በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት እና የኋላ ታሪካቸው ጥናት
ጥናት ቁጥር 4—መጽሐፍ ቅዱስና በውስጡ የተካተቱ ተቀባይነት ያገኙ መጻሕፍት ዝርዝር
“ባይብል” የሚለው ቃል አመጣጥ፤ መለኮታዊ ምንጭ ያላቸውን መጻሕፍት ለይቶ ማወቅ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያልሆኑ አዋልድ መጻሕፍት።
በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ባይብል (መጽሐፍ ቅዱስ) ተብለው ስለሚጠሩ “ባይብል” የሚለውን ቃል አመጣጥና ትርጉም ማወቃችን የተገባ ነው። ቃሉ “ትናንሽ መጻሕፍት” የሚል ትርጉም ካለው ቢብሊያ ከተባለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው። ይህ ቃል ደግሞ ቢብሎስ ከተባለው ቃል የተገኘ ሲሆን ቢብሎስ በጥንት ዘመን ለመጻፊያነት የሚያገለግል “ወረቀት” የሚሠራበትን የፓፒረስ ተክል ውስጠኛ ክፍል ያመለክታል። (ፊንቄያውያን ከግብፅ ፓፒረስ የሚያስገቡበትን ጌባል የተባለውን ወደብ ግሪካውያን ባይብሎስ ብለው ይጠሩት ነበር።a) ለመጻፊያነት በሚያገለግለው በዚህ ነገር አማካኝነት የሚደረገው ማንኛውም የጽሑፍ ግንኙነት ቢብሊያ ተብሎ ይጠራ ነበር። በዚህ መንገድ ቢብሊያ የሚለው ቃል የማንኛውም መጣጥፍ፣ ጥቅልል፣ መጽሐፍ፣ ሰነድ ወይም ቅዱሳን መጻሕፍት አልፎ ተርፎም የትናንሽ መጻሕፍት ስብስብ መጠሪያ ሆኖ ያገለግል ጀመር።
2 የሚገርመው ግን “ባይብል” የሚለው ቃል በእንግሊዝኛም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች በተዘጋጁ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉሞች ውስጥ አይገኝም። ይሁን እንጂ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በመንፈስ መሪነት የተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ስብስብ በግሪክኛ ቋንቋ ታ ቢብሊያ ተብሎ ይጠራ ነበር። በዳንኤል 9:2 ላይ ነቢዩ “እኔ ዳንኤል . . . ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተዋልሁ” ሲል ጽፏል። እዚህ ላይ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቢብሎስ የሚለው ቃል ብዙ ቁጥር የሆነውን ቢብሎይስ የተባለ ቃል ተጠቅሟል። ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 4:13 ላይ “ስትመጣ . . . የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን [በግሪክኛ ቢብሊያ] . . . አምጣልኝ” ሲል ጽፏል። ቢብሊዮን እና ቢብሎስ የተባሉት የግሪክኛ ቃላት በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተለያየ የሰዋስው አገባብ ከ40 ጊዜ በላይ የሚገኙ ሲሆን በአብዛኛው “ጥቅልል(ሎች)” ወይም “መጽሐፍ(ፎች)” ተብለው ተተርጉመዋል። ከጊዜ በኋላ ቢብሊያ የሚለው ቃል በላቲን ነጠላ ቁጥር ሆኖ ይሠራበት ጀመር፤ “ባይብል” የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል የመጣው ከዚህ የላቲን ቃል ነው።
3 የአምላክ ቃል ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ መሪነት የጻፉትና ከበኩረ ጽሑፉ ዛሬ ወደሚገኙት በርካታ ቋንቋዎች የተረጎሙት የተለያዩ ሰዎች ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው፤ አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት ለሰዎች የገለጠው ራእይ ነው። በመንፈስ መሪነት የጻፉት ጸሐፊዎች ራሳቸው ‘ከእግዚአብሔር አፍ የሚወጣ ቃል’ (ዘዳ. 8:3)፣ “እግዚአብሔር የተናገረን” (ኢያሱ 24:27)፣ ‘የእግዚአብሔር ትእዛዝ’ (ዕዝራ 7:11)፣ “የእግዚአብሔር ሕግ” (መዝ. 19:7)፣ ‘የእግዚአብሔር ቃል’ (ኢሳ. 38:4)፣ ‘ከይሖዋ አፍ የሚወጣ ቃል’ (ማቴ. 4:4) እና ‘የይሖዋ ቃል’ (1 ተሰ. 4:15) ብለው መናገራቸው መጽሐፍ ቅዱስን የአምላክ ቃል እንደሆነ አድርገው እንደሚመለከቱት ያሳያል።
መለኮታዊው ቤተ መጻሕፍት
4 በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ የሚጠራው መጽሐፍ ጥንት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት ስብስብ ነው። እነዚህ መጻሕፍት በጽሑፍ መልክ የተዘጋጁትና የተቀናበሩት ከ16 መቶ ዘመናት በሚበልጥ ጊዜ ውስጥ ነው። የእነዚህን መጻሕፍት ስብስብ ጀሮም በላቲን ቢብሊዮቴካ ዲቫይና ወይም መለኮታዊው ቤተ መጻሕፍት ብሎ ጠርቶታል። ይህ ቤተ መጻሕፍት ካታሎግ ወይም በዚህ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸውን ተቀባይነት ያገኙ መጻሕፍት የሚገልጽ ዝርዝር አለው። እውቅና ያላገኙ መጻሕፍት ሁሉ በዚህ ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም። የትኞቹ መጻሕፍት መካተት እንዳለባቸው ለመወሰን የሚያስችል መሥፈርት የሚያወጣው የቤተ መጻሕፍቱ ዋና ኃላፊ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አመራር የተጻፉ 66 መጻሕፍትን ያካተተ ቋሚ የሆነ የመጻሕፍት ዝርዝር አለው።
5 እውነተኛና በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው በሚል ተቀባይነት ያገኙት ቅዱሳን መጻሕፍት ስብስብ ወይም ዝርዝር በእንግሊዝኛ ብዙውን ጊዜ ባይብል ካነን (ቀኖና) ተብሎ ይጠራል። ጥንት በትር በማይኖርበት ጊዜ መቃ (በዕብራይስጥ ቃነህ) እንደ መለኪያ ዘንግ ሆኖ ያገለግል ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የሥነ ምግባር መሥፈርትን’ ወይም ደንብን እንዲሁም የተሰጠውን የአገልግሎት “ወሰን” ለማመልከት ካኖን የሚለውን የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። (ገላ. 6:16፤ 2 ቆሮ. 10:13) ስለዚህ ተቀባይነት ባገኙት ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት መጻሕፍት እውነተኛ የሆኑና በመንፈስ መሪነት የተጻፉ እንዲሁም ትክክለኛውን እምነት፣ መሠረተ ትምህርትና ምግባር ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል መለኪያ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው። እንደ ቱንቢ “ቀጥ ያሉ” መጻሕፍትን የማንጠቀም ከሆነ “የምንገነባው ሕንፃ” ጥሩ አይሆንም፤ በተጨማሪም በዋናው መሐንዲስ ዘንድ ተቀባይነት አያገኝም።
