በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት እና የኋላ ታሪካቸው ጥናት
ጥናት ቁጥር 5—የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት
በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል የሆኑት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተገለበጡት፣ የጽሑፎቹ ይዘት ሳይለወጥ ተጠብቀው የቆዩልንና ለዘመናችን የተላለፉልን እንዴት እንደሆነ።
በጽሑፍ የሰፈረው ‘የይሖዋ ቃል’ አስደናቂ በሆነ በመንፈስ የተጻፉ ሰነዶች ባሕር ውስጥ በተጠራቀሙ የእውነት ወንዞች ሊመሰል ይችላል። ይሖዋ ሐሳቡን ከሰማይ ወደ ምድር ባስተላለፈባቸው ዘመናት በሙሉ እነዚህ “ወንዞች” አንድ ላይ እንዲሰባሰቡና ተቀድቶ የማያልቅ ሕይወት ሰጪ የመረጃዎች ምንጭ እንዲሆኑ በማድረጉ ምንኛ አመስጋኞች ነን! የነገሥታት ዘውዶች፣ ቅርሶችና ሐውልቶችን የመሳሰሉ የጥንት ሀብቶች ብዙ ዘመን ከመቆየታቸው የተነሳ ሲዝጉና ሲሸረሸሩ እንዲሁም ሲፈራርሱ፣ እንደ ውድ ንብረት የሚቆጠሩት የአምላካችን ቃላት ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም ይኖራሉ። (ኢሳ. 40:8) ይሁን እንጂ እነዚህ የእውነት ወንዞች ወደ ባሕሩ ከገቡ በኋላ ተበክለው ይሆን የሚል ጥያቄ ይነሳል። ሳይበላሹና ሳይበረዙ ቆይተዋል? ባሁኑ ጊዜ በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ለምድር ሕዝቦች በሙሉ የተዳረሱት ቅጂዎች ይዘታቸው ሳይለወጥ ከመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች በታማኝነት ተላልፈዋል? የዚህ ባሕር አንደኛ ክፍል የሆኑት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛነታቸውን ጠብቆ ለማኖር ምን ያህል ጥንቃቄ እንደተደረገ እንዲሁም በተለያዩ እትሞችና አዳዲስ ትርጉሞች ለምድር ሕዝቦች በሙሉ እንዲዳረሱ እንዴት ያለ አስደናቂ ዝግጅት እንደተደረገ ለማወቅ በምናደርገው ጥናት በጣም እንደነቃለን።
2 በዕብራይስጥና በአረማይክ ቋንቋዎች የተዘጋጁት የመጀመሪያዎቹ ሰነዶች አምላክ በመረጣቸው ሰብዓዊ ጸሐፊዎች አማካኝነት በጽሑፍ የሰፈሩት ከሙሴ ዘመን፣ ከ1513 አንስቶ እስከ 443 ዓ.ዓ. ድረስ ነው። እስከዛሬ በተገኘው መረጃ መሠረት ከእነዚህ የመጀመሪያ ጽሑፎች መካከል በአሁኑ ጊዜ አንዳቸውም አይገኙም። ይሁን እንጂ ከመጀመሪያው አንስቶ እነዚህን በመንፈስ የተጻፉ መጻሕፍትም ሆነ ትክክለኛነታቸው የተረጋገጡትን ቅጂዎች ጠብቆ ለማቆየት ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። በ642 ዓ.ዓ. አካባቢ በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን በኩረ ጽሑፉ እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚታሰብ፣ ሙሴ ራሱ የጻፈው ‘የሕጉ መጽሐፍ’ በይሖዋ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ተገኘ። ይህ መጽሐፍ በዚህ ጊዜ የ871 ዓመት ዕድሜ ነበረው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የነበረው ኤርምያስ ለዚህ ግኝት ከፍተኛ ግምት በመስጠቱ መጽሐፉ ስለተገኘበት ሁኔታ በ2 ነገሥት 22:8-10 ላይ ሲጽፍ ዕዝራ ደግሞ በ460 ዓ.ዓ. ገደማ ይህንኑ ሁኔታ በድጋሚ ገልጾታል። (2 ዜና 34:14-18) ዕዝራ “የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ” ስለነበረ እንደነዚህ ላሉት ጉዳዮች ትልቅ ግምት ይሰጥ ነበር። (ዕዝራ 7:6 የ1954 ትርጉም) በመንፈስ የተጻፉትን አንዳንድ በኩረ ጽሑፎች ጨምሮ በጊዜው ተዘጋጅተው የነበሩትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ሌሎች ጥቅልሎች ማግኘት ይችል እንደነበረ አያጠራጥርም። በእርግጥም ዕዝራ በዘመኑ የመለኮታዊ ጽሑፎች ባለ አደራና ጠባቂ የነበረ ይመስላል።—ነህ. 8:1, 2
ቅዱሳን መጻሕፍት ይገለበጡ የነበረበት ዘመን
3 ከዕዝራ ዘመን በኋላ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ተፈላጊነት በጣም ጨመረ። በ537 ዓ.ዓ. በተከናወነው ተሐድሶና ከዚያ በኋላ በነበረው ጊዜ ሁሉም አይሁዶች ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ፓለስቲና ምድር አልተመለሱም። በሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያን በባቢሎን ሲቀሩ ሌሎቹ ደግሞ በንግድና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ወደተለያዩ አገሮች ተበትነው በጥንቱ ዓለም በነበሩ ታላላቅ የንግድ ማዕከል በሆኑ ከተሞች ይኖሩ ነበር። ብዙ አይሁዳውያን በቤተ መቅደሱ ይከናወኑ በነበሩ ዓመታዊ በዓላት ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳቸው መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ ይከናወኑ በነበሩ የአምልኮ ሥርዓቶች ላይ እንዲገኙ አስችሏቸዋል። በዕዝራ ዘመን በእነዚህ ራቅ ያሉ አገሮች ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የሚነበቡባቸውና ውይይት የሚደረጉባቸው ምኩራብ ተብለው የሚጠሩ የመሰብሰቢያ ቦታዎች በየከተሞቻቸው መሥራት ጀመሩ።a እነዚህ የአምልኮ ቦታዎች በጣም በርካታና በተለያዩ አካባቢዎች የተበታተኑ በመሆናቸው ገልባጮች በእጅ የተጻፉ ብዙ ግልባጮችን ማዘጋጀት ነበረባቸው።
4 እነዚህ ምኩራቦች ገኒዛ ተብሎ የሚጠራ ግምጃ ቤት ነበራቸው። ከጊዜ በኋላ አይሁዳውያን የተቀደዱትን ወይም በእርጅና ምክንያት የተበላሹ መጻሕፍትን በገኒዛ ውስጥ እያስቀመጡ በአዳዲስ መጻሕፍት መገልገል ጀመሩ። ይሖዋ የተባለው ቅዱስ ስም የሰፈረበት ጽሑፍ እንዳይረክስ በማሰብ በገኒዛ ውስጥ የተከማቹትን መጻሕፍት በየተወሰነ ጊዜው መሬት ውስጥ በሥርዓት መቅበር ተጀመረ። በበርካታ መቶ ዓመታት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ አሮጌ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ግልባጮች በዚህ መንገድ ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል። ይሁን እንጂ በድሮው ካይሮ ይገኝ በነበረው ምኩራብ ገኒዛ ውስጥ የተጠራቀሙት በርካታ ጽሑፎች ይህ ዕጣ አልደረሰባቸውም። ይህም የሆነው በግንብ በመታጠሩና እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ድረስ ተረስቶ በመቆየቱ እንደሆነ ይገመታል። በ1890 ምኩራቡ በሚጠገንበት ጊዜ በገኒዛው ውስጥ የነበሩት ጽሑፎች ይዘት ዳግመኛ የተመረመረ ሲሆን ቀስ በቀስም በስጦታና በሽያጭ መልክ ተወስደው አለቁ። ከዚህ ቦታ፣ ሙሉ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ናቸው ሊባሉ የሚችሉና በሺህ የሚቆጠሩ ቁርጥራጮች (አንዳንዶቹ በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንደተጻፉ ይነገራል) ወደ ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት እንዲሁም በአውሮፓና በአሜሪካ ወደሚገኙ ሌሎች ቤተ መጻሕፍት ተወስደዋል።
