የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ዳዊት እና ጎልያድ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ዳዊት ጎልያድ ላይ ድንጋይ ሲወነጭፍ

      ትምህርት 40

      ዳዊት እና ጎልያድ

      ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ እሴይ ቤት ሂድ። ከእሴይ ልጆች መካከል አንዱ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ ይሆናል።’ ስለዚህ ሳሙኤል ወደ እሴይ ቤት ሄደ። ከዚያም የመጀመሪያ ልጁን ሲያይ ‘ይሖዋ የመረጠው ይህን ወጣት መሆን አለበት’ ብሎ አሰበ። ይሖዋ ግን ሳሙኤልን ‘የመረጥኩት እሱን አይደለም። እኔ የማየው የሰውን መልክ ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ባሕርይውን ጭምር ነው’ አለው።

      ሳሙኤል ዳዊትን ሲቀባው

      እሴይ ሌሎቹን ስድስት ልጆቹን ጠርቶ ሳሙኤል ፊት አቀረባቸው። ሳሙኤል ግን ‘ይሖዋ እነዚህንም አልመረጣቸውም። ሌላ ልጅ የለህም?’ አለው። እሴይም ‘የመጨረሻው ልጄ ዳዊት አለ። ውጭ በጎቹን እየጠበቀ ነው’ አለ። ዳዊት ወደ ቤት ሲገባ ይሖዋ ሳሙኤልን ‘የመረጥኩት እሱን ነው!’ አለው። ሳሙኤልም በዳዊት ራስ ላይ ዘይት በማፍሰስ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ቀባው።

      ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ጋር ለመዋጋት ተሰለፉ፤ ፍልስጤማውያን ጎልያድ የሚባል ግዙፍ ተዋጊ ነበራቸው። ጎልያድ በየቀኑ በእስራኤላውያን ላይ ያሾፍ ነበር። ‘ከእኔ ጋር የሚዋጋ ሰው ካለ ይምጣ። እሱ ካሸነፈኝ እኛ የእናንተ ባሪያዎች እንሆናለን። እኔ ካሸነፍኩት ደግሞ እናንተ የእኛ ባሪያዎች ትሆናላችሁ’ እያለ ይጮኽ ነበር።

      ጎልያድ

      የዳዊት ወንድሞች ወታደሮች ስለነበሩ ዳዊት ለእነሱ ምግብ ለማድረስ ወደ እስራኤል ጦር ሰፈር መጣ። ከዚያም ጎልያድ የሚናገረውን ሲሰማ ‘እኔ እዋጋዋለሁ!’ አለ። ንጉሥ ሳኦል ግን ‘አንተ እኮ ገና ልጅ ነህ’ አለው። ዳዊትም ‘ይሖዋ ይረዳኛል’ በማለት መለሰ።

      ሳኦል የጦር ልብሱን ለዳዊት ሊሰጠው ፈልጎ ነበር፤ ዳዊት ግን ‘ይህን ለብሼ መዋጋት አልችልም’ አለ። ከዚያም ዳዊት ወንጭፉን ይዞ ወደ ወንዝ ሄደ። አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች መረጠና ኮሮጆው ውስጥ ጨመራቸው። ከዚያም ወደ ጎልያድ እየሮጠ ሄደ። ጎልያድም ‘እስቲ ወደዚህ ና። ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ’ በማለት ጮኸበት። ዳዊት ግን አልፈራም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ሰይፍና ጦር ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን በይሖዋ ስም እመጣብሃለሁ። የምትዋጋው ከእኛ ጋር ሳይሆን ከአምላክ ጋር ነው። እዚህ ያሉት ሰዎች ሁሉ ይሖዋ ከሰይፍ ወይም ከጦር የበለጠ ኃይል እንዳለው ያያሉ። ሁላችሁንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣችኋል።’

      ዳዊትም አንድ ድንጋይ ወንጭፉ ላይ አድርጎ ባለ በሌለ ኃይሉ አሽከረከረው። ይሖዋ ዳዊትን ስለረዳው ድንጋዩ ሄዶ የጎልያድ ግንባር ውስጥ ተቀረቀረ። ከዚያም ግዙፉ ጎልያድ መሬት ላይ ተደፋ፤ በዚህ ሁኔታ ዳዊት ጎልያድን ገደለው። ፍልስጤማውያንም ሸሹ። አንተስ እንደ ዳዊት በይሖዋ ትተማመናለህ?

      “ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል።”—ማርቆስ 10:27

      ጥያቄ፦ ይሖዋ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው ማንን ነው? ዳዊት ጎልያድን ያሸነፈው እንዴት ነው?