6 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን ለይቶ ማወቅ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት 66 መጻሕፍት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መሆናቸውን የሚያሳዩት አንዳንድ መለኮታዊ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው? በመጀመሪያ ደረጃ መጻሕፍቱ ይሖዋ በምድር ላይ ካከናወናቸው ነገሮች ጋር የተያያዙ፣ ሰዎችን ወደ እውነተኛው አምልኮ የሚመልሱ እንዲሁም ለአምላክ ስም፣ ለሥራውና ከምድር ጋር በተያያዘ ላሉት ዓላማዎች ጥልቅ አክብሮት እንዲያድርባቸው የሚያነሳሱ መሆን ይኖርባቸዋል። በአምላክ መንፈስ መሪነት ማለትም በቅዱስ መንፈሱ መሪነት የተጻፉ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ የያዙ መሆን አለባቸው። (2 ጴጥ. 1:21) ሰዎች በአጉል እምነት እንዲጠመዱ ወይም ፍጡራንን እንዲያመልኩ የሚያበረታቱ መሆን የለባቸውም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክን እንዲወዱና እንዲያገለግሉ የሚያበረታቱ መሆን ይገባቸዋል። በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ ያለው ሐሳብ ከጠቅላላው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር የሚጋጭ መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ መጽሐፍ ከሌሎቹ መጻሕፍት ጋር ስምምነት ሊኖረው የሚገባ ከመሆኑም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንጭ ይሖዋ አምላክ መሆኑን የሚደግፍ መሆን ይኖርበታል። እንዲሁም መጻሕፍቱ ጥቃቅን በሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ሊኖራቸው ይገባል። መሠረታዊ ከሆኑት ከእነዚህ መሥፈርቶች በተጨማሪ እንደየመጽሐፉ ይዘት በመንፈስ መሪነት የተጻፈና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆኑን የሚያሳዩ ሌሎች ማስረጃዎችም ይኖራሉ። እነዚህ ማስረጃዎች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ለእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በተሰጠው የማስተዋወቂያ ሐሳብ ላይ ተብራርተዋል። ከዚህም ሌላ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆኑትንና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆኑትን መጻሕፍት ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉ ሌሎች ማስረጃዎችም አሉ።
የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት
7 በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ቅዱስ ጽሑፍ፣ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ተጽፈው እስከተጠናቀቁበት እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ድረስ ተቀባይነት አላገኘም ነበር ብለን ማሰብ አይኖርብንም። እስራኤላውያን ሙሴ የጻፋቸውን መጻሕፍት ከመጀመሪያው አንስቶ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት አድርገው ተቀብለዋቸው ነበር። በዚያን ጊዜ በነበረው የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት የኦሪት መጻሕፍት ብቻ ነበሩ። ከዚያ በኋላ ይሖዋ ዓላማዎቹን በተመለከተ በመንፈሱ አማካኝነት ለሰዎች ተጨማሪ ራእዮችን የገለጠ ሲሆን እነዚህ ራእዮች በኦሪት መጻሕፍት ውስጥ እውነተኛውን አምልኮ በተመለከተ ከተገለጹት መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር መስማማት ይኖርባቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እያንዳንዱን መጽሐፍ ስንመረምር እንደተመለከትነው ሁሉም በተለይ ትንቢት በተነገረለት ዘር ማለትም በክርስቶስ በሚመራው መንግሥት አማካኝነት የይሖዋ ስም እንደሚቀደስና ሉዓላዊነቱ እንደሚረጋገጥ ስለሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ በሚናገሩበት ጊዜ ፍጹም የሆነ ስምምነት አላቸው።
8 የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በትንቢት የተሞሉ ናቸው። አንድ ትንቢት እውነተኛና ከአምላክ የመጣ መሆን አለመሆኑን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችለውን መሥፈርት በሙሴ በኩል የሰጠው ይሖዋ ራሱ ነው። ይህ ደግሞ አንድ የትንቢት መጽሐፍ ተቀባይነት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆን አለመሆኑን ለይቶ ለማወቅ ያስችላል። (ዘዳ. 13:1-3፤ 18:20-22) በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን እያንዳንዱን የትንቢት መጽሐፍ ከመላው መጽሐፍ ቅዱስና ከዓለም ታሪክ ጋር እያመሳከርን መመርመራችን ወደፊት የሚሆነውን አስመልክቶ በመጽሐፉ ውስጥ የተነገረው “ቃል” በይሖዋ ስም የተነገረ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ይረዳናል። እንዲሁም ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ‘የተፈጸመ ወይም እውነት ሆኖ የተገኘ’ መሆኑን ብሎም ሰዎችን ወደ አምላክ መመለሱን በማያሻማ ሁኔታ ለማረጋገጥ ያስችለናል። አንድ ትንቢት እውነተኛና በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው ሊባል የሚችለው እነዚህን መሥፈርቶች ካሟላ ነው።