5 ዛሬ በመላው ዓለም በሚገኙ የተለያዩ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ 6,000 የሚያክሉ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ሙሉ ወይም ከፊል ግልባጮች ተመዝግበው በሥርዓት ተቀምጠዋል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ (ከጥቂት ቁርጥራጮች በስተቀር) ከአሥረኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ቀደም ብለው የተዘጋጁ ጥንታዊ ቅጂዎች አይገኙም ነበር። በ1947 ግን በሙት ባሕር አካባቢ የኢሳይያስ መጽሐፍ ጥቅልል ተገኘ። በቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ በሙት ባሕር አካባቢ በሚገኙ ዋሻዎች ለ1,900 ዓመታት ያህል ተደብቀው የቆዩ እጅግ ውድ የሆኑ የቅዱሳን መጻሕፍት በርካታ ጥቅልሎች ተገኝተዋል። ከእነዚህ ቅጂዎች መካከል አንዳንዶቹ የተጻፉት ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበሩት የመጨረሻ መቶ ዓመታት እንደሆነ ሊቃውንቱ ደርሰውበታል። ወደ 6,000 ገደማ የሚሆኑትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች እርስ በርስ በማመሳከር የተደረገው ጥናት ጽሑፎቹ በትክክል ተጠብቀው እንደተላለፉልን አረጋግጧል።
የዕብራይስጥ ቋንቋ
6 ባሁኑ ጊዜ ሰዎች ዕብራይስጥ ብለው የሚጠሩት ቋንቋ ጥንት አዳም በኤደን የአትክልት ሥፍራ ሲኖር የተናገረው ቋንቋ ነው። በመሆኑም የሰው ልጅ የመጀመሪያ ቋንቋ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ብዙ ቃሎች የተጨመሩበት ከመሆኑ በቀር በኖኅ ዘመን ይነገር የነበረው ቋንቋ ይኸው ነው። ይሖዋ በባቤል ግንብ የሰው ልጆችን ቋንቋ በዘበራረቀበት ጊዜም መሠረታዊ ይዘቱን ሳይለውጥ የቀጠለው ይኸው ቋንቋ ነበር። (ዘፍ. 11:1, 7-9) ዕብራይስጥ ከሴማዊ ቋንቋዎች የሚመደብ ከመሆኑም ሌላ የቤተሰቡ ራስ ነው። በአብርሃም ዘመንም ከከነዓናውያን ቋንቋ ጋር የተዛመደና ከነዓናውያን ከሚናገሩት የዕብራውያን ቋንቋ ቅርንጫፍ የተለያዩ ቀበሌኛዎችን የፈጠሩ ይመስላል። በኢሳይያስ 19:18 ላይ ‘የከነዓን ቋንቋ’ ተብሎ ተጠርቷል። ሙሴ በዘመኑ በግብፃውያን ጥበብ ብቻ ሳይሆን በአባቶቹ በዕብራይስጥ ቋንቋ ጭምር የተጠበበ ምሁር ነበር። በዚህም ምክንያት በእጁ የገቡትን የጥንት ሰነዶች ለማንበብ የሚያስችል እውቀት ስለነበረው ዘፍጥረት ተብሎ በተጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የመዘገባቸውን አንዳንድ መረጃዎች ያገኘው ከእነዚሁ ሰነዶች ይሆናል።
7 ቆየት ብሎ በአይሁድ ነገሥታት ዘመን ዕብራይስጥ “የዕብራውያን ቋንቋ” ተብሎ ይጠራ ነበር። (2 ነገ. 18:26, 28) በኢየሱስ ዘመን አይሁዳውያን አዲስ ዓይነት ወይም ይበልጥ ስፋት ያለው ዕብራይስጥ መናገር የጀመሩ ሲሆን ይህም ከጊዜ በኋላ ረቢ የሚባሉት የአይሁድ መምህራን የሚጠቀሙበት ቋንቋ ሆኗል። ይሁን እንጂ ይህ ቋንቋ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥም “ዕብራይስጥ” ተብሎ ይጠራ ነበር እንጂ አረማይክ አልተባለም። (ዮሐ. 5:2፤ 19:13, 17፤ ሥራ 22:2፤ ራእይ 9:11) ከጥንት ዘመን ጀምሮ፣ የመጽሐፍ ቅዱሱ ዕብራይስጥ ከክርስትና በፊት የነበሩት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ምሥክሮች የሚያውቁትና ሁሉንም የሚያገናኝ ቋንቋ ሆኖ ቆይቷል።
8 የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በመለኮታዊ መንፈስ መሪነት የተላለፈውና የተሰባሰበው የጠራ የእውነት ወንዝ ማጠራቀሚያ ባሕር ሆነው አገልግለዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ መለኮታዊ ባሕር ቀጥተኛ ተጠቃሚ ሊሆኑ የቻሉት የዕብራይስጥ ቋንቋ ማንበብ የሚችሉ ብቻ ነበሩ። ታዲያ ሌሎች በርካታ ቋንቋዎችን የሚናገሩ የተለያዩ ሕዝቦችስ ይህን የእውነት ውኃ ጠጥተው ለነፍሳቸው እርካታና ለሕይወታቸው መለኮታዊ መመሪያ ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው? (ራእይ 22:17) ብቸኛው መንገድ ከዕብራይስጥ ወደተለያዩ ቋንቋዎች መተርጎምና መለኮታዊ የእውነት ወንዞች ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ፈስሰው ለበርካታ ሕዝቦች እንዲዳረሱ ማድረግ ነው። ከአራተኛው ወይም ከሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ ወይም በከፊል 1,900 በሚያክሉ ቋንቋዎች በመተርጎሙ ይሖዋ አምላክን ከልብ ልናመሰግነው ይገባናል። አዎን፣ በዚህ ውድ ውኃ “ደስ” ሊሰኙ ለቻሉ የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች በሙሉ እንዴት ያለ ግሩም አጋጣሚ አስገኝቶላቸዋል!—መዝ. 1:2፤ 37:3, 4
9 መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በውስጡ የሰፈሩት ሐሳቦች ወደ ሌሎች ቋንቋዎች እንዲተረጎሙ ሥልጣን ወይም ፈቃድ ይሰጣል? አዎን ይሰጣል! አምላክ ለእስራኤል የተናገረው “አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” የሚለው ቃልና ኢየሱስ ለክርስቲያኖች የሰጠው “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” የሚለው ትንቢታዊ ትእዛዝ ፍጻሜ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህ እንዲፈጸም ደግሞ ቅዱሳን መጻሕፍት የግድ መተርጎም ይኖርባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሲተረጎም የቆየባቸውን 24 መቶ ዘመናት ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ይህ ሥራ የይሖዋ በረከት እንዳልተለየው በግልጽ መረዳት ይቻላል። በተጨማሪም እስከ ዘመናችን ተጠብቀው የቆዩት በእጅ የተጻፉ የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የዕብራይስጡ የእውነት ባሕር ሳይበከልና ሳይበረዝ በትክክል እንደተላለፈ ለማረጋገጥ አስችለዋል።—ዘዳ. 32:43፤ ማቴ. 24:14
የመጀመሪያ ትርጉሞች