      1 ሳሙኤል 16:1-13፤ 17:1-54

  • ዳዊት እና ሳኦል
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ዳዊት ተራራ ላይ ሆኖ ሲጣራ

      ትምህርት 41

      ዳዊት እና ሳኦል

      ዳዊት ጎልያድን ከገደለ በኋላ ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን የሠራዊቱ መሪ አደረገው። ዳዊት ብዙ ጦርነቶችን አሸነፈ፤ እስራኤላውያንም በጣም ወደዱት። ዳዊት ከጦርነት በሚመለስበት ወቅት፣ ሴቶች ‘ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤ ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ’ ብለው እየዘፈኑና እየጨፈሩ ይቀበሉት ነበር። ስለዚህ ሳኦል በዳዊት ይቀና ጀመር፤ በዚህም የተነሳ ሊገድለው ፈለገ።

      ዳዊት በገና ሲጫወት ጎበዝ ነበር። አንድ ቀን ዳዊት ለሳኦል በገና እየተጫወተለት ሳለ ንጉሡ በዳዊት ላይ ጦሩን ወረወረበት። ሆኖም ዳዊት ጎንበስ ሲል ጦሩ ግድግዳው ላይ ተሰካ። ከዚያ በኋላም ሳኦል በተደጋጋሚ ዳዊትን ለመግደል ሞክሯል። በመጨረሻም ዳዊት ሸሽቶ በረሃ ውስጥ ተደበቀ።

      ዳዊት ሳኦል ተኝቶ በነበረበት ወቅት ጦሩን ሲወስድ

      ሳኦል 3,000 ወታደሮችን ይዞ ዳዊትን ፍለጋ ሄደ። ከዚያም አንድ ዋሻ ውስጥ ገባ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች የተደበቁት እዚሁ ዋሻ ውስጥ ነበር። ከዳዊት ጋር የነበሩት ሰዎችም ‘ሳኦልን ለመግደል ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ አታገኝም’ በማለት ዳዊትን አደፋፈሩት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ቀስ ብሎ ወደ ንጉሥ ሳኦል ተጠጋና የልብሱን ጫፍ ቆረጠ። ሳኦል፣ ዳዊት ምን እንዳደረገ አላወቀም ነበር። በኋላ ግን ዳዊት፣ ይሖዋ ለቀባው ንጉሥ አክብሮት ባለማሳየቱ በጣም አዘነ። አብረውት የነበሩት ሰዎችም በሳኦል ላይ ጉዳት እንዲያደርሱበት አልፈቀደላቸውም። ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ ሳኦልን በመጥራት ሊገድለው ይችል እንደነበረ ነገረው። ታዲያ ሳኦል ከዚህ በኋላ ዳዊትን ማሳደዱን ይተው ይሆን?

      በፍጹም፤ ሳኦል ዳዊትን ማሳደዱን አልተወም። አንድ ቀን ዳዊትና የእህቱ ልጅ አቢሳ ተደብቀው ወደ ሳኦል ድንኳን ገቡ። የሳኦል ጠባቂ የነበረው አበኔርም ተኝቶ ነበር። በዚህ ጊዜ አቢሳ ‘ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነው! ሳኦልን ልግደለው’ አለ። ዳዊት ግን እንዲህ ብሎ መለሰ፦ ‘ይሖዋ ራሱ በሳኦል ላይ እርምጃ ይወስድበታል። አሁን ጦሩንና የውኃ መያዣውን ይዘን እንሂድ።’

      ከዚያም ዳዊት፣ ሳኦል በሰፈረበት አካባቢ የሚገኝ ተራራ ላይ ወጣ። ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ ‘አበኔር፣ ንጉሡን የማትጠብቀው ለምንድን ነው? የሳኦል የውኃ መያዣና ጦር የት አለ?’ ሳኦልም እየተናገረ ያለው ዳዊት መሆኑን ሲያውቅ ‘ልትገድለኝ ትችል ነበር፤ ግን አልገደልከኝም። ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ አንተ እንደምትሆን አውቃለሁ’ አለ። ከዚያም ሳኦል ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ። ሳኦል ዳዊትን ይጠላው የነበረ ቢሆንም ከቤተሰቡ አባላት መካከል ዳዊትን የሚወድ ሰው ነበር።

      “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ።”—ሮም 12:18, 19

      ጥያቄ፦ ሳኦል ዳዊትን መግደል የፈለገው ለምንድን ነው? ዳዊት ሳኦልን መግደል ያልፈለገው ለምንድን ነው?

