-
ስለ ወይን እርሻ የተነገሩ ሁለት ምሳሌዎችኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 106
ስለ ወይን እርሻ የተነገሩ ሁለት ምሳሌዎች
ማቴዎስ 21:28-46 ማርቆስ 12:1-12 ሉቃስ 20:9-19
ስለ ሁለት ልጆች የተነገረ ምሳሌ
ስለ ወይን እርሻ ገበሬዎች የተነገረ ምሳሌ
ኢየሱስ የፈጸማቸውን ነገሮች የሚያከናውነው በምን ሥልጣን እንደሆነ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እያለ ለጠየቁት የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ግራ የሚያጋባ መልስ ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ የሰጠው መልስ አፋቸውን አስያዛቸው። ከዚያም እውነተኛ ማንነታቸውን የሚያጋልጥ ምሳሌ ተናገረ።
ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ወደ መጀመሪያው ልጁ ሄዶ ‘ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ወደ ወይኑ እርሻ ሄደህ ሥራ’ አለው። ልጁም መልሶ ‘አልሄድም’ አለው፤ በኋላ ግን ጸጸተውና ሄደ። ሁለተኛውንም ቀርቦ እንደዚሁ አለው። ልጁም መልሶ ‘እሺ አባዬ፣ እሄዳለሁ’ አለው፤ ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” (ማቴዎስ 21:28-31) መልሱ ግልጽ ነው፤ በኋላ ላይ የአባቱን ፈቃድ ያደረገው የመጀመሪያው ልጅ ነው።
ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች ወደ አምላክ መንግሥት በመግባት ረገድ ይቀድሟችኋል።” ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች አምላክን ለማገልገል በመጀመሪያ ፈቃደኞች አልነበሩም። ይሁንና እንደ መጀመሪያው ልጅ በኋላ ላይ ንስሐ የገቡ ሲሆን አሁን እያገለገሉት ነው። በሌላ በኩል ግን የሃይማኖት መሪዎቹ እንደ ሁለተኛው ልጅ ናቸው፤ አምላክን እናገለግላለን ቢሉም ተግባራቸው ሌላ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “[መጥምቁ] ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ መጣ፤ እናንተ ግን አላመናችሁትም። ይሁን እንጂ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች አመኑት፤ እናንተ ይህን አይታችሁም እንኳ ጸጸት ተሰምቷችሁ እሱን ለማመን አልፈለጋችሁም።”—ማቴዎስ 21:31, 32
ኢየሱስ በመቀጠል ሌላም ምሳሌ ተናገረ። በዚህ ምሳሌ ላይ የሃይማኖት መሪዎቹ ጥፋት አምላክን አለማገልገላቸው ብቻ እንዳልሆነ አመልክቷል። እነዚህ ሰዎች ክፉ ናቸው። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው የወይን እርሻ አለማ፤ ዙሪያውንም አጠረው፤ ጉድጓድ ቆፍሮም የወይን መጭመቂያ አዘጋጀ፤ ማማም ሠራለት፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። ወቅቱ ሲደርስ ከወይኑ ፍሬ ድርሻውን ከገበሬዎቹ እንዲያመጣለት አንድ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ። እነሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት። በድጋሚ ሌላ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ፤ እሱንም ራሱን ፈነከቱት፤ ደግሞም አዋረዱት። ሌላም ባሪያ ላከ፤ እሱን ደግሞ ገደሉት፤ ሌሎች ብዙዎችንም ላከ፤ አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ ገደሉ።”—ማርቆስ 12:1-5
ኢየሱስን የሚያዳምጡት ሰዎች ምሳሌውን ይረዱ ይሆን? ኢሳይያስ የተናገረውን የሚከተለውን ውግዘት አዘል ሐሳብ ያስታውሱ ይሆናል፦ “የሠራዊት ጌታ የይሖዋ የወይን እርሻ የእስራኤል ቤት ነውና፤ የይሁዳ ሰዎች እሱ ይወደው የነበረው የአትክልት ቦታ ናቸው። ፍትሕን ሲጠብቅ እነሆ፣ ግፍ ይፈጸማል።” (ኢሳይያስ 5:7) የኢየሱስ ምሳሌም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። ባለ ርስቱ ይሖዋ ሲሆን የወይን እርሻው ደግሞ የአምላክ ሕግ እንደ አጥር ከለላ የሆነለት የእስራኤል ብሔር ነው። ይሖዋ፣ ሕዝቡን ለማስተማርና መልካም ፍሬ እንዲያፈሩ ለመርዳት ነቢያት ልኳል።
