የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በሰንበት መልካም ሥራ መሥራት ይፈቀዳል?
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ኢየሱስ አንድን የታመመ ሰው በቤተዛታ ገንዳ አጠገብ ሲያናግረው

      ምዕራፍ 29

      በሰንበት መልካም ሥራ መሥራት ይፈቀዳል?

      ዮሐንስ 5:1-16

      • ኢየሱስ በይሁዳ ሰበከ

      • በውኃ ገንዳ አጠገብ ያገኘውን የታመመ ሰው ፈወሰ

      ኢየሱስ በገሊላ ባከናወነው ታላቅ አገልግሎት ብዙ ነገሮችን አድርጓል። ይሁንና “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ” ሲል በገሊላ ብቻ ስለ መስበክ መናገሩ አልነበረም። በመሆኑም “በይሁዳ ምኩራቦች መስበኩን ቀጠለ።” (ሉቃስ 4:43, 44) ጊዜው ጸደይ ስለሆነና በኢየሩሳሌም የሚከበረው በዓል እየተቃረበ ስለመጣ በዚህ ወቅት ኢየሱስ በይሁዳ መስበኩ ተገቢ ነው።

      ኢየሱስ በገሊላ ስላከናወነው አገልግሎት ከሚገልጹት ዘገባዎች አንጻር ሲታይ በይሁዳ ስለፈጸማቸው ነገሮች በወንጌሎች ውስጥ ተመዝግቦ የምናገኘው ሐሳብ አነስተኛ ነው። በይሁዳ አብዛኛው ሕዝብ ግዴለሽ ቢሆንም ይህ ኢየሱስ በቅንዓት ከመስበክና በሄደበት ቦታ ሁሉ መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንዲል አላደረገውም።

      ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ በ31 ዓ.ም. በሚከበረው የፋሲካ በዓል ላይ ለመገኘት የይሁዳ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ። ሰው በሚበዛበት በበጎች በር አጠገብ ቤተዛታ ተብሎ የሚጠራ በዙሪያው መተላለፊያዎች ያሉት ትልቅ የውኃ ገንዳ አለ። በርካታ ሕመምተኞች፣ ዓይነ ስውሮችና አንካሶች ወደዚህ ገንዳ ይመጣሉ። ለምን? ብዙዎች፣ ውኃው በሚናወጥበት ጊዜ ገንዳው ውስጥ መግባት ፈውስ እንደሚያስገኝ ስለሚያምኑ ነው።

      ዕለቱ ሰንበት ነው፤ ኢየሱስ ለ38 ዓመታት ታሞ የቆየ አንድ ሰው በገንዳው አጠገብ አየ። በመሆኑም ይህን ሰው “መዳን ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታዬ፣ ውኃው በሚናወጥበት ጊዜ ገንዳው ውስጥ የሚያስገባኝ ሰው የለኝም፤ ወደ ገንዳው ስሄድ ደግሞ ሌላው ቀድሞኝ ይገባል።”—ዮሐንስ 5:6, 7

      በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ሰውየውንም ሆነ በአቅራቢያው ሆነው የሚሰሙ ሰዎችን የሚያስደንቅ ነገር ተናገረ፤ “ተነስ! መኝታህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። (ዮሐንስ 5:8 ግርጌ) ሰውየውም ያደረገው ይህንኑ ነው። ወዲያው ስለተፈወሰ መኝታውን ይዞ ሄደ!