9 ኢየሱስም ሆነ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት መጥቀሳቸው ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል ብዙዎቹ ተቀባይነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ጥሩ ማስረጃ ይሆነናል። እርግጥ ይህ መመዘኛ እንደ አስቴርና መክብብ ላሉት መጻሕፍት ላይሠራ ይችላል። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተካተቱት ተቀባይነት ያላቸው መጻሕፍት ዝርዝር ስናስብ ለሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚሠራ አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሌላ ነጥብ ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ፣ የሰው ልጆች ለእሱ ከሚያቀርቡት አምልኮና አገልግሎት ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ትምህርት እንዲቀስሙ፣ እንዲታነጹና እንዲበረታቱ ሲል ሰዎች በመንፈስ መሪነት መለኮታዊ ሐሳቡን በጽሑፍ እንዲያሠፍሩ እንዳደረገ ሁሉ ተቀባይነት ያላቸውን ቅዱሳን መጻሕፍት አሰባስበው አንድ ላይ እንዲያጠናቅሩ በመንፈሱ አማካኝነት ይመራቸዋል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው። ይህን የሚያደርገው የእውነት ቃሉም ሆነ የእውነተኛው አምልኮ መሥፈርት የሚገኘው በየትኞቹ መጻሕፍት ውስጥ እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ ተለይቶ እንዲታወቅ ሲል ነው። በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት ‘በአምላክ ቃል አማካይነት እንደ አዲስ መወለዳቸውን’ ሊቀጥሉና ‘የይሖዋ ቃል ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር’ ሊመሠክሩ የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው።—1 ጴጥ. 1:23, 25
10 የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ዝርዝር ማጠናቀር። የአይሁድ አፈ ታሪክ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆኑትን መጻሕፍት ማሰባሰብና ዝርዝሩን ማጠናቀር የጀመረው ዕዝራ እንደሆነና ይህን ሥራ ያጠናቀቀው ነህምያ እንደሆነ ይናገራል። ዕዝራ መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ መሪነት ከጻፉት ጸሐፊዎች አንዱ ከመሆኑም በላይ ካህን፣ ምሁርና የታወቀ ገልባጭ ስለነበረ ይህን ሥራ ለማከናወን ብቁ ነበር ማለት እንችላለን። (ዕዝራ 7:1-11) የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር የተጠናቀቀው በአምስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው የሚለውን ለረጅም ጊዜ የቆየ አመለካከት የምንጠራጠርበት አንዳችም ምክንያት የለም።
11 በአሁኑ ጊዜ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ 39 መጻሕፍት ሰፍረው እናገኛለን፤ ጥንታዊው የአይሁዶች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር እነዚህን መጻሕፍት በሙሉ ያካተተ ቢሆንም በ24 ከፍሎ አስቀምጧቸዋል። አንዳንድ የማመሳከሪያ ጽሑፎች ደግሞ ሩትንና መሳፍንትን እንዲሁም ሰቆቃወ ኤርምያስንና ኤርምያስን አንድ ላይ በማጣመር የመጻሕፍቱን ቁጥር ወደ 22 ያወርዱታል።b ይህም በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን መጻሕፍት ቁጥር ከዕብራይስጥ ሆሄያት ቁጥር ጋር እኩል አድርጎታል። መጻሕፍቱን በ24 የከፈለው ጥንታዊው የአይሁዶች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር የሚከተለው ነው፦
የሕጉ መጻሕፍት (ኦሪት)
1. ዘፍጥረት
2. ዘፀአት
3. ዘሌዋውያን
4. ዘኍልቁ
5. ዘዳግም
የትንቢት መጻሕፍት
6. ኢያሱ
7. መሳፍንት
8. ሳሙኤል (አንደኛውና ሁለተኛው እንደ አንድ መጽሐፍ ተቆጥረው)
9. ነገሥት (አንደኛውና ሁለተኛው እንደ አንድ መጽሐፍ ተቆጥረው)
10. ኢሳይያስ
11. ኤርምያስ
12. ሕዝቅኤል
13. አሥራ ሁለቱ የትንቢት መጻሕፍት (ሆሴዕ፣ ኢዩኤል፣ አሞጽ፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ሚክያስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስ እና ሚልክያስ እንደ አንድ መጽሐፍ ተቆጥረው)
መጽሐፎች (ሃጊዮግራፋ)
14. መዝሙር
15. ምሳሌ
16. ኢዮብ
17. ማሕልየ መሓልይ
18. ሩት
19. ሰቆቃወ ኤርምያስ
20. መክብብ
21. አስቴር
22. ዳንኤል
23. ዕዝራ (ነህምያ ከዕዝራ ጋር ተጠቃሏል)
24. ዜና መዋዕል (አንደኛውና ሁለተኛው እንደ አንድ መጽሐፍ ተቆጥረው)
12 ክርስቶስ ኢየሱስም ሆነ የጥንቱ ክርስቲያን ጉባኤ በመንፈስ መሪነት የተጻፉ አድርገው የተቀበሏቸው መጻሕፍት ዝርዝር ይህ ነው። በመንፈስ መሪነት የጻፉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች ይጠቅሱ የነበረው ከእነዚህ መጻሕፍት ብቻ ነበር። ከእነዚህ መጻሕፍት በሚጠቅሱበት ጊዜ “ተብሎ እንደተጻፈው ነው” እንደሚለው ያሉ መግለጫዎችን መጠቀማቸው መጻሕፍቱ የአምላክ ቃል እንደሆኑ ያረጋግጣል። (ሮም 15:9) ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናውንበት እስከነበረው ዘመን ድረስ በመንፈስ መሪነት ተጽፈው የተጠናቀቁትን ቅዱሳን መጻሕፍት “በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙራት” የተጻፉ እንደሆኑ ገልጿል። (ሉቃስ 24:44) “መዝሙር” የሃጊዮግራፋ የመጀመሪያ መጽሐፍ እንደመሆኑ መጠን እዚህ ጥቅስ ላይ በሃጊዮግራፋ ሥር የተዘረዘሩትን መጻሕፍት ሁሉ ለማመልከት ተሠርቶበታል። ተቀባይነት ባገኙት የዕብራይስጥ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የተካተተው የመጨረሻው የታሪክ መጽሐፍ ነህምያ ነው። ይህ የሆነው በአምላክ መንፈስ መሪነት ነው ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት አለ። “ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ” መሲሑ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ያሉትን 69 ትንቢታዊ ሳምንታት ለማስላት የሚያስችለውን መነሻ ዓመት የያዘው የነህምያ መጽሐፍ ብቻ መሆኑ ይህን የሚያረጋግጥ ነው። (ዳን. 9:25፤ ነህ. 2:1-8፤ 6:15) ከዚህም በተጨማሪ የነህምያ መጽሐፍ የመጨረሻው የትንቢት መጽሐፍ ለሆነው ለሚልክያስ መሠረት የሆነውን ታሪካዊ ሁኔታ ይገልጻል። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ሳይቀር ከሚልክያስ መጽሐፍ በተደጋጋሚ ጊዜያት መጥቀሱ ደግሞ ይህ መጽሐፍ በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ያረጋግጣል። (ማቴ. 11:10, 14) የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች ከነህምያና ከሚልክያስ በፊት ከተጻፉት ከአብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሱ የተናገሩ ቢሆንም ከነህምያና ከሚልክያስ በኋላ እስከ ክርስቶስ ዘመን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ከተጻፉት በመንፈስ መሪነት ተጽፈዋል ከሚባሉት መጽሐፎች ላይ ግን አልጠቀሱም። ይህም አይሁዶችና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር በነህምያና በሚልክያስ መጽሐፎች አብቅቷል የሚል የቆየ አመለካከትና እምነት እንደነበራቸው ያረጋግጥልናል።
በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጨመሩ አዋልድ መጻሕፍት
13 አዋልድ መጻሕፍት የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? እነዚህ መጻሕፍት አንዳንዶች በተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ያካተቷቸው ሆኖም በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ለመሆናቸው ማስረጃ የሌላቸው በመሆኑ ሌሎች የማይቀበሏቸው መጽሐፎች ናቸው። አዋልድ ተብሎ የተተረጎመው አፖክራይፎስ የሚለው ግሪክኛ ቃል ‘የተሸሸጉ’ ነገሮችን ያመለክታል። (ማር. 4:22፤ ሉቃስ 8:17፤ ቆላ. 2:3) ይህ ቃል ምንጫቸው በእርግጠኝነት የማይታወቅ መጻሕፍትን ወይም በግል ቢነበቡ በተወሰነ ደረጃ የሚያበረክቱት ጠቀሜታ እንዳለ ተደርጎ ቢታሰብም እንኳ በአምላክ መንፈስ መሪነት ለመጻፋቸው በቂ ማስረጃ ያልተገኘላቸው መጻሕፍትን ለማመልከት ይሠራበታል። እንዲህ ያሉት መጻሕፍት ተለይተው የተቀመጡና በሕዝብ ፊት የማይነበቡ ስለነበሩ ‘የተሸሸጉ’ ናቸው ማለት ይቻላል። በ397 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተካሄደው የካርቴጅ ጉባኤ ላይ ሰባት የአዋልድ መጻሕፍት በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንዲካተቱ እንዲሁም በመንፈስ መሪነት በተጻፉት የአስቴርና የዳንኤል መጻሕፍት ውስጥ ተጨማሪ ጽሑፍ እንዲታከል ሐሳብ ቀረበ። ይሁን እንጂ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በትሬንት ጉባኤ እስከተካሄደበት እስከ 1546 ድረስ እነዚህን ተጨማሪ መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አድርጋ በይፋ አልተቀበለቻቸውም ነበር። የተጨመሩት መጻሕፍት ጦቢት፣ ዮዲት፣ በአስቴር መጽሐፍ ላይ የተጨመረ ጽሑፍ፣ ጥበብ፣ ሲራክ፣ ባሮክ፣ በዳንኤል ላይ የተጨመሩ ሦስት ጽሑፎች፣ መቃብያን ቀዳማዊና መቃብያን ካልዕ ናቸው።
14 መቃብያን ቀዳማዊ የተሰኘው መጽሐፍ በምንም መንገድ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ ተደርጎ ሊቆጠር ባይችልም እንኳ ታሪካዊ መረጃ ይዟል። አይሁዳውያን በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የክህነት አገልግሎት ያከናውኑ በነበሩት የመቃብያን ቤተሰቦች አመራር ነፃ ለመውጣት ያደረጉትን ትግል ይተርካል። የተቀሩት አዋልድ መጻሕፍት በአፈ ታሪክና በአጉል እምነቶች እንዲሁም በስህተት የተሞሉ ናቸው። ኢየሱስም ሆነ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን የጻፉት ሰዎች ስለ እነዚህ መጻሕፍት ምንም የተናገሩት ነገር የሌለ ከመሆኑም በላይ ከእነዚህ መጽሐፎች ላይ አልጠቀሱም።
15 በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የኖረው አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ፍሌቪየስ ጆሴፈስ አጌነስት አፒየን (I, 38-41 [8]) በተባለው ጽሑፉ ላይ ዕብራውያን ቅዱስ መጻሕፍት አድርገው ይቀበሏቸው የነበሩትን ጽሑፎች በሙሉ ጠቅሷል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እርስ በርሳቸው የሚጋጩና የማይስማሙ በርካታ መጻሕፍት የሉንም። ትክክለኛ ተቀባይነት ያገኙት መጽሐፎቻችን ሃያ ሁለት [አንቀጽ 11 ላይ እንደተገለጸው በአሁኑ ጊዜ ያሉትን 39 መጻሕፍት የያዘ ነው] ሲሆኑ የሁሉንም ዘመናት ታሪክ የያዙ ናቸው። ከእነዚህ መካከል አምስቱ ሕጉንና ከሰው ልጅ መፈጠር አንስቶ ሕጉን ያስተላለፈው ሰው እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ያለውን የጥንት ታሪክ የሚዘግቡት የሙሴ መጻሕፍት ናቸው። . . . ሙሴ ከሞተበት ጊዜ አንስቶ በፋርሱ ንጉሥ በዜርሰስ እግር እስከተተካው እስከ አርጤክስስ ዘመን ድረስ ደግሞ ከሙሴ በኋላ የተነሱት ነቢያት በዘመናቸው የተከናወነውን ታሪክ በአሥራ ሦስት መጻሕፍት ውስጥ ዘግበዋል። የቀሩት አራት መጻሕፍት ደግሞ ለአምላክ የቀረቡ የውዳሴ መዝሙሮችንና ለሰው ልጆች የሚሆኑ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን የያዙ ናቸው።” በዚህ መንገድ ጆሴፈስ ተቀባይነት ያገኙት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ብዙ ዘመን ቀደም ብሎ የተጠናቀቀ መሆኑን አመልክቷል።