10 የሳምራውያን ፔንታቱች። ከጥንት ዘመናት ስንነሳ የሳምራውያን ፔንታቱች የሚባለውን ትርጉም እናገኛለን። ይህ ትርጉም ስሙ እንደሚያመለክተው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን የመጀመሪያ አምስት መጻሕፍት ብቻ ያካተተ ነው። ከጥንቱ የዕብራይስጥ ፊደል ተሻሽሎ የተቀረጸውን የሳምራውያን ፊደል በመጠቀም የዕብራይስጡን ጽሑፍ በቀጥታ በመገልበጥ የተዘጋጀ ትርጉም ነበር። በዘመኑ የነበረውን የዕብራይስጥ ጽሑፍ ለመረዳት የሚያስችል በጣም ጠቃሚ የሆነ እርዳታ ሰጥቷል። ይህ ቀጥተኛ የሆነ ግልባጭ አሥር ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት በ740 ዓ.ዓ. ሲወረር በሰማርያ የቀሩትና በዚያው ወቅት አሦራውያን ከሌላ አካባቢ አምጥተው ያሰፈሯቸው ሰዎች ዝርያዎች ያዘጋጁት ትርጉም ነበር። ሳምራውያን የእስራኤላውያንን አምልኮ ከራሳቸው አረመኔያዊ አማልክት አምልኮ ጋር አጣምረው ያካሂዱ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ አምስቱን የኦሪት መጻሕፍት ይቀበላሉ። ይህን ጽሑፋቸውን ያዘጋጁት በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እንደሆነ የሚያምኑ አንዳንድ ምሁራን ቢኖሩም በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እንደተዘጋጀ ይታሰባል። ጽሑፉን በሚያነቡበት ጊዜ ለሆሄያቱ የሚሰጡት ድምጽ የዕብራይስጡን ድምጽ ነበር። ከዕብራይስጡ ጽሑፍ 6,000 ልዩነቶች ቢኖሩትም ልዩነቶቹ በአብዛኛው ጥቃቅን ለውጦች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ከ13ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ያለፈ ዕድሜ ያላቸው በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች በጣም ጥቂት ናቸው። በአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ላይ በአንዳንድ ቦታዎች የሳምራውያን ፔንታቱች ተጠቅሷል።b
11 የአረማይክ ታርገም። ታርገም ማለት በአረማይክ “ትርጉም” ወይም “ውርስ ትርጉም” ማለት ነው። ከነህምያ ዘመን ጀምሮ አረማይክ በፋርስ ግዛት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ብዙ አይሁዶች መነጋገሪያ ቋንቋ በመሆኑ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የአረማይክ ትርጉም መጨመር አስፈላጊ ሆነ። እነዚህ ትርጉሞች አሁን ያለውን የመጨረሻ ይዘታቸውን ያገኙት በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ገደማ ነው። ትርጉሞቹ የዕብራይስጡ ጽሑፍ ውርስ ትርጉም እንጂ ትክክለኛ ትርጉም ባይሆኑም እንኳ ጥቅሶቹን ለመረዳት የሚያስችሉ በርካታ ሐሳቦችን የሚሰጡ በመሆናቸው አንዳንድ አስቸጋሪ የሆኑ አንቀጾችን ለመረዳት ትልቅ እገዛ አበርክተዋል። በአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ ታርገም ብዙ ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል።c
12 የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት። ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የጥንት ትርጉሞች ሁሉ በጣም አስፈላጊ የሆነውና በጽሑፍ የሰፈረ የመጀመሪያው ከዕብራይስጥ የተተረጎመ ትክክለኛ የትርጉም ሥራ የግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ነው። የትውፊት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ትርጉሙ የጀመረው በ280 ዓ.ዓ. በግብፅ፣ እስክንድርያ ይኖሩ በነበሩ 72 አይሁዳውያን ምሁራን ነው። ከዘመናት በኋላ 70 የሚለው ቃል በሆነ ምክንያት አገልግሎት ላይ በመዋሉ ትርጉሙም ሰብዓ ሊቃናት ተብሎ ተጠራ። በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ተተርጉሞ እንዳለቀ መረጃዎች ያመለክታሉ። ግሪክኛ ተናጋሪ ለሆኑ አይሁዶች በቅዱስ ጽሑፍነት ያገለገለ ከመሆኑም በላይ እስከ ኢየሱስና ሐዋርያት ዘመን ድረስ በሰፊው ሲሠራበት ቆይቷል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት እንዳለ በቀጥታ ከተወሰዱት 320 የሚያክሉ ጥቅሶችና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከተጠቀሱት በድምሩ 890 የሚያክሉ ጥቅሶች መካከል አብዛኞቹ የተመሠረቱት በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ላይ ነው።
13 ዛሬም ለጥናት ሊያገለግሉ የሚችሉ በፓፒረስ ላይ የተጻፉ በርካታ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቁርጥራጮች ይገኛሉ። እነዚህ ቁርጥራጮች በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የተጻፉ በመሆናቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ በአብዛኛው ጥቂት ቁጥሮች ወይም ምዕራፎች ብቻ የያዙ ቢሆኑም እንኳ የሰብዓ ሊቃናትን ጽሑፍ ለመመርመር ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታሉ። ፓፒረስ ፉአድ 266 የተባለው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቅጂ የተገኘው በግብፅ ሲሆን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የተጻፈ እንደሆነ ታውቋል። የዘፍጥረትንና የዘዳግምን መጻሕፍት አንዳንድ ክፍሎች የያዘ ቅጂ ነው። ከዘፍጥረት መጽሐፍ የተገኙት ቁርጥራጮች የተሟሉ ስላልሆኑ በውስጣቸው መለኮታዊው ስም አይገኝም። ይሁን እንጂ በግሪክኛ በተጻፈው የዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ የአምላክ ስም በባለ አራት ማዕዘኑ የዕብራይስጥ ፊደላት በበርካታ ቦታዎች ላይ ተጽፎ ይገኛል።d ሌሎች የፓፒረስ ቅጂዎች እስከ አራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የሚደርስ ዕድሜ ያላቸው ሲሆን በአብዛኛው ከጥጃ፣ ከበግ ወይም ከፍየል ቆዳ የተሠራ ጥራት ያለው ብራና ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በዚህ ዘመን ነበር።
14 በ245 ዓ.ም. ገደማ ተጽፎ ባለቀው በኦሪገን ባለ ስድስት አምድ ሄክሳፕላ ሰብዓ ሊቃናት ላይም መለኮታዊው ስም በአራቱ ፊደላት ተጽፎ መገኘቱ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ኦሪገን መዝሙር 2:2ን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ ሰብዓ ሊቃናትን በተመለከተ “በጣም ትክክል በሆኑት የእጅ ግልባጮች ላይ ስሙ በዛሬው የዕብራይስጥ ፊደላት ሳይሆን በጣም ጥንታዊ በሆኑት የዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ ይገኛል” ብሏል።e በሰብዓ ሊቃናት ላይ ለውጥ የተደረገውና በባለ አራት ፊደላቱ የአምላክ ስም ምትክ ኪሪዮስ (ጌታ) እና ቴኦስ (አምላክ) የሚሉት ቃላት የገቡት ቀደም ባሉት ዘመናት እንደሆነ የማያሻማ መረጃ ተገኝቷል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይጠቀሙባቸው የነበሩ የቅዱሳን መጻሕፍት ግልባጮች መለኮታዊው ስም የሚገኝባቸው ስለሆኑ በአገልግሎታቸው ወቅት የአይሁዳውያንን ወግ በመከተል “ስሙን” ሳያነቡ ያልፉ ነበር ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ከግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት በቀጥታ በመጥቀስ ስለ ይሖዋ ስም ይመሰክሩ እንደነበረ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።