      አይሁዳውያን ኢየሱስ የፈወሰውን ሰው ሲያናግሩት

      አይሁዳውያን በዚህ አስደናቂ ተአምር ከመደሰት ይልቅ ሰውየውን ሲያዩ “ሰንበት እኮ ነው፤ መኝታህን እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” ብለው ኮነኑት። ሰውየውም “የፈወሰኝ ሰው ራሱ ‘መኝታህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው። (ዮሐንስ 5:10, 11 ግርጌ) እነዚህ አይሁዳውያን በሰንበት የሚፈውስ ሰው መኖሩ አላስደሰታቸውም።

      ስለዚህ “‘መኝታህን ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ ሰው ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ሰውየውን እንዲህ ብለው የጠየቁት ለምንድን ነው? “ኢየሱስ ከቦታው ዞር ብሎ ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅሎ ስለነበር” ነው፤ ሰውየው ደግሞ የኢየሱስን ስም አያውቀውም። (ዮሐንስ 5:12, 13 ግርጌ) ይሁን እንጂ ሰውየውና ኢየሱስ እንደገና ሊገናኙ ነው። በኋላ ላይ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይህ ሰው ኢየሱስን ሲያገኘው በገንዳው አጠገብ የፈወሰው ማን እንደሆነ አወቀ።

      የተፈወሰው ሰው፣ ማን እንዳዳነው ከጠየቁት አይሁዳውያን ጋር ሲገናኝ የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ነገራቸው። አይሁዳውያኑ ይህን ሲሰሙ ወደ ኢየሱስ ሄዱ። ወደ እሱ የሄዱት እነዚህን ተአምራት መፈጸም የቻለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ፈልገው ይሆን? አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሰንበት መልካም ነገሮች በመሥራቱ እሱን ለመንቀፍ ነው። እንዲያውም ስደት ያደርሱበት ጀመር!

      • ኢየሱስ ወደ ይሁዳ የሄደው ለምንድን ነው? ምን ማድረጉንስ አላቆመም?

      • ቤተዛታ ወደተባለው ገንዳ ብዙዎች የሚሄዱት ለምንድን ነው?

      • ኢየሱስ በገንዳው አጠገብ ምን ተአምር ፈጸመ? አንዳንድ አይሁዳውያን ይህን ሲያዩ ምን አደረጉ?

  • ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • አይሁዳውያን ኢየሱስን ሰንበትህን ጥሰሃል በሚል ሲወነጅሉት

      ምዕራፍ 30

      ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው

      ዮሐንስ 5:17-47

      • ይሖዋ የኢየሱስ አባት ነው

      • የትንሣኤ ተስፋ ተሰጠ

      አንዳንድ አይሁዳውያን፣ ኢየሱስ አንድን ሰው በመፈወሱ የሰንበትን ሕግ እንደጣሰ ገልጸው በከሰሱት ጊዜ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም እሠራለሁ” ሲል መለሰላቸው።—ዮሐንስ 5:17

      ኢየሱስ ያደረገው ነገር፣ አምላክ ስለ ሰንበት በሰጠው ሕግ ላይ የተከለከለ አይደለም። ኢየሱስ መስበኩና መፈወሱ፣ መልካም ሥራዎችን በማከናወን ረገድ የአምላክን ምሳሌ እንደተከተለ ያሳያል። በመሆኑም ኢየሱስ በየዕለቱ መልካም ነገር ያከናውናል። ከሳሾቹ ግን ኢየሱስ የሰጣቸው መልስ ከበፊቱ ይበልጥ አናደዳቸው፤ ሊገድሉትም ፈለጉ። ለምን?

      ሊገድሉት የፈለጉት፣ ‘ኢየሱስ ሰዎችን በመፈወስ የሰንበትን ሕግ ጥሷል’ የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ስላላቸው ብቻ ሳይሆን የአምላክ ልጅ እንደሆነ በመናገሩ በጣም ስለተበሳጩም ጭምር ነው። ኢየሱስ፣ ይሖዋ አባቱ እንደሆነ መናገሩ አምላክን እንደ መዳፈር በሌላ አባባል ራሱን ከአምላክ ጋር እኩል እንደ ማድረግ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ኢየሱስ ግን የፍርሃት ስሜት አላደረበትም፤ እንዲያውም ከአምላክ ጋር ስላለው ልዩ ዝምድና ተጨማሪ ነገር ነገራቸው። “አብ ወልድን ይወደዋል፤ እንዲሁም እሱ ራሱ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ያሳየዋል” አላቸው።—ዮሐንስ 5:20