ይሁንና “ገበሬዎቹ” ወደ እነሱ ከተላኩት “ባሪያዎች” አንዳንዶቹን አሠቃዩአቸው፤ ሌሎቹንም ገደሏቸው። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “[የወይን እርሻው ባለቤት] የቀረው የሚወደው ልጁ ነበር። ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት በመጨረሻ እሱን ላከው። እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው። ኑ እንግደለው፤ ርስቱም የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ። ስለዚህ ይዘው ገደሉት።”—ማርቆስ 12:6-8
ኢየሱስ “እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” በማለት ጠየቀ። (ማርቆስ 12:9) የሃይማኖት መሪዎቹም እንዲህ አሉ፦ “ክፉዎች ስለሆኑ ከባድ ጥፋት ያደርስባቸዋል፤ ከዚያም የወይን እርሻውን፣ ፍሬውን በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል።”—ማቴዎስ 21:41
ይህን ሲናገሩ ሳያውቁት የፈረዱት በራሳቸው ላይ ነው፤ ምክንያቱም የይሖዋ “የወይን እርሻ” የሆነውን የእስራኤልን ብሔር ከሚያስተዳድሩት “ገበሬዎች” መካከል እነሱም ይገኙበታል። ይሖዋ ከእነዚህ ገበሬዎች ከሚጠብቃቸው ፍሬዎች አንዱ፣ በልጁ ማለትም በመሲሑ ማመን ሲሆን ይህን መጠበቁም ተገቢ ነው። ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹን ትኩር ብሎ በመመልከት እንዲህ አለ፦ “እንዲህ የሚለውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል አላነበባችሁም? ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ሆነ። ይህ የይሖዋ ሥራ ነው፤ ለዓይናችንም ድንቅ ነው።’” (ማርቆስ 12:10, 11) ከዚያም ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል የምላችሁ ለዚህ ነው” በማለት ነጥቡን ግልጽ አደረገ።—ማቴዎስ 21:43
“በዚህ ጊዜ ጸሐፍትና የካህናት አለቆች ይህን ምሳሌ የተናገረው እነሱን አስቦ እንደሆነ” ተረዱ። (ሉቃስ 20:19) ስለዚህ ሕጋዊ ‘ወራሽ’ የሆነውን ኢየሱስን ለመግደል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጠው ተነሱ። ይሁንና ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለሚያየው ሕዝቡን ፈሩ፤ በመሆኑም በዚህ ወቅት ሊገድሉት አልሞከሩም።
-
-
ንጉሡ ታዳሚዎችን ወደ ሠርግ ድግስ ጠራኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 107
ንጉሡ ታዳሚዎችን ወደ ሠርግ ድግስ ጠራ
የሠርጉ ድግስ ምሳሌ
ኢየሱስ፣ አገልግሎቱ እየተገባደደ ባለበት በዚህ ወቅት ጸሐፍትንና የካህናት አለቆችን ለማጋለጥ ምሳሌዎችን መናገሩን ቀጠለ። በመሆኑም ሊገድሉት ፈለጉ። (ሉቃስ 20:19) ሆኖም ኢየሱስ እነሱን ማጋለጡን አላቆመም። እንዲያውም ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦
“መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሠርግ ከደገሰ ንጉሥ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ንጉሡም ወደ ሠርጉ የተጋበዙትን እንዲጠሩ ባሪያዎቹን ላከ፤ ተጋባዦቹ ግን ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም።” (ማቴዎስ 22:2, 3) ኢየሱስ ምሳሌውን የጀመረው ስለ “መንግሥተ ሰማያት” በመናገር ነው። በመሆኑም “ንጉሡ” ይሖዋ አምላክን እንደሚያመለክት ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። የንጉሡ ልጅና ወደ ሠርጉ ድግስ የተጋበዙትስ? የንጉሡ ልጅ፣ ምሳሌውን እየተናገረ ያለው የይሖዋ ልጅ ኢየሱስ እንደሆነና ወደ ድግሱ የተጠሩት ደግሞ ከልጁ ጋር ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡትን ሰዎች እንደሚያመለክቱ መገንዘብ አይከብድም።
ወደ ሠርጉ ድግስ እንዲመጡ መጀመሪያ የተጋበዙት እነማን ናቸው? ኢየሱስና ሐዋርያቱ ስለ መንግሥቱ ሲሰብኩ የቆዩት ለእነማን ነው? ለአይሁዳውያን ነው። (ማቴዎስ 10:6, 7፤ 15:24) ይህ ብሔር በ1513 ዓ.ዓ. የሕጉን ቃል ኪዳን ተቀበለ፤ በመሆኑም “የካህናት መንግሥት” የመሆን አጋጣሚ መጀመሪያ የተከፈተው ለዚህ ብሔር ነው። (ዘፀአት 19:5-8) ይሁንና ብሔሩ ወደ ‘ሠርጉ ድግስ’ የተጠራው መቼ ነው? ማስረጃዎቹ እንደሚጠቁሙት ይህ ግብዣ የቀረበው ኢየሱስ ስለ መንግሥተ ሰማያት መስበክ በጀመረበት ጊዜ ማለትም በ29 ዓ.ም. ነው።
ለመሆኑ አብዛኞቹ እስራኤላውያን ለግብዣው ምን ምላሽ ሰጡ? ኢየሱስ እንደተናገረው ወደ ሠርጉ “ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም።” ከሃይማኖት መሪዎቹም ሆነ ከሕዝቡ መካከል ብዙዎቹ፣ ኢየሱስን መሲሕና አምላክ የመረጠው ንጉሥ አድርገው አልተቀበሉትም።