16 የላቲን ቩልጌት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምን በ405 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያጠናቀቀው የመጽሐፍ ቅዱሱ ምሁር ጀሮም በአዋልድ መጻሕፍት ረገድ የነበረው አቋም ግልጽ ነበር። በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን 39 መጻሕፍት ልክ ጆሴፈስ በቆጠረበት መንገድ 22 እንደሆኑ አድርጎ በመቁጠር በቩልጌት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ለሳሙኤልና ለነገሥት መጻሕፍት ባሰፈረው መቅድም ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በመሆኑም ሃያ ሁለት መጻሕፍት አሉ . . . ከእነዚህ መጻሕፍት ውጭ ያሉት ሁሉ በአዋልድ መጻሕፍት ውስጥ መካተት እንዳለባቸው እናውቅ ዘንድ ይህ የቅዱሳን መጻሕፍት መቅድም ከዕብራይስጥ ወደ ላቲን ለምንተረጉማቸው መጻሕፍት ሁሉ ሊያገለግል ይችላል።”
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት
17 የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ዝርዝር የተጠናቀረበትን የካርቴጅ ጉባኤ (397 ዓ.ም.) ማስረጃ አድርጋ በመጥቀስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መካተት ያለባቸው የትኞቹ መጻሕፍት እንደሆኑ የመወሰን መብት እንዳላት ትናገራለች። እውነታው ግን ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ ነው። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተካተቱትን መጻሕፍት ጨምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑት መጻሕፍት ዝርዝር በየትኛውም ጉባኤ ድንጋጌ ሳይሆን መጀመሪያውኑ እነዚህን መጻሕፍት ባስጻፈው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አመራር አስቀድሞ ተጠናቅቆ ነበር። ከጊዜ በኋላ የአምላክ መንፈስ አመራር ሳይኖራቸው የቅዱሳን መጻሕፍትን ዝርዝር ያዘጋጁ ሰዎች የሰጡት ምሥክርነት ቀድሞውኑ በአምላክ መንፈስ ድጋፍ የተዘጋጀውን የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ትክክለኝነት ከማረጋገጥ ውጭ የሚፈይደው ነገር አይኖርም።
18 የጥንት ካታሎጎች የሚሰጡት ማስረጃ። በዚህ ቡክሌት ላይ የሚገኘው ሰንጠረዥ እንደሚያሳየው ከላይ ከተጠቀሰው ጉባኤ አስቀድሞ በአራተኛው መቶ ዘመን ከተዘጋጁት ካታሎጎች መካከል አንዳንዶቹ የራእይ መጽሐፍን ያላካተቱ ከመሆናቸው በስተቀር ብዙዎቹ በአሁኑ ጊዜ ካለው የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ጋር አንድ ናቸው። ከሁለተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ በፊት አራቱ ወንጌሎች፣ የሐዋርያት ሥራና 12ቱ የሐዋርያው ጳውሎስ ደብዳቤዎች በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ነበራቸው። ከትናንሾቹ መጻሕፍት ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ በአንዳንድ አካባቢዎች ሙሉ ተቀባይነት አላገኙም ነበር። ይህ የሆነው እነዚህ መጻሕፍት መጀመሪያ ላይ በሆነ ምክንያት በስፋት ባለመሠራጨታቸው ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም ተቀባይነት አግኝተው በቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ረዘም ካለ ጊዜ በኋላ ነው።
19 ከፍተኛ ጠቀሜታ ካላቸው ጥንታዊ ካታሎጎች መካከል ኤል ኤ ሙራቶሪ ጣሊያን ውስጥ በሚላን ከተማ በአምብሮዚያን ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ያገኙትና በ1740 ያሳተሙት የካታሎግ ቁራጭ ይገኝበታል። የዚህ ካታሎግ የመጀመሪያ ክፍል ያልተገኘ ቢሆንም እንኳ ሉቃስን ሦስተኛ ወንጌል አድርጎ መጥቀሱ መጀመሪያ ላይ ማቴዎስንና ማርቆስን እንደጠቀሰ ይጠቁማል። በላቲን ቋንቋ የተጻፈው ይህ ካታሎግ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ መጨረሻ አካባቢ የተዘጋጀ ነው። ከዚህ ቀጥሎ በከፊል የቀረበው ትርጉም ይህ ካታሎግ በጣም ጠቃሚ ሰነድ እንደሆነ ያሳያል፦ “ሦስተኛውን የወንጌል መጽሐፍ የጻፈው ሉቃስ ነው። ታዋቂ ሐኪም የነበረው ሉቃስ ወንጌሉን የሰየመው በራሱ ስም ነው . . . አራተኛውን ወንጌል የጻፈው ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነው ዮሐንስ ነው። . . . በእያንዳንዱ የወንጌል መጽሐፍ ውስጥ የሠፈረው ታሪክ የቀረበበት መንገድ ሊለያይ ቢችልም በአማኞቹ መካከል የእምነት ልዩነት አልነበረም። ምክንያቱም ሁሉም [ወንጌሎች] በአምላክ መንፈስ አመራር ስለ ኢየሱስ ልደት፣ ስለደረሰበት ሥቃይ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ስላደረገው ውይይት እንዲሁም በሁለት መንገድ ስለመገለጡ ይኸውም በመጀመሪያ ተንቆና ተዋርዶ እንደተገለጠና ወደፊት ደግሞ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ይዞ በክብር እንደሚገለጥ ዘግበዋል። እንግዲያው ዮሐንስ እነዚህን ነገሮች በመልእክቶቹ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተመሳሳይ በሆነ መንገድ መጥቀሱ ምንም አያስገርምም። እሱ ራሱ ‘የጻፍነው በዓይናችን ያየነውን፣ በጆሯችን የሰማነውንና በእጆቻችን የዳሰስነውን ነገር ነው’ ሲል ተናግሯል። በመሆኑም ዮሐንስ ጌታ ያከናወናቸውን ድንቅ ነገሮች ሁሉ በዓይኑ ከመመልከት በተጨማሪ በጆሮው እንደሰማና በቅደም ተከተላቸው መሠረት እንደተረከ ገልጿል። ከዚህም ሌላ ሐዋርያት ያከናወኗቸው ሥራዎች በሙሉ በአንድ መጽሐፍ ተጽፈዋል። ሉቃስ ለክቡር ቴዎፍሎስ [በዚህ መንገድ] አቀናብሮ ጽፏቸዋል . . . የጳውሎስ መልእክቶች የማወቅ ጉጉት አድሮበት ለሚያነባቸው ሰው ምን ይዘት እንዳላቸው፣ ከየት እንደተላኩ ወይም ለምን ዓላማ እንደተጻፉ መልእክቶቹ ራሳቸው ግልጽ ያደርጉለታል። በመጀመሪያ የቆሮንቶስ ሰዎች በኑፋቄ ትምህርት እንዳይከፋፈሉ ረዘም ያለ መልእክት ጻፈላቸው፤ ከዚያም ለገላትያ ሰዎች ስለ ግዝረት፣ ለሮም ሰዎች ደግሞ ቅዱሳን መጻሕፍት በዋነኝነት የሚያተኩሩት በክርስቶስ ላይ እንደሆነ በመግለጽ እነዚህ መጻሕፍት ስለተዘጋጁበት ቅደም ተከተል ጻፈ። ቅዱሱ ሐዋርያ ጳውሎስ ራሱ ከእሱ በፊት የነበረውን የዮሐንስን ምሳሌ በመከተል በሚከተለው ቅደም ተከተል መሠረት ከሰባት የማይበልጡ ቤተ ክርስቲያናትን በስም በመጥቀስ የጻፈላቸው በመሆኑ እያንዳንዱን መልእክት መመርመራችን አስፈላጊ ነው፦ ለቆሮንቶስ ሰዎች (አንደኛ)፣ ለኤፌሶን ሰዎች (ሁለተኛ)፣ ለፊልጵስዩስ ሰዎች (ሦስተኛ)፣ ለቆላስይስ ሰዎች (አራተኛ)፣ ለገላትያ ሰዎች (አምስተኛ)፣ ለተሰሎንቄ ሰዎች (ስድስተኛ) እና ለሮም ሰዎች (ሰባተኛ)። ለቆሮንቶስና ለተሰሎንቄ ሰዎች እርማት ለመስጠት ሲል ለእያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ የጻፈ ቢሆንም [? በእነዚህ ሰባት መልእክቶች እንደታየው] በመላው ዓለም ተሰራጭቶ የሚገኘው አንድ ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ዮሐንስም በራእይ መጽሐፍ ላይ ለሰባት ቤተ ክርስቲያናት የጻፈ ቢሆንም መልእክቱን ያስተላለፈው ለሁሉም ነው። ሆኖም በፍቅር ተገፋፍቶ ለፊልሞና አንድ፣ ለቲቶ አንድ እንዲሁም ለጢሞቴዎስ ሁለት መልእክቶች [ጽፏል]፤ ቤተ ክርስቲያን [ለእነዚህ መልእክቶች] ከፍ ያለ ግምት በመስጠት ቅዱስ አድርጋ ትመለከታቸዋለች። . . . ከዚህም በተጨማሪ የይሁዳ መልእክትና በዮሐንስ ስም የተጻፉ ሁለት መልእክቶች ተካትተዋል . . . አንዳንዶቻችን [ከጊዜ በኋላ] በቤተ ክርስቲያን እንዲነበቡ ያልፈለግናቸውን የዮሐንስና የጴጥሮስ ራእዮች ብቻ ተቀብለናል።”—ዘ ኒው ሻፍ-ሄርዞግ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅየስ ኖውሌጅ፣ 1956፣ ጥራዝ VIII ገጽ 56
20 በሙራቶሪያን ካታሎግ የመጨረሻ ክፍል ላይ ከዮሐንስ መልእክቶች መካከል የተጠቀሱት ሁለቱ ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሰው ኢንሳይክሎፒዲያ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ገጽ 55 ላይ እንደሚገልጸው እነዚህ ሁለት የዮሐንስ መልእክቶች “ሁለተኛውና ሦስተኛው መልእክቶች መሆን አለባቸው፤ የእነዚህ መልእክቶች ጸሐፊ ራሱን ‘ሽማግሌው’ ብቻ ብሎ ጠርቷል። የካታሎጉ አዘጋጅ በአጋጣሚ የመጀመሪያውን መልእክት ከአራተኛው ወንጌል ጋር አያይዞ በመጥቀሱና ጸሐፊው ዮሐንስ መሆኑን በእርግጠኝነት እንደሚያምን በመግለጹ እዚህ ቦታ ላይ ሁለቱን ትናንሽ ደብዳቤዎች ብቻ መጥቀስ እንደሚችል ተሰምቶታል።” ኢንሳይክሎፒዲያው የመጀመሪያው የጴጥሮስ መልእክት ሳይጠቀስ የታለፈ የሚመስልበትን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ከሁሉ ይበልጥ የሚታመንበት መላ ምት አንደኛ ጴጥሮስንና የዮሐንስን ራእይ እንደተቀበሉ የሚገልጹትን ጥቂት ቃላት የያዘው መስመር ጎድሎ ሊሆን ይችላል የሚል ነው።” በመሆኑም ይህ ኢንሳይክሎፒዲያ የሙራቶሪያን ካታሎግ ካሰፈረው ሐሳብ በመነሳት ገጽ 56 ላይ እንደሚከተለው ሲል ደምድሟል፦ “አዲስ ኪዳን አራቱን ወንጌሎች፣ የሐዋርያት ሥራን፣ አሥራ ሦስቱን የጳውሎስ መልእክቶች፣ የዮሐንስን ራእይና ምናልባትም ሦስቱን መልእክቶቹን፣ ይሁዳን፣ ምናልባትም ደግሞ አንደኛ ጴጥሮስን ያካተተ እንደሆነ በእርግጠኝነት ይታመናል፤ ሌላኛውን የጴጥሮስ መልእክት በተመለከተ የሚሰነዘረው ተቃውሞ ግን ገና ምላሽ አላገኘም።”
21 በ230 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ኦሪጀን በሙራቶሪያን ካታሎግ ቁራጭ ላይ ያልተጠቀሱትን የዕብራውያንና የያዕቆብ መጽሐፎች በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል አድርጎ ተቀብሏቸዋል። ኦሪጀን እነዚህ መጻሕፍት የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ስለመሆናቸው አንዳንዶች ጥርጣሬ እንዳላቸው ያመለከተ ቢሆንም ይህ ራሱ በዚያ ወቅት ጥቂቶች ብዙም የማይታወቁትን የተወሰኑ መልእክቶች በተመለከተ ጥርጣሬ የነበራቸው ከመሆኑ በስተቀር ከግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል አብዛኞቹ በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መሆናቸው ይታመንበት እንደነበረ ያሳያል። ከጊዜ በኋላ አትናቴዎስ፣ ጀሮም እና ኦገስቲን በአሁኑ ጊዜ እኛ የምንጠቀምባቸው 27ቱ መጻሕፍት ተቀባይነት ያላቸው የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል እንደሆኑ በመግለጽ የጥንቶቹ የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝሮች የደረሱበትን መደምደሚያ አምነው ተቀብለዋል።c
22 በሰንጠረዡ ላይ ያሉት አብዛኞቹ ካታሎጎች ተቀባይነት ያገኙት ቅዱሳን መጻሕፍት የትኞቹ እንደሆኑ በግልጽ ያሳያሉ። የኢራኒየስ፣ የእስክንድርያው ክሌመንት፣ የተርቱሊያንና የኦሪጀን ካታሎጎች የተዘጋጁት እነዚህ ሰዎች ለጽሑፎቹ ያላቸውን አመለካከት ከሚገልጹት አስተያየቶቻቸው በመነሳት ነው። እነዚህ ካታሎጎች የጥንቱ ታሪክ ጸሐፊ ዩሲቢየስ ካሰፈራቸው ዘገባዎች በተወሰዱ መረጃዎች እንዲሟሉ ተደርጓል። ይሁን እንጂ እነዚህ ጸሐፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን አንዳንድ መጻሕፍት አለመጥቀሳቸው እነዚህ መጻሕፍት የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል አይደሉም ሊያሰኝ አይችልም። ይህ ሊሆን የቻለው አንድም እነዚህን መጻሕፍት በጽሑፎቻቸው ውስጥ መጥቀስ ስላልፈለጉ አሊያም ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ስለማይያያዝ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ከሙራቶሪያን ካታሎግ በፊት የነበሩ ትክክለኛ የሆኑና የተሟሉ የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝሮችን ማግኘት ያልቻልነው ለምንድን ነው?