      ሕይወት የሚሰጠው አብ ነው፤ እሱም ቀደም ባሉት ዘመናት ሰዎች ሙታንን እንዲያስነሱ ኃይል በመስጠት ይህንን አሳይቷል። ኢየሱስ በመቀጠል “አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸውና ሕያው እንደሚያደርጋቸው ሁሉ ወልድም እንዲሁ የፈለገውን ሰው ሕያው ያደርጋል” አለ። (ዮሐንስ 5:21) ትልቅ ትርጉም ያለው ይህ ሐሳብ እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው! አሁንም እንኳ ወልድ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሙታንን እያስነሳ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “ቃሌን የሚሰማና የላከኝን የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወደ ፍርድም አይመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻግሯል” ብሏል።—ዮሐንስ 5:24

      እስከዚህ ጊዜ ድረስ ኢየሱስ ከሞት ያስነሳው ሰው ስለመኖሩ የሚናገር ዘገባ ባይኖርም ወደፊት ቃል በቃል ሙታን እንደሚነሱ ለከሳሾቹ ነግሯቸዋል። ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት ይመጣል’ ብሏቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29

      ኢየሱስ ልዩ ሚና የተሰጠው ቢሆንም የአምላክ የበታች መሆኑን በግልጽ ሲናገር ‘በራሴ ተነሳስቼ አንድም ነገር ማድረግ አልችልም። የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ መፈጸም እፈልጋለሁ’ ብሏል። (ዮሐንስ 5:30) ያም ቢሆን ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ገልጿል፤ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በሕዝብ ፊት እንዲህ በግልጽ ተናግሮ አያውቅም። የኢየሱስ ከሳሾች ከእሱ በተጨማሪ ስለ እነዚህ ነገሮች የመሠከረላቸው ሰው አለ። ኢየሱስ “ወደ [መጥምቁ] ዮሐንስ ሰዎች ልካችሁ ነበር፤ እሱም ለእውነት መሥክሯል” በማለት አስታውሷቸዋል።—ዮሐንስ 5:33

      የኢየሱስ ከሳሾች፣ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ዮሐንስ ከእሱ በኋላ ስለሚመጣው ሰው ይኸውም “ነቢዩ” እና “ክርስቶስ” ተብሎ ስለተጠራው ግለሰብ ለሃይማኖት መሪዎቹ መናገሩን ሰምተው መሆን አለበት። (ዮሐንስ 1:20-25) ኢየሱስ፣ ከሳሾቹ አሁን በእስር ላይ የሚገኘውን ዮሐንስን በአንድ ወቅት ከፍ አድርገው ይመለከቱት እንደነበር ለማስታወስ “ለጥቂት ጊዜ በእሱ ብርሃን እጅግ ለመደሰት ፈቃደኞች ነበራችሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 5:35) ሆኖም ኢየሱስ፣ ከመጥምቁ ዮሐንስ የላቀ ምሥክር እንዳለው ገልጿል።

      “እየሠራሁት ያለው ይህ ሥራ [በዚህ ወቅት የፈጸመውን ተአምር ጨምሮ] አብ እንደላከኝ ይመሠክራል” አለ። አክሎም ኢየሱስ “የላከኝ አብም ራሱ ስለ እኔ መሥክሯል” ሲል ተናገረ። (ዮሐንስ 5:36, 37) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ አምላክ ስለ እሱ መሥክሯል።—ማቴዎስ 3:17

      በእርግጥም የኢየሱስ ከሳሾች እሱን ላለመቀበል ምንም ምክንያት የላቸውም። ከሳሾቹ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደሚመረምሩ ይናገራሉ፤ እነዚያው መጻሕፍት ግን ስለ እሱ ይመሠክራሉ! ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ፦ “ሙሴን ብታምኑት ኖሮ እኔንም ታምኑኝ ነበር፤ እሱ ስለ እኔ ጽፏልና። ሆኖም እሱ የጻፈውን ካላመናችሁ እኔ የምናገረውን እንዴት ታምናላችሁ?”—ዮሐንስ 5:46, 47

      • ኢየሱስ በሰንበት ቀን መልካም ነገር ማድረጉ ሕጉን እንደጣሰ የማያስቆጥረው ለምንድን ነው?

      • ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና የገለጸው እንዴት ነው?

      • ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን የሚያረጋግጠው ማን የሰጠው ምሥክርነት ነው?

  • በሰንበት እሸት መቅጠፍ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሰንበት እሸት እየቀጠፉ ሲበሉ

      ምዕራፍ 31

      በሰንበት እሸት መቅጠፍ

      ማቴዎስ 12:1-8 ማርቆስ 2:23-28 ሉቃስ 6:1-5

      • ደቀ መዛሙርቱ በሰንበት እሸት ቀጠፉ

      • ኢየሱስ “የሰንበት ጌታ” ነው

      ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በስተ ሰሜን ወደ ገሊላ እየተጓዙ ነው። ጊዜው የጸደይ ወቅት ስለሆነ በማሳዎቹ ላይ ያለው አዝመራ አሽቷል። ደቀ መዛሙርቱ ስለራባቸው እሸቱን ቀጥፈው በሉ። ዕለቱ ሰንበት ነው፤ ፈሪሳውያኑም ይህን ሲያደርጉ ተመለከቷቸው።

      ከጥቂት ጊዜ በፊት፣ በኢየሩሳሌም የሚገኙ አንዳንድ አይሁዳውያን ኢየሱስ የሰንበትን ሕግ እንደጣሰ በመግለጽ ሊገድሉት ፈልገው እንደነበር አስታውስ። አሁን ደግሞ ፈሪሳውያን፣ ደቀ መዛሙርቱን ባደረጉት ነገር ከሰሷቸው። “ተመልከት! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር እያደረጉ ነው” አሉት።—ማቴዎስ 12:2

      ፈሪሳውያን እሸት መቅጠፍና በእጅ አሽቶ መብላት ከማጨድና ከመውቃት ተለይቶ እንደማይታይ ይናገራሉ። (ዘፀአት 34:21) ሰንበት የተሰጠበት ዓላማ ዕለቱ አስደሳችና በመንፈሳዊ የሚገነባ እንዲሆን ታስቦ ቢሆንም ፈሪሳውያን ሥራ ሲባል ምን ነገሮችን እንደሚጨምር የሚሰጡት የማያፈናፍን ፍቺ ስለ ሰንበት የተሰጠው ሕግ ሸክም እንዲሆን አድርጓል። ስለዚህ ኢየሱስ አመለካከታቸው የተሳሳተ መሆኑን ለማሳየት ይሖዋ አምላክ የሰንበትን ሕግ ያወጣው በዚህ መንገድ እንዲሠራበት አስቦ እንዳልሆነ የሚጠቁሙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ጠቀሰ።

      ኢየሱስ የጠቀሰው አንዱ ምሳሌ ስለ ዳዊትና አብረውት ስለነበሩት ሰዎች ነው። እነዚህ ሰዎች በተራቡ ጊዜ ወደ ማደሪያው ድንኳን ሄደው በአምላክ ፊት የቀረበውን ኅብስት ወይም ዳቦ በልተዋል። ይህ ዳቦ በይሖዋ ፊት ከቀረበ በኋላ በሌላ ትኩስ ዳቦ ሲተካ በደንቡ መሠረት ለካህናቱ ይቀመጣል። ሆኖም በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ዳዊትና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ይህን ዳቦ መብላታቸው እንደ ጥፋት አልተቆጠረም።—ዘሌዋውያን 24:5-9፤ 1 ሳሙኤል 21:1-6