15 እስከዛሬ ድረስ ተጠብቀው የቆዩ በብራና የተዘጋጁ በመቶዎች የሚቆጠሩ የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቅጂዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ከአራተኛው እስከ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የተጻፉ ሲሆኑ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት አብዛኛውን ክፍል ያካተቱ በመሆናቸው ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው። ዘርዘር ባሉ ትላልቅ ፊደላት የተጻፉ በመሆናቸው ኡንስያል ተብለው ይጠራሉ። የቀሩት ደግሞ በአነስተኛና ቅጥልጥል የእጅ ጽሑፍ አጣጣል የተጻፉ በመሆናቸው ሚኒስኪዩል ይባላሉ። የሚኒስኪዩል ወይም ቅጥልጥል የአጻጻፍ ስልት ከዘጠነኛው መቶ ዘመን አንስቶ ኅትመት እስከተጀመረበት ዘመን ድረስ ዋነኛው የአጻጻፍ ስልት ሆኖ ቆይቷል። ቫቲካን ቁጥር 1209፣ ሳይናይቲክ እና አሌክሳንደሪን የተባሉት የአራተኛውና የአምስተኛው መቶ ዘመን ዋነኛ ኡንስያል ቅጂዎች በሙሉ በጣም ጥቃቅን ልዩነቶች ያሏቸው ከመሆኑ በስተቀር የግሪክኛውን ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም አካትተዋል። በአዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ በግርጌ ማስታወሻዎችና ማብራሪያዎች ላይ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል።f
16 የላቲን ቩልጌት። በጣም ብዙ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑ ተርጓሚዎች በምዕራቡ ዓለም ባሉት ሕዝበ ክርስትና በተንሰራፋባቸው አገሮች ውስጥ በሚነገሩት ቋንቋዎች በሚተረጉሙበት ጊዜ የተጠቀሙት ይህን ትርጉም ነው። የቩልጌት አመጣጥ እንዴት ነው? ቩልጋቱስ የሚለው የላቲን ቃል ትርጉሙ “ተራ፣ በስፋት የሚሠራበት” ማለት ነው። ቩልጌት ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው በሮም ምዕራባዊ ግዛት የሚኖሩ ተራ ሕዝቦች በቀላሉ ሊረዱት እንዲችሉ አብዛኛው ሕዝብ በዘመኑ ይናገር በነበረው ቀላልና ተራ ላቲን ነበር። ይህን ትርጉም ያዘጋጀው ጀሮም የተባለ ምሁር ቀደም ሲል የጥንቱን የላቲን መዝሙር ከግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ጋር በማነጻጸር ሁለት የተሻሻሉ ትርጉሞችን አዘጋጅቶ ነበር። የቩልጌት መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከመጀመሪያው ዕብራይስጥና ግሪክኛ በቀጥታ የተተረጎመ በመሆኑ የትርጉም ትርጉም አልነበረም። ጀሮም ከዕብራይስጥ ወደ ላቲን የመተርጎም ሥራውን ያከናወነው ከ390 እስከ 405 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር። ተጠናቅቆ ያለቀው ሙሉ ሥራው በዚያ ዘመን በሰብዓ ሊቃናት ቅጂዎች ውስጥ ተካትተው የተገኙትን አዋልድ መጻሕፍት ያካተተ ቢሆንም ጀሮም 66ቱን መጻሕፍት ከሌሎቹ አዋልድ መጻሕፍት በግልጽ ለይቷል። የአዲስ ዓለም ትርጉም በግርጌ ማስታወሻው ላይ የጀሮምን ቩልጌት ብዙ ጊዜ ይጠቅሳል።g
የዕብራይስጥ ቋንቋ ቅጂዎች
17 ሶፌሪም። ከዕዝራ ዘመን ጀምሮ እስከ ኢየሱስ ዘመን የዘለቁት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጮች ጸሐፍት ወይም ሶፌሪም ተብለው ይጠሩ ነበር። እነዚህ ገልባጮች ከጊዜ በኋላ የጽሑፍ ለውጥ ለማድረግ እስከመድፈር ደረሱ። እንዲያውም ኢየሱስ ራሱ እነዚህ የሕጉ ጠባቂ ተብዬዎች የማይገባቸውን ሥልጣን ይዘው በመገኘታቸው በኃይል አውግዟቸዋል።—ማቴ. 23:2, 13
18 ማሶራ ለውጦቹን አመለከተ። ከክርስቶስ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት የተነሱት የሶፌሪም ተከታዮች ማሶሪታውያን ተብለው መጠራት ጀመሩ። እነዚህ ገልባጮች ሶፌሪሞች ያደረጓቸውን ለውጦች በዕብራይስጡ ቅጂ ሕዳጎች ላይ ወይም መጨረሻ ላይ አመልክተዋል። እነዚህ የሕዳግ ማስታወሻዎች ማሶራ ተብለው መጠራት ጀመሩ። ማሶራ የሶፌሪሞችን 15 እንግዳ ነጥቦች ማለትም በዕብራይስጡ ቅጂ ውስጥ የነጥብና የጭረት ምልክት የተደረገባቸውን 15 ቃላት ወይም ሐረጎች ይዘረዝራል። ከእነዚህ እንግዳ ነጥቦች መካከል አንዳንዶቹ በእንግሊዝኛው ትርጉም ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ የማያመጡ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን ለውጥ የሚያመጡ በመሆናቸው ልብ ሊባሉ የሚገባቸው ናቸው።h ሶፌሪሞች የአምላክን ስም መጥራት ያስቀስፋል በሚል አጉል እምነት ተጠምደው ስለነበር 134 ቦታዎች ላይ ይሖዋ የሚለውን ስም በአዶናይ (ጌታ)፣ በጥቂት ቦታዎች ላይ ደግሞ በኤሎሂም (አምላክ) ተክተዋል። ማሶራ እነዚህን ለውጦች መዝግቧል።i በተጨማሪም ማሶራ ላይ የሰፈረ ማስታወሻ እንደሚያሳየው ሶፌሪሞች ወይም የጥንት ጸሐፍት ቢያንስ 18 ሌሎች እርማቶች እንዳደረጉ ቢታወቅም ለውጦቹ በእነዚህ ብቻ የሚያበቁ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው።j የጥንቶቹ ገልባጮች ለአምላክ ወይም ለአምላክ ወኪሎች አክብሮት የጎደላቸው ሆነው በመገኘታቸው ማሶሪታውያን ማስተካከያውን ያደረጉት በበጎ ዓላማ ተነሳስተው ሳይሆን አይቀርም።
19 ባለተነባቢ ፊደል ቅጂ። የዕብራይስጥ ፊደል 22 ተነባቢዎችን የሚያካትት ሲሆን አናባቢዎች አልነበሩትም። መጀመሪያ ላይ አንባቢው ባለው የቋንቋ እውቀት ላይ ተመሥርቶ አናባቢ ድምጾችን እየጨመረ ያነብ ነበር። የዕብራይስጥ አጻጻፍ እንደ አሕጽሮተ ጽሑፍ ያለ ነበር። በዘመናዊዎቹ ቋንቋዎች እንኳ ብዙ ሰዎች ጥቂት ተነባቢ ፊደላትን በመጻፍ የሚሠራባቸው በርካታ አሕጽሮተ ጽሑፎችን ያውቃሉ። ለምሳሌ ዓመተ ምሕረት ብሎ ከመጻፍ ይልቅ ዓ.ም ተብሎ ይጻፋል። የዕብራይስጥ ቋንቋም በተመሳሳይ በተነባቢ ፊደላት ብቻ የሚጻፉ በርካታ ቃላት አሉት። ስለዚህ “ባለተነባቢ ፊደል ቅጂ” ስንል አለአናባቢ የተጻፈውን የዕብራይስጥ ቅጂ ማለታችን ነው። በተለየ የአጻጻፍ ስልት የተጻፉ ቅጂዎች ረዘም ላሉ ዓመታት መሠራጨታቸው ቢቀጥልም በተነባቢ ፊደላት ብቻ የሚጻፈው የዕብራይስጥ አጻጻፍ ስልት በመጀመሪያውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አካባቢ አንድ ወጥ መልክ ይዞ ነበር። በቀደሙት የሶፌሪም ዘመናት ይደረግ እንደነበረው ለውጦችን ማድረግ ቀረ።
20 የማሶሪታውያን ቅጂ። በአንደኛው ሺህ ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ማሶሪታውያን (በዕብራይስጥ ባሌህ ሃምማሶህራህ “የትውፊት ጌቶች”) አናባቢዎችንና የድምጽ ቃና ለውጦችን የሚያሳዩ ምልክቶችን አዘጋጁ። ከዚያ በፊት የቃላት አነባበቦች በአፋዊ ትውፊት ብቻ ይተላለፉ የነበሩ ሲሆን እነዚህ ምልክቶች ከተዘጋጁ በኋላ ግን በእነሱ አማካኝነት የቃላትን አነባበብና አጠራር ማወቅ ተቻለ። ማሶሪታውያን በሚያስተላልፏቸው ቅጂዎች ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ባያደርጉም አስፈላጊ ሆኖ ባገኙባቸው ቦታዎች ሕዳጎች ላይ ተጨማሪ ማስታወሻ ይጽፉ ነበር። በጽሑፎቹ ላይ ለውጥ እንዳይደረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር። በተጨማሪም በማሶራ ውስጥ ለየት ብለው የታዩ አጻጻፎችን በማመልከት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ትክክለኛውን አነባበብ ይጠቁሙ ነበር።