ይሁንና ኢየሱስ፣ አይሁዳውያን ሌላ አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “[ንጉሡ] በድጋሚ ሌሎች ባሪያዎች ልኮ ‘ተጋባዦቹን “የምሳ ግብዣ አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ፍሪዳዎቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ነው። ወደ ሠርጉ ኑ” በሏቸው’ አለ። እነሱ ግን ግብዣውን ችላ በማለት አንዱ ወደ እርሻው፣ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ ሌሎቹ ደግሞ ባሪያዎቹን ይዘው ካንገላቷቸው በኋላ ገደሏቸው።” (ማቴዎስ 22:4-6) ይህ ምሳሌ የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ የሚፈጸመውን ሁኔታ ያመለክታል። በዚያ ወቅት አይሁዳውያን ወደ መንግሥቱ የመግባት አጋጣሚ የተከፈተላቸው ቢሆንም ብዙዎቹ ግብዣውን አልተቀበሉም፤ እንዲያውም ‘የንጉሡን ባሪያዎች’ አንገላቷቸው።—የሐዋርያት ሥራ 4:13-18፤ 7:54, 58
ታዲያ ይህ በብሔሩ ላይ ምን ያስከትላል? ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ንጉሡም እጅግ ተቆጣ፤ ወታደሮቹንም ልኮ እነዚያን ነፍሰ ገዳዮች ገደለ እንዲሁም ከተማቸውን አቃጠለ።” (ማቴዎስ 22:7) አይሁዳውያን ይህ የደረሰባቸው በ70 ዓ.ም. “ከተማቸውን” ኢየሩሳሌምን ሮማውያን ባጠፏት ጊዜ ነው።
ይሁንና ይህ ብሔር የንጉሡን ጥሪ ስላልተቀበለ ሌላ ማንም አይጋበዝም ማለት ነው? ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ይህ እንዳልሆነ ያሳያል። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ከዚያም [ንጉሡ] ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ሠርጉ ተደግሷል፤ የተጋበዙት ግን የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም። ስለዚህ በየአውራ ጎዳናው ሂዱና ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ወደ ሠርጉ ጥሩ።’ በዚህ መሠረት ባሪያዎቹ ወደ አውራ ጎዳናዎች ሄደው ክፉውንም ጥሩውንም፣ ያገኙትን ሰው ሁሉ ሰበሰቡ፤ የሠርጉ አዳራሽም በተጋባዦች ተሞላ።”—ማቴዎስ 22:8-10
ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ አሕዛብን ይኸውም በትውልድ አይሁዳዊ ያልሆኑ እንዲሁም ወደ ይሁዲነት ያልተለወጡ ሰዎችን እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። የሮም ሠራዊት አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ በ36 ዓ.ም. የአምላክን መንፈስ በመቀበላቸው ኢየሱስ የጠቀሰውን መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ አጋጣሚ ተከፈተላቸው።—የሐዋርያት ሥራ 10:1, 34-48
ወደ ግብዣው ከመጡት መካከል ‘በንጉሡ’ ዘንድ ተቀባይነት የማያገኙ እንደሚኖሩ ኢየሱስ ጠቁሟል። እንዲህ አለ፦ “ንጉሡ እንግዶቹን ለማየት ሲገባ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አየ። በዚህ ጊዜ ‘ወዳጄ ሆይ፣ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልክ?’ አለው። ሰውየውም የሚለው ጠፋው። ከዚያም ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። እዚያም ሆኖ ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል’ አላቸው። የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”—ማቴዎስ 22:11-14
ኢየሱስን የሚያዳምጡት የሃይማኖት መሪዎች እሱ የተናገረውን ነገር ትርጉምም ሆነ አንድምታ ሙሉ በሙሉ ላይረዱ ይችላሉ። ያም ቢሆን በተናገረው ነገር ቅር የተሰኙ ከመሆኑም ሌላ እንዲህ እያሳፈራቸው ካለው ሰው ለመገላገል ይበልጥ ተነሳሱ።
-
-
ኢየሱስን ለማጥመድ የተጠነሰሰው ሴራ ከሸፈኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 108
ኢየሱስን ለማጥመድ የተጠነሰሰው ሴራ ከሸፈ
ማቴዎስ 22:15-40 ማርቆስ 12:13-34 ሉቃስ 20:20-40
የቄሳር የሆነውን ለቄሳር
ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች ያገባሉ?