      ኢየሱስ እንዲህ ሲል ሌላም ምሳሌ አቀረበ፦ “ካህናት የሰንበትን ሕግ እንደሚተላለፉና ይህም እንደ በደል እንደማይቆጠርባቸው በሕጉ ላይ አላነበባችሁም?” ይህን ሲል በሰንበት ቀንም እንኳ ካህናቱ መሥዋዕት የሚሆኑ እንስሳትን እንደሚያርዱና በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሌሎች ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ መግለጹ ነው። ኢየሱስ “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ከቤተ መቅደሱ የሚበልጥ እዚህ አለ” አላቸው። (ማቴዎስ 12:5, 6፤ ዘኁልቁ 28:9) ኢየሱስ በአምላክ የተሾመ ሊቀ ካህናት እንደመሆኑ መጠን በሰንበት ዕለት ኃላፊነቱን መወጣት ይችላል፤ እንዲህ ማድረጉ የሰንበትን ሕግ ጥሷል አያስብለውም።

      ኢየሱስ ቀጥሎም ከቅዱሳን መጻሕፍት ሌላ ማስረጃ አቀረበ፦ “‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን ቃል ትርጉም ተረድታችሁ ቢሆን ኖሮ ምንም በደል ባልሠሩት ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር።” ከዚያም “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና” በማለት ንግግሩን ደመደመ። እንዲህ ሲል በመንግሥቱ ለሺህ ዓመት የሚገዛበትን ሰላማዊ ወቅት ማመልከቱ ነው።—ማቴዎስ 12:7, 8፤ ሆሴዕ 6:6

      የሰው ዘር፣ ዓመፅና ጦርነት በተስፋፋበት የሰይጣን አስጨናቂ አገዛዝ እንደ ባሪያ ሲማቅቅ ኖሯል። በሌላ በኩል ግን ክርስቶስ ሲገዛ በሚኖረው ታላቁ ሰንበት እንዴት ያለ እረፍት እናገኛለን! እንዲህ ያለ እረፍት በጣም የሚያስፈልገን ከመሆኑም ሌላ በጉጉት የምንጠብቀው ነገር ነው።

      • ፈሪሳውያን በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ ምን ክስ ሰነዘሩ? ለምንስ?

      • ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ያረማቸው እንዴት ነው?

      • ኢየሱስ “የሰንበት ጌታ” የሆነው በምን መንገድ ነው?

  • በሰንበት የተፈቀደው ምንድን ነው?
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ኢየሱስ እጁ የሰለለን ሰው ሊፈውስ ሲል

      ምዕራፍ 32

      በሰንበት የተፈቀደው ምንድን ነው?

      ማቴዎስ 12:9-14 ማርቆስ 3:1-6 ሉቃስ 6:6-11

      • በሰንበት የአንድን ሰው እጅ ፈወሰ

      በሌላ ሰንበት ኢየሱስ ወደ አንድ ምኩራብ ሄደ፤ ቦታው በገሊላ ሳይሆን አይቀርም። በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ተመለከተ። (ሉቃስ 6:6) ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ኢየሱስን በትኩረት እየተከታተሉት ነው። ለምን? “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል?” በማለት ያቀረቡት ጥያቄ ዓላማቸው ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል።—ማቴዎስ 12:10

      የሃይማኖት መሪዎቹ በሰንበት ሕክምና መስጠት የሚቻለው ለሕይወት የሚያሰጋ ሁኔታ ከተፈጠረ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ወለም ቢለው አጥንቱን ቦታው ማስገባት ወይም በጨርቅ መጠቅለል የተከለከለ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ሁኔታዎች ለሕይወት የሚያሰጉ አይደሉም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ለኢየሱስ ይህን ጥያቄ ያቀረቡለት የዚህ ሰው ሥቃይ ስላስጨነቃቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስን የሚከስሱበት ሰበብ ለማግኘት ስለፈለጉ ነው።