21 በተነባቢ ፊደላት ብቻ የተጻፈውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂ አነባበብና የድምጽ ቅላጼ በማመልከት ሥራ የተካፈሉ ሦስት የማሶሪታውያን ወገኖች ሲኖሩ እነሱም የባቢሎን፣ የጢባርዮስና የፓለስቲና ወገኖች ተብለው ይጠራሉ። በአሁኑ ጊዜ ታትሞ የተሠራጨው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ የማሶሪታውያን ቅጂ ተብሎ የሚጠራው ሲሆን የሚጠቀመው የጢባርዮስ ወገን የተጠቀመበትን የአጻጻፍ ስልት ነው። ይህ የአጻጻፍ ስልት በገሊላ ባሕር ምዕራባዊ ዳርቻ በምትገኘው በጢባርዮስ ከተማ ይኖሩ የነበሩ ማሶሪታውያን ያቋቋሙት ስልት ነው። የአዲስ ዓለም ትርጉም በግርጌ ማስታወሻዎች ላይ ከማሶሪታውያን ቅጂ (M በሚል ምልክት ሥር) እና ከሕዳግ ማስታወሻው ማለትም ከማሶራ ላይ (Mmargin በሚል ምልክት ሥር) ብዙ ጊዜ ይጠቅሳል።k
22 የፓለስቲናው ወገን የአናባቢ ምልክቶችን በተነባቢ ፊደላት አናት ላይ ያሰፍር ነበር። ከእነዚህ መጻሕፍት ለዘመናችን ተላልፈው የተገኙት በጣም ጥቂት በመሆናቸው ይህ ዓይነቱ የአጻጻፍ ስልት የተሟላ እንዳልነበረ ያመለክታል። የባቢሎኑ ወገን የአናባቢ ማመልከቻ ስልትም በተመሳሳይ ከአናት ላይ የሚደረግ ነበር። የባቢሎኑ ስልት በሩሲያ፣ ሴይንት ፒተርስበርግ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ በሚገኘው የ916 ዓ.ም. የፒተርስበርግ የነቢያት ኮዴክስ ላይ ይታያል። በዚህ ኮዴክስ ውስጥ የኢሳይያስ፣ የኤርምያስ፣ የሕዝቅኤልና “የንዑሳን” ነቢያት መጻሕፍት ከነሕዳግ ማስታወሻቸው (ማሶራ) ተካትተዋል። ምሁራን ይህን ግልባጭ በታላቅ ጉጉት የመረመሩ ከመሆኑም ሌላ ከጢባርዮስ ግልባጭ ጋር አነጻጽረውታል። ይህ ኮዴክስ የሚጠቀመው ከፊደላት አናት ላይ የሚደረገውን የአናባቢ ማመልከቻ ስልት ቢሆንም በተነባቢዎችና በአናባቢዎች እንዲሁም በማሶራ ረገድ የሚከተለው የጢባርዮስን የአጻጻፍ ስልት ነው። የባቢሎን የፔንታቱች ቅጂ በብሪታንያ ሙዚየም የሚገኝ ሲሆን ከጢባርዮስ ቅጂ ጋር በጣም እንደሚስማማ ተረጋግጧል።
23 የሙት ባሕር ጥቅልሎች። በ1947 በዕብራይስጥ መጻሕፍት ታሪክ ረገድ በጣም የሚያጓጓ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። በሙት ባሕር አካባቢ ዋዲ ኩምራን (ናሃል ኩመራን) በሚባል ሥፍራ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ የመጀመሪያውን የኢሳይያስ ጥቅልል ጨምሮ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ጥቅልሎች ተገኙ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይህ በጥሩ ሁኔታ ተጠብቆ የቆየ የኢሳይያስ ጥቅልል (1QIsa) በፊልም ተቀርጾ ምሁራን ምርምር እንዲያካሂዱበት ተሠራጨ። ይህ ጥቅልል በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መጨረሻ ገደማ እንደተጻፈ ይታመናል። በእርግጥም ሊታመን የማይችል ግኝት ነበር። እስከዚያ ጊዜ ድረስ እጅግ ጥንታዊ ነው ይባል ከነበረው የኢሳይያስ የማሶሪታውያን ግልባጭ አንድ ሺህ ዓመት የሚበልጥ ዕድሜ ያለው የዕብራይስጥ ጽሑፍ ግልባጭ ነው።l በኩምራን በሚገኙ ሌሎች ዋሻዎችም ከአስቴር መጽሐፍ በስተቀር የሁሉንም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች የያዙ ከ170 የሚበልጡ ጥቅልሎች ቁርጥራጮች ተገኝተዋል። በእነዚህ ጥቅልሎች ላይ የሚደረገው ጥናት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
24 አንድ ምሁር በጣም ረጅም የሆነውን የመዝሙር 119 የሙት ባሕር ጥቅልል ቅጂ (11QPsa) ከማሶሪታውያን የመዝሙር 119 ቅጂ ጋር አወዳድሮ ቃል በቃል አንድ ሆነው እንዳገኛቸው ዘግቧል። ፕሮፌሰር ጄ ኤ ሳንደርስ ስለ መዝሙር ጥቅልል ሲጽፉ “አብዛኞቹ ልዩነቶች የአጻጻፍ እንዲሁም ስለ ጥንቱ የዕብራይስጥ ቃላት አጠራርና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች ማወቅ የሚፈልጉ ምሁራን ብቻ ሊያስተውሏቸው የሚችሉ ልዩነቶች ናቸው” ብለዋል።a የእነዚህ አስደናቂ የሆኑ የእጅ ጽሑፎች ሌሎች ጥቅልሎች በአብዛኛው ይህ ነው የሚባል ልዩነት አልታየባቸውም። የኢሳይያስ ጥቅልል ራሱ አንዳንድ የሆሄያትና የሰዋስው አወቃቀር ልዩነቶች ቢታዩበትም የመሠረተ ትምህርት ልዩነት የሚያመጣ ለውጥ የለውም። ይህ ለኅትመት የበቃ የኢሳይያስ ጥቅልል የአዲስ ዓለም ትርጉም በሚዘጋጅበት ወቅት ያሉት ልዩነቶች ተመርምረው ተመዝግበዋል።b
25 እስካሁን ድረስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ወደ እኛ የተላለፉባቸው ዋነኛ መንገዶች ተብራርተዋል። እነሱም የሳምራውያን ፔንታቱች፣ የአረማይክ ታርገም፣ የግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት፣ የጢባርዮስ የዕብራይስጥ ቅጂ፣ የፓለስቲና የዕብራይስጥ ቅጂ፣ የባቢሎን የዕብራይስጥ ቅጂና የሙት ባሕር ጥቅልሎች የዕብራይስጥ ቅጂ ናቸው። እነዚህን የተለያዩ ቅጂዎች በማነጻጸርና በማጥናት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በአብዛኛው የአምላክ አገልጋዮች በመንፈሱ እየተመሩ ከጻፏቸው የመጀመሪያ ጽሑፎች መሠረታዊ ለውጥ እንደሌላቸው ማረጋገጥ እንችላለን።
የተጣራው የዕብራይስጥ ቅጂ
26 እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ድረስ ሲሠራበት የቆየውና ለኅትመት የበቃው መደበኛ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ከ1524-25 የታተመው የጀከብ ቤን ካይም ሁለተኛ ረቢያዊ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ምሁራን የዕብራይስጥ ቅጂዎችን በጥንቃቄ መተንተንና መመርመር የጀመሩት ከ18ኛው መቶ ዘመን ወዲህ ነበር። ከ1776-80 ቤንጃሚን ኬኒኮት፣ በኦክስፎርድ 600 የሚያክሉ ግልባጮችን መርምረው በመካከላቸው የተገኘውን ልዩነት አውጥተዋል። ከዚያም ከ1784-98 በፓርማ፣ ጄ ቢ ደ ሮሲ የተባለ ጣሊያናዊ ምሁር 731 የሚያክሉ ተጨማሪ ግልባጮችን መርምሮ ያገኛቸውን ልዩነቶች ገልጿል። በተጨማሪም በጀርመን የሚኖር ኤስ ባየር የተባለ የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁር ለማመሳከሪያነት የሚያገለግል ቅጂ አዘጋጅቷል። በቅርብ ዓመታት ደግሞ ሲ ዲ ጊንስበርግ ከብዙ ዓመት ድካም በኋላ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ዋነኛ ማመሳከሪያ የሚሆን ጽሑፍ አውጥቷል። ከእነዚህም የመጀመሪያው የወጣው በ1894 ሲሆን የመጨረሻው ማስተካከያ የተደረገበት እትም ደግሞ በ1926 ለስርጭት በቃ።c ጆሴፍ ሮዘርሃም የዚህን ጽሑፍ የ1894 እትም በመጠቀም ዚ ኢምፋሳይዝድ ባይብል የተባለውን የእንግሊዝኛ ትርጉም በ1902 ሲያወጣ ፕሮፌሰር ማክስ ኤል ማርጎሊስና ባልደረቦቻቸው ደግሞ የጊንስበርግንና የባየርን ጽሑፎች በመጠቀም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉማቸውን በ1917 አውጥተዋል።
27 በ1906 ሩዶልፍ ኪተል የተባለው የዕብራይስጥ ምሁር በጀርመን አገር ቢብልያ ሂብራይካ ወይም “የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ” የተባለውን የተጣራ የዕብራይስጥ ቅጂ የመጀመሪያ እትም (በኋላ ደግሞ ሁለተኛውን እትም) አወጣ። ኪተል በዚህ መጽሐፉ በዘመኑ የተገኙትን በርካታ የዕብራይስጥ የማሶሪታውያን ቅጂዎች በርካታ በሆኑ የግርጌ ማስታወሻዎች እርስ በርሳቸው በማመሳከርና በማነጻጸር ጥሩ የትርጉም መሣሪያ አዘጋጅቷል። መሠረት አድርጎ የተነሳው ሰፊ ተቀባይነት ያገኘውን የጀከብ ቤን ካይምን ቅጂ ነበር። በአሥረኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መደበኛ ግልባጭ እንዲሆን የተደረገውና የበለጠ ጥራትና ዕድሜ የነበረው የቤን አሸር የማሶሪታውያን ቅጂ በተገኘ ጊዜ ኪተል ሙሉ በሙሉ የተለየ የቢብልያ ሂብራይካ ሦስተኛ እትም ማዘጋጀት ጀመረ። ይህ ሥራ የተጠናቀቀው እሱ ከሞተ በኋላ በሥራ ባልደረቦቹ ነበር።
28 በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው የአዲስ ዓለም ትርጉም የዕብራይስጥ ክፍል መሠረት ያደረገው የኪተልን ቢብልያ ሂብራይካ ሰባተኛ፣ ስምንተኛና ዘጠነኛ እትሞች (1951-55) ነበር። በ1984 የወጣውን የአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻዎች አሻሽሎ ለማቅረብ ያገለገለው በ1977 የወጣው የቢብልያ ሂብራይካ ስቱትጋርቴንስያ አዲስ የዕብራይስጥ ቅጂ ነው።
29 በአዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ ይሖዋ የተባለውን መለኮታዊ ስም ወደ ቀድሞ ቦታው መመለስን ጨምሮ ትክክለኛ ትርጉሞችን ማስቀመጥ የተቻለው የቅድመ ክርስትና ጸሐፍት ያደረጓቸው በርካታ ለውጦች የተመዘገቡበትን የኪተል የሕዳግ ማሶራዎች በመጠቀም ነው። እየጨመረ የመጣው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የሥራ ውጤት በአዲስ ዓለም ትርጉም አማካኝነት እየተዳረሰ ነው።
30 የአዲስ ዓለም ትርጉም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለመተርጎም በምንጭነት ያገለገሉት ቅጂዎች በዚህ ጥናት ሥር በሚገኘው ሰንጠረዥ ላይ ተዘርዝረዋል። ይህ ሰንጠረዥ በዋነኛ ምንጭነት እስካገለገለው የኪተል ቢብልያ ሂብራይካ ድረስ የዕብራይስጥ ቅጂዎች አመጣጥ ሂደት እንዴት እንደነበረ በአጭሩ ያሳያል። ለማመሳከሪያነት ያገለገሉ በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ ምንጮች በነጭ ነጠብጣጦች ተመልክተዋል። ይህ የተደረገው እንደ ላቲን ቩልጌት እና እንደ ግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ባሉት ትርጉሞች ረገድ በኩረ ጽሑፎቹን እንዳመሳከርን ለማመልከት አይደለም። የእነዚህ ትርጉሞች በኩረ ጽሑፎች በመንፈስ እንደተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአሁኑ ጊዜ አይገኙም። እነኚህን ምንጮች ማመሳከር የተቻለው አስተማማኝ በሆኑ የእነዚህ ጽሑፎች ቅጂዎች ወይም ትርጉሞችና የንጽጽር ጽሑፎች አማካኝነት ነው። የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ እነዚህን የተለያዩ ምንጮች በማመሳከር በመንፈስ የተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በኩረ ጽሑፍ አስተማማኝና ትክክለኛ ትርጉም ሊያዘጋጅ ችሏል። እነዚህ ምንጮች በሙሉ በአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ ተመልክተዋል።
31 ስለዚህ የአዲስ ዓለም ትርጉም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም የበርካታ ዘመናት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ምርምር ውጤት ነው። ምንም ሳይለወጥ ለዘመናት ተጠብቆ የቆየን አስተማማኝ የሆነ ግልባጭ መሠረት ያደረገ የትርጉም ሥራ ነው። አእምሮ የሚመስጥ የሐሳብ ፍሰትና የአጻጻፍ ስልት ያለው በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን በጥሞና ለሚያጠኑ ሰዎች የሚያገለግል ሐቀኛና ትክክለኛ ትርጉም ሆኗል። ዛሬም ቃሉ ሕያውና ኃይለኛ ሆኖ በመገኘቱ ሐሳቡን ገላጭ የሆነው ይሖዋ አምላክ የተመሰገነ ይሁን! (ዕብ. 4:12) በርካታ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ውድ የሆነውን የአምላክ ቃል በማጥናት እምነታቸውን ለመገንባትና በዚህ ታሪካዊ በሆነ ወቅት የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ እንዲነሳሱ ምኞታችን ነው።—2 ጴጥ. 1:12, 13
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ምኩራቦች መቋቋም የጀመሩት መቼ እንደሆነ በትክክል አይታወቅም። ቤተ መቅደስ ባልነበረበት የ70 ዓመት የባቢሎን ግዞት ዘመን ወይም በዕዝራ ዘመን አይሁዳውያን ከግዞት ከተመለሱ በኋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት ሊሆን ይችላል።
b በዘፍጥረት 4:8፤ በዘፀአት 6:2፤ 7:9፤ 8:15 እና 12:40 ሥር የግርጌ ማስታወሻው ላይ “Sam” የሚለውን ተመልከት። ይህ የመጨረሻ አተረጓጎም ገላትያ 3:17ን እንድንረዳ ያስችለናል።
c በዘኁልቁ 24:17፤ በዘዳግም 33:13 እና በመዝሙር 100:3 ላይ “T” በሚለው ሥር ያሉትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት።
d ባለማጣቀሻው መጽሐፍ ቅዱስ (እንግሊዝኛ)፣ የተጨማሪው ክፍል 1c፣ “መለኮታዊው ስም በጥንታዊው የግሪክኛ ትርጉም።”
e ጠለቅ ብሎ ማስተዋል፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 9።
f የአዲስ ዓለም ትርጉም እነዚህን ልዩነቶች ለማመልከት ለሳይናይቲክ LXXא፣ ለአሌክሳንድሪን LXXA እንዲሁም ለቫቲካን LXXB ምልክቶች ይጠቀማል። በ1 ነገሥት 14:2 እና 1 ዜና መዋዕል 7:34፤ 12:19 ላይ የሚገኙትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት።
g በዘፀአት 37:6 የግርጌ ማስታወሻ ላይ “Vg” የሚለውን ተመልከት።
h ባለማጣቀሻው መጽሐፍ ቅዱስ (እንግሊዝኛ)፣ የተጨማሪው ክፍል 2A፣ “እንግዳ ነጥቦች።”
i ባለማጣቀሻው መጽሐፍ ቅዱስ (እንግሊዝኛ)፣ የተጨማሪው ክፍል 1B፣ “መለኮታዊውን ስም በተመለከተ ጸሐፊዎች ያደረጓቸው ለውጦች”
j ባለማጣቀሻው መጽሐፍ ቅዱስ (እንግሊዝኛ)፣ የተጨማሪው ክፍል 2B፣ “የሶፌሪም እርማቶች።”
k በመዝሙር 60:5፤ 71:20፤ 100:3 እና 119:79 ሥር ያሉትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት።
l ጠለቅ ብሎ ማስተዋል፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 322።
a የሙት ባሕር የመዝሙር ጥቅልል፣ 1967፣ ጄ ኤ ሳንደርስ ገጽ 15።
b በኢሳይያስ 7:1፤ 14:4 የግርጌ ማስታወሻ ላይ “1QIsa” የሚለውን ተመልከት።
c በዘሌዋውያን 11:42 የግርጌ ማስታወሻ ላይ “Gins.” የሚለውን ተመልከት።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው አንዳንድ የፓፒረስ ቅጂዎች
ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት
የጽሑፉ ስም ናሽ ፓፒረስ
ዘመን 2ኛው ወይም 1ኛው መ.ዘ. ዓ.ዓ.