ከሁሉ የሚበልጡት ትእዛዛት
የኢየሱስ ጠላቶች የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች ተበሳጭተዋል። ኢየሱስ ክፋታቸውን የሚያጋልጡ ምሳሌዎች ተናግሮ መጨረሱ ነው። በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያን እሱን ለማጥመድ ሴራ ጠነሰሱ። እሱን ለሮም አገረ ገዢ አሳልፈው ለመስጠት የሚያስችላቸው ነገር እንዲናገር ለማድረግ የሞከሩ ሲሆን ለደቀ መዝሙሮቻቸው ገንዘብ በመክፈል እሱን እንዲያጠምዱ ላኳቸው።—ሉቃስ 6:7
እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦ “መምህር፣ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም እንደማታዳላ፣ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፦ ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባናል ወይስ አይገባንም?” (ሉቃስ 20:21, 22) ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ግብዞችና ተንኮለኞች መሆናቸውን ስለሚያውቅ በሽንገላቸው አልተታለለም። ‘ግብር መክፈል ተገቢ አይደለም’ ብሎ ቢመልስ ‘በሮም መንግሥት ላይ ዓመፅ አነሳስተሃል’ ተብሎ ሊወነጀል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ‘ግብር መክፈል ተገቢ ነው’ ቢል በሮም ቀንበር ሥር በመውደቃቸው የተማረሩት አይሁዳውያን በተሳሳተ መንገድ ሊረዱትና በእሱ ላይ ሊነሱ ይችላሉ። ታዲያ ኢየሱስ ምን ብሎ ይመልስ ይሆን?
“እናንተ ግብዞች፣ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? እስቲ ለግብር የሚከፈለውን ሳንቲም አሳዩኝ” አላቸው። እነሱም አንድ ዲናር አመጡለት። ኢየሱስ “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። እነሱም “የቄሳር” አሉ። በዚህ ጊዜ “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” በማለት ጥበብ የተንጸባረቀበት መመሪያ ሰጣቸው።—ማቴዎስ 22:18-21
ሰዎቹ ኢየሱስ በሰጠው መልስ ተደነቁ። ማስተዋል ለታከለበት ንግግሩ ምላሽ መስጠት ስላልቻሉ ትተውት ሄዱ። ይሁንና ቀኑ ገና አላበቃም፤ ሰዎቹም እሱን ለማጥመድ መሞከራቸውን አላቆሙም። ፈሪሳውያን ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፤ ከዚያም ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ወደ ኢየሱስ መጡ።
በትንሣኤ የማያምኑት ሰዱቃውያን፣ ከትንሣኤና ከዋርሳ ጋብቻ ጋር በተያያዘ ጥያቄ አነሱ፦ “መምህር፣ ሙሴ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የሟቹን ሚስት ማግባትና ለወንድሙ ዘር መተካት አለበት’ ብሏል። በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ ወንድሙ የሟቹን ሚስት አገባ። ሁለተኛውም ሆነ ሦስተኛው እስከ ሰባተኛው ድረስ ልጅ ሳይወልዱ ሞቱ። በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች። እንግዲህ ሁሉም ስላገቧት በትንሣኤ ከሰባቱ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”—ማቴዎስ 22:24-28
ኢየሱስ፣ ሰዱቃውያን የሚያምኑባቸውን የሙሴን መጻሕፍት በመጥቀስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ባለማወቃችሁ አይደለም? ከሞት በሚነሱበት ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ። ስለ ሙታን መነሳት ግን በሙሴ መጽሐፍ፣ ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ አምላክ ሙሴን ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ እንዳለው አላነበባችሁም? እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እናንተ እጅግ ተሳስታችኋል።” (ማርቆስ 12:24-27፤ ዘፀአት 3:1-6) ሕዝቡ በኢየሱስ መልስ በጣም ተደነቁ።
