደርጉ ንገራቸው’ አለው። በመሆኑም እስራኤላውያን ወርቅ፣ ብር፣ መዳብ፣ የከበሩ ድንጋዮችና ጌጣጌጦች ሰጡ። በተጨማሪም ሱፍ፣ በፍታ፣ የእንስሳት ቆዳና ሌሎች ብዙ ነገሮች አመጡ። ሕዝቡ ብዙ መዋጮ ስለሰጡ ሙሴ ‘የሚበቃንን ያህል አግኝተናል! ተጨማሪ ነገር አታምጡ’ አላቸው።

      እስራኤላውያን የማደሪያ ድንኳኑን ለመገንባት የሚያገለግሉ ስጦታዎች ሲያመጡ

      የማደሪያ ድንኳኑ ሲሠራ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ብዙ ወንዶችና ሴቶች በሥራው ተካፍለዋል። ይሖዋ ለሥራው የሚያስፈልገውን ጥበብ ሰጥቷቸዋል። አንዳንዶቹ ይፈትሉ፣ ይሸምኑ ወይም ጥልፍ ይጠልፉ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ በድንጋይ፣ በወርቅ እንዲሁም በእንጨት የተለያዩ ቅርጾችን ይቀርጹ ነበር።

      ሕዝቡ የማደሪያ ድንኳኑን የሠሩት ልክ ይሖዋ ባዘዛቸው መንገድ ነበር። የማደሪያ ድንኳኑን ለሁለት የሚከፍል የሚያምር መጋረጃ ሠሩ፤ አንደኛው ክፍል ቅድስት የሚባል ሲሆን ሌላኛው ክፍል ደግሞ ቅድስተ ቅዱሳን ይባል ነበር። ቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከግራር እንጨትና ከወርቅ የተሠራ የቃል ኪዳን ታቦት ነበር። ቅድስቱ ውስጥ ደግሞ ከወርቅ የተሠራ መቅረዝ፣ ጠረጴዛና ዕጣን የሚጨስበት መሠዊያ ይገኛል። ግቢው ውስጥ ከመዳብ የተሠራ ገንዳና ትልቅ መሠዊያ ነበር። የቃል ኪዳኑ ታቦት እስራኤላውያን ይሖዋን ለመታዘዝ የገቡትን ቃል ያስታውሳቸው ነበር።

      ይሖዋ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ አሮንንና ልጆቹን መርጦ ነበር። እነሱም የማደሪያ ድንኳኑን መንከባከብና በዚያ ለይሖዋ መባ ማቅረብ ነበረባቸው። ቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ መግባት የሚፈቀድለት ሊቀ ካህናቱ አሮን ብቻ ነበር። እሱም በዓመት አንድ ጊዜ ወደዚያ በመግባት ለራሱ፣ ለቤተሰቡ እንዲሁም ለመላው የእስራኤል ብሔር ኃጢአት መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።

      እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከአንድ ዓመት በኋላ የማደሪያ ድንኳኑን ሠርተው ጨረሱ። አሁን በዚህ ቦታ ይሖዋን ማምለክ ይችላሉ።

      ይሖዋ የማደሪያ ድንኳኑን በክብሩ ሞላው፤ እንዲሁም ከድንኳኑ በላይ ደመና እንዲታይ አደረገ። ደመናው ከማደሪያ ድንኳኑ በላይ እስካለ ድረስ እስራኤላውያን ከሰፈሩበት ቦታ አይንቀሳቀሱም ነበር። ደመናው ሲነሳ ግን ያንን ቦታ ለቀው መጓዝ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር። የማደሪያ ድንኳኑን ይነቃቅሉና ደመናውን ተከትለው ይጓዛሉ።

      “በዚህ ጊዜ ከዙፋኑ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ ‘እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል።’”—ራእይ 21:3

      ጥያቄ፦ ይሖዋ ሙሴን ምን እንዲሠራ ነገረው? ይሖዋ ለአሮንና ለልጆቹ ምን ኃላፊነት ሰጣቸው?