ቋንቋ ዕብራይስጥ
የሚገኝበት ቦታ ካምብሪጅ፣ እንግሊዝ
የጽሑፉ ስም ራይላንድስ 458
መለያ ምልክት 957
ዘመን 2ኛው መ.ዘ. ዓ.ዓ.
ቋንቋ ግሪክ
የሚገኝበት ቦታ ማንቸስተር፣ እንግሊዝ
የያዛቸው ጽሑፎች የዘዳግም ምዕ. 23-28 ቁርጥራጮች
የጽሑፉ ስም ፎኤድ 266
ዘመን 1ኛው መ.ዘ. ዓ.ዓ.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ካይሮ፣ ግብፅ
የያዛቸው ጽሑፎች የዘፍጥረት እና የዘዳግም የተወሰኑ
ክፍሎች
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ዘዳ. 18:5፤ ሥራ 3:22፤
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ ተጨማሪ መረጃ 1
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም የሙት ባሕር የዘሌዋውያን ጥቅልል
መለያ ምልክት 4Q LXX Levb
ዘመን 1ኛው መ.ዘ. ዓ.ዓ.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ኢየሩሳሌም፣ እስራኤል
የያዛቸው ጽሑፎች የዘሌዋውያን ቁርጥራጮች
የጽሑፉ ስም ቼስተር ቢቲ 6
መለያ ምልክት 963
ዘመን 2ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ዳብሊን፣ አየርላንድ እና
አን አርበር፣ ሚሽገን፣ ዩ.ኤስ.ኤ.
የያዛቸው ጽሑፎች የዘኁልቁ እና የዘዳግም የተወሰነ ክፍል
የጽሑፉ ስም ቼስተር ቢቲ 9, 10
መለያ ምልክት 967/ 968
ዘመን 3ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ዳብሊን፣ አየርላንድ እና
ፕሪንስተን፣ ኒው.ጄ.፣ ዩ.ኤስ.ኤ.
የያዛቸው ጽሑፎች የሕዝቅኤል፣ የዳንኤልና የአስቴር
የተወሰኑ ክፍሎች
ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት
የጽሑፉ ስም ኦክሲሪንከስ 2
መለያ ምልክት P1
ዘመን 3ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ፊላደልፊያ፣ ፔንሲ.፣ ዩ.ኤስ.ኤ.
የያዛቸው ጽሑፎች ማቴ. 1:1-9, 12, 14-20
የጽሑፉ ስም ኦክሲሪንከስ 1228
መለያ ምልክት P22
ዘመን 3ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ግላስጎው፣ ስኮትላንድ
የያዛቸው ጽሑፎች የዮሐንስ ምዕ. 15, 16 ቁርጥራጮች
የጽሑፉ ስም ሚሽገን 1570
መለያ ምልክት P37
ዘመን 3ኛው/4ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ አን አርበር፣ ሚሽገን፣ ዩ.ኤስ.ኤ.
የያዛቸው ጽሑፎች ማቴ. 26:19-52
የጽሑፉ ስም ቼስተር ቢቲ 1
መለያ ምልክት P45
ዘመን 3ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ዳብሊን፣ አየርላንድ፤ ቪየና፣ ኦስትሪያ
የያዛቸው ጽሑፎች የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስ፣ የዮሐንስ
እና የሥራ ቁርጥራጮች
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ሉቃስ 10:42፤ ዮሐንስ 10:18
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም ቼስተር ቢቲ 2
መለያ ምልክት P46
ዘመን 200 ዓ.ም. ገ.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ዳብሊን፣ አየርላንድ፤
አን አርበር ሚሽገን፣ ዩ.ኤስ.ኤ.
የያዛቸው ጽሑፎች ከጳውሎስ ደብዳቤዎች ዘጠኙ
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ሮም 8:23, 28፤ 1 ቆሮ. 2:16
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም ቼስተር ቢቲ 3
መለያ ምልክት P47
ዘመን 3ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ዳብሊን፣ አየርላንድ
የያዛቸው ጽሑፎች ራእይ 9:10–17:2
የጽሑፉ ስም ራይላንድስ 457
መለያ ምልክት P52
ዘመን 125 ዓ.ም. ገ.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ማንቸስተር፣ እንግሊዝ
የያዛቸው ጽሑፎች ዮሐንስ 18:31-33, 37, 38
የጽሑፉ ስም ቦድመር 2
መለያ ምልክት P66
ዘመን 200 ዓ.ም. ገ.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ
የያዛቸው ጽሑፎች አብዛኛው የዮሐንስ ወንጌል
የጽሑፉ ስም ቦድመር 7, 8
መለያ ምልክት P72
ዘመን 3ኛው/4ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድና ቫቲካን
ቤተ መጻሕፍት ሮም፣ ጣሊያን ውስጥ
የያዛቸው ጽሑፎች ይሁዳ፣ 1 ጴጥሮስ፣ እና 2 ጴጥሮስ
የጽሑፉ ስም ቦድመር 14, 15
መለያ ምልክት P75
ዘመን 3ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ
የያዛቸው ጽሑፎች አብዛኛው የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌል
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው አንዳንድ የብራና ጽሑፎች
የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት (በዕብራይስጥ)
የጽሑፉ ስም አሌፖ ኮዴክስ
መለያ ምልክት Al
ዘመን 930 ዓ.ም.
ቋንቋ ዕብራይስጥ
የሚገኝበት ቦታ ቀደም ሲል በአሌፖ፣ ሶርያ
በአሁኑ ጊዜ በእስራኤል
የያዛቸው ጽሑፎች አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን
መጻሕፍት (የቤን አሸር ጽሑፍ)
የጽሑፉ ስም ብሪትሽ ሙዚየም
Codex Or4445
ዘመን 10ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ዕብራይስጥ
የሚገኝበት ቦታ ለንደን፣ እንግሊዝ
የያዛቸው ጽሑፎች አብዛኞቹ የኦሪት መጻሕፍት
የጽሑፉ ስም ካይሮ የቀረዓታውያ ን ኮዴክስ
መለያ ምልክት Ca
ዘመን 895 ዓ.ም.
ቋንቋ ዕብራይስጥ
የሚገኝበት ቦታ ካይሮ፣ ግብፅ
የያዛቸው ጽሑፎች የፊተኞቹና የኋለኞቹ ነቢያት
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ኢያሱ 21:37፤ 2 ሳሙ. 8:3
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም ሌኒንግራድ ኮዴክስ
መለያ ምልክት B 19A
ዘመን 1008 ዓ.ም.
ቋንቋ ዕብራይስጥ
የሚገኝበት ቦታ ሌኒንግራድ፣ ሩሲያ
የያዛቸው ጽሑፎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ኢያሱ 21:37፤ 2 ሳሙ. 8:3፤
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ ተጨማሪ መረጃ 1A
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም ፒተርስበርግ የነቢያ ት ኮዴክስ
መለያ ምልክት B 3
ዘመን 916 ዓ.ም.