      ኢየሱስ ግን አስተሳሰባቸው ጠማማ እንደሆነ አውቋል። ‘በሰንበት መሥራትን የሚከለክለው ሕግ ተጣሰ’ የሚባለው መቼ እንደሆነ ያላቸው አመለካከት ከቅዱስ ጽሑፉ የራቀና ሚዛናዊነት የጎደለው እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ዘፀአት 20:8-10) መልካም ሥራ በመሥራቱ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ የተሳሳተ ትችት ተሰንዝሮበታል። ስለዚህ ኢየሱስ እጁ የሰለለበትን ሰው “ተነሳና ወደ መሃል ና” ብሎ በመጋበዝ በጉዳዩ ላይ ፊት ለፊት ለመነጋገር የሚያስችል መድረክ አመቻቸ።—ማርቆስ 3:3

      ኢየሱስ ወደ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ዞር ብሎ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው ሰው ቢኖርና በሰንበት ቀን ጉድጓድ ውስጥ ቢገባበት በጉን ጎትቶ የማያወጣው ይኖራል?” ብሎ ጠየቃቸው። (ማቴዎስ 12:11) በግ በገንዘብ የሚገኝ ንብረት በመሆኑ እስከሚቀጥለው ቀን ድረስ እዚያው ጉድጓድ ውስጥ አይተዉትም፤ ምክንያቱም እዚያ እያለ ቢሞት ኪሳራ ይሆንባቸዋል። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ የቤት እንስሳቱን ይንከባከባል” ይላል።—ምሳሌ 12:10

      ቀጥሎም ኢየሱስ የሚከተለውን ምክንያታዊነት የተንጸባረቀበት ንጽጽር ተጠቀመ፦ “ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥም? ስለዚህ በሰንበት መልካም ነገር ማድረግ ተፈቅዷል።” (ማቴዎስ 12:12) ከዚህ አንጻር ኢየሱስ ሰውየውን መፈወሱ የሰንበትን ሕግ መጣስ አይሆንበትም። የሃይማኖት መሪዎቹ ይህን ምክንያታዊነትና ርኅራኄ የተሞላበት አነጋገር ማስተባበል ስላልቻሉ ዝም አሉ።

      ኢየሱስ በተዛባ አስተሳሰባቸው በማዘን በዙሪያው ያሉትን በብስጭት ተመለከተ። ከዚያም ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። (ማቴዎስ 12:13) ሰውየው የሰለለ እጁን ሲዘረጋ ተፈወሰ። ግለሰቡ በዚህ እንደሚደሰት ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና ኢየሱስን ለማጥመድ የሞከሩት ሰዎች ምን ተሰማቸው?

      የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን ለመግደል ተማከሩ

      ፈሪሳውያን የሰውየው እጅ በመዳኑ መደሰት ሲገባቸው “ወዲያው ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች ጋር በመሰብሰብ [ኢየሱስን] እንዴት እንደሚገድሉት መመካከር ጀመሩ።” (ማርቆስ 3:6) ይህ የፖለቲካ ቡድን፣ ሰዱቃውያን የሚባሉትን የሃይማኖት ሰዎች ያቀፈ ሳይሆን አይቀርም። እንደ ወትሮው ቢሆን ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን እርስ በርስ አይስማሙም፤ አሁን ግን ኢየሱስን በመቃወም ግንባር ፈጠሩ።

      • ኢየሱስና የሃይማኖት መሪዎቹ ፊት ለፊት እንዲነጋገሩ መንገድ የከፈተው ሁኔታ ምንድን ነው?

      • የሃይማኖት መሪዎቹ የሰንበትን ሕግ በተመለከተ ምን የተሳሳተ አመለካከት አላቸው?

      • ኢየሱስ፣ ስለ ሰንበት በዘመኑ የነበረው አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን በዘዴ ያሳየው እንዴት ነው?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