23 ክርስቲያኖች ሊቀበሏቸው የሚገቡት የትኞቹን መጻሕፍት እንደሆነ አከራካሪ ሁኔታ የተነሳው በሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ዓ.ም. እንደ ማርሲዮን ያሉ ሃያሲያን ብቅ ካሉ በኋላ ነው። ማርሲዮን የራሱን መሠረተ ትምህርቶች ለመደገፍ ሲል ከጳውሎስ መልእክቶች መካከል የተወሰኑትን ብቻ በመውሰድና በሉቃስ ወንጌል ላይ ማስተካከያ በማድረግ የራሱን የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር አዘጋጅቷል። ማርሲዮን ይህን ማድረጉና በዚያን ጊዜ በዓለም ዙሪያ በርካታ አዋልድ መጻሕፍት መሠራጨታቸው ካታሎግ የሚያዘጋጁ ሰዎች ተቀባይነት ያላቸው ቅዱሳን መጻሕፍት የትኞቹ እንደሆኑ ለይተው እንዲናገሩ አነሳስቷቸዋል።
24 አዋልድ ጽሑፎች። በመንፈስ መሪነት በተጻፉት የክርስቲያን መጻሕፍትና ያለ አምላክ መንፈስ ድጋፍ በተጻፉት የሐሰት ጽሑፎች መካከል ያለውን ልዩነት ከጽሑፎቹ ይዘት በግልጽ መረዳት ይቻላል። አዋልድ ጽሑፎች ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ሲነጻጸሩ ተራ ከመሆናቸውም በላይ አብዛኛውን ጊዜ ከእውነታ የራቁና ከልጆች መጻሕፍት የማይሻሉ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በስህተት የተሞሉ ናቸው።d ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያልሆኑትን እነዚህን መጻሕፍት አስመልክተው የሰጧቸውን የሚከተሉትን አስተያየቶች ተመልከት፦
“እነዚህን ጽሑፎች ማንም ሰው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ባያካትታቸው ምንም አያስገርምም፤ ጽሑፎቹ ራሳቸው ራሳቸውን ያገለሉ ናቸው።”—ኤም አር ጄምስ፣ ዚ አፖክሪፋል ኒው ቴስታመንት፣ ገጽ xi, xii
“በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተካተቱትን መጻሕፍት በሙሉ ከሌሎቹ መጻሕፍት ጋር በማወዳደር በመካከላቸው ያለውን ሰፊ ልዩነት መገንዘብ እንችላለን። ብዙውን ጊዜ እንደሚባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያልሆኑት ወንጌሎች ለእውነተኞቹ ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኝነት ከሁሉ የተሻሉ ማስረጃዎች ናቸው።”—ጂ ሚሊጋን፣ ዘ ኒው ቴስታመንት ዶክመንትስ፣ ገጽ 228
“ቤተ ክርስቲያን ጠብቃ ካቆየቻቸው የጥንት ጽሑፎች መካከል በዛሬው ጊዜ በቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ሊካተት ይገባዋል የሚባል አንድም የረባ ጽሑፍ የለም።”—ኬ አላንድ፣ ዘ ፕሮብለም ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ካነን፣ ገጽ 24
25 በመንፈስ መሪነት የጻፉ ጸሐፊዎች። መነሳት የሚገባው ሌላም ነጥብ አለ። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን የጻፉት ጸሐፊዎች ኢየሱስ በቀጥታ የመረጣቸውን ሐዋርያት ያካተተው የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ የበላይ አካል አባላት ወይም ከዚህ አካል ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ናቸው። ማቴዎስ፣ ዮሐንስና ጴጥሮስ ከመጀመሪያዎቹ 12 ሐዋርያት መካከል የነበሩ ሲሆን ጳውሎስ ከ12ቱ አንዱ ባይሆንም ከጊዜ በኋላ ሐዋርያ ሆኖ የተመረጠ ሰው ነው።e ምንም እንኳ ጳውሎስ በጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ለየት ባለ ሁኔታ በወረደበት ጊዜ በቦታው ያልነበረ ቢሆንም ያዕቆብንና ይሁዳን ምናልባትም ማርቆስን ጨምሮ ማቴዎስ፣ ዮሐንስና ጴጥሮስ በዚያ ነበሩ። (ሥራ 1:13, 14) ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ የጻፋቸውን መልእክቶች ‘ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት’ ጋር ደምሯቸዋል። (2 ጴጥ. 3:15, 16) ማርቆስና ሉቃስ የጳውሎስና የጴጥሮስ የቅርብ አጋሮችና የጉዞ ጓደኞች ነበሩ። (ሥራ 12:25፤ 1 ጴጥ. 5:13፤ ቆላ. 4:14፤ 2 ጢሞ. 4:11) እነዚህ ሁሉ ጸሐፊዎች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት አስደናቂ ችሎታዎች ተሰጥተዋቸው ነበር። ይህን ልዩ ችሎታ ያገኙት በጴንጤቆስጤ ዕለትና ጳውሎስ ወደ ክርስትና በተለወጠበት ጊዜ እንደተከሰተው ልዩ በሆነ መንገድ መንፈስ ቅዱስ ወርዶባቸው አሊያም በሉቃስ ሁኔታ ላይ እንደታየው ሐዋርያት እጃቸውን ጭነውባቸው ነው። (ሥራ 8:14-17፤ 9:17, 18) የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በሙሉ ተጽፈው ያበቁት የመንፈስ ቅዱስ ልዩ ስጦታዎች በነበሩበት ጊዜ ውስጥ ነው።
26 ቃሉን በመንፈሱ አማካኝነት ባስጻፈውና እስከ ዛሬ ድረስ ተጠብቆ እንዲቆይ ባደረገው ሁሉን ቻይ አምላክ ላይ ያለን እምነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በሙሉ አንድ ላይ እንዲሰባሰቡ አመራር የሰጠው እሱ መሆኑን እንድናምን ያደርገናል። ስለዚህ 39ኙን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት እና 27ቱን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በይሖዋ አምላክ አመራር የተጻፈ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ አድርገን እንቀበላቸዋለን። በ66ቱ መጻሕፍት ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘው ቃሉ መመሪያችን ነው። ይህ ቃል እርስ በርሱ የሚስማማና ሚዛናዊ መሆኑ ፍጹም የተሟላ እንደሆነ ያሳያል። ወደር የማይገኝለት የዚህ መጽሐፍ ምንጭ የሆነው ይሖዋ አምላክ ሊወደስ ይገባዋል! ቃሉ ሙሉ በሙሉ የታጠቅን እንድንሆንና በሕይወት ጎዳና እንድንጓዝ ይረዳናል። እንግዲያው በማንኛውም አጋጣሚ በሚገባ እንጠቀምበት።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ባይብሎስ ፓፒረስ ከተባለው ተክል ለጽሑፍ የሚያገለግል ወረቀት የሚሠራባት ቦታ ነበረች። ከጊዜ በኋላ ቢብሊያ የሚለው ቃል የተለያዩ መጣጥፎች፣ ጥቅልሎች፣ መጽሐፎች ብሎም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑት ትናንሽ መጻሕፍት ስብስብ መጠሪያ ሆነ።
b ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ፣ 1973፣ ጥራዝ 4፣ አምድ 826, 827
c ዘ ቡክስ ኤንድ ዘ ፓርችመንትስ፣ 1963፣ ኤፍ ኤፍ ብሩስ፣ ገጽ 112
d ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1 ገጽ 122-125
e ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1 ገጽ 129-130
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ
የላቀ ግምት የሚሰጣቸው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥንታዊ ካታሎጎች ስም እና ቦታ
ተ - የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያገኘ
አ - በተወሰነ መጠን አጠራጣሪ
አተ - በተወሰነ መጠን አጠራጣሪ፣ ሆኖም የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑ ካታሎጉን ባዘጋጀው ሰው ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ
? - ምሑራን ስለ ጽሑፉ አነባበብ ወይም የካታሎጉ አዘጋጆች ስለ መጽሐፉ ምን አመለካከት እንደነበራቸው እርግጠኞች አይደሉም
- ክፍት የተተወው ቦታ ካታሎጉን ያዘጋጁት ሰዎች መጽሐፉን እንዳልተጠቀሙበት ወይም እንዳልጠቀሱት ያመለክታል
ስም እና ቦታ
የሙራቶሪ ካታሎግ ኢራንየስ የእስክንድሪያው ተርቱሊያን
ቁራጭ ትንሹ እስያ ክሌመንት ሰሜን አፍሪካ
ጣሊያን
በ . . . ዓ.ም.