ኢየሱስ ፈሪሳውያንንም ሆነ ሰዱቃውያንን ዝም አሰኝቷቸዋል፤ በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ የሆኑት እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች እንደገና ሊፈትኑት ግንባር ፈጥረው ወደ እሱ መጡ። አንድ ጸሐፊ “መምህር፣ ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው።—ማቴዎስ 22:36
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የመጀመሪያው ይህ ነው፦ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ይሖዋ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው፤ አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።’ ሁለተኛው ደግሞ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚል ነው። ከእነዚህ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።”—ማርቆስ 12:29-31
ጸሐፊው የኢየሱስን መልስ ሲሰማ እንዲህ አለው፦ “መምህር፣ የተናገርከው እውነት ነው፤ ‘እሱ አንድ ነው፤ ከእሱ ሌላ አምላክ የለም’፤ እሱን በሙሉ ልብ፣ በሙሉ አእምሮና በሙሉ ኃይል መውደድ እንዲሁም ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ፣ ሙሉ በሙሉ ከሚቃጠል መባና ከመሥዋዕት ሁሉ እጅግ ይበልጣል።” ኢየሱስ፣ ጸሐፊው በማስተዋል እንደመለሰ ሲመለከት “አንተ ከአምላክ መንግሥት የራቅክ አይደለህም” አለው።—ማርቆስ 12:32-34
ኢየሱስ ለሦስት ቀናት (ኒሳን 9, 10 እና 11) በቤተ መቅደሱ ሲያስተምር ቆይቷል። እንደዚህ ጸሐፊ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ደስ እያላቸው አዳምጠውታል። የሃይማኖት መሪዎቹ ግን እንዲህ አልተሰማቸውም፤ እነሱ ‘ከዚህ በኋላ ሊጠይቁት አልደፈሩም።’
-
-
ተቃዋሚዎቹን አወገዘኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 109
ተቃዋሚዎቹን አወገዘ
ማቴዎስ 22:41–23:24 ማርቆስ 12:35-40 ሉቃስ 20:41-47
ክርስቶስ የማን ልጅ ነው?
ኢየሱስ የተቃዋሚዎቹን ግብዝነት አጋለጠ
የኢየሱስ ተቃዋሚ የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች፣ እሱን ተቀባይነት ለማሳጣትም ሆነ እሱን በማጥመድ ለሮማውያን አሳልፈው ለመስጠት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። (ሉቃስ 20:20) ዕለቱ ኒሳን 11 ሲሆን ኢየሱስ አሁንም ያለው በቤተ መቅደሱ ነው፤ በዚህ ጊዜ በተራው ጥያቄዎችን በማንሳት እውነተኛ ማንነቱን እንዲያውቁ አደረገ። ቅድሚያውን በመውሰድ “ስለ መሲሑ ምን ትላላችሁ? የማን ልጅ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። (ማቴዎስ 22:42) መሲሑ ወይም ክርስቶስ ከዳዊት የዘር ሐረግ እንደሚመጣ በሰፊው ይታወቃል። እነሱም ይህን መልስ ሰጡ።—ማቴዎስ 9:27፤ 12:23፤ ዮሐንስ 7:42
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “ታዲያ ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ እንዴት ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ምክንያቱም ዳዊት ‘ይሖዋ ጌታዬን፦ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው’ ሲል ተናግሯል። ታዲያ ዳዊት ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?”—ማቴዎስ 22:43-45
ፈሪሳውያን ምንም መልስ አልሰጡም፤ ምክንያቱም እነሱ የሚጠብቁት ከሮማውያን አገዛዝ ነፃ ሊያወጣቸው የሚችል የዳዊት ዘር የሆነ ሰው እንደሚመጣ ነው። ኢየሱስ ግን በመዝሙር 110:1, 2 ላይ ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ በመጥቀስ መሲሑ ከሰብዓዊ ገዢ የበለጠ ሚና እንደሚኖረው ገለጸ። መሲሑ የዳዊት ጌታ ሲሆን በአምላክ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ በሥልጣኑ መጠቀም ይጀምራል። ኢየሱስ የሰጠው መልስ ተቃዋሚዎቹን ጸጥ አሰኛቸው።
ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ብዙ ሰዎች ኢየሱስን እያዳመጡት ነው። አሁን ኢየሱስ ጸሐፍትንና ፈሪሳውያንን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ሰጠ። እነዚህ ሰዎች የአምላክን ሕግ ለማስተማር “በገዛ ሥልጣናቸው የሙሴን ቦታ ወስደዋል።” ኢየሱስ አድማጮቹን “የሚነግሯችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ሆኖም የሚናገሩትን በተግባር ስለማያውሉ እነሱ የሚያደርጉትን አታድርጉ” በማለት አስጠነቀቀ።—ማቴዎስ 23:2, 3
ቀጥሎም ኢየሱስ ግብዝነታቸውን የሚያሳይ ምሳሌ ሲጠቅስ “ትልቅ ክታብ ያስራሉ” አለ። አንዳንድ አይሁዳውያን የሕጉን የተወሰኑ ክፍሎች የያዘ ትንሽ ማኅደር በግንባራቸው ወይም በግራ ክንዳቸው ላይ ያስራሉ። ፈሪሳውያን ግን ለሕጉ የሚቀኑ መስለው ለመታየት ሲሉ ትልቅ ክታብ ያስራሉ። ከዚህም ሌላ ‘የልብሳቸውን ዘርፍ ያስረዝማሉ።’ እስራኤላውያን በልብሳቸው ጫፍ ላይ ዘርፍ እንዲያደርጉ ታዘዋል፤ ይሁንና ፈሪሳውያን የልብሳቸውን ዘርፍ በጣም ያስረዝሙታል። (ዘኁልቁ 15:38-40) ይህን ሁሉ የሚያደርጉት “በሰዎች ለመታየት ብለው ነው።”—ማቴዎስ 23:5
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም እንኳ ከፍ ያለ ቦታ የማግኘት ፍላጎት ሊያድርባቸው ይችላል፤ በመሆኑም የሚከተለውን ምክር ሰጣቸው፦ “መምህራችሁ አንድ ስለሆነ ረቢ ተብላችሁ አትጠሩ፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ። በተጨማሪም አባታችሁ አንድ እሱም በሰማይ ያለው ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ። እንዲሁም መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ መሪ ተብላችሁ አትጠሩ።” ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ ለራሳቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ምን ማድረግስ ይኖርባቸዋል? ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ከመካከላችሁ ታላቅ የሆነው የእናንተ አገልጋይ መሆን ይገባዋል። ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።”—ማቴዎስ 23:8-12
ኢየሱስ በመቀጠል ግብዝ የሆኑትን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የሚያወግዝ ነገር በተከታታይ ተናገረ፦ “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ በሩን ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ ለመግባት የሚመጡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።”—ማቴዎስ 23:13
ፈሪሳውያን፣ ይሖዋ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ነገሮች አቅልለው ስለሚመለከቱ ኢየሱስ አወገዛቸው፤ ይህ አስተሳሰባቸው ለእነሱ እንደሚመቻቸው በሚያወጧቸው ደንቦች ላይ ተንጸባርቋል። ለምሳሌ ያህል “አንድ ሰው በቤተ መቅደሱ ቢምል ምንም አይደለም፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል ግን መሐላውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት” ይላሉ። እንዲህ ማለታቸው፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንደማይችሉ ያሳያል፤ ምክንያቱም የይሖዋ የአምልኮ ቦታ ከሆነው ቤተ መቅደስ ይልቅ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለውን ወርቅ ከፍ አድርገው ተመልክተዋል። በመሆኑም “በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች” ችላ ብለዋል።—ማቴዎስ 23:16, 23፤ ሉቃስ 11:42
ኢየሱስ እነዚህን ፈሪሳውያን “እናንተ ዕውር መሪዎች! ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ!” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 23:24) ፈሪሳውያን ከሚጠጡት ወይን ውስጥ ትንኝን አጥልለው የሚያወጡት በሕጉ መሠረት ርኩስ ስለሆነች ነው። ሆኖም በሕጉ ውስጥ ያሉትን የበለጠ ክብደት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ችላ ማለታቸው ርኩስ የሆነውንና ከትንኝ እጅግ የሚበልጠውን ግመል ከመዋጥ የሚተናነስ አይደለም።—ዘሌዋውያን 11:4, 21-24
-