      1 ሳሙኤል 16:14-23፤ 18:5-16፤ 19:9-12፤ 23:19-29፤ 24:1-15፤ 26:1-25

  • ዮናታን ደፋርና ታማኝ ነበር
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ዮናታንና አገልጋዩ

      ትምህርት 42

      ዮናታን ደፋርና ታማኝ ነበር

      የንጉሥ ሳኦል የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ዮናታን ደፋር ተዋጊ ነበር። ዳዊት ራሱ ዮናታን ከንስር ይበልጥ ፈጣንና ከአንበሳ ይበልጥ ጠንካራ እንደሆነ ተናግሯል። አንድ ቀን ዮናታን የተወሰኑ ፍልስጤማውያን ወታደሮችን አንድ ተራራ ላይ አየ። ከዚያም አገልጋዩን ‘የምንዋጋው ይሖዋ ምልክት ከሰጠን ብቻ ነው። ፍልስጤማውያኑ ኑና ግጠሙን ካሉን ሄደን እንዋጋለን’ አለው። ፍልስጤማውያኑም ‘ወደ እኛ ኑና እንጋጠም!’ ብለው ጮኹ። ስለዚህ ዮናታንና አገልጋዩ ወደ ተራራው ወጥተው ከፍልስጤማውያኑ ጋር በመዋጋት አሸነፏቸው።

      ዮናታን አንዳንድ ዕቃዎቹን ለዳዊት ሲሰጠው

      ዮናታን የሳኦል የመጀመሪያ ልጅ በመሆኑ ቀጣዩ ንጉሥ የሚሆነው እሱ ነበር። ሆኖም ዮናታን ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ይሖዋ የመረጠው ዳዊትን እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ ቢሆንም በዳዊት አልቀናም። እንዲያውም ዮናታንና ዳዊት የቅርብ ጓደኛሞች ሆኑ። አንዳቸው ሌላውን ለመጠበቅና እርስ በርስ ለመረዳዳት ቃል ገቡ። ዮናታን ዳዊትን በጣም እንደሚወደው ለማሳየት ልብሱን፣ ሰይፉን፣ ቀስቱንና ቀበቶውን ሰጠው።

      ዳዊት ከሳኦል እየሸሸ በነበረበት ወቅት ዮናታን ወደ ዳዊት ሄዶ ‘በርታ፤ ደፋር ሁን። ይሖዋ ንጉሥ እንድትሆን መርጦሃል። አባቴም ቢሆን ይህን ያውቃል’ አለው። አንተም እንደ ዮናታን ያለ ጥሩ ጓደኛ ቢኖርህ ደስ አይልህም?

      ዮናታን ጓደኛውን ለመርዳት ሲል በተደጋጋሚ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሏል። ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን መግደል እንደሚፈልግ ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ አባቱን እንዲህ አለው፦ ‘ዳዊትን ብትገድል ኃጢአት ይሆንብሃል፤ ዳዊት ምንም መጥፎ ነገር አልሠራም።’ በዚህ ጊዜ ሳኦል በዮናታን በጣም ተበሳጨ።

      ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሳኦልና ዮናታን ጦርነት ላይ ሞቱ። ዮናታን ከሞተ በኋላ ዳዊት የዮናታንን ልጅ ሜፊቦስቴን ፈልጎ ለማግኘት ጥረት አደረገ። ዳዊት ሜፊቦስቴን ካገኘው በኋላ እንዲህ አለው፦ ‘አባትህ በጣም ጥሩ ጓደኛዬ ስለነበር ከአሁን በኋላ እኔ እንከባከብሃለሁ። ቤተ መንግሥቴ ውስጥ ትኖራለህ፤ እንዲሁም ከእኔ ጋር ትበላለህ።’ ዳዊት ጓደኛውን ዮናታንን ፈጽሞ አልረሳውም።

      “እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።”—ዮሐንስ 15:12, 13

      ጥያቄ፦ ዮናታን ደፋር መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? ዮናታን ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

      1 ሳሙኤል 14:1-23፤ 18:1-4፤ 19:1-6፤ 20:32-42፤ 23:16-18፤ 31:1-7፤ 2 ሳሙኤል 1:23፤ 9:1-13

  • ንጉሥ ዳዊት የሠራው ኃጢአት
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ነቢዩ ናታን ለንጉሥ ዳዊት ተግሣጽ ሲሰጠው