ገደማ 170 180 190 207
ማቴዎስ ተ ተ ተ ተ
ማርቆስ ተ ተ ተ ተ
ሉቃስ ተ ተ ተ ተ
ዮሐንስ ተ ተ ተ ተ
የሐዋርያት ሥራ ተ ተ ተ ተ
ሮም ተ ተ ተ ተ
1 ቆሮንቶስ ተ ተ ተ ተ
2 ቆሮንቶስ ተ ተ ተ ተ
ገላትያ ተ ተ ተ ተ
ኤፌሶን ተ ተ ተ ተ
ፊልጵስዩስ ተ ተ ተ ተ
ቆላስይስ ተ ተ ተ ተ
1 ተሰሎንቄ ተ ተ ተ ተ
2 ተሰሎንቄ ተ ተ ተ ተ
1 ጢሞቴዎስ ተ ተ ተ ተ
2 ጢሞቴዎስ ተ ተ ተ ተ
ቲቶ ተ ተ ተ ተ
ፊልሞና ተ ተ
ዕብራውያን አ አተ አተ
ያዕቆብ ?
1 ጴጥሮስ ተ? ተ ተ ተ
2 ጴጥሮስ አ? ተ
1 ዮሐንስ ተ ተ አተ ተ
2 ዮሐንስ ተ ተ አተ
3 ዮሐንስ ተ?
ይሁዳ ተ አተ ተ
ራእይ ተ ተ ተ ተ
ስም እና ቦታ
ኦሪጀን ዩሲቢየስ የኢየሩሳሌሙ የቼልተንሃም
እስክንድርያ ፓለስቲና ሲረል ዝርዝር
ሰሜን አፍሪካ
በ . . . ዓ.ም.
ገደማ 230 320 348 365
ማቴዎስ ተ ተ ተ ተ
ማርቆስ ተ ተ ተ ተ
ሉቃስ ተ ተ ተ ተ
ዮሐንስ ተ ተ ተ ተ
የሐዋርያት ሥራ ተ ተ ተ ተ
ሮም ተ ተ ተ ተ
1 ቆሮንቶስ ተ ተ ተ ተ
2 ቆሮንቶስ ተ ተ ተ ተ
ገላትያ ተ ተ ተ ተ
ኤፌሶን ተ ተ ተ ተ
ፊልጵስዩስ ተ ተ ተ ተ
ቆላስይስ ተ ተ ተ ተ
1 ተሰሎንቄ ተ ተ ተ ተ
2 ተሰሎንቄ ተ ተ ተ ተ
1 ጢሞቴዎስ ተ ተ ተ ተ
2 ጢሞቴዎስ ተ ተ ተ ተ
ቲቶ ተ ተ ተ ተ
ፊልሞና ተ ተ ተ ተ
ዕብራውያን አተ አተ ተ
ያዕቆብ አተ አተ ተ
1 ጴጥሮስ ተ ተ ተ ተ
2 ጴጥሮስ አተ አተ ተ አ
1 ዮሐንስ ተ ተ ተ ተ
2 ዮሐንስ አተ አተ ተ አ
3 ዮሐንስ አተ አተ ተ አ
ይሁዳ አተ አተ ተ
ራእይ ተ አተ ተ
ስም እና ቦታ
አትናቴዎስ ኤፒፋኒየስ ግሪጎሪ አምፊሎሲየስ
እስክንድርያ ፓለስቲና ናዚያንዙስ ትንሹ እስያ
ትንሹ እስያ
በ . . . ዓ.ም.
ገደማ 367 368 370 370
ማቴዎስ ተ ተ ተ ተ
ማርቆስ ተ ተ ተ ተ
ሉቃስ ተ ተ ተ ተ
ዮሐንስ ተ ተ ተ ተ
የሐዋርያት ሥራ ተ ተ ተ ተ
ሮም ተ ተ ተ ተ
1 ቆሮንቶስ ተ ተ ተ ተ
2 ቆሮንቶስ ተ ተ ተ ተ
ገላትያ ተ ተ ተ ተ
ኤፌሶን ተ ተ ተ ተ
ፊልጵስዩስ ተ ተ ተ ተ
ቆላስይስ ተ ተ ተ ተ
1 ተሰሎንቄ ተ ተ ተ ተ
2 ተሰሎንቄ ተ ተ ተ ተ
1 ጢሞቴዎስ ተ ተ ተ ተ
2 ጢሞቴዎስ ተ ተ ተ ተ
ቲቶ ተ ተ ተ ተ
ፊልሞና ተ ተ ተ ተ
ዕብራውያን ተ ተ ተ አተ
ያዕቆብ ተ ተ ተ ተ
1 ጴጥሮስ ተ ተ ተ ተ
2 ጴጥሮስ ተ ተ ተ አ
1 ዮሐንስ ተ ተ ተ ተ
2 ዮሐንስ ተ ተ ተ አ
3 ዮሐንስ ተ ተ ተ አ
ይሁዳ ተ ተ ተ አ
ራእይ ተ አተ አ
ስም እና ቦታ
ፊላስተር ጀሮም፣ ኦገስቲን ሦስተኛው
ጣሊያን ጣሊያን ሰሜን አፍሪካ የካርቴጅ ጉባኤ
ሰሜን አፍሪካ
በ . . . ዓ.ም.
ገደማ 383 394 397 397
ማቴዎስ ተ ተ ተ ተ
ማርቆስ ተ ተ ተ ተ
ሉቃስ ተ ተ ተ ተ
ዮሐንስ ተ ተ ተ ተ
የሐዋርያት ሥራ ተ ተ ተ ተ
ሮም ተ ተ ተ ተ
1 ቆሮንቶስ ተ ተ ተ ተ
2 ቆሮንቶስ ተ ተ ተ ተ
ገላትያ ተ ተ ተ ተ
ኤፌሶን ተ ተ ተ ተ
ፊልጵስዩስ ተ ተ ተ ተ
ቆላስይስ ተ ተ ተ ተ
1 ተሰሎንቄ ተ ተ ተ ተ
2 ተሰሎንቄ ተ ተ ተ ተ
1 ጢሞቴዎስ ተ ተ ተ ተ
2 ጢሞቴዎስ ተ ተ ተ ተ
ቲቶ ተ ተ ተ ተ
ፊልሞና ተ ተ ተ ተ
ዕብራውያን አተ አተ ተ ተ
ያዕቆብ ተ አተ ተ ተ
1 ጴጥሮስ ተ ተ ተ ተ
2 ጴጥሮስ ተ አተ ተ ተ
1 ዮሐንስ ተ ተ ተ ተ
2 ዮሐንስ ተ አተ ተ ተ
3 ዮሐንስ ተ አተ ተ ተ
ይሁዳ ተ አተ ተ ተ
ራእይ አተ አተ ተ ተ