      ዘፀአት 25:1-9፤ 31:1-11፤ 40:33-38፤ ዕብራውያን 9:1-7

  • አሥራ ሁለቱ ሰላዮች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • እስራኤላውያን የከነአንን ምድር ሲሰልሉ

      ትምህርት 26

      አሥራ ሁለቱ ሰላዮች

      እስራኤላውያን ከሲና ተራራ ተነስተው፣ በፋራን ምድረ በዳ በኩል በመጓዝ ቃዴስ ወደሚባል ቦታ ደረሱ። በዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ለእስራኤላውያን የምሰጣቸውን የከነአንን ምድር እንዲሰልሉ ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው መርጠህ 12 ሰዎችን ላክ።’ ሙሴም 12 ሰዎችን መረጠና እንዲህ አላቸው፦ ‘ወደ ከነአን ሄዳችሁ ምድሪቱ ጥሩ እህል የምታበቅል መሆን አለመሆኗን እዩ። ሰዎቹ ደካማ ወይም ጠንካራ መሆናቸውን እንዲሁም የሚኖሩት በድንኳን ይሁን በከተሞች አጣርታችሁ ኑ።’ ኢያሱና ካሌብን ጨምሮ 12ቱ ሰላዮች ወደ ከነአን ሄዱ።

      እስራኤላውያን ተስፋ ቆርጠው ሲያጉረመርሙ

      ከ40 ቀን በኋላ ሰላዮቹ በለስ፣ ሮማንና ወይን ይዘው ተመለሱ። ሰላዮቹ ‘ምድሪቱ ለኑሮ ተስማሚ ነች፤ ሰዎቹ ግን በጣም ጠንካሮች ናቸው፤ ከተሞቹም ረጃጅም ግንብ አላቸው’ በማለት ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ካሌብ ‘ሰዎቹን እናሸንፋቸዋለን። አሁኑኑ እንሂድ!’ አለ። ካሌብ እንዲህ ያለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? እሱና ኢያሱ በይሖዋ ይተማመኑ ስለነበረ ነው። ሌሎቹ አሥር ሰላዮች ግን እንዲህ አሉ፦ ‘አይሆንም! እዚያ ያሉት ሰዎች በጣም ግዙፎች ናቸው! እኛ ከእነሱ ጋር ስንነጻጸር እንደ ፌንጣ ነን።’

      እስራኤላውያን ይህን ሲሰሙ ተስፋ ቆረጡ። ማጉረምረምና እርስ በርሳቸው እንዲህ መባባል ጀመሩ፦ ‘ወደ ከነአን ሄደን እነዚያ ሰዎች ከሚገድሉን ሌላ መሪ መርጠን ወደ ግብፅ ብንመለስ አይሻለንም?’ በዚህ ጊዜ ኢያሱና ካሌብ ‘በይሖዋ ላይ አታምፁ፤ አትፍሩ። ይሖዋ ይጠብቀናል’ አሏቸው። እስራኤላውያን ግን አልሰሟቸውም። እንዲያውም ኢያሱንና ካሌብን ለመግደል አሰቡ!

      ይሖዋ ይህን ሲያይ ምን አደረገ? ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ለእስራኤላውያን ብዙ ነገር አድርጌላቸዋለሁ፤ እነሱ ግን አሁንም አይታዘዙኝም። ስለዚህ በምድረ በዳ ለ40 ዓመት ይቆያሉ፤ ከዚያም እዚያው ይሞታሉ። እሰጣቸዋለሁ ብዬ ቃል ወደገባሁላቸው ምድር የሚገቡት ልጆቻቸው እንዲሁም ኢያሱና ካሌብ ብቻ ናቸው።’

      “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትሸበራላችሁ?”—ማቴዎስ 8:26

      ጥያቄ፦ ሙሴ የላካቸው 12 ሰላዮች ከከነአን ከተመለሱ በኋላ ምን ሆነ? ኢያሱና ካሌብ በይሖዋ እንደሚተማመኑ ያሳዩት እንዴት ነው?