      ትምህርት 43

      ንጉሥ ዳዊት የሠራው ኃጢአት

      ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት ንጉሥ ሆነ። በወቅቱ ዳዊት 30 ዓመቱ ነበር። ለተወሰኑ ዓመታት ንጉሥ ሆኖ ከገዛ በኋላ አንድ ከባድ ስህተት ሠራ። አንድ ቀን ምሽት ላይ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ አንዲት ቆንጆ ሴት አየ። ዳዊት ስለ ሴትየዋ ማንነት ሲጠይቅ ስሟ ቤርሳቤህ እንደሆነና ኦርዮ የሚባል አንድ ወታደር ሚስት እንደሆነች ነገሩት። ዳዊት ቤርሳቤህን ወደ ቤተ መንግሥቱ አስመጣት። ከዚያም አብሯት ተኛ፤ እሷም አረገዘች። ዳዊት ያደረገውን ነገር ለመደበቅ ሞከረ። ለጦር አዛዡ መልእክት ልኮ ኦርዮን ውጊያው ላይ ፊት ለፊት እንዲያሰልፈውና ሌሎቹ ወታደሮች ጥለውት እንዲሸሹ እንዲያደርግ ነገረው። ኦርዮ በጦርነቱ ከተገደለ በኋላ ዳዊት ቤርሳቤህን አገባት።

      ንጉሥ ዳዊት ኃጢአቱ ይቅር እንዲባልለት ሲጸልይ

      ሆኖም ይሖዋ የተፈጸመውን መጥፎ ድርጊት በሙሉ ተመልክቶ ነበር። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? ይሖዋ ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው። ናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘አንድ ሀብታም ሰውና አንድ ድሃ ሰው ነበሩ፤ ሀብታሙ ሰው ብዙ በጎች ነበሩት፤ ድሃው ግን የነበረችው አንዲት ትንሽ የበግ ጠቦት ብቻ ነበረች። እሷንም በጣም ይወዳት ነበር። ሀብታሙ ሰው ድሃው የነበረችውን አንዲት ጠቦት ወሰደበት።’ በዚህ ጊዜ ዳዊት በጣም ተናዶ ‘ያ ሀብታም ሰው መሞት ይገባዋል!’ አለ። ከዚያም ናታን ዳዊትን ‘ያ ሀብታም ሰው አንተ ነህ!’ አለው። ዳዊት በጣም አዘነ፤ ከዚያም ጥፋቱን በማመን ‘በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ’ አለ። ይህ ኃጢአት በዳዊትና በቤተሰቡ ላይ ብዙ ችግር አምጥቷል። ይሖዋ ዳዊትን የቀጣው ቢሆንም ዳዊት ሐቀኛና ትሑት በመሆኑ በሕይወት እንዲኖር ፈቅዶለታል።

      ዳዊት ለይሖዋ ቤተ መቅደስ መገንባት ፈልጎ ነበር፤ ይሖዋ ግን ቤተ መቅደሱን እንዲገነባ የመረጠው ልጁን ሰለሞንን ነበር። ዳዊት ቤተ መቅደሱን ለመገንባት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለሰለሞን ማዘጋጀት ጀመረ፤ እንዲህም አለ፦ ‘የይሖዋ ቤተ መቅደስ በጣም ውብ መሆን አለበት። ሰለሞን ገና ልጅ ነው፤ ስለዚህ የሚያስፈልገውን ነገር በማዘጋጀት እረዳዋለሁ።’ ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚሆን በጣም ብዙ ገንዘብ ሰጠ። እንዲሁም ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞችን አዘጋጀለት። ወርቅና ብር አሰባሰበ፤ ከጢሮስና ከሲዶናም የአርዘ ሊባኖስ እንጨት አስመጣ። ዳዊት መሞቻው ሲቃረብ ለሰለሞን ቤተ መቅደሱ እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳይ ንድፍ ሰጠው። እንዲህም አለው፦ ‘ይሖዋ እነዚህን ነገሮች በጽሑፍ እንዳሰፍርልህ ነግሮኛል። ይሖዋ ይረዳሃል። አትፍራ። ደፋር ሁን፤ ሥራውን በትጋት አከናውን።’

      ዳዊት ስለ ቤተ መቅደሱ ንድፍ ከወጣቱ ሰለሞን ጋር ሲነጋገር

      “የሠራውን በደል የሚሸፋፍን አይሳካለትም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ሁሉ ግን ምሕረት ያገኛል።”—ምሳሌ 28:13

      ጥያቄ፦ ዳዊት የሠራው ኃጢአት ምንድን ነው? ዳዊት ልጁን ሰለሞንን ለመርዳት ምን አደረገ?

      2 ሳሙኤል 5:3, 4, 10፤ 7:1-16፤ 8:1-14፤ 11:1–12:14፤ 1 ዜና መዋዕል 22:1-19፤ 28:11-21፤ መዝሙር 51:1-19

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