ቋንቋ ዕብራይስጥ
የሚገኝበት ቦታ ሌኒንግራድ፣ ሩሲያ
የያዛቸው ጽሑፎች የኋለኞቹ ነቢያት
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ተጨማሪ መረጃ 2B
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም የሙት ባሕር የመጀመሪያው
የኢሳይያስ ጥቅልል
መለያ ምልክት 1QIsa
ዘመን 2ኛው መ.ዘ. መጨረሻ ዓ.ዓ.
ቋንቋ ዕብራይስጥ
የሚገኝበት ቦታ ኢየሩሳሌም፣ እስራኤል
የያዛቸው ጽሑፎች ኢሳይያስ
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ኢሳ. 11:1፤ 18:2፤ 41:29
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም የሙት ባሕር የመዝሙር ጥቅልል
መለያ ምልክት 11QPsa
ዘመን 1ኛው መ.ዘ. ዓ.ዓ.
ቋንቋ ዕብራይስጥ
የሚገኝበት ቦታ ኢየሩሳሌም፣ እስራኤል
የያዛቸው ጽሑፎች ከመጨረሻዎቹ 50 መዝሙራት
የአርባ አንዱ የተወሰኑ ክፍሎች
የሰብዓ ሊቃናት እና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት
የጽሑፉ ስም ሳይናይቲከስ
መለያ ምልክት 01( א)
ዘመን 4ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ለንደን፣ እንግሊዝ
የያዛቸው ጽሑፎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት
የተወሰኑ ክፍሎችና የግሪክኛ
ቅዱሳን መጻሕፍት በሙሉ
እንዲሁም አንዳንድ የአዋልድ መጻሕፍት
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ 1 ዜና 12:19፤ ዮሐ. 5:2፤
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ 2 ዜና 12:4
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም አሌክሳንደሪነስ
መለያ ምልክት A (02)
ዘመን 5ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ለንደን፣ እንግሊዝ
የያዛቸው ጽሑፎች የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቅዱሳን
መጻሕፍት በሙሉ (ጥቂቱ ክፍል
ጠፍቷል ወይም ተበላሽቷል)
እንዲሁም አንዳንድ የአዋልድ ጽሑፎች
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ 1 ነገ. 14:2፤ ሉቃስ 5:39፤
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ ሥራ 13:20፤ ዕብ. 3:6
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም ቫቲካን 1209
መለያ ምልክት B (03)
ዘመን 4ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ሮም፣ ጣሊያን በሚገኘው
የቫቲካን ቤተ መጻሕፍት
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ማርቆስ 6:14፤
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ ዮሐንስ 1:18፤ 7:53–8:11
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም ኤፍራይሚ ሱሪ ሬስክሪፕተስ
መለያ ምልክት C (04)
ዘመን 5ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ
የሚገኝበት ቦታ ፓሪስ፣ ፈረንሳይ
የያዛቸው ጽሑፎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት
በከፊል (64 ገጾች) እንዲሁም
የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በከፊል
(145 ገጾች)
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ሥራ 9:12፤
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ ሮም 8:23, 28, 34
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
የጽሑፉ ስም ኮዴክስ ቤዜ ካንታቢይሪኤንሲስ
መለያ ምልክት Dea (05)
ዘመን 5ኛው መ.ዘ. ዓ.ም.
ቋንቋ ግሪክኛ-ላቲን
የሚገኝበት ቦታ ካምብሪጅ፣ እንግሊዝ
የያዛቸው ጽሑፎች የአራቱ ወንጌሎች አብዛኛው
ክፍል እንዲሁም ሥራ፣
የ3 ዮሐንስ ጥቂት ቁጥሮች
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ማቴ. 24:36፤ ማር. 7:16፤
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ ሉቃስ 15:21 (የተጠቀሰው “D”
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት) ለሚለው መለያ ምልክት ብቻ ነው)
የጽሑፉ ስም ኮዴክስ ክላሮሞንታንነስ
መለያ ምልክት DP (06)
ዘመን 6ኛው መ.ዘ. ዓ.ዓ.
ቋንቋ ግሪክኛ-ላቲን
የሚገኝበት ቦታ ፓሪስ፣ ፈረንሳይ
የያዛቸው ጽሑፎች የጳውሎስ ደብዳቤዎች
(ዕብራውያንን ይጨምራል)
በባለ ማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ገላ. 5:12 (የተጠቀሰው “D”
ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳይ ምሳሌ ለሚለው መለያ ምልክት ብቻ ነው)
(ለጥቅሶቹ የገቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት)
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ለአዲስ ዓለም ትርጉም በምንጭነት ያገለገሉ መጻሕፍት—የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት
የመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥ ጽሑፎችና ጥንታዊ ቅጂዎች
የአረማይክ ታርገም
የሙት ባሕር ጥቅልሎች
የሳምራውያን ፔንታቱች
የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት
ጥንታዊው ላቲን
ኮፕቲክ፣ ግዕዝ፣ አርመንኛ
አናባቢ የሌለው የዕብራይስጥ ጽሑፍ
የላቲን ቩልጌት
የግሪክኛ ትርጉሞች—አቂላ፣ ቲኦዶሸን፣ ሲመአከስ
የሲሪያኩ ፐሺታ
የማሶሬቶች ቅጂ
የካይሮ ኮዴክስ
የፒተርስበርግ የነቢያት ኮዴክስ
የአሌፖ ኮዴክስ
የጊንስበርግ ዕብራይስጥ ቅጂ
የሌኒንግራድ ኮዴክስ B 19A
ቢብሊያ ሂብራይካ (BHK)፣ ቢብሊያ ሂብራይካ ስቱትጋርቴንስያ (BHS)
አዲስ ዓለም ትርጉም
የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት—እንግሊዝኛ፤ ከእንግሊዝኛ በዘመናችን ወደሚነገሩ ሌሎች በርካታ ቋንቋዎች
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ለአዲስ ዓለም ትርጉም በምንጭነት ያገለገሉ ጽሑፎች—የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት
የመጀመሪያዎቹ የግሪክኛ ጽሑፎችና ጥንታዊ ቅጂዎች
የአርመንኛ ትርጉም
የኮፕቲክ ትርጉሞች
የሲሪያክ ትርጉሞች—ኪዩርተኒያን፣ ፊሎሲኒያን፣ ሃርክሌን፣ ፓለስቲንያን፣ ሳይናይቲክ፣ ፐሺታ
የጥንቱ ላቲን
ላቲን ቩልጌት
የሲክስተስና የክሌመንት ተሻሽለው የተዘጋጁ የላቲን ትርጉሞች
የቅጥልጥል ፊደላት ግሪክኛ ቅጂዎች
የኢራስመስ ትርጉም
የስቴፋነስ ትርጉም
ቴክስቱስ ሪሰፕቱስ
የግሪስባኽ ግሪክኛ ትርጉም
ኢምፋቲክ ዲያግሎት
ፓፒረስ—(ለምሳሌ፦ ቼስተር ቢቲ P45፣ P46፣ P47፤ ቦድመር P66፣ P74፣ P75)
በጥንታዊ ግሪክኛ በትላልቅ ፊደላት የተጻፉ ቅጂዎች—ቫቲካን 1209 (B)፣
ሳይናይቲክ (א)፣ አሌክሳንድራይን (A)፣ ኢፍራይሚ ሱሪ ሬስክሪፕተስ (C)፣ ቤዜ (D)
ዌስትኮት እና ሆርት የግሪክኛ ጽሑፍ
ቦቨር የግሪክኛ ጽሑፍ
መርክ የግሪክኛ ጽሑፍ
ኔስትል-አላንድ የግሪክኛ ጽሑፍ
የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ግሪክኛ ጽሑፍ
23 የዕብራይስጥ ትርጉሞች (ከ14ኛው-20ኛው መቶ ዘመናት)፣ የተተረጎሙት
ከግሪክኛ ወይም ከላቲን ቩልጌት ሲሆን መለኮታዊውን ስም የሚወክሉትን አራቱን
የዕብራይስጥ ፊደላት ተጠቅመዋል
አዲስ ዓለም ትርጉም
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት—እንግሊዝኛ፤ ከእንግሊዝኛ ደግሞ በዘመናችን ወደሚነገሩ ሌሎች በርካታ ቋንቋዎች