      ዘኁልቁ 13:1–14:38፤ ዘዳግም 1:22-33፤ መዝሙር 78:22፤ ዕብራውያን 3:17-19

  • በይሖዋ ላይ ዓመፁ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ቆሬና ተባባሪዎቹ በሙሴና በአሮን ፊት ቆመው

      ትምህርት 27

      በይሖዋ ላይ ዓመፁ

      ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ቆሬ፣ ዳታን፣ አቤሮንና ሌሎች 250 ሰዎች በሙሴና በአሮን ላይ ዓመፁ። እንዲህም አሏቸው፦ ‘አላበዛችሁትም እንዴ! አንተ መሪያችን የሆንከው ለምንድን ነው? አሮንስ ሊቀ ካህናት የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ ከእናንተ ጋር ብቻ ነው እንዴ? ከእኛም ጋር ነው።’ ይሖዋ ግን በዚህ አልተደሰተም። እነዚህ ሰዎች ልክ በራሱ ላይ እንዳመፁ አድርጎ ነበር የቆጠረው!

      ሙሴም ቆሬንና ተባባሪዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ነገ የዕጣን ማጨሻዎቻችሁ ላይ ዕጣን ጨምራችሁ ወደ ማደሪያው ድንኳን ኑ። ይሖዋ ማንን እንደሚመርጥ እናያለን።’

      በቀጣዩ ቀን ቆሬና አብረውት የነበሩት 250 ሰዎች ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ሄዱ። ዕጣን ማጨስ የሚፈቀድላቸው ካህናት ብቻ ቢሆኑም ዕጣን አጨሱ። ይሖዋ ሙሴንና አሮንን ‘ከቆሬና ከተባባሪዎቹ ራሳችሁን ለዩ’ አላቸው።

      ቆሬ ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ ማደሪያ ድንኳኑ የሄደ ቢሆንም ዳታን፣ አቤሮንና ቤተሰቦቻቸው ወደዚያ ለመሄድ ፈቃደኞች አልሆኑም። ይሖዋ እስራኤላውያንን ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳን እንዲርቁ ነገራቸው። እስራኤላውያንም ወዲያውኑ እንደተባሉት አደረጉ። ዳታን፣ አቤሮንና ቤተሰቦቻቸው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆሙ። ከዚያም በድንገት መሬቱ ተሰነጠቀና ዋጣቸው! በማደሪያ ድንኳኑ መግቢያ ላይ የነበሩትን ቆሬንና 250 ተባባሪዎቹን ደግሞ እሳት ከሰማይ ወርዶ አቃጠላቸው።

      መሬቱ ተሰንጥቆ ዳታንን፣ አቤሮንንና ቤተሰቦቻቸውን ሲውጣቸው

      ይሖዋ በመቀጠል ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ከእያንዳንዱ ነገድ አለቃ አንድ በትር ውሰድና የነገድ አለቃውን ስም ጻፍበት። ከሌዊ ነገድ በተወሰደው በትር ላይ ደግሞ የአሮንን ስም ጻፍ። ከዚያም በትሮቹን በማደሪያው ድንኳን ውስጥ አስቀምጣቸው፤ እኔ የምመርጠው ሰው በትር አበባ ያወጣል።’

      በቀጣዩ ቀን ሙሴ በትሮቹን በሙሉ አምጥቶ ለነገድ አለቆቹ አሳያቸው። የአሮን በትር አበባ አውጥቶና የበሰለ የአልሞንድ ፍሬ አፍርቶ ነበር። በዚህ መንገድ ይሖዋ አሮንን ሊቀ ካህናት እንዲሆን የመረጠው እሱ እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጠ።

      “በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ።”—ዕብራውያን 13:17

      ጥያቄ፦ ቆሬና ተባባሪዎቹ በሙሴና በአሮን ላይ በማመፅ ምን አሏቸው? አሮንን ሊቀ ካህናት እንዲሆን የመረጠው ይሖዋ እንደሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

      ዘኁልቁ 16:1–17:13፤ 26:9-11፤ መዝሙር 106:16-18

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